Administrator

Administrator

የዛሬ 368 ቀናት ነበር - ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ዓ.ም ማለዳ ላይ ወደ 6ሺ የሚጠጉ የሃማስ ታጣቂዎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል በመሻገር በንጹሃን ዜጎች ላይ ያልተጠበቀ ድንገተኛ ጥቃት የፈጸሙት፡፡

በዚህ ጭካኔ በተሞላበት አሰቃቂ ጥቃት፣ ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች - እስራኤላውያንና ሌሎች የበርካታ አገራት ዜጎች - በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ ሲሆን፤ 251 ያህሉ ደግሞ በታጣቂው ቡድን ታግተው መወሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 101 ያህሉ አሁንም በጋዛ ታግተው ይገኛሉ፡፡

በዚህ አሰቃቂ የሽብር ጥቃት፣ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ እየታደኑ በጥይት ተደብድበዋል፤ ተደፍረዋል፤ ታግተዋል። ትንንሽ ልጆችና አዛውንቶች ጭምር ታግተው ወደ ሃማስ አስፈሪ የሽብር ዋሻዎች ተወስደዋል፡፡

ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል እቤታቸው ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የነበሩ ህጻናት፣ የሰላምና ሙዚቃ ፌስቲቫል ሲያከብሩ የነበሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ አዛውንቶችን ጨምሮ ከናዚ እልቂት የተረፉ እስራኤላውያን ይገኙበታል፡፡

በጋዛ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ታግተው ለሚገኙ 101 ሴቶች፣ ወንዶችና ህጻናት አሁንም ስቃዩ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ በስድስት ታጋቾች ላይ በተፈጸመው ግድያና አስከፊ በደል ሳቢያ የታጋች ቤተሰቦችም በከፍተኛ ጭንቀትና ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡


ለሌሎች እስራኤላውያንም ኦክቶበር 7 አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይህም በደቡብና በሰሜን እስራኤል ውስጥ፣ ከቁስላቸው እያገገሙ የሚገኙትና ወደፈራረሱና ዒላማ ወደተደረጉ ቤቶቻቸው ለመመለስ የሚጠባበቁ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ይጨምራል፡፡ ሌላ የሞተ ወታደር ወይም የተገደለ ታጋች ዜና በተለቀቀ ቁጥር በመላ አገሪቱ የበርካቶች ልብ በሃዘን ይደማል፡፡

 

የእስራኤል ጦር ሰራዊት ከጥቃቱ ማግስት ጀምሮ ታጋቾችን ወደ ቤታቸው ለመመለስና ሃማስን ለመደምሰስ ከባድ የአየርና ምድር ጥቃት በጋዛ ላይ ሲሰነዝር የቆየ ሲሆን፤በጋዛ አስከፊ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡ እስራኤላዊያን ግን አሁንም እረፍት አላገኙም፤ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ኢራንንና ሄዝቦላን ጨምሮ በ7 ግንባሮች ውጊያ እንደተከፈተበት የእስራኤል ጠ/ሚኒስትር በቅርቡ
አስታውቀዋል፡፡


ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ፣ ባለፈው ዓመት፣ ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ዓ.ም በእስራኤል የሽብር ጥቃት የተፈጸመበትን አንደኛ ዓመት የሚዘክር የመታሰቢያ ሥነስርዓት “ጽናትና አይበገሬነት” በሚል መሪ ቃል ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል አከናውኗል፡፡

በመታሰቢያ መርሃግብሩ ላይ በጥቃቱ ለተገደሉ ሰዎች የህሊና ጸሎትና የሻማ ማብራት ሥነስርዓት የተደረገ ሲሆን፤ በሥነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የፓርላማ አባላት፣ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሟች ቤተሰብ አባላትና በአዲስ አበባ የአይሁድና እስራኤል ኮሙኒቲ አባላት ተገኝተዋል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በ2012 ዓ.ም ታትሞ ለንባብ የበቃውና ተወዳጅነትን አትርፎ በዚያው ዓመት ብቻ አራት ጊዜ ታትሞ ዝናን ያተረፈው የደራሲ ሜሪ ፈለቀ "ጠበኛ እውነቶች" መጽሐፍ፤ ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ አምስተኛ ዕትም መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀርቧል።

"ጠበኛ እውነቶች" በ4 ክፍሎች የተከፈለ ልብወለድ ሲሆን፤ የተለያየ ማህበራዊና ግላዊ ሕይወትን የሚዳስስ መፅሐፍ ነው።

መጽሐፉ በ252 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤ በውስጡ የተካተቱ አራቱ ታሪኮች፡- “ቅዳሴና ቀረርቶ፣ ቀላውጦ ማስመለስ፣ እናቴን ተመኘኋት፣ ምርጫ አልባ ምርጫ” ይሰኛሉ ::

"ጠበኛ እውነቶች"፤ በሁሉም መጻሕፍት መደብሮች እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

• ለከተማዋ ነዋሪዎች የቤት መስሪያ እንዲሆን 100 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል
• “ከ95 በመቶ በላይ ጥራት ያለው ስራ ሰርተናል” ብለዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ “የሌሎች መጠቀሚያ አትሁኑ፤ ራሳችሁ ተጠቃሚ ሁኑ እንጂ” ሲሉ ለከተማዋ ወጣቶች ጥሪ አቀረቡ። ከንቲባዋ ይህን ጥሪ ያቀረቡት ዛሬ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ስለሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
በዚሁ ማብራሪያቸው ከንቲባዋ “ከተማችንን ኦርጅና ተጫጭኗታል” ያሉ ሲሆን፣ አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ፣ ለስራ እና ቱሪዝም አመቺ ማድረግ ከኮሪደር ልማቱ ዓላማዎች መካከል በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል። እንዲሁም አዲስ አበባ ከ76 በላይ ወንዞች እንዳሏት እና እነዚሁ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ለ50 ሺሕ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ከንቲባ አዳነች በማውሳት፣ በዚያው ዙር ላይ ከተስተዋሉ ድክመቶች መካከል በከተማዋ ነዋሪ እና አመራሮች መካከል የነበረው የተግባቦት ችግር ለተዛቡ መረጃዎች መሰራጨት እንደአንድ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም፣ የደላሎች እና አመራሮች፣ ብሎም አንዳንድ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች በቅንጅት የማይፈርሱ አካባቢዎች እንደሚፈርሱ አድርገው መረጃ በማሰራጨት ነዋሪው እንዲንገላታ ማድረጋቸውን በማንሳት፣ ሆኖም ግን እነዚሁ አመራሮች እንደተቀጡ ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስምንት ኮሪደሮች የተለዩ ሲሆን፣ ከካዛንቺስ እስከ ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ድረስ 2 ሺሕ 817 ሄክታር መሬት “ይሸፍናል” ተብሏል። በርዝማኔ ደረጃ 132 ኪሎሜትር እንደሚሸፍን ከእርሳቸው ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል።
ትልቁ የኮሪደር ልማት ስራ የሚሰራው በካዛንቺስ ሲሆን፣ 1 ሺሕ ሄክታር ስፋት እና 40 ነጥብ 4 ኪሎሜትር ርዝማኔ እንደሚኖረው ተጠቅሷል። ለልማት ተነሺዎች ወደ 4 ሺሕ ግድም መኖሪያ ቤቶች “ተዘጋጅተዋል” ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ “በገላን - ጉራ፣ አራብሳ፣ ልደታ፣ ቦሌ፣ አራዳ...ለጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ተቋማት በቂ የመስሪያ ሼድ ተዘጋጅቷል። በአስተዳደሩ ወደ 5 መቶ አዳዲስ ሱቆች ዝግጁ ሆነዋል” ብለዋል።
ለቤት መስሪያ 100 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን እና በትምሕርት ቤት ጉዳይ ዙሪያ ዝግጅት መደረጉንም ከንቲባዋ በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል። “ተማሪዎች አዲስ በሚማሩበት ትምሕርት ቤት ትምሕርት ወዲያው መጀመር ይችላሉ። ካስፈለገም፣ የማካካሻ ትምሕርት ሊሰጣቸው ይችላል።” ነው ያሉት።
“በዚህ ስራ አዲስ የጥራት ደረጃ አምጥተናል” የሚሉት ከንቲባዋ፣ የኮሪደር ልማቱ ከአጠቃላይ የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ጋር የተጣጣመ እና የተንተራሰ መሆኑን ገልጸዋል። የልማት ስራው በባለሃብቶች እና በበጎፈቃደኞች ተሳትፎ እየተሳለጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ክብርት ከንቲባ አዳነች “በዋጋ፣ በጥራት እና በፍጥነት ዕንከን አልታየባቸውም” ሲሉ በኮሪደር ልማቱ ውስት ስለሚሳተፉ ኮንትራክተሮች የስራ አፈጻጸም አስረድተዋል። ይሁንና በአንዳንድ ስራዎች ላይ የጥራት ችግር ቢታይ “ኮንትራክተሮቹ ወጪውን ሸፍነው አስተካክለው እንዲሰሩ ይደረጋል” ብለዋል።
“ጨረታን በሽፋን አንጠቀምበትም። ሃብትን በቁጠባ እየተጠቀምን ነው። ከ95 በመቶ በላይ ጥራት ያለው ስራ ሰርተናል” ሲሉ፣ ከንቲባ አዳነች ሲናገሩ ተደምጠዋል። ከንቲባዋ ለአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ባስተላለፉት ጥሪ “የሌሎች መጠቀሚያ አትሁኑ፤ ራሳችሁ ተጠቃሚ ሁኑ እንጂ” በማለት፣ በኮሪደር ልማቱ ሳቢያ “ተፈጥሯል” ስላሉት ሰፊ የስራ ዕድል ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይሁንና “ሌሎች” ሲሉ የሰየሟቸው አካላት በትክክል የትኞቹ እንደሆኑ በውል ለይተው አላስቀመጡም።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

• ቤታቸው ለሚፈርስ ነዋሪዎች የ5ቢ.ብር በጀት ተመድቧል

የአዲስ አበባ ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ዕቅድ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት መዲናዋ 8 አዳዲስ የኮሪደር ልማቶችን ታከናውናለች ተብሏል፡፡ የኮሪደር ልማቱ በአጠቃላይ 132 ኪ.ሜ ርዝመት የሚሸፍን ይሆናል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በዚህ የኮሪደር ልማት ቤታቸው ለሚፈርስ ነዋሪዎች የ5 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፕሮጀክቱን ዕቅድ ዘርዝረዋል፡፡ የመጀመሪያው ኮሪደር ካዛንቺስ፣ መስቀል አደባባይ፣ ሜክሲኮና ቸርችልን ያገናኛል፡፡ ሁለተኛው ኮሪደር ደቡብ በርን ከመስቀል አደባባይ የሚያገናኝ ሲሆን፤ ሦስተኛው ከሲኤምሲ እስከ ሰሚት ጎሮ፣ እንዲሁም ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናልና አዲሱ የአፍሪካ ዓለማቀፍ ኮንቬንሽን ኤግዚቢሽን ማዕከል ይደርሳል፡፡

አራተኛው ኮሪደር ከአንበሳ ጋራዥ በጃክሮስ ጎሮ በኩል የሚያልፍ ሲሆን፤ አምስተኛው ኮሪደር ሳርቤትን ከካርል አደባባይ እንዲሁም ብስራተ ገብርኤል፣ አቦ ማዞሪያ፣ ላፍቶ አደባባይና ፉሪ አደባባይ ያገናኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ስድስተኛው ኮሪደር አራት ኪሎና ሽሮሜዳ ላይ ይገነባል። ሰባተኛው ኮሪደር በቀበና ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ስምንተኛው ደግሞ በእንጦጦ ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ የሚሄድ ይሆናል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 2,817 ሄክታር ለመሸፈን ያለመ ነው። ከተማዋ ለተፈናቀሉ የቤት ባለቤቶች ካሳ ከመክፈል በተጨማሪ 100 ሄክታር የሚሸፍን ምትክ ቦታ እና የሁለት አመት የቤት ኪራይ ክፍያ ለመክፈል ማቀዱ ተነግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ይህንን ሰፊ የልማት ጥረት ከዳር ለማድረስ ጥልቅ ዝግጅት መደረጉን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉ ተገለጸ። በዚህም መሰረት የቤንዚን ዋጋ በሊትር 91 ብር ከ14 ሳንቲም መግባቱ ነው የተገለጸው።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባሰራጨው ደብዳቤ እንዳመለከተው፣ የዋጋ ጭማሪ የተደረገው በዓለም ገበያ የታየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ላይ በመመስረት ነው። ይኼው የነዳጅ ምርቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ከዛሬ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ በስራ ላይ እንደሚውል ተጠቅሷል።

የቤንዚን ዋጋ 91 ብር ከ14 ሳንቲም በሊትር ሲሆን፤ ነጭ ናፍጣ 90 ብር ከ28 ሳንቲም በሊትር፤ ኬሮሲን 90 ብር ከ28 ሳንቲም በሊትር፤ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 100 ብር ከ20 ሳንቲም በሊትር፤ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 97 ብር ከ67 ሳንቲም በሊትር እና የአይሮፕላን ነዳጅ በሊትር 77 ብር ከ76 ሳንቲም እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባሰራጨው መረጃ ተጠቁሟል።

አንድ ኤርትራዊ እዚያው ኤርትራ ቤተ መንግስት ስብሰባ ላይ አንድ ሐሳብ አመጣ፡፡ ይኼ የኤርትራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይላል፡፡ ኢትዮጵያን ይወዳል፤ ሆኖም ኢትዮጵያን አያውቅም፡፡ እናም እስቲ ገበሬውንም፣ ሠራተኛውንም ተራ ተራ  አስገብተን፣ ወደ  መሃል ሀገር ወደ ደቡብም፣ ወደ ሰሜንም፣ ወደ  ምዕራብም  እየወሰዳችሁ፣ ኢትዮጵያ ሀገሩ ምን እንደምትመስል አሳዩ፡፡ የሚል ሐሳብ አቀረበ፡፡  ኋላም አራት  መቶ አምስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ እያሰባሰብን፣  አሩሲ፣ ሲዳማ፣  ወለጋ በሙሉ ኢትዮጵያ ሀገሩንም ሰውንም እያሳየን፣ እንደ ትውውቅም እንደ ልምድ ልውውጥም የማድረግ ሙከራ አደረግን፡፡  በሌላ ጊዜ ኤርትራ ስሄድ ሰበሰብኩኝና፤ “እንዴት አገኛችሁት ሀገራችሁን?” ብዬ ጠየቅሁ፡፡ በመጀመሪያ በከፍተኛ ጭብጨባ ድጋፋቸውን  አሰሙ፡፡ በኋላም  አመስግነው ሲያበቁ፤ “በእርግጥም ኢትዮጵያን አናውቃትም” አሉ፡፡
ኤርትራ ጥሩ ሀገር አይደለም፤ ትንሽ ሀማሴንና ከረን አካባቢ ካልሆነ በቀር ለም አይደለም፡፡ ሳር የለም፤ ሜዳ የለም፡፡ በምጽዋ እሳት  የሆነ አሸዋ ነው ያለው፡፡ ቆላው አቧራና ሜዳ ነው፤ ሌላው ደግሞ የድንጋይ ተራራ ነው፡፡ አየሩ ሁለት ነው፤ እርር ንድድ ያለ ቆላ እና እላይ ያለው ደጋ፡፡ ደጋው መሬቱ ወጣ ገባ፣ ድንጋያማ ስለሆነ፤ መሬቱ ለእርሻ  ይኼን ያኽል  የሰጠ አይደለም፡፡ ዝናቡ በቋሚነት  እንዲኽ ነው ተብሎ የሚያስተማምን አይደለም፡፡ ደጋው ነፋሻማ ነው፣ አልፎ አልፎ ባልታመነ  መልኩ ኃይለኛ ዝናብ ይዘንባል፣ ሌላ ጊዜ  ጨርሶ ይጠፋል፡፡ ቆላው ግን  በአመዛኙ ዝናብ የለውም፡፡ ስለዚኽ  ቆላው በከብት አርቢነት ነው  የሚኖረው፡፡ ፍየል፣ በጎች፣ ግመሎች እነዚኽን ነው  የሚያረባው፡፡ አብዛኛው  ሕይወቱና የንግድ ግንኙነቱ ከሱዳን ጋር ነው፡፡  ከመሃል ሀገር ጋር ያለው ግንኙነት  ውሱን ነው፡፡
የትግራይ አማጽያን ከመጀመሪያው አንስቶ የቋንቋና የመልከዓ ምድርን ተቀራራቢነት በማስላት ከኤርትራ አማጽያን ጋር  ለመለጠፍ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ኤርትራውያን  ግን “ጥያቄያችን ከትግሬ የተለየ ነው” በማለት የትግራይ አማጽያንን አላቀረቧቸውም፡፡ በመጀመሪያ  ነገር፣ በኤርትራ ከጣሊያኖቹ ጋር ብዙ በመኖር ከሞላ  ጎደል የክልላዊ የሆነ ብሔርተኝነትና ናሽናሊዝም ጎልብቷል፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በጊዜው በነበረው ኤክስፖዠር አኳያም በንቃተ ህሊና ኤርትራውያኑ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ወትሮም ካላቸው የተዋጊነት ጸባይ ጋር  ንቃተ-ህሊናቸው ከፍ በማለቱና ለምንድን ነው የምንዋጋው? የሚለውን  ጠንቅቀው ማወቃቸው አድቫንስ  እንዲያደርጉ  አደርጓቸዋል፡፡
የትግራይ ፖለቲከኞች ምንድን ነው ከኢትዮጵያዊነት  ይልቅ ወደ ኤርትራ ወገን የሚስባቸው?  እንዴትስ  ሆኖ ነው እነርሱ ከኤርትራ ጋር  ሊቀላቀሉ  የሚችሉት? ኤርትራ ሌላ፤ ትግራይ  ሌላ! ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ቢሆን ሌላውን ይዞ ሲዋጋ ቆይቶ እንደ ተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች እነርሱንም ጥሎ ነው የወጣው፡፡ ከኤርትራው ጋር  ስናስተያየው፣  ትግራይ በምንም ምክንያት ከኢትዮጵያ የሚገነጠልበት ምክንያት የለም፡፡
ከእዚያ በላይ ኤርትራውያን እርስ በእርስ ስለሚተባበሩ፣ እነርሱን (የትግራይ አማጽያንን) እንደ በለጧቸው ሁሉ እኛንም  ብዙ  እንዲያስከፍሉን አቅም ሆኗቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የትግራይ አማጽያን (ወያኔዎች) በብሔርተኝነት፣ አማራን በመጥላት፣ ታሪክ እየቆጠሩ  “ጥንት እኛ ነበርን አክሱምንና ሌላን ሌላን የገነባን፣ ያለንን ሥልጣንና ኃያልነታችንን የነጠቀን አማራ ነው” የሚል አጓጉል ነገር በህብረተሰብ ውስጥ ለመርጨት ይጥሩ ነበር፡፡
የኤርትራ አማጽያን መጀመሪያም በንጉሡ ዘመንና በለውጡ ሂደት ወቅት ሠራዊታችን ተመናምኖ፣ ተዳክሞ በነበረበት ጊዜ እየገፉ እየገፉ ብዙ አስከፍለውን ነው አስመራን የከበቡት፡፡ እንደሚታወቀው ሁለቱም አንድ  ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም አምሳያ ቢሆኑም በየራሳቸው የመኖሪያ ክልል የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ በየትም አካባቢ ሊፈጠር እንደሚችለው በታሪክ፣ በኑሮና፣ በህይወት ዘይቤ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይኼም ሁኔታ በአብዛኛው ከጊዜ በኋላ  በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና በወረራ የተፈጠረ ነው፡፡ የሰሜኑን ክልል ጣልያኖችም፣ ግብፆችም፣ ዐረቦችም እየተመላለሱ ብዙ ችግር የፈጠሩበት ሆኖ የኖረ በመሆኑ፣ ያ ሁኔታ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ልዩ ልዩ  መልክ ከማላበሱ ባሻገር፣ በክልሉ ከፍ ያለ የውጊያ ልምድ ሰጥቷል፡፡  የአካባቢያዊነት ስሜትንና የብሔርተኝነትን ባኅርይ ፈጥሯል፡፡ ለዚህ  ሁሉ ምክንያት በዚያም ሆነ በዚህ በኩል “አንበገርም ሀገር አናስወርርም” ከሚል መከላከል፣ የረጅም ጊዜ የተዋጊነት ሥነ-ልቦና ተገንብቷል፡፡
በአልበገርም  ባይነት ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከባብረን፣ ኋላ ላይ ተሸንፈን ሰሜኑ (ኤርትራ) በጣሊያኖቹ ቁጥጥር ሥር ሲውል፣  በስድሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከጣሊያኖቹ ጋር በመኖር አዳዲስ ሁኔታዎች  ተፈጠሩ፡፡  ይሄም  ሁኔታ በእነዛ ዓመታት አንደኛ፣ ከኢትዮጵያዊነት ይበልጥ በተለየ መልኩ ኤርትራዊ ብሔርተኝነት ተገንብቷል፡፡ ሁለተኛ፣ “ኢትዮጵያ ለጠላት ባትሰጠን ልትከላከልልን ሲገባ፣ ኋላም ምኒልክ ሊዋጋና  ጣሊያንን ማባረር ሲችል፣ ለጣሊያን ሸጦናል” ብለው ያምናሉ፡፡ ይሄንን ሐሳብ ከመሃል ሀገር ሰዎችም አንዳንዶች ይጋሩታል፡፡
በግሌ ግን ይሄን ሐሳብ ተንተርሼ ለመፍረድ አስቸጋሪ  ይሆንብኛል፡፡ እርግጥ ነው በዚያ ጊዜና ቦታው ላይ የለንም፡፡ በራሱ  አህያና አጋሰስ የራሱን መሳሪያና ጥይት ይዞ፣ በሶና ቆሎ እየበላ ያን ሁሉ  ነገር  የሠራ ሠራዊት፣ ከእዚያ ተነስተህ ሂድና እንደ ገና አስመራና ምጽዋ ተዋጋ ቢባል፣ በጦርነት ጊዜ ያለውን ችግር ስለማውቅ፣ በእውኑ “ምኒልክ ሲቻላቸው ነው ሳይፈልጉ የቀሩት” ብሎ ለመፍረድ እቸገራለሁ፡፡
ብዙ ሰዎች ግን “ይቻላል፤ ጣሊያን ተፍረክርኮ እየሸሸ ነው፤ ቢከተሉት እስከ ባህሩ ድረስ አይቆምም፡፡ ከዚያ በኋላ  አካባቢው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከውጭ ወራሪዎች ነጻ ይሆን ነበር” ይላሉ፡፡ “ያ የተተወ ሁኔታ  እንደገና መልሶ ተደራጅቶ አርባ ዓመት አድብቶ ኢጣሊያ  በ1928  ኢትዮጵያን  ወረረ፡፡ ይሄ የምኒልክ ጥፋት ነው” ብሎ የሚያምን ከመሃል ሀገር ብዙ ሰው አለ፡፡ ኤርትራውያኑ ደግሞ “ሆን ብሎ ነው፣  ለመሳሪያ ነው የሸጠን” ብለው ያምናሉ፡፡
በነገራችን ላይ፣ ወታደሩም ውስጥ ሲቪልም  ውስጥ እንደ ቀልድ እንደ ፌዝ፤ “እናንተ የመውዜር ሽያጮች” እየተባለ ይፎተት ስለነበር፣ ኤርትራውያኑ “ተሸጠናል” ነበር የሚሉት፡፡ ምኒልክ በደቡብና ምዕራብ ያን ያህል ተጋድሎ አድርገው ሀገሩን ሲያድኑ፣ ቀይ  ባህርንና ኤርትራን የመሰለውን ሀገር ሸጠዋል (እየቻሉ ሳይከላከሉ ቀርዋል) መባላቸው ለማመን ያስቸግረኛል፡፡ “የዚህ ጉዳይ ብልቱ ምንድን ነው?” ብሎ  መጠየቅ ከሁላችንም የሚገባ  ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ሻዕቢያ እና  የሰሜኑ አማጽያን፣ ይሄን “ተሸጠናል” የሚለውን የተንኮል ፕሮፓጋንዳ፣ የሕዝብን ልብ ለማስሸፈት ከተገቢው በላይ  አስተጋብተውታል፡፡ በመካከላችን ልዩነቱ እንዲሰፋ የሚፈልጉ ወገኖች ጥላቻውን ለማክረር ይኼንን ሬቶሪክ ተጠቅመውበታል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ በሚገባ እንዲሠራጭ አድርገውታል፡፡ አዲስ የተወለደው ወጣቱ ሁሉ  ሳይመረምረው  ውጦታል፡፡ ሁሌም  ቢሆን የሀገራችን ዋና ችግር ይኼው  ነው፡፡
 በኤርትራ የጣሊያኖች ጣልቃ ገብነት ባይከሰት፣ ከላይ ያነሳነው  በአካባቢው የተፈጠረው ስሜት ባይመጣ  ኖሮ፣ ያ ሀገር  የስልጣኔዎቻችን በር፣ የመጀመሪያው የመንግሥታችን  ማዕከል ከመሆኑ አንጻር ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተሻለ  የኢትዮጵያዊነት ስሜት  መፍጠር የነበረበት ቦታ ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ሳይሆን ቀርቶ የተቀረነው ትውልድ  ሁሉ ስንት ከፈልንበት?... ስንት?!… እኔ እንጃ… የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈልነውን ዋጋ በቅጡ የሚያውቀው  አይመስለኝም፡፡ ስንቱ ደማ!?  አስራ ሰባት ዓመት ሀገር  በማልማትና ብዙ ግንባታ  በመሥራት ፈንታ፣  ሁል ጊዜ ሥራችን ጦርነት ነው፣ መሞት ነው፤ መግደል ነው፡፡
(ከይታገሱ ጌትነት ገበየሁ ”መንግሥቱ ኃ/ማርያም፤ የስደተኛው መሪ ትረካዎች”፤ ከገጽ 126-129 የተቀነጨበ)

Monday, 07 October 2024 20:01

የግጥም ጥግ

ውሽንፍር ለብሼ

ይኸው ሰማይ በራ… ህዋው ቦገግ አለ፣
 የኮከቦች መንደር ….ተመሰቃቀለ፣
 ከበደ ነጎድጓድ…. በረዶም ወረደ፣
 ዘመናት የፀናው… አለት ተንጋደደ፣
  …………………….
በዚህ ምፅዓት መሀል…ወንጀሌን ቆጥሬ፣
መጥፋቴ ነው አልኩኝ፣
ከሃያል ክንዱ ላይ… ቅንጣት ቢልክብኝ፣
እንክርዳድ አከልኩኝ፣
በቆምኩበት ራድኩኝ፣
………………………..
እናም ባሻገሬ…በፅናት የቆመ
ታየኝ እና ፃድቅ፣
ሸሸሁኝ ወደ እርሱ…ቢሸሽገኝ ብዬ
ከዚያ ሁሉ ድቅድቅ፣
ግን ከፋ ነጎድጓድ…ብልጭታ ጨመረ፣
ምድርን ይንጣት…ያስጮሃት ጀመረ፣
ፍጥረት ተከተተ፣
ከፃድቅ ሰው ጉያ… ከእግሮቹ ስር ሆኜም
ቁጣ በረከተ፣
…………………………
አዘንኩ ለዚያ ሰው… እኔ በእሱ ልድን
ስገባ በእቅፉ፣
እሱ በእኔ ሰበብ..ታሰበኝ መርገፉ፣
ለኃጥዓን የመጣ… እንዲል መፅሐፉ፣
………………………
ፃድቅ ከሚጠፋ…ልጥፋ ከአጠገቡ
ከእቅፉ ወጥቼ፣
ሄድኩኝ ከእርሱ ርቄ
ቆምኩኝ ለብቻዬ…አንገቴን አቅንቼ፣
    ድንገት ልብ ገዛሁ፤
ምህረቱ እንደማያልቅ… ሲታወሰኝ ክብሩ
ጀገንኩኝ በዶፉ፣
ሊያጠፋኝ በበራው…ሄድኩኝ በብልጭታው
     በብርሃን አክናፉ፣
ፍፁም ጠፋሁ ካለም…ከመቅደሱ ገባሁ
    ቆምኩኝ ከደጃፉ፣    
    ወንጀሌን ሳልቆጥር…በምህረቱ ሳምን
    እንደ ንስር ፀናሁ…ጀገንኩኝ በዶፉ፣
    ዙፋኑ ስር ሆኜ…ቅጣቶቼ አለ.፡፡ (አብዱራሕማን ጀማል፤ ከ“ደቦ 60 ደራስያን” መድበል)


የመክፈቻ ጉባኤያቸወን እያደረጉ ያሉት ሁለቱ ምክር ቤቶች የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን በአምስት ድምጸ ተአቅቦ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት አድርገው ሰይመዋል።

ፕሬዝዳንቱ በምክር ቤቱ ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

ዛሬ ምሽት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የመሬት ንዝረት ለ18 ሰከንድ ያህል መቆየቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም አስታውቋል፡፡
 
የተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤልያስ ሌዊ በመዲናዋ የተከሰተው የመሬት ንዝረት በአዋሽ ፈንታሌ ተራራ አካባቢ በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ሞገድ አማካይነት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።    
 
ህብረተሰቡ በአዲስ አበባ የተከሰተው የመሬት ንዝረት መሆኑን አውቆ፤ የእለተ እለት እንቅስቃሴውን በተረጋጋ መንገድ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
 
በፈንታሌ ተራራ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን ዶ/ር ኤልያስ ሌዊ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል።

(በጓድየ ብሽየ ኤረማ) - የቤተ ጉራጌ ምሳሌያዊ አነጋገር


አንድ በጣም ባለፀጋ የሆኑ የተከበሩ ባላባት ባንድ መንደር ይኖራሉ። ጌታዬ ጌታዬ የማይላቸው የለም። እኚህ የተከበሩ ባላባት፣ አንድ ብርቄ የሚባል አሽከር ነበራቸው። ብርቄ አሽከርነት ያምርበታል። ሲልኩት ወዴት፣ ሲጠሩት አቤት ማለት ይችልበታል፡፡ ዘወትር ግብር ገብቶ፣ ድግሱ ተበልቶ ጌትየውን ብርቄ እጅ ሲያስታጥብ፤
“ሰማህ ወይ ብርቄ” ይሉታል።
“አቤት ጌታዬ” ይላል ብርቄ።
“አሁን እኔ ብሞት ምን ታደርግ ይመስልሃል?”
“ጌታዬ እርስዎ ከዚህ አለም ተለይተው፣ እኔ አዚህ ቤት አልቀመጥም”
“ታዲያ ምን ትሆናለህ?”
“እመንናለሁ። ዓለም በቃኝ እላለሁ። ጀርባዬን ለዓለም፣ ፊቴን ለገዳም እሰጣለሁ”
“ተው አታረገውም ብርቄ?”
“በጭራሽ። እርስዎ ሞተው እኔ እዚህ ቤት አንዲት ቀን እህል ውሃ አልቀምስም!”
“መልካም። ለዚህ ታማኝነትህ አንድ ኩታ ተሸልመሃል!”
 ብርቄ እጅ ነስቶ ኩታውን ያገኛል።
ሌላ ቀን “ብርቄ እኔ ብሞት ምን ታደርጋለህ?” ይሉታል።
“ምን ያጠያይቃል ጌታዬ? መመነን ነዋ! ከእርስዎ ወዲያ ዓለም ለምኔ!” ይላል።
“ብርሌ ጠጅ ስጡት ይባላል!”
ሌላ ቀን። “ብርቄ እኔ ብሞት ምን ታደርጋለህ?”
“ዕለቱን ቅሌን ጨርቄን ሳልል ወደ ገዳም ነዋ ጌታዬ!”
“ዕውነት ታደርገዋለህ ብርቄ?”
“አይጠራጠሩ ጌታዬ! ምን ቀረኝ ብዬ እዚህ ቤት እቀመጣለሁ?”
“እኔ እምልህ ብርቄ?”
“አቤት ጌታዬ?”
“እንዲያው ለነገሩ ከእኔ ቀድመህ መሞት ታስቦህ ያውቃል? አንዳንዴ ለምን እኔ ቀድሜዎት ልሙት እንኳ አትለኝም?”
ብርቄም ትንሽ አሰብ አድርጎ፤
“አይ ጌታዬ ሳላስበው ቀርቼ መሰለዎት? አስቤዋለሁ። ግን ከተናገርኩ የጌታዬን ሞት የተሸማሁ እንዳይመስልብኝ ብዬ ነው።”
ሌላ ቀን። ብርቄን ጠርተው ደግመው በጨዋታ መሀል፤
“ከእኔ ቀድመህ የምትሞት አይመስልህም?”
“ኧረ በጭራሽ ጌታዬ!”
“ለምን?”
“እኔ ከሞትኩ ማን እንደኔ ያለቅስልዎታል ጌታዬ! ኧረ በጭራሽ እግዜር እንደዚያ ያለ ነገር አያድርስብን!! እርስዎ ከሞቱ ግን እዚች ቤት አንዲት ጀምበር አላድርም - ወደ ገዳም ነው!”
“ይሄን ያህል ትወደኛለሃ?”
ከባድ ጉርሻ ያጎርሱትና “ጠጅ ስጡት!” ብለው ያዙለታል።
ጌታዬው እንዳሉት እሳቸው ቀድመውት ሞቱ። ከሚስታቸው አንድ ትንሽ ወንድ ልጅ ብቻ ነው ያላቸው። ሚስታቸው 6 ወር ካዘኑና መንፈቃቸውን ካወጡ በኋላ ሌላ ባል አገቡ። ብርቄም ያዲሱ ጌታ አሽከር ሆነ። “እርስዎ ከሞቱ  እመንናለሁ ጌታዬ!” ማለቱን ቀጠለ።
አንድ ቀን አዲሱ ጌታው ግብር አግብተው፣ ሰው በድንኳን ግጥም ብሎ እየተበላ እየተጠጣ፣ ብርቄ እንደ ልማዱ ተፍ ተፍ እያለ እያስተናገደ ሳለ፣ አንድ አዝማሪ ተነስቶ መሰንቆውን እየገዘገዘ ጨዋታ ጀመረ።
ድምፁን አዝልጎ፤ “ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ” አለና ጀመረ። ህዝቡ በከፊል፣ አዝማሪው የሞቱትን ጌታ በማንሳቱ “ምን ሊል ይሆን?” በሚል አይነት ፀጥ አለ። አዝማሪው ደገመና፤
“ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ
….ሚስቴስ ደህና ናት ወይ? (ወደ ሚስትየው እያየ)
…ልጄስ አደገ ወይ? (ወደ ልጅየው እያየ)
…ብርቄስ መ…ነ…ነ ወይ?” (ወደ ብርቄ ቀና ብሎ) ብለው ቢጠይቁኝ፤
ሚስትዎ ደህና ናቸው ልጅዎትም አድጓል።
(ቆም አድርጎ ወደ ብርቄ እያየና እያንዳንዱን ቃ  እየረገጠ)
..ብ..ር..ቄ..ም አ..ል…መ..ነ..ነ…ም!! ብዬ ብነግራቸው
አይ ጉድ! አይ ጉድ! አይ ጉድ! ያሉበት ረገፈ ጣታቸው!!”
ሲል ገጠመ። ሰው ሁሉ ወደ ብርቄ ተመለከተ። ብርቄን የሰው ዐይን ከአገር አስወጣው።
*  *  *
ለእምነታቸው የሚኖሩ፣ ማተባቸውን የማይበጥሱ፣ የተናገሩትን የማያፈርሱ፣ በምላሳቸው የማይኖሩ ብቻ ናቸው በህዝብ የሚታመኑ። ቤታቸውንና አለቃቸውን ለማስደሰት ወይም ለመሸንገል ሲሉ ብቻ “አቤት!” “ወዴት!” የሚሉ የየሥርዓቱ አሸርጋጅ ይሆናሉ እንጂ፣ በየተደገሰበት ሁሉ ከበሮ መቺ ይሆናሉ እንጂ፣ ለህሊናቸውና ለእምነታቸው አያድሩም።
“ህዝቡን ልናገለግል”፣ “ሀገርን ልናድን”፣ “ምድር ሰማዩን ልናለማ”፣ “የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ልንለውጥ”፣ “ከተማ ልናሰፋ”፣ “የገጠሩን ህዝብ ልናሰለጥን”፣ ወዘተ የሚል አይነት ቃል መግባትና “ይህ ካልሆነ ወንበሬን እለቃለሁ”፣ “ይህ ካልሆነ የጓዶች አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋኝ!”፣ “ይህ ካልሆነ ማናቸውንም ፍዳ ልቀበል!” ማለት የተለመደ ሆኗል። እንደ ብርቄ “እርስዎ ከሞቱ በቃ እመንናለሁ” ማለት። ከዚያ ምንም ለውጥ ሳያመጣ ሲቀር ለአዲሱ ጌታ ማደር። አይንን በጨው ታጥቦ “ዛሬም እንደትላንት በአላማ ጽናት ራእዬን እውን ለማድረግ እስከመጨረሻው የደም ጠብታ፣ እስከመጨረሻው አንድ ሰው፣ እታገላለሁ” ሲሉ ቃለ መሀላ ማዥጎድጎድ። ጌታዬ ከሞቱ እዚች አገር አንዲት ቀን አልውልም አላድርም ማለት!.. ቃል መግባት… ዕቅድ ማቀድ…. ፖሊሲ መንደፍ….በየወንዙ መማል….. መማማል መመሪያ ማውጣት ….አዋጅ ማወጅ…. በየፌርማታው አበጀህ አበጀህ መባባል…. መግለጫ ማውጣት…. መጽሀፍ መግለጥ… ፕሮጄክት መቅረጽ… መርቆ መክፈት… መጨባበጥ… “ከመቼውም በበለጠ በአዲስ መንፈስ ተነስተናል” ማለት… ትላንትናን በላጲስ ማጥፋት…ነገን በእርሳስ መሳል…ተግባርና “አፈፃፀም” ግን የለም። ቃል ይፈርሳል። ቃል ይበላል። የሚወገዝ ይወገዛል። መካድ። መካካድ ይቀጥላል። የሚረገም ይረገማል። በትብብር በደቦ፣ በብዙኃን ድምፅ መራገም እንጂ ከልብ የሚሆን ምንም ነገር የለም እንደ ማለት ነው። “ሲቸግር የእንጀራ እናትን እምዬ  ይሏል” ነውና፣ የትላንቶቹን ለመርገም የትላንት ወዲያውን መጥቀስና ማወደስ ይቀጥላል።
አዲስ መፈክር ይቀመራል። በህብረት ያንን መፈክር ማስገር ይቀጥላል። በልብ መክዳት፣ በአካል አለሁ ማለት ይዘወተራል። እስከሌላ መከዳዳት… እስከሌላ ቃል ማፍረስ… “ልጅ እገሌ”፣ “ጓድ እገሌ”፣ “ክቡር እምክቡራን” መባባል። ሆኖም “በጨለማ ማፍጠጥ ደንቆሮን መቆጣት ነው” እንደሚባለው ልብ ውስጥ እውነተኛው ፍቅር፣ እውነተኛው አገር መውደድ፣ እውነተኛው ለህዝብ የመቆም ስሜት ሳይኖር፣ ዓላማና እቅድን በስራ ላይ ማዋል ከቶም ዘበት ነገር ነው። መሪና መሪ፣ አለቃና አለቃ፣ ፓርቲና ፓርቲ፣ ባለስልጣንና ባለስልጣን፣ ዜጋና ዜጋ በመካከላቸው ልባዊ መተማመን ከሌለ ሥራ አይሰራም። ዕቅድ አይፈፀምም። ፕሮግራም አይተገበርም። ቃል ህይወት አይሆንም። ይስሙላ፣ ለበጣ፣ የአደባባይ ማስመሰል፣ የሸንጎ ዲስኩር፣ የስብሰባ ንግግር ብቻ ሆኖ ይቀራል።
የሀገራችን አንዱ አንኳር ችግር፣ ከእቅድ ነዳፊ እስከ ፈፃሚው ድረስ ልባዊ መተማመን አለመኖር ነው። “ይህን ያለው ይህን ሊል ፈልጎ ነው” በሚል የግራ ትርጉም የታጠረ አስተሳሰብ ይበዛል። ቡድንና ቡድን አይተማመንም። መስመሩን ሳይሆን በመስመሮች ማህል ማንበብ (Between the lines እንዲሉ) ነው ፈሊጡ። በውስጥ የተቀበረ ፍላጎት (Hidden Motive) ካለ ምንዛሪ ይበዛል። ቅጥያና ዘርፍ እያበዙ “ትርጉም የኔ”፣ “ስርዝ ያንተ”፣ “ቅንፍ የነሱ” ማለት ቋንቋ ይሆናል። አፍአዊ የሆነ ያሸበረቀ ቃል ሲበዛ ተግባር ባዶውን ይቀራል። ዞሮ ዞሮ ወሳኙ ግን ልባችን ውስጥ ምን አለ የሚለው ነው። ልባችን ትግል እያሰበ፣ አፋችን ድል ቢያወራ ዋጋ የለውም። ልባችን ሹመት እያሰበ፣ አፋችን የኢኮኖሚ ልማት ቢያወራ ነገ የሚጋለጥ ከንቱ ዲስኩር ይሆናል። ሁሉም የሚያስተጋባውና የሚተገብረው ጥንት የተሰራበትን ንጥረ-ነገር ነው፤ የውስጡን። የጠዋቱን።
እውነተኛ ፍሬ ከእውነተኛ ተግባር፣ ከእውነተኛ እምነት ነው የሚገኘው። ያ ሳይኖር ፍሬ መጠበቅ ከንቱ ነው። ነጭ ባህር ዛፍ ላይ፣ ቀይ ባህር ዛፍ አይበቅልም ማለትም ይሄው ነው።

Page 1 of 727