Administrator

Administrator

Saturday, 13 September 2014 13:20

የዛሬ 40 ዓመት፡፡

(መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም)
… መስከረም ሁለትን ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡ ደርግ ከንጉሰ ላይ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ትልቅ ክብረበአል ነበር፡፡ ወጣቱ አብዮት የሚባለውን ሲያይ መጀመሪያ አካባቢ ጉጉና ደስተኛ ነበር፡፡ በአሉም በሠራዊቱ የተለያዩ ትርኢቶች ታጅቦ፣ በየአመቱ በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ወታደሩ ከ4-5 ሰአት የሚዘልቅ ትርኢቶችን ያቀርባል፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግስትና በብሔራዊ ቤተመንግስትም በእለቱ ጓድ መንግሥቱ ኃለማርያም እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውብአንቺ ቢሻው በተገኙበት ለሁሉም የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ታላቅ ግብዣ ይደረግ ነበር፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ ሲታወስ ደርግ አዋጁን ከተናገረ በኋላ፣ ህዝቡ የእርስ በእርስ ግጭት ጠብቆ ነበር፡፡ ከፍተኛ እልቂት ይመጣል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ታንኮችና መትረየስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱ ነበር፡፡ ሰው መተያየት ፈርቷል፣ መኪናዎቹንና ታንኮቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቷል፡፡ ሰው በአጠቃላይ እርስ በእርስ ተፈራርቷል፡፡ ምናልባት ሌሊት አሜሪካን በአውሮፕላን ወረራ ፈጽማ ወይም እስራኤል መጥታ ንጉሱን ይወስዳሉ የሚሉ ሃሳቦች በፍራቻ መሃል ይንሸራሸሩ ነበር፡፡
ክቡር ዘበኛ እና ወታደሩ ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን ክቡር ዘበኛ ምንም የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የመሣሪያ ድምጽ እንኳ በእለቱ ኮሽ አላለም፡፡ መውረዳቸውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ መፈንቅለ መንግስት አድራጊው ወገን፣ ክቡር ዘበኛ ካንገራገረ ማጥቃት የሚችል ሠራዊት በቤተ-መንግስቱ በድብቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
ንጉሡ ከቤተ-መንግስታቸው በደርጉ ሃይሎች ተከበው፣ በተዘጋጀችለቸው ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ገብተው ወደ 4ኛ ክ/ጦር ሲወሰዱ፣ ብዙ ህዝብ በመንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ በእድሜ ጠና ባሉት ሰዎች ላይ የማዘን ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ወጣቱ ደግሞ “ሌባው! ሌባው! ሌባው!” የሚል ስድብ በፉጨትና በጩኸት እያጀበ ይሰነዝራል፡፡ ወጣቱ በጣም ይሳደብ ነበር፡፡ በተለይ ቮልስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ የነበረው ፉጨትና ጭብጨባ ልዩ ነበር፡፡
ደርጉ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት ስልጣኖች በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ከዋለ በኋላ ስለነበር እሣቸውን ከስልጣን ያወረደው መንገዱ ሁሉ የቀና ሆኖለታል፡፡ ጃንሆይም ይህን ስለሚያውቁ በአጋዦቻቸው አማካይነት ሌላ እርምጃ ለመውሰድ አላንገራገሩም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡ ወደ ቮልስዋገኗ እንዲገቡ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፡፡ ለምን በቮልስዋገን ተወሰዱ? ተብሎ ሲታሰብ ደርግ እሣቸው መሆናቸው ሳይታወቅ እንዲሄዱ የተጠቀመበት ቴክኒክ ነበር፡፡ ተራ ሰው እንዲመስሉና ግርግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አውቆታል፡፡ በኋላ ዳርና ዳር መትረየስ የጫኑ ጂፖች አጅበዋቸው ሲሄዱ ሰው ከፉጨትና ጭብጨባ፣ ስድብ በቀር አንዲት ጠጠር እንኳ አንስቶ አልወረወረም፡፡ በዚያ ላይ ደህንነቱ በሰው መሃል ተሰግስጓል፡፡ ወታደሩም አንዳንዱ ሲቪል ለብሷል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በእውነቱ ምስኪናዊ ህይወት ነው ያሳለፉት፡፡ ማንም ጠያቂ የላቸውም ነበር፡፡ የሚቀርባቸውም ሰው አልነበረም፡፡ ብቻቸውን አንድ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ንጉሱ ዘወትር ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ አዙረው ፀሎት ሲፀልዩ ስታይ በጣም ያሳዝኑ ነበር፡፡ ማንም አያናግራቸውም፤ አይጠጋቸውም ነበር፡፡ አንዲት ምግብ የምታበስል ልጅ አለች፤ እሷም ብትሆን በተወሰነ ሰዓት መጥታ ስራዋን ሰርታ ነው የምትሄደው፡፡ አርብ እና አሮብን ጠንቅቀው ይፆሙ ነበር፡፡ ልጅቱም ዘግይታ ነው ምግብ የምትሰራላቸው፡፡ ልጅቱ ልብሱን አዘጋጅታላቸው ትሄዳለች፡፡ ራሳቸው ይለብሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዚያው በቤተ መንግስቱ በቀን እስረኝነት ከሰው ተገልለው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ…
(“ህይወት በመንግስቱ ቤተ-መንግስት” የተሰኙ ተከታታይ መፅሃፎች ደራሲና የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል ወ/ር እሸቱ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አስመልክቶ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡)

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የግል አሽከርና አልባሽ ስዩም ጣሰው በ14 ዓመት የቤተመንግስት አገልግሎታቸው፣ በዕለት ማስታወሻቸው ላይ ሲያሰፍሩ የቆዩትን መረጃ ጋዜጠኛ ግርማ ለማ አስተካክሎ በ2006 ዓ.ም “የንጉሡ ገመና” በሚል ለንባብ አብቅቶታል፡፡ የጃንሆይ የመጨረሻ ሰዓት ምን እንደሚመስል ለማስታወስ ከዚሁ መጽሐፍ ላይ ተከታዩን ቀንጭበን አቅርበናል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን የወረዱት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ነው - የዛሬ
40 ዓመት፡፡

…እርሳቸውም የተቀበሉት ከልብ ነው፡፡ ማታ የሻምበል ደምሴ የክብር ዘበኛ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ከጀ/ፍሬሰንበት ቢሮ ድረስ መጥቶ አቶ ክበበው ኃይሌንና አቶ ወንደሰን አንዳርጌን አነጋግሮአል፡፡ ይኸውም ግርማዊነታቸው ምናልባት ሕይወታቸውን በገዛ እጃቸው እንዳያጠፉ በአጠገባቸው የሚገኘውን መሣሪያና መድኃኒቶች በሙሉ እንዲያሸሹ ነግሮአቸው ሄደ፡፡ እነርሱም መድኃኒት ይኑር አይኑር ስለማያውቁ፣ መሳሪያው ብቻ ከአጠገባቸው ወደሌላ ኰሜዲኖ ውስጥ ተዛውሮ እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡ እኔም ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡
በ2/1/67 ዓ.ም ጠዋት አድሚራል እስክንድር መጥተው፤ “አዋጅ ስለአለ ሬዲዮ ይከፈትላቸው” ስላሉ ገብተው፣ ሬዲዮ በ1፡30 ሰዓት ሲከፈት ሳይሠራ ትንሽ ቆየት ብሎ ግርማዊነታቸው ከሥልጣን መውረዳቸውን ሲያውጅ፣ ጃንሆይም “ወይ አንተ እግዚአብሔር” ብለው በጥሞና እስከመጨረሻው ድረስ አደመጡ፡፡ ከዚያም ትንሽ ቆይተን ከመኝታ ቤት ወደ ውጭ ወጣን፡፡
ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ አድሚራል እስክንድር መጥተው ጠሩንና ገባን፡፡ ከዚያም ልብስ መልበስ ጀመሩ፡፡ በሚለብሱበት ጊዜ ከመጥቆራቸው በስተቀር ከሰሞኑ ምንም ለውጥ አላሳዩም፡፡ ለብሰው ከጨረሱ በኋላ ፀሎት ለማድረስ ስለቆሙ ትተናቸው ወጣን፡፡ ፀሎት እንደጨረሱ 2፡10 ሰዓት ሲሆን በረንዳ ወጥተው ከተንሸራሸሩ በኋላ፣ ወደ ውስጥ ተመልሰው ከአሽከሮች መኝታ ቤት ሲደርሱ ልዕልት ሰብለ ደስታና ወ/ሮ ሜሪ አበበ ከአድሚራል እስክንድር ጋር ሲመጡ አገኙዋቸው፡፡ እጅ ነስተው ሳሙዋቸው፡፡ ከዚያም ተያይዘው ወደ መኝታ ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም አድሚራል መጡና “ቁርስ ገበታ ቤት ከሚሆን መኝታ ቤት ቢሆን ይሻላል” ስላሉ ለቦዮቹ ነገርንና ወደዚያው ተዘጋጅቶ፣ ቁርስ በተለመደው ሰዓት 2፡20 ሰዓት ቀረበ፡፡
እርሳቸውም ከተዘጋጀላቸው ከመልበሻ ቤት ገቡና ተቀመጡ፡፡ ሲያዩዋቸው ታዲያ የመዝናናት መልክ ነበራቸው፡፡ ቁርሳቸውንም ከወትሮው ባልተለየ ሁኔታ በሉ፡፡ እንደውም ከውሻቸው ጋር እየቀለዱ ሥጋ ሲያጐርሱ፣ ሲስቁ በጣም ገረመኝ፡፡ እንኳን ከሥልጣን የወረዱ ምንም የሆኑ አልመሰላቸውም ነበረ፡፡ ቁርስ በልተው እንደጨረሱ ፀሎት አደረሱና በ 2፡38 ወደ ሳሎን ወጡ፡፡
በ2፡43 ሰዓት ደግሞ ከመኝታ ቤት ተመለሱና እቢሮአቸው ቁጭ ብለው “ቦርሳዬን አምጣልኝ” አሉኝና ወስጄ ሰጥቼ ሲከፍቱት ወጣሁ፡፡ ትንሽ እንደቆየሁ አንድ ነገር ተሰማኝ፡፡ ይኸውም ምናልባት መድኃኒት ከቦርሳቸው ውስጥ አስቀምጠው እንደሆነ አውጥተው የጠጡ እንደሆነ ብዬ ስለተጠራጠርኩ፣ አድሚራልን ጠርቼ ገብተው ከእርሳቸው ጋር እንዲቆዩ ስለነገርኳቸው፣ ከእህቶቻቸው ጋር ተያይዘው ገቡ፡፡
እነርሱም ሲገቡ ቦርሳቸውን ከፍተው ከውስጡ ዕቃ ይፈልጉ ነበር፡፡ መሳሪያቸውን ግን ማታ ካደረበት ቦታ አንስተው ከዱሮው ቦታ አሽከሮቹ መልሰው አስቀምጠውት ስለነበር፣ ለፀሎት እንደቆሙ ተመካክረን፣ እኔ ሁለት ሽጉጥና አንድ በቦርሳ ውስጥ ያለ አውቶማቲክ ሽጉጥ (በጣም ትልቅ ነው) አወጣሁና፣ ከተረኛው አሽከር መኝታ ቤት ካለው የወረቀት መመርመሪያ ውስጥ አስቀመጥኩት፡፡ ስለዚህ ከመድኃኒት ሌላ መሳሪያ ስለሌለ የሰጋሁት መድኃኒት ይጠጣሉ ብዬ ነበር፡፡
ጃንሆይና ልዑል ራስ እምሩ ቢሮ ገብተው ትንሽ ቆይተው፣ በ4፡00 ሰዓት የደርጉ አባሎች በጀ/ኃይለጊዮርጊስ ተጠርተው ከቢሮ ገቡ፡፡ ወደዚያው ሠላምታ ሰጡና አንድ የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ ሻለቃ አዋጁን አነበበላቸው፡፡ ይኸው ሻለቃ በቀደም ስለውጭ አገር ገንዘብ መመለስ ጉዳይ ለመነጋገር የመጡት የደርጉ አባሎች መሪና ወረቀቱንም ያነበበው ደበላ ዲንሳ ነበር፡፡ አዋጁን ለማንበብና ጃንሆይን ይዘው ለመሄድ በገቡ ጊዜ፣ ከ8 ቀን በፊት የክብር ዘበኛ መረጃ ሠራተኞች በሻምበል ኃይሉ አዴሳ ኃላፊነት ለውስጥ ጥበቃ ተብሎ የገቡት፣ ከአሽከሮች መካከል እደርጐቹ ላይ አደጋ እንዳይጣል ቁጥጥራቸው ፍፁም ሌላ ነበር፡፡ ከውጭ ደግሞ ዙሪያውን ከፎቅ ሆኖ እንዳይተኮስባቸው መሳሪያዎቻቸውን ወደላይ አድርገው ይጠብቁ ነበር፡፡
ደርጐቹም ገብተው ጃንሆይን እስከተገናኙ ድረስ የነበራቸው መረበሽ ከባድ ነበር፡፡ ከቢሮ ተጠርተው ሲገቡ እያንዳንዳቸው ሙሉ ትጥቅ ነበራቸው፡፡ ፊልም አንሺዎች፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች፣ የድምጽ መቅረጫ የያዙ ጋዜጠኞች፣ ሪፖርተሮችና የወታደር ጋዜጠኞች ጭምር አብረው ገብተዋል፡፡ ከጋዜጠኞች የማውቃቸው አቶ ማዕረጉ በዛብህ፣ አቶ ደበበ እሸቱ (የድምጽ መቅረጫ) የያዘ፣ አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ (የቴሌቪዥን ፊልም አንሺ) መብራት የሚያበራውን ስሙን አላውቀውም እንጂ ለዚሁ ሥራ ብዙ ጊዜ ይመጣል፡፡ ሻለቃውም አዋጁን አነበበ፡፡ በሚያነብበት ጊዜ ኡዚውን ከደረቱ ላይ አንግቶ ነው፡፡
አዋጁ ሲነበብ ግርማዊነታቸው በጽሞና በደንብ ሁነው ያዳምጡ ነበረ፡፡ ከዘወትሩ አሁንም ምንም ለውጥ አላሳዩም ነበር፡፡
አዋጁን አንብቦ ሲጨርስ፣ ግርማዊነታቸው የተገለለ ቦታ እንደተዘጋጀላቸው ስለሆነ ከልዕልት ተናኘ ጋር እንዲቀመጡ ስለተወሰነ አብረዋቸው እንዲሄዱ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ተዝናንተው ተቀመጡና “እኛ ለሀገራችን በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ሠርተንላታል፡፡ እናንተም ይህን ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ፣ ወታደሮቹ አንድ ጊዜ ግር ግር አሉና ጋዜጠኞቹን በሙሉ አስወጡዋቸው፡፡ ጋዜጠኞቹ ከወጡ በኋላ ንግግራቸውን በእርጋታ በመጀመር፣ “መጀመሪያ የጦር ኃይላችንን በዘመናዊ መልክ ስናዘጋጅ፣ ይህ አሁን የደረሰው የመሳሰሉ ነገሮች እንደሚደርሱ አስቀድመን የተገነዘብነው ስለሆነ ለኛ አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን የወታደር ተግባሩ ጠረፍን ከአጥቂ ጠላት መጠበቅ ሲሆን፤ አሁን እናንተ በከተማ ተቀምጣችሁ አላማችሁን በመርሳት የምታደርጉት ትክክል አይደለም፡፡
“ወታደር ለጠረፍ እንጂ መቼ ለከተማ” አሉዋቸውና አንዳንዶቹን እየጠሩ መጠየቅ ጀመሩ፡፡
አንዱን የአየር ኃይል ባልደረባ “ና” ብለው፤ “ዕድሜህ ስንት ነው? አገልግሎትህስ?” እያሉ ሲጠይቁ፣ እኛንም በዚያ አካባቢ የነበርነውን አባረሩን፡፡
ወደዚያው አድሚራል እስክንድር ከእህቶቻቸው ጋር ፎቅ ላይ ስለነበሩ አስጠሩኝና ወጣሁ፡፡ እርሳቸውም ጀ/ፍሬሰንበት ከአጠገባቸው በምንም ዓይነት እንዳይለይ ንገረው ብለውኝ እሺ አልኳቸውና ቆምኩ፡፡ ወደዚያው ወደ መኝታ ቤት ከወሰኔ ጋር ገብተን፣ በመስኮት ቁልቁል ስናይ አንዲት ቮልስዋገን መኪና ስትቀርብ አየንና ሊወስዱዋቸው ነው ብለን ሮጠን ስንወርድ፣ አድሚራል ተጠርተው ወርደው ጃንሆይም ሲወጡ ደረስን፡፡ ወደዚያው ጃንሆይ የሚረዳዎት አሽከር ስለሚያስፈልግ፣ እርስዎ ደስ የሚልዎትንና የሚረዳዎትን ይምረጡ ሲሉ፣ እርሳቸውም “ወሰኔ ይሁንልኝ” አሉና መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሲወጡም ዘወትር ለሽርሽር እንደሚወጡ ነበር፡፡
ወታደሮቹም ከግራና ቀኝ እንዲሁም ከኋላ አጅበዋቸው ነበር፡፡ ውጭ እንደወጡም የሹፌራቸው የጀ/ሉሉ ቮክስዋገን ቆማ ስለነበር፣ አጠገቧ ሲደርሱ ግራ ገባቸውና ቆሙ፡፡ ወደዚያው በሩ ሲከፈትላቸው ስለገባቸው ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ውሾቻቸው አብረው ገቡ፡፡ ጐትተው አስወጡዋቸው፡፡ ከእሸቱ ጋር ጭቅጭቅ ተፈጠረ፡፡ በመጨረሻ ውሾቹን ታቅፎ ወደ ውስጥ አስገባቸው፡፡ በማግስቱ ዶክተር ግርማ መጥቶ ወሰዳቸው፡፡ በፊትም የሚያክማቸውና ሲያማቸውም እርሱ ቤት ነበር የሚሄዱት፡፡ እርሳቸው በቮክስዋገንዋ ሲሄዱ፣ አድሚራልን ደግሞ በትልቁዋ ኩምቢ ቮክስዋገን (የፖሊስ ናት) አስገብተው ወሰዱዋቸው፡፡ እኛም ተመልሰን እኔና ወሰኔ ዕቃ መክተት ጀመርን፡፡ ለኛ የመሰለን፣ የወሰዱዋቸው ግርማዊት ቪላ/የልዕልት ቤት/ ወይም ልዑል መኰንን ቤት እንጂ 4ኛ ክፍለ ጦር አልመሰለንም፡፡ ምክንያቱም የወጡት በ2ኛ በር ስለነበረ ነው፡፡ እኛም የሚያስፈልገውን ልብስ አዘጋጀን፡፡ ብዙውንም አውጥተን ከተትን፡፡ በዚህ ጊዜ የተቀሩት ቁጭ ብለው ይተክዙ ነበረ፡፡ አንዳንድ የሴት አሽከሮች ለዚያውም ድሆቹ ከሚያለቅሱ በስተቀር ከሌሎቹ አንድም የሚያለቅስ አልነበረም፡፡
በዚያ አካባቢም የተገኙት የበሉት ሳይሆኑ ድሆቹ ነበሩ፡፡ የበሉትማ ገና ዱሮ ወጥተው ዙሪያውን ያንዣብባሉ፡፡ በ5፡30 ሌሎች የደርግ አባሎች መጡና በጀ/ወርቁ የክብር ዘበኛ ተጠባባቂ አዛዥ አማካኝነት ከመኝታ ቤት ገቡ፡፡ ወደዚያው ቤቱንና ዕቃውን እየተመለከቱ፣ ግማሾቹ “መታሸግ አለበት” ሲሉ፣ ግማሾቹ ደግሞ የተለየ ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ እኔና ወሰኔ ጀ/ወርቁን ዕቃ መክተት ያስፈልግ እንደሆነ ፈቃድ ጠየቅናቸው፡፡ እርሳቸውም “የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ቶሎ ቶሎ አውጡ” ብለው ፈቀዱልንና ጨርሰን አወጣንና ከተትን፡፡ እነርሱም ቤቱ በመታሸጉ ተስማሙና ታሸገ፡፡ ለጃንሆይ የሚያስፈልግ ዕቃ ሲኖር ከእኛ ዘንድ ሁለት ወይም ሦስት ሰው እየመጣ፣ ከአሽከሮቹ ጋር ከፍተው ዕቃው ከወጣ በኋላ እንደገና ይታሸጋል ብለው ተስማሙና አሸጉት፡፡
ከመኝታ ቤት የደርጉ አባሎች በገቡ ጊዜ አብዛኛዎቹ የሐዘን ስሜት ነበራቸው፡፡ በተለይም አንድ የጦር ሠራዊት ባሻ እንባው መጥቶ ግጥም ሲልበት፣ እንዳይታይ ዞር ብሎ እንባውን ሲጠርግ አይቻለሁ፡፡ የዕቃውንም መመሰቃቀል አይተው፣ “ይኸ ሳይነካ እንዳለ መሆን አለበት” በማለት ምንም ሳይነኩ ወጡ፡፡ ከዚያም ወደ ሳሎንና ገበታ ቤት ሄደው ዕቃውን እያዩ ሲያሽጉ፣ በ6፡45 ሌሎች የደርጉ አባሎች አቶ መንበረ ወልደማርያምን ይዘው መጡ፡፡ ከዚያም በፊት መጥተው ያሽጉ የነበሩትን የደርጉ አባሎች ጠርተው እሽጉን አስከፍተው ከመኝታ ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም ትልቁን የገንዘብ መያዣ ቦርሳ ከፍተው፣ ከውስጡ ያለውን ብርና ልዩ ልዩ ዶክሜንት ማየት ጀመሩ፡፡ ታዲያ የቦርሳው ቁልፍ ከጃንሆይ ቀለበት ሥር ነበርና ቀለበቱን አምጥተው ነው የከፈቱት፡፡ ከአንድ ፊት ያለው ግን በቁጥር የሚከፈት ስለሆነና ስለላላወቁት ግማሾቹ “ይቀደድ” ሲሉ፣ አንድ መኰንን ግን “ይህ መቀደድ አይገባውም፣ ለታሪክ መቀመጥ አለበት” ስላለ፣ በመፈልቀቅ በእጃቸው እየገቡ በጐን በኩል አወጡ፡፡ በ7፡10 ሰዓት ልብሱና ምግቡ ጃንሆይ ወደአሉበት ቦታ ሄደ፡፡ …ለዘመን መለወጫ በዓል የተዘጋጀው ግብር የቀረበው ለደርጉ አባሎች ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚያ ሲያማቱና ለዚህ ውድቀት ያበቁዋቸው፣ ሲዘርፉ የነበሩት አንደኛቸውም አልነበሩ፡፡ እዚያ ተኩራምተው ሲያለቅሱና ሲያዝኑ የነበሩት ምንም ያልተደረገላቸው ድሆቹ ብቻ ነበሩ፡፡ የጦር ሠራዊት ባልደረባ፣ ወታደር፣ ሹፌር፣ መጡ፡፡ ከዚያም እኔ ዘንድ መጥተው ምንም የሄደ “ዕቃ ስለሌለ ልንወስድ ነው የመጣነው፡፡ በተለይም የሚያርፉበት አልጋ ስለሌለ ቶሎ ቢሰጠን” ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔም “አቶ ጥላሁን እኮ ገና ከሰዓት በፊት ሄዶአል” ብለውኛል፤ ምናልባት አላስገባ ብለዋቸው እንደሆነ ብላቸው “የለም ውሸት ነው!” አለኝ፡፡
በተለይም የ10 አለቃው በጣም በማዘን “እስከ አሁን እኮ ከአንዲት ትንሽ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ነው ያሉት፤ ምነው እንደው የሚያስብ ሰውም የለ እንዴ?” አለኝ፡፡ እኔም ወደዚያው ወደ ዕቃ ክፍሉ ያሉትንና የሚያሽጉትን የደርጉ አባሎች ሄጄ ባነጋግራቸው፤ “ለምን እስከአሁን አልሄደላቸውም?” ቢሉኝ ሰው ቸልተኛ ስለሆነ ከእናንተ ዘንድ የሚያስገድድ ይሰጠኝ፡፡ በተለይም የዚህን ሥራ/ፕሮሲጀር/ የሚያውቀው ሻለቃ ሳህሌ ስለሆነ ከአለበት ቦታ ተፈልጐ እንዲወሰድ ብዬ ለአንድ የክብር ዘበኛ ሻለቃ ስነግራቸው፣ እርሳቸውም አንድ መቶ አለቃ ከላይ ግቢ ወጥቶ ለወታደሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥና ዕቃ የሚወስዱ ሰዎች እንዳይቸገሩና በተለይም የሚስቸግሩ ሰዎች እንዳሉ እንዲያስገድዱ ብለው ሰጡኝ፡፡
ግርማዊነታቸው 4ኛ ክፍለ ጦር እንደደረሱ ኪሳቸው ተፈትሾ ብዕር፣ ክራቫት፣ ብራስሌት፣ ቀበቶ… ቀለበታቸውን፣ የአንገት ሐብላቸውን አውልቀው ወሰዱባቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የማስታወሻ ደብተራቸውን ጭምር ወሰዱባቸው፡፡
በማስታወሻቸው ላይ ከመያዛቸው ሦስት ቀን በፊት ለአቶ መንበረ 10ሺ ብር ሰጥተው ኖሮ፣ ያን የሰጡትን ገንዘብ በማስታወሻቸው ላይ ጽፈውት ስለተገኘ፣ አቶ መንበረን ከታሰሩበት ቦታ ሄደው ገንዘቡን ለምን እንደወሰዱ ጠይቀው፣ “ለልጆቼ ማሳደጊያ ነው” ሲሉ፤ “አምጡ” ተብለው ያንን 10ሺ ብር መልሰው ለደርጉ አስረከቡ፡፡ ጃንሆይ የገቡባት ክፍል አራት በሦስት ስፋት ያላት ክፍል ስትሆን በውስጧም የነበሩት ሁለት ጥቋቁር የቆዳ ወንበሮች ብቻ ነበሩ፡፡ ክፍሉንና ወንበሮቹን ራሴ አይቻለሁ፡፡ ያን ጊዜ ጊዜ የነበሩት ከበረንዳ ላይ ነበር፡፡ የልዕልት ተናኘወርቅም ቦርሳ እንደዚሁ ተይዞ ከውጭ ቀርቶአል፡፡ በ12 ሰዓት አልጋና ምንጣፍ ስለሄደ ሊነጠፍላቸው ሲል፤ “ምንም አልፈልግም” ብለው ምንጣፉን አስወጥተው ጣሉት፡፡ አልጋው ደግሞ ሁለት ፍራሽ ስለነበረው፣ የላይኛውን ፍራሽ አንሱ ብለው አስነስተው እታችኛው ላይ ተኙ፡፡ ብርድ ልብሳቸውም አንድ ብቻ እንዲሆን አድርገው ከዚያው አደሩ…
=====
“…እኛ እኮ እጃችንን የሰጠነው አውቀን ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንደሚመጣ አስቀድመን የተረዳነው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በሰላም እጃችንን የሰጠነው የህዝቡ ደም እንደራሺያና ፈረንሳይ ሪቮሉሲዮን በከንቱ እንዳይፈስ በማሰብና መከራችንን እኛው እንቀበል በማለት ነው፡፡ የሩሲያንም ሆነ የፈረንሣይን ሪቮሉሲዮን ደህና አድርገን ስለምናውቅ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የወታደሩ እንቅስቃሴ ሶሺያሊስት እንደሚሆን አስቀድመን ተገንዝበነዋል፡፡ ስለዚህ ከላይ ባሉት አገሮች የደረሰው እልቂት በእኛም አገር እንዳይደርስ በማሰብ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ ሲጀመር ይህ በቀጥታ እንደሚመጣ እናውቀው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያመጣው ስለሆነ መታገል አይቻልም፡፡ የወደፊቱንስ ማን ያውቃል፡፡ ሁሉ በእርሱ እጅ አይደል?”…

የራሺያው መሪ ስታሊን ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ አደረገ አሉ፡፡
ሰዉን ስብሰባ ጠርቷል፡፡
ተሰብሳቢው ፀጥ ብሎ ያዳምጣል፡፡
ከተሰብሳቢው መካከል ድንገት አንድ ሰው አስነጠሰው፡፡
ስታሊን ንግግር ከሚያደርግበት ምስማክ ቀና ብሎ፤ በቁጣ፣ ኮስተር ባለው ድምፁ፡-
“ማነው አሁን ያስነጠሰው?” አለና ጠየቀ፡፡ ማንም አልመለሰም፡፡ ሁሉም ጭጭ አለ፡፡ ሰው ሁሉ አቀርቅሯል፡፡ በየሆዱ “ማንን ፈልጎ ይሆን?” ማን ይሆን የፈረደበት? እኔን ይሆን? እሷን ይሆን” ይላል፡፡ ያስነጠሰውም ሰው ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ስለሆነ “እኔ ነኝ ብል ምን እሆናለሁ?” ብሎ መልስ አልሰጠም፡፡ ስታሊን ሆዬ አንጋቹን ጠራና፤
“እሺ ከኋለኛው መስመር ሁለቱን ተርታ ሰው አስወጣና ግደልልኝ!” አለና አዘዘ፡፡
አንጋቹም እንደታዘዘው ሁለቱን ተርታ ሰው እያንጋጋ ወስዶ ረሸነና ተመለሰ፡፡
ስታሊን ቀጥሎ፤ “እሺ ማነው ያስነጠሰው? አሁንም ተናገሩ!” አለ፡፡
አሁንም ዝም ዝም ሆነ፡፡ መናገር ቀርቶ ቀና ብሎ የሚያይ ሰው ጠፋ፡፡ አሁንም ወደ አንጋቹ ዞሮ፤
“ከኋለኛው መስመር ሁለቱን ተርታ ሰው አስወጣና ረሽንልኝ!” አለ፡፡
አንጋች ሁለት ተርታ ሰው አስወጣ፡፡
የጥይት እሩምታ ድምፅ ተሰማ፡፡ አለቁ ማለት ነው፡፡
ስታሊን እንደገና፤ “ማነው ያስነጠሰው? ተናገሩ!!” አለ እያንባረቀ፡፡
አሁን የቀረው ሁለት ተርታ ሰው ነው፡፡
ይሄኔ፤ አንድ መነፅር ያደረጉ አዛውንት እጃቸውን አነሱ፡፡
“እሺ ምን ይላሉ?” አላቸው ስታሊን፡፡ አዛውንቱም፤ በኮሰሰ ድምፅ “እኔ ነኝ ጓድ!” አሉ፡፡ “ይማርዎት!” አላቸው፡፡
አዛውንቱም፤ “ያኑርህ!” አሉ፡፡
* * *
ከስታሊን በትር ይሰውረን!
መሪና ተመሪ፣ አለቃና ምንዝር፣ ኃላፊና የሥራ ሂደት ኃላፊ ወዘተ. የሚፈራሩበት ሥርዓት ዲሞክራሲያዊነት ይጎድለዋል፡፡ የበላይን ከልኩ በላይ የመፍራት ልማድ፣ የበታቹን ማርበትበት፣ ቅጥና፣ አቅል-ማሳጣቱ፤ አልፎ ተርፎም ውሉን ስቶ፣ ቦታውን ስቶ ወደሌላ፣የሱ ወዳልሆነ ቦታ ወይም አገር፤ እስከመሰደድ ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ኢፍትሐዊ ወይም የፈሪና የተፈሪ፣ ዘልቆም የጌታና - የሎሌን ዓይነት ግንኙነት፣ ከቶም ከዐይነ-ውሃው ስናየው ጤናማ አለመሆኑን ለማየት ብዙ ፀጉር ማከክን አይፈልግም፡፡ የባሰ ሥጋት የሚሆነው ነገር፣ የተገዢው ፈሪ መሆን ገዢው ላይ የሚፈጥረው የተዓብዮ ስሜትም ነው፡፡ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሚፈቅደው ለከት በላይ “ለካ እንዲህ ይፈሩኛል” የሚል የማስፈራራት፣ የመቆጣት፣ የማርበድበድ… እርካታ፤ ሆዱ ውስጥ ያድራል፡፡ ከእንዲህ ያለው ጉልላት ወርዶ ትህትናን ተላብሶ፣ ህዝባዊ የሆነ ተዋህዶ መፍጠርና ሰው መሆንን መገንዘብ፣ ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ ኢወገናዊ፤ ኢክፋታዊ፣ ኢአምባገነናዊ አሰራርን የመቀበልን ግለ-ሰባዊና ቡድናዊ፣ አልፎ-ተርፎም ጀማዊ ሥነ-ምግባርና ሙያዊ ብቃትን፣ እንዲሁም፤ የተጠያቂነትን መርህ የመቀበልንና ቅን ሥነ-ልቦናን የመዋሐድን ሥነ-ሥርዓት ይሻል፡፡
በዚህ አዲስ ዓመት፤ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ችግሮችን፣ በተደጋጋሚ አውስተን፣ በተደጋጋሚ እንፈታቸዋለን ብለን ፎክረን፣ በተደጋጋሚ እዚያው እተነሳንበት ሥፍራ (Back to square – one እንዲሉ) የተመለስንባቸውን ጉዳዮች የምናስተውልበት፤ ያንን በማጤን፣ በመመርመርና ዘላቂ ዘዴ በመፍጠር፣ ጥበቡን የምንቀዳጅበት ያድርግልን!
መጪው ዘመን፤
ነገን የማንፈራበት፣ በልበ-ሙሉነት የምንጓዝበት፣ በዕውቀት እንጂ በጉልበት የማንራመድበት፣ አፈጮሌ፤ ሚዲያ አገኘሁ ብሎ ‹ያለእኔ ማን አለ?›፣ የማይልበት፣ አድር-ባይ ቀን ሞላልኝ ብሎ መቀመጫውን ለማደላደል በፍየል መሳይ ምላሱ የባጥ -የቆጡን የማይቀባጥርበት፣ “ሰው ባንበደቱ ውሻ በምላሱ” ይኖራል የማይባልበት ዘመን፤ ያድርግልን!
በሀገር ጉዳይ ንቅንቅ የማንልባቸው እንደኢትዮጵያዊነት፣ ሉዓላዊነት፣ የሀገር ህልውና፣ የዜግነት ክብር፣ ሥረ-መሰረታዊ ማንነት ወዘተ. ዛሬም የማይነኩ፣ የማይደፈሩና የማይገሰሱ ይሆኑ ዘንድ፤ ይሄ ዘመን ዐይናችንን ይክፈትልን!
ዛሬም ሙስናን የምንዋጋበት፣ ዛሬም ወገናዊነትን ሽንጣችንን ገትረን የምንፋለምበት ዘመን ያድርግልን! በየተቋሙ፣ በየቡድኑ፣ በየቢሮው “ሰው -አለኝ” የምንልበትን አሰራር ይህ ዘመን ያስወግድልን!
እንደታሪክ ስላቅ ሆኖ፤
“የአሜሪካ የሀገር ደህንነት አማካሪ ለእስራኤል የፍትህ ሚኒስትር የ“AIPAC” (የአሜሪካና የእስራኤል ህዝብ ጉዳይ ኮሚቴ) ውስጥ ያለ የሚረዳኝ ሰው ታውቃለህ ወይ?” ብለው ጠየቁ አሉ፡፡ ዋናው እንጀራ ጋጋሪ አሜሪካ ሆና ሳለ የውስጥ ሰው ከእስራኤል ፈለገች ማለት ነው፡፡ የሙስና ጥልቀቱ ኃያላኑም ውስጥ አለ፡፡ ሥር - ከሰደደ መመለሻ የለውም! ሆኖም ትግሉ ጥንቃቄና ትግስት ይጠይቃል፡፡ የሀገራችን ጣጣ አላልቅ ያለው ሁሉን ባንድ ቀን ፈተን፣ ሁሉን ባንድ ጀንበር አሸንፈን፣ ለዘመናት ያጠራቀምነውን ሕመም ባንድ ሌሊት ካልፈወስን ብለን፤ ዘራፍ በማለታችን ነው፡፡ “ዐባይን በአንድ ጊዜ ከመነሻውም ከመድረሻውም መጨለፍ አይቻልም”፤ ይለናል “ራስ ኤላስ መስፍነ - ኢትዮጵያ”፡፡ ሁሉን ችግር ባንድ ቅፅበት እንፈታለን ካልን አንዱንም ሳንጨብጥ እንቀራለን ነው ነገሩ፡፡ ማንም ቢሆን ማን፤ በብልህነት፣ በጥንቃቄና ደረጃ በደረጃ እንጂ በሁሉም ነገር ላይ ባንድ ጊዜ አብዮት ማፈንዳት አይችልም፡፡ በጥድፊያ የተካሄዱ፣ ሆይ ሆይ ተብለው ሥር-ሳይሰዱ መክነው የቀሩ አያሌ ጅምሮች እናውቃለንና ልብ እንበል፡፡ “ከላሟ፤ በአንድ ጊዜ ሥጋዋንም፣ ወተቷንም፣ ጥጃዋንም ማግኘት አይቻልም” የሚባለው ለዚህ ነው፡

 

ኢትዮጵያም ተጠቅሳለች

          ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው አገራት በተጨማሪ ሌሎች 15 የአፍሪካ አገራት ከእንስሳት ወደ ሰዎች ለሚተላለፍ የኢቦላ ቫይረስ የመጋለጥ እድል እንዳላቸው ሰሞኑን ባወጣው የጥናት ውጤት ማረጋገጡን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለበሽታው የመጋለጥ እድል አላቸው ብሎ የጠቀሳቸው የአፍሪካ አገራት:- ናይጀሪያ፣ ካሜሩን፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ጋና፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ አንጎላ፣ ቶጎ፣ ታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ብሩንዲ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ማዳጋስካር እና ማላዊ ናቸው፡፡ በሽታው መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ አገራት 51 የተለያዩ አካባቢዎች በኢቦላ ቫይረስ የተጠቁ እንስሳት መገኘታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከእንስሳቱ መካከልም ዝንጀሮዎችና ፍራፍሬ ተመጋቢ የሌሊት ወፎች እንደሚገኙበትና እነዚህ እንስሳት ቫይረሱን ወደ አገራቱ ያስፋፉታል ተብሎ እንደሚገመት አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአፍሪካ ህብረት ባለፈው ሰኞ በአዲስ አበባ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአህጉሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የተከሰተውን የኢቦላ በሽታ ለመግታትና ወደሌሎች አገራት እንዳይዛመት ለማድረግ፣ የተቀናጀ አህጉራዊ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል፡፡በሽታው በተከሰተባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት እየደረሰ ካለው ከፍተኛ ሰብዓዊና ማህበራዊ ጥፋት በተጨማሪ በአገራቱ ኢኮኖሚ ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱ በስብሰባው ላይ የተገለጸ ሲሆን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽንም በበሽታው ሳቢያ በጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ላይ ከፍተኛ መቀነስ ሊፈጠር እንደሚችል ግምቱን ሰንዝሯል፡፡

           ቱርክ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ ቀዳሚነቱን ይዛ የቆየችውን ቻይናን በመብለጥ መሪነቱን መረከቧን የኢንቨስትመንት ኤጀንሲን መረጃ በመጥቀስ ወርልድ ቡሊቲን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
በኢትጵዮያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ቀድመው የተሰማሩት የቻይና ባለሃብቶች እንደሆኑ ያስታወሰው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን ዘግይተው ወደ ኢንቨስትመንቱ የገቡት የቱርክ ባለሃብቶች፣ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በመዘርጋት፣ በአገሪቱ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ረገድ በቻይናውያኑ ተይዞ የቆየውን መሪነት ለመረከብ መቻላቸውን ጠቁሟል፡፡
የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ቀዳሚነቱን እንደያዙ የጠቆመው ዘገባው፤ ቻይናውያን ባለሃብቶችም ባለፉት አስር አመታት በአገሪቱ 836 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ኢንቨስትመንት መዘርጋታቸውን አስረድቷል፡፡
በተለይ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት እየሰሩ የሚገኙት የቱርክ ባለሃብቶች በትላልቅ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ሲሰማሩ፣ ቻይናውያኑ በበኩላቸው፤ በአብዛኛው በአነስተኛና በብዙ አትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡
ቱርክ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ረገድ መሪነቱን ብትይዝም፣ የስራ ዕድል በመፍጠር ቻይና ቀዳሚነቷን ይዛ እንደቀጠለች ጠቅሶ ዘገባው አስታውቋል፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ በተሰማራችባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ከ75 ሺ 500 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል ስትፈጥር፣ ቱርክ በበኩሏ 20 ሺህ 900 ያህል የስራ ዕድል መፍጠሯን የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ ብዙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በማከናወንም ቻይና ቀዳሚነቱን እንደያዘች ገልጿል፡፡
ቻይና 437 ፕሮጀክቶች ሲኖሯት፣ ቱርክ 100 ፕሮጀክቶችን በማንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡

የአለማቀፉ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴሎች አካል ነው

በሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፍ በአለማቀፍ ደረጃ በስፋት በመንቀሳቀስ ከሚታወቁ ታላላቅ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የእንግሊዙ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ግሩፕ፣ በአፍሪካ ከከፈታቸው ሆቴሎቹ 30ኛው እንደሚሆን የሚጠበቀውን ክራውን ፕላዛ የተሰኘ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በአዲስ አበባ እንደሚከፍት ቬንቸርስ አፍሪካ ዘገበ፡፡
የሆቴሉ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ረዘነ አያሌው በበኩላቸው፣ የሆቴሉ ግንባታ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አለማቀፍ ደረጃን የጠበቀው ይህ ዘመናዊ ሆቴል፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎችን፣ ዘመናዊ ሬስቶራንቶችን፣ መዋኛ ገንዳና ሰባት ግዙፍ የስብሰባ አዳራሾችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ግሩፕ የህንድ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓስካል ጎቪን እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው ይህ ሆቴሉ በከተማዋ የሚደረገውን በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ ያለውን የቱሪስቶችና የውጭ አገራት ዜጎች ፍሰት ታላሚ ያደረገ ነው፡፡
የሆቴሉ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ረዘነ አያሌው ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ ልደታ ኢትፍሩት አካባቢ የሚከፈተው ክራውን ፕላዛ ሆቴል ግንባታ ተጠናቆ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ግንባታው በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የሆቴሉ አጠቃላይ ወጪ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚታወቅ ነው ያሉት አቶ ረዘነ፣ እስካሁን ድረስ የዓለም ባንክ ለግንባታው 19 ሚሊዮን ዶላር ማበደሩን ገልፀዋል፡፡ ሆቴሉ ተጠናቅቆ ስራ ሲጀምር፣ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል እንደሚከፍትና እያደገ ለመጣው የአገሪቱ የቱሪስት ፍሰትና ለአለማቀፍ ጉባኤዎች የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡አለማቀፉ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ግሩፕ፣ ሆቴሎቹን ክራውን ፕላዛ፣ ሆሊዴይ ኢን፣ ሆሊዴይ ኢን ኤክስፕረስ፣ ኢንተርኮንቲኔንታልና ስቴይብሪጅ ስዊትስ በተሰኙ አምስት ታዋቂ መጠሪያዎች በተለያዩ የአለም አገራት በመክፈት የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ12 የአፍሪካ አገራት 29 ሆቴሎች አሉት፡፡

 

በጆን ማክስዌል “The success Journey” በሚል ርዕስ የተፃፈውና በኢ/ር ኢዮብ ብርሃኑ “የስኬት ጉዞ” ተብሎ ወደ አማርኛ የተመለሰው መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡
 ስለስኬት መንገዶች መድረሻ፣ ስለ ትክክለኛ የስኬት ምስል፣ ስለ ሀብት፣ ስለስኬትና ስለተሳሳተ ልማዳዊ የስኬት አስተሳሰብ የሚተነትነው  መፅሀፉ፤ በ10 ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በ152 ገፆች ተቀንብቦ በ42 ብር ከ60 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡  

የሽልማት ስነ-ስርዓቱ መስከረም 24 ይካሄዳል

            በሸገር ኤፍኤም 102.1 የሚተላለፈው የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ የሆኑ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ተለይተው መታወቃቸውን አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ ለሁለት ወራት ያህል በwww.shegerFM.com እና yahoonoo.com ላይ አድማጮች ለአርቲስቶች ድምፅ ሲሰጡ መቆየታቸውን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ 60 በመቶ በአድማጮች፣ 40 በመቶው በባለሙያዎች በሚሰጥ ውጤት አሸናፊዎች ታውቀዋል ብለዋል፡፡
በ “ምርጥ ወንድ ተዋናይ” ዘርፍ ግሩም ኤርሚያስ በ “ጭስ ተደብቄ” ፊልም፣ ይስሃቅ ዘለቀ በ “ቀሚስ የለበስኩ’ለት”፣ መሳይ ተፈራ በ“ትመጣለህ ብዬ”፣ ሚካኤል ሚሊዮን በ“አይራቅ”፣ ታሪኩ ብርሃኑ በ“ህይወትና ሳቅ” እና ሰለሞን ቦጋለ በ“ሶስት ማዕዘን” ፊልሞች የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሆነዋል፡፡
በ “ምርጥ ሴት ተዋናይ” ዘርፍ፣ ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ በ“ቀሚስ የለበስኩ’ለት”፣ ሰላማዊት ተስፋዬ በ “በጭስ ተደብቄ”፣ ማህደር አሰፋ በ“አይራቅ”፣ ሩታ መንግስተአብ በ“ረቡኒ”፣ ማህደር አሰፋ በ“ህይወትና ሳቅ” እንዲሁም ማህደር አሰፋ በ “ዘውድና ጎፈር” የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሊሆኑ ችለዋል፡፡
ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ የአድማጮች ምርጫ ላይ አምስት ፊልሞች በአድማጮች የተሻለ ነጥብ ያገኙ ሲሆን ፊልሞቹም “በጭስ ተደብቄ”፣ “ትመጣለህ ብዬ”፣ “ህይወትና ሳቅ”፣ “ቀሚስ የለበስሉ’ለት”፣ “አይራቅ” እና “ረቡኒ” መሆናቸው ታውቋል፡፡ በምርጫው ላይ ምርጥ አልበሞች የተካተቱ ሲሆን የብዙአየሁ ደምሴ “ሳላይሽ”፣ የስለሺ ደምሴ “ያምራል ሀገሬ”፣ የአስቴር አወቀ “እወድሃለሁ”፣ የሚካኤል ለማ “ደስ ብላኛለች”፣ የአብርሃም ገ/መድህን “ማቻ ይሰማኒሎ” እና የተመስገን ገ/እግዚአብሔር “ኮራሁብሽ” ተመርጠዋል፡፡ በምርጥ ነጠላ ዜማም የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ ደግሞ መካከል የጃኪ ጎሲ “ፊያሜታ፣ አስቴር አወቀ የተሳፈችበትና በ“የኛ” የተሰራው “ጣይቱ”፣ የበሃይሉ አጎናፍር “አዩ እሹሩሩ”፣ የናቲ ማን “ጭፈራዬ” እና የተመስገን ገ/እግኢዘብሔር “ኮራሁብሽ” በመራጮች ልቀው መገኘታቸውን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ የግርማ ተፈራ “መቼ ትመጫለሽ”፣ የበሃይሉ አጎናፍር “አዩ እሹሩሩ”፣ የጃኪ ጎሲ “ፊያሜታ”፣ የዘሪቱ ከበደ “የወንድ ቆንጆ”፣ የአቤል ሙሉጌታ “ልብ አርማ አመት” እና የ “እኛ” እና የአስቴር አወቀ ስራ “ጣይቱ” በአድማጮች ከፍተኛ ነጥብ አግኝተዋል ተብሏል፡፡ በሽልማት ዘርፍ ውስጥ አዳዲስ ድምፃዊያን በእጩነት የቀረቡ ሲሆን ሚካኤል ለማ፣ ተመስገን ገ/እግዚአብሔር፣ እመቤት ነጋሲ፣ አዩ አሳዬኝ አለሙና ዳንኤል ፍስሃዬ የመጨረሻ እጩ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የድምፅ መስጠት ሂደቱ በቀረቡት የመጨረሻ ዙር እጩዎች ላይ ለቀጣዩ 30 ቀናት ከተካሄደ በኋላ አሸናፊዎች መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም በጣሊያን ካልቸራል ኢንስቲትዩት በሚካሄድ የቀይ ምንጣፍ የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ይሸለማሉ ተብሏል፡፡
 በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የፒያኖ ባለሙያው ግርማ ይፍራሸዋን ጨምሮ በርካታ ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን በማቅረብ የሽልማት ስነ-ስርዓቱን ያደምቃሉ ተብሏል፡፡          

የኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት “From Chopin to Ethiopia and Part way Back Again (“ከቾፐን እስከ ኢትዮጵያ እና ደርሶ መልስ”) በሚል ባስነበበው የሙዚቃ ቅኝት ስቲቭ ስሚዝ ስለግርማ ይፍራሸዋ ያሰፈረው በከፊል ይሄን ይመስላል፡-
 “…በተነፃፃሪ ሲታይ፤ ስለክላሲካል ሙዚቃ በአፍሪካ፤ የሚያመላክቱ ጥቂት ማረጋገጫዎች ብቻ ይኑሩ እንጂ የምዕራቡ ክላሲካል ባህል በሌላው ዓለም ማለትም ከቬኔዝዌላ እስከ ቻይና እንደተንሰራፋው ሁሉ የአፍሪካንም ዙሪያ መለስ ማዳረሱ ገሀድ ነው፡፡ ለዚህ አስረጅ የሚሆነን የ45 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ፒያኒስትና ቀማሪ ግርማ ይፍራሸዋ በብሩክሉን “ኢሹ ፕሮጀክት ሩም” ቅዳሜ ምሽት ያቀረበው ምርጥ የፒያኖ ሥራ፤ እጅግ ብርቅ፣ ሥነ ውበታዊና ተምሳሌታዊ የክላሲካል ሙዚቃ መናኸሪያ መሆኑን የሚያሳይ ነው!
…. ግርማ “የኢትዮጵያዊያን በገና” ሊባል በሚችለው በክራር ነው የሙዚቃ ልጅነቱን የጀመረው፡፡ አዲስ አበባ ሙዚቃ ት/ቤት ሲገባ ከፒያኖ ጋር ተገናኘ፡፡ ከዚያ ነው በነቃ አዕምሮው በቡልጋሪያ የሶፊያ ስቴት ኮንሰርቫቶሪ መደበኛ ትምህርቱን ገፍቶ የተካነው…
“… ወደ ኢትዮጵያ በ1995 እ.ኤ.አ ከተመለሰ በኋላ ግርማ ደረጃውን የጠበቀ ክላሲካል ትርዒት ምን እንደሚመስል ደርዝ ያለው ግንዛቤ ማስጨበጥን ሥራዬ ብሎ ከመያያዙ ሌላ፤ አዳዲስ የሙዚቃ ስራዎችን ፅፏል፡፡ ለነዚህ አዳዲስ የጥበብ ስራዎች መቀመሪያ ይሆነው ዘንድ የአውሮፓን የጥበብ መላ ከኢትዮጵያ ሙዚቃና ሥነ-ትውፊታዊ ዕሴት ጋር በማጋባት ተጠቅሟል፡፡....››


ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበው አዲሱ አልበሙ በአሜሪካ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ 23ኛ ደረጃ አግኝቷል ታዋቂው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ በቅርቡ በአሜሪካ ያስመረቀው “Love and peace” የተሰኘ አዲስ አልበሙ፤ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ 23ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠለት ይናገራል፡፡ በአሜሪካ ያቀረበው ኮንሰርት እንደተወደደለት የገለፀው ፒያኒስቱ፤ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በአድናቆት የተሞላ ጽሑፍ እንዳወጣለት ጠቁሟል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት ዕቁባይ ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር ያደረገችው ቃለምልልስ እንዲህ ቀርቧል፡፡ ወደ ሙዚቃ እንዴት እንደገባ በመናገር ይጀምራል፡-  


ሙዚቃ የጀመርኩት በልጅነቴ ክራር በመጫወት ነው፡፡ ክራር ስጫወት ነው ያደግሁት፡፡ ፡፡ሙዚቃን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት ደግሞ  ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በመግባት፤ ከባህል ክራር፣ ከዘመናዊ ደግሞ ፒያኖን ለአራት አመት ተማርኩ፡፡ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ፣  በ1980 ስኮላርሺፕ አግኝቼ ወደ ቡልጋሪያ  አቀናሁ፡፡
እዚያ ከሄድክ በኋላ ግን ችግር ገጠመህ…
ፒያኖ ለመማር አልሜ ቡልጋሪያ በሚገኝ የሙዚቃ አካዳሚ ለሁለት አመት ከተማርኩ በኋላ በወቅቱ  በተፈጠረው የሶሻሊስት ካምፕ መፍረክረክና መፍረስ   ሳቢያ  የእኔና  በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የነበሩ ሌሎች ተማሪዎቸ እጣ ፈንታ ስደት ሆነ፡፡ ሁሉም በየፊናው ሲበተን እኔ  ጣሊያን ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ገባሁ፡፡ ለስድስት ወራት ያህል  “ክርስቲያን ብራዘርስ” የተባሉ በጎ አድራጊዎች እየረዱኝ በካምፑ ተቀመጥኩ፡፡ ካምፑ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አገር ስደተኞች በሞሉት ፎርም ላይ አሜሪካ ወይም ካናዳ መሄድ እንደሚፈልጉ ሲያሰፍሩ፣ እኔ  ግን ትምህርቴ  ለምን እንደተቋረጠ በመግለፅ የፒያኖ ትምህርቴን ቡልጋሪያ ሄጄ መቀጠል እንደምፈልግ ገለፅኩ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱም የኔን ጥያቄ ከሌሎች በመለየት ነገሮች ሲረጋጉ የትምህርት ክፍያውን እየከፈሉ ትምህርቴን እንድጨርስ ቡልጋሪያ  መልሰው ላኩኝ፡፡ በአጠቃላይ ሰባት አመት የፈጀውን የፒያኖ ትምህርቴን አጠናቅቄ ማስተርሴን ካገኘሁ በኋላ ተመልሼ ጣሊያን ሄድኩ፡፡
ትምህርቴን እንድጨርስ የረዳኝ ድርጅት አሮጌ ፒያኖ ቢሰጠኝ እያልኩ እመኝ ነበር፡፡ ጣሊያን አገር በቆየሁበት ጊዜ ኮንሰርት ሰርቼ ስለነበር እሱን ተከትሎ ድርጅቱ አዲስ ፒያኖ በሽልማት ሰጠኝ፡፡ አሮጌ ቢሰጡኝ እያልኩ ስመኝ ፋብሪካ ድረስ ሄጄ መርጬ ባለፒያኖ ሆንኩ፡፡ ያ ለኔ ትልቅ ደስታ ነበር የፈጠረልኝ፡፡
ፒያኖዋ ግን ሌላ ስጋት ይዛ መጣች…
አዎ ፒያኖዋ በአውሮፕላን ከኔ ቀደም ብላ ነበር አዲስ አበባ የገባችው፡፡ እኔ ከመጣሁ በኋላ ፒያኖዋን ለመውሰድ ስጠይቅ፣ የቅንጦት እቃ ስለሆነ ታክስ መክፈል አለብህ በሚል ሁለት ወር ተያዘች፡፡ ሁለት ወር ሙሉ በየቀኑ አየር መንገድ እመላለስ ነበር፤ ምክንያቱም ፒያኖዋ የተቀመጠችው ደጅ ላይ ስለሆነ ፀሀይና ዝናብ እንዳያበላሻት በየቀኑ እየሄድኩ የምትሸፈንበትን ላስቲክ አስተካክላለሁ፣ እቀይራለሁ፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዲንከባከቡልኝም አደራ እላለሁ፡፡ በመጨረሻ የጣሊያንና የቫቲካን ኤምባሲዎች ጣልቃ ገብተው በስጦታ እንደተሰጠኝ ለኢትዮጵያ መንግስት በደብዳቤ አሳውቀውልኝ እጄ ገባች፡፡ ፒያኖዋን ስረከብ ገልጬ ሳያት ከወገቧ በታች ዝናብ ገብቶባታል፡፡ በጣም አዘንኩና አለቀስኩ፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ለምን እንደማለቅስ ግራ ገባቸው፤ አንዳንዶች ደግሞ ለእንጨት ያለቅሳል እንዴ ብለውኛል፡፡ በነገርሽ ላይ ይህ ታሪክ የእንግሊዝ መንግስትና አዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ፣ ለኢትዮጵያ ሚሊኒዬም  በጋራ ባወጡት ትልቅ መፅሀፍ ውስጥ ከተካተቱ ታሪኮች አንዱ ነው፡፡
ክላሲካል ሙዚቃ ምን አይነት ሙዚቃ ነው? እኛ አገር በመሳሪያ ብቻ ከተቀነባበረ ሙዚቃ ጋር የመቀላቀል ነገር ይስተዋላል…
የክላሲካል ሙዚቃ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ የሙዚቃ ስልት ሲሆን በረጅም ጊዜ የትምህርት ሂደት የሚገኝ የሙዚቃ ክህሎት ነው፡፡ ክላሲካል ሙዚቃን በልምድ መጫወት አይቻልም፡፡ የክላሲካል ሙዚቃ ተብሎ ሲነሳ  እነ ሞዛርት፣ ሀይደን፣ ቤትሆቨን የመሳሰሉት የሰሯቸው ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡
እኛ አገር ያለው የክላሲካል ሙዚቃ ተቀባይነት ምን ይመስላል?
አድማጭ አለው፤ አቅርቦት ግን የለም፡፡ ፒያኖ ማግኘት እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህ የሙዚቃ ዘርፍ መውጣት የሚፈልጉ ብዙ ልጆች አሉ፤ ግን የክትትል ችግር አለ፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ የረጅም ጊዜ ስልጠና ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች አሉ፡፡ እነሱን የሚፈልጉበት ለማድረስ ግን ብዙ ክትትል እና ድጋፍ ይፈልጋል፡፡
ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ማስተማሩን ለምን ተውከው?
እንዳልኩሽ ማስተማሩ በጣም ጊዜ ይጠይቃል፡፡ እኔ ደግሞ አጫጭር ኮርሶችን ስከታተልና ኮንሰርቶች ማሳየት ስጀምር፣ ቁጭ ብሎ የማስተማሩን ስራ እንዳያስተጓጉል በማለት ነው የተውኩት፡፡
 ቡልጋሪያ አስተማሪህ የነበሩትን ፕሮፌሰር አንተ በምታስተምርበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኮንሰርት እንዲያሳዩ አድርገህ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ንገረኝ…
ለእኔ እዚህ መድረስ የቡልጋሪያ አስተማሪዬ ፕሮፌሰር ኢታናስ ኮርቴሽ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እንደመምህሬ ሳይሆን እንደ ወላጄ ነው የማየው፡፡ እሱን ኢትዮጵያ አምጥቶ ኮንሰርት እንዲያሳይ ማድረግ ደግሞ የረጅም ጊዜ ህልሜ ነበር፡፡ በ2011 የሀንጋሪያዊው አቀናባሪ የፍራንስ ሊስታ 200ኛ አመት በአለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ይከበር ስለነበር፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ፣ እዚህ አገር ያሉትን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አግባብቼ ፕሮፌሰሩ አዲስ አበባ መጥቶ ኮንሰርት እንዲያቀርብ ጠየቅሁና ተሳካ፡፡ ኮንሰርቱም ተሰራ፡
አንተም ባለፈው ጥር ቡልጋሪያ በተማርክበት አካዳሚ ኮንሰርት አቅርበሃል…
አዎ፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በቫዮሊን፣ በቼሎ እና በሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች አዲስ ስራ ሰርቻለሁ፡፡ ቡልጋሪያ የሄደኩት እሱን ለማስቀረፅ ነበር፡፡ የተማርኩበት አካዳሚ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተቀረፀ፡፡ ከዚያ እዚህ ያደረሰችኝን ቡልጋሪያን ኮንሰርት ሰርቼ ላመስግናት አልኳቸው፡፡ በጣም ደስ አላቸውና ኮንሰርቱን ሰራሁ፡፡ እነሱ የኔን የሙዚቃ እድገት እያንዳንዷን ደረጃ ይከታተሉ ነበር፡፡ ከኮንሰርቱ በኋላ “ቡልጋሪያን በተለያዩ የአለም መድረኮች እያስጠራህ ነው” ብለው  ትልቅ ሙያተኛና አስተዋፅኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ ሜዳሊያ ሸለሙኝ፡፡ በአሜሪካን በ2010 ዓ.ም ላይ  ትልቅ ኮንሰርት ተደርጎ ተሳትፌ ነበር፡፡ ሁለት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በሙዚቃ ዲፕሎማሲ የክብር እውቅና ሰጥተውኛል፡፡
የአሜሪካኑ የአልበም ማስመረቅ ፕሮግራም እንዴት ነበር?
የአሜሪካኑ ፕሮግራም  በጣም ውጤታማ ነበር፤ እንደምታይው ደስታው እስከአሁን ከፊቴ ላይ አልጠፋም፡፡ ሂደቱ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ “ኤምሲል ዎርልድ ሪከርድስ ሌብል”  በሚል የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ ጥሩ ስራ የሰሩ ታዋቂ ሰዎችን ማስተዋወቅ ሲሆን ትልቁ ስራቸው ግን ያልታወቁ ሰዎችን መፈለግና ማስተዋወቅ ነው፡፡ “ስራህን በኢንተርኔት ላይ አይተነዋል፤ ጥሩ ነው እናስተዋውቅህ” ቢሉኝም ብዙዎች እንደዚያ እያሉ ተግባራዊ ስለማያደርጉት  አላመንኳቸውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ስራዎቼን በአዲስ እንድቀርፅና ኮንሰርት እንዳደርግ የሚያስችል የስራ ፈቃድ እና ቪዛ ላኩልኝ፡፡ በ2013 ሄጄ ኮንሰርት አቀረብኩ፤ ስራዬንም ቀረፅኩ፡፡ በወቅቱ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በአድናቆት የተሞላ ፅሁፍ አወጣ፡፡ ሞራሌን በጣም ከፍ አደረገው፡፡ ከአንድ አመት በኋላ፣ ሰሞኑን ማለት ነው ሲዲዬን ለቀቅኩ፡፡ የአልበሙ መጠሪያ “ላቭ ኤንድ ፒስ” ነው፡፡ አልበሙ  ከፍተኛ ሽያጭ ነው ያስመዘገበው፡፡ በአሜሪካ የሙዚቃ ደረጃ በሚያወጣው የቢልቦርድ ሰንጠረዥም 23 ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ከአርቲስት ሚካኤል በላይነህ ጋር የሰራሁት “መለያ ቀለሜ” የሚለው አልበምም በቢልቦርድ ሰንጠረዥ የገባ ሲሆን ለብቻዬ ከሰራኋቸው ውስጥ ግን የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
የአሜሪካው ኮንሰርት ብዙ ኢትዮጵያውያን ታድመውት ነበር?
ብዙ ባይሆኑም ነበሩ፡፡ እንዲያውም ከኮንሰርቱ በኋላ እራት ጋብዘውኝ እንዴት አናውቅህም አሉኝ፡፡ ከጋባዦቼ አንዱ ደግሞ “አንተን የሙዚቃ ግርማ ሞገስ ብዬሀለሁ” አሉኝ፡፡ ይህ አባባል ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ አባቴ አስራ ሁለተኛ ክፍል ጨርሼ ዩኒቨርሲቲ ከተማርኩ በኋላ ወደ ስራ እንድገባ ነበር የሚፈልገው፡፡ የሙዚቃ ጉዞውን እንዳታደናቅፉት ብለው ብዙ እገዛ አድርገው ለዛሬ እኔነቴ የለፉት አጎቴ ናቸው፤ ስማቸው ደግሞ ሞገስ ነው፡፡ ግርማ ሞገስ ሲሉኝ በጣም ደስ አለኝ፡፡
ልጆችህን ፒያኖ እያስተማርክ ነው?
አዎ! የትምህርት ጊዜያቸውን ሳልሻማ በትርፍ ሰአት አስተምራቸዋለሁ፡፡
በሚቀጥለው ሐሙስ አዲስ አመት ነው፡፡ መጪውን  አመት እንዴት ትቀበለዋለህ?
እንግዲህ እድሜ አግኝቶ  አዲስ አመትን መቀበል  ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተቻለ መጠን አዳዲስ ስራዎቼን እንዲሁም ተሰርተው የተቀመጡትን የማስተዋውቅበት አመት ይሆናል፣ ሌሎች ብዙ በሮችም ይከፈታሉ ብዬ በተስፋ እቀበለዋለሁ፡፡

          የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት  ጊዜው የኢትዮጵያ እንደሆነ ሱፐር ስፖርት ዘገበ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሊቢያን በመተካት በ2017 እ.ኤ.አ ላይ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ እንደሚፈልግ ያስታወቀው ከ2 ሳምንታት በፊት ሲሆን በኦፊሴላዊ ደረጃ ለካፍ ማመልከቻ ስለማስገባቱ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን  ሊቢያን በመተካት  አዘጋጅነቱን ለሚያመለክቱ አገራት የሰጠው የግዜ ገደብ  3 ሳምንታት ይቀሩታል፡፡ ኢትዮጵያ አመልክታ ተቀባይነት ካገኘች ለ4ኛ ጊዜ የምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ይሆናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በወጡ ዘገባዎች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መስራች እንደነበረች በማስታወስና ባለፉት 3 ዓመታት ለ31 ዓመታት ከውድድሩ የራቀችበትን ሁኔታ በቀየረ የእግር ኳስ ለውጥ ላይ እንደምትገኝ በመግለፅ አዘጋጅነቱን ብታገኝ ይገባታል ብለዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በአፍሪካ የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናሀርያነት የምትጠቀሰው  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት ገልፆ የዘገበው ቢቢሲ ነበር፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባና  በባህርዳር  ሁለት ዝግጁ ስታድዬሞች መኖራቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ሲሆኑ ፤ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስታድዬሞች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን በመጥቀስ ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የፊፋ እና የኦሎምፒክ ስታንዳርድን የሚያሟላ እና 60ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ብሄራዊ ስታድዬም በአዲስ አበባ ለመስራት እቅድ እንዳላት የገለፀው የሱፕር ስፖርት ዘገባ ሶስት አፍሪካ ዋንጫዎችን ያስተናገደው የአዲስ አበባው ብሄራዊ ስታድዬምም ከፍተኛ እድሳት ተደርጎለት ለመስተንግዶ ሊደርስ እንደሚችል ጠቅሷል፡፡
በ2017 እኤአ ላይ 31ኛውን አፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ  ተመርጣ የነበረችው ሊቢያ  መስተንግዶውን የተወችው በአገሪቱ በቂ ሰላምና መረጋጋት አለመስፈኑ በፈጠረባት እክል እንደሆነ ያስታወቀችው ከሶስት ሳምንት በፊት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ባወጣው መግለጫ  እንዳመለከተው ሊቢያ ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ስታድዬሞችን በመገንባት እንደማይሳካላት እና በአስተማማኝ ፀጥታ ውድድሩን ለማካሄድ እንደማትችል አረጋግጫለሁ በማለት ለአባል ፌደሬሽኖቹ ምትክ አዘጋጅን ለማግኘት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሱፕር ስፖርት  ጊዜው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የምታዘጋጅበት ነው በሚል ርእስ በሰራው ዘገባ በኢትዮጵያ ስፖርት ዙርያ ባሉ ባለድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶች የመስተንግዶውን ፍላጎት አድርገውታል፡፡ ለሱፕር ስፖርት በሰጡት አስተያየት አፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያለንን ፍላጎት መላው ኢትዮጵያዊያንና እና የአፍሪካ አገራት ከደገፉት ይሳካል ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ  ናቸው፡፡
‹‹የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት፤ በአህጉሪቱ እግር ኳስ ያለንበትን ከፍታ ለማሳየት እድል ይፈጥራል›› ብሎ የተናገረው ደግሞ ኤልሻዳይ ነጋሽ የተባለው ታዋቂ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አዲስ አበባ በአፍሪካ የባቡር ሜትሮ ኔትዎርክ ካላቸው ጥቂት ከተሞች አንዷ መሆኗን፤ በመሰረተ ልማት እየተጠናከረች መምጣቷን ለሱፕር ስፖርት የገለፀው ኤልሻዳይ  ፤ የፓን አፍሪካኒዝም መዲና በሆነች ከተማ ውድድሩ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው በማለት ድጋፉን ገልጿል፡፡ ‹‹የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለውድድሩ አዘጋጅነት ፍላጎት ማሳየቱን ስሰማ በጣም ጉጉት ፈጥሮብኛል፡፡ ለእኛ ተጨዋቾች አፍሪካ ዋንጫን በሜዳችን በደጋፊችን ፊት መጫወት ከፍተኛ ሞራል እና መነቃቃትን የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ፌደሬሽኑን እና መንግስትን በሙሉ አቅም መደገፍ አለባቸው፡፡  በዚህም አፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት ህልምን ማሳካት ይቻላል፡፡›› በማለት ለሱፕር ስፖርት የድጋፍ አስተያየት ያቀበለው የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋች አበባው ቡጣቆ ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ የአማካይ መስመር ተሰላፊ የሆነው ሽመልስ በቀለ በበኩሉ ‹‹አስደሳች  እና ታላቅ ዜና ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት እንደሚሳካላት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   አዘጋጅ ሆነች የሚለውን ዜና በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡
ከ29 የአፍሪካ ዋንጫዎች በአስሩ ላይ መሳተፍ የቻለችው ኢትዮጵያ ለሶስት ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ነበረች፡፡ በ1962 ውድድሩን በማዘጋጀት ሻምፒዮን ስትሆን እንዲሁም በሌሎች ባዘጋጀቻቸው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በ1968 እኤአ ላይ አራተኛ ደረጃ እና በ1976  እኤአ ደግሞ ከመጀመርያው ዙር ከውድድሩ ተሰናብታለች፡፡ ከኢትዮጵያ ሌላ የውድድሩን አዘጋጅነት ለመረከብ ፍላጎታቸውን የገለፁት አገራት አምስት ደርሰዋል፡፡ የመጀመርያዋ ኬንያ ስትሆን የአፍሪካ ዋንጫውን ከጐረቤቶቿ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ጋር በጣምራ የማዘጋጀት ጥያቄ አቀርባለሁ እያለች ነው፡፡ የምእራብ አፍሪካዋ ጋና እና የደቡብ አፍሪካዋ ዛምቢያም አዘጋጅነቱን እንደሚፈልጉ ሲያስታውቁ በመጨረሻም ለመስተንግዶ ፍላጎቷን እያሳየች የመጣችው አልጄርያ ናት፡፡ 16 ብሄራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበትን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟሉ ስታድዬሞች፤ የሆቴል እና የትራንስፖርት መሰረተልማቶች እጅግ ወሳኝ ሲሆኑ እስከ 55 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግም ይገመታል፡፡