Administrator

Administrator

                  የ4.5ቢ. ዶላር ድጋፍ አድርገዋል የኩዌት አሚር የተከበሩ ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-አልጃበር አል-ሳባህ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይለዩ ለዓለም ህዝብ ባደረጉት የተለያዩ ድጋፎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ “የሰብአዊ በጎ አድራጎት ስራዎች መሪ” በማለት እንደሸለማቸው የኩዌት አምባሳደር አስታወቁ፡፡ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በዩጋንዳ የኩዌት አምባሳደር ሺድ አልሃጅሪ፣ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አሚሩ ሊሸለሙ የቻሉት፣ ባላቸው መልካም አመለካከትና ቅን አስተሳሰብ የህዝቦችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ህዝቦችን ለመርዳት ያደረጉትን ሰብአዊ ስራ ለማጉላትና እውቅና ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሚሩ ያደረጉት ሰብአዊ ድጋፍ 4.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አምባሳደሩ ጠቅሰው፣ 2.5 ቢሊዮን ዶላሩ የአፍሪካ ድርሻ ነው ብለዋል፡፡ ጥቃቅንና መካከለኛ ቢዝነሶች ለመደገፍና ለማበረታታት 500 ሚሊዮን ዶላር፣ ምስራቃዊ ሱዳንን እንደገና ለመገንባት 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ለፍልስጤም ስደተኞች ድጋፍ 34 ሚሊዮን ዶላር፣ ለአፍሪካ ህብረት የጤና ክሊኒክ ማስፋፊያ 5 ሚሊዮን ዶላር፣ በአፍሪካ ለሚደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች 1 ቢሊዮን ዶላር፣ በአፍሪካ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ ለ13 የሰብአዊ በጎ አገልግሎት ሥራዎች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ስለኢትዮጵያና ኩዌት ግንኙነት የተጠየቁት አምባሳደሩ፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ግንኙነቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሱት በማስታወስ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግንኙነቱ እንዲቀጥል ባደረጉት ጥረት፣ ሁለቱ አገራት 14 የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ገልፀዋል፡፡ በኩዌት ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ መንግስታቸው ምን እርምጃ እንደወሰደ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “ኩዌት በህግ ተቋም የምትተዳደር አገር ስለሆነች፣ ፖሊስና ፍርድ ቤቶች ህጉን ለማስከበር በከፍተኛ ሁኔታ ይሰራሉ፤ የኩዌት ህግ ለማንም አያደላም፤ የአገሩም ሆነ የውጭ ዜጎች እኩል ነው የሚዳኙት፡፡” ብለዋል አምባሳደር ራሺድ አልዛድሪ፡፡ በኩዌት 80ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

             ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ከኒውዮርክ አፍሪካን ሬስቶራንት ዊክ ጋር በመተባበር ባወጣው በኒውዮርክ ሲቲ የሚገኙ ምርጥ አስር የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር ውስጥ፣ የኢትዮጵያውያኑ ሬስቶራንቶች ‘ንግስተ ሳባ’ እና ‘ባቲ’ ተካተቱ፡፡ በኒውዮርክ ሲቲ የአፍሪካውያን ምግቦችን በማቅረብ ከሚታወቁት ከ50 በላይ ሬስቶራንቶች መካከል፣ በሚያዘጋጇቸው ምግቦች ጣዕም፣ በመስተንግዶ፣ በውስጣዊ ድባብና ዘላቂነት በሚሉ መስፈርቶች ከተመረጡት 10 ሬስቶራንቶች መካከል የኤርትራውያኑ ‘ምጽዋ’ም ይገኝበታል፡፡

ከታዋቂው ታይምስ አደባባይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውና በሼፍ ፊሊጶስ መንግስቱ ባለቤትነትና አስተዳዳሪነት የሚመራው ንግስተ ሳባ፣ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ ምግቦች እያጣጣሙ ከወዳጅ ዘመድ ጓደኛ ጋር ለመጨዋወት ተመራጭ ቦታ እንደሆነ የገለጸው ፎርብስ፤ የሚያቀርበው ጣፋጭ ኬክም ልዩ መገለጫው እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በባህላዊ የቤት ማስጌጫዎች የተዋበው ይሄው የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት፤ በተለያዩ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የዘገባ ሽፋን እንዳገነ ፎርብስ አስታውሷል፡፡ በአዲስ አበባ በተወለደችው ህብስት ለገሰ ባለቤትነት የሚንቀሳቀሰው ባቲም፣ ጣፋጭ የኢትዮጵያውያን ምግቦችን በአስደናቂ መስተንግዶ ለደንበኞቹ በማቅረብ እንደሚታወቅ ፎርብስ ገልጿል፡፡ የሴኔጋሎቹ “ፖንቲ ቢስትሮ”፣ “ካፌ ሪዮ ዲክስ” እና “ሌኖክስ ሳፋየር”፣ የደቡብ አፍሪካዎቹ “ማዲባ” እና “ቶላኒ ኢተሪ ኤንድ ዋይን”፣ የናይጀሪያው “ቡካ” እንዲሁም የአይቬሪኮስቱ “ፋራፊና ካፌና ላውንጅ”ም፣ በኒውዮርክ ሲቲ ምርጥ 10 የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር እንደተካተቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባና በአምስት ክልሎች ባቋቋሟቸው የፌስቱላ ሆስፒታልና የህክምና ማዕከላት ከ40ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታማሚዎች የህክምና እርዳታ በመስጠት የሚታወቁት የዶ/ር ካትሪን ሃምሊን 90ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ሪትዝካርልተን ይከበራል፡፡ የፕሮግራሙን አዘጋጆች በመጥቀስ ታዲያስ መጽሄት ከኒውዮርክ እንደዘገበው፣ ዶ/ር ሃሚሊን በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ልዩ መልዕክት እንደሚያስተላልፉና በወሊድ ምክንያት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን ለማጥፋት ርብርብ እንዲደረግ ያስተላለፉትን ጥሪ ተቀብለው የራሳቸውን ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ዝግጅቱን እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ የዶ/ር ሃምሊን የ90ኛ አመት የልደት በዓል፣ የተከበሩ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ ከአገር ውስጥና ከሌሎች የአለም አገራት የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ጥር ወር በአዲስ አበባ መከበሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ዶ/ር ሃምሊን ፌስቱላን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ላለፉት 55 አመታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡ በአዲስ አበባና በክልሎች የፌስቱላ ሆስፒታልና የህክምና መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም በአገሪቱ ከፍተኛ የጤና ችግር ሆኖ የቆየውንና ተገቢ ህክምና ያልነበረውን ፌስቱላን ለማጥፋት ይዘው ለተነሱት ታላቅ ራዕይ መሳካት እገዛ የሚያደርገውን የአዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ተጠቃሽ ሰው መሆናቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ፌስቱላ በአፍሪካ ከአስራ ሁለት ሴቶች በአንዷ ላይ የሚከሰት አሳሳቢ የጤና ችግር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Monday, 22 September 2014 14:20

ሃይማኖት አለሙ አረፈ

          ታዋቂው ተዋናይና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት አለሙ፣ ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ በትናንትናው ዕለት አረፈ፡፡በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደውና በሆለታ ያደገው ሃይማኖት አለሙ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን፣ በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ በትወና ጥበብ በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቅ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዲሁም በስነጥበባት ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ለረጅም አመታት በአሜሪካ የኖረውና በበርካታ ቲያትሮችና ፊልሞች ላይ በተዋናይነት በመስራት የሚታወቀው ሃይማኖት፣ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ፣ አስታር አድቨርታይዚንግ በተባለው አለም አቀፍ የማስታወቂያና የኮሙኒኬሽን ተቋም ዋና ጸሃፊ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በራክማኖቭ ኮሌጅ የትወና ጥበብ ያስተማረው ሃይማኖት፤ በብሔራዊ ትያትር በስራ አስኪያጅነት ያገለገለ ሲሆን በዚሁ ትያትር ቤት በበርካታ ትያትሮች ላይ ተውኗል፡፡ የትወና ብቃቱን ካሳየባቸው ትያትሮች መካከል የታዋቂው ባለቅኔና ፀሐፌ ተውኔት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “እናት ዓለም ጠኑ” እና “ሀሁ በስድስት ወር” ተጠቃሽ ሲሆኑ “ቴዎድሮስ” በተሰኘው ትያትር ላይ በመተወንም ይታወቃል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት የሼክሰፒርን “ሃምሌት” የተሰኘ ትያትርም አዘጋጅቷል፡፡

       በዶ/ር አቡሽ አያሌው የተዘጋጁት “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 መጽሐፎች ሰሞኑን ለንባብ በቁ፡፡ አዘጋጁ በ“አልፋና ኦሜጋ ቁጥር 1” መጽሐፍ፤ ስለ ሰዎችና ዩኒቨርስ የመጀመሪያና የመጨረሻ ምስጢራት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት የጀመሩትን ሃሳብ በቁጥር ሁለትና በቁጥር ሶስት መጽሐፋቸው በስፋት እንዲቃኙት ለማወቅ ተችሏል፡፡ “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር ሁለት፤ ስለ እኛና ስለ ዩኒቨርስ የመጀመሪያና መጨረሻ ምስጢራት አልበርት አንስታይንና ስቴፈን ሐውኪንግ ደርሰውበታል ስለተባለው እውነት፣ ስለ 666 አስገራሚ የዩኒቨርስ ቁጥርነት፣ በድንገት ፈነዳ ስለተባለው መንፈሳዊ እሳት፣ በመንፈሳዊ ሃይል ስለተሞላው ጨለማ፣ በአስገምጋሚው እሳት ውስጥ ተፈጠረ ስለተባለው ሰማይና ምድር እንዲሁም የአልበርት አንስታይንን መሳጭ የህይወት ታሪክ ያካተተ ሲሆን በ125 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር ሶስት መጽሐፍ ደግሞ በተለይ ከሞት በኋላ ህይወትና የፈጣሪ መኖር በኳንተም ፊዚክስ ስለመረጋገጡ፣ በነፍስ ላይ ስለተካሄዱ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ የፈጣሪን ህልውና በማያዳግም መልኩ ስላረጋገጡ 15 ትልልቅ ፍልስፍናዎች፣ በፈጣሪ መኖር ስለሚያምኑ የዓለማችን 13 ምርጥ ሳይንቲስቶች እንዲሁም ስለ ገነት፣ ገሃነም፣ መላዕክት፣ ዲያቢሎስና ፈጣሪ፤ ሳይንስ የደረሰበትን እውነታ ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በ224 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ

ባለፈው ዓመት የያዝናቸውን የስራ እቅዶች ከሞላ ጐደል ማከናወን ችለናል፡፡ ለአዲሱ አመት የተላለፉም አሉ፡፡
በአጠቃላይ 2006 መጥፎ አመት አልነበረም፤ ጥሩ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሰው ሃላፊነት እንዲወስድ እጠይቃለሁ፡፡ ሃላፊነትን መውሰድና መወጣት ቀላል ነገር
ይመስላል እንጂ ከባድ ነው፡፡ ለምሣሌ ስለ መኪና አደጋ ችግር ሲነሳ ጥፋቱ ሁሌም በአንድ ወገን (ሹፌሩ) ላይ
ብቻ ነው የሚደመደመው፡፡ ሃላፊነቱ ለአንድ ወገን ብቻ እየተሰጠ ስለሆነ በዚህ ረገድ ውጤታማ መሆን
አልተቻለም፡፡ ነገር ግን መንገደኛው (እግረኛው)፣ የእንስሳት መንገድ አጠቃቀም፣ የመኪናው ቴክኒካዊ ብቃት
የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ መንግስትም ሃላፊነቱን እኔ ብቻ እወስዳለሁ ሣይል ወደ ህብረተሰቡም
ማውረድ አለበት፡፡ ያ ካልሆነ የምንመኘው ነገር ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡
2006 ዓ.ም እውነቱን ለመናገር ለስፖርቱ ጥሩ አልነበረም፤ በአትሌቲክስም ሆነ በእግር ኳሱ፡፡ በዚህ ዘርፍም
ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም የየራሱን ሃላፊነት ወስዶ ግዴታውን በሚገባ መወጣት አለበት፡፡ አዲሱ ዓመት
የእድገትና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞቴ ነው፡፡

አሜሪካ 300 ወታደሮች ወደ ላይቤሪያ ልትልክ ነው

እንግሊዛዊቷ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሩት አትኪንስ ሰሞኑን በኦክስፎርድ ለ60 በጎ ፍቃደኞች ሊሰጥ የታቀደውን
የኢቦላ ቫይረስ የሙከራ ክትባት በመውሰድ የመጀመሪያዋ በጎ ፈቃደኛ እንደሆነች መሆኗን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የሙከራ ክትባቱን የሚወስዱ በጎ ፈቃደኞች እንደሚፈለጉ በቢቢሲ ሬዲዮ መስማቷን የገለፀችው አትኪንስ፣
በምዕራብ አፍሪካ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ስለሆነና የዚህ ክትባት ሂደት አካል መሆን ትልቅ ውጤት ለማምጣት
በሚደረገው ጥረት ማበርከት የምችለው ትንሹ ነገር እንደሆነ በማሰብ፣ ክትባቱን በበጎፈቃደኝነት ለመውሰድ
ወስኛለሁ” ብላለች፡፡
ክትባቱ ከኢቦላ ቫይረስ ትንሽ የዘረመል ንጥረ ነገር ብቻ የያዘ በመሆኑ ተከታቢው በበሽታው እንደማይያዝ
የተገለፀ ሲሆን በኦክስፎርድ የጄነር ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተርና የሙከራ ክትባቱ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አድርያን
ሂልም፤ “ይሄ ክትባት ማንንም ኢቦላ ያስይዛል የሚል ቅንጣት ስጋት የለም” ብለዋል፡፡
ክትባቱን ለመወጋት ስታስብ የደህንነቷ ጉዳይ እንዳላስጨነቃት የተናገረችው ሚስ አትኪንስ፤ የ15 ዓመት ታዳጊ
ልጇ የኢቦላ ቫይረስ ተሰጥቷት የምትሞት መስሎት እንደነበርና እንዳረጋጋችውም ገልፃለች፡፡
ብዙ ጊዜ አዲስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ለዓመታት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግ
ይቆይ ነበር ያለው ቢቢሲ፤ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አጣዳፊነት ግን ይሄ የሙከራ ክትባት
በአስደናቂ ፍጥነት ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረቱ እንዲጠናከር አድርጓል ብሏል፡፡
በሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ ውጤታማ ሆኖ ከተገኘ፣ ክትባቱ በፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ በቫይረሱ
በተጠቁ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ሰራተኞችን ከበሽታው ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
ያን ጊዜ ግን ለ10ሺ ሰዎች ያህል የሚሆን ክትባት እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ ክፉኛ
የተጠቁ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ከቫይረሱ ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
ክትባቱ እየተሰራ የሚገኘው ግላክሶስሚዝክላይን በተባለ ኩባንያና በአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም ሲሆን፣
የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ተቋማት ለሙከራ ክትባቱ የገንዘብ
ድጋፍ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል እገዛ የሚያደርጉ 3ሺ ወታደሮችን
ወደ ላይቤሪያ የመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ባለፈው ማክሰኞ አስታወቁ፡፡ ኦባማ ይሄን ያስታወቁት የላይቤሪያዋ
ፕሬዚዳንት አለን ጆንሰን ሰርሊፍ በሽታውን ለመከላከል እገዛ ያደርጉላቸው ዘንድ ለኦባማ በቀጥታ ያቀረቡትን
ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአሜሪካ ወታደራዊ ሃይል የህክምና ማዕከሎችን ግንባታ በመቆጣጠርና የጤና ሰራተኞችን በማሰልጠን
ለላይቤሪያ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ያልሆነ ምላሽ ትችት ሲሰነዘርበት
፣ቆየቱ ይታወቃል፡፡
በበሽታው ክፉኛ የተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ ሲሆኑ ወረርሽኙ ከ2400 በላይ
ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ ተጠቁሟል፡፡ ከእዚህ የሞት አደጋ ውስጥ ግማሹ የተከሰተው በላይቤሪያ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት፤ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን በቫይረሱ ልታጣ እንደምትችል በቅርቡ
አስጠንቅቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች፣ በጄኔቫ በሚያካሂዱት ስብሰባ ለወረርሽኙ
በተሰጠው ዓለም አቀፍ ምላሽ ላይ እንደሚወያዩ ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ባለፈው ሰኞ ወረርሽኙን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤
“በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከፍተኛና ፈጣን የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

የኢቦላ ቫይረስ በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት በበሽታው ተይዘው የነበሩና ከህመማቸው ያገገሙ
ሰዎች ደም፣ ታማሚዎችን ለማከም በሚል በድብቅ እየተሸጠ መሆኑን ሲኤንኤን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በበሽታው ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ደም በውስጡ የኢቦላ
ቫይረስን የሚያጠፋ ንጥረ ነገር አለው በሚል እየተናፈሰ ባለው መረጃ የተነሳ፣ በአገራቱ የሚገኙ የኢቦላ
ታማሚዎች ደሙን በድብቅ ከሚሸጥበት ስውር ገበያ እየገዙ ይገኛሉ፡፡
የአለም የጤና ድርጅትን በሽታው በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት እየተከናወነ ያለውን ስውር የደም
ሽያጭ ለማስቆም ከአገራቱ መንግስታት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ታማሚዎች
በአገራቱ ሆስፒታሎች በሚሰጠው ህክምና ተስፋ በመቁረጥ ፊታቸውን ወደዚህ ህገወጥ ገበያ ማዞራቸውን
ገልጿል፡፡ ዘ ቴሌግራፍ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ደም ታማሚዎችን ቶሎ እንዲድኑ
በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ቢረጋገጥም፣ ደሙ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ ቫይረሶች የተበከለ
መሆን አለመሆኑ ሳይረጋገጥ በድብቅ የሚሸጥ መሆኑ ሌላ ቀውስ እንዳያስከትል ስጋት መፍጠሩን ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስን ጠቅሶ፣ ድርጅቱ ከኢቦላ በሽታ ያገገሙ ሰዎችን ደም
በአግባቡ መርምሮ በመሰብሰብና በማጠራቀም ለተመሳሳይ ህክምና ለማዋል የሚያስችል ደህንነቱ የተጠበቀ
አሰራር እየቀየሰ እንደሚገኝ የዘገበው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ፣ ድርጅቱ መሰል የደም ህክምናን እንደሚደግፍ
ቃል አቀባይዋ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡

Saturday, 20 September 2014 11:50

“ስውር ስፌት ቁ.2” ተመረቀ

በጋዜጠኛ፣ ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኰንን የተጻፈው “ስውር ስፌት ቁ.2” የግጥም መድብል ትናንት ምሽት
በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ተመረቀ፡፡የኪነጥበብ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት
በተከናወነው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ፣ ገጣሚውን ጨምሮ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ለታዳሚው
አቅርበዋል፡፡
ገጣሚ ነቢይ በመኰንን ከዚህ በፊት “ጥቁር፣ ነጭ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት ቁ.1” የግጥም መፃህፍት
ለአንባቢ ያበረከተ ሲሆን፣ በታዋቂዋ አሜሪካዊት ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል የተጻፈውን “Gone With The
Wind” የተሰኘ ተወዳጅ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉሞ
በማቅረብ ይታወቃል፡፡
“ስውር ስፌት ቁ.2” በመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡

“መንገድ ተዘረጋ
መንገድ ተቀየሰ
በተራማጅ እጦት
መልሶ ፈረሰ!...”
በገጣሚ አክሊሉ ገብረ መድህን የተጻፈው “የጭቃ ጅራፎች” የተሰኘ የግጥም መጽሃፍ፣ ነገ ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት
በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 50 የገጣሚው የግጥም ስራዎች የተካተቱበት መጽሃፉ 92 ገጾች
ያሉት ሲሆን በተለያዩ መጽሃፍት መደብሮችና አዟሪዎች ዘንድ በ20 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የጥበብ አፍቃሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት የመጽሃፉ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ፣ አንጋፋና
ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡