Administrator

Administrator

        ለተለያዩ የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራዎች የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡ ተገኝተዋል የተባሉ 3 የውጭ አገር ዜጐችና አራት የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞችን ጨምሮ 70 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ አገሪቱን በሚሊዮን የሚገመት ገቢ አሣጥተዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች፤ በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የተለያዩ ለቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በአዲስ አበባ፣ አዋሣ ጭሮ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ጅግጅጋ ከተሞች ጥቅም ላይ አውለዋል ተብሏል፡፡ ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዎቹ ህገወጥ ድርጊታቸውን በውጭና በሀገር ውስጥ በተደራጀ ሁኔታ ሲያከናውኑ እንደቆዩ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
ህብረተሰቡ በሚኖርበት አካባቢ ለየት ያሉ እንደ ትናንሽ የሳተላይት መቀበያ ያሉ የቴክኖሎጂ መጠቀሚያና መሰል መሣሪያዎች ተተክለው ሲያይ በየአካባቢያቸው ለሚገኝ የፖሊስ አካል ወይም ለኢትዮ ቴሌኮም ነጻ የጥሪ ማዕከል 994 በመጠቀም ጥቆማ ማቅረብ ይችላል ተብሏል፡፡

          ፖርትላንድ ፕሪቶሪያ ሲሜንት (ፒፒሲ) የተሰኘው ተቀማጭነቱ በደቡብ አፍሪካ የሆነ የሲሚንቶ አምራች ኩባንያ፣ በሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ውስጥ የነበረውን 27 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ወደ 51 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቤኪ ሲባያ ባለፈው ረቡዕ ለዴስቲኒ ኮኔክት ድረ ገጽ እንደተናገሩት፣ ከሁለት አመታት በፊት ከሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር 27 በመቶ የአክስዮን ድርሻ የገዛው ፒፒሲ፤ ድርሻውን ወደ 51 በመቶ ማሳደጉ፣ በአፍሪካ አህጉር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማጐልበት የቀየሰውን ስትራቴጂ የበለጠ ለማፋጠን አቅም ይፈጥርለታል፡፡
በ135 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከአዲስ አበባ በ35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ግንባታው በመከናወን ላይ የሚገኘው የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ከሁለት አመታት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ የማምረት ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅና በአመት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ሲባያ ተናግረዋል፡፡
ቀሪው 49 በመቶ የሃበሻ ሲሚንቶ የአክሲዮን ድርሻ ከ16 ሺ በላይ በሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት እንደሚቀጥልም ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል፡፡

ማረጥ በየትኛዋም ሴት ላይ ሊከሰት የሚችል ተፈጥሮአዊ ክስተት ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንደ አንድ የጤና እክል ሲቆጥሩት ይስተዋላል፡፡ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ፈፅሞ የተሳሳተና ከሳይንሰዊ እይታ ውጪ የሆነ ነው፡፡
 በዛሬው ፅሁፋችን እውን ማረጥ ተፈጥሮአዊ ነው ወይንስ ጥቂቶች እንደሚሉት የጤና እክል ነው? የሚለውን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ NIA (National Institute On Aging) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ የጤና ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
ማረጥ ምንድነው?
የአንዲት ሴት የማረጫ አማካኝ እድሜ ስንትነው?
ከማረጧ በፊት እንዲሁም በኋላስ ምን አይነት የጤና እክሎች ይገጥሟታል? የሚሉትን ጉዳዮች አስመልክቶ ያወጣውን ፅሁፍ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-
ማረጥ ምንድነው?
ማረጥ ልክ እንደ ጉርምስና ሁሉ በተወሰነ የእድሜ ክልል ላይ የሚከሰት ተፈጥሮአዊ ክሰተት ነው፤ ይህ ተፈጥሮአዊ ክሰተት የወር አበባ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ሆርሞኖች     መጠን መቀነሱን ተከትሎ የወር አበባ ሲቆም የሚፈጠር ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አከላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡! በለውጡ ሶስት ደረጃዎች ይከሰታሉ፡፡
ከማረጥ በፊት፣
በማረጥ ወቅት እንዲሁም
ከማረጥ በኋላ፡፡
አብዛኛዎቹ ለውጦች አንዲት ሴት ወደ ማረጫ የእድሜ ክልል ስትቃረብ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በሰውነቷ ውስጥ የሚገኘው የኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን ሆርሞን ስለሚቀንስ በተለያየ የሰውነት ክፍሎች ላይ የተለያዩ ለውጦች ይታያሉ፡፡
 በመቀጠልም የወር አበባ መታየቱን ያቆማል፡፡ ይህም ለማረጧ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከማረጥ በኋላ ያሉ ለውጦችም የሚከሰቱት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ብዙሀኑ ሴቶች እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሱት በሀምሳዎቹ መጀመሪያ ባለው የእድሜ ክልል ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ከዚህ ቀደም ብለው በአርባዎቹ መጀመሪያ ወይም ደግሞ ዘግይተው በሀምሳዎቹ መጨረሻ ባለው ጊዜ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከተገለፀው አማካኝ የእድሜ ክልል ቀድመው ለማረጥ ተያያዥ ምክንያት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም በማህፀን ላይ የተደረገ የቀዶ ጥገና በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ምልክቶቹ፡-
ሴቶች ወደዚህ የእድሜ ክልል ሲገቡ በሰውነታቸው ያለው የኤስትሮጅንና ፕሮጀሰትሮን መጠን በጣም ስለሚቀንስ የተለያዩ ምልክቶችን ማየት ይጀምራሉ፡፡ የሚከተሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡-
1.    የወር አበባ የሚመጣበት ቀናት በእጅጉ         መቀራረብ፣
2.    የወር አበባ መጠን መጨመር፣
3.    በሰውነት ላይ የሚወጣ ሽፍታ፣
4.    የወር አበባ ከአንድ ሳምት በላይ መቆየት፣
5.    የወር አበባ ከቆመ ከአንድ አመት በኋላ ተመልሶ ሊታይ ይችላል  
ከላይ የተጠቀሱት አንዲት ወደዚህ የእድሜ ክልል መዳረሻ ላይ ያለች ሴት የሚያጋጥሟት ምልክቶች ሲሆኑ በምታርጥበት ወቅት ደግሞ ሌሎች በሰውነቷ ውስጥ ያለው የኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አከላዊ ብሎም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ተከታዮቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
1.    ድንገተኛና በተደጋጋሚ የሚከሰት የሰውነት         ሙቀት መጨመር፣
ይህም የሚከሰተው በሰውነታችን ያለው የኤስትሮጅን መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ ሲሆን አንዲት ሴት ካረጠች በኋላም ለተወሰኑ አመታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ ድንገተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት በይበልጥ በላይኛው የሰውነታችን ክፍል ማለትም በጀርባ፣ በአንገት እንዲሁም በፊት አካባቢ ይከሰታል፡፡ በአብዛኛውም ከ30 ሰኮንድ እስከ 10 ደቂቃ ሊቆይ ይችላል፡፡
2.    ብልት አከባቢ መድረቅ እንዲሁም የኢንፌክሽን መፈጠር ይህም ለወሲብ ፍላጎት መቀነስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሴቶች የሽንት መቋጠር ችግርም ያጋጥማቸዋል፡፡
3.    እንቅልፍ ማጣት፣ በማረጥ የእድሜ ክልል         ላይ ያሉ ሴቶች በአብዛኛው በቶሎ እንቅልፍ         ለመተኛት እንዲሁም እረዥም ሰአት         ለመተኛት ይቸገራሉ፡፡
4.    የወሲብ ፍላጎት መቀነስ፣
5.    ድብርት፣ የስሜት መለዋወጥ፣ መነጫነጭ         እንዲሁም ጭንቀት፡፡ በዚህ ወቅት             የተለመዱ     የባህሪ ለውጦች ናቸው፡፡    
6.    የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የማስታወስ         ችሎታ መቀነስ፣ እንዲሁም ከአጥንት እና         መገጣጠሚያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊከሰቱ         ይችልሉ፡፡
ለችግሮቹ መፍትሄ፡-
ማንኛዋም ሴት ቀደም ሲል የተጠቀሱትን አካላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ችግሮች ሲገጥሟት የማረጥ ምልክቶች ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ግን ማረጥ እንደማንኛውም ተፈጥሮአዊ ክስተት ጊዜውን ጠብቆ ሊከሰት እንደሚችል ከዛም ጋር ተያይዞ ስለሚከሰቱ የጤና እክሎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ፅሁፉ በማረጥ ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላሉ ብሎ የሚከተሉትን ነጥቦች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ከሲጋራ እንዲሁም ከሌሎች እፆች መጠበቅ፣
የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአትን መከተል፣ የቅባት ምግቦችን መቀነስ፣ በአንፃሩ ከፍተኛ የፋይበር መጠን ያላቸውን ምግቦች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ፣
በተጨማሪም ሰውነታችን በቂ የሆነ ካልሲየም፣ ቫይታሚን ዲ፣ ሌሎች ቫይታሚኖችን እንዲሁም ሚኒራል እያገኘ መሆኑን ማረጋገጥ፣
የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር፣
የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት ሲያጋጥም ሳሳ ያሉ ልብሶችን መልበስ እንዲሁም ቀዝቃዛና ነፋሻማ በሆኑ ቦታዎች መቀመጥ፣
    ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪም ለዘወትር         ሊታወሱ     ይገባል ብሎ ፅሁፍ ተከታዮቹን         ነጥቦችም     አስፍሯል፡-
ከደም ግፊት፣ ከኮለስትሮል እንዲም ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር በተያያዘ በሀኪም የታዘዙ መድሀኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣
ብልት አከባቢ መድረቅ እንዲሁም የኢንፌክሽን መፈጠር ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መድሀኒት እንዲሁም የተለያዩ ቅባቶችን መጠቀም፣
በጡት አካባቢ ማበጥ እና ሲነካካ መጠጠር ሲያጋጥም ሀኪም ጋር ቀርቦ  አስፈላጊውን የህክምና ክትትል  ማድረግ፣ማረጥ የህክምና ክትትል በማድረግ ሊወገድ የሚችል የጤና እክል አይደለም፡፡ ነገር ግን የተለየ የጤና እክል በተለይም ተደጋጋሚ የሆነ ድንገተኛ የሰውነት ሙቀት መጠን ሲያጋጥም የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት ሲኖር፡-
ቀዝቃዛና ነፋስ ያለበት ቦታ መቀመጥ፣
ሳሳ ያሉና  ከሰውነታችን የሚወጣውን ሙቀት ማስወጣት የሚችሉ ልብሶችን መልበስ፣
ቀዝቃዛ መጠጦች መውሰድ ይመከራል፡፡

Monday, 03 November 2014 09:10

የፍቅር ጥግ

መዝፈን ህይወቴ ነው፡፡ እስከዛሬም ህይወቴ ነበር፡፡ ወደፊትም ህይወቴ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሴሊያ ክሩዝ
የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው መዝፈን የጀመርኩት፡፡ በአካባቢያችን ስትራትፎርድ አይዶል በተባለ የዘፈን ውድድር ውስጥ ገባሁ፡፡ ሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የአዘፋፈን ትምህርትና የድምጽ ስልጠና ይወስዱ ነበር፡፡ በወቅቱ እምብዛም ከቁምነገር ስላልቆጠርኩት ቤት አካባቢ ብቻ ነበር የምዘፍነው፡፡ ገና 12 ዓመቴ ነበር፤ እናም ሁለተኛ ወጣሁ፡፡
ጀስቲን ቢበር
የሻማ መደብሩ ሲቃጠል ትዝ ይለኛል፡፡
ሁሉም ዙሪያውን ቆሞ “መልካም ልደት” የሚለውን መዝሙር ሲዘምር ነበር፡፡
ስቲቨን ራይት
ከመዝፈን የሚሻል ብቸኛ ነገር የበለጠ መዝፈን ነው፡፡
ኢላ ፊትዝገራልድ
በዓለም ላይ ትልቁ መግባቢያ ሙዚቃ ነው፡፡ ሰዎች የምታቀነቅንበትን ቋንቋ ባይረዱት እንኳን ሸጋ ሙዚቃን ሲሰሙ ያውቁታል፡፡
ሌዩ ራውልስ
ፀሐይ ስትጠልቅ ከተመለከትክ፣ አንድ ትርጉም ሊኖረው ይገባል? አዕዋፍ ሲዘምሩ ከሰማህ፣ መልዕክት ማስተላለፍ አለበት?
ሮበርት ዊልሰን
ዘፈን ሁልጊዜም እጅግ ትክክለኛው ሃሳብን የመግለጫ መንገድ ነው፡፡ በጣም ግብታዊ ነው፡፡ ከዘፈን ቀጥሎ ደሞ ቫዮሊን ይመስለኛል፡፡ እኔ መዝፈን ስለማልችል ሸራዬ ላይ እስላለሁ፡፡
ጆርጂያ ኦ’ኪፌ
በዝናብ ውስጥ እየዘፈንኩ ነው፤ ዝም ብዬ በዝናብ ውስጥ እየዘፈንኩ፡፡ እንዴት ደስ የሚል ስሜት ነው! አሁንም እንደገና ደስተኛ ነኝ፡፡
አርተር ፍሪድ  

Monday, 03 November 2014 09:06

የፀሃፍት ጥግ

ስለ ወህኒ ቤት

የትምህርት ቤትን በር የሚከፍት ሰው፣ በሌላ እጁ የወህኒ ቤትን በር ይቆልፋል፡፡
ቪክቶር ሁጐ
አሜሪካ ሁለተኛ ዕድል የምትሰጥ አገር ናት፡፡ የወህኒ ቤት በር ሲከፈት፣ ፊት ለፊት የተዘረጋው መንገድ ወደተሻለ ህይወት የሚመራ መሆን አለበት፡፡
ጆርጅ ደብሊው ቡሽ
ፍፁም ደህንነት ከፈለግህ ከርቸሌ ሂድ፡፡ እዚያ ትቀለባለህ፣ ትለብሳለህ፣ ህክምና ታገኛለህ…ወዘተ፡፡ ከርቸሌ የሌለው ነፃነት ብቻ ነው፡፡
ድዋይት ዲ. አይዘንአወር
በእኔ አገር መጀመሪያ እንታሰራለን፤ ከዚያ ፕሬዚዳንት እንሆናለን፡፡
ኔልሰን ማንዴላ
ወህኒ ቤት ፈጣሪን እንድፈልገው አላደረገኝም፤ ሁሌም አጠገቤ አለ፡፡ እስር ቤት ውስጥ ሊከረችሙብኝ ይችላሉ፤ ነገር ግን መንፈሴና ፍቅሬ በእስር ቤት ግድግዳዎች ሊታጠሩ አይችሉም፡፡
ሊል ዋይኔ
በአንድ ወቅት ወህኒ ቤት ያገኘሁትን ሰውዬ ምን ሰርቶ እዚያ እንደመጣ ጠየቅሁት፡፡ ጫማ ሰርቆ መታሰሩን ነገረኝ፡፡ የባቡር ሃዲድ ብትሰርቅ ኖሮ የአሜሪካ ሴናተር ትሆን ነበር አልኩት፡፡
ሜሪ ሃሪስ ጆንስ
ሴቶች አሁን ብዙ ምርጫዎች አሏቸው፡፡ ማግባት ወይም አለማግባት፣ ሥራ መያዝ ወይም አለመያዝ፣ ልጆቻቸውን ይዘው እንዳገቡ መኖር ወይም ሳያገቡ ከልጆቻቸው ጋር መኖር፡፡ ወንዶች ግን ሁሌም የነበረው ተመሳሳይ ምርጫ ነው ያለን - ሥራ ወይም ከርቸሌ፡፡

ቲም አለን
     

በመጪው ጥር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይደረጋል
ከደ/አፍሪካው ዴክለርክ በኋላ የመጀመሪያው ነጭ አፍሪካዊ መሪ ናቸው

        ዛምቢያን ላለፉት ሶስት አመታት ያህል ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ሚካኤል ሳታ፤ ባለፈው ማክሰኞ በ77 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በነጭ ጊዜያዊ መሪ መተዳደር መጀመሯን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ለንደን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን ለሳምንታት ሲከታተሉ የቆዩት ሳታ መሞታቸውን ተከትሎ  የዛምቢያ መንግስት ምክር ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአገሪቱ ህገመንግስት በተቀመጠው መሰረት በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩትን ጋይ ስኮት ጊዜያዊ መሪ አድርጎ መርጧል፡፡
ሟቹ ፕሬዚዳንት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለህክምና ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ፣ አገሪቱን በተጠባባቂነት የመምራቱን ሃላፊነት ለመከላከያ ሚኒስትሩ ኤድጋር ሉንጉ ሰጥተው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ሞታቸውን ተከትሎ ግን፣ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ እስከሚካሄድና አዲስ ፕሬዚዳንት እስኪመረጥ ድረስ፣ ጋይ ስኮት አገሪቱን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡እ.ኤ.አ በ2001 “ፓትሪዮቲ ፍሮንት” የተባለውን ፓርቲ በመቀላቀል በወቅቱ በተካሄደው ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ የስኮትላንድ ዝርያ ያላቸውና ወላጆቻቸው ከዛምቢያ ውጭ የተወለዱ በመሆናቸው የአገሪቱ ህገመንግስት ስለሚከለክላቸው በመጪው ጥር በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ላይሳተፉ እንደሚችሉም ገልጿል፡፡
የ60 አመቱ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ጋይ ስኮት፣ ከደቡብ አፍሪካው መሪ ዴክለርክ በኋላ አንድን የአፍሪካ አገር ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያው ነጭ መሪ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
ሟቹ ፕሬዚዳንት ሳታ ላለፉት አራት ወራት ከአደባባይ መራቃቸውን ተከትሎ፣ የከፋ ህመም ላይ ወድቀዋል የሚል ወሬ በስፋት ሲናፈስ መቆየቱን ዘገባው አስታውሶ፤ ፕሬዚዳንቱ በመስከረም ወር አጋማሽ በተከናወነው የአገሪቱ ፓርላማ የመክፈቻ ስነስርአት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የከፋ የጤና ችግር ላይ ናቸው በሚል በስፋት የተሰራጨውን ወሬ በተመለከተ ዘና ያለ ምላሽ ሰጥተው ነበር - “እስካሁን አልሞትኩም” በማለት፡፡ከዚህ የመክፈቻ ስነስርዓት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውዮርክ ጽህፈት ቤት ሊያደርጉት የነበረው ንግግር መሰረዙን ተከትሎ በአሜሪካ ባረፉበት ሆቴል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው እንደነበር ፖሊስ አስታውቶ ነበር፡፡የአገሪቱ መንግስት ፕሬዚዳንቱ በውጭ ሃገር እየታከሙ እንደሚገኙ ከመግለጽ ባለፈ፣ የት አገር እንደሚገኙ ሳይጠቁም መቆየቱንና የዛምቢያ ተቃዋሚ ቡድኖችም ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን የመምራት ብቃት እንደሌላቸው ሲናገሩ እንደነበር ዘገባው አስታውቋል፡፡
የተባ አንደበት ባለቤት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአገሬው ዘንድ ‘ንጉስ ኮብራ’ በሚል የቅጽል ስም የሚጠሩትና በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ተወዳድረው በ2011 ስልጣን የያዙት አምስተኛው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሳታ፤ ታጋሽነት የሚጎላቸው መሪ ናቸው” በሚል ሲተቹ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ፕሬዚዳንቱን ለሞት የዳረጋቸው ህመም ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፡

ባለፈው ማክሰኞ በምስራቃዊ ቨርጂኒያ ውስጥ ከሚገኝ ማዕከል ተነስታ ወደ ህዋ ጉዞ በጀመረች በሰከንዶች ጊዜ ውስጥ የፍንዳታ አደጋ የደረሰባት ሰው አልባ ሮኬት ስብርባሪዎች በሰዎች ላይ የጤና ጉዳት ስለሚያደርሱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ፡፡
የጠፈር ምርምር ቁሳቁሶችን ወደ አለማቀፉ የጠፈር ጣቢያ ለማጓጓዝ አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ ከናሳ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው “ኦርቢታል ሳይንስስ” የተባለው ተቋም ምክትል ፕሬዚዳንት ፍራንክ ከልቤርስቶን፤ በድንገተኛ ፍንዳታ በእሳት የጋየችውን ሮኬት ስብርባሪ መንካት፣ ሮኬቷ ጭናቸው በነበሩ አደገኛ ቁሳቁሶች ምክንያት ለጤና እክል የሚያጋልጡ ስለሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ መምከራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
“አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የማስጠንቀቂያ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ አደጋ የደረሰባት ሮኬት በርካታ አደገኛ ቁሳቁስ ጭና ነበር፡፡ ስብርባሪዎችን ፍለጋ ወደ ስፍራው መንቀሳቀስ አደጋ አለው፡፡” ብለዋል ከልቤርስቶን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
ማንም ሰው በአካባቢው ወድቆ ያገኘውን ማንኛውንም አይነት ቁስ ከመንካት እንዲቆጠብና ሌሎችም ከአካባቢው እንዲርቁ በማድረግ፣ ለሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
2ሺ 200 ኪሎ ግራም የሚመዝን ጭነት የያዘ መንኮራኩር ይዛ ጉዞ የጀመረችውን ሮኬት ለአደጋ ያጋለጣት ምክንያት እስካሁን አልታወቀም፡፡ ሮኬቷና መንኮራኩሩ 123 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጡ ዘገባው ገልጿል፡፡

Monday, 03 November 2014 08:11

የአዳም ረታ ሃሳቦች

ስለስኬታማ ደራሲነት

         ስኬታማ ደራሲ ላልከው አንፃራዊነት ለሚንከባከቡ፣ ከጥናትም ይሁን ከግል ስሜትና ፍላጎት ተነስተው ለሚፈርዱ ወይም ለሚያደሉ ቦታውን ብለቅ ይሻላል፡፡ ስኬታማ የሚለውን ቃል ሙሉ ፍቺ አይናአፋር የተጠየቅ ቅንፍ ውስጥ ልክተተው፡፡
ስኬታማነት ተነቃናቂ ኢላማ ነው፡፡ ማታ ላይ አጠናቅቄ በሰራሁት ድርሰት ረካሁ ብዬ ብተኛም፣ ሲነጋ ቅር የሚሉኝ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከአመታት በፊት በፃፍኩት ዛሬ ላልደሰት እችላለሁ፡፡ የስኬታማነት መለኪያዎች አስራ አስር ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው አገሩ ውስጥ መኖሩን ወይም አለመኖሩን የስነ-ፅሁፍ ስኬታማነት መገምገሚያ ማድረግ ምስፋርን/ስፍራን (place) ብቻ የብቃት መለኪያ ማድረግ ነው፡፡ ይሄ ነጠላ ብቆታ በአብዛኛው ከውጤቱ ወይም ከድርሰቱ ውጭ ያለ ነው፡፡ የተለያዩ የስፍራ መደቦች አሉ፡፡ የግል ስፍራ አለ (Personal space)፣ የቤትህ፣ የቀበሌህ ስፍራ፣ ወዘተ … አለ፡፡ በተጨማሪም ደራሲው በኢምንትነቱ የሙሉኩሌው ወይም የወተትማው መንገድ አባል ነው፡፡ ግንባሩ በሶላር ፍሌርስ ይግላል፣ በበጋ በሚመጣ ዝናብ የሚከረስስ ቆዳ አለው፡፡ በምድር የመግነጢስ መረብ ይረግባል፣ ይወጠራል፡፡
አንድ ደራሲ ዋናው መሳሪያው ምናቡ ነው፡፡ ግን ነባር ልዩ ቦታህ በነበርክ ጊዜ በስርነቀል ልምድ ውስጥ እንድታልፍ ደንብ መሰለኝ (ይሄ ልምድ ፖለቲካ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ የልምድ ዝርያ ላይ ብቻ በማተኮርና ለዛም የማይገባውን ክብደት ብቻ በመስጠት በልምድ የመብሰል መለኪያ ሊደረግ ይሞክራል፡፡ ይሄ አድልኦ ነው፡፡)
ትተኸው (በእርግጥ ትተኀዋል ወይ?) የሄድከው ህብረተሰብ ውስጡ ምን ይመስል እንደነበር በመጠኑም ቢሆን መረዳት አለብህ፡፡ የትኛው ክስተትና ዕውነታ ነው ውዝፍ? (constant) የትኛው ነው ተለዋዋጩ? የቱ ነው ፈዞ/ተለውጦ የሚጠብቅህ? አለዋወጡ የሚገዙት የግንጵሊት ንጥረ ነገሮቹ (elements of metamorphosis) ምንድናቸው? ወዘተ…
ብዙ ብሑት (innovators) የሚባሉ የባዕድ ደራሲዎች ትልልቅ ድርሰቶቻቸውን የፃፉት ከትውልድ አገራቸው ውጭ ሆነው ነው፡፡ እንደውም አንዳንዴ ስለ ራሳቸው አገር በጠለላቸው አገር ቋንቋም ይፅፋሉ፡፡ ወሳኙ ያሳለፍከው የልምድ ስፋትና ጥልቀት፣ ለዚያም ያለህ ግንዛቤና በንቁነት ወይም በኢ-ንቁነት የምታነሳቸው ንፅፅሮች ናቸው እንጂ አካላዊ ዕርቀትና ቅርበት መለኪያ አይደለም፡፡
በራስህ ከምትገነዘበው፣ ተገንዝበህ የምታሰላስለው፣ አሰላስለህ መደምደሚያ የምትወስድበት፣ አንድ ተራ የመሰለ ድርጊት/ገጠመኝ ሰዎችን በግል ብቻ ሳይሆን ስርአት ውስጥ ያላቸውን ባህርይ እንድትረዳ ሰፊም ይሁን ጠባብ መንገድ ይከፍትልሃል፡፡ በስደት ስኖር በእርግጥ አዲስ የረቀቀ የስነፅሁፍ መሰረተልማት (Infrastructure) ውስጥ እገባለሁ፡፡ እነዚያ መኖራቸውን ታያለህ ግን ለእኔ ስራ መመጠናቸውን ማመዛዘን አለብኝ፡፡ ንፅፅር ያልኩት ይሄንን ነው፡፡
ባዕድ አገር ሆኜ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ የቄስ ትምህርት ቤት ዘመን ብፅፍ በግል ተዘክሮዬ ይዤው የመጣሁት የመረጃ ወይም የዕውነታ አንኳር አለ፡፡ ዝርዝሩ ምናብ ነው፡፡ ጥቂት የሚታወሱ ነጥቦች አንስተህ እነዚያን ሚዛን በመጠበቅ የማያያዝና ጊዜ - ዘላይ ጭብጥ የማስነከስ ነው፡፡ ከልጅነቴ አርባ አመታት እርቄአለሁ በሚል ስለ ልጅነት ልብወለድ የመፃፍ መብቴን አላነሳም፡፡ የተወለድኩት አዋሳ ነው፣ አዲስ አባ መጥቼ ለምን ስለ አዋሳ እፅፋለሁ? ብዬ በቦታ መሸጋሸግን ወሳኝ አላደርግም (በአገር ውስጥ ስደት)፡፡ ይሄን መሰረታዊ ነጥብ ሃያሲው ከሳተ የቀረበው ትችት ሳይሆን ስህተት ፍለጋ ነው፡፡ የልጅነታችን ቦታዎችና ጊዜዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንኩዋን ብንሆን ሁሉንም ትተናቸው ሄደናል፡፡ ሁሉም ደራሲ ላለፈው ዘመንም ይሁን ቦታ/ስፍራ በሆነ ደረጃና መልክ ባዕድ ነው፡፡ ቦታዎችም እንደ ሰው ይለወጣሉ፡፡ እንደ ደራሲው እንደ ራሱ እና እንደ ገፀባህርያት፡፡ ልበወለድ ዶክመንታሪ አይደለም፡፡

ስለግንዛቤውና አፃፃፉ
የተወሳሰቡ ልምዶች አሳልፌአለሁ፡፡ በእኔ የተፈጠሩ ወይም በሌሎች ተየሰጡኝ፡፡ (ምርቃትም ይሁን እርግማን) አስከፊም ይሁን ደስ የሚሉ፡፡ እነዚህን ልዘረዘርልህ አልችልም፡፡ ብዙም ናቸው፤ ጥቂትም ናቸው፡፡
በባህርዬ በደንብ አያለሁ፡፡ አድልዖ አላደርግም፡፡ ይሄ ሁኔታዎች በነፃነት ለእኔ እንዲከሰቱ ያደርጋል፡፡ በጣም የሚሞቅ ፀሐያማ ቀን ባልወድም ፀሐይ ውስጥ እቆማለሁ፣ አለመውደዴን አጠናለሁ፡፡ እሱንም አወጣና አወርደዋለሁ፡፡ የሆነ የዜን ዝንባሌ (zen attitude) እይዛለሁ፡፡ ያለ ይሉኝታ (ምን መሆኔ ነው? ሰዎች ምን ይሉኛል?) ሳልል ለማየው ህያው ወይም ጎፍ (physical) አለም ራሴን በመስጠት ነው፡፡
ቅን መሆን አለብህ፡፡ ይሄን ደሞ አስበህ አታመጣውም (የሚያደርጉትይኖራሉ፡፡) ጥንቁቅ አይደለሁም፡፡ ዕቅድ የለህም፡፡ መረጃዎችን ብቻቸውን ሳይ (መገንዘገብ) ከፍፁም ግንኙነት አርቃቸዋለሁ ማለትም አይደለም፡፡ ያኔውኑ በፍጥነት ሊከሰትባቸው የሚችሉ አውታሮችን አስባለሁ፣ ወይም በትካቴ ይመጣሉ፡፡ በቀለ የተባለ ረዥም ልጅ ስልክ እንጨት ሊያስታውሰኝ ይችላል፡፡ ስልክ እንጨቱን ሳይ በቀለ ትዝ ሊለኝ ይችላል፡፡ አልማዝን ሳይ ቄጤማ ትዝ ሊለኝ ይችላል፡፡ የትርሲትን ድምፅ ስሰማ ሚጥሚጣ፣ ቁሶቹን ሳይ ደሞ አልማዝና ትርሲት፡፡ ዝርው የመሰለው ነገር በተለዋጭና በንፅፅር ስርአት ውስጥ ይገባል፡፡ ነጠላነትና ውህድነት በአያዎነት ይተገበራሉ፡፡ የመገንዘብ አድልኦ (Cognitive bias) ብዙ ነገር የመፃፍ ግላዊ ነፃነትህን ሊጋፋ ይችላል፡፡ በእኛ አገር ያልተነገረለት ሳንሱር ይሄ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወሳኝም ይሆናል፡፡
እነዚህ በእንግሊዘኛው ተሳፋሪነት (bandwagon effect) ፣ የጥማድ ህልዮ (group think) የጂም ባህርይ (herd behavior) ፣ ምናምን የሚባሉ ናቸው፡፡
ይሄ ወደ ስሜት ህዋስ አድልዖ (observational bias) ወይም የፅንሰ ሃሳብ አድልዖ (Conceptual bias) ይወስዳል፡፡ ብዙ ሰው ስለሚያደርገው ላድርገው ብዬ ማድረግ፣ ያለ ዝርዝር ብቆታ መርጬ ማየት፣ እኔ ነገሩ ገብቶኛል ብዬ ከመጀመሪያው የማየውን ነገርና የምሰማውን ወስኜ በራሴም ይሁን በሌሎች ትርጓሜ መጥኜ ማስቀመጥና የግል/የቡድን እሴቴን ወይም ሕልዮዬን የማየው/የምገነዘበው/ ጉዳይና ነገር ላይ በጫና ማሸጋገር ከእውነታው ስለሚያሸሹኝ አልጠለልባቸውም፡፡
ሁሉ ነገር ለደራሲ መረጃ ነው፡፡ መረጃ ስል በተጨባጭ የማየው (በራሴ የስሜት ህዋሶች)፣ ከሰው የምሰማው፣ የማነበው፣ በህልሜ የማየው፣ የምቃዠው ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኔ ክብደትና መራሂነት ያለው የመጀመሪያው ነው፡፡ አንዳንድ የመረጃ አንኩዋሮች ጥቅጥቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እሴታቸው ቸኩሎ ላይከሰት ይችላል፡፡ ዛሬ ያነጫነጨኝ ልምድ ነገ ሊያስቀኝ ይችላል፡፡ ትናንት አደገኛ ያልመሰለህ ልምድ ቆይቶ አደገኛነቱ ይከሰታል፡፡ ዛሬ አደገኛ የመሰለ ልምድ ነገ ምቹ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንዳንዱ ተራ የመሰለ ተፅዕኖ ወደ ድንጋግ የለሽ (ዳርቻ የለሽ) መረጃ ሊፈነዳ ይችላል፡፡ የማደርገው ከፈነዳ በሁዋላ የተበታተኑ የኩነት ፍንጣሪዎችን ወይም ዛላዎችን በማያያዝ መስራት ነው፡፡ …

ቅርፅና ይዘትን በተመለከተ
ዘመናዊ ደራሲዎች በየትም አገር በተለያየ መልክ የአገራቸውን የጥንት ተረቶች ለድርሰቶቻቸው ቅርፅና ይዘት መስሪያ ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ይሄ መሸጋገር (translation) ብዙ ጊዜ ግን ከትረካ ወደ ትረካ ነው፡፡ ከድርሳን ወደ ድርሳን ነው፡፡ ከተረት ወደ ተረት ነው፡፡
“ግራጫ ቃጭሎች” የተባለው የመጀመሪያ ልብወለድ እዚህ ይመጣል፡፡ ይሄ መጽሐፍ ዋናውን ታሪክ በሚያጅቡ ንዑስ ታሪኮች በህዳግ ማስታወሻዎች፣ በቁርጥራጭ መረጃዎች፣ በአንዳንድ  የቁዘማ ውጤቶች አጀብ የተሰራ ነው፡፡ ይሄ ቅርፅን ለማደን መጣር አይደለም፡፡ ሁልጊዜ በደቡላወዊ (dualistic) ስልት ስለምናስብ እንጂ፣ ቅርፅና ይዘት የተናጠል ቦታ የላቸውም፡፡ እዚያና እዚህ አይደሉም፡፡
አንድ ላይ የሚተገበሩ ናቸው፡፡ በፍልስፍናም ይሁን ሃይማኖቶቻችን በምድራሶቻቸው (hermeneutics) ሁልጊዜ ባለቤትና ተሳቢ (Subject – object) ክፍፍል ላይ ስለሚያተኩሩ ከዚያ የተበደርነው ይሆናል፡ እንጀራ ጠንካራ የልዋጭነት እሴት አለው (metaphorical value)፡፡ ለመፃፊያ ሞዴልነት ለመጠቀም ይመቻል፡፡
ሞዴል ሲደረግ ከእንጀራነት ይላቀቅና ንፁህ ጂኦሜትሪ ይሆናል፡ ብዙ ጊዜ ሞዴሎች ከሚያጠኑት ጉዳይ የበለጠ ወይም የሚስተካከል ውስብስብነት ይኖራቸውና ራሳቸው መልሰው ችግር ይሆናሉ፡፡ እንጀራ እንደ ሞዴል የቀላልነቱ ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፡፡
1/እንጀራ የተሟላ አይነት ውክልና አለው፡፡ ይታያል (እንደ ስዕል)፣ ይነካል፣ ይቀመሳል፣ እናም ይበላል፡፡ የመጨረሻው ፀባዩ የተለየ ያደርገዋል፡፡ እንደ ብዙ ቁሳቁስ በሩቅ የሚታይ አይደለም፡፡ ከሳብጀክቱ (የሰው ልጅ) ጋር ይዋሃዳል (embodied)፡፡
2/ የትውስታም ሰሌዳ ነው፡፡ አርኪዮሎጂስቶች በጥንት ጊዜ የተሰራ ቁስ አግኝተው በመሳሪያቸው መርምረው የእነዚህን ቁሶች ምንነታቸውን ያነባሉ፡፡ ተፎካካሪ ወይም የሚጋጭ ትርጉም ቢሰጣቸውም መረጃ ይሆናሉ፡፡ አፄ ሰንደቅአላማ የፈጠረው ጤፍ ተፎካካሪዎች የሚሻሙበት ጽላት (Icon) ነው፡፡ እንጀራ በሆነ መልክ ወገናዊነትን ያመልጣል፡፡ ተፎካካሪዎች ሁለቱም ይሽቱታል፡፡ በልቶ የማያድር የለም፡፡ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ሲጠፉ፣ ሲቃጠሉ፣ ሲዘረፉ፣ ከቦታ ቦታ ተላልፈው ሲጠፉ፣ እንጀራን ማንም ሊያሸሸው ባለመቻሉ እዚህ ደርሷል፡፡ ብዙ ዘመን የኖረው ሰንደቅአላማ መቃብር ላይ መገኘቱ ረዥም ዕድሜ ከእሱ መዋሱ ምሳሌ ይሆን?
በአሁኑ ወቅት ለምሰራው ስራ መረጃ ስለምፈልግ ብዙ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ ነበርኩ፡፡ የግጥም ባሕር፣ የመጣጥፍ ሃይቅ በዛ አለ፡፡ ፌስ ቡክ በመጠቀም ብቸኛ ደራሲ መሆኔን አንተ ነህ የነገርከኝ፡፡ “ፍሬንዶች” ለሚያቀርቡልኝ አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ግን ብዙ ጊዜ አረፍዳለሁ፡፡ ከእኔ ይልቅ የአገራችንን ስነፅሁፍ ወደ መርበትብተ - ኤሌክትሮኒክ ያመጡት ወጣቶች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የእነሱ የድርጊት ሕልውና ስለሚቀድም ልፋታቸው የገነነ ነው፡፡ ስለ ራሴም እንዳውቅ ገፋፍተውኛል፡፡ ልክ እንደ ጠንቋይ፣ ደራሲ ስለራሱ አያውቅም፡፡
ምናልባት ወጣቶቹ የበዙት ደራሲያን ማንሳት ይገባቸዋል የሚሏቸውን እስከ ዛሬ የተሳቱ ጉዳዮች ስላነሳሁ ይሆናል፤ ወይም ገና ወጣትነቴ አልከሰመምና (እስከ አሁን ድረስ ከምኑም ከምኑም እየተላተመ መጥቶ ከተረፈ፣ በተአብነት ይመዘገባል) እኔን የሚመዘምዘኝ ጉዳይ እነሱንም ይመዘምዝ ይሆናል፡፡ እነዚህ ግምቶቼ ናቸው፡፡ በግምት ደግሞ እርቀት አይኬድም፡፡

ስለአስገራሚ ገጠመኙ
በብዙ ነገር ተገርሜ የጨረስኩ ይመስለኛል፡፡ ድሮ የገረሙኝ ነገሮችን ዛሬ ሳስባቸው ለዛሬ አስገራሚ ሆነው አይታዩኝም፡፡ የሚያስቅ? ሎል (lol) ከመጣች ጀምሮ መንተክተክ ሳይቀንስ አልቀረም? (ለማሾፍ ይፈቀድልኛል?)  

Monday, 03 November 2014 08:17

እስቲ ይሞክሩት

እስቲ ይሞክሩት
1. ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ (IMF)
ዋና መ/ቤት የት ነው የሚገኘው?
2. ፒልስነር ቢራ የተፈጠረበት አገር
የት ነው?
3. ስክሪው ድራይቨር የሚባለው
ኮክቴል የሚሰራው በምንድነው?
4. እ.ኤ.አ በ1925 ጆን ሎጊ ባየርድ
የፈለሰፈው ምንድነው?
5. ወደ ጨረቃ የመጀመርያውን
የስልክ ጥሪ ያደረገው ማነው?

መልስ
1. ዋሺንግተን ዲሲ
2. ቼክ ሪፐብሊክ
3. በቮድካና በብርቱካን ጭማቂ
4. ቴሌቪዥን
5. ሪቻርድ ኒክሰን

Monday, 03 November 2014 08:15

የፍቅር ጥግ

መዝፈን ህይወቴ ነው፡፡ እስከዛሬም ህይወቴ ነበር፡፡ ወደፊትም ህይወቴ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሴሊያ ክሩዝ
የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው መዝፈን የጀመርኩት፡፡ በአካባቢያችን ስትራትፎርድ አይዶል በተባለ የዘፈን ውድድር ውስጥ ገባሁ፡፡ ሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የአዘፋፈን ትምህርትና የድምጽ ስልጠና ይወስዱ ነበር፡፡ በወቅቱ እምብዛም ከቁምነገር ስላልቆጠርኩት ቤት አካባቢ ብቻ ነበር የምዘፍነው፡፡ ገና 12 ዓመቴ ነበር፤ እናም ሁለተኛ ወጣሁ፡፡
ጀስቲን ቢበር
የሻማ መደብሩ ሲቃጠል ትዝ ይለኛል፡፡
ሁሉም ዙሪያውን ቆሞ “መልካም ልደት” የሚለውን መዝሙር ሲዘምር ነበር፡፡
ስቲቨን ራይት
ከመዝፈን የሚሻል ብቸኛ ነገር የበለጠ መዝፈን ነው፡፡
ኢላ ፊትዝገራልድ
በዓለም ላይ ትልቁ መግባቢያ ሙዚቃ ነው፡፡ ሰዎች የምታቀነቅንበትን ቋንቋ ባይረዱት እንኳን ሸጋ ሙዚቃን ሲሰሙ ያውቁታል፡፡
ሌዩ ራውልስ
ፀሐይ ስትጠልቅ ከተመለከትክ፣ አንድ ትርጉም ሊኖረው ይገባል? አዕዋፍ ሲዘምሩ ከሰማህ፣ መልዕክት ማስተላለፍ አለበት?
ሮበርት ዊልሰን
ዘፈን ሁልጊዜም እጅግ ትክክለኛው ሃሳብን የመግለጫ መንገድ ነው፡፡ በጣም ግብታዊ ነው፡፡ ከዘፈን ቀጥሎ ደሞ ቫዮሊን ይመስለኛል፡፡ እኔ መዝፈን ስለማልችል ሸራዬ ላይ እስላለሁ፡፡
ጆርጂያ ኦ’ኪፌ
በዝናብ ውስጥ እየዘፈንኩ ነው፤ ዝም ብዬ በዝናብ ውስጥ እየዘፈንኩ፡፡ እንዴት ደስ የሚል ስሜት ነው! አሁንም እንደገና ደስተኛ ነኝ፡፡
አርተር ፍሪድ