Administrator

Administrator

በወቅታዊ የመብት ጥሰቶች ዙሪያ የሰራውን ጥናት ይፋ አድርጓል

መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን አስታወቀ፡፡ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ቢሆንም የአገሪቱ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ግን እየተባባሱ ቀጥለዋል ያለው ሲፒጄ፣ ይፈጸማሉ ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያ የሰራውን ጥናት በትላንትናው ዕለት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ያወጣቸውን ህጎች ከቅርብ አመታት ወዲህ ዜጎችን በሚጨቁን መልኩ ያለአግባብ እየተጠቀመበት ነው ያለው ሲፒጄ፤ መንግሥት በሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ በፕሬስ ነጻነትና በዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጥሰት እየፈጸመ ነው በሏል፡፡
በጸረ-ሽብርተኝነት ህግ ሽፋን ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ቁጥር እያደገ ነው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር እንዳይችሉ ተደርገዋል ሲል ኮንኗል - ሲፒጄ፡፡
“ቶም ላንቶስ ሂውማን ራይትስ ኮሚሽን” የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በሚገኘው ሬይበርን ሃውስ አዳራሽ ባዘጋጀው የመወያያ መድረክ፣ በአገሪቱ ይፈፀማሉ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የሚዳስስ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሱኢ ቫለንታይን የተሰራው ጥናት፤ በኢትዮጵያ መንግስት ይፈፀማሉ የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖችን እንቅስቃሴ የመገደብ፣ መገናኛ ብዙሃንን የመጨቆንና በልማት ፕሮጀክቶች ሰበብ የነዋሪዎችን ሰብዓዊ መብት የመጣስ ድርጊቶች ያብራራል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ በየዓመቱ የ800ሚ. ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ የጠቆመው ሲፒጂኤ፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በመጠቀም ድጋፉ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይውልና መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር ተፅእኖ ማድረግ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጿል፡፡
በውይይት መድረኩ የፓርላማ አባላት፣ የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ተወካዮች፣ ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደተሳተፉበት ሲፒጂ ጠቁሟል፡፡

          አፍሪካን ሰርቪስ ኮሚቴ ለ25 ችግረኛ እናቶች፤ እንጀራ ጋግረው መሸጥ እንዲችሉ ከጤፍ ጀምሮ የሚያስፈልጉትን ጠቅላላ ጥሬ እቃዎች በማሟላት ከትላንት በስቲያ ሾላ አካባቢ በሚገኘው ክሊኒኩ ውስጥ አስረከበ፡፡
ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ለእነዚህ እናቶች ሁለት ኩንታል ጤፍ፣ የኤሌክትሪክ ምጣድ፣ የዱቄት ማስቀመጫ በርሜል፣ የሊጥ ማቡኪያና የውሃ ባልዲ፣ የአብሲት መጣያ ብረት ድስት፣ ጆግና ማስታጠቢያ፣ ማሰሻ ጨርቅ፣ ጎመን ዘር፣ መሶብ፣ እንቅብና የእንጀራ ማውጫ ሰፌድ በነፍስ ወከፍ ተከፋፍሏል፡፡
ተረጂዎቹ በጨረቃ ቤት፣ በዘመድ ቤትና ባስጠጓቸው በጎ ሰዎች ቤት የሚኖሩ በመሆናቸው የመጀመሪያ ወር የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ለእያንዳንዳቸው 300 ብርና የተረከቡትን እቃ የሚያጓጉዙበት የትራንስፖርት ወጪ ሁለት መቶ ብር ተሰጥቷቸዋል፡፡
አፍሪካዊ ስደተኞችን ለመርዳት ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው አቶ አስፈሃ ሃደራ በተባሉ ግለሰብ አሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ የተቋቋመው “አፍሪካን ሰርቪስ ኮሚቴ” ከ10 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ተከፍቶ ሥራ የጀመረ ሲሆን ክሊኒኩ የምስጢር ኤችአይቪ ምርመራ፣ የፀረኤችአይቪ (ART) ስርጭት፣ የቲቢ እንዲሁም የአባላዘር በሽታ ምርመራና ህክምና በመስጠት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንን ሲያገለግል መቆየቱን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሪት ሃና ወ/ገብርኤል ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት የክልል ከተሞች በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ በመቀሌ በዝዋይ እንዲሁም በሃሳዋ የጤናና የማህበረሰብ ልማት ማዕከል በማቋቋም፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም እናቶችና ህፃናትን በማገልገል ላይ መሆኑን ወ/ሪት ሃና አብራርተዋል፡፡
ድርጅቱ ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ላለባቸው ህፃናት የወተትና የአልሚ ምግብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ18 ዓመት በታች ላሉ ህፃናትና ታዳጊዎች አሜሪካ ከሚገኝ “ቶምስ ሹ” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር በዓመት ሁለት ጊዜ የጫማ  የትምህርት መሳሪያዎችና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ከትላንት በስቲያ ችግረኛ እናቶች የገቢ ማስገኛ ስራ እንዲሰሩ ለተደረገው የጥሬ እቃና የገንዘብ ድጋፍ አገር በቀልና የውጭ ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው የተገለፀ ሲሆን “በፔፕፋር ስሞምል ግራንት ፕሮግራም” በኩል የአሜሪካ ኤምባሲ የ30 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡ እስከዛሬ ለድርጅቱ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ዲኬቲ ኢትዮጵያ፣ አይካፕ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ ኤምባሲ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማህበራት ኤጀንሲ እንዲሁም ድርጅቱ የሚንቀሳቀስባቸው የክልል መንግስታት የወረዳና የዞን ቢሮዎች በእለቱ ተመስግነዋል፡፡ በእለቱ የአንበሳ ማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ድርጅት ባለቤትና “የትውልዱ አምባሳደር” አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁና አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በክብር እንግድነት ተገኝተው ስለ ድርጅቱ እንቅስቃሴ የተሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥሬ እቃ ድጋፉን የተረከቡት 18 እናቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሰባት እናቶች በሌላ ድርጅት መደገፍ አለመደገፋቸው ተጣርቶ እቃቸውን መረከብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
አርቲስት ዳንኤል ተገኝና አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ ለገና በዓል ለተረጂዎቹ የተወሰነ ስጦታ ለማበርከት ቃል እንደገቡም ታውቋል፡፡

ሽልማቱን ላለፉት 3 ተከታታይ አመታት ተቀብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በያዝነው ሳምንት በአልጀርስ በተካሄደው የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር 46ኛ አመታዊ ጉባኤ ላይ፣ የአመቱ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተብሎ መሸለሙን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ለአመቱ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማት የበቃው በ2013 የበጀት አመት ባስመዘገባቸው ከፍተኛ ውጤቶች፣ ዘላቂነት ባለው ትርፋማነቱ እና ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ለመስራት በሚያስችለው አግባብነት  ያለው ስትራቴጂው እንደሆነ ገልጾ፣ ይህንን ሽልማት ላለፉት ሶስት አመታት በተከታታይነት እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ ሽልማቱን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር አየር መንገዱ ለዚህ ሽልማት በመብቃቱ ኩራት እንደሚሰማው ገልጸው፣ ለዚህ ስኬት መሰረቱ ከ8ሺህ በላይ የሚሆኑ ጠንካራ ሰራተኞቹ ትጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  • በሽታው በፍጥነት ህክምና ካላገኘ ለሞት ሊዳርግ ይችላል
  • የበሽታው ምልክቶች ከአሜባ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው
  • በሽታውን ለማከም ይሰጡ የነበሩት መድሃኒቶች ከባክቴሪያው ጋር ተላምደዋል


             “የምግብ ፍላጐቷ እየቀነሰ፣ ሰውነቷ እየከሳና እየደከመ ሲሄድ ሃሳብ ገባኝ፡፡ በየዕለቱ ምግብ በቀመሰች ቁጥር ሽቅብ ሲተናነቃት ስመለከት ደግሞ ልቤ ሌላ ነገር ጠረጠረ፡፡ ምልክቶቹ በአብዛኛው ከእርግዝና ምልክቶች ጋር የሚመሳሰሉ በመሆናቸው ሁኔታዋ እጅግ አስደነገጠኝ፡፡
ሁለታችንም ከወላጆቻችን ጋር አብረን የምንኖርና የመሰናዶ ተማሪዎች በመሆናችን በዚህ ሁኔታና በዚህ ዕድሜዋ ማርገዟ አሳዘነኝ፡፡ ምንድነው የማደርገው? ወላጆቻችንስ እንዴት ነው የሚነገራቸው? የሚለው ሃሳብ እንቅልፍ ነሣኝ፡፡ በሁለት ዓመት የምበልጣት ታላቋ ብሆንም እንደ እኩያዬ ነበር የማያት፤ የምትደብቀኝም ሆነ የምደብቃት ሚስጢር አልነበረም፡፡ አሁን ግን ድብቅ የሆነችብኝ መሰለኝ፡፡ ነገሩን ለማውጣጣት ያላደረግሁት ሙከራ አልነበረም፡፡ ሆኖም ምንም ፍንጭ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆዷ እንደ ከበሮ እየተነፋና እየተወጠረ ሄደ፡፡ ከእንብርቷ በታችም ከፍተኛ ስቃይ ያለው ህመም እንደሚሰማትም ነገረችን፡፡ የምግብ ፍላጐቷ ጨርሶውኑ በመጥፋቱ ሚሪንዳና ጭማቂዎችን ትንሽ ትንሽ ልንሰጣት ሞከርን፡፡ የምትወስደው ምግብ ሁሉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ይወጣል፡፡ ሠገራ መቀመጥ ስቃይ ሆነባት፡፡ ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ ወደ ዩኒቨርሳል ክሊኒክ ይዘናት ሄድን፡፡ በክሊኒኩ በተደረገላት ምርመራም የአንጀት ቁስለት በሽታ እንዳለባትና የአንጀቷ ግድግዳዎች ክፉኛ መጐዳታቸው ተነገረን፡፡
በሽታው ያለበት ደረጃ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑም አስቸኳይ ህክምና ሊደረግላት እንደሚገባ ተነገረን፡፡ በዚህ መሰረትም ህክምናውን ማድረግ ጀመረች፡፡
“በሽታው ሥር የሰደደ በመሆኑና የአንጀቷን አብዛኛውን ክፍል በማጥቃቱ በቀላሉ ሊድን አልቻለም፡፡ ለሁለት ሳምንታት ህክምናው ሲደረግላት ብትቆይም አልዳነችም፡፡ ገና በ18 ዓመት ዕድሜዋ ህይወቷ አለፈ፡፡
“የእህቴን ሞት ባሰብኩ ቁጥር እጅግ የሚፀፅተኝ ችግሯን ቶሎ አውቀንላት ወደ ህክምና ልንወስዳት አለመቻላችን ነው፡፡ ስለ በሽታው ምልክቶች ቀደም ብዬ ባውቅ ኖሮ እርግዝና ነው ከሚለው ጥርጣሬዬ ተላቅቄ፣ እህቴ በወቅቱ ህክምና እንድታገኝና ህይወቷ እንዲተርፍ  ልታደጋት እችል ነበር፡፡” ይህንን አሳዛኝ ታሪክ የነገረችኝ በቅርቡ ታናሽ እህቷን በሞት የተነጠቀችው ትዕግስት መንግስቴ ናት፡፡ ህክምና በወቅቱ ባለማግኘቷ የተነሳ በሽታው የአንጀቷን አብዛኛውን ክፍል ጐድቶ ለሞት እንደዳረጋት እህቷን የመረመራት ሐኪም እንደነገራቸው ገልፃልኛለች፡፡
ለመሆኑ የትልቁ አንጀት ቁስለት በሽታ ምንድነው? ምልክቶቹና መንስኤዎቹስ ምንድናቸው? ህክምናውስ የሚለውን ጉዳይ እንዲያብራሩልን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑትን ዶክተር ታዲዮስ መንከርን አነጋገርናቸዋል፡፡
1.5 ሜትር ርዝመት ያለውና በትንሹ አንጀታችን ዙሪያ የሚገኘው ትልቁ አንጀት የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን በአግባቡ እንዲሆን የሚያደርግና ከጨጓራ ተፈጭቶና ልሞ ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚሰራጩት ምግቦች ውስጥ በቆሻሻነት የሚወገዱትን ወደ ታች ገፍቶ በሰገራ መልክ የሚያስወግድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከቆሻሻው ውሃንና አንዳንድ ጠቃሚ ንጥረነገሮችን መጥጦ ወደ ደም እንዲገቡ ያደርጋል፡፡
ትልቁ አንጀታችን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስበትና አየርና አይነምድርን ቋጥሮ ሲይዝ፣ ድንገት ሆዳችን ይወጠርና ግሣትና እረፍት የለሽ ስቃይ ይገጥመናል፡፡ ይህ አይነቱ ችግር በሚከሰትበት ወቅት ታማሚው አስቸኳይ የቀዶ ጥገና ህክምና ካላገኘ ህይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለ በሽታው ምንነትና መንስኤዎቹ ዶክተር ታዲዎስ ከዚህ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

ለአንጀት ጤና ችግር መነሻው
የትልቁ አንጀት መኮማተር
ይህ አይነቱ የጤና ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው በወጣትነትና በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ውጥረት፣ ጭንቀትና እረፍት የለሽ ህይወት ለዚህ ዓይነቱ የጤና ችግር ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡
ኢንፌክሽን
በቫይረስ፣ በባክቴሪያና በተለያዩ ጥገኛ ህዋሳቶች አማካኝነት አንጀታችን ሲመረዝ፣ የአንጀት ቁስለት ይከተላል፡፡ ይህም አንጀት ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን በማድረግ አጣዳፊ የሆድ ውስጥ ህመም፣ ማስመለስና ማቅለሽለሽ እንዲሁም ትኩሳትና ድካም ያስከትላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ችግር የሚከሰተው በአብዛኛው ንፅህናቸውን ባልጠበቁ ምግቦች ውሃ ሳቢያ ነው፡፡
የትልቁ አንጀት ቁስለት
በሰውነታችን ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ኢንፌክሽን በሚፈጠርበት ወቅት ሰውነታችን ኢንፌክሽኖቹን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ተፈጥሮአዊ ትግል አንጀታችን ለጉዳት ሊዳርገው ይችላል፡፡ ይህም የአንጀት ጉዳት ትልቁ አንጀታችን እንዲላጥና እንዲቆስል በማድረግ ለህመም ሊዳርገን ይችላል፡፡ የአንጀት ቁስለት ህመም አልፎ አልፎ በዘር ሊከሰትም ይችላል፡፡
የአንጀት ካንሰር
ይህ አይነቱ የአንጀት ህመም እጅግ አደገኛና ከጡት፣ ከማህፀንና ከሳንባ ካንሰር ቀሎ ብዙዎችን ለስቃይና ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ በሽታው ዕድሜያቸው ከአርባ አመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል፡፡
ጮማና ስብነት ያላቸውን ምግቦች መመገብ የሚያዘወትሩ፣ በሽታው በቤተሰባቸው ውስጥ ያለባቸውና በሆዳቸው አካባቢ የጨረር ህክምናን የወሰዱ ሰዎች ለዚህ ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡
የፊንጢጣ ኪንታሮት
በፊንጢጣ አካባቢ በሚገኙ የደም ስሮች ማበጥ ሳቢያ የሚከሰት ችግር ሲሆን ችግሩን ሰገራ ለመውጣት ማማጥ፣ ለረዥም ጊዜ መቆም፣ በሙቀት ውስጥ ለረዥም ሰዓት መኪና ማሽከርከርና እረፍት ማጣት ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡ የሆድ ድርቀትም በሽታውን ሊያባብሱት ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
የምግብ መመረዝ
በተለያዩ ለጤና ጎጂ በሆኑ ባክቴሪያዎች የተመረዙ ምግቦችን በምንመገብበትና የተበከለ ውሃን በምንጠጣበት ወቅት ተህዋስያኑ ወደ አንጀታችን ውስጥ በመግባት አጣዳፊ የሆድ ህመምን፣ ማስመለስንና ተቅማጥን ሊያመጡብን ይችላሉ፡፡ ይህ ችግርም በወቅቱ ህክምና ካላገኘ  ተባብሶ አንጀታችንን በማቁሰል ለአንጀት ቁስለት ሊዳርገን ይችላል፡፡
ምልክቶቹ
የትልቁ አንጀት ህመም ውስጣዊና ውጫዊ ምልክቶች አሉት፡፡ አንድ ሰው የትልቁ አንጀት ቁስለት እንዳለበት ጠቋሚ ከሆኑት ምልክቶች መካል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው:-
ውስጣዊ ምልክቶች
ከእንብርት በታች ሃይለኛ ስቃይ ያለው የህመም ስሜት
ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና፣ የድካም ስሜት
የሆድ መነፋት፣ መጮህና የሆድ ድርቀት
የፈስ መብዛት፣ ማስማጥና በፊንጢጣ ደም መውጣት
ውጫዊ ምልክቶች
በቆዳ ላይ እጅብ ያለ ሽፍታ መውጣት
በተለያዩ የሰውነት ክፍሎችና በአጥንት መገጣጠሚያዎች ላይ እብጠት
ክብደት መቀነስ፣
የሆድ መነፋት ወይም ግልፅ ሆኖ የሚታይ የሆድ መነረት ናቸው፡፡
ትልቁ አንጀትን የሚያጠቁት በሽታዎች በርካቶች ቢሆኑም በአገራችን በብዛት የተለመዱትና ለበርካቶች ህመምና ሞት ምክንያት የሚሆኑት ቀደም ሲል የተዘረዘሩት ሲሆኑ የአንጀት ካንሰር  በገዳይነቱ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል፡፡
ስብና ፕሮቲን የበዛባቸውን ምግቦች አዘውትረው የሚመገቡ፣ በተፈጥሮ የአንጀት ቁስለትና አንጀት ላይ የሚፈጠሩ ትናንሽ እብጠቶች ያሉባቸው ሰዎችን በይበልጥ የሚያጠቃው ይህ በሽታ፤ ወደተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች የሚሰራጭና የማይሰራጭ አይነቶች አሉት፡፡ በአገራችን በስፋት የሚታየው በሰውነት ውስጥ የሚሰራጨው አይነቱ ካንሰር ነው፡፡ የትልቁ አንጀት ካንሰር ምልክቶች አሜባ እየተባለ ከሚጠራው በሽታ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ማስማጥ፣ ደም የተቀላቀለበት ተቅማጥ፣ የሆድ ህመምና ቁርጠት በሁለቱም በሽታዎች ላይ የሚታዩ ሲሆን አሜባ በአጭር ጊዜ ህክምና መዳን መቻሉና በሰገራ ምርመራ የበሽታው ምንነት መታወቁ ከአንጀት ካንሰር ይለየዋል፡፡
የትልቁ አንጀት ካንሰር በአገራችን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ የተደረጉ ጥናቶች አለመኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ታዲዮስ መንክር፤ ከሆስፒታሎች የሚገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በጉልምስና ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የበሽታው ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡
የተሟላና የተጠናከረ መረጃ የመያዝ ልምድ ባለመኖሩ ትክክለኛውን የአንጀት ቁስለት በሽታ ታማሚዎች ቁጥር ለይቶ መናገር አስቸጋሪ እንደሆነም ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡
የሽንት ቱቦ፣ የፊኛና የማህፀን ካንሰር ምልክቶች ከትልቁ አንጀት ካንሰር በሽታ ጋር የመመሳሰል ባህርይ ስለአላቸውም አንዳንድ ጊዜ በምርመራ ወቅት የጤና ባለሙያዎችን ሊያሳስቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ባለሙያዎች የትልቁ አንጀት ካንሰር ምርመራን በሚደርጉበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል ሲሉ ዶክተሩ አሳስበዋል፡፡ አንድ ሰው የአንጀት ካንሰር በሽታ ምርመራ ተደርጎለት በሽታው መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በሽታው በሰውነቱ ውስጥ ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩ ሌሎች ምርመራዎች ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህም በሽታው የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹን መንካት አለመንካቱን ለማወቅ ይጠቅማል፡፡ በዚህም በሽታው ያለበትን ደረጃ ማወቅና የህክምናውን ዓይነት መወሰን ይቻላል፡፡  የህመምተኛውን የመዳን እድል ለማወቅም ይረዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለአንጀት ቁስለት ህመም በስፋት የሚታዘዘው መድኀኒት Amoxicillin የተባለው ሲሆን Omepazole እና Clarithromycine የተባሉት መድኀኒቶችም በሽታውን ለማከም አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ቀደም ሲል የአንጀት ቁስለት ህመም መድኀኒት የነበሩት Tetracycline እና Metronidazole (ሜዝል) እየተባሉ የሚጠሩትን መድኀኒቶች የአንጀት ቁስለት አምጪ ባክቴሪያዎች ስለተለማመዷቸውና መድኀኒቶቹ በሽታውን የማዳን ኃይላቸውን በማጣታቸው ምክንያት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እየተደረገ መሆኑን ሃኪሙ ተናግረዋል፡፡
ህክምናው
የቆሰለው የአንጀቱ ክፍል የሚደማ ከሆነ በኢንዶስኮፒ የሚደማውን ቦታ በማከም፣ ደሙን ማቆም፡፡
ህመምተኛው ደም የሚያንሰው ከሆነ፣ የደም ዓይነቱን በመለየት ደም እንዲሰጠው ማድረግ፡፡
ለቁስለቱ መነሻ ምክንያቱ ባክቴሪያ ከሆነ፣ ባክቴሪያውን የሚያጠፉ መድሃኒት መስጠት፡፡
ህመምተኛው የመጠጥ፣ የጫትና የሲጋራ ሱስ ካለበት ሱሱን እንዲያቆም ማድረግ፡፡     

በሰው ልጆች አመጣጥ ጥናት መስክ ውስጥ አለማቀፍ ቁልፍ ግኝት እንደሆነች የሚነገርላት ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሬተ-አካል በአፋር ክልል ሃዳር የተባለ አካባቢ በቁፋሮ የተገኘበት 40ኛ ዓመት በያዝነው ወር በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ እንደሚከበር ሳይንስ ኒውስ ድረገጽ ዘገበ፡፡
ዶናልድ ጆንሰን እና ቶም ግሬይ በተባሉ አንትሮፖሎጂስቶች እ.ኤ.አ በ1974 የተገኘችውና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አመታት በፊት በሁለት እግሮቿ ትራመድ  የነበረችው ሉሲ፤ የሰው ልጆችን አመጣጥ በተመለከተ ቀደም ብሎ የነበረውን አስተሳሰብ የቀየረችና ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያረጋገጠች ታላቅ ግኝት መሆኗን ዘገባው አስታውቋል፡፡
ሉሲ ከመገኘቷ በፊት “የሰው ልጆች መገኛ አውሮፓ ነው አፍሪካ?” የሚል ክርክር እንደነበር ያስታወሱት የግኝቱ ባለቤትና በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጆች መገኛዎች ኢንስቲቲዩት መስራችና ዳይሬክተር ዶናልድ ጆንሰን፤ የእሷ መገኘት በመስኩ የነበረውን አመለካከት በወሳኝነት እንደቀየረው ለዘ ታይምስ ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
ሉሲ በአንትሮፖሎጂ የጥናት መስክ ቁልፍ ሚና እንዳላት የገለፁት ዶናልድ፤ የሰው ልጆች አመጣጥ ታሪክን የቀየረችው ሉሲ የተገኘችበት 40ኛ ዓመት በዚህ ወር በዩኒቨርሲቲው በሚካሄዱ ውይይቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በጤናው ዘርፍ የምእተ አመቱ ግብ ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደውጭው አቆጣጠር በ2020/ዓም ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚለው አንዱ ሲሆኑ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በተግባር ላይ ውለዋል ከእነዚህም መካከል፡-
በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በጋራ መስራት፣
የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የPMTCT አገልግሎትን እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣
አገልግሎቱን በሚመለከት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣
የሚሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል የPMTCT (Prevention of mother-to-child transmission) አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የግል እንዲሁም የመንግስት የህክምና ተቋማት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተለይም ከግል የህክምና ተቋማት ጋር በመተባበር ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን ተግባር በመከወን ላይ ያለ ሲሆን በዛሬው ፅሁፋችን የምንመለከተው ግን በደሴ ከተማ ተገኝተን አገልግሎቱ በመንግስት የህክምና ተቋማት በምን መልኩ እንደሚሰጥና ለግል የህክምና ተቋማቱ ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍ የሚመለከት ነው፡፡
ሮዛ ሽፈራው በደሴ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ መምሪያ የአገልግሎቱ አስተባባሪ ኦፊሰር ናቸው፡፡ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የግል የህክምና ተቋማት ከመንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይገልፃሉ፡፡ ምንም እንኳን በተወሰነ መልኩ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ቢኖርም መንግስት ከተቋማቱ ለሚደርሰው የቁሳቁስ እንዲሁም የሙያ ድጋፍ ጥያቄ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡ ምን ያህል እናቶች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“...አሁን ባለው ሁኔታ በግል የህክምና ተቋማቱ አገልግሎቱን የሚጠቀሙት ታካሚዎች ከተለያየ ቦታ ነው የሚመጡት አንዳንዶቹ ምጥ ይዟቸው በመጡበት ሰአት ፖዘቲቭ የሚሆኑበት ግዜ አለ አንዳንዴ ደግሞ ፖዘቲቭ ሆነው መጥተው የሚወልዱበትም ሁኔታ አለ፣ ብዙዎቹም ከተለያየ ቦታ ይመጣሉ፣ ከአፋር ክልል ጀምሮ ከሰሜን ወሎ ከሌላም     ቦታ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎቹን ቁጥር በውል ለማወቅ  ያስቸግራል፡፡”
ለህክምና ተቋማቱ የምታደርጉት የቁሳቁስም ሆነ ሌሎች ድጋፎች በትክክል ለተጠቃሚዎቹ መድረሳቸውን በምን መንገድ ታረጋግጣላችሁ? ቀጥለን ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡
“...ያው ምርመራ ያደረጉትን ታካሚዎችን ለማየት እንሞክራለን ግን ምርመራን ያደረጉት ሁሉ ፖዘቲቭ ላይሆኑ ይችላሉ በዋናነት ግን ምን ያህል ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን አውቀዋል የሚለውን እናያለን፡፡ ምን ያህሉን PMTCT አገልግሎት ላይ አዋሉት የሚለውንም እንመለከታለን፡፡ አንዳንድ ግዜ እጥረት የሚፈጠረው ለሌላም     ስለሚጠቀሙበት ይሆናል ብለን እንገምታለን።”
አያይዘውም በመንግስት የህክምና ተቋማት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል በሚመለከት ማንኛዋም አገልግሎቱን ፈልጋ የምትመጣ እናት የነፃ ህክምና ታገኛለች ብለዋል፡፡
“አንዲት እናት እኛ ጋር ስትመጣ ነብሰጡር ናት ተብሎ አገልግሎቱን ከጀመረችበት ግዜ አንስቶ እስከምትወልድ ግዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ አገልግሎት ታገኛለች፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ እንዲሁም ሌሎች ከእናቶችና ህፃናት ጋር ተያያዥ የሆኑ     አገልግሎቶችም በአብዛኛው ነፃ ናቸው፡፡”  
በመንግስት በኩል አገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀና በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተመርምሮ እራስን በማወቁ እንዲሁም እራስን ካወቁም በኋላ በግልፅ ለሌሎች በማሳወቁ እረገድ በርካታ ችግሮች አሉ ያሉን ደግሞ በደሴ ከተማ የቧንቧ ውኀ ጤና ጣቢያ የነብሰጡር ክትትልና የማዋለጃ ክፍል ውስጥ ሲሰሩ ያገኘናቸው ሲስተር ካሳነሽ ግዛው ናቸው፡፡
“...ብዙዎቹ እራሳቸውን አውቀውም እንኳን ቢሆን ግልፅ መሆን አይፈልጉም እራሳቸውን አውቀው መድሀኒት እየወሰዱ እኛ ጋር መጥተው ሲመረመሩ እንደ አዲስ ነው የሚሆኑት ቀድመው እያወቁት ይደብቃሉ፡፡”
በቅርብ የገጠመጥ ብለውም የሚከተለውን አጫውተውናል፡፡
“...አንዲት እናት ...ቀደም ሲል በወለደችበት ወቅት አሁን ያለው ኦፕሽን ቢ ፕላስ ስላልተጀመረ በምጥና በወሊድ ግዜ የሚሰጠውን መድሀኒት ሰጥተው ነው ያዋለዷት፡፡ ጤና ጣቢያ  ስትመጣ ኤችአይቪ መመርመር አለብሽ ብዬ የምክር አገልግሎት ስሰጣት ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ነገረችኝ፡፡ ከመቼ ጀምሮ ... ስላት ከሁለት ሺህ አመተምህረት ጀምሮ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ስለዚህ አሁን ቫይረሱ ወደ ልጅሽ እንዳይተላለፍ ጤነኛ ልጅ እንድትወልጂ መድሀኒቱን መጀመር አለብሽ ስላት ሲዲፎርሽ ዘጠኝ መቶ ነው ስላሉኝ መድሀኒት አልጀምርም ነው ያለችኝ፡፡ ይህ እንግዲህ ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ይህ መድሀኒቱን ለመጀመር መመሪያ ወይም ቅድመሁኔታ አይደለም፡፡ ሲዲፎር ቢወርድም ባይወርድም ኤችአይቪ በደምሽ ውስጥ እንዳለ ከታወቀና ነብሰጡር ከሆንሽ... ወዲያው ነው መድሀኒቱን መጀመር ያለብሽ ብዬ ስላት ባለቤቴን አማክሬ እመጣለሁ ብላ መድሀኒቱን ሳትይዝ ሄደች፡፡ ለእኔ ግልፅ ላለመሆን እንጂ መድሀኒቱን የምትወስድ ይመስለኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግሮች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ ብዙዎቹ የመኖሪያ አድራሻቸውን ካርዳቸው ላይ እንኳን ማስመዝገብ አይፈልጉም፡፡”
ምን ቢደረግ ነው ይህን ችግር ማስቀረት የሚቻለው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲ/ር ካሳነሽ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“...እንግዲህ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በየጊዜው በሚዲያ ይነገራል፡፡ በእኛም በኩል ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት በደንብ ነው የምክር አገልግሎት የምንሰጣቸው፡፡ መድሀኒቱ የእድሜ ልክ እንደሆነና ተጀምሮ መቋረጥ እንደሌለበት... ከተቋረጠ የቫይረሱ መጠን እንደሚጨምር እንዲሁም ወደ ልጁ የመተላለፍ እድሉም በዛው ልክ እንደሚጨምር እንነግራቸዋለን፤ ግን አሁንም ወደ ፊትም እኔ ለውጥ ያመጣል የምለው የmother support  ቡድኑ የሚሰራው ስራ ነው ምክንያቱም እነሱ ናቸው እታች ወዳለው የህብረተሰቡ ክፍል ወርደው ብዙውን ስራ የሚሰሩት ስለዚህ ያለን አማራጭ እነሱን ማጠናከር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”
ከሁሉም በላይ ግን ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የትዳር አጋሮች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ባለትዳሮች በጋራ ተመርምረው ውጤታቸውን ቢያውቁ አሁን እየታየ ባለው ለውጥ ላይ የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ሲ/ር ናሳነህ ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
“...ሚስቱ ለእርግዝና ክትትል ወደ ጤና ተቋም ስትሄድ ባልዋ ሀላፊነት ተሰምቶት ከእሷ ጋር አብሮ     ሄዶ የምክር አገልግሎት ሲደረግላት ስለ ኤችአይቪ ብቻም ሳይሆን ስለ    አመጋገብ ስለ ንፅህና ሌሎችንም ነገሮች እንመክራለን፡፡ ኤችአይቪም አብሮ ይመረመራል እዚሁ አብረው ተመርምረው ሚስት እንኳን ቢገኝባት የምክር አገልግሎት አግኝቶ ከሄደ ለመድሀኒቱ እንኳን ጫና አያሳድርባትም፡፡ አንቺ ነሽ ያመጣሽብኝ ምናምን     የሚለው ነገር አይኖርም፡፡ ዲስኮርዳንት ከሆኑም ወደፊት እንዴት አብረው መኖር እንዳለባቸው፣ አንዱ አንዱን እንዴት ከኤችአይቪ መጠበቅ እንዳለበት በዛው እናስተምራለን፡፡ እንደገና በእርግዝና ወቅት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዲሁም     እናቲቱ ነፃ ሆናም ከሆነም ከባል ወደ እሷ እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ አድርገው አንዱ ለአንዱ እንዲተሳሰቡ አብረው ስለሚመከሩ የትዳር አጋርም አብሮ ወደ ጤና ጣቢያ     ቢመጣ ለኤች አይቪ     ስርጭት መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡”
የባልና ሚስት ውጤት መለያየት በሚገጥምበትም ወቅት ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት መግታት ይቻላል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ተከታዩን መልእክት አስተላልፈዋል፡-
“...ኤችአይቪ በደም ውስጥ ባይገኝ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከተገኘ መንግስት አሁን አገልግሎቱን በነፃ እየሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ክትትል አድርገው ጤነኛ ልጅ ወልደው እንዲያሳድጉ ይመከራል ...መደባበቁ ጥቅም የለውም... በተለይም በደሴ ከተማ ኤችአይቪን በሚመለከት ግልጽነት ይጎድላል፡፡ ለመመርመር የሚመጡ እናቶች ሳይደብቁና ሳይሳቀቁ ግልፅ ሆነው መጥተው ቢስተናገዱ ለወደፊቱ ከኤችአይቪ ነፃ ሆነ     የሆነ ትውልድ ለማፍራት ይረዳል።”        

Saturday, 08 November 2014 11:41

የፍቅር ጥግ

በጥልቀት መፈቀር ጥንካሬ ሲሰጥህ፣ በጥልቀት ማፍቀር ፅናት ይሰጥሃል፡፡
ላኦ ትዙ
ሃዘን ለራሱ መሆን አያቅተውም፡፡ የደስታን ሙሉ ዋጋ ለማግኘት ግን አንድ የምታካፍለው ሰው ሊኖር ይገባል፡፡
ማርክ ትዌይን
ፍቅር ምን እንደሆነ ታውቃለህ ከተባልኩ ባንቺ የተነሳ ነው፡፡
ሔርማን ሄሲ
አንቺ ለእኔ ጣፋጭ ስቃይ ነሽ፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
ጨርሶ ሳያፈቅሩ ከመቅረት ይልቅ አፍቅሮ ማጣት ይሻላል፡፡
ሄሚንግ ዌይ
ብልህ ልጃገረድ ብትስምም አታፈቅርም፤ ብታዳምጥም አታምንም፡፡ ከዚያም ሳይተዋት በፊት ትታ ትሄዳለች፡፡
ማሪሊን ሞንሮ
እናም በመጨረሻ የወሰድከው ፍቅር ከሰራኸው ፍቅር ጋር እኩል ነው፡፡
ጆን ሌኖን እና ፓል ማእካርትኒ

Saturday, 08 November 2014 11:38

የፀሃፍት ጥግ

ያልበሰሉ ገጣሚዎች ሲኮርጁ፤ የበሰሉ ገጣሚዎች ይሰርቃሉ፡፡
ቲ ኤስ ኢሊዮት
ቤት የማይመታ ግጥም መፃፍ መረቡን አውርዶ ቴኒስ እንደመጫወት ነው፡፡
ሮበርት ፎርስት
አብዛኛው ሰው አብዛኛውን ግጥም ችላ የሚለው አብዛኛው ግጥም አብዛኛውን ሰው ችላ ስለሚል ነው፡፡
አድሪያን ሚሼል
ሥነግጥም፤ በአየር ላይ መብረር የሚመኝ፣ በመሬት ላይ የሚኖር የባህር እንስሳ ዜና መዋዕል ነው፡፡
ካርል ሳንድበርግ
በመጀመሪያ ራሴን እንደገጣሚ አስባለሁ፤ ቀጥሎ በሙዚቀኛነት፡፡ እንደ ገጣሚ ኖሬ እንደገጣሚ እሞታለሁ፡፡
ቦብ ዲላን
መጨረሻውን የማውቀው ግጥም ፈጽሞ ጀምሬ አላውቅም፡፡ ግጥም መፃፍ ግኝት ነው፡፡
ሮበርት ፍሮስት
ገጣሚ የምናባዊው ዓለም ቄስ ነው፡፡
ዋላስ ስቲቨንስ
ግጥም ሲገላለጥ የህይወት ሂስ ነው፡፡
ማቲው አርኖልድ
ገጣሚ፤ ራሱን ገጣሚ ብሎ የማይጠራ ማንኛውም ሰው ይመስለኛል፡፡
ቦብ ዲላን

    እናት የማስታወቂያ ድርጅት፤ “ትርጉም ያለው የንባብ ባህል ለወጣቶች ስኬታማነት” በሚል መርህ ዛሬ ረፋድ ላይ ተጀምሮ  ለግማሽ ቀን የሚዘልቅ ውይይት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሐፍት ኤጀንሲ አዳራሽ እንደሚካሄድ አስታወቀ፡፡ደራሲ ዘነበ ወላ እና ፀጋአብ ለምለም ለውይይቱ የመነሻ ሃሳብ እንደሚያቀርቡ የታወቀ ሲሆን በውይይት መድረኩ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የስነ - ፅሁፍ ማህበራት ተወካዮች፣ ባለስልጣናት፣ ደራሲያን፣ የስነ ጽሑፍ ምሁራን፣ መጽሐፍት አሳታሚዎችና አከፋፋዮች እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ መድረክ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ፍላጐት ያለው ማንኛውም ሰው እንዲታደም ተጋብዟል፡፡ እናት የማስታወቂያ ድርጅት፤ ለንባብ ባህል መዳበር አስተዋጽኦ ባላቸው ስራዎች ላይ በማተኮር ላለፉት አምስት አመታት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ ዘወትር እሁድ ከምሽቱ 2፡00 እስከ 4፡00 ሰዓት በሚያቀርበው “ብራና” የተሰኘ ፕሮግራሙና በአዲስ አበባና በክልሎች በሚያዘጋጃቸው የመፃህፍት አውደ ርዕዮች ይታወቃል፡፡

Charlie and the Chocolate Factory” በሚል በሮዋልድ ዳህል ተፅፎ “ቻርሊና የቼኮሌት ፋብሪካው” በሚል በጌታነህ አንተነህ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የተዘጋጀው አዲስ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሀፉ በቻርሊ ቸኮሌት ፋብሪካ ዙሪያ የሚያጠነጥን ወጥ ተረት ሲሆን በ157 ገፆች የተቀነበበ ነው፡፡
 በኦላንድ አታሚዎችና አሳታሚዎች ድርጅት የታተመው መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ40 ብር፣ ለውጭ አገር በ20 ዶላር ለገበያ እንደቀረበ ታውቋል፡፡