Administrator

Administrator

 “ሆቴሉን እንድሰራ ያደረገኝ የህዝቡ ፍቅር ነው”


         ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ በኬ ከተማ፣ ድንገት የበቀለ የሚመስል ባለ ግርማ ሞገስ  ዘመናዊ ሆቴል ተንጣሎ  ይታያል፡፡
በእርግጥ ለከተማዋ ነዋሪና በአካባቢው ለሚመላለስ  ሰው ድንገት የበቀለ  አይደለም፡፡ ከ5 ዓመት በላይ ጊዜና 450 ሚሊዮን ብር ገደማ የፈጀ ኢንቨስትመንት ነው፡፡
የበኬ ከተማ ሃብትና ጌጥ እንደሆነ የተነገረለት “ቱ አር ኤን ሰለሞን ሆቴልና ስፓ”፤ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም፣ ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት እንደሚመረቅ የሆቴሉ አስተዳደር አስታውቋል፡፡  
በቀድሞው የደርግ መንግሥት  አገራቸውን በወታደርነት ባገለገሉት መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ የተገነባው ይኸው ባለ  5 ኮከብ ሆቴል፣ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 7፣ በሚዲያ ቡድን አባላት ተጎብኝቷል፡፡
 በጎጃም ጠቅላይ ግዛት፣ ይልማና ዴንሳ በሚባለው አካባቢ የተወለዱት ሰለሞን አዳሙ፤ ገና በ5 ዓመት  ዕድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው፣ አውቶብስ ተራ አካባቢ ነው ያደጉት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ1973 ዓ.ም፣ በ21ኛ ተራራ ክፍለ ጦር ውስጥ ተቀጥረው፣ በተራ ወታደርነት፣ ለ4 ዓመታት በኤርትራ ውስጥ  ማገልገላቸውን ይገልጻሉ፤ በብዙ ውጊያዎች ላይ መሳተፋቸውንና በተዋጊ መሃንዲስነት መሥራታቸውንም በማከል፡፡  
“በ1977 ዓ.ም ባገኘሁት  ዕድል የ48ኛ የእጩ መኮንኖች   ኮርስ ተወዳድሬ በጥሩ ተማሪነት ተመርቄ እዚያው ተሹሜአለሁ፤ የቶፖግራፊ አስተማሪም ነበርኩ፡፡” ይላሉ፡፡
በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረ ጊዜ ጦላይ ተሃድሶ መግባታቸውን የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ፤ከዚያ ከወጡ በኋላ ወደ ሥራ የመመለስ ዕድል ቢያገኙም፣ ከእንግዲህ ወዲያ ወታደር አልሆንም ብለው ወደ ሲቪሉ ማህበረሰብ መቀላቀላቸውንና ወደ ንግድ ሥራ መግባታቸውን  ይገልጻሉ፡፡
የንግድ መነሻ  የሆናቸውን  3ሺ ብር ያገኙት ግን ከድለላ ሥራ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ ብዙ ነገሮችን ነግጄአለሁ የሚሉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሲጋራ ጅምላ ፈቃድ እንደነበራቸው፣ እህል መነገዳቸውን፣ መርካቶ ዱባይ ተራ የልብስ ሱቅ እንደነበራቸውና  ጣውላ መነገዳቸውን  ይናገራሉ፡፡ በመጨረሻም አሁን  በከተማችን  የሚታወቀውንና ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የከፈተውን  “ቱ አር ኤን ሰለሞን ፈርኒቸር” አቋቁመዋል፡፡
ይሄ ድርጅት አድጎና ጎልብቶ ባፈራው ሃብት ነው የሰንዳፋው  ዘመናዊ ሆቴል የተገነባው የሚሉት  ባለሃብቱ፤ በዚህ ትልቅ ኢንቨስትመንት ላይ  አዋሽ ባንክና ዳሽን ባንክ ብድር በመስጠት አሻራቸውን አሳርፈዋል ብለዋል፡፡   
በ2ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ በግርማ ሞገስ የተሰደረው  ውብ  ሆቴል፣ ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው 40 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡ ከሬስቶራንት ባርና ካፌ በተጨማሪም፣ የሳውና ስቲም ባዝና ማሳጅ  አገልግሎቶችንም አካትቶ ይዟል፡፡
በሆቴሉ ግንባታ አብዛኛው ግብአት ከውጭ የመጣ ሳይሆን የአገር ውስጥ መሆኑን የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሆቴል የእንጨት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የተከናወኑት በ”ቱ አር ኤን ሰለሞን ፈርኒቸር” መሆኑን ገልጸዋል፡፡  
“ይህን ሆቴል ለመሥራት ቦታ የወሰድነው  በ2009 ዓ.ም ነው፤በዚያን ወቅት በኦሮሚያና በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የነበረውን የጸጥታ  ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ነው” ያሉት ባለሃብቱ፤ “በብዙ መስዋዕትነት ነው እዚህ የደረስነው፡፡” ብለዋል፡፡
“የሰንዳፋ በኬ አካባቢ ህዝብ በጣም ጨዋና ትልቅ  በመሆኑ እኛንም እንድንሰራ፣ እንዳንሸሽ አድርጎ፣ ይህንን ሆቴል የራሱ ሃብት አድርጓል፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፤መቶ አለቃ ሰለሞን፡፡
ህዝቡ ሆቴሉን  እንደራሱ ንብረት እንደሚቆጥረውና እንደሚጠብቀው  ባለሃብቱ ሲገልጹም፤ “የእኛ ካሜራ የአካባቢው ህዝብ ነው፤ኮሽ ባለ ቁጥር ህዝቡ ነው ሆቴሉን ወጥቶ  የሚጠብቀው፡፡ ይህን ሆቴል ያሰራኝ የአካባቢው ህዝብ ፍቅር ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በረብሻና ግርግር  ወቅት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰውም፤ “ከበኬ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ሁሌም የአካባቢው ነጋዴዎች  በመኪና አጅበው  ይሸኙኝ ነበር፤ቤቴ በደህና መግባቴንም ስልክ ደውለው ያረጋግጡ ነበር፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህንን እውነታ በዕለቱ  ለጋዜጠኞች አጭር  መግለጫ  የሰጡት  የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ ተንኮሉም በድጋሚ  አረጋግጠውታል፡፡  የበኬ ህዝብ እንደሌላው የኦሮሚያ አካባቢዎች ህዝብ ሁሉ ሰላም ወዳድና አቃፊ ነው  ያሉት  ከንቲባው፤ ህብረተሰቡ የአቶ ሰለሞንን  ሆቴል እንደራሱ ንብረት እንደሚያየውና እንደሚሳሳለት መሥክረዋል፡፡  
በኬ ከተማ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚከናወንባት ሥፍራ መሆኗንና፣ ሃቀኛ አልሚዎችን ብዙ ርቀት ተጉዘው እንደሚያስተናግዱ የገለጹት ከንቲባ አለማየሁ ተንኮሉ፤ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አቶ ኃይልና አቶ ትህትና የአንድ አገር ተወላጅ በመሆን አብረው ሲኖሩ ሲኖሩ፣ ከድህነት ወጥተውና በልፅገው ያለ ቅጥ ከበርቴነት ተሰማቸው፡፡ መቼም ሰው መክበርና መበልፀግ ሲጀምር ምኞቱ ሁሉ በዚያው ክብርና ሀብቱ ላይ ቶሎ ቶሎ ሲጨምርበትና ተፊተኛው የበለጠ ሃብት ለማፍራት መባዘን መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡
“ገንዘብም አግኝተን ቶጅረናል፡፡ እዚህ ሌሎች የመሰረቱትና እየጠበበ ያለ ከተማ ሰለቸን፡፡ አዲስና ውብ ከተማ እንድንሰራ ንጉሱ በሀገሪቱ ውስጥ ጠፍ የሆነ ሰፊ ቦታ ፈልጎ ይስጠን” ሲሉ አመለከቱ፡፡
ንጉሱም፤ “እንደ እናንተ ያሉ ልማትንና ክብረትን ለሀገሬ ያሳዩ ጎበዛዝት እንዲበዙልኝ ስል የጠየቃችሁትን ያህል እንዲሰጣችሁ እፈቅዳለሁ፡፡ ለመሆኑም ምን ያህል ቦታ ነው የምትፈልጉት?” በማለት ለአቶ ኃይልና ለአቶ ትህትና ጥያቄ አቀረበ፡፡ እነሱም እንደ ዘመኑ ልማድ ለጥ ብለው እጅ ነሱ፡፡ መሬት ሳሙና “ተፀሃይ መውጫ እስተ ፀሃይ መግቢያ ያለውን የሚያህል መሬት ይሰጠን” በማለት አስር አስር ጊዜ እጅ ነሱ፡፡
ንጉሱም፤ “ምን ልትሰሩበት ነው የወጠናችሁት?” አለ፡፡ አቶ ኃይልና አቶ ትህትና እንደተማከረ ሰው በአንድነት “ቤተ መንግስትና ከተማ” አሉ፡፡  
ንጉሡ፤ “እንዲህ ያለ የተቀደሰ ሀሳባችሁንማ ቦታ በመስጠት ብቻ ሳይሆን የጎደለባችሁን ሁሉ እኔ እየሞላሁላችሁ እንድትሰሩ ለመደገፍ ከአምላክ የተቀበልኩት የህዝብ አደራ አለብኝ” አለና ለሀገር ግዛት ሚኒስትሩ የጠየቁት እንዲሰጣቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ በትእዛዙም መሰረት መሬቱን ተረከቡ፡፡
ተረከቡና እንደየጠባያቸው ለመስራት እንዲቻላቸው መሬቱን ለሁለት መካፈል ጀመሩ፡፡ ክፍፍልም ጀምረው ጥቂት ሳይቆዩ፣ በሁለቱም በኩል “የኔን ቤተ መንግስት ወደ ላይ ልስራ! ወደ ላይ ልስራ!” በማለት ወደ አለመግባባት ተዳረሱና አዋቂ ይለየን! ብለው በፈቃዳቸው ወደ ሽማግሌ ቀረቡ፡፡
ሽማግሌዎቹም አቤቱታውን መስማት ሲጀምሩ ያገኙት ፍሬ ነገር፣ አቶ ኃይልና አቶ ትህትና በየፊናቸው ከፍ ያለውን ቦታ መርጠው “ወደ ላይ ልስራ! ወደ ላይ ልስራ!” ማለታቸውን ነበር፡፡
ከሽማግሌዎቹ የሚበዙት አቶ ኃይል “ወደ ታች ይስራ”፣ ያነሱት ደግሞ “ወደ ላይ ይስራ” ብለው ወሰኑ፡፡ ለአቶ ትህትና በተቃራኒው ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጠ፡፡
የሽማግሌዎቹ ፍርድ ያልተዋጠላቸው ሁለቱ ተከራካሪዎች፣ ይግባኝ ጠየቁና ወደ መጨረሻው ፍርድ ሰጪ ወደ ‘ብላታ ህሊና‘ ዘንድ ቀረቡ፡፡
ብላታ ህሊናም “አቶ ኃይልና አቶ ትህትና ተስማምተው በህብረት ሰርተው በአንድነት ቢኖሩበት መልካም ነበር፡፡ ስምምነት ከሌለ ግን እንኳንስ አንድነቱ ጉርብትናውም ያስቸግራል። ስለዚህ ትህትናን ማሸነፍ ይቻላልና ወደ ላይም ወደ ታችም ስራ ብንለው ባላወከንም ነበር፡፡ ኃይልን ግን ወደ ላይ እንዲሰራ ማድረግ ታላቅ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ ሃይል ወደ ታች ይስራ፣ ትህትና ወደ ላይ ይስራ በማለት በግጥምና ምሳሌ መደምደሚያ ፍርዳቸውን ሰጡ፡፡
አንዲት የሱፍ ፍሬ ተዘርታ ሳለች
እሷ ሳትነሳ አገዳ ሰራች፡፡
የሚያምር አበባ በአገዳው ላይ ታይቶ፣
እሾህ ያጥር ጀመር ቤቱን ከዚያ ሰርቶ፡፡
ያቺ ቅንጣት ፍሬ ከስር የወጣች፣
አገዳው የኔ ነው ስትል ከሰሰች፡፡
አበባ ግን ደፍሮ በሰጠው አርአያ፣
እሾህን ቆጠረ ለመከላከያ፡፡
አበባ መኖሩን ከፍሬ በፊት፣
እሾህ መሰከረ ነውና እውነት፡፡
ነገ ግን በርትታ ያቺ ቅንጣት ሱፍ፣
በመከራከሯ ከስር እስከ ጫፍ፣
ነገሩን ከስሩ ዳኞቹ ቢያዩት፣
የሚያከራክረው ያገዳው ንብረት፣
ከ ‘ዘር’ የተገኘ ሆኖ አገኙት፡፡
ስሩ ሳይታወቅ በጣም ተፈልፍሎ
ነገር አይያዝም ጫፍ ያምራል ተብሎ፡፡
***
እዚህ አገር የተጫነን አባዜ ሃይልና ትህትናን ለማቀራረብ ስልታችን እያደር አንድ አይነት መሆኑ ነው፡፡ ከዘር የተገኘው የባህሪ ዳፋ አልቀን ብሎ ከፍሬው ይልቅ እሾሁ ይታየናል፡፡ ምን እናፈራለን? ሳይሆን ምን ይወጋናል? ማለቱ ያመዝንብናል፡፡
መንግሥቱ ንጉሱን ከሰሱ እንጂ እሳቸው አልተማሩበትም፡፡ አዲሶቹም መንግሥቱን ወቀሱ እንጂ እነሱ አልተማሩበትም፡፡ ተቃዋሚዎቹም ይወቅሳሉ፤ ይከሳሉ እንጂ ከተከሳሾቹ መሻላቸውን በተግባር ማሳየት ተስኗቸዋል፡፡
መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች ስለ ህዝብ የሚሰጡት አስተያየት “ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ” እንዳይባሉ ከወዲሁ አርቀው ቢያስቡ ይበጃቸዋል፡፡ “በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” መባል ይከተላል፡፡ “የእንትን ህዝብ ፈሪ ነው፤ የእንትን ህዝብ ጀግና ነው” በማለት የትም አይደረስም፡፡ ለህዝብ በጅምላ አመልና ፀባይ መስጠቱ ይቅር የማይባል የታሪክ በደል ነው፡፡
“መነኩሴ አሳማ በላ፣ ከበላው የሰማው ገማ” እንዲል መፅሐፉ፣ የጅምላ መትረየስ ርሸና ትዝታችን ሳይደበዝዝ፣ የጅምላ ቃላት ርሸና ስናክልበት አዲስ ስርአት ለመገንባት ያለንን ብቃትና ችሎታ ጥያቄ ዉስጥ ይከተዋል፡፡
ትህትና የጎደለው ጀግንነት ማንን ወደምን እንዳደረሰ ከራሳችን በላይ ምስክር የለም፡፡ “የእንትን ህዝብ ፈሪ ነው” ማለትን ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅትና መሪ መስማት፣ እንደ ዜጋ ለእኛ አስፈሪ ምስል ይከስትብናል፡፡ በ1968 እና 69 ጀግና የነበሩት ወጣቶች የት ደረሱ? ምን አፈሩ? ናቅፋ ቃሮራ የወደቁት ጀግኖች ምን አገኙ? 30 ዓመት ጦር ነክሰው የረገፉ የኤርትራ ወጣቶች ዛሬ ምን ተሸለሙ? … ምን?!ምን?!...‘ጀግንነት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተደብቃ ምንጊዜም አለች፡፡ ግን ጊዜ ቦታንና ሰው ትፈልጋለች- ትመርጣለች’ እንዲል ማክሲም ጎርኪ፤ ጀግንነት ያለ ጊዜውና ያለ ቦታው ሲሆን ትጨነግፋለች፡፡
መምህርና ባለቅኔ ዮፍታሄ ንጉሴ፣ ቢደንቃቸው …
“ሲያቅተኝ ዝም ብል ዝም ያልኩኝ መስሎታል
ሲታሰብ ነው እንጂ ዝም ማለት የታል?”
በማለት የተቀኙትን ያስታውሷል፡፡ ያለበለዚያ…
“ካቻምና በፈረስ አምና በበሬ አረስኩ፣
ዘንድሮ በአህያ የእህል አረማሞ፣
በፍየል ቀርቶኛል ከእንግዲህ ለከርሞ”… መባልን ያስከትላልና ልብ ያለው ልብ ይበል!
መብትና ነፃነት ለጥቂት ታዋቂ ሰዎችና ለህጋዊ ፓርቲዎችም ቢሆን በመጠኑ እንጂ ለህዝቡማ ገና አልተዳረሰችም፡፡ ቀበሌና ገበሬ ማህበር የዲሞክራሲ ወሬዋን ከርቀት እየሰሙ ናቸው እንጂ እነሱ ዘንድ አልደረሰችም፡፡ በየትኛውም ዘመን ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞ አያውቅማ!! ተቃዋሚዎች “አስቀድመህ ስሩን ትከል፣ ጫፉ ኋላ ብቅ ይልልሃል” የሚለውን ብሂል ተከትለው በተስተዋለ እርምጃ ህዝቡን በህብረት ለማታገል መታጠቅ ለነገ የማይባል የቤት ስራቸው መሆኑን ማጤን ግድ ነው፡፡
“ለሚፈታተነው የንፋስ ማእበል?
ማማው ለአፍታ እንኳን ጎንበስ ዝቅ እንዳይል፣
ተጠናክረህ ግፋ እንዳትዘናበል…”
እንዲል ባለቅኔው ዳንቴ አሊጌራ፣ ከኛም ይኸው ይጠበቃል፡፡ የህዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጡ በመራመድ ፋንታ ያለጊዜው ድል ማማጥ፣ ያለፈርጁ ሸማ መልበስ ይሆናል፡፡ ህዝብ ታሪክ ሰሪ ነው፡፡ ታሪክ ሰሪን አይሰድቡትም፤ እስኪ ከታሪክ ሰልፍ ቀላቅለኝ ይሉታል እንጂ! ከታሪክ ሰልፍ መቀላቀልም “ቢወዱት ታንቆ የሞተ- ቢጠሉት ምን ሊሆን ነበር?” ከመባል ያድናል፡፡


በአነስተኛ ካፒታል በኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ  ተመስርቶ ከ30  አመታት በላይ በኮንስትራክሽንና በሪልእስቴት ዘርፍ ጉልህ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው ፍሊንትስቶን ኢንጅነሪንግ ፤ ከሃምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አክሲዮኖቹን ለህዝብ ክፍት በሆነ ገበያ ለሽያጭ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡   
ኩባንያው ይህን ያስታወቀው ባለፈው ማክሰኞ፣ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም፣  በሃያት ሪጀንሲ  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ነው፡፡
የኩባንያው መሥራችና ባለቤት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ የአክሲዮን ሽያጩን ለመጀመር ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ፍሊንትስቶን ኢንጅነሪንግ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በግለሰብ ደረጃ ተመሥርቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማድረስ ከቻለ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖችን በውስጡ ቢይዝ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ይችላል።” የሚል እሳቤን መነሻ ማድረጋቸውን  ገልጸዋል።
10 ሚሊዮን አክሲዮኖች ለሽያጭ መዘጋጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺህ ብር ሆኖ የአክሲዮን ባለቤትነቱ ከ20 ሺህ ብር የማያንስና ከሁለት ሚሊዮን ብር የማይበልጥ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
ለሽያጭ የቀረበው አነስተኛ የአክሲዮን መጠን ዝቅተኛው 20 ሺህ ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ  የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ማቲያስ ሲያስረዱ፤ ከፍተኛ የገንዘብና የዕውቀት አቅምን በመገንባት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ደንበኞች ጀምሮ ብዙኃኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕዝብ ኩባንያን ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
የአክሲዮን ገዢዎች ለአክሲዮኑ ያዋሉት ገንዘብ በቀጣይ ለቤት መግዣነት ማዋል ቢፈልጉ፤ በማንኛውም ጊዜ ኩባንያው አክሲዮናቸውን ገዝቶ፣ ያላቸውን ገንዘብ በካሬ ሜትር በማስላት የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ሥርዓት መዘርጋቱም ተገልጧል፡፡የግል ድርጅቶችን ለህዝብ ክፍት በሆነ ገበያ ማቅረብ ሁለት ቁልፍና ተመጋጋቢ ፋይዳ እንደሚያስገኝ የተጠቆመ ሲሆን፤ አንደኛው ከፍተኛ የገንዘብና የዕውቀት አቅም ማምጣቱ ነው፤ ሁለተኛው  ደግሞ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን በማስፈን መልካም የኮርፖሬት አስተዳደርን  ያሰፍናል ተብሏል፡፡
ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሃገሪቱ በልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ ተቋራጭነት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ከአስራአምስት ዓመታት በፊት ወደ ቤቶች ልማት ገበያ የተቀላቀለው ፍሊንትስቶን ሆምስ፤ በትምህርት፣ በውሃ፣ በመብራት ሃይል፣ በመንገድና በመንግስት የቁጠባ ቤቶች ፕሮጀክቶች ላይ ግዙፍ አሻራዎችን ማኖሩ ታውቋል፡፡
ወደ ሪልእስቴት ከተቀላቀለ በኋላ ባሉት አስራአምስት ዓመታትም በሺህ የሚቆጠሩ ደንበኞችን የቤት ባለቤቶች ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
“ሁሌም በለውጥ ሰዓት ለባለሃብቶች ሦስት ነገሮች የመሆን ዕድል ያጋጥማል፤ ቆዛሚም፣ አዝጋሚም፣ ተምዘግዛጊም መሆን ይቻላል፡፡ እንደ ንግድ ድርጅት ተምዘግዛጊ መሆኑ ግን እጅጉን ያዋጣል፤ ሀገራችንን በጋራ፣ ሀብታችንን በአክሲዮን እንገንባ” ብሏል፤ፍሊንትስቶን ሆምስ በመግለጫው፡፡


 በዲኤምጂ ኢቨንትስና በአገር በቀሉ ኢቲኤል ኢቨንትስ ኤንድ ኮሚዩኒኬሽን ትብብር የተዘጋጀውና ለ3 ቀናት የዘለቀው የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ኤግዚቢሽን ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡
በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ አለማቀፍና አገር በቀል ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ይኸው ከግንቦት 10 ቀን 2015 ጀምሮ እስከ ዛሬ ለ3 ቀናት ክፍት ሆኖ የቆየው ኤግዚቢሽኑ፤ በዘርፉ ያሉ እድሎችንና አማራጮችን በመጠቆም በዘርፉ የተሰማሩ ግብአት አቅራቢዎች በተለያዩ ግዙፍ ግንባታዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉና የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ ምቹ እድሎችን ፈጥሯል ተብሏል፡፡ ከ24 የአለማችን አገራት የተውጣጡ ከ140 በላይ የኤግዚቢሽን አቅራቢዎች የተሳተፉበት ይኸው ኤግዚቢሽን፤ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዕውቅናና ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡በሚሊኒየም አዳራሽ የተካሄደውና በቆየው ኢግዝቢሽን ላይ ከ6ሺ በላይ የህንፃ ንድፍና ግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የህንፃ ጥገናና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎችና እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የዘርፉ አካላት እና ልሂቃን ጋር በአንድ መድረክ ለመገናኘት ያስቻለም ነው፡፡ ቢግ 5 በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ በግንባታ እንዱስትሪ ውስጥ ከአራት አስርት አመታት በላይ ግንባር ቀደም ሆኖ ቆይቷል፡፡
ቢግ 5 ኮንስትራክት፤ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥና የውጪ ኩባንያዎች ሙያዊ ክህሎታቸውንና እውቀታቸውን ለኢትዮጵያ የግንባታ እንዱስትሪ የሚያሳዩበት ሁነኛ መንገድ እንደሆነም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡


 ሕብረት ባንክ፤ የቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግርና ልምድን ማካፈል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙርያ ከዘምዘም ባንክ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ባለፈው ረቡዕ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በሕብረት ባንክ ዋና መሥርያ ቤት ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም፣ ሁለቱ ባንኮች በቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርና ሥልጠና አብረው የሚሰሩ ሲሆን፤ ሕብረት ባንክም በዘርፉ ያለውን የካበተ እውቀትና ልምድ በማካፈል፣ ለዘምዘም ባንክ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡  
የስምምነት ሰነዱ በባንኮች መካከል ሲፈረም በአይነቱ የመጀመሪያው መሆኑን የገለፁት የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ፤ ስምምነቱም በትብብርና በውድድር ውስጥ አብሮ መስራትን የሚያበረታታ፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀርና የውስጥ ሠራተኞችን አቅም የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡
የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በባንኪንግ ኢንዱስትሪው ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልፀው፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለማስቀረትና የዕውቀት ሽግግርን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሁለቱ ባንኮች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ የተለያዩ ሥራዎች ላይ በቅንጅት ለመሥራትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡
 ሕብረት ባንክ “ኦራክል ፍሌክስኪዩብ ኮር ባንኪንግ ሲስተም”ን በራሱ ከመተግበሩ ባሻገርም፣ በቅርቡ የሞባይል ባንኪንግ አፕሊኬሽኑንም በራሱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ማዘመኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ኤሊት ፊንቴክስ ሶሉሽንስ ኃ/የተ/የግል ማኀበር፣  ኢ- ብድር በተሰኘ ሲስተም አማካኝነት፣ “ብድር ለገበሬውና ብድር ለወጣቱ”  የተሰኘ ኢንሽዬቲቭ፣ ባለፈው ረቡዕ  በሀርመኒ ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አልአዛር ሰለሞን  እንደተናገሩት፤  በማኀበራዊ ክሬዲት ኢንሽየቲቭ ሥር፣ “ብድር ለገበሬ፣ ብድር ለወጣቶች” በሚል በድምሩ ሁለት ሚሊዮን ዜጎችን በኢ - ብድር ክሬዲት ማኔጅመንት ሲስተም ለመድረስ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አንድ ደንበኛ በኢ- ብድር አማካኝነት ተመዝግቦ ለባንኮች የብድር ጥያቄ ለማቅረብ አስፈላጊ መረጃዎች ከ5 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ የገለፁት አቶ አልአዛር፤ ባንኮች ሥራውን በተናጠል ሲያከናውኑ የብድር አናሊስስ መሥራት ብቻውን ወራትን ይፈጅባቸው እንደነበር በማስታወስ፣ ኢ- ብድር ይህን ችግርም በአስተማማኝ መልኩ ይፈታል ብለዋል። ገበሬዎች በእጃቸው የሚገኘውን መሬት፣ ከብቶች፣ የንብ ቀፎ በዋስትና በማስያዝ እንዲበደሩ የሚያስችል ሕግ ትግበራ ላይ በገጠመው ችግር በአመዛኙ ተፈፃሚ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ የኢ-ብድር ሲስተም ይኸንን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል።


 የብልፅግና አመራሮች የም/ቤት አባላትን “ም/ቤቱን ለቃችሁ ውጡ” እያሉ ነው


         ብፅግና ፓርቲ፤ በደቡብ ክልል ህዝብ ም/ቤት፣ የቁጫ ህዝብ ተወካዮች የሆኑ የም/ቤት አባላትን “ከም/ቤት አባልነት አሰርዣችኋለሁ” በማለትና ደብዳቤውን ለሚዲያ በማሰራጨት በቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የሰብአዊ የመብት ረገጣ እየፈጸመ ነው ሲል ከሰሰ።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ፣ በቁጫ ምርጫ ክልል የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢወዳደሩም የቁጫ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ያቀረባቸው ዕጩዎች በአብላጫ ድምጽ ማሸነፋቸውን ያመለከተው ፓርቲው፤ ውጤቱን ከብልጽግና ፓርቲ ውጭ ያሉ ፓርቲዎች በጸጋ መቀበላቸውን ይገልፃል።
በተቃራኒው ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ በመሸነፉ ምክንያት አኩርፎ በርካታ የምርጫ ሥነ-ምግባር ጥሰቶችን በመፈጸም መራጭ ህዝቡንና በየደረጃው ያሉ የቁህዴፓ አባላትን በማሰር፣ በመደብደብና በገንዘብ በመቅጣት በሃይል ከፓርቲው እንዲወጡ አስገድዷል ብሏል- ፓርቲው። የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ቦሌ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ቢሮ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የቁሕዴፓ አመራርና አባላት በብልፅግና ፓርቲ እየደረሰባቸው ነው ያለውን ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብት ረገጣ በዝርዝር ገልጿል።
በምርጫው መሸነፉን ተከትሎ፣ የቁጫን የህዝብን ቀልብ መሳብ ያልቻውና የህዝብን ድጋፍ ይሁንታ ያላገኘው የብልፅግና ፓርቲ፣ ከህግ አግባብ ውጭ የቁህዴፓ አመራርና የደቡብ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቁጫ ህዝብ ተወካዮች የሆኑ ሦስት የም/ቤት አባላትን “ከምክር ቤት አባልነት አሰርዣለሁ” የሚል ደብዳቤ በተለያዩ ሚዲያዎች ማሰራጨቱን የጠቆመው ቁህዴፓ፤ ይህም ሳይበቃው በቁጫ ምርጫ ክልል በሁሉም መዋቅሮች “የቁህዴፓ ተወካዮች ከም/ቤቱ ተባርረዋል” በማለት የደስታ መርሃ ግብር በማሰናዳት ተወካዮቹን በመረጠው ህዝብና  በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ቁጣና ግጭት እንዲፈጠር የተለያዩ ቀስቃሽ ድርጊቶችን በመፈጸም ላይ ይገኛል” ብሏል- በመግለጫው።
“የደቡብ ክልል ም/ቤት፤ አንድ አባል ከም/ቤት አባልነት ሊወጣ የሚችልበት የህግ አሰራና ሂደትን በሚጣረስ መልኩ “የቁጫ ህዝብ ተወካዮች ከክልል ም/ቤት አባልነት ተሰርዛችኋል” በማለት ያሰራጨው ደብዳቤ፣ የምርጫ ህግና ሥርዓት ዋጋ እንዲያጣ ብሎም በሃገራችን የተጀመረው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲገባ የሚገፋፉ ኢ- ህገመንግስታዊ ድርጊት ነው።” ሲል ኮንኗል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ተባባሪ ፕ/ር ገነነ ገደቡ በቁጫ ሰላምበር የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው ም/ቤቱ ምንም አለማለቱ ጥሩ መልዕክት የሚያስተላልፍ አይደለም ለምክርቤቱም ክብር የሚመጥን አይደለም ሲል ፓርቲው አማርሯል።“ይህ አድራጎት በሰላማዊ ትግል መስመር ብዙ ጫናዎችን አልፎ ይወክለኛል ያላቸውን ተወካዮቹን ለውክልና ያበቃውን ህዝብ በእጅጉ መናቅና ከህገመንግስቱ ድንጋጌዎች ጋር በእጅጉ የሚቃረን እንዲሁም በአገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ዕድገትን ለማምጣት የምናካሂደውን ጥረት የሚያጨናግፍ ነው” ብሏል- ፓርቲው።
በሌላ በኩል በደቡብ ክልል በጋሞ ዞንና በቁጫ ሦስቱም መዋቅሮች የብልፅግና ፓርቲ ገና ሊካሄድ የታቀደውንና በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበትን የሃገራዊ ምክክር ሂደትን ዋጋ የሚያሳጣ የሴራ ድራማ ላይም መትጋቱን ቁህዴፓ ይገልፃል።
በዚህም መሰረተ ብልፅግና “ሚያዚያ 28 እና 29 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ በቁጫ ሰላምበር ከተሞች  “የቁጫ ህዝብ የእርቀ ሰላም ኮንፍረንስ” ማካሄዱን የጠቀሰው ቁህዴፓ፣ የቁጫ ህዝብ ህጋዊ ተወካይ  ሆን ተብሎ ባልተጋበዘበት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንም ባልተሳተፈበት፤ የምክክር ተግባራትን እንዲያከናውን ሥልጣን የተሰጠው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማያውቀው መልኩ፣ የገዛ ራሱን ካድሬዎች ሰብስቦ መላውን መራጭ ህዝብ በአስነዋሪ ሁኔታ በሚያንኳስሱ መፈክሮች የተሞላ ጉባኤ ማድጉን በመግለጫው አመልክቷል።
“ገዢው ፓርቲ ብቻውን ተሰብስቦ ራሱ አጥፊ፣ ራሱ አስታራቂ፣ ራሱ ከራሱ ጋር ታራቂ የሆነበትንና የቁጫ ህዝብንና በቁጫ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎችን ያላማከለ “ድራማ” መሰራቱ ሳያንስ፤ ጉባኤውን “የህዝብ ሃሳብ የተንጸባረቀበት ነው” በሚል ለፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት ሪፖርት  ማድረጉ ከባድ የማጭበርበር ተግባር ነው ሲል ወቅሷል- ፓርቲው። ከዚህ አንፃር የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ተደርጓል የተባለውን የእርቀ ሰላም ሂደት ምን ይመስል እንደነበር  በገለልተኛነት እንዲያጣሩም ጥሪ አቅርቧል።
እነዚህን መሰል ኢ-ሰብአዊና ህገ-መንግሥታዊ ተግባራት በጋሞ ዞን ባሉና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የህዝብ ይሁንታ ባገኙባቸው የቁጫና የዛይሴ ምርጫ ክልሎች በገዢው ፓርቲ ትውልድ ይቅር የማይሉት በደሎች እየተፈጸሙ ናቸው ያለው ቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ገዢው ፓርቲ ሰላማዊ ትግልን ወደ ጎን የመተውን አካሄድ ትቶ፣ ለማናቸው የህዝብ ጥያቄዎች ጆሮ እንዲሰጥ እንዲሁም፣ የታችኛው የመንግስት ባለስልጣናትን ገደብ ያጣ አምባገነንነትና ሌብነት እንዲያስቆም እንጠይቃለን ብሏል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ማንም እየተነሳ የምክር ቤት አባላትን “የምክር ቤት መታወቂያ ካርዳችሁን ተመላሽ አድርጋችሁ ም/ቤቱን ለቃችሁ ሂዱ” እያሉ ኢ-ህገመንግሥታዊ ብይን እንዳይሰጡ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ፓርቲው፤ የብሄር ማንነትና የራስ አስተዳደር የህዝብ  ጥያቄዎችም በህገ-መንግስቱ መሰረት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸውና በመላ አገሪቱ እውነተኛ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲቻል ጥሪውን አቅርቧል።

ባለሃብቱ፤ ሆቴሉን እንድሰራ ያደረገኝ የህዝቡ ፍቅር ነው ብለዋል

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ በኬ ከተማ ድንገት የበቀለ የሚመስል ባለ ግርማ ሞገስ ድንቅ ሆቴል ቆሞ ይታያል፡፡ በእርግጥ ለከተማዋ ነዋሪና አካባቢውን ለሚያውቅ ሰው ድንገት የበቀለ አይደለም፡፡ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ5 ዓመት በላይ ጊዜና 450 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡

የበኬ ከተማ ሃብትና ጌጥ እንደሆነ የተነገረለት ይኸው "ቱ አር ኤን ሰለሞን ሆቴልና ስፓ"፣ ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት እንደሚመረቅ ነው የተገለጸው፡፡

በቀድሞው የደርግ መንግሥት ጦር ሠራዊት ውስጥ አገራቸውን በወታደርነት ባገለገሉት መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ የተገነባው ይህ ባለ  5 ኮከብ ሆቴል፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በሚዲያ ቡድን አባላት የተጎበኘ ሲሆን ጋዜጣዊ መግለጫም ተሰጥቷል፡፡

በ1982 ዓ.ም የደርግ መውደቅን ተከትሎ፣ የድለላ ሥራ መጀመራቸውን  የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በኋላም በ3ሺ ብር ካፒታል ወደ ንግድ ሥራ መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ባለሃብቱ በከተማችን  የሚታወቀው የቱ አር ኤን ሰለሞን ፈርኒቸር  ባለቤት ሲሆኑ፤የሆቴሉ ህንጻ የእንጨት ሥራዎች በሙሉ የተከናወኑት በዚሁ ድርጅታቸው ነው ተብሏል፡፡

በሰንዳፋ በኬ ከተማ በ2ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ በግርማ ሞገስ የተንጣለለው ሆቴሉ፤ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው 40 የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ ከሬስቶራንት ባርና ካፌ በተጨማሪም የጃኩዚና ስፓ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡

በተለይ የአካባቢው ቀዝቃዛ አየርና ያማረ ተፈጥሯዊ ዕይታ  ሆቴሉን ተመራጭና ተወዳጅ እንደሚያደርገውም ተነግሯል፡፡

ሆቴሉ ያረፈበትን ቦታ በ2009 ዓ.ም መውሰዳቸውን የተናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሊዝ ክፍያውን የፈጸሙት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን  መልቀቃቸውን ያስታወቁ ዕለት መሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ጎጃም ውስጥ የተወለዱት ባለሃብቱ፣ የጸጥታና ደህንነቱ ሁኔታ እጅግ አስጊ በነበረበት ወቅት መዋዕለንዋያቸውን እንዴት በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው የሰንዳፋዋ ቤኪ ከተማ ለማፍሰስ እንደደፈሩ ተጠይቀው ነበር፡፡ መቶ አለቃ ሰለሞን ሲመልሱም፤ "የእኛ ካሜራ የአካባቢው ህዝብ ነው፤ኮሽ ባለ ቁጥር ህዝቡ ነው ሆቴሉን ወጥቶ ከአደጋ የሚጠብቀው፡፡ የአካባቢው ህዝብ ፍቅር ነው ይህን ሆቴል ያሰራኝ፡፡" ብለዋል፡፡

ባለሃብቱ አክለውም፤ "ረብሻና ግርግር በነበረበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ ስመለስ የአካባቢው ነጋዴዎች  በመኪና አጅበው ለገጣፎ ድረስ ይሸኙኝ ነበር፡፡" ሲሉ የህዝቡን ፍቅር ገልጸዋል፡፡

ይህንን እውነታ ለጋዜጠኞች መግለጫና ማብራሪያ የሰጡት  የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ ተንኮሉም አረጋግጠውታል፡፡  በኬ የሁሉም ብሔር ተወላጆች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ ናት የሚሉት ከንቲባው፤ ህብረተሰቡ መቶ አለቃ ሰለሞን የገነቡትን ሆቴል እንደራሱ ንብረት እንደሚያየውና እንደሚሳሳለት ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ያሉትን ሃብቶች ለጋዜጠኞች በዝርዝር የጠቀሱት ከንቲባ አለማየሁ፤አሁን ደግሞ ሌላ ሃብት ጨምረናል ብለዋል - ባለ 5 ኮከቡን አስደማሚ  ሆቴል ማለታቸው ነው፡፡ ሃቀኛ አልሚዎችን ብዙ ርቀት ተጉዘው እንደሚያስተናግዱ በመግለጽም፤ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡•   አንድ ባጃጅና 2 ሞተርሳይክሎችንም ለአሸናፊዎች ሸልሟል

ሳፋሪኮም ከወር በፊት ከ1ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ተሸላሚ የሚያደርግ "ተረክ በጉርሻ" የተሰኘ አገር አቀፍ የሽልማት መርሃ ግብር በይፋ ማስጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤በዛሬው ዕለት የመጀመሪያዎቹን የከፍተኛ ሽልማቶች አሸናፊዎች ይፋ በማድረግ፣ የመኪና የባጃጅና የሞተር ሳይክሎች ሽልማቶችን አበርክቷል፡፡

 የዕጣው አሸናፊ ተሸላሚዎች  የአዲስ አበባውን  የመኪና አሸናፊ፣ የአዳማውን የባጃጅ አሸናፊ እንዲሁም የአፋርና የድሬዳዋውን የሞተርሳይክል  አሸናፊዎች  ጨምሮ ከመላው አገሪቱ በርካታ ስልኮችና ታብሌቶችን ያሸነፉ ደንበኞች እንደሚገኙበት ሳፋሪኮም አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ አውቶብስ ተራ፣ ማማድ ህንጻ ላይ በሚገኘው  የሳፋሪኮም አከፋፋይ ሱቅ ባዘጋጀው አሸናፊዎችን ይፋ የማድረግ  ሥነሥርዓት ላይ ነው፣ ለባለዕድለኞች  ሽልማታቸውን ያበረከተው፡፡

ሳፋሪኮም ባዘጋጀው በዚህ "ተረክ በጉርሻ" የተሰኘ አገር አቀፍ የሽልማት መርሃግብር፣ የመጀመሪያውን የመኪና ሽልማት ያሸነፈው የአዲስ አበባው፣ የጉርድ ሾላ ነዋሪ፣ ሙባረክ ሱሩር መሆኑ ታውቋል፡፡

ሙባረክ እንዴት ሽልማቱን እንዳሸነፈ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፤"የሳፋሪኮም መስመርን ለጥቂት ጊዜ ስጠቀምበት ቆየሁና እኔ ሌሎች ዘመዶችን ለመጠየቅ ወደ ገጠር ስሄድ እዚህ ላለ ዘመዴ ሰጠኹት፡፡ በ0700 700 700 ሲደወል ዘመዴ ነበር የመለሰው፤ከዚያም ሽልማቱን ማሸነፌን አስታወቀኝ፡፡ መኪናውን ማሸነፌን ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ የዕጣ ሽልማት መጀመሩን አውቅ ነበር፤ነገር ግን መኪና አሸንፋለሁ የሚል ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ መጥቶ አያውቅም፡፡ እጅግ አስደሳች ዕድል ነው፤ድንገተኛ! ሁሉም ሰው እንደኔ የማሸነፍ ዕድል እንዲያገኝ የሳፋሪኮም መስመርን እንዲጠቀም እመክራለሁ፡፡" ብሏል፡፡

የአዳማው ናኦሊ መሃመድ፣ ሁለተኛውን የባጃጅ ሽልማት ያሸነፈ ሲሆን፤ ሁለት ሞተርሳይክሎችን ደግሞ የድሬዳዋው አሸናፊ ታደሰ አሰፋና የአፋር ክልሉ ሙክታር ሞሃመድ አሸንፈዋል፡፡

ሁለተኛውን የደንበኞች የአሸናፊዎች ቡድን ለመሸለም በመብቃታቸው በስሜት መጥለቅለቃቸውን የገለጹት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሪጂናል የሽያጭ ማናጀር አቶ ቢኒያም ዮሐንስ፤ አገር አቀፉ የዕጣ ሽልማት መርሃ ግብር ተጨማሪ በርካታ ደንበኞቹን መሸለሙን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የዛሬ ወር ገደማ የዕጣ ሽልማት መርሃግብሩ ይፋ ከተደረገ ወዲህ፣ ተጨማሪ 400ሺ ደንበኞች  ዕለታዊ የአየር ሰዓት ሽልማቶች ማሸነፋቸውንም ኩባንያው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ሳፋሪኮም በመጪዎቹ ሰባት ሳምንታት ለበርካታ ተጨማሪ ደንበኞቹ፤ ሁለት መኪኖችን፣ 5 ባጃጆችን፣በርካታ ስልኮችንና ታብሌቶችን እንዲሁም የአየር ሰዓቶችን እንደሚሸልምም አስታውቋል፡፡

የሽያጭ ሃላፊው አቶ ቢኒያም ዮሐንስ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ "እንደ ሳፋሪኮም ደንበኛ አገልግሎታችንን ስትጠቀሙ በየዕለቱ ተጨማሪ እሴት ታገኛላችሁ፤ማንኛውም ሰው የ07 ኔትዎርኩን በመቀላቀልና የሳፋሪኮም መስመርን በየዕለቱ በመጠቀም የዕጣ ሽልማቶች የማሸነፍ  ዕድሉን ማሳደግ ይችላል" ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ፤የቤት ሻጮችና ገዢዎች፤ አንዲሁም ገንቢዎችና የተለያዩ ተቋማትን ለማገናኘትና ለማስተሳስር እድል የሚሰጠው አርኪ የሪል እስቴት ኤክስፖ በዛሬው እለት ተከፍቷል።

ከዛሬ ግንቦት 5 እስከ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በሚዘልቀው  ኤክስፖ፤ በርካታ የቤት አልሚዎች እየገነቡት ያሉት ቤቶች የሚገኙበትን  ደረጃ ፣ የቤቶቹን ዋጋ ፣ ሊገነቡት ስላቀዱት ቤት ፣ ስለሚፈልጉት  እቃ እና አገልግሎት ከኤክስፖ ተሳታፊዎችና ጎብኚዎች ጋር መረጃና ልምድ ይለዋወጣሉ ተብሏል፡፡

አርኪ ኤቨንት ኦርጋናይዘር  ባዘጋጀው በዚህ  ኤክስፖ  ላይ ለሽያጭ ባለሙያዎች ነፃ ስልጠና እንደሚሰጥና  የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡

Page 3 of 647