Administrator

Administrator

 የሴቶች ማህጸን መውጣት ማለት የሴቶች የጀርባ ወይንም የወገብ አጥንት ሲደክም የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ይህ እድሜአቸው ከ50-79 አመት የሚደርሱ ከአጠቃላይ ሴቶች ግማሽ የሚያህሉት የሚገጥማቸው ሕመም ነው፡፡ ይህን መረጃ ያወጣው ማዮ ክሊኒክ በ2020/ዓ/ም ነው።
Uterine prolapse የህክምና ቋንቋው ሲሆን prolapse የሚለው ቃል የተገኘው ከግሪክ ነው። ትርጉዋሜውም አንድ ነገር ከነበረበት ወይንም ከተፈጠረበት እና ከሚቀመጥበት ቦታውን ሲለቅ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ቃል ለማህጸን ብቻም ሳይሆን ለተለያዩ አካላትም ይገለግላል። ለምሳሌ በወገብ ላይ የዲስክ መንሸራተት እንዲሁም በብልት ላይ የሚደርሱ መንሸራተቶች ይገለጹበታል፡፡
ማህጸን በአንዲት ሴት Hip joint ወይንም Hip Bon በሚባለው አጥንት ውስጥ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ይህ አካል እግራችንን እና የላይኛውን የሰውነት ክፍላችንን የሚያገናኝ የአ ጥንት ክፍል ነው፡፡ ማህጸን የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ አንዱ እርግዝናውን የሚሸከም ሌላው እንደበር የሚያገለግል ቱቦ ነው፡፡ እነዚህ ቱቦዎች በየወሩ የሚወጣውን እንቁላል ወደ ማህ ጸን የሚያጉዋጉዙ ናቸው፡፡ የማህጸን ቱቦው፤ የማህጸን ከረጢቱ እና የእንቁላል ከረጢቱ በዚሁ አጥንት ውስጥ ተጣብቀው የሚገኙ ናቸው። የዚህ አካል አቀማመጥ እና የሚያደ ርገው ድጋፍ ማህጸኑ እዛው ቦታ ላይ ሆኖ እንዲቆይ የሚያደርጉ በአካባቢው ያሉ  ጅማቶ ችን፤ ጡንቻዎችን እንዲሁም አጥንቱ እና ነርቮቹ ሁሉ ተዳምረው ማህጸንን ከቦታው ሳይን ቀሳቀስ እንዲኖር ለማድረግ የሚረዱ ናቸው፡፡ የሴት ልጅ ሌሎች አካላት ማለትም የሽ ንት ፊኛ እና ትልቁ አንጀት(ደንዳኔ) ጭምር ከማህጸን ፊትና ሁዋላ የሚገኙ ሲሆን እነ ዚህም ከቦታቸው ወደውጭ ሳይወጡ እንዲኖሩ የሚያደርጉ ድጋፎች በአጥንቱ፤ በጡን ቻው፤ በጅ ማቶች ይደረግላቸዋል፡፡  ጅማቶች አካላቱን ከአጥንቱና ማህጸኑ ጋር በማያያዝ ማህጸኑም ሆነ በአካባቢው ያሉ አካላት ከቦታው ሳይንቀሳቀሱ እንዲኖሩ ያስችሉአቸዋል፡፡
ማህጸን ማለትም ልጅ የሚሸከመው አካል ከፊት ለፊቱ የሽንት ፊኛ እንዲሁም ከሁዋላው ደግሞ ደንዳኔ የተባለው ትልቅ አንጀት ይገኛል። ማህጸን በእነዚህ የውስጥ አካላት አማካ  ኝነት ወደላይ ተደግፎ የሚኖር አካል ነው፡፡ ማህጸን በተፈጥሮው ያገኘውን መደገፊያ ጥን ካሬ በሚያጡበት እና በሚላሉበት ወቅት ማህጸን ወደ ብልት ወደታች እየተገፋ ይመጣል። በዚህ ጊዜ ማህጸን ብቻም ሳይሆን የሽንት ፊኛና ደንዳኔውን ደግፎ የሚይዘው ብልትም ወደውጭ ይወጣል፡፡ ማህጸን ወደውጭ ይወጣል ሲባል አራት ደረጃዎች አሉት። ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕምና እስፔሻሊስት ከአሁን ቀደም እንደነገሩን፡፡
ልጅ የሚሸከመው የማህጸን ክፍል ወደ ብልት መንጠልጠል ይጀምራል፡፡
ማህጸን በብልት አካባቢ ክፍት ወደሆነው ቦታ በመውረድ ይቀመጣል፡፡
ማህጸን በብልት በኩል መውጣት ይጀምራል፡፡
ማህጸን እንዲሁም ብልት ተያይዘው ሙሉ በሙሉ ወደውጭ ይወጣሉ፡፡
የማህጸን ወደውጭ መውጣት በምን ምክንያት ያጋጥማል? ማዮ ክሊኒክም ሆነ ዶ/ር ዳዊት የገለጹት ተመሳሳይ ምክንያቶችን ነው::
ዋናው ምክንያት እድሜ ነው፡፡ ሴቶች በማንኘውም እድሜ የማህጸን መውጣት ሊያጋጥ ማቸው የሚችል ሲሆን በዋናነት ግን እድሜአቸው ለወር አበባ መቋረጥ የደረሰ ሴቶች ላይ ይከሰታል፡፡ በወር አበባ መቋረጥ እድሜ ክልል ያሉ ሴቶች ኢስትሮጂን የሚባለው ቅመም በሰውነታቸው መመረቱን ስለሚያቆም የጡንቻዎች መላሸቅ ይጀምራል፡፡
ሌላው ችግር ከመውለድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመውለድ ጊዜ ኪሎአቸው ከበድ ያሉ ልጆችን በመውለድ ወይንም ለረጅም ጊዜ በምጥ ላይ መቆየት እንዲሁም ብዙ ልጆችን መውለድ ለማህጸን መውጣት ችግር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
ልጅ በማዋለድ ወቅት የልጅ ጭንቅላት አልወጣ ሲል ወይንም በተለያየ ምክንያት ለመርዳት ሲባል የሚጠቀሙበት ዘዴ ለማህጸን ከቦታው መልቀቅ ምክንያት ሊሆን የሚችልበት አጋ ጣሚ መኖሩም በባለሙያዎች ይገለጻል፡፡  
ከፍተኛ የሆነ ውፍረት ለማህጸን መውጣት ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ውፍረት በራሱ በማህጸን አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን እንዲላሉ ማድረግ ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የሆድ እቃ ግፊት መብዛትም ለማህጸን መውጣት እንደ አንድ ምክንያት ይወሰዳል፡፡
እንደ ሳል፤የሆድ ድርቀት የመሳሰሉተ ሕመሞችም ለማህጸን መውጣት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የማህጸን መውጣት ሲያጋጥም ምን አይነት ስሜቶች ይኖራሉ?
የወገብ አጥንት ላይ ክብደት ወይንም የመጎተት ስሜት ይኖራል፡፡
በብልት በኩል ጎልቶ የሚወጣ ስጋ መሰል ነገር መኖሩ ይሰማል፡፡
ሽንትን በመሽናት በኩል በትንሽ ትንሽ (ጭርቅ ጭርቅ)እንደሚባለው ወይንም የመሽናት ሁኔታ መዘግየት ሊኖር ይችላል፡፡
በትንሽ ኳስ ላይ እንደተቀመጡ ወይንም ከብልት ውስጥ አንድ ነገር እየወደቀ እንዳለ ያለ ስሜት ሊሰማ ይችላል፡፡
ወሲባዊ ግንኙነትን በሚመለከት በብልት አካባቢ ያለው ስሜት ሴትየዋ ወሲብን እንደማት ፈልግ፤ወይንም ያ የፍላጎት ስሜትዋ እንደተቋረጥ አድርጋ እንድታስብ የሚያደርግ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ስሜቶች ምናልባትም በጠዋቱ ጊዜ ብዙም የማይሰሙ ቢሆኑ እንኩዋን ቀኑ እየጨመረ ወይንም እየመሸ ሲሄድ ግን ጭንቀቱ እና መረበሹ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በጠዋቱ ጊዜ ህመሙ ላይሰማ ይችላል ማለትም ሌሊቱን በመኝታ ስለሚያሳልፉ በመጠኑ መረጋጋት ስለሚኖር ሊሆን ይችላል፡፡ የማህጸን መውጣት አይነት ሕመም በአንዳንድ በወገብ (የደም ጋን) አካባቢ ባሉ የውስጥ አካላት ላይም ይከሰታል፡፡  
ለምሳሌም የሽንት ፊኛን እና የሴት ብልትን ለያይተው የሚይዙ ጡንቻዎች ወይም ጅማቶች ድክመት ወይንም መላላት፤ መሳሳት ሲገጥማቸው የሽንት ፊኛው በማበጥ ወደ ብልት ሊንሸራተት ይችላል፡፡ Anterior Prolapse (systocele) በመባል የሚታወቀው መንሸራተት የሽንት ፊኛ መንሸራተት በሚል ይታወቃል፡፡
ሌላው በህክምናው ቋንቋ Posterior vaginal prolapse (rectocele) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ፊንጢጣን እና ብልትን ከፍሎ ለየብቻቸው እንዲሆኑ የሚይዘው ጡንቻ ወይንም ጅማት መላላት ወይንም መድከም የሚያመጣው የብልት መንሸራተት ችግር ነው፡፡
የማህጸን መውጣት አስከፊ ገጽታው ብልት ላይ በሚያደርገው ግፊት የተነሳ የብልትን ቅር ጹን ወይንም አቀማመጡን በማበላሸት ማህጸኑ ወደታች በመገፋት በብልት በኩል ጎልቶ በመውጣት ተፈጥሮአዊ ሁኔታውን መለወጡ ነው፡፡ በብልት አካባቢ የሚለበሱ ልብሶች ጋር በሚፈጠረው መነካካት ወይንም መፈጋፈግ የተነሳ ከብልት ተንሸራቶ በወጣው አካል ላይም ጭምር መቁሰል ፤መድማት መከሰቱ ሌላው አስከፊ ገጽታው ነው፡፡ ቁስለት ሲከሰት በሚፈ ጠረው ኢንፌክሽን ምክንያት ሴትየዋ ሕክምና ካላገኘች ከፍተኛ ወደሆነ ጉዳት ልትገባ ትችላለች፡፡
የማህጸን መውጣት እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡
የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በተለይም በብልት አካባቢ ወይንም በወገብ አካባቢ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን መርዳት ፤ማጠንከር በመሳሰለው ሁኔታ በብልት አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን ለማጠ ንከር መሞከር ይጠቅማል፡፡ በተለይም ልጅ ከወለዱ በሁዋላ በማህጸን ዙሪያ ያሉ ጡንቻዎች እንዲጠነክሩ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ፈሳሽን መጠጣት፤ ምቹ የሆኑ ሆድን የሚያለሰልሱ (ፍራፍሬ፤ አትክልት፤ ባቄላ፤ የመሳሰሉ ምግቦችን መመገብ ይጠቅማል፡፡
ከፍተኛ ሳልን መቆጣጠር ያስፈልጋል ፡፡ እንደ ብሮንካይትስ ያለ ህመምን በህክምና መርዳት በሚከሰተው ሳል ምክንያት የሚኖረውን ግፊት ይከላከላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሳልን ለመቀነስ ወይም እንዳይከሰት ለማድረግ ሲጋራ ማጤስን ማቆም ይመከራል፡፡
ከፍተኛ ውፍረትን ማስወገድ የማህጸን መውጣት ችግር እንዳይመጣ ይረዳል፡፡

  ሩስያ በዩክሬን የከፈተችው ጦርነት በመላው አለም እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የሸቀጦች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ሊያስከትል እንደሚችል የአለም ባንክ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስጠንቅቋል፡፡
የሁለቱ አገራት ጦርነት በመላው አለም ከተፈጥሮ ጋዝ እስከ ስንዴ እና ጥጥ በተለያዩ አይነት ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል የተነበየው ባንኩ፣ ጦርነቱ እስካሁን ያስከተለው የዋጋ ጭማሪ በአለማችን ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ሰብዐዊ ጫና እያደረሰ እንደሚገኝም ማመልከቱንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የምግብ እህሎች ዋጋ ባለፉት 60 አመታት ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆመው ባንኩ፣ በቀጣይም በርካታ የምግብ እህሎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና የስንዴ ዋጋ በ42.7 በመቶ፣ የገብስ ዋጋ በ33.3 በመቶ፣ የዘይት ዋጋ በ29.8 በመቶ ያህል ሊጨምር እንደሚችል ነው በትንበያው የገለጸው፡፡
የዋጋ ጭማሪው በተለይም በድህነት ውስጥ የሚገኙ የአለማችን ዜጎችን ለከፋ አደጋ እንደሚያጋልጥ የጠቆመው የባንኩ ትንበያ፣ የሃይል ዋጋ በ50 በመቶ ያህል ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅና በተለይ ከፍተኛው የአውሮፓ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በእጥፍ  ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ያመለክታል፡፡

የሞላ ሽንት ቤት
ጭር ያለ ቤተሰብ
የተጠረገ ድስት፥ ድርቅ የመታው ሞሰብ፥
ያደፈ ቄጤማ
በበግ በሰው እግር ፥የተደቀደቀ
ወዙ ባንድ ሌሊት፥ ተመጦ ያለቀ
መጥረጊያ ሚጠብቅ ፥ወድቆ ተበታትኖ
ትናንት ጌጥ የነበር፥ ዛሬ ጉድፍ ሆኖ፥
የተወቀጠ ፊት ፥ የነጋበት ድንገት
በዳንኪራ ብዛት፥ወለም ያለው አንገት ፡ :
የዞረበት ናላ ፥ጌሾ ያበከተው
እንኳንስ መገንዘብ፥ መጀዘብ ያቃተው ::
የወለቀ ወገብ፥ የዛለ ትከሻ
መኪና ይመስል፥ ብየዳ የሚሻ ::
የጠጅና የጢስ ፥ድብልቅ እስትንፋስ
ከሆድ ሸለቆ ውስጥ፥ የታፈነ ነፋስ
ባንጀት የታሰረው
እንደተከበበ አመጸኛ ሽፍታ፥ መውጫ የቸገረው ፥
የማይፈካ ሰማይ፥ የማይዘንብ ደመና
በላባና በፈርስ፥ ያደፈ ጎዳና
በበግ የራስ ምላስ የተልከሰከሰ
የጠገበ ውሻ
በመንፈቅ አንድ ጊዜ ፥ አጥንት የቀመሰ ፥
ሀንጎበር ያዛገው ፥ መሂና አሽከርካሪ
እግረኛ አስደንባሪ
በከፊል የነቃ፥ በከፊል የተኛ
ከሱ የማይሻል፥ የመኪና እረኛ
ካውራ ጎዳናው ዳር፥ ቆሞ ሚያንቀላፋ
ድብርትን ባናቱ፥ እንደቆብ የደፋ
….
የተድላ ማገዶ
ላጭር ጊዜ ነዶ
ላጭር ጊዜ ደምቆ
ላጭር ጊዜ ሞቆ
አመዱ ብዙ ነው ፥ አያልቅም ተዝቆ፤
(አዳምኤል ከተሰኘው መድብል የተወሰደ)

  በ7 ቀናት የሞቱት 15 ሺህ ያህል ሰዎች ብቻ ናቸው

             እስካለፈው ረቡዕ የነበረው አንድ ሳምንት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተስፋፍቶ ከጀመረበት መጋቢት ወር 2020 ወዲህ በመላው አለም ዝቅተኛው የኮሮና ሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት እንደሆነና በሰባት ቀናት ውስጥ በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር 15 ሺህ ያህል ብቻ መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ቅናሽ ማሳየት መጀመሩ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፤ የምርመራ መጠን መቀነሱ ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ሊያሰናክል የሚችል ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ቫይረሱ ለሞት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር 6 ሚሊዮን ያህል ነው ተብሎ በይፋ ቢነገርም፣ ትክክለኛው መጠን ግን ከሚባለው ከሶስት እጥፍ በላይ ሊበልጥና 18 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል በቅርቡ በላሰንት መጽሄት ላይ የወጣ ጥናት ማመልከቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 የአለማችን ቁጥር አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ የጃፓኑ ቶዮታ ሞተር ኮርፖሬሽን እስካለፈው መጋቢት ወር ባለው አንድ አመት 9.51 ሚሊዮን መኪኖቹን ለአለማቀፍ ገበያ ማቅረቡንና ይህም በታሪኩ 2ኛውን ከፍተኛ አመታዊ ሽያጭ ሆኖ መመዝገቡን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው ባለፈው መጋቢት ወር ብቻ ከ903 ሺህ በላይ መኪኖቹን መሸጡን፣ በ12 ወራት ውስጥ ያስመዘገበው አጠቃላይ ሽያጭም 9.51 ሚሊዮን መድረሱንና ይህም ከዕቅዱ በላይ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 8.57 ሚሊዮን መኪኖችን ማምረቱን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ምንም እንኳን በአመቱ የግዢ ጥያቄዎች ቅናሽ ቢያሳዩበትም 9.4 ሚሊዮን መኪኖችን ለመሸጥ አቅዶ 9.51 ሚሊዮን መኪኖችን ለመሸጥ መቻሉን የጠቆመው ብሉምበርግ፣ ለሽያጩ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ምርቶቹ መካከልም  በእስያና በሰሜን አሜሪካ ገበያ በብዛት የተሸጡት ራቫ4 ሱቭ ሞዴል መኪኖቹ እንደሚገኙበት ገልጧል፡፡

 በፈረንጆች አመት 2021 አለማቀፍ ወታደራዊ ወጪ ካለፈው አመት የ0.7 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 2.113 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንና ወጪው ከ2 ትሪሊዮን ዶላር ሲያልፍ በታሪክ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲቲዩት የተባለው ተቋም ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ ወታደራዊ ወጪ ዘንድሮም ለ7ኛ ተከታታይ አመት ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአመቱ 801 ቢሊዮን ዶላር ያወጣችው አሜሪካ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛውን ወታደራዊ ወጪ ያወጣች ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ቻይና በ293 ቢሊዮን ዶላር፣ ህንድ በ76.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚከተሉም ያሳያል፡፡
በአመቱ አሜሪካ ወታደራዊ ወጭዋን በ1.4 በመቶ ያህል ብትቀንስም ቻይና በበኩሏ ለ27ኛ ተከታታይ አመት አምናም ወታደራዊ ወጪዋን በ4.7 በመቶ ያህል መጨመሯን ያሳየው ሪፖርቱ፣ በአመቱ በመላው አለም ከተመዘገበው አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ 62 በመቶውን ያወጡት አምስት የአለማችን አገራት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ እንግሊዝና ሩስያ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችው ሩስያ በአመቱ ወታደራዊ ወጪዋን በ2.9 በመቶ በመጨመር 65.9 ቢሊዮን ዶላር ማድረሷን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ዩክሬን በበኩላ 5.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ወጪ ማድረጓን ነው የሚያሳየው፡፡

 ከዕለታት አንድ  የቅዳሜ ሹር ለት፣ ቤተ ክርስቲያን የ“ፈስኩ” ደውል ከተደወለ በኋላ፣ የአንድ ቤተ-ሰብ መላው አባላት እቤት ተሰብስበዋል፡፡ የመጀመሪያው ወንድ ልጅና የመጨረሻ ትንሿ ሴት ልጅ፣ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ሄደው እናትና አባታቸውን ይዘው ነው የመጡት። መካከለኛውና ሞገደኛው ወንድ ልጅ ግን ቤት ተኝቶ ነበርና በመከራ ተቀስቅሶ ነው ወደ ገበታው የቀረበው!
እንደተለመደው አባት እንጀራውን እየቆረሱ፣ “የተባረከ ይሁን!” እያሉ ለሁሉም  ሰጡ፡፡ ቀጥሎም ያው  እንደተለመደው ለአባ-ወራው ፈረሰኛ ወጣላቸው፡፡
ሞገደኛው ልጅ - “እኛስ?” አለ
እናት - “እንግዲህ ነገር አታምጣ - በተራህ ይሰጥሀል” አሉት፡፡
በድንገት አንድ ጥቁር እንግዳ፣ የአባትየው ጓደኛ ከተፍ አሉ፡፡
ሞገደኛው ልጅ - “ይሄውላችሁዋ እንደፈራሁት!; አለ
እናት - “እንግዲህ እረፍ ብዬሀለሁ፡፡ ዶሮው እንደሆነ ለአስር ሰውም ይበቃል!”
ሞገደኛው ልጅ - “ለእኔ በጊዜ ድርሻዬን ስጡኝ። ገና የእማማ ነብስ አባት ከች ይሉላችኋል!”
ከደጅ ድምጽ ይሰማል፡፡
“እንደምን አመሻችሁ?” አሉ፡፡
“ደሞ መምሬ ሞገስ መጡላችሁ! እሳቸው ደግሞ ያገሬ ዲያቆን አስከትለው ነው እሚመጡት”
ዕውነትም መምሬ ሞገስ አራት ዲያቆናት ይዘው ነው የመጡት።
አባት - “ይባርኩልና መምሬ!?”
መምሬ ሞገስ ተነስተው መድገም ጀመሩ፡፡
ሞገደኛው ልጅ ፀጉሩን ነጨ፡፡  ምን ማድረግ ይችላል? ምንም አስቸጋሪ ልጅ ቢሆንም፣ የአገር ባህል ይገባዋል፡፡ ባህልን ትኖረዋለህ እንጂ አትማረውም!
“እስቲ ደህና አርፌ የተኛሁትን ቀስቅሳችሁ ትጫወቱብኛላችሁ” አለ ወደ አባቱ እያየ።
አባቱም፤
“ለአንድ ሌሊት ብትነቃ ምን ትሆናለህ? በዓል ሽሮ የከበረ፣ፆም ገድፎ የወፈረ የለምኮ!” አሉት፡፡
አርፎ ዶሮዋን መጠበቁን ቀጠለ፡፡
ዶሮይቱ ሙሉ በሙሉ እንደቀረበች፣አባትዬው፤
“በሉ እንደተለመደው የምትፈልጉትን ብልት  ተናገሩ?” አሉ፡፡
የመጀመሪያው ወንድ ልጅ፤
“አባዬ ለእኔ እንደተዳረሰላችሁ ይሰጠኝ”
የመጨረሻዋ ሴት ልጅ፣
“ለእኔ ቆዳዋም ቢደርሰኝ ደስ ይለኛል!”
ሞገደኛው ልጅ፤
 “ከየአንዳንዳችሁ ትንሽ ትንሽ!”
አባት፤
“አንት የማትረባ! የራስህ ምርጫ የለህም?; ብለው ተቆጡ።
ሞገደኛው ልጅ፤
“ምርጫ አለኝ ግን ያንሰኛል ብዬ ነው! በዛ ላይ የእናንተ ድርሻ (ምርጫ) ምን ምን እንደሚል ባውቅ ምናለበት?” አለ ይባላል፡፡
*   *   *
በማንኛውም መንግስት ዘንድ የህዝቡን ፍላጎት  ይሁነኝ ብሎ ማወቅ ዋና ነገር ነው፡፡ ያ ደግሞ ዋና ፍሬ ጉዳይ ነው የሚያሰኘው የህዝቡን ባህልና ልማድ መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲካውና ኢኮኖሚው ላይ  ስናነጣጥር፣ ባህልን ቸል የማለት አዝማሚያ ይታይብናል። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ግን የሁሉም መጠቅለያና መሰብሰቢያ የህዝቡ ሥነ-ልቦና፣ አኗኗሩና ማህበራዊ እሴቱ ሆኖ እናገኘዋለን! ዕምነቱ፣ ትውፊቱ፣ አፈ-ታሪኩ፣ ተረቱ፣ ቅኔው ወዘተ ከየትም አይፈልቅም፤ ከባህላዊ ሕላዌው ነው፡፡ ለቅሶው፣ ሙሾው፣ ዘፈኑ፣ዜማው፣እስክስታው፣ዜማውና የሠርግ ሥነ-ሥርዓቱ ከየትም አይመጣም፡፡ ስረ ነገሩ ባህል ነው፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጠበብት፤ሁሉም ፖለቲካ፣ሁሉም ኢኮኖሚ በባህል ይንፀባረቃል ይበሉን እንጂ፣ አንዳንዴ ባህል ራሱን ችሎ የሚቆም ፅንሰ ሀሳብ ሆኖ የምናገኝበት ጊዜ ሊኖር  እንደሚችል በፍጹም አንዘንጋ! ኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ ባለቤት ናት፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፤ “መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር” በተባለው መፅሐፋቸው ላይ፤
“በየአንዳንዱም መንግስት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ስለ፣ ሆነ መንግስት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይደለም፡፡ አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግስት መቆሙ ለህዝቡ ሁሉ ጥቅም ነውና፣ መንግስት ሕዝቡን ሁሉ ለመጥቀም በትክክል ካላሰበ በዙፋኑ ሊቆም አይችልም፡፡ ላንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግስት የሚገባ ሥራው አይደለም፡፡; ይሉናል፡፡
በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው የዲሞክራሲ ረሃባችን፣ከምግብ አቅርቦት ረሀባችን ጋር ሳይነጣጠል እያጠቃን ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ማእቀፋችን፤ ከኢኮኖሚያዊ አንቀልባችን ጋር ተወዳድሮ  በአንድ ሁነኛ ማሰሪያ መቋጠር ይኖርበታል፡፡
“የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብቱና ዕውቀቱ ሊያድግ ሲጀምር ዘወት ባገሩ  ሁከትና ጦርነት ይነሳል” (ነጋድራስ ገ.ሕይወት ባይከዳኝ)
ዛሬም ይሄው አጣዬና ሸዋ ሮቢት ጦርነት ነው፡፡ ሰው ወደ ደብረብርሃን መሰደዱን ተያይዞታል። ሰሜን ሸዋም እዚያው አረንቋ ውስጥ ነው፡፡ ተሻለው ሲባል ማገርሸቱ እንደ ባህል ተቆጥሯል፡፡ የመከላከያ ኃይሉን እንደ አዲስ ማስተማር ያስፈለገበት ጊዜ መሆኑ፣ ቢያንስ የቀጠናውን የጦርነት ስጋት ያመለክታል፡፡
“ሁሉ ነገር ይለወጣል፤ ከለውጥ ሕግ በስተቀር” (Everything changes except the law of change) የሚለው የጥንት ንድፈ-ሀሳብ እየተጫነን መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ለውጥ ሲሸታት የኑሮ ውድነትን ታስቀምጣለች።  ድርቋን ትሸሽጋለች፡፡ መሪዎቿ ዲስኩር ያበዛሉ፡፡ አዳዲስ የለውጥ ሕግ ሊያስተምሩን ይሞክራሉ፡፡ ድንቅና ተዓምረኛ ለውጥ ነው እያሉ ሲያስረዱን ቆይተው፣ “ገና ዛሬ ነው ያለቀው” ይሉናል፡፡ እንደተለመደው ኮሪያና ቻይና አርአያዎቻችን ሆነው ይጠቀሳሉ። “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ያበዛለት ነው” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ለመከላከያም፣ ለፖለቲካ ካድሬም፣ የሠራዊትን ከፖለቲካ መለየትም ድንገት እንደብራ መብረቅ ዱብ ዕዳ አድርገን ማየት የወቅቱ አቅጣጫ ነው፤ እንባላለን፡፡ ለማንኛውም ቅድም ተከተልን የመሰለ ለአገር የሚበጅ ጥበብ የለም! ለማንኛውም በዓል ሽሮ የከበረ፣ ፆም ገድፎ የወፈረ የለም!  

  የቁጫ ህዝብ በደልና መገፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና በዚህም ህዝብ የከፋ እንግልትና ሰቆቃ እየተጋፈጠ መሆኑን የቁጫ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ቁህዴፓ) አስታወቀ። ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ ቦሌ የሺ ህንፃ ላይ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር  ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቁጫ፣ በቁጫ አልፋና  በቁጫ ሰላም በር ከተማ “ ቁህዴፓን ለምን መረጣችሁ” በሚል ህዝቡ እስራት፣ መሰደድ፣ ከስራና ከንግድ መፈናቀልና ድብደባ እየተፈጸመበት ነው ሲል አማርሯል።
የቁጫ ህዝብ ለውጡ በፈነጠቀው አንጻራዊ ሰላምና ነፃነት ተጠቅሞ ለዘመናት የዘለቀውንና ያጎበጠውን ጭቆና፤ህጋዊ ሰውነት ባለው ፓርቲ ለመታገል ቁህዴፓን መመስረቱን ያስታወሱት የፓርቲው አመራሮች፤ በ6ኛው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1 ለክልል ምክር ቤት ተወካዮች ሶስት አባላቱ እንደተመረጡለት አውስተዋል። ይህን ተከትሎ ግን  በቁጫ ወረዳ፣ በቁጫ አልፋና በሰላም በር ከተማ ውስጥ ያሉ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በአካባቢው የብልጽግና አመራሮች ከስራ ከመታገድ ጀምሮ የእስራት፣ የግርፋት የንግድ ስራ መስተጓጎልና በርካታ ሰቆቃዎች እየደረሱበት መሆኑን የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታመነ በሌ በመግለጫው አብራርተዋል።
ያለመከሰስ መብት ያላቸውና ቁጫን ህዝብ ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የገቡት የተከበሩ ገነነ ገዴቦ (ረ/ፕ)፣ ከህዝቡ ጋር ለመወያየት ወደ ቁጫ ባቀኑበት ጊዜም በብልጽግና አመራች የመታገትና የመጉላላት ችግር የደረሰባቸው ከመሆኑንም በላይ  ከህዝብ ጋር እንዲወያዩ ተደርገው መኪናቸውን አዙረው እንዲመለሱ መደረጉንም  በመግለጫው ላይ ተገኝተው ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከሚሰሩበት ቦታ እየታደኑ ለወራት ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውንና ያለጥፋት ያለ ማስረጃ ለወራት ታስረው መለቀቃቸውን አቶ ታመነ ጨምረው ተናግረዋል።
የቁጫ ህዝብ በብዙ ጫና ውስጥ ሆኖ የመረጠው የምርጫ ውጤት እንዲታጠፍ በብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የተጀመረውን ክስ አጥብቀን እንቃወማለን ያሉት የቁህዴፓ አመራሮች ይህ ህገ-ወጥ ክስ የሚያሳየው የመራጭ ህዝቡን ሉአላዊነት፣ ክብርና መብትን የሚያሳንስ እና ሀገራችን የምታደርገውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚያቀጭጭ መሆኑን ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ፓርቲው ባወጣው ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫም በቁጫ፣ ወረዳ፣ በቁጫ አልፋ ወረዳና በቁጫ ሰላም በር ከተማና በመላ አገሪቱ በቁጫ ህዝብና በፓርቲው ቁህዴፓ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በጽንፈኝነትና በብሄርተኝነት ስሜት የቁጫ ማህበረሰብ አባላትን ከመንግስት ስራ ማፈናቀል እንዲቆም፣ በምርጫው ፓርቲያችን ቁህዴፓ ማሸነፉን ተከትሎ የብልጽግና አመራሮች ባደረባቸው ብስጭት የቁጫን መራጭ ህዝብ የእልህ መወጣጫ አድርጎ የተከፈቱት የእስር፣ የድብደባና ከፓርቲ አልባነት እንዲወጡ ማስገደድና መሰል በደሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ ቁህዴፓን መርጣችኋል በሚል የፓርቲውን አመራሮች፣ አባላትንና ደጋፊዎቹን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከየቀበሌው ለበርካታ ወራት እያሰሩ መቅጣት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የገዢው ብልፅግና ፓርቲ የቁጫ ህዝብ የምርጫ ውጤት እንዲታጠፍ የጀመረው ክስ ህጋዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ በአስቸኳይ ከዚህ እንቅስቃሴውእንዲቆም፣ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች በቁጫ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደልና እንግልት በማጋለጥ ከጭቁኑ የቁጫ ህዝብ ጎን እንዲቆሙና ለዘመናት የዘለቀው የቁጫ ህዝብ የማንነት ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ እንዲመለስ  ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን አቶ ባንዲራ በላቸውን፣ ከቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ የመጡ ፖሊሶች፣ በዛሬው ዕለት ከልደታ ፍርድ ቤት አስረው እንደወሰዷቸው የቁህዴፓ አመራሮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡


 ከአባቷ ከ፲ አለቃ ገሠሠ ነጋሽና ከእናቷ ወ/ሮ ስመኝ ዓለሙ፣ በቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት፣ ጎርጎራ ከተማ ሚያዝያ 27 ቀን 1956 ዓ.ም. የተወለደችው አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ፤ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን በቀዳማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡
ባደረባት ሕመም ምክንያት በተወለደች በ57 ዓመቷ፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ያረፈችው አርቲስት ዘነቡ፣ በነጋታው ሚያዝያ 17  በቦሌ ቡልቡላ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥርዓቷ ተፈጽሟል።
ሁለገቧ የጥበብ ባለሙያ አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ በተወዛዋዥነት፣ በድምፃዊነትና በተዋናይነት ከአርባ ዓመታት በላይ  ከፖሊስ ሠራዊት ኤርኬስትራ፣ እስከ ራስ ቴአትር አገልግላለች፡፡  
በቀድሞዋ የኤርትራ ክፍለ ሀገር በአስመራ ከተማ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ከጥበብ ጋር የተዋወቀችው  በ1970 ዓ.ም. ከተቀጠረች በኋላ ነው። በህይወት ታሪኳ ላይ እንደተገለጸው፣ በአስመራ በነበራት የአራት ዓመታት ቆይታ በተወዛዋዥነት፣ በድምፃዊነትና በአጫጭር ተውኔቶች አገልግላለች፡፡
ከዚያም በራስ ቴአትር በ1976 ዓ.ም. የተቀጠረችው አርቲስት ዘነቡ፤ በተወዛዋዥነትና በመድረክ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ከተውኔቱ ዓለም ይበልጥ በተዋወቀችበት ራስ ቴአትር ከተወነቻቸው ተውኔቶች መካከል ላጤ፣ የሰው ሰው፣ ዘር አዳኝ፣ አሻራ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
አርቲስቷ ከዚህም ባሻገር በሜካፕ፣ በአልባሳትና በቁሳቁስ ባለሙያነት፣ በአዳራሽና በሌሎች ኃላፊነቶችም በትጋት ማገልገሏ በህይወት ታሪኳ ላይ ተከትቧል፡፡
ሁለገብ አርቲስቷ ከተወነችባቸ  የሙሉ ጊዜ ፊልሞችና ሲትኮም ድራማዎች መካከልም "አያስቅም፣ ያለ ሴት፣ አስታራቂ፣ የከበረ ደሃና ሹገር ማሚ" በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ በህይወት ዘመኗ ላበረከተችው ሙያዊ አስተዋጽኦ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝታለች - ጉማ አዋርድ አንዱ ነው፡፡  
አርቲስት  ዘነቡ የሁለት ሴትና የሁለት ወንድ ልጆች እናት የነበረች ሲሆን፤ የሁለት ሴት ልጆችም አያት ለመሆን በቅታለች፡፡
         አምባሳደር ልብስ ስፌትና ንግድ ኃ.የተ.የግል ማህበር በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ ያሰራውን የገበያ ማዕከል (አምባሳደር ሞል) በቅርቡ ያስመርቃል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ፓርላማ ፊት ለፊት የተገነባው አምባሳደር ሞል፤ በቅርቡ ለምረቃ እንደሚበቃ የድርጅቱ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰኢድ መሃመድ ብርሃን ተናግረዋል።
ከ120 መኪኖች በላይ በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ እንዳለው በተነገረለት በዚሁ የገበያ ማዕከል፤ በአንድ ሰኮንድ 10 ሊትር ውሃ ለማምረት የሚችል የከርሰ ምድር ውሃ በቁፋሮ እንዲወጣና አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉም ተገልጿል።
አምባሳደር ሞል ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ታውቋል።  
ከ40 ዓመታት በፊት በአንድ የልብስ ስፌት ማሽን ስራ የጀመረው አምባሳደር ልብስ ስፌት ኃ.የተ.የግ.ማህበር አምባሳደር ሪልእስቴት፣ አምባሳደር ሆቴልና አምባሳደር ሞል የተባሉ ድርጅቶችን ማፍራት ችሏል።