Administrator

Administrator

•  በቅርቡ በድጋሚ ሊደረግ የታሰበውን ህዝበ ውሳኔ እንደማይቀበሉትም  ገልጸዋል

ሁለት የዎላይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤የወላይታ ዞን ወደፊት በሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ  ክልል ውስጥ ከሌሎች ዞንና ወረዳዎች ጋር እንዲደራጅ መወሰኑን በመቃወም፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ ክስ መመሥረታቸውን አስታወቁ፡፡ በቅርቡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድጋሚ ሊደረግ የታሰበውን ህዝበ ውሳኔ እንደማይቀበሉትም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን  የሚንቀሳቀሱት የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሲሆኑ፤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በ8 ሰዓት ላይ ቦሌ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጽ/ቤት ውስጥ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) ሊቀ መንበር አቶ ጎበዜ ጎአ  እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ፣ የዎላይታ ህዝብ የራሱን ክልል ለመመሥረት ያቀረበው ህገመንግሥታዊ ጥያቄ እየተስተናገደ ያለበት ኢ-ህገመንግሥታዊ ሂደት ምን እንደሚመስል ያወጡትን መግለጫ በንባብ ካሰሙ በኋላ፣ የወላይታ ዞን ወደፊት በሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ  ክልል ውስጥ ከሌሎች ዞንና ወረዳዎች ጋር እንዲደራጅ መወሰኑን በመቃወም፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ ክስ መመሥረታቸውን ያስታወቁ ሲሆን በቅርቡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊደረግ የታቀደው ህዝበ ውሳኔ የዎላይታን ህዝብ የማይወክልና ሂደቱም ኢ-ሞራላዊና ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆኑ እንደማይቀበሉት ነው ያስታወቁት፡፡  

”ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ተደርጎ ውድቅ በተደረገው ህዝበ ውሳኔ ለደረሰው የጉልበት፣ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እንዲሁም የሞራል ኪሳራ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ተጣርቶ በህግ ሳይጠየቁ፤ ለዎላይታ ህዝብ የራሱን ክልል ለመመሥረት የሚያስችል ዕድል፣ ህገመንግሥታዊ መብት በተነፈገበት ድጋሚ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ መያዙ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ከህዝቦች እኩልነት፣ ከእኩል ተጠቃሚነትና ከእኩል ተደማጭነት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት ያለውና የህዝቡን ዕጣፈንታ አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ” ብለዋል፤ ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፡፡

ገዢው ፓርቲ በአሁኑ ሰዓት ዎላይታን ጨምሮ ስድስት ዞኖችንና አምስት ልዩ ወረዳዎችን ያለ ህዝብ ፍላጎት በሃይል በአንድ ክልል ጨፍልቆ ለማደራጀት የህዝብ ሃብት በማባከን ላይ ታች እያለ ይገኛል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ይህ በዎላይታ ህዝብ ላይ ህገመንግሥትን በሚጻረር መንገድ እየተፈጸመ ያለ አፈናና ኢ-ህገመንግሥታዊ ውሳኔ በህግ እንዲሻርና እንዲታገድ በፍርድ ቤት ክስ መሥርተናል ብለዋል፤ በመግለጫቸው፡፡

ፓርቲዎቹ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወላይታ ዞን ከሌሎች መዋቅሮች ጋር እንዲደራጅ ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሻርና የዞኑ ምክር ቤት ከአራት ዓመት ተኩል ገደማ በፊት ወላይታ ክልል እንዲሆን የሰጠው ውሳኔ እንዲጸና መጠየቃቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

 ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

 
        በቻይና ጓንጉዙ ውስጥ የሚገኘው ይህ ስፍራ ቁጥር 28 ዮንግክዢንግ ይባላል። ባልተለመደ ሁኔታ ይህ ባለ ስምንት ፎቅ አፓርትመንት የቱሪስቶችን ቀልብ ስቧል።እ.ኤ.አ በ2008 ዓመት በጓንግዙ አዲስ መንገድ ለመስራት፣ በሃይዙ አውራጃ  በርካታ ህንጻዎች እንዲፈርሱ ሲታቀድ፣  የ’ቁጥር 28 ዮንግክሲንግ ጂ’ ነዋሪዎች ግን ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርተዋል። አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ከአልሚዎች ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ቤታቸውን ሽጠው ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር ቢወስኑም፣ በአሁኑ ጊዜ ታዋቂ የሆነው ቢጫ አፓርትመንት ውስጥ ሦስት ነዋሪዎች ግን ጥያቄያቸው ካልተሟላላቸው፣ ቤታቸውን ጥለው ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ድርድር ያደርጋሉ። በመጨረሻም፣ ገንቢዎች ድርድሩ የማያዋጣቸው መሆኑን ሲያውቁ፣ በምትኩ በህንፃው ዙሪያ መሻገሪያ ለመገንባት ወሰኑ። ዛሬ ላይ  በመንገድ የተከበበው ህንፃ የቱሪስት መስህብ ሆኗል። በThat’s Mags መፅሔት ዘገባ መሠረት ፣ ባለ ስምንት ፎቅ አፓርትመንት ውስጥ አሁን ላይ የቀሩት ጉኦ ዚሚንግ እና ወንድሙ ብቻ ናቸው ፣ 30 ካሬ ሜትር ብቻ ስፋት ካለው ቤታቸው ለመውጣት ፈቃደኛ አልሆኑም። ምንም እንኳን የመካካሻ ዕድል ባይኖራቸውም ።  አፓርታማው አሁንም የውሃና የመብራት አቅርቦት ያለው ሲሆን፤ በእግር መንገድ ርቀት የአውቶቡስ ጣቢያና ሱፐርማርኬቶች ይገኛሉ።         (Via ዳጉ ጆርናል)



  ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

 ማርዮ ፑዞ በጠባብ መኖሪያ ክፍሉ ውስጥ ተመስጦ በታይፕ ራይተር እየጻፈ ነው። ነገር ግን ብዙም ሳይርቁ እየተጫወቱ የነበሩት የአምስት ልጆቹ ድምፅ ከተመስጦው እያወጣው ሲቸገር. ..ወደ ልጆቹ ዞሮ እስኪ አንድ ጊዜ ዝም በሉ  አላቸው።
”በአለም ዝነኛ የሆነ፡ በብዙ ሺህ ኮፒ ሊሸጥ የሚችል የሚገርም መፅሀፍ እየጻፍኩ ነው። ድምጻችሁን  ቀንሱ ወይም ራቅ ብላችሁ ተጫወቱ”
ማርዮ ፑዞ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ሲናገራቸው፤. . .. በተለይ ወንድ ልጁ ቶኒ በአባቱ ንግግር ተገረመ ። ምክንያቱም አባቱ ይህን በሚናገርበት ወቅት. ..  ዝነኛ መፅሐፍ ፅፈው በብዙ ሺህ ኮፒ ከሚሸጥላቸው ታዋቂ  ደራሲያን ተርታ የሚመደብ ሰው አልነበረም።ማርዮ ፑዞም ይህን እውነት ያውቃል። የመጀመሪያ ስራው ከሆነው The Dark Arena ጀምሮ እስካሁን የጻፋቸው መፅሐፍት. . ስምም ሆነ ብዙ ብር እንዳላስገኙለት፣ ሌላው ቢቀር የተሻለ ኑሮ እንኳን እንዲኖር እንዳላስቻሉት ያውቃል። ይህ ያለፈ ታሪኩ ነው። አሁን ግን ይህን ነገር ለመለወጥ ቆርጦ ተነስቶአል ። ለዛም ነው ለልጆቹ  ”በአለም የታወቀ ዝነኛ መፅሐፍ እየጻፍኩ ስለሆነ አትረብሹኝ” ያላቸው ።
ማርዮ ፑዞ ይህን ካለ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ያንን ታሪኬን ይለውጠዋል ብሎ ወስኖ የጻፈውን መፅሐፍ አሳተመ።ይህ መፅሀፍ እንደታተመም ፡ የጋዜጦች የፊት ገፅ በሱ ፎቶዎች ተጥለቀለቁ። አለም ቆሞ አጨበጨበለት ። ይህ ብቻ አይደለም፡
ባልተስተካከለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ፣ ነገን አሻግሮ በማየት የጻፈው መፅሐፍ፣ በአለም ዙሪያ ከ21 ሚሊዮን በላይ ኮፒዎች ተሸጠ። በአለማችን ካሉት የምንጊዜም ምርጥ ልቦለድ ስራዎች መሀከልም The Godfather ዋንኛው ሆኖ ተመዘገበ።
ስሙ ከዝነኛ ደራሲያን ተርታ እጅግ ርቆ ባለበት ወቅት ማርዮ ያስብ የነበረው የነገውን ስኬታማነቱን ነበር። ያ ራእይ ወዳላሰበው ከፍታ ገፋው ።
The Godfather መፅሐፍ  አማርኛን ጨምሮ ፡ በብዙ የአለም ሀገራት ቋንቋዎች ተተረጎመ። የማርዮ ፑዞ ይህ ዝነኛ ስራው ወደ ፊልም ተለውጦም ፡ ከምንጊዜም ምርጥ ፊልሞች መሀከል አንዱ ከመሆኑም ሌላ፣ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል። ለመደምደሚያ ያህል. .. ማርዮ ፑዞ ይህ መፅሐፉ  ወደፊልም ሲለወጥ ፡  ስክሪፕት የመጻፍ ብዙም ልምድ ስለሌለው ፡ ከሌሎች ሁለት የስክሪፕት ፀሃፊዎች ጋር በመሆን ነበር የጻፈው። ፊልሙ ዝነኛ ሆነ። እና ግን ማርዮ ፑዞ የፊልም ስክሪፕት ራሱን ችሎ ለመጻፍ ሲል፡ የፊልም ፅሑፍ አጻጻፍን ለመማር የሚያግዘው አንድ መፅሐፍ ገዛ ። እና መፅሐፉን ማንበብ ሲጀምር. ..በመጀመሪያ ገፁ ላይ፤ ”የፊልም ስክሪፕት አጻጻፍ መማር የሚፈልግ ሰው በቅድሚያ The Godfather ን ደጋግሞ  ማንበብ አለበት” የሚል ፅሁፍ ነበር ያገኘው።
(ዋስይሁን ተስፋዬ)




Saturday, 03 June 2023 20:16

ቤት ለእንግዳ

በየጧት ይመጣል
ማለዳ ይመጣል
አዳዲስ እንግዳ!
ለሰው ፀጉረ-ልውጥ ለሀገሩ ባዳ።
እንደ ለሰው-ማሰብ ያለ አዲስ እንግዳ
እንደ ጭንቀት ያለ አዳዲስ እንግዳ
እንደ ሀሴት ያለ አዳዲስ እንግዳ
እንደ ሀዘን ያለ ቅስም እንደመስበር
ወይ እንደብልግና
ወይ እንደማቀርቀር
ድንገት ሳይጠበቅ ከተፍ የሚል ሀሳብ
አዳዲስ እንግዳ፣ ለቀልብ የማይቀርብ
ቀን በቀን ማለዳ
ሁሉም ይመጣሉ!
በል ተቀበላቸው!
ያዘን ማ´ት ቢሆኑም፤ ቤትን የሚያፈርሱ
ንብረት የሚያወድሙ
እንደ እንግዳ አክብረህ፣ በል ተቀበላቸው!
አንድ- ባንድ አጫውተህ
ለእያንዳንዱ ስቀህ
ኑ ግቡ በላቸው።
ማን ያውቃል ምናልባት፣ በእንግድነታቸው
ለተሻለ ደስታ እያዘጋጁህ ነው
እንግዳህ ብዙ ነው…
የጨለማ ሀሳብ የጽልመት ጥቀርሻ
የሀፍረት መቀመቅ የማንጓጠጥ ዋሻ
ሁሉም የአንተ እንግዶች፣ የአንተው እዳ
ናቸው
“ቤት ለእንግዳ´ኮ ነው ኑ ግቡ” በላቸው።
በሳቅ አጅባቸው።
ለአዳዲስ ሀሳቦች ደግ ሁን ውለታ ዋል
ምናልባት ማን ያውቃል?
የነገን ማን አይቷል?
ካልታወቀው አገር
ከወዲያኛው ማዶ
መንገድ እንዲመሩህ ተልከው ይሆናል!?
(ነ.መ)

Saturday, 03 June 2023 20:10

”ያለ ፈቃዷ አይሆንም!”

ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ


                   ”ያለ ፈቃዷ አይሆንም!”

        የጎጃሙ ንጉስ ተክለሀይማኖት ከሞቱ ከጥቂት አመታት በሁዋላ፣ ሴት ልጃቸው ወይዘሪት ንግስት፣ የዚህን ዓለም  ጣጣ ሸሽታ  በዲማ ገዳም ተቀምጣ ነበር፤ ብዙ ሳይቆይ አድራሻዋ ተደረሰበት! በዘመኑ ያሉት ሀያላን ወንዶች  ካላገባናት ብለው መፎካከር ጀመሩ፤ ከፖለቲካ ፋይዳው አንጻር ካየነው በጊዜው፥  የንጉሱን ልጅ ማግባት ሙሉ ጎጃምን እንደማግባት ነው! አንዱ የእቴጌ ጣይቱ የእህት ልጅ፣ ደጃዝማች ገሰሰ ሲሆን ሁለተኛው ተፎካካሪ የዳሞቱ ገዢ ራስ መርእድ ነበር፡፡
 እንደምትገምቱት ፥ በጊዜው ሴቶች በራሳቸው ላይ የመወሰን መብት አልነበራቸውም፤ ይመረጣሉ እንጂ አይመርጡም! ወይዘሮ ንግስትን የቱ ይሻልሻል ብሎ የጠየቃት የለም፤ እንደ አስቴር አወቀ  ”ነጻ ነኝ ! ነጻ ነኝ “ እያለች የመቀመጥ እድሉን አልሰጧትም::
 የዳሞቱ ገዢ ንግስትን ለማግባት ወስኖ በርበሬ መቀነጣጠስ   ጀመረ፤ በዚያ በኩል፥   እቴጌ ጣይቱ  ለዘመዳቸው በማዳላት “ ደጃች ገሰሰ ይሻልሻል “ የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ጻፉላት፤  ሴቲቱ ቢጨንቃት ለአጼ ምኒልክ “ እናቴም አባቴም እርስዎ ነዎት! እርስዎ ለወደዱት ይዳሩኝ “ የሚል ደብዳቤ ወደ ሸዋ ሰደደች:: አጼ ምኒልከ የመለሱት ምላሽ በአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቧል  ፥  በከፊል እንዲህ ይላል፤“አንቺ ልብሽ ከወደደው ፥ከሰዎች ጋራ መክረሽ ሂጂ ፥ ቢከፋሽ እኔ አለሁልሽ“
 ይህንን ያጼ ምኒልክ ምላሽ የዳሞቱ ገዢ  በሰማ ጊዜ ፥ ላጼ ምኒልክ  የተቃውሞ አቤቱታ አቀረበ፤  ንጉሱ ቃል በቃል እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ እሺ ታለች እኔ አልከለክልም ! ያለ ፈቃድዋ ግን አይሆንም! እዚያው እርስዋን ማቆላመጥ ነው”
 ዘመናይ  ከተሜ  አንባቢያን ፤ ማቆላመጥ የሚለውን ቃል  መጀንጀን፤ ማሞጋገስ ብላችሁ ልትረዱት ትችላላችሁ::
በወይዘሪት ንግስት ጉዳይ ዙርያ፥ የእቴጌ ጣይቱንና የባልየውን ምላሽ ሳነጻጽር፥ ለካ የመጀመርያው  የሴቶች መብት ሻምፒዮን ወንድ ኑሯል እላለሁ! በሌላ በኩል፤ ከመቶ አመት የዘገየ አስተሳሰብ ያለው  ወንድ በዘመናችን በመኖሩ እገረማለሁ፡፡
ሰሞኑን  የወልቂጤዋ  ቆንጆ የጠለፋ ዜና ሲወጣ፤  “ የኔ ባረገው ! ወይም በረከትሽ ይደርብን” አይነት ቀልድ ቀመስ አስተያየት የጻፉ ሴቶች  ታይተዋል፤  በነዚህ  ሴቶች ዙርያ ቁጣ አዘል ምላሽ ከወዳጆቻችን  ሲሰነዘር ነበር፤  ምላሹ ተገቢ መሰለኝ: :
 ግን ግን   እኒህ ሴቶች ኦሪጅናል ገልቱ፥ ወይም አምስት ኮከብ ሰገጤ መሆናቸውን እያወጁ ነው?   ወይስ ሴዲስት ናቸው?
 ( በሌላው ስቃይ የሚደሰት ሰው ሴዲስት ይባላል) ፤ ወይስ የራሳቸውን ፌንታዚ በልጂቷ ዜና ላይ እያንጸባረቁ ይሆን ?
ፌንታዚ (Fantasy)
ፌንታዚ ከራሳችን ያልተገደበ ሀሳብ ጋራ መጫወት ማለት ነው፤  ሰዎች እንደየ ምናባቸው ስፋት መጠን፣ የተለያዩ ስእሎችን በአአምሮቸው ይፈጥራሉ፤ ለመቀበል ከባድ ቢሆንም  የመጠለፍ  ፌንታዚ ያላቸው ሴቶች አሉ፤ እዚህ ጋ ወንዶች ልብ አድርጉ! ፌንታዚ  ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ላይሆን ይችላል፤  ሰዎች ድንገት በልቦናቸው  ሽው የሚልባቸውን   ሀሳብ ሁሉ  በገሀድ እንዲፈጸም ይፈልጋሉ ማለት አይደለም! ከሞላ ጎደል ሁላችንም የአደጋ ስሜት ይስበናል!  የአደጋ ስሜት ልብን በፍጥነት ያስመታል! ቀልብን ሰቅዞ ይይዛል፤ ከመሰላቸት ከመታከት ይገላግላል፤ ሆረር ፊልም ላይ የምንቸከለው ለዚያ ነው፡፡
 ይሁን እንጂ  የገሀዱ አለም ከህልም አለም የበለጠ ውስብስብ መሆኑን የኖረ  ያውቀዋል፤  ስልጣኔና ህግ የተፈጠረው ሰዎችን ካላስፈላጊ መከራ ለመታደግ ነው፤ የስልጣኔ ተካፋይ ነን ብለን የምናምን ከሆነ፥  “ያለ ፈቃድዋ አይሆንም!“ ማለት አለብን !
(በእውቀቱ ስዩም)





 ‘’በሥነ ጥበባት ሕብራዊ መልክ የተዋበች ኢትዮጵያ’’ በሚል መርህ ከተማ አቀፍ  የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል፣ ከነገ በስቲያ አርብ  ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት፣ በግዮን ሆቴል እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡  
የአዲስ አበባ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ የኪነጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሃት፤ ቢሮው በከተማዋ ያለውን የኪነ-ጥበብ ሀብቶች  በዕይታዊና ክውን ጥበብ  አጉልቶ ለማሳየት የሚረዳ ዓመታዊ ትልቅ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።ቢሮው ለ14ኛ ጊዜ ባዘጋጀው ፌስቲቫል፤ የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴዎችና ውድድሮች፣ ዐውደ ርዕይና ሥነ-ጥበባዊ ክዋኔዎች ይቀርባሉ ተብሏል።
 በፌስቲቫሉ ላይ በዕይታዊ ጥበባት፣ በክውን ጥበባት፣ በሥነ ፅሑፋዊ ጥበባት መስኮች ሥራዎች የሚቀርቡ ሲሆን በከተማዋ የሚገኙ የሥነ ጥበብ ተቋማት፣ ቴአትር ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች፣የውጭ  ዲፕሎማቶች፣ የሀይማኖት  ተቋማት ፣ ከ11ዱም ከተማ የተወጣጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የሙያ ማህበራት ይሳተፋሉ ተብሏል።

   ህብረት ባንክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከፍ ለማድረግና የተቀማጭ ገንዘቡን ለማሳደግ ለሦስተኛ ጊዜ ባካሄደው  “ይቆጠቡ፣ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩና ይሸለሙ” መርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ የዕጣ አሸናፊዎችን ትናንት ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በባንኩ ዋና መ/ቤት ሸለመ።
የዕጣው አሸናፊዎች ከሞባይል ቀፎ እስከ መኪና ድረስ ነው የተሸለሙት። በዚህም መሰረት፡- የቤት አውቶሞቢል አቶ ፀጋዘአብ ምንውዬለት ናቸው። አቶ ክንፈ ሃይሉና አቶ ግርማ ታደሰ አብዲሳ ደግሞ ባለ 3 እግር ተሸከርካሪ ተሸልመዋል።
 አቶ ግርማ ኤጀርሳና አቶ ይልማ የተባሉ ደንበኞች የውሃ መሳቢያ ሞተር ሲያሸንፉ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ያሸነፉት ደግሞ አቶ ሁሴን ኡመር መሃመድና አቶ እሸቱ ሽፈራው ናቸው።በተመሳሳይ አቶ ስለው ወርቁ ወ/ሚካኤልና አቶ ደርቤ ሳቀው አለማየሁ ፍሪጅ (ማቀዝቀዣ) ተሸልመዋል።
ሌሎች የባንኩ ደንበኞችም ስማርት ቴሌቪዥን፣ የውሃ ማጣሪያና ዘመናዊ የስልክ ቀፎ አሸንፈው ሽልማቶቹን ከባንኩ ከፍተኛ አመራሮች እጅ ተረክበዋል።



 በደራሲ ሰለሞን ደረሰ አመኑ የተሰናዳውና ለ67 ዓመታት በደራሲው ህሊና ውስጥ ሲጉላላ ነበር የተባለለት “የቀን ፍርጃ” መጽሐፍ ነገ ሀምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል።
መፅሀፉ ከ1940ዎቹ እስከ ኢትዮጵያ ሚሊኒየም 2000 ዓ.ም ድረስ ያሉ የደራሲው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ታሪኮችና ለ67 ዓመት ለደራሲው ምጥ ሆነው የቆዩ ድንቅ የሀገራችን ቤተሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና  ድብቅ ፍቅር ያመጣው መዘዝን ጨምሮ በርካታ አስደናቂ ታሪኮችን በውስጡ ይዟል።
ደራሲ ሰለሞን ደረሰ አመኑ ኑሮአቸውን በሀገረ አሜሪካ ካደረጉ የሰነበቱ ሲሆን ይህ መፅሐፋቸው ከ67 ዓመት በኋላ ለንባብ በቅቶ ለትውልድ መማሪያ ይሆን ዘንድ ሰሞኑን ወደ ሀገራቸው መግባታቸውም ተጠቁሟል።
በዕለቱ ከመፅሐፉ ጎን ለጎን የጥንቷ አዲስ አበባ ምን ትመስል እንደነበር የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ አውደ-ርዕይ፣ የመጽሐፍ ዳሰሳ፣ ከመጽሐፉ የተወሰዱ ታሪኮች ለታዳሚ የሚቀርቡበት መርሃ ግብርና ሌሎችም ጉዳዮች ይከናወናሉ ተብሏል። በዕለቱ ደራሲያን፣ ምሁራን፣ የስነ-ጽሁፍ አፍቃሪዎች የደራሲው ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላው እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል።



  በኮቪድ19 ወረርሽኝ ወቅት ከተጀመሩቀዳሚ ንቅናቄዎች አንዱ የሆነውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው “የጓሮ ማህበረሰብ” (Home Gardening Community) የተመሰረተበትን 3ኛ ዓመት ዛሬ ግንቦት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በፈንድቃ የባህል ማእከል በባዛርና ኤግዚቢሽን እንደሚከበር ተገለፀ፡፡ በጥንዶቹ ጋዜጠኛ ትእግስት ታደለና ስለሺ ባየህ የተመሰረተው “የጓሮ ማህበረሰብ”፤ ሰው ባለችው ጥቂት ክፍት ቦታ ላይ የጓሮ አትክልቶችንና ቅመማ ቅመሞችን ቢያመርትና ቢመገብ ወጪውን ሁለትም ኦርጋኒክ  የሆኑ ምግቦችን በመመገብ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ከማዳበር አንፃር ያለውን ፋይዳ በፊስቡክ ገፅ ለማስታወቅ “የጓሮ ማህበረሰብ” የተሰኘ የፌስቡክ ገፅ መክፈታቸውን ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው አቶ ስለሺ ባየህ ተናግሯል፡፡
በዚህ የፌስቡክ ገፅ ላይ ለየ ሀገራችን ቅመማ ቅመሞችና ዝርያዎች ስላላቸው ጥቅምና ለመሰል ጉዳዮች እየተፃፈና የጓሮ ማህበረሰብ አባላት መረጃ እየተለዋወጡ ከቆየ በኋላ ይህ እሳቤ እያደገ መጥቶ ዛሬ ላይ ከ30 ሺህ በላይ ተከታዮችን ማፍራት መቻሉንም አቶ ስለሺ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ይህንኑ ስራ ህጋዊ ሰውነት ባለው ተቋም ለማከናወን “ጓሮ ሚዲያ ኤቨንትስና ፕሮሞሽን” የተሰኘ ተቋም በማቋቋም በርካታ ፋይዳ ያላቸውን ስራዎች እያከናወኑ እንደሚገኙ የተናገረው መስራቹ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት አትክልቶችና ቅመማ ቅመሞች የሚለዋወጡበት፣ ስለጓሮ ጠቀሜታ ውይይትና ተሞክሮ የሚካፈሉበት የጓሮ ማህበረሰብ ባዛርና ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ዛሬም 3ኛ ዓመቱን በደመቀ ባዛርና ኤግዚቢሽን እንደሚያከብር አቶ ስለሺ ተናግሯል።
በባዛር ኤግዚቢሽኑ ላይ ኦርጋኒክ ማር አምራቾችና ከተፈጥሮ ዕፅዋት የውበት መጠበቂያ ምርት አምራች ኩባንያዎች በርዕስ ጉዳዮ ዚሪያ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል። በዕለቱም ምሁራን፣ ከጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ከተፈጥሮና ኦርጋኒክ ምግቦች አንጻርና ከተለያዩ ጉዳዮች አኳያ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ተፈጥሮን በመንከባከብ ለተተኪ ትውልድ ያቆዩ ጀግኖች የሚመሰገኑበት መርሃ ግብርም እንደሚኖር አቶ ስለሺ ባየህ ገልፀዋል።

 የአጫጭር ልብወለዶች ነው መጽሐፉ - “አዎ! እሱ ጋ ያመኛል” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ:: የአድኃኖም ምትኩ ድርሰት።
የትረካዎቹን ጠቅላላ ይዘትና የድርሰት ጥበቦቹን በደፈናው ከመዳሰስ፣ ከዳር እስከ ዳር ከመቃኘት ይልቅ፣ ሁለት አጫጭር ትረካዎችን በምሳሌነት ብንመለከት መርጫለሁ። የትኛውን እናስቀድም?
ሁለቱም ትረካዎች ፈጣን ናቸው። - የመስፈንጠሪያ ሰበባቸው ምንም ሆነ ምን፣ ወደ ዋናው ታሪክ ይንደረደራሉ። ጥሩ ነው። ለነገሩ፣ ረዥም ልብወለድም፣ ገና ከመነሻው ወደ ታሪኩ ህብለ ሰረሰር ቢገሰግስ ይመረጣል። ለአጭር ልብወለድ ግን፣ ፍጥነት የግድ ነው።
ተዓማኒነትንና አስደናቂነትን አንድ ላይ የማዋሀድ ጥበብም አሟልተዋል - ሁለቱም አጫጭር ትረካዎች።
በአንድ በኩል፣ የገፀባሕርያትና የታሪክ ተዓማኒነትን፣…
 በሌላ በኩልም ያልተጠበቁ አስደናቂ የታሪክ ቅያሶችን ወይም እጥፋቶችን በብልሃት ማሟላት፣ አንዱ የጥበብ መለኪያ ነውና።
እስቲ እኛም ለመፍጠን እንሞከር። አንዱን እናስቀድምና፣ ከአጀማመሩ ተነስተን ትረካውን እንመልከት፤ እናጣጥም።
ከቀልድ እስከ ረዥም ልብወለድ፣ ከአጭር ግጥም እስከ ትያትር ሁሉም የፈጠራ ድርሰቶች፣ የዚህ ተዓምር ጌቶች ናቸው። ተዓማኒ የታሪክ ጅረትንና አስደናቂ የታሪክ እጥፋትን በአንድነት ማዋሃድ፣… ለዚያውም በፍጥነት!
ኀሰሳችን ከሽፎ እንጂ
“ጥዑም ጊዜ ላይ ነበርን። ወይን እየተጎነጨን፣ እየተሳሳምን”…
የትረካው አጀማመር፣… ያው፣… “መዋደዳቸውን ያዝልቅላቸው” የሚያስብል ነው። “መጨረሻቸውን ያሳምርላቸው” የሚያሰኝ፣ ከፍቅር ታሪክ ውስጥ የተቀነጨበ አንድ ጥዑም ጊዜ ሳይሆን ይቀራል? ጨዋታቸውም፣… ዘና ያለ፣ ደግሞም ከልብ የመነጨ ይመስላል። እንዲህ ይላል።
ትክ ብዬ ሳያት፣ ፈገግ ብላ፣ “እቺን የመሰለች ልጅ ጠበስክ ኣ?” አለችኝ -ወደ ራሷ እያመለከተች። በትንሹ ፈገግ አልኩ። ፈገግታዬን እንደ መስማማት ቆጥራ፣ የሚያምር ፈገግታዋን እያሳየችኝ፣ “እናትህማ መርቀውሃል” ስትለኝ”፣…
የትረከካውን ጅረት እየተከተላችሁ፣…የሚያስቀና ፍቅር ብላችሁ ልታደንቁ ትችላላችሁ። ነገር ግን፣…
…”ይሄኔ ነው የልቤ እውነት ያመለጠኝ።” ይለናል። ይቀጥላል።
“ታወቂያለሽ ግን አንቺ ህልሜ እንዳልሆንሽ። የመጣሽበት መንገድ፣ ዕቅድሽ፣ መርህሽ፣ ከእኔ ጋር መች ይሄዳል?” አልኳት።
ዎው፣ ዎው… ዋው! ምን ሆኗል? በጠራ ሰማይ ላይ መብረቅ፣… ምን የሚሉት ጨዋታ ነው ይሄ?  ዘመኑ ነው በማንኛውም ሰዓት መብረቅ ጠብቁ! ዱብዳ ያልሰማችሁበት ቀን አለ? የዘመኑ መንፈስ ይሆን? ወይስ፣ መጠጡ ወይኑ በዛ? እስቲ ጉዱን እንስማለት።
ሽማግሌ ከላክሁኝ በኋላ፣ በጋራ ስለምንወልዳቸው ልጆቻችን ስናወራ ከርመን፣ እንዴት እንዲህ ይባላል? ትበሳጫለች ብዬ ነበር። ግን፣… ረጋ እንዳለች፣ ፊቷ ሳይለዋወጥ ትክ ብላ አየችኝ። ቅፍፍፍ የሚል ስሜት ዋጠኝ። ምናለ አስማተኛ በሆንኩና እንዳልሰማች ማድረግ፣… እንዳልተናገርኩ መሆን ብችል።
“ፍቅርን የመሰለ አስማት” በስለታም ቃላት አስተንፍሶ ሲያበቃ፣ ሌላ አስማት ይመኛል። ፍቅረኛው፣ ሙሽሪት ለመባል የተቃረበች እጮኛው፣ እንደ ሐውልት ፊቷ ሳይለዋወጥ የተቀመጠችው፣ ድንጋጤው አደንዝዟት ቢሆን ነው። ለማመን ቢከብዳት ይሆናል! መቼም ሳትፈነክተው ከተረፈ፣ ትልቅ አስማት ነው? “ህልሜ አይደለሽም” የተባለች ፍቅረኛ ምን ልትል ትችላለች?
“ትክክል!!” አለች።
ምን? ትክክል! ምን ለማለት ፈልጋ ነው። ኧረ ተናሪ። ያለ ጎትጓች እንዲህ ትናገራለች።
…”ጊዜው አሳዝኖን ነው አብረን የሆንነው። አብረን ሆነን በስሱ ሌላ የፍለጋ ሙከራ ስላልተሳካልን ነው የምንጋባው። `Messenger`ህን ከፍቼ አይቻለሁ። የምታወራቸውን እንስቶች ቀልብ ለመግዛት የምትሄድባቸውን መንገዶች፣ መሻፈዶች፣ ላጤ ነኝ ጨዋታዎች፣ ብልግናዎች ተመልክቻለሁ። ሁሉም ከእኔ ጋር አንድ ዓይነት ነበሩ። የማደርገውን ነበር የምታደርገው። ከፍቶኝ ነበር። እንዳላኮርፍ፣ እንዳልጨቀጭቅህ፣ እንዳልጣላህ ካንተ አለመሻሌ አሸማቀቀኝ። የብዙ ሰዎች ትዳር እንዲህ እንደሆነ አይቻለሁ፤ ከገቡበት በኋላ በልጆቻቸው ይጽናናሉ። ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሚስት እና ባላቸውን እየከሰሱ ኑሮን ይገፉታል።”
በሰርግ ዋዜማ፣ በየፊናቸው እንዲህ አይነት የፍንዳታዎች ናዳ የሚያወርዱት ምንድነው? ደግሞ፣ የሷ ባሰኮ። መች በዚህ አበቃች? እንዲያውም “ተመስጌን ብንል ይሻላል” የምትል ትመስላች። “የፍቅር ትዳር”፣… ከንቱ ምኞት እንደሆነ ትነግረዋለች።…
ለዛ ነው እንከን የለሽ ትዳር የሚያስሱት ቆመው የሚቀሩት! በቆዩ ቁጥር መለኪያቸውን እየቀየሩ፣… ካጣጣሉት ከተጠየፉት የኑሮ ቀንበር ላይ ራሳቸውን ያገኙታል። ለዛ ነው እንደሚታረድ በግ ሁሉን እያወቅኩ ሽማግሌ ስትልክ፣ ቀለበት ስታጠልቅልኝ፣ የልቤን እውነት አፍኜ የምከተልህ።”
ሲዘበራረቅብኝ ይታወቀኛል።… በዚህ ደረጃ ይገባታል ብዬ አላሰብኩም። ሴት ልጅ ትታለልልሃለች እንጂ አታታልላትም።…
ለምን ታዲያ አብረን እንሆናለን ሁለታችንም እንዲህ ከተሰማን? (ስሜታችንን ከተዋወቅን?)… አለማወቅ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? አንዳንድ እውቀት ምቾት አይሰጥም። እውቀት ትካዜን ታበዛለች እንዲል መጽሐፉ። አንዳንድ ውይይቶች ሽንቁር ያበጃሉ። የጀመርኩትን ወይኔን በአንድ ትንፋሽ ወደ ጉሮሮዬ አንቆረቆርኩት።
እንዳለችው ፍርሀት ነው? እጦት ነው? መላመድ ነው? ምን ይሆን ያጋመደን?... እውነታ ከተዘራዘሩ በኋላ እንዴት ጎጆ ይቀለሳል?...
እንዲህ ከተፈላሰፈ በኋላ “ያጋመዳቸውን” ነገር ለመቁረጥ፣ በርካታ ምክንያቶችን ይደረድራል። ምክንያት ይሁኑ ማመካኛ እርግጡን እናንተ ፍረዱ። ግን፣ “ልጅ ሳይመጣ፣ ንብረት ሳናፈራ፣ ኑሮ ሳይንጠን”… ቶሎ መቁረጥ ያስፈልጋል ባይ ሆኗል። “አሁን የምጎዳት ነገ ከምሰብራት አይበልጥም፤ ዛሬ የሚሰማኝ ሕመም ነገ ከሚያጋረጥብኝ መከራ አይበልጥም።” በማለትም “ቁርጡን” ይነግራታል።
“ማሬዋ ሰው ውድ ፍጡር ነው። ችኮላችን፣ ብልጣብልጥነታችን፣… የእኛ የራሳችን ከሆኑት ሰዎች ጋር እንድንሸዋወድ ያደርገናል።…
“ብቸንነት አባብቶን፣ የአቻ ግፊት ወትውቶን፣ መላመድ አሳስሮን፣ የቤተሰብ ግፊት ገፈታትሮን… ኑሮ አይመሰረትም። የሁሉም ጓዳ እንዲህ ነው ተብሎ፣ አዲስ ጎጆ አይበጅም። ሁሉም ሄዷል ተብሎ፣ እንኳን በስሕተት መንገድ በትክክለኛ መንገድ መሄድ ተገቢ አይደለም።… ከመጣንበት መንገድ የምንሄድበት ሩቅ ነው።…
ስለዚህ? …እንዲህ ስለ ሰው ልጆችና ስለ እውነት፣ ስለ ፍቅርና ስለ ትዳር ከተናገረ በኋላ፣… ከተፈለሰፈ በኋላስ? ራሳችሁ እንድትጨርሱት እንድታነብቡት ብተውላችሁ ይሻላል። ወደ ሁለተኛው አጭር ትረካ እናምራ።
“አንተ የሌለህ ጊዜ”
ተማሪ እያለን ለብዙ ጊዜ የፍቅር ሕይወት ተጋርተናል። ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ ትልቅ ሰው ከሆንን፤ የተለያየ የሕይወት መሥመር ውስጥ ከሰመጥን፣ አጀንዳዎቻችን ከተቀየሩ፣ ፍላጎት እና ህልማችን ሌላ ከሆነ በኋላ ስራ አገናኘን።
የወዳጅነት ሰላምታ ሰላም ተባባልን። ሁለታችንም አይናችን የጣት ቀለበት ሲያስስ ተገጣጠምን፤ ሁለታችንም አግብተናል። ያገናኘን ሥራ ላይ ተጠመድን። ደጋግሞ ሥራ አገናኘን፤ ደጋግመን `e-mail` ተለዋወጥ።
(ኦኦ። “የከረመ ፍቅር” የሚል ዜማ ሊያመጣ ነው እንዴ? የከረመ ፍቅር፣ የአስደሳች ትዝታ ግሩም ዓለም ሊሆን ይችላል። ግን በየፊናቸው የተለያየ ቀለበት ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ የፍቅር ትዝታዎችን መምዘዝ፣ ከጥቅሙ ጣጣው መዘዙ ይብሳል። እንግዲህ፣ የከረመ ፍቅር የሚነካኩ ከሆነ፣ ምን ይባላል? “በጥበቡ ይርዳቸው”። ትረካው ይቀጥላል።)
አንድ ቀን ማኪያቶ እየጠጣን፣ ከላይ ከላይ እየተጨዋወትን፣… የሕይወትሽ አስቸጋሪ ጊዜ መቼ ነበር? አልኳት።
(የባሰ መጣ። የከረመ ፍቅር ሳይሆን የከረመ ሕመም መቀስቀስ ነው የፈለገው? እሱም ምክንያቱን የሚያውቀው አይመስልም።
 ሕመም ባይሰማው ይሆናል። ወይ የሷ ሕመም እንደሚበልጥ ለማየትና ራሱን ለማጽናናት… ወይስ የህሊና ወቀሳ ቢከነክነው? ምን ለማግኘት እንደፈለገ ምኑ ይታወቃል? ግን ይተርክልናል።)
አየችኝ፤ በትንሹ ፈገግ አለች። ፈገግ ስትል ዲምፕል አላት። ጥርሶቿ እንደ ድሮው ያምራሉ። ከፊት ለፊት በግንባሯ የመጡት ዘለላ ጸጉሮቿን በቄንጥ ወደኋላ መለሰቻቸው።
ዝም ብዬ ስመለከታት…
“አንተ የሌለህ ጊዜ። ማለቴ የተውከኝ ለታ” አለችኝ።
ስትቀልድ መስሎኝ ሳቅሁ። “እማ ትሙት” አለችኝ። በእናቷ ምላ ዋሽታ አታውቅም።…
ወደ ተመደብኩበት ዩኒቨርስቲ … መራመድ እንደመብረር እየከበደኝ ሄድኩ። ቀልቤን፣ ሳቄን ትቼ ነበር የሄድኩት።
ዶርም ሜቶቼ ለሚያወሩት ቋንቋ ባዳ ነበርኩ።
አብሮነታቸው ሲደራ ባይተዋርነት አራቆተኝ።… የካምፓስ ምግብ አልተስማማኝም፤… ናፍቆት ገላዬን በላው። ምግብ ስለማይስማማኝ ብዙ አልበላም። ሰለልኩ። የጨጓራ ህመም ጨፈረብኝ”
“እንደማትፈልገኝ፣… ሁሉ ነገርህ ይናገር ነበር። ስልክህ ረጅም ሰዓት ይያዛል። በፍጥነት ተቀያየርክ። ለስሜቴ መጠንቀቅ አቆምክ። እንደቀለልኩብህ ድርጊትህ ይናገር ነበር።… ነገሮችን ለማስተካከል በአፍላ ጭንቅላቴ ተፍጨረጨርኩ። ጓደኞቼ ሊሰሙኝ እንጂ መንገድ ለማሳየት ጥበብ እና ልምዱ አልነበራውም። ታላላቆቼ ጋ በዛ ዕድሜዬ በዚህ ጉዳይ ማውራት… ነውር ነበር።
ሸሸሁ!
የባሰ የቀዘቀዘ ድምጽ እንዳልሰማ ሸሸሁ። አዲስ የተወዳጀሃት ልጅ እንዳለች ስድስተኛ ስሜቴ አንሾካሾከልኝ። ስደውል በእሷ ፊት ተራ ጓደኛዬ ነች ዓይነት ወሬ እንዳታወራኝ ሰጋሁ። አትደውይልኝ እንዳትለኝ… ሸሸሁ።…
 ላ´ንተ ያለኝን ፍቅር የባሰ አጣጥለህ እንዳይቋጭ ስለሳሳሁ ሸሸሁ!
የጋራ ጓደኞቻችን በልቤ ያለውን ፍርሃት እንዳይነግሩኝ ሁሉንም ዘጋኋቸው። …ፍቅር ነክ ልብ-ወለድ ጽሑፎች ትውስታዬን ቀስቅሰው ናፍቆቴን እንዳያብሱት ማንበብ አቆምኩ።… ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን ረጅም ሰዓት እቀመጣለሁ፣ ስብከት አዳምጣለሁ፣ ጉባኤ እከታተላለሁ።
ጾታዊ ፍቅር ስለሌለው፣ የሁሉ ነገር መሠረት ክርስቶስ እንደሆነ ስለሚነገር፣ በፈተናው የጸና የተባረከ ነው ስለሚባል፣ ብዙ ነገር በዲያቢሎስ ስለሚላከክ፣ የጭንቀታች ችግር መፍቻ፣… ጸሎት፣ ንሰሃ መሆኑን በአማረ ቋንቋ ስለሚያስተምሩ ጣፈጠኝ። መጽሐፍ ቅዱስን የሙጥኝ አልኩ። ችግሮቼ እየቀለሉኝ መጡ። አዳስ ሃይማኖተኛ ጓደኞች ተወዳጀሁ።
የመጀመሪያ ዓመት ጨርሼ ስመጣ፣… ግሬይ ሱሪ፣ ቀይ ቲሸርት አድርህ ቆመህ አየሁህ። ሳይህ፣ ከእስራቴ ከሱሴ መላቀቄ ነው የተገለጠልኝ። የሆነ ቀጫጫ ልጅ፣ ኖርማል ወንድ፣ ለዓይን የማይሞላ ልጅ አየሁኝ። ለካ ችግራችንን የምናይበት መንገድ የገዘፈ ስለሆነ ነው ከችግራችን በታች የምንሆነው።
… የሕመሟን ታሪክ ትነግረዋለች። ወይስ ተፍጨርጭሮ የመዳን ታሪክ? ከመነሻውስ፣ ፍቅር ነበራቸው? ወይስ ፍቅር የመሰለ ሱስ ነገር? “ለዓይን የሞይሞላ ልጅ” ሆነባትኮ!
አጀማመሩ፣ የከረመ ፍቅር ይመስላል። እጥፍ ብሎ፣ የከረመ ሕመም ይሆናል። ዞር ብለው  ሲያዩት የማንሰራራት ታሪክ ነው። ለዚያውም ለዓይን በማይሞላ ልጅ ሳቢያ የተፈጠረ ነው ያ´ሁሉ ውጣ ውረድ።


Page 1 of 648