Administrator

Administrator

በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በየሳምንቱ ቅዳሜ ለንባብ የምትበቃው “ፍቱን” መጽሄት ከህትመት ታገደች፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የግልም ሆነ የመንግስት ማተሚያ ቤቶች መፅሔቷን እንዳያትሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ባስተላለፈው መልዕክት የመፅሄቷን አሳታሚ አቶ ፍቃዱ በርታን ለጥያቄ ቢፈልጓቸውም ሊያገኟቸው አለመቻላቸውን ጠቁሟል፡፡ አሳታሚዎቹ፤ ከመንግስት ደረሰኞች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ደረሰኞችን በማሳተም ህገወጥ ስራ ሲሰሩ ተደርሶባቸዋል ያለው የባለስልጣኑ መግለጫ፤ በዚህ ምክንያትም መፅሄቷ ከህትመት ውጪ እንድትሆን ለማድረግ የሚያስችል የፍርድ ቤት ማገጃ ማውጣታቸውንና የትኛውም ማተሚያ ቤት መፅሄቷን ከማተም እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡
“ፍቱን” መፅሄት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አተኩራ በየሳምንቱ ቅዳሜ ለንባብ የምትበቃ መፅሔት ነበረች፡፡

ተመላሽ ኢትዮጵውያኑ በማቆያ ውስጥ ተቀምጠው ክትትል እየተደረገባቸው ነው
የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ወደ አገር ውስጥ አይገቡም ተብሏል፡፡
በሽታው ወደ አገር ውስጥ ቢገባ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

በምዕራብ አፍሪካ አገራት በድንገት ተከስቶ ለሺዎች ሞት ምክንያት የሆነውና ዓለምን ስጋት ላይ የጣለው የኢቦላ በሽታ አሁንም ሥጋት መሆኑ አላበቃም። በበሽታው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት በሽታው ወደተከሰተባቸው አገራት ሄደው ለወራት የቆዩት ኢትዮጵያውያን ኮንትራታቸው በመጠናቀቁ ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ተመላሽ ኢትዮጵያውያኑ ለኢቦላ ክትትልና ቁጥጥር በተዘጋጁት የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ሆነው ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኢቦላን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ዳዲ ጂማ እንደተናገሩት፤ ኢቦላ የዓለም ስጋትነቱ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመው የስጋቱ መጠን ቀደም ብሎ ከነበረው የተለየ አለመሆኑንና ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ ከበሽታው ነፃ መሆኗ መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ በሽታው በአገሪቱ ቢከሰት እንኳን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በሽታውን በቀላሉና በፍጥነት ለመለየት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ግዥ መፈፀሙንም ገልፀዋል፡፡
በኢቦላ ወደተጠቁ አገራት በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ለስራ የሄዱ ኢትዮጵያውያን የሥራ ኮንትራታቸውን አጠናቀው ወደአገራቸው እየተመለሱ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳዲ፤ እነዚህ ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለሥራ በቆዩባቸው ጊዜያት ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ተመላሾቹ በኢቦላ ክትትል ማዕከል ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ክተትልና ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በመግታት እዚያው ባሉበት ቦታ ላይ ክትትልና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ጠቁመው በዚህም በሽታው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በበሽታው ወደተጠቁ አገራት በመንግስት የተላኩ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችም በቅርቡ የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው እንደሚመለሱና በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ክትትል እንደሚደረግ ዶ/ር ዳዲ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  

“የኛ” የሬዲዮ ፕሮግራም አምስተኛ ሲዝን ጀምሯል

ታዋቂ ድምጻውያን ለመሆን በሚጥሩ አምስት ወጣት ሴቶች የህይወት ውጣውረድ ዙሪያ የሚያጠነጥነው “የኛ” ፊልም ከዛሬ ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች ለእይታ እንደሚበቃ ፕሮዲውሰሮቹ አስታወቁ፡፡
ፊልሙ በክልሉ በሚገኙ 26 ከተሞች በትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ አዳራሾች ውስጥ በነጻ እንደሚታይና 40ሺህ ያህል ተመልካቾች ያዩታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡
የኛ በተባለው የሬዲዮ ድራማ ላይ የሚታወቁት ሚሚ፣ ሜላት፣ እሙየ፣ ሳራ እና ለምለም የተባሉት ገጸባህሪያት የሚሳተፉበት ይህ ፊልም፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በኢቢኤስ እና በአማራ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ልዩ ፕሮግራሞች ለእይታ እንደሚበቃም ተገልጧል፡፡
የናይኪ ፋውንዴሽንና የእንግሊዝ መንግስት አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዲፊድ) ጥምረት በሆነው ገርል ሃብ ኢትዮጵያ የሚከናወነው የኛ ፕሮጀክት በሸገር ኤፍ ኤም እና በአማራ ክልል ሬዲዮ ጣቢያዎች፤ ሲያስተላልፈው የቆየውን የኛ የሬዲዮ ፕሮግራም አምስተኛ ሲዝን መጀመሩንም የኛ ቤት የተባለው የ3 ተቋማት ጥምረት አስታውቋል፡፡
የኛ የሬዲዮ ድራማ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና እና በአዲስ አበባ ከ1 ሚሊዮን በላይ አድማጮች እየተከታተሉት እንደሚገኙና፣ ድራማውን ከሚከታተሉት ልጃገረዶች 84 በመቶው በህይወታቸው ስኬታማ ለመሆን የራስ መተማመናቸው እንዳደገና፣ 76 በመቶ የሚሆኑትም ድራማው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲቀጥሉ እንዳነሳሳቸው በጥናት መረጋገጡም ተገልጧል፡፡
የኛዎች በለቀቋቸው ነጠላ ዜማዎችና የቪዲዮ ክሊፖች እንዲሁም በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በሚያቀርቧቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች ተወዳጅነትን ማትረፍ መቻላቸው ይታወቃል፡፡

     የአገራችንን የኢኮኖሚ እድገት የሚያበስሩ ዜናዎችን በየግዜው በሚዲያ እንሰማለን፡፡ ሆስፒታሎች፤ ፋብሪካዎች፤ ት/ቤቶች፤ ድልድዮች ወዘተ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች መንግስት መስራቱን በሰማሁ ቁጥር የላቀ ደስታ ይሰማኛል፤ እሰየው! ብራቮ ኢትዮጵያ እላለሁ፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ሰፋ ባለ እቅድ፤ ብዙ ልፋትና የህዝብ ገንዘብ ፈሶባቸው ለህዝብ አገልግሎት በሚበቁበት ግዜ ይሄንን ትልቅ ስኬት ማክበር አግባብ ነው፡፡ ደስም ይላል፤ የሁላችንም ድል ስለሆነ፡፡
እድለኛ ሆኜ አንዳንድ ምርቃቶች ላይ ብገኝም አብዛኞቹን ያየሁት ግን በቴሌቪዥን ነው፡፡ እነዚህን በዐሎች ስመለከት ግን ሁልግዜ የሚከነክነኝ አንድ ነገር አለ፡፡ አስተውላችሁ እንደሆነ ባለስልጣኖችም ሆነ ተጋባዥ እንግዶች ለምርቃቱ የተዘጋጁ ልዩ ካናቴራዎችና ኮፍያዎች ለብሰው እናያለን፡፡ እነዚህን ካናቴራዎችና ኮፍያዎች በብዛት ለማዘጋጀት ብዙ ብር ያስፈልጋል፡፡ ፅሁፍ ያላቸው ኮፍያና ካናቴራዎች  እያንዳንዳቸው በአማካይ 100 ብር ድረስ ያወጣሉ፡፡ ለአንድ ምርቃት በግምት ከ500 እስከ 1000 ሊዘጋጅ ይችል ይሆናል፤ እንግዲህ ሂሳቡን እናንተ አስሉት፡፡
ጥቅምና ፋይዳ ቢኖረው ግድ ባልሰጠኝ ነበር፤ ግን እነዚህ ካናቴራዎችና ኮፍያዎች አገልግሎታቸው ለዚያች ቀን ብቻ ነው፤ በእለቱ የተገኙት ሰዎች ሌላ ቀን ደግመው የሚለብሱትም አይመስለኝም፡፡ ጥቂቶቹ ቢጠቀሙባቸውም እንኳን ለካናቴራውና ለኮፍያዎቹ ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነፃፀር ከጥቅሙ ጉዳቱ  ያይላል፡፡ በየአመቱ፤ በየክልሉ ስንት የምርቃት በዐል እንደሚደረግ እንግዲህ አስቡት፡፡ አንድ ብዙ የምርቃት በዐል የተካፈለ ጓደኛዬ ሴት ልጅ፤ ‹ቤት ያሉትን ኮፍያዎችና ካናቴራዎች ሰብስቤ ቡቲክ ልከፈትበት--› እያለች በአባትዋ ስትቀልድ ሰምቼአለሁ፡፡ የበዐሉ ዋናውና መሰረታዊ አላማው የመሰረተ ልማቱን ስኬት ማክበር እንጂ ተሳታፊዎቹን በኮፍያና ካናቴራ ማንበሽበሽ አይደለም፤ መንግስትም ይሄን ማድረግ አይጠበቅበትም፡፡  
ለበዐሉ ማስታወሻነትም ከተፈለገ፤ ስለስራው የሚገልፁ ብሮሽሮች፤ መፅሄቶች--- ማዘጋጀት የተሻለና ዘላቂ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ሠው ቤቱም ሆነ ቢሮው ስለሚያስቀምጠው በበዐሉ ላይ ላልተገኙ ወይም በሚዲያ ላልተከታተሉ ሰዎች በማስታወሻነትም በመረጃነትም ለረጅም ግዜ ሊያገለግል ይችላል፡፡
በአገራችን እንጭጭ ኢኮኖሚ ከድህነት ጫና ለመውጣት ገና ዳዴ በምንልበት ወቅት፤ ለምርቃት በሚል ኮፍያና ካናቴራ ማሰራት አላስፈላጊ ወጪ ይመስለኛል፡፡ ይሄንና ሌሎች አላስፈላጊ ወጪዎችን ከዚህም ከዚያም መቀናነስና መቆጠብ ከቻልን ትልቅ የገንዘብ ሀይል ይሆኑናል፤ አንዳንድ አንገብጋቢ የልማት ቀዳዳዎችንም ሊደፍኑልን ይችላሉ፡፡ ግብር ከፋይ ነኝና ጉዳዩ ያገባኛል ብዬ ነው ሃሳቤን የሰነዘርኩት፡፡  በእርግጥ ነገሩ የግል ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን አይመለከትም።
ኃይለማርያም ገ/ሕይወት- ከቀጨኔ

   በአፍሪካ ለሚነሱ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች የተቀናጀ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የተጠንቀቅ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሁም የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጐች የቻይና ቪዛን የሚያስቀር አዋጅን ጨምሮ ሌሎች ስድስት አዋጆች ፀድቀዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም ካፀደቃቸው አዋጆች መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል አዋጅና የኪዮቶ ፕሮቶኮልን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጆች ይገኙበታል፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚያመለክተው፤ የተጠንቀቅ ሃይሉ ከአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በሚሰጠው ፍቃድ መሰረት በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት የሚሰጡትን ግዳጆች እየተቀበለ በፍጥነት ምላሽ ይሰጣል፡፡ የተጠንቀቅ ሃይሉ ዋና መቀመጫውና የስልጠና ማዕከሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሆንም አዋጅ አመልክቷል፡፡ በአምስቱ የአህጉሩ ቀጠናዎች በሚገኙ አገሮች ውስጥ ካሉ ፖሊሶች፣ ወታደሮችና ሲቪሎች በተውጣጡ አባላት የሚዋቀረው የተጠንቀቅ ኃይሉ የሚያከናውናቸው ተግባራት በአፍሪካ ህብረት ከለላ ውስጥ እንደሚሆንና ኢትዮጵያ ለተጠንቀቅ ሃይሉ ሰራዊቶችን የማሰልጠንና አስፈላጊ መሳሪያዎችን የማቅረብ ግዴታ እንደተጣለባት አዋጁ አመላክቷል።
ሌላው ምክር ቤቱ ያፀደቀውና በኢትዮጵያና በቻይና መንግስታት መካከል የተፈረመው ስምምነት፤ የሁለቱ አገራት ዜጐች ያለቪዛ መውጣት መግባት የሚያስችላቸው ነው፡፡ የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የኢትዮጵያና የቻይና አገራት ዜጐች ያለቪዛ ለሰላሳ ቀናት ወደየአገራቱ መውጣትና መግባት የሚያስችላቸውን ይህንኑ ስምምነትም ምክር ቤቱ አጽድቆታል፡፡ ከምክትል ሚኒስቴር በላይ የሆነ ማዕረግ ያላቸው የማዕከላዊ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ኦፊሰሮች ወይም ከሜጀር ጀነራል በላይ ማዕረግ ያላቸው የመከላከያ ባለስልጣናት ለኦፊሴሊያዊ ሥራ ወደ ሌላኛው ተዋዋይ አገር ድንበር ከመግባታቸው በፊት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማሣወቅ እንደሚገባቸው በስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ የፀጥታ የደህንነትና የጤና ችግሮች በሚከሰቱባቸው ጊዜያት ተዋዋይ አገራት የስምምነቱን ተፈፃሚነት በሙሉ ወይም በከፊል መገደብ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡   

   የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በአንድ ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ቻርጅ መደረግ የሚችልና የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ የአልሙኒየም የሞባይል ስልክና የላፕቶፕ ኮምፒውተር ባትሪ መስራታቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
አዲሱ የሞባይል ስልክና የላፕቶፕ ባትሪ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መደበኛው የሊቲየም ባትሪ ጋር ሲነጻጸር፣ በከፍተኛ ፍጥነት ቻርጅ ከመደረጉ በተጨማሪ ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉም እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡
“ፈጠራችን በባትሪው ቴክኖሎጂ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡ እኛ የሰራነው ባትሪ በእሳት የማይቃጠል ነው፡፡ ለአጠቃቀምም ምቹ በሆነ መልኩ ነው የተሰራው፡፡ ሊቲየም አዮን ባትሪን ከመሳሰሉ ሌሎች ነባር የባትሪ አይነቶች ጋር ሲነጻጸር፣ ሳይደክም ለብዙ ጊዜያት ቻርጅ የመደረግ አቅሙ እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ተመራጭ ያደርገዋል” ብለዋል፤ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የተመራማሪ ቡድኑ መሪ ሆንጊ ዳይ፡፡
ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የአልሙኒየም ባትሪዎች፣ በሙሉ አቅማቸው መስራት የሚችሉት እስከ መቶ ጊዜ ያህል ተደጋግመው ቻርጅ እስኪደረጉ ነበር፡፡ ይሄኛው ባትሪ ግን 7ሺህ 500 ጊዜ ያህል ቻርጅ እስኪደረግ አቅሙ የማይቀንስ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡
ተመራማሪዎቹ የፈጠራ ውጤታቸውን ሰርተው ማጠናቀቃቸውን ሰሞኑን ለህትመት በበቃ መጽሄት ላይ ይፋ ቢያደርጉም፣ ባትሪው በብዛት ተመርቶ ለገበያ የሚቀርብበትን ጊዜ በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡

Tuesday, 14 April 2015 11:26

የየአገሩ አባባል

 የአይሁዶች አባባል
ሰው ሲያቅድ እግዚአብሔር ይስቃል፡፡
እናት፤ ልጅ ሳይናገር ይገባታል፡፡
ሃጢዓትን ሁለቴ ከፈፀምከው ወንጀል አይመስልም፡፡
ፍየልን ከፊት ለፊት፣ ፈረስን ከኋላ፣ ሞኝን በየትኛው በኩል አትጠጋቸው፡፡
ብልህነትህን በተግባር እንጂ በቃላት አታሳይ፡፡
ሻማ ለመግዛት ፀሃይን አትሽጥ፡፡
እግዚአብሔር ሸክምን ሲሰጥ ትከሻም አብሮ ይሰጣል፡፡
እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ ሊሆን ስለማይችል እናቶችን ፈጠረ፡፡
ለጎረቤቱ የሚፀልይ ለራሱ ይደርስለታል፡፡
ልዕልት ማግኘት የምትሻ ከሆነ ራስህን ልዑል አድርግ፡፡
እግር የሌለው ሰው እስከማገኝ ድረስ ጫማ የለኝም ብዬ አዝን ነበር፡፡
በዓይንህ ያላየኸውን በአፍህ አትመስክር፡፡
ሳሙና ሰውነትን እንደሚያጥበው ሁሉ እንባም ነፍስን ያጥባል፡፡
አባት ለልጁ ሲሰጥ ሁለቱም ይስቃሉ፤ ልጅ ለአባቱ ሲሰጥ ሁለቱም ያለቅሳሉ፡፡

  - “በርበሬን የመረጥነው የከፋ ጉዳት ስለማያደርስ ነው” - የአገሪቱ ፖሊስ
   በሰሜናዊ ህንድ የምትገኘው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው የላክኖው ፖሊስ፣ ከአየር ላይ በርበሬ የሚረጩ አነስተኛ አድማ በታኝ ድሮኖችን በስራ ላይ ማዋል ሊጀምር ነው ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የግዛቷ ፖሊስ ህገወጥ ተቃውሞ የሚያደርጉ ዜጎችን ለመበተን የሚያስችሉና እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ግራም በርበሬ የመጫን አቅም ያላቸው አምስት አነስተኛ ድሮኖችን በስራ ላይ ለማዋል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
“ህገወጥ አመጽ የሚያካሂዱ ዜጎችን በርበሬ እየረጨን እንበትናለን፡፡ ይህን ያልተለመደ የአድማ ብተና መሳሪያ ለመጠቀም የመረጥነው፣ በአመጹ ተሳታፊዎች ላይ የከፋ ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ ነው፡፡ ህገወጥ ተቃውሞዎችንና የጎዳና ላይ አመጾችን በቁጥጥር ውስጥ በማዋል ረገድ ውጤታማ እንደሚሆንም ተስፋ አለን” ብለዋል ያሻዝቪ ያዳይ የተባሉት የግዛቲቱ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን፡፡
የግዛቲቱ አስተዳደር ባለፈው አመት ባደረገው ሙከራ፤ በርበሬ የሚረጩ ድሮኖች አድማን በመበተን ረገድ ውጤታማነታቸውን በማረጋገጡ፣ ለእያንዳንዳቸው 10ሺህ ዶላር የከፈለባቸውን ድሮኖች በስራ ላይ ለማዋል መወሰኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ህንድ በርበሬ የሚረጩ አድማ በታኝ ድሮኖችን በመጠቀም ከዓለማችን አገራት ቀዳሚዋ እንደሆነችም ዘገባው አክሎ ገልጿል።

በሽብር ጥቃቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀርበዋል
መንግስት 13 የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን ዘግቷል፤ 86 የባንክ ሂሳቦችን አግዷል
   አልሻባብ ባለፈው ሳምንት በኬንያዋ በጋሪሳ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከፈጸመውና 148 ያህል ተማሪዎችን ለህልፈተ ህይወት ከዳረገው የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተጎዳ እንደሚገኝና የመገበያያ ገንዘቧ የመግዛት አቅም እየቀነሰ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና በሚጫወተውና ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በሆነው የቱሪዝም መስክ እንቅስቃሴ ላይ መዳከም መታየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በርካታ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ወደ ኬንያ ለመሄድ የያዙትን ፕሮግራም ሰርዘዋል ብሏል፡፡
የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ሺልንግ የመግዛት አቅም፣ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በዚህ አመት ብቻ 2 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ዘገባው ጠቁሞ፣ ቅናሹ በመጪዎቹ ቀናትም ይቀጥላል ተብሎ እንደሚገመት ገልጿል፡፡
አልሻባብ በ2013 በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ላይ ጥቃት ከፈጸመ ጊዜ አንስቶ፣ የቱሪስት ፍሰቱ እየቀነሰና አገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ የመገበያያ ገንዘቡን የመግዛት አቅም ለማሻሻል ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱንም ጠቁሟል፡፡
ካለፈው ሳምንት የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ግለሰቦች ማክሰኞ ዕለት ናይሮቢ በሚገኝ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የዘገበው ደግሞ አሶሼትድ ፕሬስ ነው። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለፈጸሙት አራት ግለሰቦች የጦር መሳሪያ አቅርበዋል በሚል በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱም ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሏል፡፡ ከአምስቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ አንድ ታንዛኒያዊ በሽብር ጥቃቱ ተሳትፏል በሚል በቁጥጥር ስር እንደዋለ የጠቆመው ዘገባው፤ ፖሊስ ግለሰቡ ላይ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ባለው መሰረት እንደተፈቀደለትም አክሎ አስታውቋል፡፡
የኬንያውን “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ፣ የአገሪቱ መንግስት ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ ያስተላልፋሉ ብሎ የጠረጠራቸውን 13 የሶማሊያ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን የዘጋ ሲሆን በግዛቷ ውስጥ የሚፈጸሙ የሽብር እንቅስቃሴዎች በገንዘብ ይደግፋሉ ያላቸውን የ86 ግለሰቦችንና ድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ አግዷል፡፡
የመንግስት ውሳኔ በኬንያ በሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሶማሊያውያን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል ያሉት የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ በሽር አሊ፤ ኬንያውያኑ ኑሯቸውን የሚገፉት ከተለያዩ የአለም አገራት ከዘመዶቻቸው በሚላክላቸው ገንዘብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኬንያ መንግስት እንዲዘጉ የተወሰነባቸው የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ሃላፊዎችም ውሳኔውን በመቃወም፣ በዚህ አካሄድ ሽብርተኝነትን መዋጋት አይቻልም ብለዋ።
የኬንያ አየር ሃይልም ባለፈው እሁድ በሶማሊያ በሚገኙ ሁለት የአልሻባብ ካምፖች ላይ በፈጸመው የአየር ድብደባ ጥቃት ካምፖቹን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ቢያስታውቅም፣ አልሻባብ በበኩሉ፤ ጥቃቱ አልተፈጸመብኝም ሲል አስተባብሏል፡፡
አልሻባብ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በኬንያ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ከ400 በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት እንደዳረገም ቢቢሲ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስታውሷል፡፡

Tuesday, 14 April 2015 08:45

የፍቅር ጥግ

ሰውን ማፍቀር የእግዚአብሔርን ፊት ማየት ነው፡፡
(Les Miserables)
ራሴን በወደድኩበት መንገድ ሌላን ሰው ወድጄ አላውቅም፡፡
ማ ዌስት
ፍቅር፤ ሁለት ልቦችን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
ፍቅረኛሞች እርስ በርስ የማይሰለቻቹት ሁሌም ስለራሳቸው ስለሚያወሩ ነው፡፡
ፍራንሶይስ ሌላ ሮቼፎካልድ
 ፍቅር ምን ይመስላል? ሌሎችን የሚረዳበት እጅ አለው፡፡ ለድሆችና ለችግረኞች ፈጥኖ የሚደርስበት እግር አለው፡፡ ችግርንና መከራን የሚያይበት ዓይን አለው፡፡ የሰዎችን ሃዘንና ጭንቀት የሚያዳምጥበት ጆሮ አለው፡፡ ፍቅር ይህንን ነው የሚመስለው፡፡
ቅዱስ አጉስቲን
ፍቅር መጠለያ ከሆነ በዝናብ ውስጥ እጓዛለሁ፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
ፍቅር እውር ሊሆን ይችላል፤ ግን በእርግጠኝነት በጨለማ መንገዱን አይስትም፡፡
ያልታወቀ ምንጭ
ፍቅር ምርጫችን ሳይሆን ዕጣ ፈንታችን ነው፡፡
ጆን ድራይደን
አፍቃሪ ልብ ሁልጊዜም ወጣት ነው፡፡
የግሪኮች ምሳሌያዊ አባባል
ፍቅር፤ በጋብቻ የሚፈወስ ጊዜያዊ እብደት ነው፡፡
አምብሮሴ ቢርስ
በፍቅር ውስጥ ግንኙነቱን የሚቆጣጠሩት ብዙ ያላፈቀሩት ናቸው፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
ፍቅርን ስትከተለው ይሸሽሃል፤ ስትሸሸው ይከተልሃል
ምሳሌያዊ አባባል