Administrator

Administrator

ታላቁ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ከሞተ አራት አመት ሆነው፡፡ የሟቹ ቤተሰብ ግን አሁንም የሞቱ ምክያኒያት አልተዋጠልኝምና ይመርመርልኝ ማለቱን ቀጥሏል፡፡ ምርመራው በአንደኛነት ያነጣጠረው የሙዚቃ ንጉሱን የልብ ጤና ይከታተል በነበረው ዶክተር ኮንራድ ሙሬ ላይ ነው፡፡ የክሱ አይነት፡- በስህተት ነብስ ማጥፋት (involuntary manslaughter) እና የታማሚውን የጤና ሁኔታ ያላገናዘበ ንዝህላልነት የሚል ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ሂደት ላይ የማይክል ጃከሰን የቀድሞ ሚስት (ዴቢ ሮው) በእንባ እየታጠበች ስለ ሟቹ ባሏ ባህሪ ተናዝዛለች፡፡ ትዝታዋን በመመርኮዝ የሰጠችው ምስክርነት የዚህ ሳምንት ትኩስ ዜና ሆኖ ሰንብቷል፡፡

“ማይክል ምንም አይነት ህመምን የማስተናገድ አቅም የሌለው ሰው ነው፡፡ ማመን በሚያስቸግር ደረጃ ህመምን ይፈራል፡፡ ህመምን ለማስወገድ ምንም አይነት መድሀኒት ይወስዳል፡፡ ዶክተሮቹም ለዚህ ፍርሐቱ መሳሪያ ሆነውለታል” ብላለች፡፡ ዴቢ ሮው ከማይክል ጃክሰን ጋር የተዋወቀችውም እዛው ሀኪም ቤት ነበር - የማይክልን ቆዳ በሽታ ከሚያክመው ከዶክተር አርኖልድ ክላይን ጋር በምትሰራበት ወቅት፡፡ እዛ ተዋውቀው ተጋቡ፡፡ በጋብቻ ጥምረት ሦስት አመት አብረው ኖሩ፡፡ ከ1996-1999 … የመጀመሪያዎቹን ሁለት ልጆቹን የወለደችለትም ዴቢ ሮው ናት፡፡ በፍርድ ቤት በሰጠችው ምስክርነቷ፡- ማይክል፤ ለቀዶ ጥገና ብቻ የሚወሰድ ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ይወጋ እንደነበር ተናግራለች፡፡
“… ከሞት ይልቅ እንቅልፍ የማጣቱ ነገር በበለጠ ያስጨንቀው ነበር” ትላለች ዴቢ፡፡ “ምክንያቱም ያለ እንቅልፍ በመድረክ ላይ ሙዚቃዎችን ማቅረብ ስለማይችል ነው”
ለቀዶ ጥገና የሚወሰደውን ማደንዘዣ በ1997 (በፈረንጆቹ አቆጣጠር) መጠቀም ከማዘውተሩ በፊት … የሌላ ህመም ማጥፊያ መድሐኒት ሱሰኛ ነበር፡፡ በ1993 የፔፕሲን ማስታወቂያ ለመስራት ቀረፃ በሚያደርግበት ወቅት በተፈጠረ አደጋ፣ የራስ ቅሉ ላይ የቃጠሎ አደጋ ባጋጠመው ጊዜ ህመሙን ለማስወገድ “ዲሜሮል” የተሰኘ ማደንዘዣ ይወስድ ነበር፡፡ የዚህን መድሐኒት ሱስ መላቀቅ ሳይችል በላዩ ላይ “ፕሮፖፎል” የተባለውን ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ደረበበት፡፡ የእነዚህ የህመም ማጥፊያ መድሐኒቶች መደራረብ በ2009 አለምን ላስደነገጠ ሞቱ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ሚስቱ በምስክርነቷ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡ ዴቢ ሮው የከሳሹ ቤተሰቦች (በተለይ የማይክል ጃክሰን እናት ካተሪን) ከቀጠሩዋቸው ጠበቆች የሚቀርቡላትን መስቀለኛ ጥያቄዎች በፍርዱ ቀጣይ ሂደቶች እንደምትመልስ ይጠበቃል፡፡

በየዓመቱ በነሐሴ ወር የሚዘጋጀው የሸራተን የስዕል አውደ ርዕይ ሊቀርብ ነው፡፡ “Art of Ethiopia 2013” በሚል ርዕስ የሚቀርበው አውደ ርዕይ፤ በኢትዮጵያ ያሉ የጥበቡ ፈርጀ ብዙ ገፅታዎችን የሚያሳዩ 500 ያህል ሥዕሎች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ ስራዎች ከመቶ አስር እጅ በቅርፃ ቅርፅ ላይ ያተኩራል የተባለለት ትልቅ አውደ ርዕይ፤ በሚቀጥለው ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ተከፍቶ እስከ ነሐሴ 27 በየእለቱ ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ በዝግጅቱ 450 ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን እንዲታይላቸው አቅርበው “የምርጦቹ ምርጥ” ለአውደርዕዩ መቅረቡንና ከነዚህም ሩቡ እጅ የሴት ሰዓሊያን ስራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሸራተን አዲስ ላለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ታላቅ የስዕል አውደርእይ እያሳየ ይገኛል፡፡ አውደርእዩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የስዕል ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡

ስምንተኛው የበደሌ ስፔሻል “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በህዳር 2006 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሊንኬጅ ማስታወቂያ ህትመትና ፕሮሞሽን አስታወቀ፡፡ ከህዳር 16 እስከ ህዳር 23 የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል፣ “አፍሪካዊያን የራሳቸውን ታሪክ እስኪናገሩ የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ቅኝ ገዢዎችን ያደምቃል” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን 70 ያህል ዶክመንተሪ፣አጭር፣ፊቸር እና አኒሜሽን ፊልሞች ይቀርቡበታል፡፡ “African panorama” “Cinema Landmarks” “Contemporary Cnema”, “Regional /Ethiopia Focus” እና “Community Focus” የተሰኙ ፊልሞች የሚቀርቡበት ፌስቲቫል፣ ሽልማቶችም ይኖሩታል ተብሏል፡፡

በፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ የተደረሰው “ላማ ሰበቅታኒ” የረዥም ልቦለድ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ “Fantasy” የተሰኘውን የአፃፃፍ ስልት ተከትሎ የተጻፈው መጽሐፍ 174 ገፆች ያሉት ሲሆን የታተመው በ”እማይ ፕሪንተርስ” ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 40 ብር ከ50 ሣንቲም ነው፡፡
ደራሲ ውድነህ ክፍሌ “የቼዝ አለም”፣ “ባቢሎን በሳሎን” ፣ “የታፈነ ጩኸት” እና በሌሎችም ተውኔቶቹ የሚታወቅ ሲሆን ከዓለም አቀፍ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የ2000 ዓ.ም “ምርጥ የትያትር ደራሲ” ተብሎ መሸለሙም አይዘነጋም፡፡

ጥንታዊውና ታሪካዊውን የአቡነ መልከፄዴቅ ገዳም ይበልጥ ለማስተዋወቅና ለቱሪስቶች ለማስጐብኘት እንዲሁም ለመርዳት በአርቲስቶች የተሰራው “እዩና እመኑ” ቪሲዲ ነገ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል አዳራሽ ይመረቃል፡፡
ትዕግስት ግርማ፣ ይገረም ደጀኜ፣ መሰረት መብራቴና ሌሎች ታዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበት ቁጥር አንድ “እዩና እመኑ” ከዚህ በፊት ተመርቆ ለገበያ ከቀረበ በኋላ በተደረገው ገዳሙን የማስተዋወቅ ስራ እስካሁን የ13 አገራት አምባሳደሮች፣ ሀይሌ ገ/ስላሴና የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የጐበኙት ሲሆን ዘወትር ቅዳሜ ከ33-40 መኪና ጐብኚዎች ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ተጠቁሟል።
በአቡነ መልከ ፄዴቅ ገዳም እጅግ አስገራሚ ከሆኑት መስህቦች መካከል የሰው ሬሳ ከአመታት በኋላ አለመበስበሱ፣ ያለቀለም መርገጫ በእጣን መዓዛ ብቻ የሚሰራ ማህተም፣ ከ800 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ደወል እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡

በአሊ ይመር ተጽፎ የተዘጋጀውን “እንግዳ ነፍስ” ፊቸር ፊልም ሰኞ ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር እንደሚያስመርቅ ዙምባራ ፊልም ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ በፊልሙ ላይ መንትዮችን ጨምሮ 45 ያህል ተዋንያን እንደተሳተፉበት የጠቀሰው ድርጅቱ፣ፊልሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት እንደፈጀ አስታውቋል፡፡
በሌላም በኩል “ጃንኖ” የተሰኘ ፊልም የ95 ደቂቃ ፊልም በአዲስ አበባ መታየት ጀመረ፡፡
በሐዋሳ ተሰርቶ በዚየው ከተማ ሰኔ 26 ተመርቆ የነበረው ፊልም ባለፈው እሁድ በአለም፣ በዋፋ፣ በዮፍታሔ፣ በሴባስቶፖል፣ በኢዮሃ፣ በሆሊሲቲ ሲኒማ ቤቶች ታይቷል፡፡
ፊልሙን ፋሲል አስማማው ጽፎ ፕሮዲዩስ ያደረገው ሲሆን በደረጄ ደመቀ ዳይሬክተርነት ዘነቡ ገሠሠ፣ እንቁሥላሴ ወ/አገኘሁ፣ አልጋነሽ ታሪኩ፣ ናርዶስ አዳነ፣ ተመስገን ታንቱ፣ ይልፋሸዋ መንግስቴ ደረጄ ደመቀና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡

       ሰሞኑን፣ ወደ ዝግጅት ክፍላችን አንድ በእድሜ ብዛት ንትብ ያለ ባለ 34 ገጽ መጽሔት መጣልን። ክፍለሀገር ከሚኖር፣ የእነ ፈቃደ አዘዘ የቀድሞ ተማሪ እጅ ከ40 ዓመት በላይ የቆየው ‹‹ቴዎድሮስ›› የተሰኘው ይኽ መጽሔት፣ ደብረታቦሩ ከተማ በሚገኘው፣‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› በ1964 ዓ.ም. በሰቴንስል ተባዝቶ እንደተሰራጨ ታውቋል፡፡
በወቅቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የማስተማር አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ስለነበረባቸው፣ የያኔዬው የ22 ዓመቱ ትንታግ ወጣትፈቃደ አዘዘና ሌሎች 6 ጓደኞቹ፣ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የማስተማር ‹‹ሰርቪስ›› ይወጡ ዘንድ፣ የዛሬው የደቡብ ጎንደር መስተዳድር ዞን ዋና ከተማ በሆነው ደብረታቦር፣ ከትመው ነበረ፡፡ እናም፣ መጽሔቱ፣ በዚያ የአንድ ዓመት የማስተማር ቆይታቸው ወቅት ያዘጋጁት ሲሆን፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የቀረቡ መጣጥፎች፣ ዜናዎች፣ ለፈገግታ ያህሎች፣ የአካባቢ ገለጻዎች፣ ግጥሞች፣ የካርቱ ሥዕሎች ወዘተ. ቀርበውበታል፡፡
ታዲያ በመፅሄቱ ላይ በንባብ ከቀረቡ ፅሁፎች መካከል፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማርና መመራመር ከጀመሩ፣ ዘንድሮ 40ኛ ዓመታቸውን የደፈኑት የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ፅሁፎችም ይገኙበታል። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በሚል ርዕስ ያቀረቡት መጣጥፍ፣ በወቅቱ በተማሪዎች ንቅናቄ ሲስተጋባ የነበረው የብሄር/የጎሳ ፖለቲካ የደረሰበት ጫፍና የወደፊት ጦስ አቀንቅኗል፡፡ “ታዲያኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ‹አጅባሬ ነኝ!›፣ ‹ካሳንችሴ ነኝ!› ወዘተ. ማለት ሊመጣ ነው፡፡ በአባትና ልጅ መሀከል ልዩነት አይፈጠር ብላችሁ ነው? ወይስ ተፈጥሯል? የሚለውን ገለፃ ከዛሬ ነባረ ሁኔታ ጋር በንፅፅር ስናየው የትንቢት ቃልም ይመስላል፡፡
“መቼ ሆን?” በሚል ጥያቄያዊ ርዕስ ለዘብ ብለው የቀረቡ የአስተውሎት ምልከታዎች ፣ስለ ደብረታቦር ከተማና ህዝብ ማህበረ ባህላዊና ኢኮኖሚያዎ ሁኔታ ይጠቁማሉ፡፡ የምልከታዎቹ ዋጋ ግን፣የትናንሽ የገጠር ከተሞችን ጭምር ማህበረ ባህላዊ የኑሮ መልኮች፣የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶችን ወዘተ በወቅቱ የመዘገብን አስፈላጊነት ከማመልከታቸውና ከማንቃታቸው ጭምር ሊመዘዝ ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ የደብረታቦር ከተማና ህዝብ የለውጥ ሁኔታን ቃኝቶ ምልከታውን ለሚያከፈለን ፀሐፊም መልካም አጋጣሚ ነው እንላለን፡፡ ለማንኛውም ከመፅሄቱ እንደወረደ የቀረቡትን ፁሁፎች እንደሚከተለው አቅርበናል፤

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር
በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን ኢምንት ነው፡፡ ሀይል የለውም፡፡ ስርዓት አይኖረውም፡፡ አላማውም ግላዊ ነው፡፡ ብቻውን ከመቶ ኪሎ ጤፍ እንደ አንዲቱ የጤፍ ቅንጣት ነው። ጤፍ ብቻዋን አታጠግብም፡፡ ሰውም ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ከሰው ከተባበረ ግን እራሱን ሊያሻሽልና ሊጠብቅ፣ ባላንጋራውን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ሥራውም እንደ አንዷ ጤፍ ሳይሆን እንደምንበላው እንጀራ አንጀት አርስ ይሆናል፡፡
ታድያ ምነው የሰው ልጆች ልብ ተራራቀ? ምነው ተከፋፈለ? ምነው ሕብረትን ጠላ? ለምንስ በጠቅላላው በሰው ልጅ ወንድማማችነት እንደመመስረት የጎሳ ዝምድና ይመሰረታል? ለምን ወገን ይለያል? ሀገር የጋራ ነው ተብሏል፡፡ ታዲያኮ ዝምድናውም የጋራ ነው ማለት ነው፡፡ ፍቅሩ የሁሉ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የሚታየው ድርጊት ህሊናን የማያስደስትና አንጎልን የሚያናውጥ ነው፡፡
ጠለቅ ብለን ስንመለከት ብዙ ጅል ነገር እናገኛለን፡፡ አማራና ትግሬ ወገን መርጦ፣ ና ጉራጌ ተከፋፍሎ፣ ጋምቤላና ኩናማው ተለያይቶ ደም እንዳየች ውሻ በተገናኘ ቁጥር (‹‹ሲጣላ››) ሥራው እንዴት ይሠራ? እንዴት ለትምህርት እናስብ? እንዴት ለአንዲቷ ለመከረኛዪቱ እናት እናስብላት? ልባችን ለየብቻ ሆነ፡፡ ሥራችን ለየብቻ ሆነ፡፡ በመሀከል ግን ተጎዳን፡፡ እሷንም እንደማቀቀች ጎባጣ አሮጊት፣ ቀንታ (ቀና ብላ) ዓለሟን እንዳታይ ዓይኗን አጠፋነው፡፡
የሚገርመው ደግሞ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ልዩነቱ እየጠበበ ነው የሚሄደው፡፡ አማራው እንደገና ጋይንት፣ ቡልጋ፣ እስቴ፣ ደብረማርቆስ ወዘተ. እያለ ወገን ይለያል፡፡ ጋላውም አሩሲ፣ ሰላሌ፣ በቾና ወለጋ ወዘተ. እያለ ይከፋፈላል፡፡ ትገሬውም እንደዛው፡፡ ሌላውም እንደዛው፡፡ ካፍንጫችን እርቀን ስናስብ ደግሞ ቀስ እያለ በትውልድ መንደር የሚደረግ ልዩነት ሊመጣ ሞቆብቆቡን እንረዳለን፡፡ የአጅባርና የአስፋው ግራር፣ የአራት ኪሎና የስድስት ኪሎ ወዘተ. ልጆችስ እየተፈላለጉ ይጣሉ የለ? ታዲያኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ‹‹አጅባሬ ነኝ!››፣ ‹‹ካሳንችሴ ነኝ!›› ወዘተ. ማለት ሊመጣ ነው፡፡ በአባትና ልጅ መሀከል ልዩነት አይፈጠር ብላችሁ ነው? ወይስ ተፈጥሯል?
ይህ ሁሉ የሚመጣው የስልጣኔን ጮራ፣ የትምህርትን ውጋገን ካለማገኘትና ከዚህም በላይ እውነተኛ የሀገር ፍቅር ከማጣት ነው፡፡ ስለዚህ ያገሬ ሰው ስማኝ፣ ተባበር፡፡ አትበታተን፡፡ ጠላትህን አታስደስት፡፡ ከተባበርክ እንኳን ረሃብን፣ ድንቁርናን እና ሌሎች ልዩ ልዩ በሽታዎችን ማጥፋት ትችላለህ፡፡
ተራራውን ብትገፋው ይገፋልሃል፡፡ ወደመሬት ማውረድ ወደሰማይ ማውጣት፣ ማስጠምም ማዳንም ያንተው ይሆናሉ፡፡ አትፍራ ሁሉም የሚፈልግ ህብረት ነው፡፡ አንድነትህን የሚጠላ የለም፡፡ ልብህን ይክፈተው፡፡ ብርታቱን ይስጥህ፡፡
ፈቃደ አዘዘ
የሰርቪስ መምህር
(በግል ምክንያት ሆሄ አልተጠበቀም)
መቼ ይሆን?
የደብረ ታቦር ሕዝብ መኪና በበጋ ሲመጣ በእልልታ መቀበሉ የሚቀረው?
ደብረ ታቦር መብራትና መንገድ ውሃና በቂ የሕክምና ጣቢያ የሚኖራት?
አንድ ብልህ ነጋዴ በላመነት የሚሰሩ ቦርሳዎችና ሻንጣዎች ኢንዱስትሪ የሚያያቋቁመው?
የደብረ ታቦር ጠላና ጠጅ የሚበላሸው?
የሚሲዎን ሀኪም ቤት አዋቂ ዶክቶሮች አስመጥቶ ሀብታም ደኃ ሳይል በትክክል የሚያክመው?
የደብረ ታቦር የ‹‹ቴዎድሮስ›› ቡድን (የእግር ኳስ) የቤጌምድር አሸናፊ (ሻምፒዎን) ሆኖ አዲስ አበባ የሚመጣው?
ፍርድ ቤት የሚመላለሰው ተሟጋች ቁጥር የሚቀንሰው?
እማማ የኔ ገላ የሚወፍሩት?!!!!!!!!
ተማሪዎችና መምህራን በጓድ ተከፋፍለው በትርፍ ጊዜያቸው ሕዝቡን በየቤቱ ሄደው የሚያስተምሩት?
የበኣል ቀናት ተቀንሰው የሥራ ቀናት የሚጨመሩት?
‹‹ፋርጣ ብር ቢያጣ ነገር አያጣ›› የሚባለው አነጋገር ዋጋ የሚያጣ?
በየመንገዱ፣ በየሜዳው፣ በየአጥር ጥጉና በየዱሩ መጸዳዳት የሚቀረው?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጭነት መጫኛ አውሮፕላን ሰው ማመላለሱን የሚተወው?
የደብረ ታቦር ተማሪዎች ለኮርስ መስገብገባቸውን ትተው በትምህርታቸው ለመግፋት የሚያስቡት?
አዝማሪዎች በቀን በቀን ብር አምጡ ማለት የሚተዉት?
የሰርቪስ መምህር - ፈቃደ አዘዘ
1964፣ ደብረ ታቦር

 

የሃይማኖት መሪው ቡድሐ የሚሰጠን አንድ ዕንቆቅልሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
አንድ ነጋዴ ሩቅ አገር ሄዶ ሲመለስ፤ ቤቱ በሽፍቶች ተዘርፎና ተቃጥሎ ይደርሳል፡፡
ከቤቱ የተረፈው ረመጥ - መካከል አንድ ተቃጥሎ የከሰለ የሰው ገላ ያያል፡፡ “ይሄ ትንሹ ልጄ መሆን አለበት” አለ፡፡
በዚህ ምክንያት ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡ ደረቱን መታ፡፡ ፀጉሩንም ነጨ፡፡
ገላውን እንደገና የማቃጠል፤ የሐዘን ሥነስርዓት እንዲካሄድም አደረገ፡፡
ይህ ወንድ ልጁ ነው፡፡ ከልጁ የናፍቆት ስሜት ለመላቀቅ በጭራሽ ካለመፈለጉ የተነሳ፣ ለቅጽበት እንኳ ሳይለየው የልጁን አስከሬን አመድ በከረጢት አንጠልጥሎ ይዞር ጀመር፡፡ ቆይቶም ከሀር የተሰራ ከረጢት አሠርቶ ይሸከመው ጀመር፡፡ ቀን ከሌት ይዞት ይዞራል፡፡ ሥራም ቦታ ቢሆን ተሸክሞት ይውላል፡፡ በእረፍት ሰዓቱም እንደዚያው፡፡ ከአመዱ የሚለይበት አንዳችም ደቂቃ የለም፡፡
አንድ ሌሊት፤ ለካ ወንድ ልጁን ሽፍቶቹ አግተው ወስደውት ኖሮ፤ ከታሠረበት አምልጦ አባቱ አዲስ ወደ ሠራው ቤት ይመጣል፡፡
ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ ደርሶ፤ የአባቱን ቤት በር በስሜት ፍንድቅድቅ ብሎ አንኳኳ፡፡
አባቱ፤ አሁንም የከረጢት አመዱን እንደተሸከመ ነው፡፡
“ማነው፤ በዚህ ሌሊት የሚያንኳኳው?” አለና ጮኾ ጠየቀ፡፡
“እኔ ነኝ - ወንድ ልጅህ ነኝ አባባ”፤ አለ ልጁ በበሩ ሽንቁር እያየ፡፡
“አንተ ባለጌ ሰው፡፡ አንተ የእኔ ልጅ ልትሆን ከቶ አትችልም፡፡ የእኔ ልጅ ከሶስት ወር በፊት ሞቷል፡፡ አመዱ እዚሁ እጄ ውስጥ አለ!” አለው፡፡
ትንሹ ልጅ ግን በሩን መደብደቡን ቀጠለ፡፡ ጮኾ፤
“ኧረ አባባ እኔ ያንተው ልጅ፣ የምታውቀኝ ውዱ ልጅህ ነኝ፤ አስገባኝና እየኝ!” ደጋግሞ ለመነው፡፡ ተማጠነው፡፡
አባትዬው ግን፤
“ዘወር በል ብዬሃለሁ! ከዚህ ወዲያ አልታገስህም፡፡
ድራሽህ ይጥፋ! አለዚያ ብትንትንህን ነው የማወጣህ” ለመጨረሻ ጊዜ ልንገርህ፤
የእኔ ልጅ በሽፍቶች ተቃጥሎ ሞቶ፣ እኔ አስከሬኑን አመድ አድርጌ፣ አመዱን ተሸክሜ ስዞር ከርሜያለሁ፡፡ ስለዚህ አንተ የመጣኸው የልጄን ሐዘን ዳግመኛ ለመቀስቀስና የእኔን አንጀት ለማቃጠል ነው! አንት ጨካኝ አረመኔ፤ ጥፋ ከፊቴ!”
ልጅየው ተስፋ ቆርጦ ሰፈሩን ጥሎ ጠፋ፡፡
አባት፤ በህይወት ያለ ዕውነተኛ ልጁን ለአንዴም ለዘለዓለም አጣ፡፡
* * *
እንደ ቡድሐ አመለካከት፤ ከአንድ አስተሳሰብ ጋር እኝኝ ብለን ከተጣበቅንና፤ “አንዱና አንዱ ዕውነት” ይሄ ብቻ ነው ብለን ካከረርን፣ ዕውነተኛውን ዕውነት የማወቅ ዕደላችንን እንዘጋለን። ዕውነት እንደሰው ደጃፋችሁ ቆሞ ቢያንኳኳም እንኳ የአዕምሮአችሁን በር ለመክፈት ዝግጁ አትሆኑም፡፡ ስለዚህ ስለ አንድ ዕውነት የምትገነዘቡበትን መንገድ ሥራዬ ብላችሁ መርምሩት፡፡ ተጠንቀቁ፡፡ የነገር ሁሉ መጀመሪያው፤ ከሃሳብ እሥር ነፃነትን ማወጅ ነው፡፡
ይህን ዕውነት ወደ እኛ አገር ፖለቲካ ስንመነዝረው፤ ቁልጭ ያሉ፤ አመድ የማቀፍና ህያው ልጅን የመካድ፤ ዕውነታን እናገኛለን፡፡
ዕውነተኛውን ልጃችንን እንለይ፡፡ በከረጢት ውስጥ ያለው አመድ በህይወት ካለው ልጅ የተለየ መሆኑን እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከአመዱ - ከግትር ሃሳባችን፣ እንገላገል፡፡ እኛ የጀመርነው መንገድ ብቻ ነው ዳር የሚያደርሰው ብለን ድርቅ ከማለት አባዜ ተላቀን፤ የጀመርነው መንገድ መጨረሻ የማያሳልፍ - ግድግዳ (Dead End) ቢሆንስ? አብረውን ከሚጓዙት መካከል ሃሳባቸውን የሚለውጡ ቢገኙስ? የመኪናው ጐማ ቢተነፍስስ? የባቡሩ ሃዲድ ቢጣመምስ? ብለን እንጠይቅ። አንድ የአገራችን ፀሐፌ ተውኔት እንዳለው፤
“ገና ላልተወለደ ልጅ ስም እናውጣ ብለን ለምን እንጣላለን፡፡ “ዐይናማው” ብለነው ዕውር ሆኖ ቢወለድስ? ክንዴ ብለነው እጁ ቆራጣ ቢሆንስ?...” ብለን መጠራጠር ቢያንስ ከጭፍንነት ያድነናል። ከአንድ መሥሪያ ቤት በሙስና፣ በፍትሐዊነት ወይም በኢዲሞክራሲያዊነት፤ በግምገማ የተነሳን ሰው ለሌላ መሥሪያ ቤት በኃላፊነት ማስቀመጥ አልሸሹም ዞር አሉ፤ ነው፡፡ ይሄኛው መሥሪያ ቤት አንቅሮ የጣለውን ግለሰብ ያኛው መሥሪያ ቤት በምን ዕዳው ይሸከማል? የሀገሪቱን የሥራ ሂደት ባለቤቶች በበኩር ልጅነት አቅፈንና “የባለቤቱ ልጅ” አሰኝተን ስናበቃ፤ በሀቅ የሚለፉላትን ሀቀኛ ልጆች በር እያንኳኩ ሳንከፍት እያባረርናቸው ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ይቻለናል? በቡድናዊና ድርጅታዊ መንፈስ፤ እስከመቼ እከክልኝ ልከክልህ ተባብለን እንዘልቀዋለን?
“ዕብድ ሆኜ ስለማላውቅ፣ ዕብድ የሚያስበውን አላውቅም፡፡ ዝም፣ ጭጭ ብለህ ተቀምጠህ ሳይህ፣ ምናልባት ይሄ ዕብደትህ ልዩ ሰላም ሰጥቶህ ይሆንን? ብዬ እቀናብሃለሁ-መንሳፈዊ ቅናት ማለቴ ነው” ይላል የአገራችን ፀሐፊ፡፡ ዝምታ ማስቀናቱ ይገርማል፡፡ ስንት ግፍ ሲሰራ እያየህ ዝም። ስንት ዘረፋ ሲካሄድ እያየህ ዝም፡፡ ጓዳህ እየተራቆተ፣ ኢኮኖሚህ እየተንኮታኮተ እያየህ ዝም ለማለት ከቻልክ፣ የሚያስቀና ዝምታ አለህ፤ ታድለሃል፤ ማለት ነው፡፡ ከዕብደት ውስጥ የሚገኘው ልዩ ሰላም ይሄ መሆኑ ነው፡፡ ዝም የሚሉ ያሉትን ያህል፣ ሃያ አራት ሰዓት በመለፍለፍ እኛ ነን ጀግና የሚሉም አገራችን ያፈራቻቸውና በተገለባባጭነት፣ በአድር ባይነት፣ በጥገኝነት ንፍቀ - ክበብ ውስጥ የሚኖሩ አያሌ “ቀልጣፋ” ሰዎች አሉ፡፡ ከጠቆረው መጥቆር፣ ከነጣው መንጣትን ተክነውበታል፡፡
“እንደወዶ -ገባ ኮርማ፣ ተነስ ሲሉት የሚነሳ፤
ተኛ ሲሉት የሚተኛ!”
ያለው ዓይነት ነው ገጣሚው፡፡ ከየትኛውም ማዕድ ለመቋደስ እጃቸውን (የዓለም የእጅ መታጠብን ቀንን እያከበረ እንደማለት) ታጥበው፣ ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ለእነሱ ፖለቲካ በየትኛውም የሳንቲሙ ገጽ - ማለትም በአውሬውም በሰዉም በኩል - ለመጠቀም የሚችሉ ናቸው፡፡ መቼም ቢሆን መቼም በየትኛውም ገዢ ዘመን አድርባይነታቸውን አያቋርጡም። The pendulum of opportunism never stops oscillating እንዳለው ነው ሌኒን፡፡ “ከአህያ ጋር ብጣሪ በልታ፣ ከፈረስ ጋር ገብስ ትበላለች” ይለዋል የወላይታው ተረት፡፡ ከአድባርባይነት እርግማን ይሰውረን!

በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሀመድ አማን፤ የ800 ሜትር ውድድሩን በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት አጠናቆ የወርቅ ሜዳልያውን ከወሰደ በኋላ፣ መደበኛው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥበትን አዳራሽ ያጣበብነው አምስት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና የብሄራዊ ቡድኑ ሃኪም ዶክተር አያሌው ነበርን፡፡ ውድድሩ ተጠናቅቆ ከምሽቱ ለአምስት ሰዓት ምናምን ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በመሃመድ ታሪካዊ ድል ደስታችን ልክ አልነበረውም፡፡

በፕሬስ ኮንፍረንሱ አዳራሽ የተገኘነው ከየትኛውም አገር ጋዜጠኞች ቀድመን ነበር፡፡ መሃመድ አማን በ800 ሜትር ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈርቀዳጅ ታሪክ መሆኑን፤ በሻምፒዮናው ታሪክ በ20 ዓመቱ የርቀቱን የወርቅ ሜዳልያ ለመውሰድ የበቃ ድንቅ አትሌት እንደሆነ ጋዜጠኞች ስንነጋገር፣ ዶክተር አያሌው መሃከል ገቡና፣ መሃመድ ለ800 ሜትር እና ለአጭር ርቀት ውድድር የተፈጠረ ምርጥ አትሌት መሆኑን በመጠቆም፣ በስፖርቱ ውጤታማ ለመሆን ባለው የስራ ፍቅርና ትጋት እንደሚያደንቁት ገለፁልን ፡፡ ውይይታችን በስፍራው የነበሩ የሌላ አገር ጋዜጠኞች እና የስፖርት ባለሙያዎችን ትኩረትም ስቦ ነበር፡፡
በፕሬስ ኮንፍረንሱ አዳራሽ ከመሃመድ አማን በፊት መግለጫ የሚሰጡ የሌላ ውድድር አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ የዲስከስ ውርወራ እና የሄፕታትሎን ተወዳዳሪ የነበሩ ናቸው፡፡

የሁለቱ ስፖርቶች አሸናፊዎች መግለጫዎች ሲሰጡ ኢትዮጵያውያኑ ባይተዋር ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ በረጅም ርቀት እንጂ በ800 ሜትር ኢትዮጵያዊ አትሌት አሸንፎ ለጋዜጣዊ መግለጫ እንበቃለን ብለን አስበንም አልመንም አናውቅም፡፡ የወንዶች ዲስከስ ውርወራ አሸናፊዎች እና የሴቶች ሄፕታተሎን ውድድር ሜዳልያ ተሸላሚዎች መግለጫ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ተራው የእነ መሃመድ አማን ሆነ፡፡ ወደመግለጫው የገቡት የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደው መሃመድ አማን፤ የብር እና የነሐስ ሜዳልያውን የወሰዱት የአሜሪካ አትሌቶች ነበሩ፡፡ መሃመድ አማን የወርቅ ሜዳልያውን ያስመዘገበው የሉዝንስኪ ስታድዬም በምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳዳሪዋ ራሽያዊት ዬለና ኢዝንባዬቫ ምክንያት ጥቅጥቅ ብሎ በሞላበት ወቅት ነበር፡፡

መሃመድ አማን በ800 ሜትር ያሸነፈው በጣም ጠንካራ አትሌቶች በተሳተፉበት የ800 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ሲሆን ርቀቱን የሸፈነበት 1ደቂቃ ከ43.31 ሰኮንዶች የውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ መሃመድ አማን በ5ሺ፤በ10ሺ እና በማራቶን ውድድሮች ስኬታማ አትሌቶች ከበዙባት ኢትዮጵያ መውጣቱ እያነጋገረ ሲሆን ከአጭር ርቀት ሯጭነት ወደ መካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌትነት መሻገሩም ያልተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ መሃመድ አማን መግለጫውን የሰጠው በእንግሊዘኛ መሆኑ ነው፡፡ ይሄም ሌላ ያልተጠበቀ ነገር ሆኗል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በአስተርጓሚ ነበር ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡት፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታውን ፊልሞች በመመልከት እና በማንበብ ነው ያዳበረው፡፡ ለመሃመድ የቀረበለት የመጀመርያው ጥያቄ ከመግለጫው መሪ የአይኤኤኤፍ ጋዜጠኛ ነበር፡፡
“መሃመድ ውድድሩ አስቸጋሪ ነበር፤ በሩጫው መሃል ወደ ኋላ ቀርተህ ከዚያ በኋላ ነው አፈትልከህ የወጣኸው፡፡ ስትራቴጂው ምን ነበር?” ሲል ጠየቀው፡፡
“የፍፃሜ ውድድር ነው፡፡ ስለዚህም ለማሸነፍ የተከተልኩት ስትራቴጂ ተገቢ ነው፡፡ በፍፃሜ ውድድር የሚሳተፉት ሁሉም አትሌቶች ምርጥ ብቃት እንዳላቸውና የማሸነፍ እድል እንደሚኖራቸው ግምቱ ነበረኝ፡፡ እስከመጨረሻዎቹ ሜትሮች ሁኔታውን እያጠናሁ በትዕግስት ተጠባብቄያለሁ፡፡ ከዚያም በአስፈላጊው ጊዜ አፈትልኬ ወጥቻለሁ፡፡›› በማለት መሃመድ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ቀጣዩ ጥያቄ ከፕሬስ ኮንፍረንሱ የመድረክ መሪ የቀረበ ሲሆን ያሸንፋል የሚል ግምት ለተሰጠው አሜሪካዊው ኒክ ሳይመንድስ እና ለነሐስ ሜዳልያው ባለድል የጅቡቲ አትሌት ነበር፡፡ “ኒክ ሳይመንድስ” በብር ሜዳልያው መወሰንህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?” ተብሎ ለተጠየቀው ሲመልስ፤
‹‹በብር ሜዳልያው በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ውድድሩ ሜትር እስኪቀረው ቀጣዩ የዓለም ሻምፒዮን መሆኔን እያሰብኩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ባገኘሁት የብር ሜዳሊያ ብዙም አልተከፋሁም›› ያለ ሲሆን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤቱ ጅቡቲያዊ በበኩሉ፤ ‹‹ደስተኛ ነኝ፤ ለአገሬ የተገኘ ብቸኛ እና የመጀመርያው ሜዳልያ ነው፡፡ ውጤቱ በጠንካራ ፉክክር የተገኘ በመሆኑም አኩርቶኛል›› በማለት መልሷል፡፡
ለመሃመድ አማን “በአገርህ ለወርቅ ሜዳልያ መጠበቅህ የፈጠረብህ ጫና ነበር ወይ” የሚል ጥያቄ ከኢንተር ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና የአትሌቲክስ ዘጋቢ ብዙአየሁ ዋጋው ቀርቦለት ነበር፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት እና በማራቶን ውድድሮች ውጤታማ በሆኑ በርካታ አትሌቶቿ ትታወቅ ነበር፡፡ እኔ በአጭር ርቀት ውጤታማ በመሆኔ ብዙ ጫና አልነበረብኝም፡፡ እንዴት እንደሆነ አላውቀውም፡፡ ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜት አለኝ፡፡ አራት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ማሸነፍ መቻሌ በጣም ልበ ሙሉ አድርጎኛል፡፡ የዓለም ሻምፒዮና ጠንካራ ፉክክር ያለበት ነው፡፡ በጥንቃቄ መሮጥ ያስፈልግ ነበር፡፡
ስለውድድሩ ላለመጨነቅ ስል ብዙ ሃሳብ ውስጥ አልገባሁም፡፡ ለጥ ብዬ እንቅልፌን ተኛሁ፡፡ አሰልጣኜ ስልክ ደውሎ ምን እየሰራህ ነው አለኝ፡፡ ስለ ውድድሩ ከማሰብ ጥሩ እረፍት እንደሚያስፈልገኝ አምኜበት መተኛቴን ነገርኩት” በማለት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የኢቴቪ ስፖርት ጋዜጠኛ እና የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዮናስ ተሾመ በበኩሉ፤ “ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲስ ታሪክ ሰርተሃል፡፡ በአጭር ርቀት በአለም ሻምፒዮና የተመዘገበ ብቸኛ ድል ነው፡፡ ምን ተሰማህ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦለታል፤ ለአትሌቱ፡፡
መሃመድ ሲመልስም፤ ‹‹ምንም የማይቻል ነገር የለም፡፡ ድል እንደማደርግ እምነት ነበረኝ፡፡ ያስመዘገብኩት ውጤት ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት የመጀመርያው በመሆኔም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ልምምዴን የምሰራው በኢትዮጵያ ነው፡፡ በእንጦጦ፣ በሰንዳፋና በአዲስ አበባ ዙርያ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች ጋር ነው የምሰራው፤ አሰልጣኜም ኢትዮጵያዊ ንጉሴ ጌቻሞ ነው፡፡ ›› በማለት አስረድቷል፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ ስል ጠየቅሁት፤ “በ800 ሜትር የዓለም ሪከርድ የያዘው፤ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነው ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ ቢኖር የወርቅ ሜዳልያው እድል የጠበበ ይሆን ነበር ብለህ አላሰብክም?”
‹‹በመጀመርያ እኔ ልምምድ ስሰራ የቆየሁት ለዴቪድ ሩዲሻ ብቻ አልነበረም፤ሩዲሻ ባለመኖሩ አዝኛለሁ፡፡ ጉዳት ለብዙ አትሌቶች ፈተና እየሆነ ነው፡፡ እሱ ባይኖር እንኳን ለፍፃሜ የደረሱት ሌሎቹ ሰባት አትሌቶች እጅግ ጠንካሮች ነበሩ፡፡ እነሱን በማሸነፌ ውጤቴን አስደሳች አድርጎታል፡፡› ሲል መለሰልኝ፡፡
በመጨረሻም ወደ አገሩ ሲመለስ ደስታውን እንዴት እንደሚያከብር ነበር የተጠየቀው፡፡ አማን ወደ ትውልድ ቀዬው አሰላ ለመሄድ የሚፈልገው በመስከረም ወር ዋዜማ በብራሰልስ ከሚያደርገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኋላ ነው፡፡ ከብራሰልስ በኋላ በቀጥታ ወደ እናቱ ቤት ለመሄድ እቅድ ይዟል፡፡ ቤተሰቡ በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና እና በለንዶን ኦሎምፒክ ሲሮጥ ተመልክተውታል፡፡ በሁለቱም ውድድሮች እንዲያሸንፍ ጠብቀው አልተሳካለትም፡፡ አሁን ግን የልባቸውን አድርሶላቸዋል፡፡ የቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያንን፡፡ ከብራሰልስ መልስ የዓለም ሻምፒዮና ድሉን ከወላጆቹ እና ከመላው ቤተሰቡ ጋር በፌሽታ እንደሚያከብር አማን በፈገግታ ተሞልቶ ገልፆልናል፡፡ አንድ ፌሽታ ሳይሆን ሺ ፌሽታ ይገባዋል፡፡