Administrator

Administrator

Saturday, 11 September 2021 00:00

የአዲስ ዓመት ምኞት

ያሳለፍነው  ዓመት  በጎና ክፉ ገፅታን ያስተናገድንበት ዘመን ነበር። ከበጎ ገፅታው ብንጀምር ከ3 ዓመት በፊት የተጀመረው የለውጥ ሂደት የቀጠለበት፣ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የቻልንበት፣ በብዙ ፈተናዎችና መሰናክሎች ውስጥ ሆነን የሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማጠናቀቅ የቻልንበት፣- 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ በስኬት ያከናወንበት በጎ ዘመን ነበር።
ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ዕድገትና ህልውና በማይፈልጉ አገራት የሚደረጉ ከፍተኛ ጫናን ያስተናገድንበት፣ የሱዳን፣ ጦር ወደ አገራችን በእብሪት ዘልቆ የገባበት፣ መንግስት በታላቅ ትዕግስት ሁኔታውን እየተከታተለ ያለበት፣ አገራችን በውስጥና በውጭ ሊያጠፏት ካሴሩ ወገኖች ጋር ወደ ጦርነት እንድትገባ የተገደደችበት፣ በዚህም በርካታ ወገኖቻችንን ያጣንበት፣ ስደትና መፈናቀል  የበዛበት… ከባድ ጊዜ ነበር 2013 ዓ.ም። በአጠቃላይ ዘመኑ ዕድሎች ፈተናዎችና ስኬቶች ያስተናገደ  ነበር።
መጪው አዲስ ዘመን አገራችን ሰላሟን የምታገኝበት፣ ግጭቱና ጦርነቱ እልባ የሚያገኝበት፣ አዲሱ መንግስት ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚችልበትን መንገድ የሚፈልግበት፣ ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት መብራት ማፍለቅ የሚጀምሩበት፣ ለሁለገብ ብልፅግናችን በጋራ የምንቆምበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ።
ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ
የውሃና መስኖ ሚኒስትር
ዓመቱን በብዙ ችግሮችና ፈተናዎች አልፈን ዛሬ ላይ ደርሰናል። መጪው አዲስ ዓመት ለአገራችን መልካም ነገሮች የሚሆንበት፣ አገራችን ሰላም ሆና ህዝቦቿ በሰላም ወጥተው የሚገቡባት፣ ዕቅዳችንን የምናሳካበት፣ ዘመን እንዲሆን ምኞቴ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ወደ ተረጋጋ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የምትገባበት፣ ህዝቦቿ ተረጋግተው በልማቱ ላይ ትኩረት የሚያደርጉበት ጊዜ እንዲሆንም እመኛለሁ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ፤


https://youtu.be/GonjDf73WXY

የተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም ለአገራችን እጅግ ፈታኝ ዘመን ነበር። ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት ያልቻሉበት፣ በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን በሞት የተነጠቅንበት፣ በተፈጥሮአዊ አደጋዎች፣ በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተትና መሰል አደጋዎች በርካቶች ለእልፈት ህይወታቸውን ያጡበት ጊዜም ነበር። በዓመቱ በኮቪድ ወረርሽኝና በተለያዩ ህመሞች በሞት ካጣናቸው ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከል ጥቂቶቹን እናስታውሳቸው።
የኮሮና ወረርሽኝ በ2013 ዓ.ም ካሳጣን ታላላቅ ሰዎች መካከል ቀዳሚው ታዋቂው ምሁር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ናቸው። ፕሮፌሰር መስፍን በኮሮና ሳቢያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉበት በነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ በ90 ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ሌላው ኮቪድ-19 ያሳጣን ታላቅ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰን ነው። እኚህ ታላቅ ምሁር፣ የቲአትርና የፊልም ተዋናይ፣ ደራሲና ተርጓሚ ተስፋዬ ገሰሰ፤ በኮሮና ሳቢያ በ84 ዓመታቸው በሞት የተለዩን ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።
ይህ ክፉ ወረርሽኝ ባሳለፍነው ዓመት ያሳጣን ሌላው ዕውቅ ምሁር የዓለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነብርሃን ናቸው።
በህክምና ሙያ፣ በዕርዳታ  አስተባባሪነት፣ በእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባልነትና በአገር ሽማግሌነት አገራቸውን ያገለገሉት እኚህ ታላቅ ባለሙያ በኮሮና ሳቢያ በሞት የተለዩን በያዝነው ዓመት፣ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ኮቪድ በተጠናቀቀው ዓመት በበጎ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሺዎችን የታደጉ የበጎ ተግባር አርአያዎቻችንንም አሳጥቶናል።
በኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት (ኦቲዝም) ያለባቸውን ህጻናት ህይወት በመለወጥ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱትና የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ሴንተር መስራቿ ወ/ሮ ዘሚ የኑስም ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህይወታቸው ያለፈው በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ነበር።
ኢትዮጵያዊቷ “ማዘር” ትሬዛ የሚል ስያሜ የሚታወቁት የተሰጣቸውና የሺዎች እናትና አሳዳጊ የነበሩት የክቡር ዶ/ር አበበች ጎበናም ኮቪድ-19 ለህልፈት ዳርጓቸዋል። ልጆቻቸው እዳዬ በሚል  የፍቅር ስም የሚጠሩትና በ10ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መጠጊያ በመሆን ሺዎችን ያሳደጉት ወ/ሮ አበበች፤  ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም  በሞት ተለይተውናል።
ኮቪድ ወደ ኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ጎራ ብሎም ተወዳጁን የፊልም ደራሲ፣ ተዋናይና አዘጋጅ አርቲስት መስፍን ጌታቸውንም ለሞት ዳርጎታል። “ሰው ለሰው” የተሰኘው የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ ደራሲና ተዋናይ የነበረው መስፍን ጌታቸው፤ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም  በቫይረሱ ሳቢያ ህይወቱ አልፏል።
ዘመኑ የኪነ-ጥበቡን ዘር በሞት ደጋግሞ የጎበኘበትም ነበር። አንጋፋው ሰዓሊ ለማጉያ፣  ተወዳጅ ተዋናይት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ)፣ አንጋፋው የማንዶሊን ንጉስ አየለ ማሞ፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ቀደምት ከሚባሉት የሙዚቃ አሳታሚዎች፣ አንዱ የነበረው አሊ አብደላ ኬያፍ (አሊታንጎ) በሞት የተለዩን በዚሁ በተጠናቀቀው ዓመት ነበር።
በደርግ ስርዓት ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩት ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስን ነበር። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ኮሚሽነር አበረ አዳሙም በሞት የተለዩት በተጠናቀቀው ዓመት ነበር። የመጀመሪያዋ ሴት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሕሌኒ መኩሪያም በሞት የተለየችን በዚሁ በ2013 ዓ.ም ነው።
ዓመቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ሲቀረው በድንገተኛ የልብ ህመም በሞት ያጣነው ደግሞ ተወዳጁና አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ነው። ድምጻዊው ቀብር  ስነ-ስርዓቱ የተፈጸመው ባለፈው ማክሰኞ ጳጉሜ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ለሁሉም ፈጣሪ ነፍሳቸውን በመንግስተ ሰማያት ያኑርልን!!


 28 ሰዎች በጎርፍ ህይወታቸው አልፏል
- ከ23  ሺህ በላይ ከብቶች  ሞተዋል

እየተገባደደ ባለው የክረምት ወራት በሃገሪቱ እስካሁን ከ6 መቶ ሺህ በላይ ዜጎቹ ጉዳት ሲደርስባቸው፤ ከ2 መቶ በላይ የሚሆኑት  ከቀዬአቸው  መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ  ድጋፍ ማስተባበሪያ  ጽ/ቤት ሪፖርት ያመለክታል።
በ2012 ክረምት ወቅት በአፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልል ባጋጠሙ የጎርፍ አደጋዎች  616 ሺህ 714 ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 214 ሺህ 127 የሚሆኑት ተፈናቅለዋል እንዲሁም የ28 ሰዎች ህይወት አልፏል።
የክረምቱ የጎርፍ አደጋ እንስሳትና ሰብል ምርቶች ላይም ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ 23 ሺህ 788 የቤት እንስሳት በጎርፍ ተወስደዋል፣ በ18 ሺህ 97 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ወድሟል። እንዲሁም  464 መኖሪያ ቤቶች እና 6 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ  ወድመዋል።
በጎርፍ አደጋው በእጅጉ ከተጠቁት አካባቢዎች መካከልም በሶማሌ ክልል የሸበሌ  ዶሎ፣ ጃራር፣ አፍዴር፣ ፋፈን፣ ቆራሄ፣ በደቡብ ክልል ደግሞ በወላይታ፣ ሃላባ፣ ጎፋ እና ከፋ ዞኖች ጉዳቱ ያጋጠመ ሲሆን በአፋር ክልል ዞን 2፣3 እና 4 ፤ በኦሮሚያ ክልል አርሲ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ሃረርጌ፣  የምዕራብ ሸዋ ዞን፤ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና መካከለኛው ጎንደር ዞኖች ፣ በሃረር ክልል ሶፊያ ዞን እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ላሬ  ወረዳ  የጎርፍ  አደጋዎቹን ያስተናገዱ ናቸው።
የክረምቱ ወቅት አሁንም ቀጣይነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀጣይም የጎርፍ አደጋዎቹ በእነዚህና በሌሎች አካባቢዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባለ ሲሆን ህብረተሰቡ አሁንም ጥንቃቄ አይለየው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከሶስት ሳምንታት በፊት ባጋጠመው ጎርፍ አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም።
አስቀድሞ በተሰራው የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ቅድመ ግምት፤ በክረምቱ እስከ 2 ሚሊዮን ዜጎች የጎርፍ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ ነበር።

የህወሓት አማጺያን በሰሜን ጎንደር ከ120 በላይ  ሰዎች መግደላቸውን ነዋሪዎች  ተናገሩ

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ወረዳ ጭና በሚባል አካባቢ የህወሓት ታጣቂዎች ከ120 በላይ ንፁሃን ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎችና የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ግድያው የተፈጸመው አካባቢው በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በቆዩባቸው ቀናት ውስጥ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በጥቃቱ ሽማግሌዎች፣ ቀሳውስት፣ ሴቶችና ህጻናት መገደላቸውን  ጠቁመዋል፡፡  
የጭና አጎራባች ቀበሌ አብጥራ  ነዋሪ የሆኑት አቶ አስማረ ታፈረ፤ ነሐሴ 12 ቀን 2013 ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ የህወሓት ኃይሎች ወደ  አካባቢው  በመግባት ተኩስ መክፈታቸውንና ውጊያ መካሄዱን ይናገራሉ፡፡  ጦርነቱም እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መካሄዱን የሚገልፁት አቶ አስማረ፤ እስካሁን ድረስ ተገድለው የተገኙ 119 ሰዎች በጦርነቱ ያልተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ነዋሪው ይናገራሉ። ከአንድ ቤተሰብ አምስትና ስድስት ሰዎች የሞቱ መኖራቸውንም አቶ አስማረ ገልጸዋል።
ሮይተርስና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎችም፤ በዳባት አካባቢ በምትገኘው ስፍራ በተፈጸመው ጥቃት ከ120 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የአካባቢውን ምንጮች ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡ የትግራይ የውጭ ግንኙነት ጽህፈት ቤት የተባለው አካል ግን ረቡዕ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ በህወሓት ኃይሎች ተፈጸመ የተባለውን የጅምላ ግድያ ክስን  አስተባብሏል።
የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ጭና ሲገቡ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳልደረሰባቸው የገለጹት ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሞላ ውቤ፤ “ጦርነቱ ሲፋፋምና አማጺያኑ መሸነፋቸውን ሲያውቁ አዛውንት፣ ሕጻናት፣ ሴቶች እንዲሁም እንስሳትን እየገደሉ ሄደዋል” ብለዋል።  ከአንድ ቤተሰብ አራት ሰዎችን፣ ቀሳውስትን እንዲሁም ወንድማማቾችንና ነፍሰ ጡር ሴትን  መግደላቸውን አቶ ሞላ  ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ “እኛ ችግር ያለብን ከመንግሥት ጋር ነው፤ ከእናንተ ጋር አይደለም” በማለት ለነዋሪው ይናገሩ እነደነበር የገለጹት አቶ አስማረ፣ በኋላ ግን ጦርነቱ እየተጧጧፈ ሲመጣ ንፁሃንን ገድለዋል ብለዋል።
የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ዳባት ጭና ከመድረሳቸው በፊት፣ አዳርቃይ እንዲሁም ደባርቅ ወረዳ ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈፀማቸውን አስተዳዳሪው ጨምረው ገልፀዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ከህወሓት ኃይሎች ነጻ ከወጣ ከቀናት በኋላ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ንጹሃን የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ማግኘቱን ያስታወቀው የዞኑ አስተዳደር ነው።
በዚህም የህወሓት ኃይሎች በወረዳው ውስጥ “ጭና ተክለ ሐይማኖት በተባለ ቀበሌ ቀሳውስትን ጨምሮ በንጹሃን ሰዎች ላይ ነሐሴ 26 እና 27 የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል” በማለት በአንድ መቃብር ብቻ 47 አስከሬኖች እንደተገኙ ገልጿል።
(ቢቢሲ)


==================================================

 ‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን በፅኑ እናምናለን››


የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን ጉዳይ ማወቅ ባይቻልም፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን እናምናለን›› ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ ሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተከናወነ ስላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ አቅርቦት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት የፌዴራል መንግሥት መዋቅር ባለመኖሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ዕርዳታ የሚያቀርቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለምን ያህሉ ሕዝብ፣ ምን ያህል ዕርዳታ፣ በምን አግባብ እንዳስተላለፉ ሪፖርት እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከትግራይ ክልል ሲወጣ ለአንድ ወር የሚሆን የዕለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን፣ በተመሳሳይ የዕርዳታ ድርጅቶችም ለአንድ ወር የሚሆን ተመሳሳይ አቅርቦቶችን ጥለው መውጣታቸውን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።  
በተጨማሪም ከመንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም በኋላም እሑድ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የተንቀሳቀሱ 152 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 500 ያህል ተሽከርካሪዎች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ፣ እንዲሁም የዕርዳታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሕወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ባደረጉት ወረራና በንፁኃን ዜጎች ላይ እያደረሱ ባለው ጥቃት ምክንያት፣ እንዲሁም በዕርዳታ መተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጨማሪ ዕርዳታ የማድረስ ሒደቱን ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዕለት ደራሽ የዕርዳታ ምግብ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ተሽከርካሪዎች መመለስ ሲኖርባቸው፣ 72 በመቶ የሚሆኑት አለመመለሳቸውን ወ/ሮ ሙፈሪያት አስታውቀዋል፡፡
‹‹ተሽከርካሪዎች ለተፈቀደላቸው ሥራ ብቻ መዋላቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከወጣ በኋላ የክልሉ ሕዝብ በመጪዎቹ ዓመታት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በማሰብ፣ የግብርና ግብዓት ሲያደርስ መቆየቱን በመጥቀስ፣ የመንግሥት ፍላጎትና ጥረት ሕዝቡ እንዳይጎዳ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በመሆኑም አምርቶ የሚመገብ ማኅበረሰብ መኖር እንዳለበት ስለምናምንና ሥራችን እሱን መሠረት ካላደረገ፣ ችግሩ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም በክልሉ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ ዋስትና ችግር እንደነበረበት በመጥቀስ፣ ‹‹ከአንበጣ ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ ሕወሓት በራሱ ጊዜ ፈልጎ በከፈተው ጦርነት ለሕዝቡ ያተረፈው ቀውስ እንዳይቀጥል ስለምንፈልግ፣ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ሲወጣ በመጋዘኖች ያከማቻቸውን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና አሁን እየተላከ ያለውን አቅርቦት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ፣ አሁን በአንዳንዶች የሚወሳው ረሃብና ሞት የማስከተል ዕድሉ ትንሽ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን በትግራይ ክልል ረሃብ ወይም ሞት ተከሰተ ቢባል እንኳ በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰሞኑ እየተሰማ ያለው ሰፊ የሆነ ለጦርነት የሚሆን የስንቅ ዝግጅት፣ ከሚባለው እውነት ጋር የተራራቀ ነው ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት አስረድተዋል፡፡
በሕወሓት ወረራ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 500 ሺሕ የደረሰ መሆኑን፣ በአማራ ክልል ለ150 ሺሕ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ  መቻሉን ሚኒስትሯ አክለው ተናግረዋል፡፡
በአፋርና በአማራ ክልሎች ሕወሓት በፈጸመው ጥቃት 4.5 ሚሊዮን ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
(ሪፖርተር)

============================================

“ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታል ማውደም በጦር ወንጀልኝነት መታየት አለበት”

  የህወሓት ቡድን “ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት እጅግ አስነዋሪና በጦር ወንጀለኝነት መታየት ያለበት ድርጊት ነው” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ፡፡
 “ማን ከማን ጋር እንኳ እንደተጋጨ የማያውቁ ህጻናትን ትምህርት ቤት ማውደም በምን ይገለጻል?” በማለት በምሬት ጠይቋል፤አትሌት ሃይሌ፡፡
 አትሌቱ በአማራ ክልል በዋግ ኸምራ ዞን ፃግብጂ ወረዳ በዳስ ጥላ ለሚማሩ ህጻናት ያስገነባው ትምህርት ቤት በመውደሙ እጅግ እንዳዘነም ነው የገለጸው፡፡  ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ከገንዘብ ወጪ በላይ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የገለጸው አትሌቱ፤ የትምህርት ቤቱ መውደም በአካባቢው ማህበረሰብ ቁስል ላይ እንጨት እንደ መስደድ ይቆጠራል ብሏል፡፡
 አትሌቱ ያስገነባውን ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች መውደማቸውን ጠቅሶ፤ ይህም የቡድኑን “የክፋት ጥግ ያሳያል” በማለት አስረድቷል፡፡
 በየትኛውም ዓለም በሚካሄዱ ጦርነቶች ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎችን ዒላማ ማድረግ በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ መሆኑንም አትሌት ሻለቃ ሃይለ ገብረስላሴ መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 ትምህርት ቤቱም ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ህጻናት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ (ኤፍቢሲ)


=============================================

ሳዑዲ አረቢያ ማቆያዎች ውስጥ ያሉ 60 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ እስከ 3 ወራት ጊዜ ያስፈልጋል ተባለ


በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ማቆያዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ 60 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት እንደሚወስድ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ስደተኞቹን በአጠረ ጊዜ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ያልተቻለው፤ ለተመላሾች የተዘጋጁት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ባላቸው “ውስን አቅም ምክንያት ነው” ተብሏል።
በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምባዬ ወልዴ፤ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ በሚገኙ የማቆያ ካምፖች ውስጥ 60 ሺህ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ወደ ስፍራው በተጓዘ አጣሪ ቡድን ጭምር መረጋገጡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአጣሪ ቡድኑ አባላት ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የተውጣጡ ናቸው ብለዋል።  
 “[ይህ ቁጥር] በእኛ በኩል በተላከው አጣሪ ቡድን የተረጋገጠ ነው። ከዚያም በላይ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል” የሚሉት አቶ አምባዬ፤ ቡድኑ የለያቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ስራ በመከናወን ላይ እንዳለ ጠቁመዋል። ነሐሴ 12 ቀን 2013 በተጀመረው ሁለተኛ ዙር የስደተኞች የመጓጓዝ ሂደት፤ እስካሁን ድረስ አራት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መመለሳቸውን አስታውቀዋል። ስደተኞችን ወደ አገር ውስጥ በመመለሱ ሂደት ውስጥም ለሴቶችና ህጸናት ቅድሚያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በሳምንት ሶስት ጊዜ በሚደረጉ በረራዎች፤ በእያንዳንዱ ጊዜ ከ250 እስከ 400 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ቢሆንም፤ አጠቃላይ ሂደቱ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት እንደሚወስድ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለስ የማይቻለው፤ ለእነርሱ የተዘጋጁት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ያላቸው የማስተናገድ አቅም ውስን በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አቶ አምባዬ አብራርተዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን እያስተናገዱ የሚገኙ ጊዜያዊ ማቆያዎች በቁጥር ዘጠኝ ሲሆኑ፤ ሁሉም የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ወደ እነዚህ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ የሚገቡ ስደተኞች ለአንድ ቀን እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንደሚሸኙ አቶ አምባዬ ገልጸዋል።
 ረቡዕ ጳጉሜ 3፤ 137 ህጻናትን ጨምሮ 454 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ከሁለት ሺህ በላይ የክልሉ ተወላጅ ስደተኞች በጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉንም አመልክተዋል። ተመላሾቹ በማቆያዎቹ ውስጥ እንዲሰነብቱ የተደረገው ወደ ክልሉ ለመሄድ የሚያስችል ትራንስፖርት ባለመኖሩ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ። ህወሓት “ወጣቱን እያስገደደ፣ እያፈሰ ወደ ጦርነት እየማገደ ነው” ሲሉ የሚወነጅሉት ኃላፊው፤ ይህ ሁኔታም ከስደት ተመላሾቹ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንዳይሄዱ ተጨማሪ ምክንያት ነው ይላሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር በሐምሌ ወር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከሳዑዲ አረቢያ ከተመለሱ ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንድ ሶስተኛ ገደማ የሚሆኑት የትግራይ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀው ነበር። ከእነርሱ ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከጊዜያዊ ማቆያ መውጣታቸው በወቅቱ ተገልጿል።
 (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


Saturday, 04 September 2021 17:44

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

“የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ ነገር የለም!”
                                 ጌታሁን ሔራሞ


                  Jon Abbink ኔዜርላንዳዊ የአንትሮፖሎጂ እና የታሪክ ፕሮፈሰር ነው። በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካና ብሔር-ተኮር ግጭቶች ላይ ጥናት ማድረግ ከጀመረ ዓመታት አልፈዋል። ጥናቶቹን ጎግል አድርጎ ማውረድና ማንበብ ይችላል። አንዱም ጥናቱ እ.ኤ.አ. በ2006 ይፋ የተደረገው “Ethnicity and Conflict Generation in Ethiopia: Some Problems and Prospects of Ethno-Regional Federalism” የተሰኘው ጥናቱ ነው። ፕሮፈሰሩ ከብሔር ፖለቲካ ጋር ጠበኛ ነው።
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለ ቀደምት የዮን አቢኒክ ጥናቶች ማውሳት አይደለም። ይልቁን ፕሮፈሰሩ ከአንድ ቀን በፊት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት ዙሪያ አንድ ፅሁፍ ለቋል። ይህ ሰው ስለ ኢትዮጵያ የሚፅፈው ከውስጥ ሆኖ ነው፣ ስለዚህም እንደ አንዳንድ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን እሱን መሸወድ የሚቻል አይደለም። ለምሣሌ ከአንድ ቀን በፊት ፕሮፈሰሩ ገና ከመግቢያው የፃፈው ፅሁፍ በግርድፉ ሲተረጎም ይህን ይመስላል፦
“የትግራይ መከላከያ የሚባል ነገር የለም፣ አሁን ራሳቸውን እንደዚያ ጠርተው ይሆናል፣ያለው ግን የትህነግ ሚሊሻ ነው፦ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር። ነፃ የወጣ የትግራይ መንግስት የሚባል ነገርም የለም፣ ስለዚህም የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ ነገር የለም፤ በሕግ አግባብ የተፈጠረ እንደዚያ ዓይነት ሕጋዊ አካል የለም። እ.ኤ.አ ከ2018 በፊት በኢሕአዴግ ፓርቲ ውስጥ የአንበሳ ድርሻ የነበረው ትህነግ በኢትዮጵያ ላይ ሊነገሩ ዘንድ የሚያዳግቱ አደጋዎችን ፈፅሟል፣ ባለፉት ከ2-5 ዓመታት ደግሞ በራሱ የትግራይ ክልል ላይ አደጋን አድርሷል። ትህነግ እ.ኤ.አ.ከ1991-2018 ባለው ጊዜ የዘረጋው የብሔር ፖለቲካ በአፍሪካ ፀጉረ-ልውጡና የኢትዮጵያን ብሔሮች እርስ በእርሳቸው ያቃቀረ ፖለቲካ ነው።”
“There is no ‘TDF’: they may now call themselves like that but there is only the militia of the TPLF, the Tigray Peoples Liberation Front. There is no independent Tigrai state and hence no ‘TDF’: no entity like this was ever formed in a legal manner. TPLF (the former ruling regime in Ethiopia before February 2018, dominating the EPRDF party), has done untold damage to Ethiopia and in the past 2,5 years to Tigrai, ‘their own’ region. In 1991–2018 it installed a vicious politics of ethnicity ‘unique’ in Africa that has posited all so-called ethnic groups against each other, across the country.”
በነገራችን ላይ በየትኛውም የፌዴራል ሥርዓትን በሚከተሉ ሀገራት ክልሎች የራሳቸው መከላከያ ኃይል ብሎ ነገር የላቸውም። የመከላከያ ኃይል የሚኖራቸው በኮንፌዴሬሽን የተዋቀሩ አሊያም ሉዓላዊ ሀገራት ብቻ ናቸው። ፕሮፈሰር አቢኒክ ለዚህም ነው በተደጋጋሚ “የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ ነገር የለም” የሚለው!
መልዕክት ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ፦
እባካችሁ በዚህ ፕሮፈሰር ፅሁፍ ዙሪያ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ጭምር ሰፋ ያለ የዳሰሳ ሥራ ይሰራ።
ሰውዬው ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በአካል ተገኝቶ ሕወሓት በነደፈው የብሔር ፖለቲካና ተያያዥ ግጭቶች ዙሪያ ጥናት ሲያደርግ ስለነበረ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ይኖረዋል። ኢሳት ቴሌቪዥን በአንድ ወቅት ቃለመጠይቅ እንዳደረገለት አስታውሳለሁ።


Saturday, 04 September 2021 17:42

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 "እኛም ከነሱ መማር አለብን ብለን ወስነን ነበር"
                             ሔኖክ ሔዳቶ


                 “TPLF 27 ዓመት ሲገዛ በትግራይ ሌላ ፓርቲ አልነበረም። እኛም ከነሱ መማር አለብን ብለን ወስነን ነበር፤ የምደብቅህ ነገር የለም”
ይህን የተናገረው የቀድሞው ኦዴፓ (እንዲሁም 360 አባላት ያሉት የብልጽግና ፓርቲ) ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ሚልኬሳ  ነው፤ ከሀገር ከወጣ በኋላ ሰሞኑን OMN ላይ ቀርቦ ባደረገው ቃለምልልስ። ሚልኬሳ ይህን መልስ የሰጠው ጋዜጠኛው (ጉዮ ዋርዮ) በኦሮሚያ ስላለ እስርና ግድያ ምንጭ ምን እንደሆነ ለጠየቀው ጥያቄ ነው። አክሎም “የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ደጋፊዎች፣ እኛን የማይደግፉ በህብረተሰብ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ ጠላቶቻችን ናቸው ብለን አቅጣጫ አስቀመጥን። በዛ መሰረት የዞንና የወረዳው መዋቅር ማሰርና መግደል ውስጥ ገባ” ብሏል። በዚህም አላበቃም፤ “ለምንድነው የምታስሩት? አውጥታችሁ የምታደርጉትን አድርጉ ይባል ነበር ለበታች መዋቅሩ” ሲል ተናግሯል።
ዶ/ር ሚልኬሳ አንድ ሰሞን ዝነኛ የነበረው ATM (A-አዲሱ፣ T-ታዬ፣ M-ሚልኬሳ) የኦዴፓ ተተኪ ወጣቶች ጥምረት አንዱ ፊትአውራሪ ተደርጎ ይወሰድ የነበረ፣ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲም በፌዴራሊዝም እና ህዝብ አስተዳደር ያስተምር የነበረ ሰው ነው። በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዴት ኦሮሚያን የሚያህል ሰፊና ብዝሃነት ያለው ክልል ብቸኛ ፓርቲ ለመሆን ቁጭ ብለው ተነጋግረው ሊወስኑ እንደሚችሉ ማሰቡ ይዘገንናል።
በአጭሩ፤ ኦሮሚያ ውስጥ ሊኖር የሚገባው አንድ ፓርቲ ብቻ ነው ብሎ ማመን ከተቻለ በኢትዮጵያ ደረጃም እንደዛ ለማመን የሚከለክል ነገር የለም። ብዙ ሰዎች ጭቆናን ሳይሆን ጨቋኙን እንደሚጠሉ፤ እድሉን ሲያገኙም ከተቃወሙት ጨቋኝ በላይ አፋኝ እንደሚሆኑ ነው በተደጋጋሚ እያየን ያለነው። በእርግጥ ሚልኬሳ ውስጥ ሆኖ በብዕር ሥም ይጽፍ እንደነበርና መረጃዎችን በማውጣት የተወሰነ ለውጥ ለማምጣት መሞከሩን ቢገልጽም፣ አብዛኞቹ ጥፋቶች ራሱ በተሳተፈበት መፈጸሙን አልካደም፤ ለማስተባበልም አልሞከረም።
ብቻ በጣም ያናድዳል!

Saturday, 04 September 2021 17:39

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

የምትጮህለት እንጅ፣ የምትጮህበት አይደለም!
                            ጌታቸው ሽፈራው


             አሸባሪው ትህነግ ያኔ ድሮ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ሲመጣ በአደባባይ የታገለ ሰው ነው። የአዲስ አበባ ወጣት ብሶቱን የሚተነፍስለት ሲያጣ ጮህ ብሎ የተናገረለት ታማኝ ነበር። ፖለቲከኛ አልነበረም፣ አርቲስት ለመንግስት በሚያለቀልቅበት ሀገር አርቲስቱ ታማኝ ነው ድምፅ የሆነው፣ ተስፋ የሰጠው። የትህነግ አመራሮችም ባሉበት ሳይቀር ሳይፈራ የሚናገረው ታማኝ በየነ ነበር።
ለዛም ሲባል ወጣቱ “ግባ በለው! ታማኝን ግባ በለው” እያለ ጮኾለታል። ስሜቱን፣ ብሶቱን በደንብ ስለሚገልፅለት ነበር። እውነታውን ስለሚናገርለት ነበር። ታማኝን በገዳዩ በመለስ ለቅሶ ላይ ጥልመት ለብሶ ሲነፋረቅ አላገኘኸውም። ታማኝ ለሕዝብ የተገኘው መለስ ዜናዊ ገና በአፍላው በሙሉ አቅሙ ንፁሃንን ሲገድል ነው።
ታማኝ ለገዳይ አልቃሽ ሆኖ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ድምፅ ሆኖ ነው ያገኘነው። የረባ ሰው ባልነበረበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ተስፋ ባጣችበት ወቅት!
ያ ክፉ ትህነግ ሰሞኑን ታማኝ ሲያጋልጠው ስለኖረ፣ በታማኝ በየነ ቤተሰቦች ላይ ያደረገውን ሰምተናል። ታማኝ ያኔ በወጣትነት እድሜው ትህነግን የተቃወመው ቤተሰቤ ላይ ችግር ያደርሳል ብሎ አይደለም። ሀገሬ ላይ ችግር ያደርሳል ብሎ ነው። ለረዥም ዘመን የተቃወመው፣ ብቻውን በሚባል ሁኔታ ገመናውን ያጋለጠው ለሀገሩ እንጅ ለቤተሰቡ ብሎ አይደለም። በሁለተኛው ወረራም፣ በዚህ ወቅት በፈፀመው ወረራም ታማኝ አሸባሪውን ትህነግ ያወገዘው ለቤተሰቡ ብሎ አይደለም።
ትህነግ ገና ወረራ ሲፈፅም ታማኝ በየነ ተረባርበን ወረራውን መቀልበስ እንዳለብን አስረድቶናል። የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ነግሮናል። በእርግጥ ታማኝ በአሸባሪው ትህነግ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌላው ጉዳይም ከሀገሩ ጉዳይ ተነጥሎ አያውቅም።
ያም ሆኖ ግን እሱ አሸባሪውን ትህነግ ሲቃወም ፖለቲካ የሚባል የማያውቅ፣ አንዳንዱ በሕይወትም ያልነበረ ሳይቀር ሲተቸው አያለሁ። የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ ሆኖ፣ ትህነግ ብዙዎቹን ያኮላሸበትን የሽብር አዋጅ ያስፀደቀው ኤርሚያስ ለገሰ እንኳን ታማኝ ሳያውቅ የወጣን አንድ ባነር አንጠልጥሎ ሲተቸው አይቻለሁ። አለማፈሩ!
አንዳንዶቹ “አማራ አማራ” ካላለ ብለን እንተቸዋለን። የእኛ ሰው የትም ሆኖ እንዲጠቅም እንኳን እድል አንሰጥም። የእኔን ቅላፄ አንተም ድገመው እንላለን። ደብረፅዮን ወይንም ጃል ማሮ “ኢትዮጵያ” ቢል ፕሮፋይል ለማድረግ የምንዘጋጅ ሰዎች፣ ታማኝ ከድሮም የጮኸላትን ሀገር ስም እንዳያነሳ ከፈለግን ችግሩ ከራሳችን ነው። ፌስቡክና ዩቱዩብ ላይ ፖለቲካ የጀመረው ሁሉ ያለ አግባብ ይወቅሰዋል። ታማኝ ግን አሁንም አለ።
ከአቋሙ ሳይዋዥቅ አለ። በእርግጥ አንዳንዴ የሚደርሱ ትችቶች ካለው ተቀባይነት አንፃርና፣ ያደርገዋል ተብሎ ከሚታመነው አንፃር ሊሆን ይችላል። “ይህን ቢልልኝ” ከሚል ነው። ራሳችን ማድረግ ያቃተንን እሱ እንዲያደርግ ከመፈለግ ነው።
ታማኝ በለግላጋ እድሜው ጀምሮ አሁንም ሽበት በሽበት ሆኖ እንቅጭ እንቅጩን እንዲናገርልን እንፈልጋለን። የሳምንት አጀንዳ አስመርሮት ፌስቡኩን ሰግቶ የሚወጣ ትውልድ ታማኝን እድሜ ልክህን ተናገርልኝ ይለዋል። ታማኝ እየተናገረ ነው፣ ወገኑን እያገዘ ነው። ሁሉን እንዲያደርግ፣ ችግር ባለበት ሁሉ እንዲደርስ አትጠብቅ። አንተም የራስህን አድርግ!
ታማኝ ሰው ነው። እድሜውን ሙሉ የታገለ። ከምን መጣ የማይባል አሸን ልፍለፋም ሊያሰላቸው የሚችል ሰው ነው። ያም ሆኖ አሁንም አለ። ከእነ አቋሙ። እኛ የረባ ያልጮህነው “ጩህልን” ስላልነው ሳይሆን ለህሊናው ብሎ ይጮሃል፣ ይረዳል፣ ይታገላል። ያኔ ያወገዘውን ትህነግ፣ ሲያጋልጠው የኖረውን ትህነግ አሁንም እንታገለዋለን እያለ ነው። ይህን የመሰለ ሰው አሁንም “ታማኝን ግባ በለው!” ብለህ የምትጮህለት እንጅ፣ የምትጮህበት አይደለም!Saturday, 04 September 2021 17:40

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 ጎባጣው ትዳሬ
                          በእውቀቱ ስዩም


           በየሳምንቱ ቅዳሜ አንድ መርህ አለኝ፤ ያገርቤትም ሆነ የውጭ አገር ፖለቲካ ዜና እጦማለሁ፤ ኪነጥበብና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እጣድና ነፍሴን አለመልማታለሁ፤ በዚህ መሰረት፥ ቅድም ዩቲዩብ ላይ ስርመሰመስ ቆየሁ፡፡
በቀደም አንድ የሞሮኮ ዜጋ የሆነ ዘፋኝ “ሊጋባው በየነ” የሚለውን ዘፈን በራሱ ቃና ዘፍኖ አስደምሞኝ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ ሸገር ውስጥ በስደተኝነት የሚኖር ሶርያዊ ዘፋኝ “ለዚህ ለዚህማ ምናለኝ አገሬ“ የሚለውን የጌቴ አንላይን ዘፈን ዘፍኖ አስለቀሰኝ::
ወደ ፌስቡክ ተመለስኩ፤ ባለፈው አንዱ “ላጤ” የሚለውን ግሩፕ እንድቀላቀል መጥርያ ልኮልኝ ነበር፤ ያለሁበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመሰለል ፈልጎ ይመስለኛል፤ እኔም ግሩፑን ቀስ ብየ በለሆሳስ እየተራመድኩ ሰለልኩት፤ ፍቅር የተራቡ "ሆርኒ” ወጣቶች የተደራጁበት ቡድን መሆኑን ደረስኩበት፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት ወይዘሮ "በትዳራችን ጉዳይ እንመካከር" የሚል ግሩፕ ላይ እንድሳተፍ መጥርያ ሰደደችልኝ፤ ይሄ ግሩፕ የመጨረሻ ተመቸኝ፤ የመጀመርያም ተመቸኝ። አብዛኞቹ የግሩፑ አባላት፥ የፍቅር ታሪካቸውን ተርከው፤ በትዳራቸው ላይ የገጠማቸውን ችግር ዘርዝረው፥ ካንባቢ ምክርና መፍትሄ ያማትራሉ፤ እንሆ እኔም ተሞክሮየን ለማካፈል ወሰንኩ፥
በውቄ እባላለሁ፤ ከባለቤቴ ጋራ የተገናኘነው ባጋጣሚ ነው፤ በጊዜው እሷ ሚስ ኢትዯጵያ ተብላ በቁንጅና ስትመረጥ እኔ አወዳዳሪው ነበርኩ:: የመጀመርያዎቹ ሀያ አመታት የትዳር ቆይታችን ጎረቤት የሚያስቀና ነበር:: ከቢሮ ስመጣ በደስታ በፈገግታና በውዝዋዜ ትቀበለኛለች፤ ኮቴን አውልቃ ወደ ላውንደሪው አፍ እየጨመረች “ምሳ እስኪደርስ፤ ክትፎ በቆጮ እየቀማመስክ ቆይ" ትለኛለች:: ከምሳ በሁዋላ ሶፋው ሳፋ እሲከመስል ድረስ ፍቅር እንሰራለን፤
ብዙም ሳይቆይ ጸነሰች፤ ከዘጠኝ ወራት ላልበለጠ ጊዜ በርግዝና ቆየች:: ያለ ብዙ ምጥ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ ልጃችንም ያለ ብዙ ለቅሶ ተገረዘ! ልጃችን በተወለደ በአንድ አመቱ ዶንኪቲዩብ ላይ እየቀረበ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ ምክር መለገስ እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ጀመረ:: ሰባት አመት ሲሞላው ካሮጌ ቅጥቅጥ ሚኒባስ ሂሊኮፍተር ሰራ:: አሁን ካዲስ አበባ ብሾፍቱ ራይድ እየሰራበት ይገኛል::
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለቤቴ ጸባይዋ መቀየር ጀመረ:: የገቢ ምንጯና ለኔ ያላት ፍቅር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ ለልደቴ ፍልውሃ ያለውን ፓርክ ገዝታ በስጦታ አበረከተችልኝ::
በዚህ አይነት ሁሉን የሚያስቀና ትዳር ውስጥ እየኖርን እጅግ የሚያሳዝን ነገር ተከሰተ፤ ሄቲ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ ! ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ ተቆጣጠረ፤ ይህ ግን በፍቅራችን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽኖ አልነበረውም::
አንባቢ ሆይ !! ትዳራችን ፈረሰ የሚለውን ለመስማት፥ ምክርና ከንፈር መጠጣ ለማዋጣት ሰፍ ብለህ እየጠበቅህ ነውን? በቃ ሼም የለህም? ለምን የሟርተኞችና የክፉ ታሪክ ናፋቂዎች ግሩፕ አታቋቁምም?


Saturday, 04 September 2021 17:38

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

ኢትዮጵያ ስታራምደው የነበረው ፌዴራሊዝም የሕብረ-ብሔራዊ (Multinational) ፌዴራሊዝምን መስፈርትን ያሟላ አይደለም!
                           ጌታሁን ሔራሞ             መስከረም 24 መንግስት እንደሚመሠረት አፈጉባዔው አቶ ታገሰ ጫፎ ትናንት አስታውቀዋል፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፦
አሁን ያለው ሕገመንግሥት...በተለይም ክልላዊው ኦቶኖሚው... ዜጎችን በሀገራቸው ነባርና መጤ በማለት ለሁለት የከፈለ መሆኑ ይታወቅ!
ሕገ መንግሥቱ በየክልሉ ያሉ አናሳ ብሔሮችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን የማያከብር መሆኑ ይታወቅ...ሁሉም ብሔር ከክልሉ ውጪ አናሳ መሆኑ ይሰመር (የሐረሪ ብሔር በራሱ ክልልም ጭምር አናሳ መሆኑን ሳንዘነጋ)!
ስለዚህም ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች ወረቀት ላይ የተፃፈው የብሔር ብዝሃነት ፅንሰ ሐሳብ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዲደረግ የ”Territorial Autonomy” መርህ መሻሻል እንዳለበት ከወዲሁ ይታወቅ። በሌላ አኳያ አንቀፅ 39 ለሁሉም ክልሎች በሕገ መንግሥት ደረጃ ክልላዊ ኦቶኖሚን መስጠቱ ይታወቅ ...The right for secession is meaningless without territorial autonomy! እናም አንቀፅ 39 ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥ ሁኔታዎች ይመቻቹ!
ከላይ የተዘረዘሩትን ሕገ መንግሥታዊ ግድፈቶችን ጠቅለል ስናደርጋቸው፦ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተለይም በክልሎች ደረጃ ሁሌም የሚለፈፍለትን የብሔር “Diversity”ን የሚያስከብር አይደለም፣
ስለዚህም ፦
ኢትዮጵያ እስከ አሁን ስታራምደው የነበረው ፌዴራላዊ አወቃቀር ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አይደለም። በየክልሉ ያሉ የአናሳ ብሔሮችን የዜግነትን መብት በሚቃረን መልኩ ከፖለቲካ ውክልና (በተለይም ከምርጫ ፖለቲካ) እና ከኢኮኖሚ (ከክልሉ ባለቤትነት) እያገለሉና እየነጠሉ “ፌዴራሊዝሙ ሕብረ-ብሔራዊ ነው” ማለት ቀልድ ነው። ይህን ማጠቃለያ የሚጠራጠር ካለ፣ በሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝምም ሆነ በ”Multiculturalism” ፅንሰሐሳቦች ዙሪያ የካናዳዊውን ዊል ኪሚልካ፣ የእንግሊዛዊዉን “Bhikhu Parekh”ን እና የሲንጋፖራዊቷን የ”Terry-Anne Teo”ን መፅሐፍት ያገላብጥ! በነገራችን ላይ ሕንድ ውስጥ ካሉት በሺህዎች ከሚቆጠሩ ብሔሮች መካከል በዋናነት የሦስትና የአራት ያህል አናሳ ብሔሮች መብት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ የሕንድ ፌዴራሊዝም ሕብረ-ብሔራዊ አይደለም ብለው የሚሞግቱ ምሁራን አሉ። እኛ ሀገር በየክልሉ ያልተከበረው የሁሉም ብሔሮች (80+) የዜግነት መብቶች ናቸው።

የአየርላንድ ህዝብ ብዛት ከ170 አመታት በኋላ ከ5 ሚሊዮን አልፏል

            በአለማችን ከሚገኙ የዛፍ ዝርያዎች 33 በመቶ ያህሉ ወይም 17,500 የዛፍ ዝርያዎች ከምድረ ገጽ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት አስጠንቅቋል፡፡
ቦታኒክ ጋርደንስ ኮንሰርቬሽን ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ ዛፎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ አእዋፍት እና አጥቢዎችን ጨምሮ ህልውናቸው አደጋ ላይ የወደቁ እንስሳት ዝርያዎችን ቁጥር አሳድጎታል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው የዛፍ ዝርያዎች ለመጥፋት የተቃረቡባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ብራዚል ናት ያለው ጥናቱ፣ በአገሪቱ 1 ሺህ 788 የዛፍ ዝርያዎች ለመጥፋት መቃረባቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የአየርላንድ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከ170 አመታት በኋላ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5 ሚሊዮን ማለፉን የአገሪቱ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዩፒአይ አስነብቧል፡፡
ቢሮው ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአየርላንድ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ 5.01 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የህዝብ ቁጥሩ ከ5 ሚሊዮን ሲያልፍ እ.ኤ.አ ከ1851 ወዲህ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡

Page 12 of 555