Administrator

Administrator

• የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት እንዲያቀርብ በምእመናኑና በሰንበት ት/ቤቱ ተጠይቋል
• የታገደው የቅ/ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት ለማቅረብ የፓትርያርኩን አመራር ጠየቀ


በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ አስተዳዳሪ፣ ስለ ደብሩ የአስተዳደርና የገንዘብ አያያዝ ችግር በአዲስ አድማስ የወጣው ዘገባ፤ “በማስረጃ ተደግፎ ያልቀረበ የስም ማጥፋት አስተያየት ነው” ሲሉ አስተባበሉ፡፡
አስተዳዳሪው መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ኃይለ ማርያም፣ “በአዲስ አበባ: ሰበካ ጉባኤያት በአስተዳደር ሓላፊዎች መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኗል” በሚል ርእስ በተጠናቀረው ዘገባ፤ ስለ ደብሩ የተነሡት ጉዳዮች “ማንነታቸውን ባላወቅናቸው ግለሰቦች የቀረቡ ናቸው” በማለት  ዘገባውን ተቃውመዋል፡፡
በዘገባው፣ አስተዳዳሪው የሰበካ ጉባኤውን ውሳኔ አይተገብሩም የተባለው፣ “በግልጽ ተዘርዝሮ ያልቀረበና ፍጹም ሐሰት ነው፤” ያሉት አስተዳዳሪው፤ “በሰበካ ጉባኤው ተወስኖ ተግባራዊ ያልሆነ ምንም ዐይነት ውሳኔ የለም፤” ብለዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤውን ምክትል ሊቀ መንበር ጨምሮ ሌሎችም አባላት፣ አንሠራም በማለታቸው በፈቃዳቸው ሓላፊነታቸውን የለቀቁና በደብዳቤም ቢጠሩ ለመምጣት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንጂ አስተዳደሩ አንዳቸውንም እንዳላገደ ገልጸዋል፡፡
ደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ከመፈረም ውጭ፣ በቃለ ዐዋዲው በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት በውሳኔ ሰጪነት የማይሳተፉት÷ የደብሩን ገቢና ወጪ አጥብቀው በመቆጣጠራቸው፤ የሒሳብ ሪፖርትም በመጠየቃቸው ሳቢያ እንደሆነ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተካሔደ ማጣራት እንደተረጋገጠ የቀረበው ዘገባ “ሐሰት ነው” ያሉት አስተዳዳሪው፤ ስለጉዳዩ ለበላይ አካል ሪፖርት አቅርበው የሚሰጠውን ውሳኔና መመሪያ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የአስተዳዳሪውን አልታዘዝ ባይነት በመግለጽ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤትም ለሀገረ ስብከቱ አስተላልፎታል በሚል የቀረበውን ሪፖርትም በተመለከተ፤ “የደብሩ ጽ/ቤት የማያውቀው ነገር እንደሆነ” ገልፀዋል፡፡
የደብሩ የገቢና ወጪ ሒሳብ በዘመናዊ መልክ እንደሚሠራ በመጥቀስ የአሠራሩን ትክክለኛነት የገለፁት አስተዳዳሪው፣ የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ሒሳብ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተላኩ ኦዲተሮች ተመርምሮ ያለምንም ጉድለት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡ ሪፖርቱም በደብሩ መዝገብ የሚቀመጥ በመሆኑ የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ ጠይቀው የመረዳት መብት አላቸው፤ ብለዋል፡፡ በማንኛውም ደብር ስም የሚከፈት የባንክ ሒሳብ የሚከፈተው በሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር እንደሆነና የሚንቀሳቀሰውም በአስተዳዳሪውና በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር እንደሆነ ያስረዱት አስተዳዳሪው፣ ሳይፈቀድ እንደተፈለገ የሚንቀሳቀስ አልያም የሚወጣና የሚገባ ገንዘብ የለም፤ በሚል ይህንኑ ያስረዳልኛል ያሉትን ማስረጃ አቅርበዋል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ የሚገባው የሃያ በመቶ ድርሻ ፈሰስ ሳይደረግ፣ ደብሩ ለዕዳ ተዳርጓል መባሉን በተመለከተ አስተዳዳሪው በሰጡት ምላሽ፤ እርሳቸው ተመድበው ከመምጣቸው በፊት የብር 900‚000 ውዝፍ እንደነበረበትና ከተመደቡበት ካለፈው ዓመት መጋቢት 1 ቀን ጀምሮ ግን እንዲከፈል በማድረግ “ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትመሰገን አደረግሁ እንጂ ለዕዳ ዳርገዋታል መባሉ ሐሰት ነው፤” ብለዋል፡፡
“ካህናት ፍቅርን የሚሰብኩ የሰላም አባቶች እንደሆኑና ቤተ ክርስቲያኒቱም ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ልጆቿ ተሰባስበው በአንድነት የሚያገለግሉባት ነች፤” ያሉት አስተዳዳሪው፣ በተወላጅነት የተከፋፈለ አንድም ካህንና ሠራተኛ እንደሌለ በመጥቀስ፣ የሰበካ ጉባኤው አባላት በአስተዳደር ሠራተኞች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማኅበረ ካህናቱን በተወላጅነት ይከፋፍላሉ መባሉን አስተባብለዋል፡፡ ካህናትና ሠራተኞች ከደመወዝና ከሥራ እንዳልታገዱና ያጠፋ ቢኖር እንኳ በማገድ ሳይሆን በቃለ ዐዋዲው መሠረት፣ በቃል ምክርና በማስጠንቀቂያ የገንዘብ ቅጣት ሊቀጣ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡  
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የበላይ አካል ሳያውቀው ቅጥርም ሆነ ዝውውር ተደርጎ አያውቅም፤ ያሉት አስተዳዳሪው፣ ያለአግባብ የሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር እንደሚፈጽሙ በዘገባው የቀረበው፣ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ ውድቅ ሊሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፤ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ሠራተኛ እንዳስፈላጊነቱ ከአንድ አጥቢያ ወደ ሌላ እየተዘዋወሩ የመሥራት ግዴታ ያለባቸው በመሆኑም ቅሬታው ይህንኑ ደንብና መመሪያ በጥልቀት ያልተረዳ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
አስተዳዳሪው የቤተ ክርስቲያንን መሬት ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ከሓላፊነታቸው ታግደው እንደነበር የተጠቀሰውን በተመለከተ፣ መልካም ስማቸውንና ዝናቸውን ለመጉዳት ሆነ ተብሎ የተሰነዘረባቸው “ፍጹም ሐሰትና አሳዛኝ ውንጀላ ነው” ሲሉ ተከላክለዋል፡፡ አለቃው ከሓላፊነታቸው ታግደው እንደነበር በማስተባበያቸው ቢያምኑም፤ በፍርድ ወንጀለኛ ተብለው ያልተቀጡበት እንደሆነና እገዳውም ሥልጣኑ በማይመለከተውና ደረጃው በማይፈቅድለት ሓላፊ የተላለፈ እንደነበር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መንፈሳዊ ፍ/ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. መረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡ ይኸው ውሳኔ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ታኅሣሥ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርቦ ያልተከፈላቸው ደመወዛቸው ተከፍሏቸው ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ እንደተወሰነላቸውም በመጥቀስ ክሡ፣ “ፈጽሜ በማላውቀውና ባልተደረገ” የቀረበብኝ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ከበርካታ አድባራት ሲቀርቡ በቆዩ አቤቱታዎች መነሻነት በአዲስ አድማስ በተጠናቀረው ዘገባ የተካተተው የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ፤ የሰበካ ጉባኤው አባላትና ምእመናን ለሀገረ ስብከቱ ባቀረቧቸው የጽሑፍ አቤቱታዎችና የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሀ/ስብከቱ ትእዛዝ አጣርቶ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ከሥራ ውጭ ኾኖ ባለበት በአሁኑ ወቅት አስተዳዳሪው፣ ያለሰበካ ጉባኤው ፈቃድ በሰበካ ጉባኤው ስምና ማኅተም የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣትና ሌሎች ደብዳቤዎችንም በመጻፍ አግባብነት የሌለው ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ይናገራሉ፡፡ ስለ ደብሩ ወቅታዊ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት እሑድ መወያየታቸውን ጠቅሰው፣ የሰበካ ጉባኤውና የአስተዳደር ጽ/ቤቱ በነገው ዕለት የሥራ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸው የሚጠይቅ ከ500 በላይ ፊርማ አሰባስበው ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የፓትርያርኩ መቀመጫ በሆነችው የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት በአስተዳደር ሓላፊዎች የታገደው ሰበካ ጉባኤ፣ ለመረጠው የማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ፣ እንደ ቃለ ዐዋዲው ደንብ የሥራ ሪፖርቱን ማቅረብ እንዲችል ፓትርያርኩ አመራር ይሰጡለት ዘንድ ጠይቋል፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም በደንቡ ድንጋጌዎች መሠረት ርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል፡፡
በገዳሙ ያለውን ዘረፋ በማስቆም ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ አሠራሮችን እንዲዘረጋ ከፓትርያርኩ በተቀበለው ትእዛዝ፣ መተዳደርያ ደንብና መመሪያዎችን አዘጋጅቶ በከፊል ወደ ሥራ ቢገባም አዎንታዊ እገዛም ሆነ አመራር አለማግኘቱን ጠቅሷል፡፡ ጉዳዩን በየጊዜው በተለያዩ መንገዶች ለፓትርያርኩ ሲያሳውቅ ቢቆይም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለችግር የዳረጓትን ኃይሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው እንዳለ በመጥቀስ “እናቱን በገጀራ የገደለ ጎራዴ ተሸለመ” በሚል ተችቷል፡፡
 “ሙስናን እንታገላለን፤ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን” በሚል ፓትርያርኩ በየመድረኩ የገቧቸው ቃሎች በተግባር ካልተተረጎሙም የማዘናጊያ መፈክር ከመሆን ስለማያልፉ፣ መልካም አስተዳደርን በተግባር ወደሚያሰፍን ርምጃ እንዲገባ ጠይቋል፤ በዚህ በኩልም ተስፋ ባለመቁረጥ ከፓትርያርኩ ጎን እንደሚቆምም የታገደው ሰበካ ጉባኤ ዝግጁነቱን አረጋግጧል፡፡   

የታዋቂው የቴሌቪዥን ሾው አቅራቢ ሠይፉ ፋንታሁን እና የባለቤቱ ወ/ሮ ቬሮኒካ ኑረዲን የሠርግ መልስ ስነስርአት በነገው ዕለት በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ይከናወናል፡፡ ሙሽሮቹ የመልስ ስነስርአቱን ከ550 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ  ህሙማን ጋር ከቀኑ 7 ሰአት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል ተብሏል፡፡ ባለፈው ጳጉሜ 1 ሰርጉን በሸራተን አዲስ በደማቅ ስነስርአት የፈፀመው ሰይፉ፤ለሠርጉ ሊያውለው አቅዶት የነበረውን 300ሺህ ብር ለመቄዶኒያና ለሙዳይ በጐ አድራጐት ድርጅት መለገሱ ይታወቃል፡፡ በመልሱ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና ከ5ሺህ በላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡  በሥነሥርዓቱ ላይ የመቄዶንያ አረጋውያን፤ ሙሽሮችን የሚመርቁ ሲሆን  ሙሽሮቹም ከነሚዜዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን እንዲሁም አልጋ ላይ የዋሉ ህሙማንን ይጐበኛሉ ተብሏል፡፡ ለአረጋውያን ስጦታ የመስጠትና ጋቢ የማልበስ ፕሮግራም እንደሚኖር ያመለከተው ማዕከሉ፤ አረጋውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ ግጥሞችና መነባንቦችን ያቀርባሉ ብሏል፡፡   
በማዕከሉ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሰዎች የሠርግ፣ የቀለበት፣ የልደት፣ የምረቃ ስነስርአት እንዲሁም የሙት አመት መታሰቢያዎች የማከናወን ልምድ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መንግስት በነፃ ባበረከተለት 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሰጪ ማዕከል ለመገንባትና የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 3ሺህ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ማዕከሉን ለመገንባትም 300 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መነገሩ ይታወሳል፡፡ 

  • ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ፣ የደመራ በዓልን በመስቀል ዐደባባይ ያከብራሉ
  • አክሱም ጽዮንን፣ ጎንደርን፣ ላሊበላንና የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ይጎበኛሉ


  የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶች፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ ተገለጸ፡፡
በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ከሚመራው ልኡክ ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የሚካሔደው ምክክር፤ የኹለቱን አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል ወደ ከፍተኛ መተማመን እንዲያመራ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡
በክርስትናው አስተምህሮ ባላቸው የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት፣ “እኅትማማች” የሚባሉት ኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጋራ ተልእኮዎቻቸውን በአንድነት በመፈጸም ጥንታዊውንና ታሪካዊውን ግንኙነታቸውን ለማዳበር የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት ጥር ባደረጉት የግብጽ ይፋዊ ጉብኝታቸው ወቅት ጠይቀዋል፡፡
የግብጹ አቻቸው ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም ጥያቄውን በመቀበል፤ በሃይማኖታዊ፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አብሮ የሚሠራና በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ኮሚቴ ለመሰየም ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀው እንደነበር ተወስቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈለገ ግዮን ተብሎ የሚታወቀውና ኹለቱ አገሮች በጋራ የሚጠቀሙበት ተፈጥሯዊው የዓባይ ውኃ የማኅበራዊ ትስስሩ መሠረት ሲኾን በዝግ በሚካሔደው የኹለቱ ቅዱሳት ሲኖዶሳት ምክክርም ዐቢይ ትኩረት እንደሚያገኝ ተጠቁሟል፡፡
የዓባይ ውኃን በመተማመን ከተጠቀሙበት ከኹለቱ አገሮች አልፎ ለመላው አፍሪካ የሚበቃ የአምላክ በረከት እንደኾነ ለግብጽ ባለሥልጣናት የተናገሩት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚኾኑት የእግዚአብሔር ጸጋ በኾነው በዓባይ ነው፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ደግሞ ሰው ሊለያየው አይችልም፤” ያሉ ሲኾን ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም፤ “እኛ የግብጽ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ አንድ ብርጭቆ ውኃ በጠጣን ቁጥር ኢትዮጵያን እናስታውሳታለን፤” ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በወቅቱ ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በ2008 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ እንዲገኙ ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው ግብዣ፣ ትላንት ሌሊቱን ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሃይማኖት አባቶች ልኡክ በማስከተል ዐዲስ አበባ የገቡ ሲኾን ከዛሬ ጀምሮ የአምስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡  ለጉብኝቱ የወጣው መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው ፓትርያርኩ፣ ትላንትና መስከረም 14 ቀን ሌሊት 9፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የፕሮቶኮል ባለድርሻ አካላት አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመንበረ ፓትርያርኩና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ የእንኳን ደኅና መጡ ፕሮግራም ይደረግላቸዋል፤ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም ይወያያሉ ተብሏል፡፡
ጠዋት በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተገኝተው ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራት፣ ሥርዐተ ቅዳሴውን የሚያከናውኑ ሲኾን ከቀትር በኋላም በመስቀል ዐደባባይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር የመስቀል ደመራ በዓልን ያከብራሉ፡፡
ከመስከረም 17 - 19 ቀን የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያምን፣ የጎንደርን፣ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ታሪካዊ ስፍራዎችን፣ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን እንዲኹም በአዲስ አበባ የሰበታ ጌቴሰማኔ ቤተ ደናግል ወጠባባት ገዳምንና የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመጎብኘት ጸሎት እንደሚያደርጉና እንደሚባርኩ ታውቋል፡፡ በግብፅና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ትብብር እንደ ድልድይ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ በ1951 ዓ.ም እስከሾመችበት ጊዜ ድረስ ለ1600 ዓመታት ከግብጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሾሙ ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች፡፡ በሀገራቱ መንግሥታት ምክክር ጭምር የመንበሩ ነጻነት ከተገኘም በኋላ የሚካሄዱ ፕትርክናዊ ጉብኝቶች ለውጭ ግንኙነታቸው መጠናከር አስተዋፀኦ እንዳለው ይታመናል፡፡

     ባለፈው ማክሰኞ 80ኛ የልደት በዓላቸውን ያከበሩት አንጋፋው ክላርኔት ተጫዋች መርአዊ ስጦት ተሸለሙ በዳኒ ሮጎ የማስታወቂያ ስራና ፊልም ፕሮዳክሽን ድርጅት አስተባባሪነት በሃርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው አርቲስቱን የማክበርና የማመስገን ስነ - ስርዓት ላይ ልጃቸው ኢትዮጵያ መርአዊ ላለፉት 60 ዓመታት የተጫወቱበትን ክላርኔት ያበረከተችላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርም ክብራቸውን የሚገልፅ የምስጋና የምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው ተገልጿል፡፡ በእለቱ አቶ አብነት ገብረመስቀል የ50 ሺህ ብር ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን የጃዝ አምባዎቹ ያሬድ ተፈራ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ግሩም መዝሙር፣ ሳምሶን ጃፋር፣ ፋሲል ዊሂር እና አክሊሉ ዘውዴ ለአርቲስቱ ክብር እያንዳንዳቸው ሙዚቃ ተጫውተውላቸዋል፡፡ አርቲስት ጌትነት እንየው፣ ፍቃዱ ተክለማርያምና ሙዚቀኛው ግርማ ይፍራሸዋም በየግላቸው ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን ጌትነት እንየው “ድንቅ” የተሰኘ ግጥም እንደገጠመላቸውም የዳኒ ሮጎ ስራ አስኪያጅ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ተናግሯል፡፡
 አቶ አብነት ገ/መስቀል አርቲስቱን እስከመጨረሻው ለመደገፍ ቃል የገቡ ሲሆን የላንድ ማርክ ሆስፒታል ባለቤት ፕ/ር ከበደ ወሌም በማንኛውም ሁኔታ ለህክምና ሲመጡ ሆስፒታላቸው በነፃ እንደሚያክማቸው ቃል ገብቷል፡፡ ቲሞኒየር ልብስ ስፌትም በእለቱ ሙሉ ልብሳቸውን በማልበስ ለአርቲስቱ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ 

ሳምሰንግ ምርቶቼ በስፋት መቸብቸባቸውን ይቀጥላሉ ብሏል

      በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚዎቹ ተፎካካሪዎች ሆነው ለአመታት የዘለቁት ሳምሰንግ እና አይፎን፣ ፉክክራቸው ከገበያ አልፎ ችሎት የደረሰ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባላንጣዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
“ሳምሰንግ የራሱን ፈጠራ እንደመስራት የእኔን እያየ ይኮርጃል” በሚል ሲማረርና ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ለመሰረተው ክስ፣ ተገቢ ውሳኔ የሚያገኝባትን ዕለት ለአመታት በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው አይፎን ከሰሞኑ በለስ ቀንቶታል፡፡
በዋሽንግተን የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተሰየመው ችሎት፣ “ከአሁን በኋላ ከአይፎን እያየህ መኮረጅህን እንድታቆም፤ ከዚህ በፊት የኮረጅካቸውን ሶፍትዌሮችም ዛሬ ነገ ሳትል መጠቀም እንድታቆም” ሲል ለሳምሰንግ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል - ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡
ሳምሰንግ በበኩሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በምርቶቹ ተወዳጅነት ላይ ይህ ነው የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር ገልጾ፣ ጋላክሲ በሚል መጠሪያ የሚያመርታቸው ስማርት ፎኖቹ በቀጣይም በአለም ዙሪያ በስፋት መቸብቸባቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
አይፎን ፈጠራዎቼን እየኮረጀ አስቸግሮኛል በሚል በሳምሰንግ ላይ ክስ የመሰረተው ከ3 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ወቅቱ ሳምሰንግ ኩባንያ ጋላክሲ ኤስ 2 የተሰኘውን ስማርት ፎን ለገበያ ያበቃበት እንደነበርና ከዚያ በኋላም፣ በዚህ አመት ለገበያ ያበቃውን ጋላክሲ ኤስ 6 ጨምሮ የተለያዩ አይነት የተሻሻሉ የጋላክሲ ምርቶቹን ማውጣቱን ጠቁሟል፡፡
አይፎን ክሱን የመሰረተው በጋላክሲ ኤስ 2 ላይ ሲሆን፣ ክሱ ሳምሰንግ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያመረታቸውን ስማርት ፎኖች የማይመለከት በመሆኑ የፍርድ ቤቱ  ውሳኔ ለአይፎን ያን ያህልም ተጠቃሚ እንደማያደርገው ተዘግቧል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በፈጠራ ባለቤትነት ጉዳይ መካሰስ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው የታወቀ ሲሆን በቅርቡም “ሳምሰንግ ከአይፎን ኮርጀሃል” በሚል 980 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበት እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

 መንግስት በበኩሉ፣ ከ700 ሚ ዶላር በላይ በመዝረፍ ከሷቸዋል
   ሩስያዊው ቢሊየነር ሰርጊ ፑጋቼቭ፣ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን እና ታማኞቻቸው በህገወጥ መንገድ በሸረቡብኝ ሴራ ግዙፉን የባንክ ኩባንያዬን ለኪሳራና ለውድቀት ዳርገውታል፣ የአገሪቱ መንግስት 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከታዋቂ የአገሪቱ ባንኮች አንዱ የነበረው ሜዝፕሮም ባንክ ድንገት ተንኮታኩቶ የወደቀባቸውና በባንኩ ዘርፍ ከሚታወቁ የአገሪቱ ባለጸጎች አንዱ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሰርጊ ፑጋቼቭ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንና ታማኞቻቸው ዋና ዋናዎቹን ንብረቶቼን ነጥቀው ኩባንያዬን ለውድቀት ዳርገውታል ሲሉ፣ ባለፈው ሰኞ ዘ ሄግ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ላይ ክስ መመስረታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የሩስያ መንግስት በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ2008 ተከስቶ የነበረውን የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ ሜዝፕሮም የተባለውን የግለሰቡን ባንክ ለመደጎም በማሰብ የመደበውን ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል፣ በስደት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙት ሰርጊ ፑጋቼቭ ላይ ክስ መመስረቱንና ግለሰቡ ተላልፈው እንዲሰጡት የእንግሊዝን መንግስት እንደጠየቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እያጣራ ባለበት ሁኔታ ላይ በመሃል ቢሊየነሩ ከእንግሊዝ መውጣታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሩስያን መንግስት ክስ ተከትሎ የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ የአለም አገራት ውስጥ የሚገኙና 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ የሰርጊ ፑጋቼቭ ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያዘዘ ሲሆን ቢሊየነሩ ግን ከሩስያ የተሰነዘረባቸውን ክስ፣ መሰረተ ቢስና ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ውንጀላ ነው ሲሉ ማጣጣላቸው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን እንዲወጡ በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ቢሊየነሩ ፑጋቼቭ፣ ከእንግሊዝ ከወጡ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሳይሄዱ እንዳልቀሩ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 ወታደራዊው ሃይል ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባካሄደው መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱትና በግዞት የቆዩት የቡርኪና ፋሶው የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ረቡዕ ዕለት ወደ ስልጣናቸው መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ወደስልጣናቸው መመለሳቸውን ይፋ ያደረጉት፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪና ለአንድ ሳምንት በስልጣን ላይ የቆዩት የአገሪቱ መሪ  ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬ የስልጣን ሽግግሩን ለመታዘብ ወደ አገሪቱ በመግባት ላይ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ለመቀበል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ባመሩበት ወቅት ነው ብሏል ዘገባው፡፡
የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮአስ በሽግግር መንግስቱና በወታደራዊው ሃይል መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ያስችላል በሚል ባቀረበው የድርድር ሃሳብ መሰረት፣ አገሪቱ ወደ ብጥብጥ እንዳትገባ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከቤተ መንግስቱ እንዲርቁ መደረጋቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኮፋንዶ ወደ ስልጣናቸው እንደተመለሱ ማወጃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡በወታደራዊው ሃይልና መፈንቅለ መንግስቱን በተቃወሙ የአገሪቱ ዜጎች መካከል በተነሳው ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎችም መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ከስልጣናቸው የወረዱትን የቀድሞውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬን ተክቶ መንበረ መንግስቱን የተረከበው የቡርኪና ፋሶ የሽግግር መንግስት፣ በመጪው ጥቅምት ወር በሚደረግ ምርጫ ስልጣኑን ለማስረከብ እቅድ እንደነበረውም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

    13.50 ዶላር የነበረው መድሃኒት፣ 750 ዶላር ገብቷል
    
   ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ዜጎች በሚወስዱት መድሃኒት ላይ የ5,000% የዋጋ ጭማሪ ያደረገው የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ኩባንያ፣ ከታማሚዎች፣ ከመብት ተሟጋች ቡድኖች፣ ከህክምና ማህበራት፣ ከፖለቲከኞችና ከማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመውና ዋጋውን ለመቀነስ ማሰቡን እንደገለፀው ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ፤ ዳራፕሪም በመባል የሚታወቀውን የመድሃኒት ምርቱን የመሸጫ ዋጋ ከ13.50 ዶላር ወደ 750 ዶላር ማሳደጉን ማስታወቁን ተከትሎ ከታማሚዎችና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚም የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ማሰባቸውን እንደተናገሩ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ያስነሳውን ተቃውሞ ለማጣጣል የሞከሩት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርቲን ሸክሬሊ፣ ተቃውሞውን የሚሰነዝሩት ስለ መድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪው አካሄድ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ናቸው፤ የዋጋ ጭማሪውን አድርገን የምናገኘውን ተጨማሪ ገንዘብ ሌሎች መድሃኒቶችን ለመፍጠር ለምናደርገው ምርምር ለማዋል ነበር ያሰብነው ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ማርቲን ሸክሬሊ በትዊተር ገጻቸው ላይ የተሰነዘረባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው ኩባንያቸው በቅርቡ ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ቅናሽ እንደሚደርግ ቢናገሩም፣ ምን ያህል የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ እንደታሰበ በግልጽ አላሳወቁም፡፡
ኩባንያው ዳራፕሪም የተባለውንና የቶክሶፕላዝሞሲስ የፓራሳይት ኢንፌክሽንን በማከም ረገድ ፍቱን የሆነውን መድሃኒት አምርቶ የመሸጥ ፍቃድ ያገኘው በቅርቡ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ በሽታዎች የተጠቁና በሽታን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ታማሚዎች መድሃኒቱን በስፋት እንደሚወስዱ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ፣ በአሁኑ ወቅት በአገረ አሜሪካ አይንህን ለአፈር በመባልና በመጠላት ረገድ፣ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረገውን ኩባንያ የሚመሩት የ32 አመቱ ማርቲን ሸክሬሊ ቱሪንግ፣ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

    በስኳር በሽታ ሳቢያ የተጐዱ የልብ የደም ቱቦዎችና የሰውነታችን ውስጣዊ አካላቶች የአበባ ጐመን በመመገብ በፍጥነት እንዲጠገኑ ማድረግ እንደሚቻል በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ገለፁ፡፡
 በአሜሪካ ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባሉ ምሁራን የተደረገና በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ በአበባ ጐመን ውስጥ የሚገኘውና ሰልፎራፔን የተሰኘው ንጥረ ነገር የደም ቱቦዎችን የሚጠብቁ ኢንዛይሞች በብዛት እንዲመረቱ ያደርጋል፡፡ ይህም በሴሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሞሎኪውሎች ቁጥር እንዲቀነስ እንደሚያደርግ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡ ከስኳር በሽታ ጋር ግንኙነት ያለውና Hyperglycemia በመባል የሚጠራው ከፍተኛ የጉሉኮስ መጠን በደም ስሮች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በአበባ ጐመን ውስጥ የሚገኘው ሰልፎራፔን የተባለው ኢንዛይም እንደሚጠግነው መረጋገጡንም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ የስኳር ህሙማን ከጤናማዎቹ በአምስት እጥፍ ለልብ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ የስኳር ህመም በልብ ደም ስሮች ላይ በሚያስከትለው ጉዳት ሳቢያ ስትሮክና የልብ ድካም ይከሰታል፡፡

ለጤናዎ 10 ጠቃሚ ምግቦች
ፈረሰኛ ለስኳር ህሙማን ይመከራል
የምንመገባቸውን ምግቦች በማስተካከል ጤናችን የተጠበቀ ማድረግ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ቀጥሎ የተዘረዘሩት 10 የምግብ ዓይነቶች ሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅሙን እንዲጨምር በማድረግ፣ ጤናማና ደስተኛ ህይወት ለመምራት እንደሚያስችለን Changeone.com ከተሰኘው ድረ ገፅ ያገኘነው መረጀ ያመለክታል፡፡ እነዚህ ለጤናዎ ጠቃሚ የሆኑ አስር የምግብ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
አሣ - ከእንስሳት የሚገኘውን ሥጋ የሚተካውና ጥሩ የፕሮቲን ምንጭ የሆነው አሣ Omega 3 ለተባለው ፋቲአሲድ ዋንኛ ምንጭ በመሆንም ይታወቃል፡፡ እነዚህ ፋቲአሲዶች የደም ቅዳዎቻችን ንፁህ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ አሣ በተለይ ለስኳር ህሙማን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የምግብ አይነት ነው፡፡ የስኳር በሽተኞች አብዛኛውን ጊዜ (HDL) የተሰኘው ጠቃሚ ኮሌስትሮል እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ Omega 3 ይህንን የኮሌስትሮል እጥረት በማስተካከል ይታወቃል፡፡
በሣምንት ቢያንስ ሁለት ቀን አሣን መመገብ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሳልመን፣ ማካፌል እና ቱና የተባሉት የአሣ ዓይነቶች የፋቲ አሲዱ ዋንኛ መገኛዎች ናቸው፡፡
የዶሮ ስጋ
ፈረሰኛ የምንለው የዶሮ ብልት፤ ለስኳር ህሙማን እጅግ በጣም ተመራጭና ጠቃሚ የምግብ አይነት ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ፈረሰኛን “ተአምረኛው ምግብ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ፈረሰኛ የሥጋ ምግቦች ከያዙት የስብና የኮሌስትሮል መጠን በእጅጉ ያነሰ ነው የያዘው፡፡ በ85 ግራም ፈረሰኛ ውስጥ 142 ካሎሪና 3 ግራም ስብ ብቻ ይገኛል፡፡
እርጐ
እርጐ በፕሮቲንና ክብደትን ለመቀነስ በሚረዳው ካልሲየም በተባለው ንጥረ ነገር የዳበረ ነው፡፡ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በካልሲየም የዳበሩ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች በቀላሉ ክብደታቸውን ለመቀነስ ይችላሉ፡፡ ደስተኛና ጤናማ ህይወት እንዲኖርዎ የእርጐ ወዳጅ ይሁኑ፡፡ ቁርስዎን ቅባት የሌለው እርጐ በመውሰድ ይጀምሩ፡፡
አትክልቶች
አትክልቶች በተፈጥሮአቸው ዝቅተኛ ካሎሪ ነው ያላቸው፡፡ በፋይበር (አስር) የበለፀጉም ናቸው፡፡ የምግብ ገበታዎን ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው ንጥረ ነገሮች በዳበሩት አትክልቶች ሞሉት ማለት የደም ስኳር መጠንዎን ተቆጣጠሩ ማለት ነው፡፡
ፍራፍሬ
ፍራፍሬዎች የከፍተኛ ፋይበር ምንጭ ሲሆኑ ዝቅተኛ ስብና ዝቅተኛ ካሎሪን በመያዝም ይታወቃሉ፡፡ ፍራፍሬዎች ልባችንን፣ ዓይናችንንና ጥርሶቻችንን ከበሽታ በሚከላከሉ አንቲኦክሲደንቶች የበለፀጉ ናቸው፡፡ ፍራፍሬዎችን ከጭማቂው ይልቅ እንዳለ መመገብን ይምረጡ፡፡ በርካታ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች በፍሬው ላይ ስለሚገኙና እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች በሚጨመቅበት ወቅት ስለሚጠፉ ፍሬውን እንዳለ መመገቡ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ፍራፍሬዎች በተፈጥሮ ስኳርና ካሎሪ የበለፀጉ በመሆኑ በብዛት ከመመገብ መታቀብ ይኖርብናል፡፡
ለውዝ
ለውዝ የቫይታሚን E ዋንኛው ምንጭ ነው፡፡ ይህ ቫይታሚን በውስጡ የያዘው አንቲኦክሲደንት ሴሎችን በመጠበቅ የነርቭና የአይን ጉዳት እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡ ለውዝ በበርካታ ጠቃሚ የስብ አይነቶች የተሞላ የምግብ አይነት ነው፡፡ እነዚህ ስቦች የልብ በሽታን በመከላከልና ኢንሱሊን ያለመቀበል ሂደትን በመቀነስም ይታወቃሉ፡፡ የደም ውስጥ የስኳር መጠንንም ለመቆጣጠር ያስችላሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ለውዝን አዘውትሮ መመገብ ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ የስኳር ህመምተኛ ከሆኑ ግን ለውዝን አዘውትረው አይመገቡ፡፡
ቀረፋ
በምግብዎ ውስጥ ቀረፋን ጣል የሚያደርጉ ከሆነ፣ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ የደምዎ የስኳር መጠን ቀንሶ ያገኙታል፡፡ በቀረፋ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጉታል፡፡ በስኳር ህሙማን ላይ የተደረገ ጥናት፤ ግማሽ ማንኪያ ቀረፋ በየዕለቱ የሚወስዱ ሰዎች የደም የስኳር መጠናቸው በአስገራሚ ሁኔታ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ የቀረፋን ዱቄት በዳቦ ወይንም በሌሎች ምግቦችዎ ውስጥ በመጨመር ይመገቡ፡፡ እንጨቱንም በሻይ መልክ እያፈሉ በመጠጣት ጤናዎን ይጠብቁ፡፡
ጥራጥሬ
የጥራጥሬ ምግቦች በፋይበር የበለፀጉ ናቸው፡፡ አዘውትረው ቢመገቧቸው ጤናዎን ለመጠበቅ በእጅጉ ይጠቅምዎታል፡፡
የወይራ ዘይት
የወይራ ዘይት በልብ በሽታ የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል፡፡ የደም የስኳር መጠንን ያረጋጋል፡፡ ምግብዎን በወይራ ዘይት አብስሎ ሲመገቡ ራስዎን ከተለያዩ በሽታዎች ይታደጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የስኳር ታማሚ ከሆኑ፣ የወይራ ዘይትን አዘውትረው ከመመገብ ይቆጠቡ፡፡  

በአገራችን ከአምስት ህሙማን አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል
የሃኪሙን የእጅ ፅሁፍ ማንበብ የሚያዳግታቸው ፋርማሲስቶች በዝተዋል

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተደረገለት ሙሉ ምርመራ የጉበት ህመምተኛ መሆኑ ሲነገረው ድንጋጤው ልክ አልነበረውም፡፡ ህመሙ ዕለት ከዕለት እየተባባሰበት በመሄዱ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሄዶ ምርመራ ለማድረግ ሲወስን፣ ሃኪሙ ህመሙን አውቆለት ፈዋሽ መድሃኒት እንደሚያዝለት፣ ከበሽታውም እንደሚያገግም ጽኑ እምነት ነበረው፡፡
ከሃኪሙ የተፃፈለትን የመድሃኒት ማዘዣ ይዞ መድሃኒቱን ፍለጋ ወጣ፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ በርካታ መድሃኒት ቤቶችን ቢያስስም መድሃኒቱን ማግኘት አልቻለም፡፡ ቆይቶ ግን መድሃኒቱ በአንድ ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ ሰማ፡፡ ለመድሃኒቱ የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ገዛ፡፡ ችግሩ ግን ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ ፋርማሲስቱ የነገረው ነገር አልነበረም፡፡ የገዛውን መድሃኒት ይዞ ወዳዘዘለት ሃኪም ሄደ፡፡ ሃኪሙ ዘንድ ቀርቦ መድሃኒቱን በብዙ ፍለጋ ማግኘቱን በመግለጽ፣ ስለአወሳሰዱ እንዲነግረው ጠየቀው፡፡ ሃኪሙ በጣም ተገርሞ፤
“ለመሆኑ መድሃኒቱ የተገዛው ከፋርማሲ ውስጥ ነው?” ጠየቀው
“አዎ” አለ ታካሚው፡፡
“ታዲያ እንዴት ፋርሚሲስቱ ስለአወሳሰዱ ሳይነግርህ ቀረ?” በማለት መድሃኒቱን ከነማዘዣው ከህመምተኛው ላይ ተቀብሎ አየው፡፡ ታካሚው በሃኪሙ ፊት ላይ ያየው ከፍተኛ ድንጋጤ እሱኑ ይበልጥ አስደነገጠው፡፡
“ችግር አለ?” ሲል ጠየቀው ሃኪሙን
“እርግጠኛ ነህ እኔ ላዘዝኩልህ የተሰጠህ መድሃኒት ይሄ ነው?” ሲል ጠየቀው ታማሚውን፡፡
“ጌታዬ 486 ብር የከፈልኩበት መድሃኒት እኮ ነው እንዴት ብዬ ከሌላ መድሃኒት ጋር እቀላቅለዋለሁ”
ለዚህ መድሃኒት መግዣ ያወጣውን 486 ብር ለማግኘት የተጋፈጠውን ውጣ ውረድ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ሃኪሙ በጣም አዘነ፡፡
ታካሚው ከፋርማሲ ገዝቶ ያመጣው መድሃኒት፤ ለማህፀን ህክምና የሚያገለግልና ለሴቶች ብቻ የሚታዘዝ ነበር፡፡ ሁኔታው እጅግ ቢያስደነግጠውም ለመድሃኒቱ ያወጣው ገንዘብ ኪሣራ ላይ ሊወድቅ መሆኑ ይበልጥ አበሳጨው፡፡ ወደ ፋርማሲው ሄዶ ስለጉዳዩ በመንገር፣ ገንዘቡን እንዲመልሱለት ለማድረግ መድሃኒቱን ተቀብሎ ወደዚያው አመራ፡፡ ፋርማሲው ውስጥ ላገኘው ሰውም ሁኔታውን አስረዳ፡፡ በወቅቱ የተገኘው ባለሙያ፤ ከሰውየው ላይ መድሃኒቱን ተቀብሎ አየው፡፡ ምናልባት የፋርማሲ ባለሙያው በስህተት ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል ነግሮ፣ በማዘዣው ላይ የተፃፈውን መድሃኒት ሊሰጠው እንደሚችል አግባባው፡፡ ይሁን እንጂ ይህኛውም ሰው በመድሃኒት ማዘዣው ላይ የተፃፈውን ጽሑፍ በአግባቡ በማንበብ ተገቢውን መድሃኒት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይልቁንም “መድሃኒቱ እኛ ጋ የለም ሲል” ማዘዣውንና ታማሚው ቀደም ሲል የከፈለውን 486 ብር መልሶ በመስጠት አሰናበተው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ይህንን መረጃ ያገኘሁት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለህክምና መጥቶ ካገኘሁት አንድ ታካሚ ነው፡፡ ታካሚው ከሃኪሙ የተፃፈለትን መድሃኒት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የመድሃኒት መሸጫ ፋርማሲ ለማግኘት ባለመቻሉ ነበር መድሃኒቱን ፍለጋ ከተማውን ሲያስስ የከረመው፤ ይሁን እንጂ በአብዛኛው መድሃኒት ቤቶች ውስጥ መድሃኒቱን ለማግኘት አልቻለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከበሽታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝና ምናልባትም ለከፋ ችግር ሊያጋልጠው የሚችል መድሃኒት ባለሙያ ነኝ ብሎ ከተቀመጠ የመድሃኒት ቤት ሰራተኛ መሰጠቱ ነው፡
ወደ ሆስፒታሉ ተመልሶ የመጣው ሃኪሙ መድሃኒቱን በሌላ መድሃኒት ቀይሮ እንዲፅፍለት ለመጠየቅ መሆኑን አጫውቶኛል፡፡ ለፍለጋው በተዘዋወረባቸው በርካታ መድሃኒት ቤቶች ውስጥ ያገኛቸው የፋርማሲ ባለሙያዎች፤ በማዘዣው ላይ የተፃፈው የሃኪሙ የእጅ ጽሑፍ ፈጽሞ የማይነበብ መሆኑንም ነግረውታል፡፡ ስለዚህም ሃኪሙ ሊነበብ በሚችል መልኩ ማዘዣውን እንዲፅፍለት እንደሚጠይቀውም ገልፆልኛል፡፡
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ለፋርማሲ ሙያ በሰጠው ትርጓሜ፤ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት፣ ከሃኪም በሚሰጠው ትዕዛዝና መመሪያ መሠረት፣ መድሃኒቶችን ለህሙማን ማደል፣ ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ፣ መድሃኒቱ ስለሚኖረው የጐንዮሽ ጉዳትና ከመድሃኒቱ ጋር ሊወሰዱና ላይወሰዱ ስለሚችሉ ምግብና መጠጦች በግልጽ ለህመምተኛው የሚያሳውቅ ሰው ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያው መድሃኒቶችን ለህሙማን ከማደል በዘለለ ከህሙማኑ ጋር ጥብቅ መግባባትን ማድረግ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ባለሙያው ሁልጊዜም ከህመምተኛው ጀርባ ሆኖ ስለህመምተኛው የሚጨነቅና የሚያስብ ሰው ነው፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ት/ቤት መምህር ዶክተር ተስፋዬ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ “የፋርማሲ ሙያ እንደ ህክምና ሙያ ሁሉ ትልቅ ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባና በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎች ከህክምና ባለሙያዎች ጋር ጥብቅ ትስስር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት ከሃኪሙ በሚሰጠው ማዘዣ መሠረት ታማሚው መድሃኒቱን በአግባቡ መውሰድ እንዲችል ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍ ሙያተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የሚታየው ነገር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ታካሚው መድሃኒት ፍለጋ በሚሄድባቸው ፋርማሲዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ሙያውን በሚገባ ያውቁታል ለማለት ፈፅሞ አያስደፍርም፡፡ አንዳንድ ፋርማሲስቶች፤ የመድሃኒት ማዘዣዎች አልነበብ ሲላቸው፣ በደንበኞች ፊት ሃኪሞችን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሳደቡና ሲያዋርዱ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ለሙያው የሚሰጠውን ግምት በእጅጉ የሚያወርድና በሃኪሙና በህመምተኛው መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመድሃኒት ማዘዣዎችን በሚገባ አንብቦና ተረድቶ መድሃኒቶችን ለህሙማን የሚያድል የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘቱ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው”
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሃኪም መድሃኒት ከታዘዘላቸው ታካሚዎች ከአምስቱ አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል፡፡ ሃኪሞችን የፋርማሲ ባለሙያዎችን፣ ነርሶችንና ህሙማንን ያካተተው ጥናቱ፤ በመድሃኒት አስተዛዘዝ ዙሪያ ከባድ ችግር እየተከሰተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች የሚጽፉት የመድሃኒት ማዘዣ የማይነበብና የተሟላ መረጃ የሌለው ሲሆን የሃኪሙን የእጅ ጽሑፍ በሚገባ አንብቦና ተረድቶ ተገቢውን መድሃኒት ለህመመተኛው የሚሰጥ የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ህሙማኑም ስለታዘዘላቸው መድሃኒት አወሳሰድ ሃኪማቸውን አይጠይቁም፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎቹም፤ ለህሙማኑ መድሃኒቱን ሲሰጡ ስለአወሳሰዱ፣ ስለመድሃኒቱ ባህሪያትና ስለጐንዮሽ ጉዳቱ አይናገሩም፡፡
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ህመምተኛው ስለሚወስደው መድሃኒት ምንነትና አወሳሰድ ሳያውቅ በስህተት መድሃኒቶችን ለመውሰድ መገደዱን ነው፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተው፤ ብዙውን ጊዜ ህሙማን መድሃኒት ፍለጋ ከፋርማሲ ፋርማሲ የሚንከራተቱት መድሃኒቱ በፋርማሲው ሳይገኝ ቀርቶ ሳይሆን የፋርማሲ ባለሙያው ማዘዣውን አንብቦ መረዳት ባለመቻሉ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ሁሉም ሙያተኞች የሙያውን ሥነምግባር አክብረው፣ ተገቢውን ህክምናና መድሃኒት ለህመምተኛው መስጠት እንዳለባቸው ይኸው ጥናት ይገልፃል፡፡
በሰለጠነው ዓለም የመድሃኒት ማዘዣዎች በዲጂታል ማሽኖች እየተተኩ ነው፡፡
ልክ እንደ ባንክ ኤቲኤም ማሽን፣ በደንበኞቹ በቀረበለት የመድሃኒት ማዘዣ መሠረት ትክክለኛውን መድሃኒት አውጥቶ ከነአወሳሰድ መመሪያው ለህሙማኑ መስጠት የሚችል መሣሪያ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
መድሃኒቶች ከበሽታ በመፈወስ ነፍስን የመታደጋቸውን ያህል በአግባቡ ካልተያዙና አገልግሎት ላይ ካልዋሉ አጥፊ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ስለዚህ ለህይወት ደህንነት የተሰራልን መድሃኒት አጥፊያችን እንዳይሆን፣ እራሳችንን ጨምሮ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡