Administrator

Administrator

ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ስራዎቹን ለአለም ያበረከተው ጀርመናዊ የሙዚቃ ሊቅ ሉድዊንግ ቫን ቤትሆቨን ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፉ ምርጥ ስራዎቹን የቀመረው፣ የልብ ምቱን መነሻ በማድረግ እንደሆነ በሙዚቃዎቹ ዙሪያ የተሰራ አንድ ጥናት ማስታወቁን ሃፊንግተን ፖስት ዘገበ፡፡ሰሞኑን የወጣው የዋሽንግተንና የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ጥናት እንዳለው፣ በአብዛኞቹ ተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎቹ ውስጥ የሚደመጡት ያልተለመዱ ምቶች ቤትሆቨንን ለሞት እንዳበቃው የሚገመተው ካርዲያክ አሪዝሚያ የተባለ የልብ ህመም ከሚፈጥረው የልብ ምት መዛባት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ በጋራ ያሰሩትና የልብ ህክምና ዶክተሮች፣ የህክምና ታሪክ አጥኝዎችና የሙዚቃ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ይህ ጥናት፣ በቤትሆቨን የልብ ጤንነትና በሙዚቃዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ጥልቅ ፍተሻ እንዳደረገ ተነግሯል፡፡
ቤትሆቨን መስማት የተሳነው መሆኑ፣ ለልብ ምቱ ትኩረት የሚሰጥበትን ዕድል እንደፈጠረለትና፣ የልብ ምቱ በሙዚቃ ስራዎቹ ላይ ተጽዕኖ ሳይፈጥርበት እንዳልቀረ ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በሁለት ፈረንሳውያን ሙስሊም ወንድማማቾች ፓሪስ ውስጥ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በአውሮፓ በተለይም በፈረንሳይና በጀርመን የሚኖሩ አናሳ ሙስሊሞች ጫና በርክቶባቸው ውጥረት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ከትላንት በስቲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን የምዕራቡን አለም “እስላማዊነት” በመቃወም አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የነገርየው አያያዝ አላምራቸው ያለ ሙስሊሞችም የገባቸውን ስጋት ለመግለጽ በፊናቸው አደባባይ በመውጣት አቤት ብለዋል፡
ጉዳዩ መገረምን የፈጠረባቸው እጅግ በርካታ ሰዎች ታዲያ አውሮፓውያን አብረዋቸው በሚኖሩት ሙስሊሞች ይህን ያህል ስጋት የገባቸው ቁጥራቸው ምን ያህል ቢሆን ነው የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡
በአውሮፓ የሚገኙ ሙስሊሞች ቁጥር ከተቀሩት ጋር ሲወዳደር አናሳ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በፈረንሳይና በጀርመን አተካራው ያየለበት ዋነኛው ምክንያት ሌላ ሳይሆን በምዕራብ አውሮፓ ከሚገኙት ሙስሊሞች አብዛኞቹ የሚገኙት በሁለቱ አገራት በመሆኑ ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት ብቻ 4.7 ሚሊዮን ሙስሊሞች ይኖራሉ፡፡
63 ሚሊዮን ከሚሆኑት ፈረንሳውያን ውስጥ 7.5 በመቶ የሚሆኑት ሙስሊም ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ በምዕራብ አውሮፓ ከፍተኛው ነው፡፡ 82 ሚሊዮን ከሚሆኑት ጀርመናውያን መካከል ደግሞ የሙስሊሞቹ ቁጥር 5.8 በመቶ ነው፡፡ በፈረንሳይ ከሚኖሩት ሙስሊሞች እጅግ አብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ ተወላጆች ሲሆኑ በጀርመን ከሚገኙት ሙስሊሞች ውስጥ ደግሞ እጅግ የሚበዙት ትውልዳቸውን ከቱርክ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡
በእንግሊዝ 2.7 ሚሊዮን ሙስሊሞች ይኖራሉ፡፡ ይህም ከጠቅላላው የእንግሊዝ ህዝብ 4.8 በመቶ የሚሆነውን ይወክላል፡፡ ከነዚህ ሙስሊሞች ውስጥ በጣም የሚበዙት የዘር ሀረጋቸውን የሚመዙት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከነበሩት ፓኪስታንና ናይጄሪያ ነው፡፡
በምዕራብ አውሮፓ ከሚኖሩት ሙስሊሞች ውስጥ በብዛት አራተኛ ደረጃ የያዙት መኖሪያቸውን ያደረጉት ጣሊያን ነው፡፡ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ሙስሊሞች ከጠቅላላው የጣሊያን ህዝብ ብዛት 3.7 በመቶ የሚሆነውን ይወክላሉ፡፡

በሳኡዲ አረቢያ አንድን ውሻ በከፍተኛ ሁኔታ አሰቃይተው ገድለዋል በሚል ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሁለት ወጣቶች የ5 አመት እስር ወይም የ500 ሺህ የሳኡዲ ሪያል መቀጣታቸውን አረብ ኒውስ ዘገበ፡፡
ወጣቶቹ ከሳምንታት በፊት ውሻውን በከፍተኛ ሁኔታ ሲደበድቡና ሲያሰቃዩ ቆይተው ለሞት እንደዳረጉት የሚያሳየውና በአንደኛው ወጣት ሞባይል የተቀረጸው አስር ደቂቃ ያህል የሚረዝም የቪዲዮ ፊልም በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፣ ድርጊቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስ ወንጀለኞቹን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል፡፡
ፖሊስ ወንጀለኞቹ መኪና እያሽከረከሩ ውሻውን በመሬት ላይ በመጎተት ሲያሰቃዩት እንደነበር በሚያሳየው በዚህ ቪዲዮ ላይ የታየውን የመኪናዋን ታርጋ ቁጥር በመመዝገብ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተከታትሎ በሪያድ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
የአገሪቱ የግብርና ሚኒስትር ጃቢር አል ሸሪ፤ ወጣቶቹ በውሻው ላይ የማሰቃየት ወንጀል መፈጸማቸው በመረጋገጡ፣ በአገሪቱ ህግ እና የባህረ ሰላጤው አገራት ባወጡት እንስሳትን የማሰቃየት ወንጀል ህግ መሰረት፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣት እንደተጣለባቸው አስታውቀዋል፡፡

በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ የደረሰውን የቃጠሎ አደጋ ለመታደግ በተደረገው ርብርብ ላይ ተሳታፊ ለነበሩ አካላት “ምስጋና” የሚቀርብበት ምስጋና የተሰኘ ልዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ ተከፈተ፡፡ ከጥር 14 እስከ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ይቆያል በተባለው በዚሁ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ሰዓሊያን የስዕል ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ ከስዕል ኤግዚቢሽኑ በተጨማሪ ልዩ የሰርከስ፣ የሙዚቃ ትርኢትና ሥነ ግጥሞች የሚቀርቡ ሲሆን ለህፃናት የታሪክ ነገራ እና የስዕል ስራዎች ስልጠናም እንደሚሰጥ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሀጎሽ ፕሮግራሙን መርቀው በከፈቱበት  ወቅት እንደተናገሩት፤ ታሪካዊውንና ጥንታዊውን ሆቴል ከቃጠሎው አደጋ ለመታደግና የህዝብ ሀብት የሆነውን ሆቴል  ለማዳን ህብረተሰቡ ያደረገውን ተጋድሎ እናደንቃለን ብለዋል፡፡ ሆቴሉ በቋሚነት የቀድሞ ይዘቱንና ታሪካዊነቱን በጠበቀ መንገድ እንዲታደስ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንና ሆቴሉን ከፀሐይና ከዝናብ ለመከላከል የሚያስችል ጊዜያዊ ጥገናው በሆቴል አስተዳደሩ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

በድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰና በአቶ አዲስ ገሰሰ የተሰራው የታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ የቦብ ማርሌ ሐውልት ከሁለት ወር በኋላ በሚደረግ ታላቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚቆም አዘጋጆቹ ገለፁ፡
ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ ሐውልቱ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ በተሰየመውና ገርጂ ኤምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የቦብ ማርሌ አደባባይ ላይ ለማቆም ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም የዳግማይ ትንሳኤ ዕለት በሚደረገው ታላቅ ኮንሰርትና የሀውልት ማቆም ሥነ-ስርዓት ላይ ሪታ ማርሌን ጨምሮ የቦብ ማርሌ ሁለት ልጆች እንደሚገኙና ልጆቹ በኮንሰርቱ ላይ እንደሚዘፍኑ ተገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ሃውልቱ በሚከበረው የቦብ ማርሌ የልደት በዓል ወቅት እንዲቆም ታስቦ የነበረ መሆኑን የተናገረው ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ የቦብ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል በጃማይካ ኪንግስተን ከተማ እንዲከበር በመወሰኑና የቦብ ቤተሰቦችም ለበዓሉ ወደ ስፍራው በማምራታቸው ፕሮግራሙ ተሰርዞ ለዳግማይ ትንሳኤ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የቦብማርሌ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ድምፃዊው ጨምሮ ገልጿል፡፡  

በእውነት ፊልም ፕሮዳክሽን የተሰራውና በወንድወሰን ይሁብ ተደርሶ በእውነት አሳሳህኝና በደራሲው የተዘጋጀው “የገጠር ልጅ” የተሰኘው ፊልም ነገ ከቀኑ 11፡30 በብሔራዊ ቲያትር በሚካሄድ ሥነ ስርአት ይመረቃል፡፡ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ወደ አረብ አገር በስደት ሄዳ ወደ ሀገሯ የተመለሰች አንዲት ወጣት የሚደርስባትንና የሚያጋጥማትን አሳዛኝ የህይወት ፈተና የሚያሳየው ልብ አንጠልጣይ ፊልም ሙሉ ቀረፃው የተካሄደው በአዲስ አበባ ከተማና ሰንዳፋ አካባቢ መሆኑን የፊልሙ ፕሮዲዩሰሮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በፊልሙ ላይ ተሻለ ወርቁንና ሰለሞን ሙሔን ጨምሮ ከ90 በላይ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን የተሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በደራሲ ቃልኪዳን ኃይሉ የተፃፈውና “ለምን አትቆጣም?” የተባለው አዲስ መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታውቋል፡፡

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ ከተማ “ዋን ስቶፕ ሲኒማ” የተሰኘ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ባለፈው ሳምንት ተመርቆ አገልግሎት ጀመረ፡፡ ሲኒማ ቤቱ በ1.7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን ለከተማዋና ለአካባቢው ነዋሪዎች አማራጭ የመዝናኛ ማዕከል ይሆናልም ተብሏል፡፡ ሲኒማ ቤቱ እስከ 500 የሚደርሱ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡ በከተማው ከንቲባ አቶ ዘገዬ ካሳ የዛሬ ሳምንት ተመርቆ የተከፈተው ዋን ስቶፕ ሲኒማ፤ ለአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት የድርጅቱ ባለቤት አቶ ዘላለም ተመስገን ተናግረዋል፡፡

Saturday, 24 January 2015 13:27

ሞኝ እንደነገሩት

ሞኝ እንደነገሩት
“ፍቅር ያሸንፋል” ስትለኝ አምኜህ
በጦርነት ሁሉ ልሰለፍ አብሬህ
ደብተሬን ቀድጄ
አድርቄ ወጥሬ ጋሻ ሰርቼበት
ብዕሬን ፈልፍዬ ጦር አስቀርጬበት
ጠላትን ወግቼ
ለፍቅር ደምቼ…
ካቀረቀርኩበት ቀና ብል የለህም
ያሸንፋል ባልከኝ አንተ አልተሸነፍክም
እኔ ነኝ ብቻዬን ፍልሚያውን አውጄ
ጦሬን አበጅቼ
እኔው ተማርኬ ራሴን የሰጠሁ
ሙሉው ጦርነቴን
ሙሉ መሸነፌን
ሙሉ መሰጠቴን
ያንተ ድርሻ ቢኖር ልቤን የሰወረው
“ፍቅር ያሸንፋል” ማለትህ ብቻ ነው፡፡
    (ከብሩክታዊት ጐሳዬ “ፆመኛ ፍቅር”
    የተሰኘ የግጥም መድበል የተወሰደ)

Saturday, 24 January 2015 13:24

ፀሎቴ

እንዳላዝን … እንዳልባባ
ለኔ ሲሉ፡- እያነቡ
የኔን ዕንባ
 እኔኑ
በኔው፡- ዕንባ
እያሉኝ እሹሩሩ … እሹሩሩ
ለኔ ሲሉ ፡- ሁልዜም እንደኖሩ
እስከዛሬም .. የሚኖሩ  
ነበሩ፡፡
እንዳላዝን … አባብለውኝ
እንዳልስቅም ፡- አዝነውልኝ
ከርቱዕ አንደበታቸው
ዕንባዬ ፈሶ ከዕንባቸው
ለኔ ብለው
እውነት ለኔ ብለው
የኔን ቁስል ቆስለውልኝ
የኔን ህልም ታመውልኝ፣ ታመውልኝ፡፡
ሞቴንም እንዳይሞቱልኝ
ፀሎት ላይ ነኝ
ለኔ ሲሉ፡- ያልሆኑትን እንዳይሆኑልኝ
(1994 ዲላ)