Administrator

Administrator

Monday, 31 August 2015 09:11

የግጥም ጥግ

አረማሞ
ተደባልቆ በቃይ
ሲናር አረማም
ሲዘራ ካልዘሩ
ምርጥ ዘር አክሞ
ገለባ ነው ትርፉ
ቀን ቆጥሮ ለከርሞ፡፡
ሙግት
ያኮረፈ ሌሊት
…መንጋቱን የረሳ
ውስጤ እያደመጠ
…የነፍሴን ጠባሳ
እርምጃ ውልክፍክፍ
…ጉዞውም የአንካሳ
የጨለማ ሙግት
…የንጋት ወቀሳ፡፡
ጀንበሩ ወልደዮሐንስ
(ከኒዮርክ ቡፋሎ)
* * *
“አንተ” - ማለት!...
“አንተ” ማለት፡-
ብዙ ነህ!
ብዙ - ብዙ! … የብዙ - ብዙ!
“አንተ” ማለት ….
አገር ነህ፣
አገር ከነጉዝጓዙ፡፡…
ያገር ጉዝጓዙ…
አቤትና አቤት … አቤት! ብዛቱ፡…
ጂባው፣ አጐዛው - ጀንዴው - ቁርበቱ፡፡…
ተራራው - ሸለቆው - ዱሩ፣
እንኮይ - መስኩ፣
መብሰክሰኩ…፤
እሾህ አሜኬላው - ቆንጥሩ…
ባንድ ሌማት
እሬት!
ምሬት!
የአጋም ፍሬው --- ጣዝማ ማሩ፣
ደግሞም፡-
አድባር! አውጋር! … ያለ መጣፍ፣
አማኝ - እምነት
በመጣፍም
ያለ መጣፍ፡፡…
መቼም - ሰው “አገር ነውና”
አገርም “ሰብዓ ምርቱ”
ታሪክ - ቋንቋ - ባህል - ቀኖናውና
- ትውፊቱ፣
እሱ ነው! የማንነትህ እትብቱ፡፡…
ከእኒህ - መነቀል…
ማለት፡-
ከሥር - መመንገል!
ካናት - መቃጠል!
ከእግር - መመንቀል!
ማለት ነው፣
አገር እንደ ሰው!!
ሰማህ!?
(ወንድዬ ዓሊ)

   መርዛማ የሃሞት ፈሳሾች በጉበታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉና የጉበት ሴሎችን ቀስ በቀስ ወደ ቲሹዎች በመቀየር ከጥቅም ውጪ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ተጠቆመ፡፡
በሔድልበርና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተደረገውና በቅርቡ ይፋ የሆነው አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ሃሞት የጉበት ሴሎች ጋር እንዳይደርስ የሚከላከሉት አካላት ሲጠፉና መርዛማ የሃሞት ፈሳሾች የጉበት ሴሎች ጋር ደርሰው ጉዳት ሲያስከትሉ ጉበት Cirrhosis (ኪሮሲስ) ተብሎ ለሚጠራው የጉበት በሽታ ይጋለጣል፡፡ ይህ በሽታ ደግሞ ጉበታችን ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን እንቅፋት በመሆንና ሴሎቹን ወደ ቲሹዎች በመቀየር ጉበትን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ለዚህ ችግር መነሻ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ በጥናቱ ላይ ከተገለፁት መካከልም የጉበት ቫይረሶች፣ ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ፣ መድሃኒቶችና ልዩ ልዩ ኬሚካሎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡

ቴትራሳይክሊን፣ የደም ብዛትና የካንሰር ህመም መድሃኒቶች የጉበት ስብ በሽታን ሊያስከትሉ ይችላሉ

  ጉበት መርዛማ ንጥረ ነገሮች በደም አማካኝነት ወደተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ ዘልቀው ገብተው ጤናችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ብርቱ ተጋድሎ የሚያደርግ የሰውነታችን ክፍል ነው፡፡ በምንመገባቸው ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ለተለያዩ በሽታዎች ማከሚያነት በምንወስዳቸው መድሃኒቶች ውስጥ የሚገኙና ለሰውነታችን አላስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ሁሉ በጉበት አማካኝነት እየተመረጡ እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡ ቀይ የደም ሴሎቻችን የአገልግሎት ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ የሚወገዱትም በዚሁ በጉበታችን አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጉበታችን ፋቲ አሲድ፣ ፕሮቲን፣ ጉሉኮስንና በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮችን እያመረተ ለሰውነታችን ክፍሎች እንደዳረሱ ያደርጋል፡፡ የዚህ የሰውነታችን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሰጪ የሆነው የሰውነታችን ክፍል በህመም መጠቃት በሰውነታችን ሥርዓተ ዑደት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖን ያሳድራል፡፡
ጉበትን በእጅጉ በመጉዳት ከሚታወቁ ነገሮች መካከል አልኮል ዋንኛው ነው፡፡ በአልኮል ሳቢያ የሚከሰተው የጉበት ስብ በሽታ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሃኪም የሆኑት ዶ/ር አብርሀም ባየልኝ እንደሚናገሩት አልኮል አመጣሽ በሆነው የጉበት ስብ በሽታ የተጠቁ ሰዎች አምስት አመት በህይወት የመቆየታቸው እድል 50በመቶ % ብቻ ነው፡፡ በሽታው የጉበትን የመሥራት አቅም በፍጥነት የሚያዳክምና ከአገልግሎት ውጪ የሚያደርግ በመሆኑ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ለህልፈት የመዳረጋቸው እድል ከፍተኛ ነው፡፡ በሽታው ምንም አይነት ምልክቶችን ሳያሳይ ሊቆይ እንደሚችል የሚገልፁት ሃኪሙ፤ ከ75% በላይ የሚሆኑት የጉበት ስብ ህሙማን በበሽታው የመያዛቸውን ምልክት የሚያሳዩት ጉበታቸው የመጨረሻ ደጃ ላይ ሲደርስና ውሃ መያዝ ሲያቅተው ነው ይላሉ፡፡ የበሽታው ስርጭት በአገራችን እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም፤ በተለይ እድሜያቸው ከአርባ ዓመት በላይ የሆኑና አልኮል አዘውታሪ ሰዎች በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነና ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ህፃናትም ለበሽታው ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የጉበት ጤና በማቃወስ ከሚታወቁት ነገሮች መካከል አንዱና ዋንኛው በሆነው ስብ የተጠቃ ጉበት ለጉበት ስብ በሽታ የሚጋለጥ ሲሆን ይህም በሁለት ምክንያቶች የሚከሰትና ጉበትን ወደ ቃጫነት በመለወጥ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡ የጉበት ስብ በሽታ ከሚከሰትባቸው ሁለት ምክንያቶች መካከል አንደኛው የአልኮል መጠጥ ሲሆን ሌላው ከአልኮል ውጪ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ማለትም ለተለያዩ በሽታዎች ማከሚያነት የምንወስዳቸው መድሃኒቶች እንዲሁም የስኳር በሽታ፣ ውፍረት፣ ጉሉኮስ የማከማቸት ችግርና ኮፐርና ዚንክ የተባሉ ማእድናትን በሰውነት ውስጥ ማከማቸት… ለጉበት ስብ በሽታ መነሻ ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ የአልኮል መጠጦች በጉበት ስብ በሽታ ለመጠቃት 40በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ሃኪሙ ገልፀዋል፡፡
የአልኮል መጠጦች ለጉበት ስብ በሽታ መነሻ የሚሆኑባቸውን መንገዶች ሃኪሙ ሲያብራሩ “የአልኮል መጠጦችን በምንጠጣበት ጊዜ በአልኮሉ ውስጥ የሚገኙና ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ ቅሪቱ ንጥረ ነገር በጉበታችን ውስጥ ያልፋል፡፡ በዚህ ጊዜም የጉበታችን ሴሎች ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ጉበታችን በአግባቡ ሥራውን እንዳያከናውን ያደርገዋል፡፡ ጉበታችን ስራውን በአግባቡ ማከናወን ሲሳነው ወደ ሰውነታችን የገቡትና በጉበታችን አማካኝነት መጣራት የሚገባቸው ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ ዝም ብለው ይከማቻሉ፡፡ በዚህ ጊዜም ጉበታችን ከመጠን በላይ በሆኑ ስቦች እንዲጨናነቅ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የጉበታችንን ሴሎች ወደ ቃጫነት በመቀየር ጉበታችን ፋትን ማመንጨትና መጠቀም እንዳይችል እንዲሁም ውሃ መያዝም እንዲያቅተው ያደርገዋል፡፡ ጉበት ሲታመም ፈሳሽ የመቋጠር አቅሙን ያጣል፡፡ ይህም ፈሳሽ በሆዳችን ውስጥ እንዲጠራቀም በማድረግ ሆዳችንን ያሳብጠዋል፡፡ መጣራት ሲኖርባቸው ሳይጣሩ ቀርተው በሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀሙት መርዛማ ንጥረ ነገሮችም በደም አማካኝነት ወደ ጭንቅላታችን ውስጥ ገብተው ሩሃችን ያስቱናል፡፡ በተጨማሪም ፕሮቲን ጉሉኮስ፣ ፋትና በሽታን የሚከላከሉ ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ መመረታቸው፣ መከማቸታቸውና በጥቅም ላይ መዋላቸው ያቆማል ብለዋል፡፡
ከአልኮል ውጭ የጉበት ስብ በሽታን ከሚያስከትሉ ነገሮች መካከል የሚጠቀሰው ለተለያዩ ህመሞች የምንወስዳቸው የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸው መድሃኒቶች ናቸው፡፡ በተለይ ቴትራሳይክሊን፣ የደም ብዛት መድሃኒቶች፣ ለካንሰር ህሙማን የሚታዘዙ መድሃኒቶችና ሆርሞኖች በዋናነት እንደሚጠቀሱም ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር መድሃኒቶች ተደራርበው እንዳይወሰዱ ለማድረግ የሚመከረው በመድሃኒቶች ሳቢያ የሚከሰቱ የጐንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ በማሰብ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የጉበት ስብ በሽታ ምንም አይነት ምልክቶችን ሳያሳይ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በአብዛኛው የችግሩ መኖር የሚታወቀው ጉበቱ ከጥቅም ውጪ ከሆነና ለመዳን እጅግ አስቸጋሪ ከሚሆንበት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ የጉበት ስብ በሽታ ህሙማን የእግር ማበጥ፣ የአይን ቢጫ መሆን፣ በቀኝ ጐን በኩል የህመም ስሜቶች መኖር ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡ በሽታው ስር ያልሰደደ ከሆነና ጉበቱ ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጪ ከመሆኑ በፊት ከተደረሰበት በተለያዩ ቫይታሚኖችና መድሃኒቶች በሽታውን አክሞ ማዳን እንደሚቻል ጠቁመው ከጥቅም ውጪ ለሆነ ጉበት የሚሰጥ ህክምና በአገራችን ደረጃ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
አልኮልን አዘውትሮ አለመጠጣት፣ መድሃኒቶችን አብዝቶ አለመጠቀም፣ በአመጋገብ ላይ ጥንቃቄ ማድረግና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጉበት ስብ በሽታን ለመከላከል እንደሚረዱ ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል፡፡

     ከተቋቋመ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረውና ልዩ ልዩ የህክምና ምርመራ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው ውዳሴ ዲያግኖስቲክስ ማዕከል፤ 500 ለሚሆኑና የመክፈል አቅም ለሌላቸው ህሙማን ነፃ የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራ አገልግሎት ሊሰጥ ነው፡፡ማዕከሉ “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መርህ በየአመቱ ነፃ የምርመራ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ዘንድሮም ከመንግሥት የህክምና ተቋማት ለሚመጡና አገልግሎቱን በክፍያ ለማግኘት አቅም ለሌላቸው ህሙማን ነፃ የሲቲስካንና የMRI ምርመራ እንደሚያደርግ የማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ ከመንግሥት የጤና ተቋማት የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች እንደሚያስፈልጋቸው በሃኪም የተፃፈላቸው ህሙማን ከነሐሴ 22 ጀምሮ በስልክ ቁጥሮች 0111574343 ወይም በሞባይል ቁጥር 0940040404 ደውለው በመመዝገብ፣ ወረፋ መያዝና የነፃ ምርመራው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ በጳጉሜ ተመሳሳይ የነፃ ምርመራ አገልግሎቶችን እየሰጠ ሲሆን ባለፈው ዓመት ለ500 ሰዎች ነፃ የሲቲስካንና ኤምአር አይ ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ፣ ለ820 ሰዎች ነፃ አገልግሎቱን እንደሰጠ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሶስት ሺህ ብር ክፍያን እንደሚጠይቅ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሐምሌ 18 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው  የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዕትም ላይ ዮሐንስ የተባሉ ፀሐፊ፣ በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ፓወር አፍሪካ ኢንሼቲቭ አካል በሆነው በኩርቤቲ የሚገነባው የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫን አስመልክተው የፕሮጀክቱን አክሳሪነት፤ “የኦባማ ስጦታ ለኢትዮጵያ፡ የ 40 ቢሊዮን ብር ኪሳራ!!” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት አስተያየት ለመግለጽ ሞክረዋል። በርግጥ አቶ ዮሐንስ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ኪሳራ ብለው የመደቡት ገንዘብ በየትኛው ስሌት እንዳስቀመጡት የሚያሳይ አሳማኝ መረጃ ባያቀርቡም፣ ስለ ፕሮጀክቱ ያላቸውን ስጋት በደፈናው ያስቀመጡበትን ሁኔታ ለመገንዘብ አዳጋች አይደለም፡፡ ነገር ግን ፀሐፊው መለስ ብለው የፓወር አፍሪካ ኢንሼቲቭ አላማን ለመረዳት ቢሞክሩ መልካም ነበረ በማለት የግል አስተያየቴን ለመሰንዘር እወዳለሁ።

     በፕሬዚደንት ኦባማ ሃሣብ አመንጪነት የተቋቋመው ፓወር አፍሪካ የተሰኘው ኢንሼቲቭ፤ አፍሪካ ለእድገቷ የሚያስፈልጋትን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እያደረገች ያለችውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ፕሮጀክት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ኢንሼቲቩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት የአፍሪካ አገራት፣ 20 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
 ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በሁሉም ዘርፍ የሚደረገው ልማት ወሳኝነት አለው። በተለይ የኃይል ልማቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት የሚያሻው በመሆኑ የሃገሪቱን የኃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመመለስ የ25 ዓመት የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመንደፍ፣ የኃይል አቅርቦቱን አሁን ካለው 4000 ሜጋ ዋት ወደ 37000 ሜጋ ዋት ለማሳደግ፣ የግል አልሚዎችንም በማሳተፍ ጭምር ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም ፕሮጀክቶች በዋነኝነት የትውልድ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠቃሽ ሲሆን ዮሐንስ ባሰፈሩት ሃሳብ፣ “የፓወር አፍሪካ የገንዘብ ርዳታ ለምን ለህዳሴው ግድብ አይሆንም” ሲሉ ገልጸዋል፤ ነገር ግን  የህዳሴ ግድብን በተመለከተ እኛው በኛው ለኛው የምንሰራው ግድባችን መሆኑን ፀሐፊው አልሰሙ ይሆን? የውጪ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ተደርጎ ባለመሳካቱ አልነበረም እንዴ እኛው ራሳችን ለመስራት ቃል የገባነው፡፡
እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሃገራችን 94% ያህሉ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ከሃይድሮ ፓወር መሆኑ ግልፅ ነው። ይህ ማለት ግን ያለን የኃይል አማራጭ በግድብ ግንባታ ላይ የተመሰረተ ብቻ ነው ማለት አለመሆኑን ፀሐፊው ሊረዱት ይገባል ባይ ነኝ። ለኢኮኖሚው ቀጣይ እድገት አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦትን ለማሟላት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ግድ የሚለን ወቅት ላይ ደርሰናል። ለዚህም ሲባል ከንፋስ ኃይል 800 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት በዕቅድ የተያዘ ሲሆን አሽንጎዳ 120 ሜጋ ዋት፣ አዳማ I የነፋስ ኃይል ማመንጫ 51 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል።  አዳማ II በቅርቡ 153 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የጀመረ መሆኑን ሰምተናል አይተናልም። በአፍሪካ ትልቁ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሚያሰኘው ደረጃ ላይ መገኘቱ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኢነርጂ ልማትን በማፋጠን ላይ እንደምትገኝ ዋቢ ሆኖ ሊቆጠር ይችላል። ከእነዚህ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ባጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 324 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ያስቻለ አቅምንም ፈጥረዋል።
እንደ ንፋስ ኃይልና ጂኦተርማል ያሉት የኃይል ምንጭ አማራጮች  የሃይድሮ ፓወርን በመደገፍ የዝናብ መጠን አነስተኛ በሚሆንባቸው ወቅቶች  ለክፉ ቀን ደራሾች መሆናቸው የሚያስማማን ይመስለኛል።       
ሁሉንም የታዳሽ ኃይል ምንጮች የማልማቱ ተግባር ከሚፈጥረው ሰፊ አማራጭ በተጨማሪ በተወሰኑ የኃይል ምንጮች ላይ የሚኖረውን ጥገኝነትንም ይቀንሳል። ኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ከፍተኛ የጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት በየጊዜው የሚደረጉ ጥናቶች እያመላከቱ ነው።
ከዚህ የኃይል ምንጭ ብቻ ከ10‚000 ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት እንደሚቻል ታውቋል፡፡ በእስካሁኑ ሁኔታ ከጂኦተርማል ለመጠቀም የተቻለው ኃይል 7% ብቻ ነው። ይህም በዘርፉ ያለውን አቅም የመጠቀም ውስንነት እንዳለ ቢያሳይም በቅርቡ በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ 1000 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የጂኦተርማል ኢነርጂ ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆነ አስተማማኝ የታዳሽ ኢነርጂ ምንጭ ሲሆን ከቅሪተ አካል ኢነርጂ ምንጮች ከሚወጣው ወጪ 80% ያህል ቅናሽ እንደሚኖረውም ይነገራል።
 ከዚህ አንጻርም ለትራንስፖርትና ለማመንጫ ጣቢያዎች ጽዳት የሚወጣን ወጪ ከመቀነሱ ባሻገር ለዓለማችን ስጋት ከሆነው የግሪን ጋዝ ልቀትና የአካባቢ ብክለት ነጻ የሆነ ኃይል ለማምረት ያስችላል። በግንባታው የመጀመሪያ ወቅት ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም በማመንጨት ሂደቱ በቀጥታ ለጥቅም መዋሉ ተመራጭና ርካሽ አማራጭ ያደርገዋል። እንግዲህ ዮሐንስ በአንድ አቅጣጫ ትኩረት ከሚያደርጉ ይልቅ የተለያዩ መረጃዎችን መመልከት ቢችሉ ፅሁፋቸውን በመረጃ የበለጸገ ለማድረግ በረዳቸው ነበር።
የጂኦተርማል ኢነርጂን ማልማት ለወደፊቱ ተመራጭና ተደራሽነቱም አስተማማኝ እንደሚሆን ተተንብይዋል።አገራት የወደፊቱን የኢነርጂ አማራጫቸውን በታዳሽ ኢነርጂ ላይ እንደሚያደርጉ የወቅቱ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ እያስገደዳቸው እንደሆነ በግልፅ እየታየ ነው። በዓለማችን የጂኦተርማል ኢነርጂን በማልማት  በቀዳሚነት 24 አገራት ከዚህ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 12.8 ጌጋ ዋት አቅም ያለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 28 በመቶውን ማለትም 3‚548 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት አሜሪካ በመሪነት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ፊሊፒንስ 1‚904 ሜጋ ዋት፣ ኢንዶኔዥያ 1‚222 ሜጋ ዋት በማመንጨት በሁለተኛና ሦስተኝነት ይከተላሉ፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታትም የዘርፉ አቅም ከ14.5-17.6 ጌጋ ዋት እንደሚደርስ ይገመታል።

      አንዳንድ ታሪክ ካልተደጋገመ ሰሚ አያገኝም፡፡ የሚከተለው እንደዚያ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጋብሮቮ ወደ ሩቅ መንደር ሄዶ ሲመለስ ብርቱካን ይዞ መጣ፡፡ የመንደሩ ሰዎች “ብርቱካን ስጠን”፣ “ስጠን” እያሉ አስቸገሩት፡፡
ጋብሮቮው እንዲህ አላቸው፡-
“የሰፈሬ ህዝብ ሆይ! የእኔን በጣት የምትቆጠር ብርቱካን ከምትለምኑ ለምን ከዋናው ቦታ ሄዳችሁ እንደ እኔ ፋንታችሁን አትወስዱም?”
የሰፈሩ ሰዎችም፤
“ዋናው ቦታ ወዴት ነው?” አሉት፡፡
ጋብሮቮውም፤
“ማዶ ያለው መንደር ብርቱካን በነፃ እየታደለ‘ኮ ነው!”
“አትጠራጠሩ ይልቅ ቶሎ ብላችሁ ሩጡ፡፡ በገፍ እየተሰጠ ነው!”
ህዝቡ ጋብሮቮው ያለውን በማመን ወደተባለው መንደር መሮጥ ጀመሩ፡፡
መንገድ ላይ ያሉ ሌሎች ሰዎች የሚሮጡትን ሰዎች ይጠይቋቸዋል፡፡
“ወዴት ነው የምትሮጡት?”
“እማዶ ካለው መንደር ብርቱካን እንደጉድ በነፃ ይታደላል”
እነዚህኞቹም የተባለውን አምነው መሮጥ ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስ የመንደሩ ህዝብ በጠቅላላ መሮጥ ቀጠሉ፡፡
ጋብሮቮው ዘወር ብሎ ሲመለከት አገር በሙሉ በአንድ አቅጣጫ ሲሮጥ አየ፡፡
ይሄኔ ጋብሮቮ ሆዬ፤
“እንዴ! ይሄ ነገር እውነት ይሆን እንዴ?” ብሎ ወደ ህዝቡ ሩጫውን ቀጠለ፡፡
***
ራሳችን በፈጠርነው ህልም ራሳችን ከመወናበድ ይሰውረን፡፡ ራሳችን የወለድነውን ልጅ የእኛ አይደለም ከማለትም ያድነን፡፡ የራሳችን ውሸት እውነት መስሎን ዳግመኛ ከመሳሳት አምላክ መልካሙን ያሳየን፡፡
“ዕድለ ቢስ ወፍ ማሽላ ሲያሸት ትታወራለች” ይባላል፡፡ አንዳንድ ታጋይ በሚበላበት ሰዓት ከቦታው ይሰናበታል፡፡ አንዳንድ የተማረ ሰው የሱ ሙያ ሲያብብ እሱ ይጠወልጋል፡፡
“ያውና እዛ ማዶ ብርሃን ያድላል
አሁን እኔ ብሄድ አለቀ ይላሉ” እንዳለው ነው ዐይነ ስውሩ ለማኝ፡፡
የተነገረውን ሁሉ በደፈናው የሚያምኑ የዋሃን፤ አሳዛኝ ናቸው! ህዝብ፤ ማንም ሹመኛ፣ ምሁር፣ ጊዜያዊ አለቃ፣ አውቃለሁ ባይ አፈ-ቀላጤ ወዘተ ተናገረ በሚል ሙሉ እምነቱን ዋና ማተብ አድርጐ እንዳፈተተ መጓዝ የለበትም፡፡ ቀልቡን ገዝቶ፣ ነፍሱን አግዝፎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ግዙፉን ነገር፣ ማቴሪያሉን ብቻ ሳይሆን መንፈሱን ማሰብ ቁልፍ ነገር ነው፡፡
ስለ ሹመትና ስለ ሃላፊነትም ስናስብ፤
“በግራም ወጣ ወደ ኮርቻ፣ በቀኝም ወጣ ወደ ኮርቻ”፤ እንደተባለው ተረት ውስጠቱን ማስተዋል ይገባናል፡፡
እንደ ጋብሮቮው፤ እኛው በፈጠርነው የጥንቃቄ ኢኮኖሚ ተገዝተን፣ እኛው መልሰን ተታልለን፣ “ለካ ልክ ነበርን፣ ህዝብ ከእኛ ጋር ነው” ብለን መሞኘት የለብንም፡፡
የእኛን የፖለቲካ ወዳጆች፣ አባሎች፣ አጋሮች፣ እንከንና ስህተት፣ ጥበት እና ትምክህተኝነት፣ በቅጡ አስተውለን፣ እነሱም መክረው፣ ዘክረውና አምነው ነው ወደፊት ተጉዘናል ማለት ያለብን፡፡ “እከክልኝ ልከክልህ” እንደማይሰራ ሁሉ፤ “ወገኔ ነው በዚህ እንኳ ይጠቀም” ማለትም በፍፁም አይሰራም!
አገራችንን ጉድ ያደረጋት የመዓት ዝምድና ገመድ ትብትብ ነው፡፡
የማህበረሰብ ግንዛቤያችንን ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ግንዛቤ ይልቅ በባህል ዙሪያ ማሰብ ትልቅ ፍሬ አለው፡፡ ለዚህ በዓለም ላይ ያለውን ባህልና የሃይማኖት ጦርነት ስራዬ ብሎ ማስተዋል አንዳች ዋጋ አለው፡፡ ባህል ምን ያህል ዋጋ ቢኖረው ነው ዓለም በጠቅላላው ባህል ያላቸውን ሀገሮች ጦርነት ውስጥ እየዘፈቀች ለጥፋትም እየዳረገቻቸው ያለው፡፡ (ሶርያ፣ ኢራቅ፣ ግብፅ፣ የመን፣ ወዘተ ልብ ይሏል) ብሎ መጠየቅ የአባት ነው! ሃይማኖትስ ምን ያህል የጠብ ጫሪነት ነዳጅ ቢኖረው ነው ሃይማኖት ያላቸው ሀገሮች ለጦርነት እንዲዳረጉ ማገዶ የሚሆነው? ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡
ዘመን እየተለወጠ ሲመጣ ሰዓሊው አዲስ ምስል፣ ገጣሚው አዲስ ምንባብ፣ ደራሲው አዲስ መጽሀፍ፣ ፖለቲከኛው አዲስ ግንዛቤ፣ መንግስት ደግሞ አዲስ ዕቅድ ሊያመጣ ይጠበቃል፡፡ የትላንቱን ካነበብን፣ የትላንቱን መንገድ ከደረትን፣ ሌላው ቀርቶ የትላንቱን ሳቅ ከሳቅን አዲስ ሳቅ ነጠፍን ማለት ነው፡፡ “ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት” የሚለው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡

• በቅዱስ ዐማኑኤልና በአቡነ አረጋዊ አድባራት፤ አስተዳደሩና ሰበካ ጉባኤያት ተፋጠዋል
• ፓትርያርኩ የመሩበት ጥናታዊ ሪፖርት ለቋሚ ሲኖዶሱ ይኹንታ አለመቅረቡ አነጋጋሪ ኾኗል


    በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በርካታ አድባራት፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በበላይነት ለመምራትና ለመቆጣጠር ሥልጣንና ተግባር ያላቸው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ አባላት፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር በሚታሙ የአስተዳደር ሓላፊዎች መታገዳቸው አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ መምጣቱ ተገለጸ፡፡ ሀገረ ስብከቱም ተጣርተው በሚቀርቡለት ሪፖርቶች ላይ አፋጣኝ ውሳኔ አለመስጠቱ “ትክክለኛ መፍትሔ የማግኘት ተስፋችንን አዳክሞታል፤” ይላሉ ምእመናኑ፡፡ባለፉት ሦስት ወራት ለአዲስ አድማስ የደረሱ ጥቆማዎች እንደሚያስረዱት፤ የሰበካ ጉባኤያቱ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ከሓላፊነት ይታገዳሉ አልያም በአስተዳደር ተግባር የመሳተፍ ድርሻቸው ተዳክሞ ደመወዝና ሥራ ማስኬጃ በመፈረም ብቻ ተወስኗል፡፡ ከአስተዳደሩ ሓላፊዎች የተለየ ሐሳብ የሚያነሡ የማኅበረ ካህናት ተወካዮች፤ ከሥራና ከደመወዝ ይታገዳሉ፤ ከፈቃዳቸው ውጭ ወደ ሌሎች አድባራት ዝውውር ይጠየቅባቸዋል፤ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራንና የንብረት አመዘጋገብን አጥብቀው የሚቆጣጠሩ የማኅበረ ምእመናን ተወካዮች ከአባልነት ከመታገዳቸውም በላይ “ለማበጣበጥ እየሠሩ ነው፤ አሸባሪዎች ናቸው” በሚል ለመንግሥታዊ አስተዳደርና የፍትሕ አካላት ክሥ ይቀርብባቸዋል ተብሏል፡፡
በደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ አስተዳዳሪው፤ የሰበካ ጉባኤውን ውሳኔ እንደማይተገብሩ የጠቆሙ ምዕመናን፤ በምክትል ሊቀ መንበሩ የማይታወቁ የባንክ ሂሳቦችን በደብሩ ስም እንደሚያንቀሳቅሱ፣ አግባብነት የሌለው የሠራተኞች ዕድገትና ዝውውር እንደሚፈፅሙ ተናግረዋል፡፡
አስተዳዳሪው ቀደም ሲል የቤተ ክርስቲያንን መሬት ለግል ጥቅም በማዋላቸው ከሓላፊነት ታግደው እንደነበር ያስታወሱት ምእመናኑ፤ ደብሩ ለሀገረ ስብከቱ መክፈል የሚገባውን የኻያ ፐርሰንት ፈሰስ ሳይከፍሉ በመቅረታቸው ለዕዳ እንደዳረጉት ይናገራሉ፡፡ የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ በማኅበረ ካህናቱ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በተወላጅነት እንደሚከፋፍሉና ካህናቱን ከደመወዝና ከሥራ በማገድ ለችግር እንደሚያጋልጧቸው ምዕመናኑ ይገልፃሉ፡፡
የአለመግባባቱ መንሥኤ፣ የሰበካ ጉባኤው አባላት የደብሩን ገቢና ወጪ አጥብቀው በመቆጣጠራቸውና የፋይናንስ ሪፖርት፤ በመጠየቃቸው እንደኾነ የሚገልጸው የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት አባላቱ፣ ደመወዝ ፈርሞ ከማውጣት ውጭ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ በቃለ ዐዋዲው በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር እየተሳተፉ እንዳልኾነ አረጋግጧል፡፡ የአስተዳዳሪውን አልታዘዝ ባይነት የሚገልጸው ሪፖርቱ፤ ለሀገረ ስብከቱ ማስተላለፉን ቢያውቁም ምንም ዐይነት ምላሽ አለመሰጠቱ ግራ እንዳጋባቸው - ምእመናኑ ይናገራሉ፡፡
በተመሳሳይ አኳኋን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በቅርቡ ባካሔደው የሕንጻ እና የመሬት ኪራይ ተመን ጥናታዊ ሪፖርት ከበድ ባለ ሙስና የተተቸው የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል አስተዳደር፤ ከሙዳየ ምጽዋት ቆጠራና ከንብረት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከምእመናኑ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል፡፡ በየካቲት 2007 የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ፣ የደብሩን የአሠራር ክፍተቶች በመቅረፍ ገቢውን በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠርና ለማሳደግ ቢንቀሳቀስም አንድ የካህናት ተወካይ ከሥራና ከደመወዝ፣ ኹለት የምእመናን ተወካዮች ደግሞ ከአባልነት መታገዳቸው ውዝግቡን እንዳካረረው ተጠቅሷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት ለመጠበቅ ሲባል ካህናትና ምእመናን የሥራ ሓላፊነታቸውንና የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ግዴታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ለሚፈጠርባቸው ዕንቅፋት ሀገረ ስብከቱ ሓላፊነት እንደሚወስድ ቢገልጽም ልኡካኑ ችግሩን ለመፍታት ባለመቻላቸው “ትክክለኛ መፍትሔ የማግኘት ተስፋችንን አዳክሞታል፤ ለሚደርሰው ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂዎች አንኾንም” ሲሉ ምእመናኑ አሳስበዋል፡፡
በብሥራተ ገብርኤል፣ በካራ ቆሬ ፋኑኤል፣ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፣ በላፍቶ ቅዱስ ሚካኤል፣ በፉሪ ቅዱስ ገብርኤል፣ በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ፣ በሰሚት ቅ/ጊዮርጊስ፣ በሰሚት ኪዳነ ምሕረት፣ በሰሚት ቅ/ሩፋኤል፣ በጨፌ አያት ቅ/ገብርኤል፣ በአያት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ በፉሪ ቅ/ዑራኤል እና በሰሚት መድኃኔዓለም ከሰበካ ጉባኤ አባላት የሥራ ጊዜ መጠናቀቅ፣ የካህናትና ምእመናኑን ከአስተዳደሩ ጋር አለመግባባት ውዝግብ እንደፈጠረ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤ አባላት በሥልጣናቸው አለመሥራት፣ የአስተዳደር ሓላፊዎች ብቃት ማነስ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲኹም የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ መዳከም በዐበይት መንሥኤነት ተዘርዝረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ይኹንታውን እንዲሰጥበት ፓትርያርኩ የመሩበትና ሙሰኛ የአድባራት ሓላፊዎች ምዝበራ በሕግ አግባብ እንዲታይ የሚጠይቀው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጥናታዊ ሪፖርትና ውሳኔ በአጀንዳነት አለመቅረቡ አነጋጋሪ ሆኗል ተባለ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አስፈጻሚ አካል የኾነውና በፓትርያርኩ ሊቀመንበርነት የሚመራው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በዚኽ ሳምንት መደበኛ ስብሰባው ይኹንታውን እንደሚሰጥበት ቢጠበቅም፤ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የፓትርያርኩ ምሪት እንዳልደረሳቸው በመግለጻቸውና የተመራበት ሰነድም የትኛው አካል ጋር እንዳለ በስብሰባው ወቀት ባለመታወቁ በአጀንዳነት ሳይቀርብ መቅረቱን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ዘግይቶ በደረሰን ዜና፣ ጥናታዊ ሪፖርቱና የውሳኔው ቃለ ጉባኤ ትላንት ከቀትር በኋላ ለብፁዕ ዋና ጸሐፊ አሁነ ሉቃስ ዘግይቶ በመድረሱ በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ በአጀንዳነት ቀርቦ ይኹንታ እና የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጥበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

     ከአንድ ወር በፊት ኢትዮጵያን የጎበኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባ በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ለሆቴል 1.3 ሚ. ዶላር ማውጣታቸውን ዊክሊ ስታንዳርድ ድረገጽ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
ኦባማ እና አብረዋቸው የመጡ የደህንነትና የልኡካን ቡድን አባላት በአዲስ አበባ በሚገኙ አራት ሆቴሎች ማረፋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በሁለት ቀናት ቆይታቸው ለሆቴሎቹ በድምሩ 1.3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መከፈሉን ገልጿል፡፡የጉብኝቱ አዘጋጆች በመጀመሪያ ከሂልተን ሆቴል ጋር የ412ሺ 390 ዶላር ውል መፈጸማቸውንና በቀጣይም ከኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ጋር የ246ሺ 877 ዶላር፣ ከካፒታል ሆቴልና ስፓ ጋር ደግሞ የ178ሺ 433 ዶላር ውል መፈጸማቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ በመጨረሻም ከሸራተን አዲስ ሆቴል ጋር የ488ሺ 141 ዶላር ስምምነት መፈጸማቸውን ጠቁሟል፡፡የልኡካን ቡድኑ አባል የሆነ አንድ የዋይት ሃውስ ፎቶ ግራፍ አንሺን እማኝነት በመጥቀስ ዘገባው እንዳለው፣ ኦባማ በሁለት ቀናት ቆይታቸው ያረፉት በሸራተን አዲስ ሆቴል እንደነበር መረጋገጡንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡

     በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ነጥብ አምጥተው ዩኒቨርሲቲ ለገቡ ከ2 ሺ 500 በላይ ሴት ተማሪዎች ትላንት የሽኝት ፕሮግራም ተደረገ፡፡
“ዘር ኢትዮጵያ” በተባለ ድርጅት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው ፕሮግራም፤ በተለያዩ የሥራ መስኮች ስኬታማ የሆኑ ሴቶች ለተማሪዎቹ ከህይወት ልምድና ተሞክሮአቸው አካፍለዋል፡፡
ሴት ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚገጥሟቸውን በርካታ ችግሮችና መሰናክሎች በአሸናፊነት ለመወጣት የዓላማ ፅናት ሊኖራቸው እንደሚገባ የተነገራቸው ሲሆን ለዚህም ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ምክር ተለግሰዋል፡፡ለወጣት ተማሪዎቹ የህይወት ልምድና ተሞክሮአቸውን ካጋሩ ስኬታማ ሴቶች መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሊካ በድሪ፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብ/ጄ ዘውዱ ኪሮስና  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አዜብ ወርቁ ይጠቀሳሉ፡ሽኝት የተደረገላቸው ሴት ተማሪዎች በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በኩል የተመረጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጅ “ዘር ኢትዮጵያ”፤ አራት መቶ ሴትና አንድ መቶ ወንድ ተማሪዎችን በየወሩ 200 ብር ድጋፍ እያደረገ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያበረታታ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ድጋፍ የሚደረግላቸውን ተማሪዎች ቁጥር ወደ  1000 ለማድረስ እቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡  

     በመዲናዋ ባሉ ክፍለ ከተሞች በተመረጡ 10 ወረዳዎች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የሰፈሮቹ የአድራሻና አቅጣጫ መጠቆሚያ ስርአት ሊዘረጋላቸው እንደሆነ እያካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት መሪ አቶ ማርቆስ አለማየሁ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ዝርጋታው አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶችን፣ ብሎክና የቤት ቁጥር ታፔላዎችን ያካትታል፡፡ የአድራሻ ስርዓቱ በዋናነት ለፖስታ አገልግሎት፣ የእሳት አደጋ መኪኖች ፈጥነው እንዲደርሱ እንዲሁም የአምቡላንስ አገልግሎት ለማግኘትና ወንጀልን ለመከላከል ወሳኝ መሳሪያ ይሆናል ተብሏል፡፡
ስርአቱን ለመዘርጋትም ካርታ የማዘጋጀት ስራ ሲከናወን የቆየ ሲሆን ታፔላዎቹ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲመረቱ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ ከህብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ኢንዱስትሪ ጋር የ40 ሚሊየን ብር ውል መገባቱን የጠቆሙት አቶ ማርቆስ፤ አሁን የስራው የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ሆነው ምልክት ተከላ ተሸጋግሮ ስራው እየተገባደደ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ከአስሩም ክፍለ ከተሞች አንድ አንድ ወረዳ የተመረጠ ሲሆን ለአብነትም ጉለሌ ወረዳ 10፣ የካ ወረዳ 13፣ ቂርቆስ ወረዳ 2 እና አዲስ ከተማ ወረዳ 9ን ጠቅሰዋል፡፡ የእነዚህ ወረዳዎች ተከላ እንደተጠናቀቀም 30 የሚሆኑ ወረዳዎች ላይ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል - የሥራ ሂደት መሪው፡፡