Administrator

Administrator

Saturday, 05 December 2015 09:17

ፀደኒያ ምስጋና አቀረበች

  በቅርቡ በናይጄሪያ ሌጎስ በተከናወነው “አፊርማ” የሙዚቃ ውድድር፤ “የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ሴት ድምፃዊት” ዘርፍ አሸናፊ የሆነችው ዝነኛዋ ድምፃዊት ፀደንያ ገ/ማርቆስ ድጋፋቸውን ለቸሯትና በተለያየ መንገድ ለደገፏት አድናቂዎቿ ባለፈው ማክሰኞ ባዘጋጀችው የምሽት ፕሮግራም ላይ ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡

Saturday, 05 December 2015 09:12

የሙስና ጥግ

አፍሪካውያን ስለ ሙስና)
- ሙስና ከአፍሪካ የሚጠፋ ከመሰላችሁ
ሃሳባችሁን ዳግም ፈትሹት፡፡ በሴራሊዮን
አንድ የፖሊስ መኮንን ለትራፊክ ሥራ
ከመሰማራቱ በፊት ሚስቱ ምድጃው ላይ
ውሃ እንድትጥድ ነግሯት ነው የሚወጣው።
ወደ ቤት ሲመለስ ታዲያ በእርግጠኝነት
አንዲት ከረጢት ሩዝ መያዙ የተረጋገጠ
ነው፡፡ እስቲ ንገሩኝ፤ ቀንደኞቹ ዋናዎቹ
ሙሰኞች በሆኑበት ሁኔታ ሆነው ማነው
ህጉን የሚያስፈፅመው? (ሴራሊዮን)
* * *
- ማንነትህ ወይም ከየትኛውም የአፍሪካ
ክፍል መምጣትህ ደንታ አይሰጠኝም።
እውነቱ ግን በሙስና ተዘፍቀሃል ወይም
በበርካታ የሙስና ተግባራት ውስጥ
ተሳትፈሃል፡፡ ሙስና የአፍሪካ ባህል
አንድ አካል ነው፤ የኑሮ ዘይቤ ሆኗል፡፡
ነገሮች እንደምትፈልገው እንዲያልቅልህ
ከፈለግህ፣ አንድ ነገር በእጅ ማለት ነው፡
፡ ምስጋናን የመግለጪያ መንገድ ሆኗል፡
፡ (ቶጎ)
* * *
- ሙስና ሥር ሰድዷል፡፡ ሙሉ በሙሉ
ከመጥፋቱ በፊት ጥቂት ጊዜ መውሰዱ
አይቀርም፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በመላው
ዓለም ላይ ጥቂት ሃቀኛ፣ ትጉህ፣ ቅንና
ቁርጠኛ አፍሪካውያን አሉ፡፡ እንደነዚህ
ያሉ ሰዎች ሥልጣን ሲይዙ በአፍሪካ
የሚመጣውን ተዓምራዊ ለውጥ
ታዩታላችሁ፡፡ (ቻድ)
* * *
- የሙስና ባህል በአጠቃላይ በአፍሪካና
በተለይ በናይጄሪያ፣ ህብረተሰቡ
የተገነባበትን ዋና መሰረት ቦርቡሮታል።
በትራንስፖርት አውቶብስ ውስጥ
ተሳፋሪው ከገንዘብ ተቀባዩ ለማጭበርበር
ይሞክራል፡፡ ገንዘብ ተቀባዩ በተራው
ከሹፌሩ፣ ሹፌሩ ደግሞ ከአውቶብሱ
ባለቤት ለማጭበርበር ይሞክራል፡፡ ነገሩ
ወደዚህ ደረጃ ከመዝቀጡ በፊት ግን
በመንግስት ባለስልጣናት ብቻ የሚፈፀም
ጉዳይ ነበር፡፡ (ናይጄሪያ)

Saturday, 05 December 2015 09:07

የዘላለም ጥግ (ስለ ተስፋ)

ከትላንት ተማር፣ ዛሬን ኑር፣ በነገ ተስፋ
አድርግ፡፡ ዋናው ነገር መጠየቅን አለማቆም
ነው፡፡
አልበርት አንስታይን
- ተስፋ፤ ያለ አበቦች ማር የሚሰራ ብቸኛው
ንብ ነው፡፡
ሮበርት ግሪን ኢንገርሶል
- ተስፋ ዓለምን ደግፎ የያዘ ምሰሶ ነው፡፡
ተስፋ ከእንቅልፍ የነቃ ሰው ህልም ነው፡፡
ፕሊኒ ዘ ኤልደር
- ተስፋ እንደ ሰላም ነው፡፡ የእግዚአብሔር
ስጦታ አይደለም፡፡ አንዳችን ለሌላችን
የምንለግሰው ስጦታ ነው፡፡
ኤሊ ዊሴል
- ያለ ተስፋ መኖር ከህይወት መፋታት ነው፡፡
ፍዮዶር ዶስቶቭስኪ
- ሁልጊዜ ታላላቅ ተስፋዎችን አስተናግዳለሁ።
ሮበርት ፍሮስት
- ነገ፤ ከትላንት አንድ ነገር እንደተማርን ተስፋ
ያደርጋል፡፡
ጆን ዋይኔ
- የበዛ ተስፋ ከበዛ መከራ ይወለዳል፡፡
በርትራንድ ራስል
- አንድን ሁኔታ ወይም ሰው ተስፋ-ቢስ
ስትሉ በእግዚአብሔር ፊት ላይ በሩን
እየደረገማችሁት ነው፡፡
ቻርለስ ኤል. አለን
- ርዕይ በሌለበት ተስፋ የለም፡፡
ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
- ዛሬ ጤንነቴን መጠበቄ ለነገ የተሻለ ተስፋ
ይሰጠኛል፡፡
አኔ ዊልሰን ስሻት
- ተስፋ የማልቆርጥበት ምክንያት ሁሉም ነገር
በመሰረቱ ተስፋ ቢስ ስለሆነ ነው፡፡
አኔ ላሞት
- ተስፋ የእውነትን እርቃን መሸፈኚያ
የተፈጥሮ ዓይነ እርግብ ነው፡፡
አልፍሬድ ኖብል

Saturday, 05 December 2015 09:06

የቀልድ ጥግ

አንድ ጎልማሳ በትልቅ ሱፐርማርኬት ውስጥ
ወደ አንዲት በጣም ቆንጆ የሆነች ሴት ቀረብ
ይልና፤ “ይሄውልሽ ሚስቴ እዚሁ ሱፐርማርኬት
ውስጥ ጠፍታብኛለች፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች
ልታዋሪኝ ትችያለሽ?” ይላታል::
“ለምን?” አለች ቆንጅየዋ ሴት ኮስተር ብላ፡፡
“ሚስቴ ሁልጊዜ ከቆንጆ ሴት ጋር ሳወራ
ድንገት ከሆነ ቦታ ትከሰታለች”
* * *
አንድ ትንሽ ልጅ ከእናቱ ጋር ሰርግ ይሄዳል።
እዚያም ሙሽሮቹንና ሚዜዎቹን ሲመለከት
ይቆይና ለእናቱ ጥያቄ ያቀርባል፡-
“ማሚ፤ ለምንድነው ሴቷ ነች የለበሰችው?”
እናትየዋም፤ “ሙሽራዋ ነች የለበሰችው ደስ
ስላላት ነው፤ ዛሬ የደስታዋ ቀን ነው” ስትል
መለሰችለት፡፡
ልጁ ትንሽ አሰብ አደረገና፤ “ታዲያ ሰውየው
ለምን ጥቁር ለበሰ?”
(እውነት ሙሽራው ለምንድነው ጥቁር
የሚለብሰው?)

Saturday, 05 December 2015 09:03

የጸሐፍት ጥግ

 ፀሐፊ፤ የሰዎች ነፍስ መሃንዲስ ነው፡፡
ጆሴፍ ስታሊን
- ፀሐፊ ተመልካች ነው፤ ሁሉንም ነገር በላቀ
የሰላ ዓይን የሚመለከት፡፡
በርናርድ ማላሙድ
- ፀሐፊ፤ የገጣሚ እቅጩነት፣ የሳይንቲስት
ምናብ ሊኖረው ይገባል፡፡
ቭላድሚር ናቦኮቭ
- ፀሐፊ ነኝ፤ እናም መፃፍ የምሻውን
እፅፋለሁ፡፡
ጄ.ኬ.ሮውሊንግ
- ጆሮ፤ ብቸኛው እውነተኛ ፀሐፊና ብቸኛው
እውነተኛ አንባቢ ነው፡፡
ሮበርት ፍሮስት
- ዝነኛ ፀሐፊ ማለት እንደ ጄን ኦዩስተን መሆን
ይመስለኝ ነበር፡፡
ጄ.ኬ.ሮውሊንግ
- ለፀሐፊ ትልቁ ሃጢያት አሰልቺነት ነው፡፡
ካርል ሃያሴን
- እያንዳንዱ ፀሐፊ የየራሱን የአፃፃፍ ስልት
መፈለግ አለበት፡፡
ማርጋሬት ማሂ
- ፀሐፊ በአትኩሮት መመልከትን ማፈር
የለበትም፡፡ የእሱን ትኩረት የማይፈልግ
ምንም ነገር የለም፡፡
ፍላነሪ ኦ‘ኮኖር
- የፀሐፊ የመጀመሪያ ሥራው ሃቀኝነት ነው፡፡
ኧርቪን ዌልሽ
- መፃፍ ከዝምታ ጋር የሚደረግ ትግል ነው፡፡
ካርሎስ ፉንቴስ
- የምናብ ፈጠራ የሆኑ ታሪኮች ምናብ
የሌላቸውን ሰዎች ያበሳጫሉ፡፡
ቴሪ ፕራትሼት
- እኔ በእግዜር እጅ እንዳለ ትንሽዬ እርሳስ
ነኝ። እሱ ነው የሚፅፈው፡፡ እርሳሱ ከፅሁፉ
ጋር ግንኙነት የለውም፡፡
ማዘር ቴሬዛ
- ሁሉም ፅሁፍ የሚመነጨው ከእግዚአብሔር
ፀጋ ነው፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አቴናዊና አንድ ቲቤታዊ መንገድ ላይ ይገናኛሉ። ከዚያም ውይይት ማድረግ ጀመሩ፡፡ መንገደኞች ትንሽም ይሁን ትልቅ ነገር ማንሳታቸው የተለመደ ነው፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን ካነሱ በኋላ ስለጀግኖች ወሬ ጀመሩ፡፡ ሁለቱም የየራሳቸውን ጀግኖች ማወደስ ያዙ፡፡
አቴናዊው፤
“የእኔን አገር ከተማ ጀግኖች የሚያክል ማንም የለም” አለ፡፡
ቲቤታዊው፤
“ኧረ አፍ አውጥተህ እንዲህ ያለ ድፍረት አትናገር፤ ቲቤት ምን የመሳሰሉ ጀግኖች ያፈራች ከተማ መሆኗን አለማወቅህ ገርሞኛል” ይላል፡፡
አቴናዊው፤
“የጀግና ልክ አታቅም ማለት ነው፡፡ ቴሲየስን የሚያክል ጀግና ያለን ነን እኛ፡፡”
ቲቤታዊው፤
“ሒርኩለስን የሚያክል ጀግና በዓለም ላይ እንዳልነበረ በታሪክ የተመሰከረ ነው። በአማልክቱ ዘንድ ትልቁን ሥፍራ የተሰጠው ጀግና ነው፡፡”
አቴናዊው፤
“ቴሲየስ ይህ ነው የማይባል ሀብት ያለውና ሔርኩለስን ሳይቀር አገልጋዩ ማድረግ የቻለ ነበር፡፡”
ይህን ሲል ሙግቱ ሚዛን አነሳ፡፡ እንደ ብዙዎቹ አቴናውያን አንደበተ ርቱዕና አሳማኝ ነው፡፡
ቲቤታዊው በክርክሩ የተሸነፈ መሆኑነ አውቆ በመከፋት፤
“ይሁን፡፡ መንገድህ የራስህ ነው፡፡ እኔ ተስፋ እማደርገው ጀግናዎቻችን በእኛ የተናደዱ ለታ፤ አቴናውያን የሄርኩለስ ንዴት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ቲቤታውያን ደግሞ ቴሲየስ የተናደደ ለታ የእሱን ሥቃይ ይቀበላሉ፡፡
*        *       *
ዕጣ ፈንታችን በጀግና መሪዎች ንዴትና ትኩሳት ላይ የተጣለ ከሆነ ህዝቦች እየተመራን ሳይሆን እየተነዳን ነው ማለት ነው፡፡ መሪዎች፤ ኃላፊዎችና አመራሮች ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩ ሆደሰፊነታቸውን ያስመሰከሩ፣ ሁኔታዎችን በጥሞና አይተው የሚፈርዱ መሆን አለባቸው፡፡ ከባለሙያዎች ጋር መክረው፣ ዘክረው የሚተገብሩት ተግባር ፍሬው አመርቂ ይሆናል፡፡ ፍርድ ሁሉ የብቻዬ ነው፤ ሁሉን ወሳኝ እኔ ነኝ ማለት ውሎ አድሮ ብሶትን፣ ምሬትንና በቀልን እንጂ ዲሞክራሲያዊ ትሩፋትን አያስገኝም፡፡ የምናጭደው የዘራነውን ነው! የዘራነውን ብቻ ነው!
ለራስህ ታማኝ ሁን፡፡ ያኔ ሌላውን ሰው አትዋሽም (To thine own self be true. Thou canst be false to any man) ይለናል ሼክስፒር፡፡ ለራሱ ታማኝ የሆነ ሰው ልበ - ሙሉ የሆነ ሰው ነው፡፡ ልበ - ንፁህም የሆነ ሰው ነው! ለራስ ታማኝ መሆን ከሥልጣን መባለግ ያድናል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን ከሙስና ራስን ለማዳን ይጠቅማል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን ሌሎችን በወገን፣ በጎሣ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ነጥሎ ከማየትና ከመበደል ሙሉ ልቦናን ይሰጣል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን ሌሎችን ላለመጠራጠርና በራስ መተማመንን ያበለፅጋል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን መማርንና መመራመርን ስለሚያበረታታ፤ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የሚለውን ብሂል፣ በወጉና በቅጡ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን መልካም አስተዳደርን በሀቅ እንድንረዳ፣ በሀቅም እንድንተገብር ያግዘናል! ለራስ ታማኝ መሆን ለህግ የበላይነት ታማኝ እንድንሆን ያደርገናል! በመጨረሻም ለራስ ታማኝ መሆን ለሀገር ታማኝ እንድንሆን በሩን ይከፍትልናል!
አገራችን ወደፊት ትጓዝ ዘንድ በራሳቸው የሚተማመኑ ጎበዛዝት ያስፈልጓታል! እኒያ ጎበዛዝት ከአሁኑ ትውልድ የሚፈልቁ ናቸው፡፡ ይህ ትውልድ በትምህርት፣ በዕውቀት እና በጥበብ የለማና የዳበረ መሆን አለበት፡፡ በሀገር ፍቅር የበለፀገ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትሁት ግብረገብነት ወሳኝ ነው፡፡ ግብረገብነት በተለይ ዛሬ ለሀገር ወሳኝ ነው! “የጠፋው በግ” ግብረ ገብነት ነው! ለዚህ መንግሥት፣ ህዝብ፣ ቤተሰብ፣ ት/ቤቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ሁሎችም መተባበር ወቅታዊም፣ ታሪካዊም ርብርብ ያሻሉ፡፡! የዛሬው ጥሪያችን ግብረገብነት ያለው ሀቀኛ ትውልድ መፍጠር ነው!
“የኔ ቀበሌ፣ የኔ ክፍለ ከተማ፣ የኔ ክልል፣ የኔ ከተማ፣ የኔ ብሔር - ብሔረሰብ ጀግና ነው” ማለት ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን እያደረግሁ ነው ብሎ ራስን መፈተሽ ብቻ ነው ሀገራችንን ከገባችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያወጣት፡፡ የራስን ሰፈር ብቻ የተሻለ ለማድረግ ማሰብ ለዲሞክራሲ ሩቅ ነው። ትምክህትም ሆነ ጥበት ዞሮ ዞሮ የጥፋት መፈልፈያ ነው፡፡ ይህን ማረም “የሌሊት ጀግና ባሌ ነው፣ ትላለች የሌባ ሚስት” የሚለውን ተረት ማወቅ ነው!

“ማስተር ፕላኑ ልማትን ያሻሽላል፤ በረብሻ የተሳተፉ ይከሰሳሉ” - መንግሥት

     “የአዲስ አበባና የፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን” ላይ፣ ሰሞኑን በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች  በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ፣ ሶስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ የክልሉ ፖሊስ በበኩሉ፤ በረብሻው የተሳተፉ ሰዎች ይከሰሳሉ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅ አለበት ብሏል፡፡
አምና ተመሳሳይ ግጭትና ተቃውሞ ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ “ማስተር ፕላኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በዙሪያው የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን እንዲጠቀለል የሚያደርግ ነው፤” የሚለው ተቃውሞ ከሰሞኑ እንደገና ተሰንዝሯል፡፡ “የከተሞቹ የአስተዳደር መዋቅር በማስተር ፕላኑ አይቀየርም” የሚለው መንግስት በበኩሉ፤ መሰረተ ልማትን በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ሲል ቆይቷል፡፡
“የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በዙሪያው ወዳሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች እየሰፋ መጥቷል” በማለት የሚከራከረው ኦፌኮ፤ “ማስተር ፕላኑን አንቀበልም፤ መሬታችን አጥንታችን ነው፤ አንነቀልም” በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች (ግንጪ፣ ደንቢዶሎ፣ ዲላላ፣ ወሊሶ፣ መደወላቡ፣ ሀረማያ፣ አይራ ጉይሶና በሌሎችም) ለተነሳው የተማሪዎች  ተቃውሞ፤ መንግስት ሰላማዊ ምላሽ መስጠት አለበት የሚለው ኦፌኮ፤ እየደረሰ ላለው ጉዳት መንግስት ኃላፊነቱን ይወስዳል ብሏል፡፡
እስር፣ ድብደባና ግድያ እየተፈጸመ፣ መሆኑን በማውገዝ፤ መንግሥት ይህን ድርጊት በአስቸኳይ ማቆም አለበት ብሏል- ኦፌኮ፡፡ “የአዲስ አበባ ወሰን፤ ከ1987 ዓ.ም በፊት  ወደነበረበት መመለስ አለበት፤ ከወሰን አልፈው የተከናወኑ ግንባታዎች በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ስር መተዳደር አለባቸው” ሲልም ፓርቲው ጠይቋል፡፡ የከተሞች ፕላን የፌደራል መንግስት ጉዳይ አይደለም ያለው ኦፌኮ፤ ማስተር ፕላኑ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ይጻረራል ብሏል፡፡  
ለልማት ተብሎ ከመሬታቸው የሚነሱ ገበሬዎች የህንፃዎች ጠባቂ እየሆኑ ነው ያሉት የኦፌኮ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ገበሬዎቹ የባለሀብትነት ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡  
ዓለም ባንክ ማስተር ፕላኑን መደገፍ የለበትም ያለው ኦፌኮ፤ ባንኩ እጁን ያንሳ ሲል ጠይቋል፡፡ የፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ አስተዳደር ለማስተር ፕላኑ ድጋፍ በመስጠትም አሁን ለተፈጠረው ችግር አስተዋጽኦ ስላደረገ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል ብሏል - ኦፌኮ፡፡  
የመንግስት በደልና ግፍ ካልቆመ፣ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ስጋት ላይ ይጥላል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደሚገደድ ተናግረዋል፡
“በአዲስ አበባ ዙሪያ፣  በኦሮሚያ ላይ ሰፊ የመሬት እና የባህል ወረራ ተካሂዷል  ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ከ25 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ አካባቢ የነበሩ 28  የገበሬ ማህበራት ዛሬ የሉም ብለዋል፡፡ መንግስት በርካሽ የካሳ ክፍያ ከገበሬዎች መሬት እየወሰደ  በሚሊዮን ብሮች በጨረታ ይሸጣል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ሱሉልታ አካባቢ ገበሬዎች በ50 ሺህ ብር ካሳ ይፈናቀላል ብለዋል፡፡
ሰኞ እለት በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከፖሊስ ጋር በተነሳ ግጭት በርካታ ተማሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ትምህርት ተስተጓጉሎ ሰንብቷል፡፡  ዩኒቨርስቲው በበኩሉ፣  በተቃውሞ ምክንያት ትምህርት ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቋረጠና የግቢው ሁኔታ እንደተረጋጋ ገልጿል፡፡
ተቃውሞው በበርካታ ከተሞች በሚገኙ ዩንቨርስቲዎችና ት/ቤቶች የተስፋፋ ሲሆን ፣ በአንዳንዶቹ  አካባቢዎችም  ነዋሪዎች እንደተሣተፉበት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር በበኩሉ፤ በረብሻው የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን በመግለፅ ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ማስተር ፕላኑ የፌደራል ስርአቱን አይጥስም ያለው መስተዳድሩ፤ የኦሮሚያ መሬትንም ቆርሶ ለሌላ አካል አይሰጥም ብሏል፡፡  ሁከት የሚሹ ሃይሎች፤ ለማስተር ፕላኑ የተሣሳተ ትርጉም ሰጥተውታል፣ በዚህም ለጠፋው ህይወትና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ ናቸው ብሏል መስተዳድሩ ፡፡
ባለፈው አመት በዩንቨርስቲዎችና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ማስተር ፕላኑን ተመሳሳይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ፤ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት 10 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

ከቡድኑ ጋር ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ፣ ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ነበር
  በሴካፋ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ልኡካን የመሩት የክለቡ ማናጀር ዊሊስ ዋሊያውላ፤ ስድስት የቡድኑ ልኡክ አባላት ለአስር ቀናት አርፈውበት ለቆዩት “እንዳለ እና ቤተሰቡ ቸርቺል ሆቴል መከፈል የነበረበትን 41 ሺህ 154 ብር መክፈል ባለመቻላቸው፣ ከሆቴሉ እንዳይወጡ ታግደው ከቆዩ በኋላ ከትናንተ በስቲያ ተለቀቁ፡፡
የኬንያው ብሄራዊ ቡድን “ሃራምቤ ስታርስ” ከሩብ ፍጻሜ ውድድሩ ውጭ ሆኖ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ወደ አገሩ ቢመለስም፣ ዊሊስ ዋሊያውላ ግን ከቡድኑ ጋር የመጡት ስድስት ተጨማሪ የልኡካን ቡድን አባላት በሆቴሉ የቆዩበትን ወጪ መክፈል ባለመቻላቸው ከሆቴሉ እንዳይወጡ ታግደው ከቆዩ በኋላ፣ የኬንያ የስፖርት ሚኒስቴር ክፍያውን በመፈጸሙ ትናንት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን “ሲቲዝን ቲቪ” የተባለው የአገሪቱ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ የቡድኑ መሪ የሆቴሉን ዕዳ ሳይከፍሉ ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ፓስፖርታቸውን ተቀምተው ነበር ያለው ዘገባው፤ የኬንያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የልኡካን ቡድኑን ለመሩት ለእኒሁ ግለሰብ ወጪውን እንዲሸፍኑ 250ሺህ የኬንያ ሽልንግ መላኩን ጠቁሟል፡፡
የሴካፋ አዘጋጆች፤ ኬንያ 20 ተጫዋቾችንና አምስት የልኡካን ቡድን አባላትን ብቻ እንድትልክ ቢያስታውቁም፣ የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን 23 ተጫዋቾችንና የልኡካን ቡድን አባላትን በመላኩና ተጨማሪ ስድስት አባላት በመኖራቸው የገንዘብ እጥረቱ ሊከሰት እንደቻለ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

       ለችግር ተጋላጭ በሆኑ እናቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት  አድርጎ የሚሰራው መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት፤ ጉለሌ ክ/ከተማ መቀጠያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 350 ሺህ ብር በማውጣት ምንጭ አገልብቶ የንፁህ መጠጥ ውሃ አጎልግሎት የሚያበረክተውን ፕሮጀክት፤ የፊታችን ሰኞ ረፋዱ ላይ ያስመርቃል፡፡ የጎለበተው ምንጭ ለአምስት ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥም የድርጅቱ መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የደረቅ ቆሻሻ  አወጋገድ፣ የውሃ አቅርቦትና የንፅህና አጠባበቅ ፕሮጀክትን በሚደግፈው “ሲቪል ሶሳይቲ ስፖርት ፕሮግራም” ድጋፍ የተሰራ ሲሆን በተለይ በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የውሃ እጥረት የሚንገላቱ እናቶችና ህፃናትን እፎይ ያሰኛል ብለዋል፤ ወ/ሮ መሰረት፡፡
የአካባቢው ህዝብ በጉልበት፣ በእውቀት በጥበቃ ስራና በቁፋሮ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ይህ እገዛ ባይገኝ ኖሮ ፕሮጀክቱ 900 ሺህ ብር ይወስድ ነበር ብለዋል፡፡

- በውጭ አገራት ወታደራዊ ካምፖችን እንደማታቋቁም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ነበር
- ለመርከቦቼ ነዳጅ መሙያና ለጦር መኮንኖቼ መዝናኛ ላደርገው ነው ብላለች

   በውጭ አገራት ወታደራዊ ካምፖችን የማቋቋም ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ የቆየችው ቻይና፣ የሎጅስቲክስ ማዕከል ነው ያለችውን የመጀመሪያውን ወታደራዊ ካምፕ በጅቡቲ ለማቋቋም ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተነጋገረች እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ወታደራዊ ካምፑ ለቻይና የባህር ሃይል መርከቦች የነዳጅና የሌሎች ሎጅስቲክሶች አቅርቦት የማሟላትና አገሪቱ በኤደን ባህረ ሰላጤ በምታከናውናቸው የጸረ-ስለላ ተልኮዎች ላይ ለተሰማሩ የጦር መኮንኖችና መርከበኞች በመዝናኛ ማዕከልነት የማገልገል አላማ ይዞ እንደሚቋቋም የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ወታደራዊ ካምፑ መቋቋሙ የቻይና የጦር ሃይል አለማቀፍ ግዴታዎቹን እንዲወጣ እንዲሁም አለማቀፍና ክልላዊ ሰላምና መረጋጋትን በማስጠበቅ ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ  የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል፡፡
የቻይና የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማቲክና ወታደራዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ፣ አገሪቱ ለረጅም ጊዜያት ስትከተለው የኖረችውን በሌሎች አገራት ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያለማድረግ ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተዳፈረችው እንደሆነ ያሳያል ብሏል ዘገባው፡፡
በቅርቡ በማሊ በተከሰተውና 19 ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የሽብር ጥቃት፣ 3 ቻይናውያን መሞታቸውን ተከትሎ፣ ቻይና ጽንፈኛ ቡድኖች በአፍሪካ አገራት የሚያደርሱትን ጥቃት ለመታገል ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ዜጎቿ የሞቱባት ቻይና ከጸረ-ስለላ ተልዕኮ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በማሊና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በተሰማሩ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ወታደሮቿን ማሰማራቷን ያስታወሰው ዘገባ፣ በጅቡቲ ከዚህ ቀደም የተቋቋሙ የአሜሪካ ጥምር ግብረ ሃይልና የፈረንሳይ ወታደራዊ ካምፖች እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡