Administrator

Administrator

Sunday, 03 October 2021 18:25

የግጥም ጥግ

መልሱ አልተሰጠም
አንተነህ ግዛው

ምን ይረባታል፣ መልሱ ቢጠፋኝ
እያዟዟረች፣ የምታለፋኝ

አጉል ጠያቂ - ልክ የለው ሲጠም
ያደናግራል - እያማረጠም
ልማድ ሆኖበት - ዙሪያ መጠምጠም
መልስ ነው ይላል - መልስ አልተሰጠም

መላም የለው፣ መልስም የለው፣ መላም የለው፣ የሷስ ነገር
ሆነ ብሎ ማወናበድ፣ ሆነ ብሎ ማደናገር

የአንዳንዱ ጠያቂ፣ ንፍገትስ ይደንቃል
መርጠህ መልስ ብሎ፣ መልሱን ይደብቃል
ትክክል የመሆን - ዕድልን ነፍገሽኝ
ምረጥ ትይኛለሽ - መልሱን ሸሽገሽኝ

መላም መልስም የለው - መላም የለው የሷስ ነገር
ሆነ ብሎ ለማሳሳት - በጥያቄ ማደናገር
አስመርጣ መጣል ሲያምራት - ታዞራለች ዙሪያ ጥምጥም
መልስ ብላ ስታስጨንቅ - ልከኛውን መልስ አትሰጥም

ያንቺ ቢጤ ፈታኝ፣ አውቆ ሲያሰናክል
መልስ አልተሰጠምን፣ ያደርጋል ትክክል
ፈትነሺኝ ላላልፍ፣ አልወጣም አልወርድም
ጠማማ ጥያቄሽ፣ ቀና መልስ አይወልድም።

Sunday, 03 October 2021 18:23

የስኬት ጥግ

ህልም በአንዳች ተዓምር እውን አይሆንም፤ ትጋት ቁርጠኝነትና  ላብን ይጠይቃል፡፡
ኮሊን ፖውል
ስኬትህም ሆነ  ደስታህ ያለው በእጅህ ላይ ነው፡፡
ሔለን ከለር
ስኬት ፈጽሞ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡
ጃክ ዶርሴይ
ልታልመው ከቻልክ፣ መተግበር አይሳንህም፡፡
ዋልት ዲዝኒ
ስኬት ጉዞ ወይም ሂደት እንጂ መዳረሻ አይደለም፡፡
አርተር አሼ
ስኬት መቀዳጅት የምትሻ ከሆነ፤ ህልምህን ፈጽሞ አትጠራጠረው፡፡
ሪያን ዲ ሶውዛ
ስኬት የሚጣፍጠው ከሌሎች ጋር ሲጋሩት ነው፡፡
ሆርድ ሹልትዝ
ዝናና ስኬትን አታምታታ፡፡ ማዶና አንዷ ናት፤ ሔለን ከለር ደሞ ሌላዋ፡፡
ኢርማ ቦምቤክ
ስኬት ወዳንተ አይመጣም፤ አንተ እሱ ወዳለበት ትሄዳለህ እንጂ፡፡
ያልታወቀ ሰው

የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በ2 ወራት ውስጥ ብቻ የዘረፉትን 39 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ ባለፉት 3 አመታት በድምሩ ከ73 ሚሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት መዝብረዋል በሚል ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የቀረበባቸውን ውንጀላ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው በማለት እንዳጣጣሉት ተዘግቧል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር፣ ባለፈው ሳምንት ባወጡት መረጃ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የህዝብን ገንዘብ እየዘረፉ ለግል ጥቅማቸው እንደሚያውሉ መናገራቸውን ያስታወሰው አልጀዚራ፤ የአገሪቱ መንግስት ግን ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ውንጀላቸው በአለማቀፍ ደረጃ የተከፈተብኝ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ሲል እንዳጣጣለው ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን አሊያ ሎሙሮ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ውንጀላው የደቡብ ሱዳንን መረጋጋት የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች ሴራ አካል ነው፤ ዘረፋው ቢፈጸም እንኳን ህዝቡ ይጠይቀናል እንጂ ተመድ ምን ጥልቅ አደረገው ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ፕሬዚዳንት ሳል ኬር ግን፣ እ.ኤ.አ በ2012 ባደረጉት ንግግር፣ የአገሪቱ ባለስልጣናት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት ወደ ውጭ አገራት ማሸሻቸውን በአደባባይ ማመናቸውን ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

የአለማችን እጅግ ደሃ አገራት ወደባሰ ድህነት መግባታቸው ተነገረ

በየአመቱ በመላው አለም እየተመረተ ለተጠቃሚዎች ከሚቀርበው ምግብ ውስጥ 17 በመቶ ያህሉ ወይም 1.3 ቢሊዮን ቶን ምግብ ጥቅም ላይ ሳይውል ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንደሚገባ፣ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
811 ሚሊዮን ህዝብ የረሃብ ተጠቂ በሆነባት አለም በየአመቱ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ መባከኑ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብሏል፡፡
የምግብ ብክነት ያደጉ አገራት ብቻ ሳይሆን የድሃ አገራትም ችግር ነው ያለው ድርጅቱ፤ 2 ቢሊዮን ያህል ሰዎች የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ተጠቂዎች በሆኑባት አለም የሚባክነው ምግብ ጉዳቱ የከፋ ነው ብሏል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፤  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባኤ ሰሞኑን ባወጣው የ2021 የፈረንጆች አመት ሪፖርቱ፣ ከአለማችን አጠቃላይ ህዝብ 15 በመቶ ያህሉ የሚኖርባቸው 46 የአለማችን እጅግ ደሃ አገራት በአመቱ ወደባሰ ድህነት መግባታቸውን አስታወቀ፡፡
አገራቱ በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚያቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የነፍስ ወከፍ ገቢ ድርሻቸውን አብዛኞቹ አገራት ከወረርሽኙ በፊት ወደነበረው ለመመለስ አምስት አመትና ከዚያ በላይ ጊዜ ሊፈጅባቸው እንደሚችልም አሳስቧል፡፡
አገራቱ በ2020 የፈረንጆች አመት ያስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት በሦስት አስርት አመታት ታሪካቸው እጅግ ዝቅተኛው እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አገራቱ ምርታቸውን ማሳደግና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በአለማቀፍ ንግድ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አመልክቷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ እጅግ ድሃ አገራት ብሎ ከሚጠራቸው የአለማችን 46 አገራት ውስጥ  33ቱ በአፍሪካ፣ 9ኙ በእስያ፣ 3ቱ በፓሲፊክ አይስላንድ አገራት፣  አንዷ ደግሞ በደቡብ አሜሪካ እንደምትገኝም መረጃው ያሳያል፡፡

የሰሜን ኮሪያ መንግስት ሁዋሶንግ 8 የተባለ እና በአለማችን በግዝፈቱ ሶስተኛ ደረጃን እንደሚይዝ የተነገረለትን እጅግ ፈጣን ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ ማስወንጨፉን ባለፈው ረቡዕ በይፋ አስታውቋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ማክሰኞ ዕለት እጅግ ፈጣን እንደሆነ የተነገረለትን ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማድረጉን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡ ያስነበበው ቢቢሲ፤ የጦር መሳሪያው የአገሪቱን የመከላከያ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድገዋል መባሉንም ገልጧል፡፡
ሰሜን ኮርያ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚሳኤል ሙከራ ስታደርግ ይህ ለሶሰተኛ ጊዜ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከዚህ በፊት አዳዲስ ክሩዝ እና ከባቡር ላይ የሚወነጨፉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን መሞከሯንም አስረድቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አገራቸውን ወክለው በመገኘት ንግግር  ያደረጉት ኪም ሶንግ፤ ሰሜን ኮርያ ራሷን ለመከላከልና የሰላምና ደህንነት ሁኔታዋን አስተማማኝ ለማድረግ  ብሔራዊ መከላከያ እየገነባች እንደምትገኝ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ኳታር ኤርዌይስ ባለፈው የፈረንጆች አመት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አመታዊ ገቢው በ4 ቢሊዮን ዶላር እንደቀነሰ ባለፈው ሰኞ ቢያስታውቅም፣ በአመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ አየር መንገድ መባሉን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ስካይትራክስ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ያደረገውን የአመቱ የአለማችን ምርጥ አየር መንገዶች ዝርዝር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣  አየር መንገዱ ለ6ኛ ተከታታይ አመት ነው የአመቱ ምርጥ ተብሎ ለመመረጥ የበቃው፡፡ ሲንጋፖር ኤርላይንስ፣ ኤኤንኤ ኦል ኒፖን ኤርዌይስ፣ ኤሜሬትስ፣ ጃፓን ኤርላይንስ፣ ካቲ ፓሲፊክ፣ ኢቫ ኤር፣ ኳንታስ ኤርዌይስ፣ ሃኒያን ኤርላይንስና ኤር ፍራንስ በአመቱ የስካይትራክስ የአለማችን ምርጥ አየር መንገዶች ዝርዝር ውስጥ ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የዓለማችንን ቁጥር 1 ስኬታማ ሰዎች ታሪክ ስትመረምሩ፣ ማናቸውም ቢሆኑ በአንድ ጀንበር የስኬት ማማ ላይ እንዳልወጡ ትገነዘባላችሁ። ብዙዎቹ አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ውድቀትና ሽንፈት አጋጥሟቸዋል፡፡ ሥራ ከመቀጠራቸው በፊት ብቁ እንዳልሆኑ እየተነገራቸው ብዙ ጊዜ ተባረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ለመግባት ደጋግመው ገና በታዳጊነቱ አመልክተው በመግቢያ ፈተናዎች ላይ ደጋግመው ይወድቃሉ፡፡ የተለያዩ ቢዝነሶች ጀምረው በኪሳራ ዘግተዋል፡፡ የማታ ማታ ግን የስኬት ማግ ላይ ይወጣሉ ወድቀው ወይም ተሸንፈው አይቀሩም፡፡
የአሁኑ ተራማጅ ኩባንያ አፕል፤ በሁለት ሰዎች ትብብር፣ በጋራዥ ውስጥ ነበር የተቆረቆረው፡፡ ከዓመታት በኋላ፤ ከ400 በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድር፣ የ2.ቢሊዮን  ዶላር ኩባንያ ለመሆን በቅቷል።
ስቲቭ ጆብስ ግን ራሱ ከመሰረተው ኩባንያ ለማመን በሚያዳግት መልኩ ተባረረ፡፡ ይሄን ጊዜ Next እና Pixar የተሰኙ ተጨማሪ የቢዝነስ ዘርፎችን ፈጠረ። የማታ ማታም፣ ወደ ተባረረበት ወደመሰረተው ኩባንያ ተመልሶ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለመሆን በቃ፡፡ በወቅቱ ባይታየኝም፣ ከኩባንያው መባረሬ በእጅጉ ጠቅሞኛል ይላል-ስቲቭ ጆብስ፡፡ ከኩባንያው መባረሩ ተስፋ አላስቆረጠውም። ለተጨማሪ ፈጠራና ትጋት አነቃው እንጂ።
የሃርቫርድ ትምህርቱን አቋርጦ የወጣው ቢል ጌትስ፤ ከሌሎች ጋር በመሆን Traf-o- Data የተሰኘ የበኩር ኩባንያ አቋቁሞ ነበር። ምን ያደርጋል? በአመራር ክህሎት ማነስ በኪሳራ ተዘጋ፡፡ ነገር ግን ለኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ በነበረው ክህሎትና ጥልቅ ፍቅር የተነሳ፤ ፈር ቀዳጁን የሶፍትዌር ኩባንያ፣”ማይክሮ ሶፍት” ለመመስረት በቃ፡፡ ውድቀቱንም ወደ ስኬት ለወጠ፡፡ በ31 ዓመት ዕድሜውም የዓለማችን ወጣቱ ቢሊዬነር ለመሆን ቻለ። ቢል ጌትስ በራሱ አንደበት ሲናገር  “ስኬትን ማጣጣም ሸጋ ነው፤ ግን ከውድቀት መማር የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡” ይላል።
አብርሃም ሊንከን ለሽንፈትና ውድቀት እንግዳ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በ1831 በቢዝነስ ሥራው ኪሳራ ገጥሞታል፡፡ በ1836 ዓ.ም በነርቭ ህመም ክፉኛ ተሰቃይቷል፡፡ በ1856 ዓ.ም ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ተወዳድሮ ተሸንፏል።
ይሄ ሁሉ ውድቀት ግን ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡ ደጋግሞ ከመሞከርም አላቦዘነውም፡፡ በዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ በ1861 ዓ.ም በምርጫ ተወዳድሮ የአሜሪካ 16ኛው ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ በቃ፡፡
የቱንም ያህል ሽንፈት ብትጋፈጥ፣ ስኬት ከመቀዳጀት የሚያግድህ ነገር የለም፡፡
የሚኪ ማውዝ ፈጣሪ የሆነው ዋልት ዲዝኒ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያቋረጠው የአሜሪካ ጦር ሰራዊቱን ለመቀላቀል ነበር፤ ግና አልተሳካለትም? ከትምህርቱም ከውትድርናውም ሳይሆን ቀረ ከቀደምት ቢዝነሶቹ አንዱ የነበረውን “Lough-0-Gram Studios” የዘጋው በአመራር ችሎታ ማነስ  ከስሮ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ደግሞ “ በቂ የፈጠራ ችሎታ የለህም” ተብሎ ከሚሰራበት የሚዙሪ ጋዜጣ መባረሩ ተዘግቧል፡፡
ዛሬ ግን ዲዝኒ፣ የብዙ ትውልድ ህጻናት ትውስታና ህልም ለመሆን በቅቷል። ዲዝኒ ገና ወደ ፊት አያሌ መጪ ትውልዶችን ማዝናናቱን ይቀጥላል። ልብ በሉ! ከስኬታማ ሰው ጀርባ አያሌ ያልተሳኩ ዓመታት አሉ፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች የተካተቱበትን ካቢኔ አቋቋመ። ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ በተጨማሪ፤ ሁለት የፌደራል ሚኒስትሮችም የአዲሱ ካቢኔ አካል ሆነዋል።
በከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅራቢነት፤ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 18፤ 2014 ሹመታቸው የጸደቀላቸው ተሿሚዎች ብዛት 26 ነው። ከሃያ ስድስቱ የካቢኔ አባላት መካከል ስምንቱ ሴቶች ናቸው። የካቢኔ አባላቱ ሹመት የአብዛኞቹን የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ አግኝቷል።
በአዲሱ የአዲስ አበባ ካቢኔ ምስረታ፤ የኢዜማ እና የአብን አመራሮች መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ሰኔ 14፤ 2013 በተደረገው ምርጫ፤ ገዢው ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ያሉትን 138 መቀመጫዎች በሙሉ ጠራርጎ በማሸነፉ ተቃዋሚዎች ወደ ኃላፊነት የመምጣት ዕድላቸውን ያጨለመ መስሎ ነበር።
አዲሷ የአዲስ አበባ ከንቲባ፤ በካቢኔያቸው ያካተቷቸውን ተሿሚዎች ዝርዝር ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ግን ይህን አመለካከት የሚያፈርስ አካሄድ መከተላቸው ታይቷል። ገዢው ፓርቲ የህዝብን ድምጽ ለማክበር ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደሚያሳትፍ ቃል መግባቱን ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ ይህንን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምስረታ ላይ ተግባራዊ ማድረጉን አስረድተዋል።   
በዚህ ውሳኔ መሰረት በአዲስ አበባ ካቢኔ ውስጥ ሹመት ያገኙት የኢዜማ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ እና የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ናቸው።  አቶ ግርማ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን እንዲመሩ ሲሾሙ፤ አቶ የሱፍ ደግሞ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ኃላፊ ሆነዋል።
ሁለቱም ተሿሚዎች፤ የከተማይቱ የካቢኔ አባላት ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት በአካል አለመቅረባቸው አጠያይቋል። አቶ ግርማ ሰይፉ በሹመት ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳልተገኙ የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይ
ሹመቱን በተመለከተ ፓርቲያቸው ያስተላለፈው ውሳኔ ምን እንደነበር የተጠየቁት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ በኢዜማ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውሳኔ የሚሰጠው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን ገልፀዋል። የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ የሚካሄድ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ናትናኤል፤ በዚህም ምክንያት የአቶ ግርማ ሹመት በፓርቲው ገና አልጸደቀም ብለዋል።
ኢዜማ “ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመስራት መርህ አለው” የሚሉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ የአቶ ግርማ ሹመት በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሳይጸድቅ፤ በአዲስ አበባ ካቢኔ ምስረታ ላይ መነገሩ “በመርህ ደረጃ የሚያመጣው ችግር የለም” ብለዋል። አካሄዱን ግን “በአፈፃፀም ደረጃ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት” ሲሉ ጠርተውታል። በጉዳዩ ላይ በኢዜማና በገዢው ብልፅግና መካከል የመረጃ ክፍተት እንደነበርም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።  
ዛሬ የተመሰረተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ሁለት የፌደራል መንግስት ባለስልጣናትን ማካተቱ ሌላው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል። የአዳነች አቤቤን ካቢኔ የተቀላቀሉት ሁለት ሚኒስትሮች የመከላከያ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ሲመሩ የነበሩ ባለስልጣናት ናቸው።
አቶ ለማ መገርሳን ተክተው የመከላከያ ሚኒስቴር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ቀነዓ ያደታ፤ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሂሩት ካሳው ደግሞ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮን የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
በዛሬው የካቢኔ ምስረታ ከታዩ ነገሮች አንዱ ቀደም ሲል ተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ይዘው የነበሩ ባለስልጣናት በነበሩበት እንዲቀጥሉ የመደረጉ እውነታ ነው። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ሆነው ላለፈው አንድ ዓመት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ጃንጥራር አባይ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነዋል።  
አቶ ጃንጥራር በዛሬው ሹመት ከምክትል ከንቲባነት በተጨማሪ የአዲስ አበባ የስራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊነትን ደርበው እንዲሰሩ ተሹመዋል። የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ጥራቱ በየነ፤ በነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ስልጣናቸው ቀጥለዋል። የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዘላለም ሙላቱ እና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊው አቶ ሙሉጌታ ተፈራም እንዲሁ በያዙት ቦታ እንዲቀጥሉ ተወስኗል።
ዛሬ አዲስ በተመሰረተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አወቃቀር መሰረት፤ አቶ ጥራቱን ጨምሮ አራት የስራ ኃላፊዎች የምክትል ከንቲባ ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። በገንዘብ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል።
ሌላኛዋ የምክትል ከንቲባ ማዕረግን የያዙት ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ደግሞ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በኃላፊነት እንዲመሩ ተሹመዋል። በአዲስ አበባ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊነት ስልጣን ያገኙት ወይዘሮ ነጂባ አክመልም የምክትል ከንቲባ ማዕረግን በማግኘት ሶስተኛዋ ሴት ሆነዋል።
ምክር ቤቱ የካቢኔ አባላትን ሹመት ከመመልከቱ አስቀድሞ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት እና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመዘርዝር የወጣውን አዋጅ አጽድቋል። በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው እና በሰባት ክፍሎች እና 100 አንቀጾች የተዋቀረው አዲሱ አዋጅ፤ በከተማዋ ያሉትን የአስፈጻሚ አካላት ቁጥር ከ61 ወደ 46 ዝቅ አድርጓቸዋል።
(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ለምድር ለሰማይ የከበደ የንጉሥ ልጅ፣ ያማረ ሠረገላውን አሳጥቦ፣ አስወልውሎ  ታጭታልሃለች የተባለችውን ቆንጆ ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያይ፤ አሽከር አስከትሎ ወደ ሩቅ  አገር ሊሄድ ተነሳ።
አባቱ የተከበሩ አንቱ የተባሉ ስመ-ጥር ጀግና፣ ከትውልድ ትውልድ ከሚከታተለው ሥርወ-መንግስት የመነጩ፣ የተከበሩ ሰው ናቸው። ልዑሉም ሊሰናበታቸው ወደ ዙፋናቸው ቀረበና፤
ልዑሉ- “ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ ወደ ሩቅ አገር መጓዜ ነውና ፈቃድ ይሰጠኝ?”
ንጉሡም- “ወደ የት ልትሄድ ተነሳህ?”
ልዑል- “ወደ ሩቅ አገር ነው የምሄደው።”
ንጉሥ- “እሺ መሄዱንስ ሄድክ፣ ምን ልታደርግ ነው የምትሄደው?”
ልዑሉ “ንጉሥ ሆይ! ታጭታልሃለች የተባልኳትን ቆንጆ ልዕልት፣ ቁንጅናዋንና ሰብዕናዋን ሳላይና ሳላውቅ ላገባ አልሻምና ሄጄ ማረጋገጥ ይኖርብኛል”።
ንጉሥ- “እኛ ለልጃችን ክፉና የማይሆን ነገር እንመኛለን?”
ልዑል- “አይደለም ንጉሥ ሆይ! የእናንተን ደግነት ከቶም ተጠራጥሬ አላውቅም። ሆኖም በእናንተ ውሳኔ ላይ የእኔም አስተያየት ቢታከልበት፣ ነገሩን ያጠነክረዋል እንጂ አያላላውም! ዞሮ ዞሮ ከእናንተ ፍቃድ አልወጣም።”
ንጉሥ- “ደህና፣ ሂድ። ለማንኛውም አንድ አሽከር በቅሎ ይዞ ይከተልህ። ደህና ግባ።”
ልዑሉ ምስጋና አቅርቦ የተመደበለትን አሽከር ይዞ መንገዱን ቀጠለ።
ከከተማው ወጣ እንዳሉ አንድ መንገደኛ ያገኛሉ፤
 መንገደኛውም - “እባክህ ጌታዬ አፈናጠኝና ጥቂት መንገድ አብረን እንግፋ” አለው።
ልዑሉም ደግ ሰው ነበርና፤
“ና ውጣ” አለው።
አሽከርየው ግን፣
“እኔ ይህ ሰው ከእርስዎ ጋር መሄዱ ቅር ብሎኛል። ደረጃው አይፈቅድም “ አለው።
ልዑሉም- “ግዴለም። ይሄ ሰውና እኔ በሰውነታችን አንድ ነን። ምናልባትም የጊዜና የቦታ ጉዳይ ሆኖ እንጂ የተሻለ እጣ-ፈንታ ያለው ሰው ይሆናል። ስለዚህ ይውጣና አብሮን ይሂድ” ሦስቱም አብረው ተያይዘው መንገድ ቀጠሉ።
ጥቂት እንደተጓዙ ተፈናጣጩ ሰው ልዑሉን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡
 “እንዴት ያለህ ደግ ሰው ነህ? ምንም የማታውቀኝን ሰው መጫንህ አስገርሞኛል። አንተ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው።
ልዑሉም- “እኔ ልዑል ነኝ” አለው።
 ተፈናጣጩ ሰውም- “ልዑል ማለት ምን ማለት ነው?” ሲል ጠየቀው።
ልዑል- “ልዑል ማለት በየመንገዱ ሰዎች ቆመው የሚያሳልፉት እጅ የሚነሱት ነው፤ አሁን መንገድ ላይ የሚሆነውን ተከታተል” ሲል መለሰለት።
ጥቂት እንደሄዱ እውነትም ሰው ሁሉ ቆሞ፣ እጅ እየነሳ ያሳልፋቸው ጀመር።
ልዑሉ ወደ ተፈናጣጩ ዞሮ፤
“አሁንስ ልዑል ማን እንደሆነ አወቅህ?”
ተፈናጣጭ- “አዎን”
ልዑል- “ማን ነው?”
ተፈናጣጭ- “እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ ነሃ” አለው።
*   *   *
የአንድን አገር ልዑል አገሬው ሳያውቅ ከቀረ ትልቅ እርግማን ነው። ተገዥው ገዥው ማን እንደሆነ ሳያውቅ የሚኖርበት ሁኔታ አለ እንደ ማለት ነው። አሳሳቢ ሁኔታ አለ እንደ ማለትም ነው። በዚህ ዓይነት መንፈስ፣ መሪው ተመሪውን  ህዝብ  እንደምን ሊያውቀው ይችላል?  ስለዚህ፤ ምንም እንኳን የሥራ ድርብርብና ጫና ሰንጎ ሊይዛቸው ቢችልም፤ የአገራቸውን ፖለቲካዊ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ነገረ-ሥራውን ሁሉ በሚገባ ማጤን ይገባቸዋል፡ ለዚህም ዋናና ቁልፍ ናቸው ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ ከሙያው ጋር አግባብ አላቸው የሚባሉ ሁነኛ ምሁራንን አሰባስቦ መምከር ነው። የሚቀጥለው ዋና ነገር የምሁራኑን አስተያየት በቅጡ ማዳመጥና ስራዬ ብሎ ለሥራ መዘጋጀት ነው። ከዚህ በኋላ እንግዲህ አስፈላጊውን ግብረ-ሃይል በተጠናከረ ሁኔታ አደራጅቶ ማሰማራት  ነው። የዚህ  ሁሉ ጉዳይ መጠቅለያው ቆራጥ አቋም ነው። ቆራጥነትም ቢሉ ዘላቂና የተቀናጀ መሆን ይኖርበታል “Sustainable and Integrated” እንዲሉ”፡፡
ይህ በፈንታው አንድ ፈታኝ ጥያቄ ላይ ያነጠጥራል። ይኸውም ቁጥጥር ማድረግና የስራ ግምገማን ማካሄድ ነው። (Monitoring and Evaluation እንዲሉ)  ቀጥሎ ደግሞ ሳይታክቱ “የሰራነው ሁሉ የት ደረሰ?” ማለት ያሻል። ችግኝ ተክሎ ማደግ አለማደጉን አለመከታተል፣ ካለመትከል እኩል ነው፡፡ ቸልተኝነትም አንድ የልማድ ዘርፍ ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግኸው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሃል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ  ያጠፋል
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል” ይለናል።
ከላይ የተዘረዘሩትን አበክረን ስንገነዘብ ልማድ በእኛ ላይ በሰለጠነ ቁጥር- በተለይ አሉታዊው ፈሊጥ- ሚዛናዊነትን ያሳጣናል። ያ ደግሞ ሁለንተናዊነታችንን ይሰልብብናል። ስለዚህ በጥናት ላይ መመሥረት ዋና ነገር ነው። ያንን በፅናት ማጠናከር ደግሞ ለዘላቂነት ብርቱ መነሻ ነው።
ጉዞህን በእርምጃህ መጠን ለካ፣ አልጋህን በቁመትህ ልክ አድርግ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ማረፍ ካለብህ እረፍ (Rest If you Must) ሆኖም አርፈህ መቅረት የለብህም። ቆይተህ መንቀሳቀስ፣ ብሎም መለወጥ ግዴታህ መሆኑን አትርሳ። ሊቃውንት (A change is as good as rest)  ለውጥ የእረፍት መልካም እኩያ ነው፤” የሚሉን ለዚህ ነው።
ወጣም ወረደም ህይወታችን ይለመልም ዘንድ ምንጊዜም ጥናትና ጽናትን ከልቡናችን አለመነጠል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ሳናሰልስ እናስብ!
አዲሱ ዓመት የሰላምና የፍቅር እንዲሆን ትምህርታችንን ይግለጥልን!

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን ያፈራው ቻይና ሰራሹ የአጫጭር ቪዲዮዎች ማሰራጫ ድረገጽ ቲክቶክ ወርሃዊ ቋሚ ደንበኞች ቁጥር ከ1 ቢሊዮን ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በመላው አለም ከፍተኛ ተወዳጅነት ካገኘባቸው አገራት መካከል አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ብራዚልና የደቡብ ምስራቅ እስያ አገራት እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ ቲክቶክ ምንም እንኳን በአሜሪካና በአንዳንድ አገራት የተለያዩ የገደብ ውሳኔዎች ቢተላለፉበትም፣ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ግን በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እስካለፈው 2020 ሃምሌ ወር 689 መድረሱን ያስታወሰው ዘገባው፤ አፕሊኬሽኑ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ከ2 ቢሊዮን ጊዜያት በላይ ዳውንሎድ መደረጉንም አስታውሷል፡፡