ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ (40)

Saturday, 29 May 2021 14:37

ታሪክን የሁዋሊት

Written by

     በአገሮች መካከል የሚፈጠረውን ግንኙነት የሚወስኑት ሶሰት ነገሮች ናቸው፤ ያገሮች አቅም፥ የጊዜው ሁኔታና የመሪዎች ችሎታ፡፡ ከአድዋ ድል በሁዋላ ኢትዮጵያ የረባ ንብረት ሳታፈራ፤ ዳማ ፈረሷን በታንክ ሳትቀይር ተዘናግታ ቆየች፤ ጣልያን በሞሶሎኒ መሪነት ሁለተኛውን ወረራ ፈጸመች፡፡ ያገራችን እናትና አባት አርበኞች በሚያስደንቅ ወኔ ተከላከሉ፤ ግን በጦርነቱ መሸነፍ አልቀረላቸውም። ቀዳማዊ ሃይለስላሴም ነገሩ እንዳልሰላ ሲያውቁ ሰራዊታችውን በትነው፥ ዘመድ ወዳጅ ሰብስበው ወደ አውሮፓ ተሰደዱ፤ የመንግስታት ማህበር ለሚባለው፥ የጉልቤ አገሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተመሰረተው ድርጅት ፊት አቤቱታ አቀረቡ፤ ሃያላን አገሮች ሀይለኛዋን ጣልያንን ከማስቀየም ቺስታዋ ኢትዮጵያ “እንደ ፍጥርጥሯ” ትሁን ብለው ፊታቸውን አዞሩባት፤ ግርማዊነታቸው በኢንግላንድ ብርድ እየማቀቁ፥ የአዱገነትን ጣይ እየናፈቁ፤ ያባቶቻቸውን አምላክ ተአምር እየተጠበቁ በስደት ተቀመጡ፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ አርበኞች በየፊናቸው አገራችንን ከጣልያን ያገዛዝ ቀንበር ለማውጣት ተፍጨረጨሩ፤ ምንም ጀግንነታቸው ባይጠረጠር የቄሳርን መንግስት ማስወገድ የሚሳካላቸው አልሆነም፤ ኢትዮጵያ ለቀጣይ መቶ አመታት የጣልያን ርስት ሆና አንደምትቆይ ተተነበየ፡፡
በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ግን ድንገት ነገሮች ተለወጡ!
ጀርመን የሁለተኛው አለም ጦርነትን አውሮፓ ላይ መርቃ ከፈተችው፤(1939) ምድረ አውሮፓ በሁለት ምድብ ተከፍሎ መፈሳፈስ ጀመረ፤ ጣልያን ሲያቀብጣት ከጀርመን ጋር ተሰለፈች፤ አለቀላት የተባለቺው ኢትዮጵያ ፈጣን ሎተሪ ወጣላት፤ በተቃራኒው ምድብ ላይ የቆመቺው ታላቂቱ ብሪታኒያ በምስራቅ አፍሪካ በቅኝ የምትገዛችው አገሮች (ግብጽ፤ ሱዳን፤ ከፊል ሱማሊያ) በሞሶሎኒ መዳፍ ከመውደቃቸው በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለመዝመት ወሰነች፡፡ ዊንስተን ቸርቺል ግርማዊነታቸውን ከአንግሊዝና ከሱዳን ሰራዊት ጋር አሰልፎ አዘመታቸው፤ ጣልያን ፒያሳን በገነባበት አጁ ሃያ ሁለት ማዞርያን ሳይገነባ(ልን) በእንግሊዝና ጦቢያ አርበኞች ጥምረት በካልቾ ተመቶ ተባረረ፡፡
እንግሊዞች ለከፈልነው መስዋእትነት ዋጋ እንፈልጋለን አሉ፤ ኢትዮጵያውያንም ከኪሳቸው አውጥተው ነጻነታቸውን ከፈሉ ፤ እነ ቸርቺል ቀዳማዊ ሃይለስሳሴን ዙፋን ላይ አስቀምጠው አገሪቱን ተቆጣጠሩ፤ ጦሩ፤ ፖሊሱ፤ ስልኩ ፖስታው ባቡሩ በእንግሊዞች መዳፍ ገባ፡፡ ግርማዊነታቸውም” ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” እያሉ አንጎራጎሩ፤ ግን ጮሌ ናቸውና ቀንበሩን የሚሰበሩበትን መንገድ ማብሰልሰል ጀመሩ፤ በጉዋሮ በር፤ የእንግሊዞችን የመረጃ ከበባ ጥሰው አጋዥ ፍለጋ ወጡ፤ ለአጋዥነት ወይም ለጭንቅ ደራሺነት የተመረጠቺው ደግሞ አመሪካ ነበረች፤ የኦክስፎርድ ምሩቁ ልጅ ይልማ ደሬሳ የዋየታውስ ባለስልጣኖችን ይጀነጅን ዘንድ ወደ ዋሸንግተን ተላከ፤ ጅንጀናው ሰመረ፤ አሜሪካኖቹ፤ ጣልያን ጣጥሎት የሄደውን ትራክተር ወርሰው፤ ኢትዮጵያ የምትሰጣቸውን መሬት አርሰው በጦርነት ላይ ላሉ ወታደሮቻቸው ለስንቅ የሚሆን ቢያመርቱ እንደሚያዋጣቸው አሰሉ፤ በምትኩ፤ የአንግሊዝን ቀንበር ለማላላት አገዙ፤ ለኢትዮጵያ መገበያያ ብር አተሙ፤ ገንዘብ፤ ጠመንጃ ወዘተ መለገስ ጀመሩ፤ እንዲህ እንዲህ እያለ፤” እሬትና - ማር” የሆነው የሁለቱ አገሮች የትስስር መሰረት ተጣለ፡፡



Saturday, 08 May 2021 14:11

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by

    ክፍል 1 የአቶ ሌንጮ ለታ የመገንጠል መብት ንድፈ ሐሳባዊ ብዥታ



            “አንቀፅ 39ን አነሳህ አላነሳህ ገፊ ምክንያት ካለ ለመገንጠል የፈለገ መገንጠሉ አይቀርም። ሕዝብ እኮ ያስባል ፣ ያሰላስላል። እኩልነትን የማይቀበል ሀይል እስካለ ድረስ ወደድንም ጠላንም በወረቀት ተፃፈ አልተፃፈ መገንጠል ስራ ላይ ይውላል።”
(አቶ ሌንጮ ለታ፤ ፍልስምና 6 ገፅ 15)
አቶ ሌንጮ ለታ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ያሳዩት የአቋም ለውጥ በተወሰነ ደረጃ የሚደገፍ ነው። ነገር ግን የለውጡ መጠንና ንድፈ ሐሳባዊ ሚዛን  በብዥታዎች የተሞላ ነው ማለት ይቻላል። ማለትም ለውጡ ፅንሰ ሐሳባዊ ግልፅነት(Conceptual Clarity) ይጎድለዋል። ዝርዝር ውስጥ ከገባሁ ፅሁፌ ምናልባትም እስከ አምስት ክፍል ሊዘልቅ ይችላል፣ ነገር ግን እንዳይሰላቻችሁ እያሳጠርኩ በሁለት ወይም ቢበዛ በሦስት ክፍሎች ምልከታዬን አጋራችኋለሁ። (ማጣቀሻ መጽሐፍትን በመጨረሻው ፅሁፌ አስቀምጥላችኋለሁ።) ለአሁኑ አጀማመሬ ይህን ይመስላል፦
1. በእኔ ምልከታ፤ የአቶ ሌንጮ ዕይታ ከመገንጠል ንድፈ ሐሳቦች (Theories of secession) አኳያ ብዥታ ያጠላበት ነው። በአንድ በኩል አንቀፅ 39 ሕገ መንግስቱ ኖረ አልኖረ ጭቆና እስካለ ድረስ መገንጠል አይቀሬ ነው ይሉናል። ነገር ግን በአቶ መለስ ዋና አጋፋሪነት በአንቀፅ 39 ላይ የተካተተው የመገንጠል መብትና አቶ ሌንጮ ያስቀመጡት የመገንጠል ዓይነቶች ከመገንጠል ንድፈ ሐሳብ አኳያ ለየቅል ናቸው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 1 የሚለው እንደዚህ ነው፦
“ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡”
እዚህ ጋ “መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው" የሚለውን አስምሩልኝ። ይህ መብት ለመገንጠል ምናልባት ሂደታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን (Procedural requirements) ከማስቀመጥ ባለፈ የመገንጠል ጥያቄን ለማንሳት የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለም። ይህ ቅድመ ሁኔታ-አልባ የመገንጠል ጥያቄ የሚመደበው በ”Primary Rights Theory” ውስጥ ነው። ዕውቁ የመገንጠል ንድፈ ሐሳብ አጥኚ “Allen Buchanan” ይህን ቀዳሚ የመገንጠል መብትን ‘A no-fault political divorce’ በማለት ይገልፀዋል። በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሠረት፤ የመገንጠል መብቱ የተሰጠው ለማን ነው? የሚለውን ጥያቄንም መመለስ ግድ ነው። ማለትም የመብቱ ባለቤት (The Right holder) ማነው? ምላሹ በግልፅ ተቀምጧል። የአንቀፅ 39 ርዕስንና ንዑስ አንቀፅ 5ን መመልከት በቂ ነው፣ መብቱ የተሰጠው ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው። በንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ደግሞ ለሶስቱም የመብቱ ባለቤቶች የተሰጠው ትርጉም አንድና ወጥ ትርጉም ነው። ከዚህም ባለፈ የየክልሎቹ አከላል ለዚሁ ተመቻችቶ የተሸነሸነ ይመስላል። በ”Primary Right Theory” ሥር የመገንጠል መብቱ ለብሔር ሲሰጥ ንዑስ ንድፈ ሐሳቡ “Ascriptive Group Theory” ተብሎ ይጠራል። በሌላ አንፃር የመገንጠል መብቱ በብሔር ላይ ተወስኖ ሳይሆን ለምሣሌ በመልክዓ ምድር ተሰባጥረው ለሚኖሩ ሕዝቦች ሲፈቀድ ንዑስ ንድፈ ሐሳቡ “Associative Group Theory” ተብሎ ይጠራል።
Now, theoretical categorization of Article 39 is possible. በአጭሩ አንቀፅ 39 የሚመደበው በ”Primary Right theory” ውስጥ በ”Ascriptive Group Theory” ንዑስ ንድፈ ሐሳብ ሥር ነው። ቀደም ሲል በሌሎች ፅሁፎቼ እንደገለፅኩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገንጠል መብትን በዚህ መልኩ አጡዘውት ሕገ መንግስታቸው ውስጥ የከተቱት ሀገራት ሁለት ብቻ ናቸው። የኛዋ ኢትዮጵያና ከካሪቢያን በስተምሥራቅ የምትገኝ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ የምትባል ሚጢጢዋ ባለሁለት ደሴቶች ሀገር (53,000 ሕዝብ ብቻ ነው የሚኖርባት) ናቸው። በነገራችን ላይ “Ascriptive Group Theory” ላይ የተመሠረተ የመገንጠል መብት በዓለም አቀፍ ሕጎችም ሆነ በመገንጠል ንድፈ ሐሳብ አጥኚዎች ዘንድ ቅቡልነት የሌለው ከይሲው የመገንጠል መብት ነው። ይህ ፅንፍ የረገጠው የመገንጠል መብት የሀገርን የወደፊት ሉዓላዊ ሕልውናን ከተገማችነት የሚያፋታ (ዶ/ር ኤርሲዶ እንደሚለው)፣ ሁሌም ዜጎች የሀገራቸውን ነገ በጥርጣሬና በስጋት እንዲስሉ የሚያስገድድ ነው። እዚህ ጋ ሀገራት ሕገ መንግስታቸውን መቅረፅ ያለባቸው ወቅታዊውን ሁኔታ እየተመረኮዙ ነው የሚለውን የአቶ ፋሲል ናሆምን (ደራሲው የእሳቸውንም ቃለ መጠይቅ በመፅሐፉ አካትቷል) አመለካከት መቶ በመቶ መቀበል ያዳግታል። እንደሱ ከሆነ የሕገ መንግስቱ መሻሻልም በጣም ወቅታዊ መሆን አለበት። ለምሣሌ አሁን ባለው ሕገ መንግስት አንቀፅ 39ን ማሻሻል የሚታሰብ አይደለም። ማሻሻያውን ከአስሩ ክልሎች ዘጠኙ ደግፈው ለምሣሌ የሐረሪ ክልል ከተቃወመ ውሳኔው ፉርሽ ይሆናል (Veto power)። በእኔ ዕይታ፤ ለወቅታዊ ችግር ማሻሻያ ለማድረግ እጅግ አዳጋች የሆነውን ግትር ሕገ መንግስት መንደፍ ለቀጣዩ ትውልድ የማይፈታ እንቆቅልሽ እንደማስረከብ ይቆጠራል። ለዚህም ነው አሜሪካኖቹ ሕገ መንግስታቸው ወቅታዊ ሁኔታዎችን ማስተናገድ እንዳለበት ቢያምኑም ለ”Amendment” እና “Flexibility” ክፍት የሚያደርጉት። እነ አቶ ፋሲል ሕገ መንግስቱ ውስጥ አንቀፅ 39 እንዳይሻሻል አድርገው በነሐስ ቁልፍ ከቆለፉበት በኋላ “ወቅቱ አስገድዶን ነው” የሚል ሰበብ የሚያቀርቡት! ዓለም ሁሉ ገፍትሮት ወደ ዳር ያሽቀነጠረውን “Ascriptive Group Theory”ን በብቸኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ውስጥ የከተቱ የወቅቱ ሕገ መንግስት አርቃቂዎች በሰሩት ፀጉረ-ልውጥ ሥራ ሊያፍሩ ዘንድ ይገባል። “The drafters design the constitution, the next generation pays for it.” ያለው ማን ነበር?
እንግዲህ የአንቀፅ 39 ንድፈ ሐሳባዊ ዳራው ከላይ ያስቀመጥኩትን ይመስላል። አሁን ወደ አቶ ሌንጮ የመገንጠል ዕሳቤ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረት ምንነት ልወስዳችሁ ነው። መግቢያው ላይ እንደጠቆምኩት፤ አንቀፅ 39 ላይ የተቀመጠው የመገንጠል ንድፈ ሐሳባዊ ምድብና የአቶ ሌንጮ የመገንጠል አተያይ መሳ ለመሳ ናቸው። የአቶ ሌንጮ ለታ የመገንጠል ዕሳቤ ከአንቀፅ 39 በተለየ ቅድመ ሁኔታን በግልፅ ያስቀመጠ ነው። ይህን ቅድመ ሁኔታ እሳቸው መነሻ ላይ “ገፊ ምክንያት” ብለው ካስቀመጡ በኋላ በመቀጠል ገፊው ምክንያት ምን እንደሆነ ያስቀመጡት “እኩልነትን የማይቀበል ኃይል እስካለ ድረስ” በማለት ነው። በሌላ አባባል ጭቆና ባለበት የመገንጠል መብት ሊከበር ዘንድ ይገባል እንደማለት ነው። ይኼኛው አተያይ በ”Remedial Right Theory” ንድፈ ሐሳብ ውስጥ የሚመደብ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፣ አቶ ሌንጮ ምንም እንኳን በቃለ መጠይቃቸው እንደ ወትሮው ለኦሮሞ መብት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ሀገረ መንግስት እታገላለሁ ቢሉም ከGroup Theory አንፃር አሁንም እንደ ቀድሞው “Ascriptive” ናቸው። ለዚህም አቋቁመውት የነበረውን የፓርቲ ስም... #የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር;.. መጥቀስ በቂ ነው። ማለትም አሁንም የሚታገሉት ለራሳቸው ብሔር መብት ነው። በ”Remedial Right Theory” ንድፈ ሐሳብ መሠረት፤ ያለ ገደብ በማናቸውም ሁኔታ የተሰጠ የመገንጠል መብት የለም። ጭቆና ሲኖር ብቻ ነው መገንጠል የሚቻለው። ይህን ንድፈ ሐሳብ የሚደግፉ አያሌ ዓለም አቀፍ ምሁራን አሉ (መብቱ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ይካተት ወይስ ሌላ መፍትሔ ይፈለግለት? የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ) የዓለም አቀፍ ሕጎችም በተወሰነ መልኩ ለዚህኛው ንድፈ ሐሳብ ዕውቅናን ይሰጣሉ።
የአቶ ሌንጮ ለታ ገለፃ ትልቁ ችግር፤ ለየቅል የሆኑትን የመገንጠል መብት ዓይነቶችን በአንድ ቋት ውስጥ አስቀምጠው በጅምላ ማብራራታቸው ላይ ነው። ይህ ንድፈ ሐሳባዊ ጭፍለቃ፣ በመብቱ ትግበራ ወቅት ችግር ፈጣሪ ነው። ስለዚህም አቶ ሌንጮ በዝምታ ወደ “Remedial Right Theory” ካምፕ ከመዛወራቸው በፊት አንቀፅ 39 ላይ (Primary Right Theory) ያላቸውን አቋም ይፋ በማድረግ ብዥታችንን ማጥራት አለባቸው። ለምሣሌ አቶ ሌንጮ ጭቆና በሚኖርበት ወቅት መገንጠል እውን መሆን እንደሚችል ገልፀውልናል። ነገር ግን የመገንጠል ጥያቄ በጭቆና ሰበብ ብቻ ላይነሳ ይችላል። ከጭቆና ክስተት ውጪ የመገንጠል ጥያቄ የሚነሳበት አያሌ ሥነ ልቦናዊ ምክንያቶች አሉ (የሀገራችን የብሔር ፖለቲካ ከሶሻል ሥነ ልቦና አኳያ ትኩረት አግኝቶ ጥናቶች እንዳልተደረጉ መጥቀስ ግድ ይላል።) ከነዚህም ውስጥ አንዱ በዕውቁ ፈላስፋ ሄግል የተተነተነው የዕውቅና (Recognition) ንድፈ ሐሳብ ነው። ብሔሮች ዲሞክራሲያዊ መብታቸው እየተከበረላቸው፣ ምንም ዓይነት ውጫዊ ገፊ ምክንያትም ሳይኖር ኢኮኖሚው ከፈቀደላቸው ሀገር የመሆን ስሜት ውስጣቸው ሊቀሰቀስ ይችላል...በአጭር ቃል የመገንጠልን ጥያቄ የሚያነሳው ብሔር በ”ሀገርነት” መታወቅን “Status”ን ከፍ ማድረጊያ ስልት አድርጎ ሊወስደው ይችላል (በተለይም በልሂቃኑ የሚቀሰቀሰው የ”Political status” ውዝግብ ለአደገኛ ጦርነት የሚያበቃ ድብቅና ድምፅ-አልባ ገፊ ምክንያት ነው።) ሁለተኛው ጭቆና ሳይኖር የመገንጠል ጥያቄ እንዲነሳ በገፊ ምክንያትነት የሚጠቀሰው የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ የስስታምነት ባሕሪይ ነው። ይህ በሶሽዮሎጂ ዲስፒሊን በ”Rational Choice Theory” ሥር የሚጠና የመገንጠል ሰበብ ነው። ለምሣሌ ብዙ የተፈጥሮ ሀብትን በክልሉ አቅፎ የያዘ ብሔር ምንም ጭቆና በሌለበት ሁኔታ የተፈጥሮ ሀብቱን በብቸኝነት ለመጠቀም ካለው የስስታምነት ባሕሪይ (Human Greediness) ተንደርድሮ የመገንጠል ጥያቄን ሊያቀርብ ይችላል።
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱ ሥነ ልቦናዊ ገፊ ምክንያቶች ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈተለኩ ናቸው። ከውጭ ወደ ብሔሩ የሚሰነዘሩ አይደሉም። አንቀፅ 39 እነዚህን መብቶች ያከብራል...መገንጠሉ የተፈቀደው “በማናቸውም መልኩ ያለገደብ” ስለሆነ። የአቶ ሌንጮ የ”Remedial Right Theory” ግን ፈፅሞ እንደዚህ ዓይነቱን መገንጠል አይፈቅድም። ስለዚህም ብሔሮች ከጭቆና ውጭ ባሉ ከውስጥ ወደ ውጭ በሚፈነዱ ገፊ ምክንያቶች የተነሳ የመገንጠል መብት ጥያቄን በሚያነሱበት ወቅት የአቶ ሌንጮ ምላሽ ምን ይሆን? ለምሣሌ የኦሮሚያ ክልል ምንም ገፊ የጭቆና ምክንያት በሌለበት በ”Recognition” እና በ”Rational Choice Theory” መነሻነት የመገንጠል ጥያቄን ቢያነሳ የአቶ ሌንጮ አቋም ምን ይሆን? ምናልባት አቶ ሌንጮ አሁን የተነተኑትን የ”Remedial Right Theory”ን መርህ የሚያከብሩ ከሆነ መገንጠሉን ይቃወማሉ፣ ሕዝባዊ አመፁንም የሚቀሰቅሱት መገንጠሉን በመቃወም መሆን አለበት። በተቃራኒው አቶ ሌንጮ “ክልሉ ሀገር መሆን ከፈለገ መብቱ ነው” ካሉ ወደ “Primary Right Theory” ካምፕ ገቡ ማለት ነው። ያኔ “ገፊ ምክንያት” የሚለውን ትንታኔአቸውን ውኃ በላው ማለት ነው። ስለዚህም በእኔ ዕይታ፤ አቶ ሌንጮ ለታ በገለፃቸው ውስጥ የመገንጠል ንድፈ ሐሳብ ብዥታ አጥልቶባቸዋል። የ”Conceptual clarity” እክልም ይስተዋልባቸዋል። ይህን ለማስተካከል እኔ ወዳነሳሁት ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ በአንድና ሁለት ዐ/ነገር ብቻ ግልፅ ማድረግ ይችላሉ። ለምሣሌ “እኔ ሌንጮ አንቀፅ 39 ውስጥ የተቀመጠውን የ”Primary Right Theory” እቃወማለሁ፣ ጭቆና በሌለበት የመገንጠል ጥያቄ ያለገደብ መነሳት የለበትም፣ ይልቁን የምደግፈው የ”Remedial Right Theory”ን ነው” ቢሉን ኖሮ ብዥታው በጠራልን ነበር!
በቀጣዩ ፅሁፌ... አቶ ሌንጮ ያነሱት “ገፊ ምክንያት መለኪያው ምን ይሆን?” “አንቀፅ 39ን አነሳህ አላነሳህ” የሚለው አባባላቸው የቱን ያህል ልክ ነው? አቶ ሌንጮ በጣም አቅላይ (Reductionist) ሆነው በእግረ መንገድ ያስቀመጧቸው ሐሳቦች የዘርፉን ምሁራን በሁለት ጎራ ከፍሎአቸው የሚያነታርኳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።



Monday, 15 March 2021 08:09

የመደመር መንገድ;

Written by


          አንድ የንስር ጫጩት እናቱ መብረር ስታለማምደው ቆይታ በመጨረሻ #አሁን ያለ እኔ ድጋፍ መብረር ስለምትችል ከእንግዲህ ብቻህን ከጎጆ ወጥተህ ክንፍህን ማንቀሳቀስ ትችላለህ; አለችው።
ጨቅላው ንሥርም በደስታ ከጎጆ ሲወጣ በአቅራቢያው አንድ አሳማ ሲሮጥ ያያል። በደስታ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል ለእናቱ ነገራት፤ "እዪውማ! ያንን ጮማ የሆነ አሳማ" አለና ሄዶ ለቀም ሊያደርገው ተጣደፈ።
"ተው ተው የእኔ ልጅ! እሱ ይቅርብህ!" በማለት ተቃወመች፤ የንሥሩ እናት። "አንተ አሁን አሳማ ለማደን አልደረስክም፤ ገና ነህ። ባይሆን አነስ አነስ ያሉትን አይጦች በማደን ብትጀምር ጥሩ ነው፤ ጉልበትህ መጠንከር አለበት"  አለችው።
ንሥሩ በእናቱ ክልከላ ቅር ቢለውም ምክሯን ግን ከመስማት አላመነታም። ከዚያ እየዞረ አይጦችን እያደነ ይበላ ጀመር። መጀመሪያ ላይ አይጦቹን ለመያዝ በጣም ተቸግሮ ነበር። እየቆየ ግን አያያዙን ስለለመደው በቀላሉ ለቀም ያደርጋቸው ጀመር። እያደገ ሲመጣ አይጥ ማደኑ በጣም ቀላል ሆነበት፤ ሥጋቸውም አላጠግብ አለው። በዚህ መሐል ግዙፉን አሳማ ሲሮጥ ተመለከተው።
"አሃ! አሁን ተገኘህ፣ መጣሁልህ ጠብቀኝ"  ብሎ ወደ አሳማው ሊወረወር ሲል እናቱ በድጋሚ አስቆመችው።
"አሁን ጥንቸል ምናምን ማደን ጀምር። አሳማውን ለጊዜው ተወው" አለችው።
ንሥሩ ሳያመነታ አሳማውን ትቶ ጥንቸል ማደን ጀመረ። ሆኖም ጥንቸሎቹ እንደ አይጥ ለማደን ቀላል አልሆኑለትም። ሲሮጡ አይጣል ነው። ደርሶ ለቀም ሊያደርጋቸው ሲል እጥፍ ብለው አቅጣጫ ይቀይሩበታል። መጀመሪያ አካባቢ ቀኑን ሙሉ ታግሎ አንድ ጥንቸል መያዝ ይከብደው ነበር። እየቆየ ሲሄድ በቀን ሁለትም ሦስትም መያዝ ለመደ። በዚህ መሐል የተለመደው አሳማ ትውስ ሲለው ከእንግዲህ እሱን ማደን አለብኝ ብሎ ተነሳ። ችግሩ አሁንም እናትየው አልፈቀደችለትም።
"በጥንቸሎቹ ቅልጥፍና ብትማርም ክብደት ያለው ነገር መሸከም ደግሞ በግና ፍየሎችን በማደን መለማመድ አለብህ" ስትል ነገረችው።
ንሥሩም እንደተባለው አደረገ። ብዙ በጎችንና ፍየሎችን እያደነ ሲበላ ከረመ።
አንድ ቀን እንደተለመደው በግ ሊያድን ሲወጣ ያንን አሳማ አየው። ዞር ብሎ እናቱን ሲመለከት በዐይኗ "አሁን ጊዜው ነው" የሚል ምልክት ሰጠችው። ክንፉን እያማታ ሽቅብ ወጣና አነጣጥሮ ቁልቁል ተወረወረ። ተወርውሮም አልሳተውም፤ አፈፍ አደረገው። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዐቅሙን ሲያከማች መቆየቱ አሳማውን ያለ ችግር እንዲጨብጥ አደረገው።
ደራሲ: ዐቢይ አህመድ አሊ (ዶ/ር)
(kገፅ 19 እና 20 የተቀነጨበ)

Monday, 22 February 2021 09:03

የፍቅር ቀጠሮ

Written by

ታገል ሰይፉ


ጠበቅኩሽ እኔማ-እዚያው ሥፍራ ቆሜ
በአክሱም ቁመና- በላሊበላ ዕድሜ
እግሮቼን ተክዬ-ቀኔን አስረዝሜ
በሔድሽበት መንገድ- ልቤ እንደነጎደ
ስንት ነገር መጣ-ስንት ነገር ሄደ
ስንት ጊዜስ ነጋ- ስንቴ ጎህ ቀደደ
ስንቴ ዝናብ ጣለ-ስንት ጊዜ አባራ
ትመጫለሽ ብዬ -በቆምኩበት ሥፍራ
ስንቴ አድማሱን ማተርኩ-ስንትና ስንት ዓመት
አንገቴን አስግጌ-በራስ ዳሽን ቁመት
በአክሱም ቁመና- በላሊበላ ዕድሜ
በቀጠርሽኝ ሥፍራ-ስጠብቅሽ ቆሜ
ስንት ሳቅ አለፈ-ስንትና ስንት ዕንባ
ስንቴስ ክረምት ሆነ-ስንቴ ፀደይ ጠባ
ስንቱ ተገናኘ-ስንቱ ሰው ተጋባ
ሽል ስንቴ ልጅ ሆነ-ስንትስ ጊዜ አረጀ
ስንት ኮት ጨረሰ- ስንት እንጀራ ፈጀ
ስንት ዓይነት ሞት አየሁ- ስንት ዓይነት ፍፃሜ
በአክሱም ቁመና-በላሊበላ ዕድሜ
በቆምኩበት ሥፍራ-ስጠብቅሽ ቆሜ?
ስንት ውበት አለፈ-ስንት ውበት ነጎደ
ስንት ትውልድ መጣ -ስንት ትውልድ ሄደ
ስንት ዕውነት ከፍ አለ-ስንት ዕውነት ወረደ
ስንት ዓለም ተሻረ- ስንት ዓለም ነገሠ
ስንት ሀገር ተሰራ-ስንት አገር ፈረሠ
ስንት ሺህ ዓመት ሸኘሁ-ስንት ሺህ ተቀበልኩ
እዚያች ሥፍራ ቆሜ-አንችን እየጠበቅኩ
እግሬን አስረዝሜ-ቆየሁ ቆየሁና
በላሊበላ ዕድሜ- በአክሱም ቁመና
ሳትመጪ ወደኔ-ሳላገኝሽ ገና
ብዙ ነገር መጥቶ -ብዙ ነገር ያልፋል
የራስ ዳሽን ራስ-አንገቱን ይደፋል
አክሱምም ተንዶ- እንደጨው ይረግፋል
ላሊበላም ወርዶ-ቁልቁል ይነጠፋል
ሰማይና ምድርም ያልፋሉ ታያለሽ
እኔ ግን እዛው ነኝ-አንች እስክትመለሽ…

Monday, 22 February 2021 08:44

የቄሳርን ለቄሳር

Written by

 በእውቀቱ ስዩም


             የድሮ የብሔራዊ ትያትር መርሃግብር
- በመጀመርያ ነቢይ መኮንን ግጥም ያነባል::
- ቀጥሎ ተስፋየ ካሳ አጭር ኮሜዲ ያቀርባል::
- በማስከተል ክበበው ገዳ ፥ የኮንሶ ባህላዊ ውዝዋዜ ያቀርባል( ክቤ ያኔ ተወዛዋዥ ነበር)
- ቀጥሎ ወይዘሮ የዱር ፍሬ፣ 125 ገፅ ያለው አጭር ልቦለድ ያነባሉ ፤
- በመጨረሻ ፊርማዬ አለሙ፣ የፈረመቺበት የግጥም VHS ለሽያጭ ይቀርብና የዝግጅቱ ፍፃሜ ይሆናል፡፡
(ላዲሱ ትውልድ አንባቢ፡- VHS ማለት ከብሉኬት በላይ የሚመዝን የቪድዮ ካሴት ሲሆን አሁን በፍላሽ ዲስክ ተተክቷል፤ ቡሉኬት ራሱ ምን እንደሆነ ማብራራት ይጠበቅብኝ ይሆን?)
ዘንድሮ በብሔራዊ ትያትር
- በመጀመርያ ዲያቆን ዶክተር ገነነ፣ በኢትዮጵያ ትንሳኤ ዙርያ ስብከት ያቀርቡልናል፡፡
-በማስከተል ኡስታዝ ሙሳ፣ ነፍስ እሚያለመልም ትምህርት ይለግሱናል፡፡
-ቀጥሎ፤ አቶ ንጉስ መሳይ፣ የፖለቲካ ፓርቲያቸውን መተዳደርያ ደንብ በስንኝ ያስደምጡናል፡፡ - ለጥቆ ፓስተር ቀልቤሳ ኢጄታ፤ “ አለሌነትና ጦሱ; የሚል ስብከት ይለቁብናል ፡፡
-በመጨረሻ ድምፃዊት ሎዛ “ ነጨኝ በቅበላው ፤ የገጠር ሸበላው; የሚለውን ተወዳጅ ዜማዋን ታቀርብና ፍፃሜ ይሆናል፡፡
ማጠቃለያ መፈክር፤ የእግዜርን ለእግዜር! የቄሳርን ለቄሳር!


 እኛ ሀገር ሰው ስለ ፖለቲካው ሲያለቃቅስ ካየህ፣ የራሱን ቡድን ብቻ ስለሚያምንና ያ የሚያምነው ቡድን ከላይ እየገዛ ስላልኾነ ብቻ ነው። “እኩልነት፣ መቻቻል፣ ጭቆና ..” ገለመሌው ማስክ ነው።
“የራሱ” ቡድን ከላይ ሲወጣ፣ ራሱ ሲጠራቸው የነበሩት “እኩልነት፣ መቻቻል፣ ጭቆና” ምናምን ቃላት “የአሸባሪዎችና ሥራ ፈቶች” ቃላት ይኾኑበታል። “ከዚህ በላይ እኩልነት ከየት ይምጣላቸው?” ይላል፡፡
ይልቅ በየጊዜው እነዚህን “እኩልነት፣ መቻቻል፣ ጭቆና” መፈክሮች እየተሸከሙ የፖለቲካውን አጫዋቾች የሚያነግሡ ወጣቶች ያሳዝኑኛል። እነሱን እንዳይኾኑ ልጆቼን አስተምራለሁ።
“እንደ እምነታችሁ፣ ለጎረቤታችሁ እየራራችሁ፣ ለባልንጀራችሁ እያካፈላችሁ፣  ኑሯችሁን ኑሩ። ቢፈልጉ ይጥሏችሁ እንጂ አትጥሉ።” እላቸዋለሁ። ወደ ፖለቲካው ምን በወጣቸውና ይውረዱ?
እህእ--    

  በሀገራችን የፖለቲካ ውይይት መድረኮች እንደነገሩ አድበስብሰን ለማለፍ ጥረት የምናደርገው የግልና የቡድን/የወል መብቶች ቁርኝት ርዕሰ ጉዳይ፣ በሌላው የዓለም ክፍል የፖለቲካ ሳይንቲስቶችንና ፈላስፎችን ለሁለት ከፍሎ የሚያነታርክ አጀንዳ ነው። ቀደም ሲል ከተስተዋሉ የሀገራችን የምርጫ ውድድር ክርክሮች ካለን ተሞክሮ አኳያ፣ የሀገራችን ፖለቲከኞች በዚህኛው ርዕሰ ጉዳይ ሲበዛ “reductionist” ነበሩ ብንል ማጋነን አይሆንም፣ ማለትም ውስብስቡን ፅንሰ ሐሳብ አቅልለው የማየት አባዜ አለባቸው።
ለማንኛውም በግለሰብና በቡድን/በወል መብቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ሁለት ዓይነት ዕሳቤዎች አሉ።
1. አንዳንድ የፖለቲካ ሳይንቲስቶችና ፈላስፎች፣ የግለሰብ መብቶችን መነሻ የሚያደርገው መደበኛው የሊብራል ዲሞክራሲ ሞዴል (John Rawls, Immanuel Kant,Jean Jacques Rousseau) የቡድን/የወል መብቶችን የማቀፍ አቅም አለው የሚል አቋም አላቸው። እነዚህ ሳይንቲስቶች የቡድን/የወል መብቶች ጥያቄ በግለሰብ መብቶች መከበር ዕውን ይሆናሉ የሚል እምነት አላቸው። ይህን አቋም ከሚያራምዱ ሳይንቲስቶች ውስጥ ጀርመናዊው ዩርገን ሐበርመስ እና ካናዳዊው ዊል ኪሚሊካ ተጠቃሾች ናቸው።  
2. በሁለተኛው ጎራ ያሉ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ የቡድን/የወል መብቶችን ከግለሰብ መብቶች ነጥለው የሚፈትሹ ናቸው። በዚህኛው ምድብ ያሉ አጥኚዎች፣ የቡድን/የወል መብቶች በግለሰብ መብቶች ውስጥ ሳይጠቀለሉ በራሳቸው ለብቻቸው መጠናት አለባቸው ይላሉ። ይህን አቋም የሚያራምዱ የዘርፉ ሳይንቲስቶች “Communitarians” ተብለው ይጠራሉ። ካናዳዊዉ ፈላስፋ ቻርልስ ታይለር፣ አሜሪካዊው ፈላስፋ ሚካኤል ዋልዜርና የሕግ ፕሮፈሰሩ ዱዋይት ኒውማን የዚህ ዕሳቤ አራማጆች ናቸው።
ትናንት ይፋ በተደረገው በብልፅግና አዲሱ ማኒፌስቶ ወትሮ ሚዛኑን በዋናነት ወደ ቡድን መብት ያጋዳለው ኢሕአዴጋዊው ዕሳቤ በተሻሻለና በልምድ ላይ በተመሠረተ ዕሳቤ ተተክቶ ይሆናል የሚል እምነቱ ባይኖረኝም፣ የማኒፌስቶው አሁናዊ ይዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ፍላጎቱ አለኝ። በአንፃሩም በተለይም ኢዜማ በግለሰብና የዜግነት መብቶች አተገባበር ሂደት፣ ቡድናዊ መብቶች “by default” ይከበራሉ የሚል አቋም እንዳለው የፓርቲው መሪዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚሰጡት ማብራሪያዎች መረዳት ይቻላል። አሁንም ደግሜ የማሰምረው በእኔ አተያይ፣ በርዕሰ ጉዳዩ ብልፅግናም ሆነ ኢዜማ “reductionist” የሆነ ፅንፍ ይዘው የሚከንፉ ይመስላሉ። በተለይም በግለሰብና በቡድን/በወል መብቶች መካከል ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት የመፍትሔ አፈላለግ ሂደቱ ምን እንደሚመስል በግልፅ መቀመጥ አለበት። ለምሣሌ ከመላ ሀገሪቱ አንፃር አናሳ የሆኑ የካናዳ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ኪውቤካዊያን፣ በኪውቤክ የራስ ገዝ አስተዳደር ውስጥ አብላጫዎቹ በመሆናቸው፣ በክልላቸው የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች በሙሉ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ብቻ እንዲፃፉና ነዋሪዎችም ልጆቻቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ወደሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት እንዳይልኩ ማዕቀብ እስከመጣል ሁሉ ደርሰው ነበር። ይህ ውሳኔ ከግለሰብ መብት አኳያ የካናዳዊያንን ፖለቲከኞች ናላ ያዞረ ርዕሰ ጉዳይ ነበር።
እኛም ሀገር በኢሕአዴጋዊዉ የቡድን መብት ሰበብ፣ በየክልሉ የሚጣሱትን ግለሰባዊ መብቶችንና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሚፈፀሙ መገለሎችን ቆጥሮ መጨረስ የሚቻል አይደለም። በነገራችን ላይ ኪውቤክ ከካናዳ ጋር ያላት ዕድሜ-ጠገብ ውዝግብ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም፣ በተወሰነ መልኩ ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፣ በሌላ አንፃር የግለሰብንና የቡድንን መብት ቁርኝትን ለማመላከት፣ የኢዜማ አመራሮች የሚጠቅሷት አሜሪካ፣ ከእኛ ሀገር ፖለቲካዊ አውድ ጋር ያላት ምስስሎሽ እምብዛም ነው። በአብዛኛው በፍልሰት የተገነባውን ብዝሃ-ባሕልን፣ እንደ ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊነት ከተዋቀረው ጋር በእኩል ሚዛን ላይ አስቀምጦ ማነፃፀር ተገቢ መስሎ አይታየኝም።
 በእንደዚህ ዓይነት የተለያየ አውድ ውስጥ የሚነሱ ቡድን-ተኮር ጥያቄዎች ተመሳሳይነትም በእጅጉ አጠያያቂ ነው። እንዲያውም ካናዳዊው የብዝሃ-ባሕል አጥኚ ዊል ኪምሊካ፣ የአሜሪካው ሕገ መንግሥት “Ethnicty-blind” ነው በማለት ይተቸዋል። ሌላው ይቅርና በውስጡ ላቀፋቸው ለአሜሪካ-ሕንዳዊያንና “Puerto Ricans” ዕውቅናን የነፈገ ነው ይለናል (Multicultural Citizenship, 1996) ስለዚህም ሕገ መንግሥታዊ ንፅፅሮች በሚደረጉበት ወቅት አውዳዊነት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል።
የዚህ ፅሁፍ ዋናው መልዕክት፤ የግለሰብንና የቡድን/የወል መብትን ከማስከበር አኳያ፣ ለሀገራችን ፖለቲካዊ እንቆቅልሾች መፍትሔ በማፈላለጉ ሂደት፣ ከገዳፊነት ዕይታ (Reductionist view) እንድንቆጠብ ማሳሰብ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የማህበራዊና የፖለቲካ ሳይንስ ዘርፎችን ሳይንቲስቶች፣ በሁለት ጎራ ከፍሎ የሚያፋልማቸውን ፅንሰ ሐሳብ፣ እንደነገሩ በአንድና ሁለት ዐረፍተ ነገር ሸውዶ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት፣ ውሎ ሲያድር መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር መጣረሱ የማይቀር ነው። በእኔ እምነት፤ በግለሰብና በቡድን/የወል መብቶች ዙሪያ ጥልቀትነት ያላቸው፣ የሀገራችንን ፖለቲካዊ አውድ ማዕከል ያደረጉ፣ ሰፋ ያሉ ውይይቶች፣ በቀጣዩ የምርጫ ዋዜማ መደረግ አለባቸው። እኔም በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ፣ በምርጫ ፉክክር ወቅት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አቋም ይፋ ሲሆን፤ በየዘርፉ ሳይንስ ላይ በመመስረት፣ በፌስ ቡክ ገፄ ላይ እንደ አንድ ዜጋ የበኩሌን ለማለት እንደምሞክር ከወዲሁ ለወዳጆቼ አሳውቃለሁ።

Saturday, 06 February 2021 14:34

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by

በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስራ -- ከትውልድ ወቀሳ ነጻ ያወጣል
                       ሙሼ ሰሙ

            ጦርነት የሚጠላውና የሚፈራው የሚያስከፍለው ዋጋ፣ ኪሳራና መዘዙ ገደብና ልክ የሌለው፤ በተለይ ደግሞ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ቁማር አስይዞ የሚካሄድ የእሳት ላይ ጨዋታ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ጦርነት አንዴ ከፈነዳ የቀጥተኛም ሆነ የጎንዮሽ (Collateral) ጉዳቱንና የተዋናዮቹን ጣልቃ ገብነት መቀነስ እንጂ ማስቀረት የማይቻለው። ጦርነት ይቆየን የተባለውም ለዚሁ ነበር።
በእርግጥ ጦርነትን ስለሸሹትና ስለፈሩት አይቀርም። ይህም ሆኖ ግን ጦርነት የሚፈራና የሚሸሽ ጉዳይ እንጂ እሰይ መጣልኝ ተብሎ አታሞ የሚደለቅለት ተግባር አይደለም። እሳት የሚተፋ መሳርያ ተደግኖ፣ መግደልና መሞት ከተጀመረ በኋላ ጦርነት ምቹና ሚዛናዊ (Fair) እንዲሆን መጠበቅ ቅንጦት ነው። ጦርነት ምቹና ሚዛናዊ (Fair) የሚሆነው፣ አቅምን ሁሉ አሟጦ በመጠቀም በድርድርና በጠረጴዛ ዙርያ ጦርነት እንዳይጀመር “ሰጥቶ የመቀበልን” ተግባር መርህ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡
ዜጎች አላፊዎች ነን፣ ሀገር ግን ዝንተ ዓለማዊ ነው። የጦርነትን፣ ሂደትና ውጤቱን ከማጦዝ፣ ከማጋነንና በጥላቻ ተሞልቶ እርስ በርስ ጭቃ ከመለጣጠፍ ይልቅ ፕሮፓጋንዳውን በቅጡና በልኩ ይዞ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር መረባረብ፤ ስለ ነገና ከነገ ወዲያ ትውልድ ማሰብ ነው የሚበጀው። ይህ ደግሞ ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር አይደለም።
የጦርነት ፍሬው ወደ ግራም ሞት ነው፤ ወደ ቀኝም ውድመት ነው። ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ሹመኞች የጦርነቱን ሂደትና ውጤቱን ለፖለቲካ ፍጆታ፣ ለምርጫ ቅስቀሳ፣ ለማሻሻጫና ለዳግም እልቂት መቀስቀሻነት መጠቀማቸውን አቁመውና አደብ ገዝተው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ሊገነቡና ሊያጎለብቱ ይገባል። በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስራ መስራት፣ ከትውልድ ወቀሳ ነጻ ያወጣል።
“ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፣ ከቤትሽም አልወጣ
የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ” እንዲሉ።

Saturday, 06 February 2021 12:42

ቅጥቅጥ! በላባ ትራስ!

Written by

 ብልፅግና ፓርቲን ለመደገፍ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ወዳጄ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሲወገዝ አይቸ ገረመኝ ! ብልጥግናን እንደግፋለን ዳንኤል ክብረትን እናወግዛለን ማለትኮ “ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንሞታለን በረኛውን ግን እንገድለዋለን “ እንደማለት ነው ፤ ዳኒ አንደበቱ የማይደነቃቀፍ ተናጋሪ ብእሩም የማይደክም ፀሀፊ ነው፤ በተሰጥኦው ወፍራም እንጀራም ሆነ ሜዳልያ ማግኘት የሚያቀተው ሰው አይደለም ፤ እንግዲህ እሳቱ በማያንቀላፋው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የተጣደ አገር እጠቅም ብሎ መሆን አለበት !
አንባቢ ሆይ! ይሄን አንብበህ ምን ያኮማትርሃል? እያንዳንድህ በዚች አገር ልማትም ሆነ ጥፋት ላይ እጅህም እግርህም አለበት !
ዳንኤልን የማውቀው ገና በካምፓስ ፍሬሽ ሳለሁ ነው ፤ ያኔ የሱን ስብከት ለመታደም እማይጋፋ አልነበረም ፤ በነገራችን እያዝናኑ መስበክን ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው ዳንኤል ይመስለኛል ፤ ፓስተር ዳዊትሳ ትይኝ ይሆናል ? እሱ ከስብከቱ በላይ የህይወት ውጣ ውረዱ ያዝናናኛል ፤
በነገራችን ታች ፥ ፓስተር ዳዊት ድሮ ምስኪን ቦክሰኛ ነበር ፤ የሰውነቱ ቅጥነት ብታዩት እንኩዋን ለቦክስ ለቼዝ ግጥሚያ እንኩዋ እሚመች አልነበረም ፤ ክንዱ እጅግ የመነመነ ከመሆኑ የተነሳ ሴኮ ሰአቱን እሚያስረው አንገቱ ላይ ነበር ! ለሰይፉ ሲነግረው እንደሰማሁት ለመጀመርያም ለመጨረሻም በተሳተፈበት ግጥሚያ ላይ” በዝረራ ነው የተሸነፈው” ! ተጋጣሚው እንዴት ጨክኖ ቡጢ ሰነዘረበት ? ! የጉዋንቱ ክብደት ራሱ ስቦ በግንባሩ ይደፋዋል!
ወደ ዳኒ እንመለስ!
እና በሚሰብክበት ጊዜ በየደቂቃው ምእመኑ በሳቅ ይደክማል፤ አንድ ቀን እንዲህ አለ፤
“መንግስተ ሰማያት ኬኔዲ ላይበራሪ አይደለም! የፀደቀ ጉዋደኛህን ወንበር ይዘህ ጠብቀኝ ልትለው አትችልም! “
ዳንኤል ክብረት ስለ ፍትህ ርትእ እንደምትሰራ ተስፋ አለኝ ! ከዚያ ወለም ዘለም ካልህ አለቅህም! በጨዋ ደንብ አርምሀለሁ! በላባ በተሞላ ትራስ እቀጠቅጥሀለሁ !
በነገራችን ላይ በጨዋ ደንብ መተቸት ሲባል አያቴ ናት ትዝ እምትለኝ፤
ልጅ እያለሁ ከለታት ባንዱ ቀን ካያቴ እማሆይ ዘውዴ ጋር ገበያ ሄድን፤አንዱ ባላገር ቁጭ ብሎ የሆነ ነገር ይሸጣል፤ በሰፊ ቁምጣ ውስጥ ቆ..ጦቹ የተነፈሰ የላስቲክ ኩዋስ መስለው ይታያሉ፤
 እና አያቴ እንዲህ አለችው፤
“አንቱ ሰውየ! እስቲ ብድግ ብለው ይቀመጡ”
ያው አቀማመጡን ሲያስተካክል ነገርየው ይሸፈናል ብላ ነው፤

 ወንጀል ሀላፊነቱ የግል ነው፣ የፈፃሚው ነው። መግደል ከባድ ወንጀል ነው። ለአንድ ሰው ኃላፊነቱ ይከብዳል። ነገር ግን የመግደል ሃላፊነቱን ከራስህ አውርደህ ለህዝብ ካከፋፈልከው (በህዝብ ስም ካደረግኸው) ሸክሙ ይቀላል። የብሄር ነገር የሚያንገበግባቸው ሰዎች የሚያስፈሩን ለዚህ ነው። የወንጀል ሀላፊነትን ለብሄራቸው በቡድን ስለሚሸነሽኑት ብሄረተኞች ሁሉ ጨካኝ ነፍሰ ገዳዮች የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው። ፖቴንሻሊ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው።
ህጻናትን አርዶ፣ ገደል ከትቶ፣ ቤት ውስጥ አቃጥሎ መሄድን ሃላፊነቱን ለህዝብ እስካስተላለፉት ድረስ ያለ ምንም ችግር ያደርጉታል። የግል ተጠያቂነት የለባቸውም። በቄሮ ስም፣ በፋኖ ስም፣ ኤጀቶ ስም መዓት አውርደህ “ቄሮ፣ ፋኖ፣ ኤጀቶ፣ ሄጎ እርምጃ ወሰደ!” በሚል ግለሰቦችን ነፃ በማድረግ ለብሄር የወንጀል ሀላፊነት በመሸንሸን እራስህን ነፃ ታወጣለህ። በአለማችን ታሪክ በሰው ልጆች ላይ የተፈፀሙ አሰቃቂ ወንጀሎች ሁሉ በዚሁ በብሄርተኝነት መንገድ የተፈፀሙ ናቸው። ውጣ ከጥበት። ውጣና ነፃ ሰው ሁን።

Page 3 of 3