ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ (40)

Friday, 15 April 2022 16:45

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by

 ዳቦ፣ የዳቦ አመጽና ግብጽ ያላቸው ዝምድና
                            ጌታቸው ወልዩ (ሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)
የዳቦ ዋጋን ተመን ለማውጣት የሚፈቅድ አሰራር የለንም›› ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡ -  አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን

                ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ትንታኔዬ፤ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መዘዝ በገጠመ የስንዴ እጥረት በግብጽ የተባበሰው የዳቦ አመጽን ለማርገብ፣ የአገሪቱ መንግሥት በየቀኑ 270 ሚሊዮን ቂጣ/ሽልጦ ዳቦ ለሕዝቡ ለማቅረብ እየተከተለ ያለውን የመሿለኪያ መንገድና የግብጽ የዳቦ ሕልውና ምን ያህል በዩክሬንና ሩሲያ መዳፍ ሥር እንደሆነ ዘርዘር ያለ ጽሑፍ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ እና ትኩረት ሰጥታችሁ ትከታተሉት ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።
ውድ ወገኖቼ:- በዘመናዊቷ ግብጽ “ዳቦ” እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ መሠረታዊ የምግብ ዓይነቶች አንዱ (one of the most important food staples) ተብሎ የሚንቆለጳጰስ፤ በነገ በጠባ ከብዙ ሚሊየኖች ደጅና ጓዳ የሚዳረስ፤ በገበያ ላይ ሲኖር የመኖር ሕልውናን የሚያረጋግጥ፤ የኑሮ ውድነት ሲገጥም የፖለቲካ ሥልጣንን እንደ ቅቤ የሚንጥ ፖለቲካ አዘል ተወዳጅ ምግብ ነው።
ለዚህም ነው “ግብጽ ውስጥ ዳቦ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፦ ከላይኛው የኅብረተሰብ ክፍል በሀብት ብዛት ከናጠጡ ቱጃሮችና በሥልጣን ማማ ላይ ከተኮፈሱ ሹመኞች አንስቶ እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ በመወደድ ዕለት ተዕለት ለምግብነት የሚውል፤ እጥረት ሲገጥም ብሶትን ወልዶ አመጽን የሚያበቅል፤ ፖለቲካዊ አንድምታው እጅጉን የሚያመዝን፤ የመንግሥት ሥልጣን መውጣትና መውረድ ቋንቋን የሚያቀነቅን፤ የብዙ ሚሊዮን ግብጻውያን መነጋገሪያ ቋንቋ ነው።” የሚሰኘው።
እነሆ ደግሞ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ፌብሩዋሪ 24 ቀን 2022 ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 16 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ፤ በዓለም አቀፍ ገበያ የስንዴ እጥረት በመግጠሙና ያለውም ዋጋው በመናሩ፤ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ስንዴ በግንባር ቀደምትነት በመግዛት የምትታወቀው ግብጽ፤ የዳቦ አመጽ በርትቶና ገፍቶ፤ በ”ዳቦ እንፈልጋለን?” የሚሊዮኖች ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መከራዋን እያየች ትገኛለች።
እናም! በአሁኑ ጊዜ በግብጽ ውስጥ ከ102 ሚሊዮን ከሚበልጠው የግብጽ ሕዝብ 72 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕዝብ በየቀኑ 270 ሚሊዮን ቂጣ/ሽልጦ መሰል ዝርግ የግብጽ ዳቦ እንዴት ይቅረብለት? ለሚለው ከባዱ አሊያም ፈታኙ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እጅግ ከባድ ፈተና ሆኗል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴቭ ታራቬላ፣ የካቲት 19 ቀን 2014 ለቮክስ ዶት ኮም በሰጡት መግለጫ፤ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ከሚበልጠው የግብጽ ሕዝብ አሥር (10) ሚሊዮን የሚሆኑት በአገሪቱ በገጠመ የስንዴ እጥረት የተነሳ ለከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት ተጋልጠዋል ብለዋል። ይህ ደግሞ ለግብጽ መንግሥት በቡሃ ላይ ቆረቆር ሆኖበታል።
ግብጽ በዋናነት ስንዴ የምትገዛው ከዓለማችን ትልቋና ቀዳሚዋ የስንዴ አቅራቢ ሩሲያና ከአራተኛና አምስተኛ ስንዴ አምራችነት እርከን ላይ ካለችው ዩክሬን ሲሆን፤ ሩሲያና ዩክሬን ደግሞ በጋራ ሩብ በመቶ የስንዴ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የሚታወቁ ናቸው። በዚህ መነሻነት ግብጽ ከፍላጎቷ ግማሽ ያህሉን ስንዴ ከሩሲያ ስትገዛ፣ ሰላሳ (30) በመቶ ያህሉን ደግሞ ከዩክሬን ታስመጣለች ማለት ነው።
በምኅጻረ-ቃል “ካፕማስ” የሚሰኘው የግብጽ የሕዝብ ሞቢላይዜሽን (ንቅናቄ) እና ስታቲስቲክስ ማዕከላዊ ኤጀንሲ፤ “የግብጽ ዋነኛ ስንዴ አቅራቢዎች ዩክሬንና ሩሲያ ሲሆኑ፤ ከ80 በመቶ በላይ እስከ 85 በመቶ ወይም ከአምስት እጅ 4 ነጥብ 25 ያህሉን ስንዴ የምትገዛው ከባድ ጦርነት ውስጥ ከገቡት ዩክሬንና ሩሲያ ነው!” ማለቱ የግብጽ የስንዴም ሆነ የዳቦ ማግኘት ሕልውና ክር ለአመታት በሩሲያና ዩክሬን ላይ ለመንጠልጠሉ አገርኛ ምስክር ይሆናል።
ለአብነት ያህል በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር በ2019 ግብጽ ከሩሲያ በ1 ነጥብ 44 ቢሊየን ዶላር፣ ከዩክሬን 773 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ስንዴ መግዛቷን፣ በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 25 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት የተነበበው የኢንቨስትመንት ሞኒተር ዘገባ አመልክቷል።
እንዲሁም በ2020 ላይ ዩክሬን ለዓለም ገበያ ካቀረበችው ስንዴ መጠን ሦስት (3) ሚሊዮን ቶን ወይም 14 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ስንዴ የገዛችው ግብጽ ነበረች። በተመሳሳይ አመት፣ ግብጽ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከሩሲያ ገዝታለች።
በዚህም መሠረት፦ ግብጽ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር በ2020 ላይ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋ በዋናነት ከዩክሬንና ሩሲያ እንዲሁም ሌሎች አገሮች 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ገዝታ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቷን የግብጽ የሕዝብ ሞቢላይዜሽን (ንቅናቄ) እና ስታቲስቲክስ ማዕከላዊ ኤጀንሲ ገልጿል።
የግብጽ ስንዴ ፍላጎትም እጅግ እየበዛ ከመጣው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አኳያ በየአመቱ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ በጎርጎሮሳዊያኑ አመት በ2021-2022 ላይ ግብጽ የሚያስፈልጋት የስንዴ ግዢ መጠን ከቀዳሚው የ2020-2021፤ በ2 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ በማሳየት፣ ወደ 21 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ስንዴ መጠን ከፍ ማለቱን የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የውጭ ግብርና አገልግሎት (US Foreign Servive) አስታውቋል።
የግብጽ ገበሬዎች ማኅበር ሊቀመንበር ሁሴን አቦ ሣዳም፣ በፌብሩዋሪ 4 ቀን 2022 ለተነበበው አል-ሞኒተር በስልክ እንደገለጹት ደግሞ፤ ግብጽ በአገር ውስጥ ዘጠኝ (9) ሚሊዮን ቶን ስንዴ የምታመርት ሲሆን፤ ይህ የስንዴ መጠን እየሸፈነ ያለው አገሪቱ ከምትፈልገው የስንዴ መጠን ወደ ግማሽ ያህሉን ነው።
ለንጽጽር ያህል ኢትዮጵያን ብንመለከት፦ የብዙ የዓባይ ተፋሰስን ጨምሮ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተፋሰሶች፣ ሐይቆችና ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ-ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ፤ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከምታቀርበው ስንዴ ሦስት አራተኛ እጁን ወይም 75 በመቶውን የምታመርተው በአገር ውስጥ እንደሆነ ለመገንዘብ እንችላለን። ኢትዮጵያ ቀሪውን የስንዴ መጠን ደግሞ ከውጭ የስንዴ ላኪ አገሮች ትገዛለች። እንዲሁም ደግሞ ከለጋሽ  አገሮች የስንዴ ዕርዳታ ትቀበላለች።
እንደሚታወቀውና ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ግብጽ አብዛኛውን ስንዴ ከሩሲያና ዩክሬን የምትገዛ ሲሆን ቀሪውን ወደ ሀያ በመቶ ገደማ ደግሞ በዋናነት ከፈረንሳይ፣ ሩማኒያና አውስትራሊያ ታስመጣለች። ይህ ደግሞ የግብጽ የውጭ አገር ስንዴ ምርት ሸመታ እጣ ፈንታና መዳረሻ ሩሲያና ዩክሬን ላይ ማረፉን በግልጽ ያመላክታል።
እዚህ ላይ በዓለምአቀፍ ስንዴ ገዢ አገርነት ጎራ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ተመሳሳይ ጉዳይ አለ። እርሱም የዐረብ አገሮች የሆኑት ግብጽና ሊባኖስ ከውጭ አገሮች ከሚያስገቡት የስንዴ መጠን ከአራት አምስተኛ በላይ ወይም ከሰማንያ (80) በመቶ የሚበልጠውን የሚያስመጡት ከሩሲያና ዩክሬን የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ለዚህም ነው ፌብሩዋሪ 24 ቀን 2022 በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተጀመረውና በየዕለቱ የጥፋት አድማሱ እየጨመረ በመጣው ጦርነት የተነሳ እጅግ ለከፋ የስንዴ እጥረት ከተጋለጡ የዐረብ አገሮች መካከል ሊባኖስና ግብጽ ሊጠቀሱ የቻሉት።
ሌላ ተጨማሪ ማሳያ ማቅረብ ካስፈለገ፣ በሩሲያና ዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት በዓለም አቀፍ የስንዴ ገበያ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ ያደረሰውን ጫና በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፤ በጎርጎሮሳዊያኑ ዘመን በ2007-2008 ለተቀሰቀሰው የዐረቡ ዓለም የፀደይ አብዮት አንዱ መንስኤ የዳቦ አመጽ እንደሆነ አስታውሰው፤ አሁንም በሩሲያና ዩክሬን መካከል በሚካሄደው ጦርነት መዘዝ ከሁለቱ አገሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ የሚያስገቡት ግብጽ፣ ሊባኖስ፣ ሱዳን፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያና ሌሎች አገሮችም ለከፋ የስንዴ እጥረት ከመጋለጥ እንደማይድኑ ስጋታቸውን መግለጻቸውን አስመልክቶ አልጀዚራ መጋቢት 2 ቀን 2014  ያሠራጨውን ዘገባ መጥቀስ ይቻላል።
ስለዚህ ግብጽ ያጋጠማትን የከፋ የስንዴ እጥረት ለመቅረፍ የመጀመሪያ አማራጭ አድርጋ የወሰደችው እርምጃ በአገር ውስጥ እያመረተች ወደ ውጭ ትልካቸው የነበሩትን ስንዴና በቆሎን ጨምሮ የምግብ ዘይት ምርቶችን ከመጋቢት 3 ቀን 2014 አንስቶ እንዲታገዱ ማድረግ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ ምንም እንኳን የተወሰኑ እህል አምራች ገበሬዎችን ጠቅሞ አንዳንዶችን ቢጎዳም የአገር ውስጥ ስንዴ አምራቾች ስንዴ ለመንግሥት እንዲሸጡ የአገሪቱ መንግሥት ጫን ያለ ትዕዛዝ አስተላልፏል። የተጣለባቸውን የስንዴ ኮታ ላለማቅረብ የሚያንገራግሩ ገበሬዎችን ከማስፈራራት አንስቶ ለእስራት እስከ መዳረግ ተደርሷል።
የግብጽ መንግሥት የአገር ውስጥ ስንዴ አምራቾች፣ ስንዴ ለመንግሥት እንዲሸጡ ያስተላለፈውን ውሳኔ ከደገፉት መካከል፦ በግብጽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእርሻና መስኖ ኮሚቴ ኀላፊ ሂሻም አል-ሁሳሪ፤ “የአገር ውስጥ ስንዴ አምራቾች ስንዴ ለመንግሥት እንዲሸጡ መወሰኑ ለግብጽ ሕዝብ ዳቦን ጨምሮ ሌሎች የስንዴ ውጤት የሆኑ የምግብ ዓይነቶችን ለማቅረብ በጣም ጠቃሚ ነው!” በማለት አወድሰው፣ መጋቢት 11 ቀን 2014  ለተነበበው ሚድሊስት አይ ድረ ገጽ ተናግረዋል።
ገና ሩሲያና ዩክሬን ወደ ጦርነት በገቡ በሦስት ሣምንታት ውስጥ ግብጽ ውስጥ የማይደጎመው ዳቦ ዋጋ በሃያ አምስት በመቶ በመጨመር አንድ የግብጽ ፓውንድ ይሸጥ የነበረው ቂጣ፣ አንድ ከሀያ አምስት የግብጽ ፓውንድ ሊሸጥ መብቃቱንና የዱቄት ዋጋም አሥራ አምስት በመቶ (15%) መጨመሩን፣ የካይሮ ንግድ ምክር ቤት የሥራ ኃላፊ አቲያ ሀማድ መናገራቸውን ሮይተርስ  ከካይሮ ዘግቧል።
ከዚህም አልፎ የግብጽ መንግሥት ቁርጥ የሆነ የዳቦ መሸጫ ዋጋ (ተመን) አውጥቷል። በዚህም መሠረት፦ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ፣ ከሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014  አንስቶ አንድ ኪሎ ግራም ዳቦ በ11.50 የግብጽ ፓውንድ ወይም በ66 የአሜሪካ ሳንቲም መሸጥ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በአዲሱ የመንግሥት ውሳኔ መሠረት፤ 45 ግራም ቂጣ በ0.50፤ 65 ግራም በ0.75፤ 90 ግራም በ 1.00 የግብጽ ፓውንድ እንዲሸጡ ትዕዛዝ ተላልፏል። 40፣ 60 እና 80 ግራም ከፊኖ ዱቄት የሚሠሩ ትናንሽ ቂጣዎች ደግሞ፤ በ0.50፣ በ0.75 እና በ1.00 የግብጽ ፓውንድ ሽያጭ ለገበያ እንዲቀርቡ መንግሥት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይህን ለሦስት ወራት የሚቆይ ትዕዛዝ የሚጥሱ ስንዴ አምጪና አከፋፋዮች፣ የዳቦ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶችና ማናቸውም ግብጻውያን፣ ከአንድ መቶ ሺ እስከ አምስት ሚሊዮን የግብጽ ፓውንድ እንደሚቀጡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ ጽሕፈት ቤት የወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በተጨማሪም፤የአገሪቱ መንግሥት ተጨማሪ የስንዴ ግዢ ከሕንድ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ሩማኒያ፣ ካዛክስታንና ሌሎች አገሮች ለማግኘት እጅግ እየተሯሯጠ ይገኛል።
የስንዴ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መጨመሩን ተከትሎ፣ የግብጽ መንግሥት ለስንዴ ግዢ የሚያወጣውን ሦስት ቢሊዮን ዶላር፣ ወደ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ማሳደጉን የዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ዘገባ አመልክቷል።
በግብጽ ውስጥ 38 ጊዜ የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸው፣ ሕይወታቸው ተርፋ፣ ኦክቶበር 6 ቀን 1981 በአክራሪዎች በተተኮሰባቸው ተከታታይ የጥይት ተኩስ ሕይወታቸው በተቀጠፈው የፕሬዚዳንት አንዋር ሣዳት የአገዛዝ ዘመን የዳቦ አመጽ ተካሂዷል።
በፕሬዚዳንት አንዋር ሣዳት እግር የተተኩት ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ሁሴን ሙባረክ፤ ከሥልጣናቸው የተመነገሉት ሕዝባዊ የዳቦ አመጽ በወለደውና እ.ኤ.አ በ2010-2011 በተቀሰቀሰው በዐረቡ የፀደይ አብዮት (ዐረብ ስፕሪንግ) ፈጣን ጎርፍ የተነሳ ነው።
በ2013 መፈንቅለ መንግሥት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት መሐመድ ሞርሲ ከሥልጣን አስወግደው፤ በአንድ ቀን ጀምበር ከ800 በላይ ሰልፈኞችን ያስገደሉና ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ለእስር የዳረጉ ጨካኝ ወታደራዊ አምባገነን መሪ በሚሰኙት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ የሥልጣን ዘመን ምንም እንኳን አፈናው ቢበዛም፣ በግብጽ የከፋ የዳቦ አመጽ እየተካሄደ ይገኛል።
አሁን የግብጽ ፈተና በየቀኑ 270 ሚሊዮን ቂጣ/ሽልጦ ዳቦ ለሕዝቡ እንዴት ይቅረብ? የሚለውን ጥያቄ ከመመለሱ ላይ ነው።
ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊው ምግብ”፣ “በመላው ዓለም ምርጡ ምግብ” እና “ከዓለማችን እጅግ ተወዳጅ ጥንታዊ ምግቦች አንዱ” (one of the world’s oldest and most beloved foods.) ተብሎ የተንቆለጳጰሰውና የተወደሰው “ዳቦ”፤ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ፣ የዓለማችን የስንዴ ዳቦ አቅርቦት ፈትኖ ካብረከረካቸው አገሮች አንዷ የሆነችው ግብጽና መሪዎቿ፣ ይህን የዳቦ አመጽ እንዴት ይሻገሩት ይሆን? የነገ ሰው ይበለን! የዳቦ አመጹን ሂደት ወደ ፊት አስቃኛችኋለሁ። እስከዚያው ቸር ሰንብቱልኝ።
በመጨረሻም ቸሩ እግዚአብሔር አገራችንን ይጠብቅልን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

_________________________________________
===============================

                        የፑቲን አለም!
                              ፉዣዥ


              ስለ ሳይቤሪያ ነብሮች እንቅልፍ የሚያጣው ቭላድሚር ፑቲን የሚመራው ህዝብ፥ የሚወዳት ሩሲያ እስክትጠፋ ድረስ ውጤት ላለው የኒውክለር ጦርነት መነሳት (እና ወዲያው መጠናቀቅ) ምክንያት ሊሆን ይችላል?
“አለም ዘጠኝ ናት አስር ሞልታ አታውቅም” ያለው ማን ነበር። ስጠረጥር ግን ትክክል ይመስለኛል። አለም ዘጠኝ ትመስለኛለች። አንደኛዋ አለም የፑቲን አለም ናት። ስምንተኛዋ አለም ሁሉ ትመስለኛለች። የፑቲን አለምን ለመረዳት የመጀመሪያው ስራ ፑቲን ምን እንደሚሻ፥ እንደሚፈልግ ማወቅ ነው።
ፑቲን ምን ይፈልጋል?
ህይወቱንና እጣፈንታውን በመቆጣጠር ራሱን መጠበቅ (መከላከል) ፑቲን ይፈልጋል።
ዋናው ግን ፍላጎቱ አይደለም። የሰው ልጅን ባህሪ (ሃሳብ ተግባር ንግግር) በአብዛኛው፥ በአመዛኙ የሚቃኘው ፍላጎት ሳይሆን ፍርሃት ነው።
ሰው እንቅልፍ የሚያጣው ስለ ፍላጎቱ እያሰበና እያቀደ ሳይሆን ስለ ፍርሃቱ እያሰበና እያቀደ ነው። የሚፈራው ነገር እንዳይደርስ በሃሳቡ፥ በንግግሩ፥ እና በድርጊቱ ሲታገል ወይም ሲሸሽ ነው የሚኖረው፥ የሰው ልጅ። ፑቲንን ጨምሮ።
እና ፑቲንን ምን ያስፈራዋል?
ፍርሃት የፍላጎት “የመስታወት ምስል” ወይም ግልባጭ ነው። በሌሎች መጎዳት ወይም ቁጥጥር ስር መዋልን ፑቲን ይፈራል። ዝርዝር ባህሪው የሚቀዳው ከእነዚህ ነገሮች ነው፥ በተለይ ከፍርሃቱ። እንደ ፑቲን አይነት ሰዎች ተገዳዳሪዎች ሊባሉ ይችላሉ። ሃሳቦቹንም ሆነ ሰዎችን የሚቀበሉትና የሚያከብሩት ብዙ ከተገዳደሩ በኋላ ነው። ለማያውቅ ሰው “ከእኔ ምን ነገር አለው ይህ ሰው” ሊል ይችላል። የሚገዳደሩት ካንተ ነገር ስላላቸው ሳይሆን አንተን ለመመርመር ነው። ሳይመረምሩ አያደንቁህም፥ አያከብሩህም።
ኮንዶሊዛ ራይስ እንዳለችው፤ ከፑቲን ጋር ተደራድረህ ጥቅምህን ለማስከበር እርሱ ሊያከብርህ ይገባል፥ አንተም ልታከብረው ይገባል። እንዲያከብርህ ደግሞ ሃይለኛ፥ ጠንካራ መሆን አለብህ። የምታስበውን በቀጥታ የምትናገር መሆን አለብህ።
እንደ ፑቲን ያሉ ሰዎች ዲፕሎማቶች አይደሉም፥ ፊት ለፊት ነው የሚናገሩት። የሆነ የተሞረደ፥ የሰለጠነ ሰው አይነት ንግግር ከእነ ፑቲን አትጠብቅ። የዱርዬ የሚባሉ ቃላትን ሊጠቀሙ ይችላሉ። እንዲሁም የሚናገርውን፥ ቃል የገባውን የሚፈፅም ሰው ፑቲን ያከብራል። ፑቲን የሚጠላው በሌሎች ቁጥጥር ስር መዋልን ነው። እርሱን የማዘዝ፥ የመቆጣጠር ሙከራ ነው ብሎ ያመነውን ማንኛውንም ነገር በፅናት ይታገላል።
ፑቲንን ስታከብረው፥ በእኩልነት ስትመለከተው፥ ደህንነት እንዲሰማው ስታደርግ፥ እና እርሱ ሲያከብርህ ውጤታማ ድርድር የምታደርግ ይመስለኛል። ሌሎችን በመርዳት፥ በማገልገል ስራዎች ላይ አጋር ልታደርገው ትችላለህ። ፑቲን አጋር የሆነባቸው አያሌ አለም አቀፍ ስምምነቶች ተደርገዋል፥ አሜሪካ የተሳተፈችባቸው።
በአንፃሩ አልተከበርኩም፥ እንደ ታናሽና ታዛዥ ተቆጠርኩ ብሎ ካመነ ድርድርን እርሳው። አሰቃቂ ግጭት ውስጥ ትገባለህ። ጨካኝ፥ ፈላጭ ቆራጭ፥ ወንጀለኛ፥ አጭበርባሪ፥ በቀለኛ፥ ነፍሰ ገዳይ፥ አረመኔ ሊሆን ይችላል። እንዲያም ሆኖ ባልከፋ ነበር። ግድየለሽነቱ፥ እጅ ከመስጠት ይልቅ የማይታዘዘውን ሁሉ የማውደም አዝማሚያው ግን ያስፈራል።
______________________________________________
-----------------------------------------------------------------------

                          አብየ መንግሥቱና በርትራንድ ረስል
                              እሱባለው አማረ

              ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹የመንግስቱ ለማ ትዝታዎቼ - በእንግሊዝና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በጻፉት ባለ አስራ አንድ ገጽ ትውስታ ይህን ይላሉ፦ስለ አብዬ መንግሥቱ ለማ (ካም ቲዩብ)-ግንቦት 25-2010 – kAMM Tube / ካም ቲዩብ/
“ሌላው መቼም የማልረሳው ትልቅ ቁም ነገር [መንግሥቱ ለማ] ከታላቁ የአውሮፓ ፈላስፋ ከበርትራንድ ረስል ጋር የተገናኘበትን አጋጣሚ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የወጣቶች ጀግና የነበረው ትልቁ ሊቅ የምዕራብና የምስራቅ አገሮች በሰላም መኖር የሚያስፈልጋቸው ስለመሆኑ ለመግለፅ ወደ ት/ቤታችን ይመጣል፡፡ ታዲያ ፈላስፋው ንግግሩን ይጀምርና እሱ የሚለው ዓይነት ሰላምና አብሮ መኖር በዓለማችን እንዲሰፍን ለማድረግ የሚቻለው ኃያላኑ አገሮች በተቻለ መጠን አንዱ ተሰሚነት ባለው ክልል ሌላው ጣልቃ እንዳይገባ በመከላከል ብቻ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በዚህ መሰረት ሰላም ከተፈለገ ሶቪየት ህብረት በምስራቃዊ ግማደ ዓለም ‹‹ዶሚናንት›› እንደሆነች ትቀጥል ዘንድ ሊፈቀድላት እንደሚገባና በአንፃሩም ምዕራባዊያን ኃይሎች ደግሞ በአፍሪካና በአብዛኛው እስያ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲኖራቸው መደረግ እንደሚኖርበት ይገልፃል፡፡ በዚያን ጊዜ ስብሰባው ይገመሳል፡፡ ጉባኤው በዚህ አስተሳሰብና ፕሮፓዛል መስማማቱና ሰላምን ለማምጣት ያለውም አማራጭ ይኸው ብቻ መሆኑን አሜን ብሎ የተቀበለ መሆኑ ግልፅ ይሆናል፡፡ ለመንግሥቱ ግን ሁኔታው እንዲያ አልነበረም፡፡ አጅሬ ተቀምጦ ከነበረበት አዳራሹ የኋላ አካባቢ ከማንም ቀድሞ በመነሳት ንግግር ማሰማት ይጀምራል፡፡ የአፍሪካ ህዝቦች የማንም ተፅዕኖና ‹‹ዶሚኔሽን›› ሳይኖርባቸው እንደማንም አገርና ህዝብ ነፃ ሆነው መኖር እንደሚፈልጉ በአፍሪካዊነቱ አብራርቶ ገለፀ፡፡ /ይህ የሚሆነው እንግዲህ አፍሪካን ከቅኝ ገዥዎች የማስለቀቁ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ ቢያንስ አንድ አስርት ቀደም ብሎ መሆኑ ሊታወስ ይገባል/ ታላቁ ፈላስፋ ወደደም ጠላ መንግስቱ ሆዬ ሀሳቡን በመቀጠል አፍሪካውያን ከዚያ በኋላ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ለመቀጠል አንዳችም ፍላጎት እንደሌላቸው በማስረዳት ተቃውሞውን በይፋ አሰምቶና ራስልን ያህል ሰው ተጋትሮ ቁጭ አለ፡፡”
እንግዲህ፣ አብየ መንግሥቱ ለማ በዘመኑ ገናን ፈላስፋ ተደርጎ ይሰፈር የነበረውን በርትራንድ ረስልን እንዲህ በዘመነ ሐሳብ በአደባባይ ረትተውት ነበር፡፡ ዛሬ በርትራንድ ረስልን የሚያደንቅ (ምናልባት የሚያመልክ)፣ አብየ መንግሥቱ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክን የማያውቅ (ምናልባት ከነመፈጠራቸው) ኢትዮጵያዊ ብዙ ነው፡፡
ምን ይበጀናል?
__________________________________________

                  ያንድ ምሽት አሳብ
                       በእውቀቱ ስዩም
በጎረቤቱ የጨከነ ለቤተሰቡ አይራራም (በእውቀቱ ስዩም) - Bawza
በሺህ ፈረስ ጉልበት፥ በሺህ ግመል አቅም
ሺህ ጊዜ ቢራመድ፥ ሰው ከቤቱ አይርቅም::
ስጥል ዋልኩኝና፥ ስወድቅ አመሸሁ
ትግሉ ሲበረታ ፥ ወደ ቤቴ ሸሸሁ ፥
ሌቱ ጣራየ ላይ ፥ እንደ እንጀራ ሰፋ
እፍ አልኩት ኮከቡን ፥ እንደ ኩራዝ ጠፋ::
እንግዲህ ምን ቀረኝ?
ምንድነው ያማረኝ?
ወገግ
ፈገግ -ልበል?
ፊትሽን አስቤ?
አልጋ ላይ ልንበልበል
እንቅልፍን ከጎሬው ፥ እንደ ጋኔን ስቤ?
ወዲህ ውብ ትውስታ፤ ወዲያ ንጹህ አልጋ
የቱ ይመረጣል? ያም ተድላ፥ ያም ጸጋ
ገላ ሲስለመለም፤ ልብ ይቀሰቀሳል
ለጊዜውም ቢሆን
እንቅልፍ እና ፍቅር መከራን ያስረሳል።

  ከኢድሪስ ሻህ
ዛሬ ደግሞ ወደ አፍጋኒስታን ተረትና ስነ-ቃል ልውሰዳችሁና አንድ ውብ ወግ ላውጋችሁ። ይህንን ወግ በልጅነቴ የማውቀው ቢሆንም፣ አሁን በማወጋችሁ ቅርጽ ተጽፎ ያነበብኩት ከኢድሪስ ሻህ ድርሰቶች ጋር ከተዋወቅኩ በኋላ ነው። ኢድሪስ ሻህ በአባቱ አፍጋናዊ፣ በእናቱ ደግሞ ስኮትላንዳዊ ሲሆን በአፍጋኒስታንና በመካከለኛው እስያ የሚነገሩትን ጥዑም የሆኑ የሱፊ ወጎችንና ህዝባዊ ስነ-ቃሎችን በተለያዩ መጻሕፍት አሰባስቦ ለዓለም ህዝብ በማስነበቡ ይታወሳል። ከኢድሪስ ሻህ ድርሰቶች መካከል ዝነኛ ለመሆን የበቁት በሙላህ ነስሩዲን ላይ በተከታታይ የጻፋቸው መጻሕፍት ናቸው።
ስለ ኢድሪስ ሻህ ይህንን ያህል ካልኳችሁ ለጊዜው ይበቃል። አሁን ወደ ተረቱ ልውሰዳችሁ።
ሶስት ባልንጀራሞች ወደ ሩቅ ሀገር ጉዞ ጀመሩ፡፡ የመንገዱን አጋማሽ ከሄዱ በኋላ የግመል ፋንዲያ ታያቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ “ይህንን ፋንዲያ የጣለው ግመል ጅራተ-ቆራጣ ነው” አለ፡፡ ሰዎቹ እንደገና ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት ከተጓዙ በኋላም ምሳ መብላት አሰኛቸውና ከአንድ ዛፍ ጥላ ስር አረፉ፡፡ እዚያ ሳሉም የቡድኑ ሁለተኛ ሰው ወደ ላይ አንጋጦ እያየ “ከዚህ ዛፍ የበላው ግመል አንድ-ዐይና ነው” በማለት ተናገረ፡፡
ሰዎቹ ምሳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንደገና መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ በመንገዳቸው ላይም ግመል የሄደበትን ፋና አዩ፡፡ በዚህን ጊዜም የቡድኑ ሶስተኛ ሰው “ይህንን ዳራ (ፋና) በአሸዋው ላይ ያሳረፈው ግመል ከባድ እቃ ተጭኖበታል” በማለት ተናገረ፡፡
ሰዎቹ ጥቂት ከተጓዙ በኋላ “አንድ ግመል ጠፍቶብኛል፣ በዚህ መንገድ ስትመጡ አይታችሁታል?” ከሚል ሰው ጋር ተገጣጠሙ፡፡
አንደኛው ሰውዬ: “ግመልህ ጅራተ-ቆራጣ ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “ግመልህ አንድ ዐይና ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን! ትክክል ነህ”
ሶስተኛው ሰው፡ “ግመልህ ከባድ እቃ ተጭኖበታል?”
ባለ ግመል፡ “በትክክል!”
ሶስቱም በአንድነት፡ “ግመልህን አላየነውም፣ ሂድና ፈልገው ወንድም”
ባለ ግመል፡ “እንዴ ምልክቱን አንድ በአንድ እየነገራችሁኝ ሂድና ፈልገው ስትሉኝ አታፍሩም? ግመሌን ስርቃችሁታልና ቶሎ መልሱልኝ፡፡ አለበለዚያ ከዳኛ ላይ ከስሼ አስቀፈድዳችኋለሁ”
ሶስቱ ሰዎች፡ “በእውነት እኛ አላየነውም”
ባለግመሉ በሶስቱ መንገደኞች አባባል ተናድዶ ከዳኛ ላይ ከሰሳቸው፡፡ ሶስቱ ሰዎች ከተከሰሱበት ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡ ዳኛውም “እናንተ ግመሉን ለምን ሰረቃችሁት?” አላቸው::
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ አልሰረቅነውም። ጭራሽ ግመሉን አላየነውም”
ዳኛው፡ “ታዲያ ሰውየው ግመሌን አይተውታል ነው የሚለው?”
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ ስለግመሉ የተናገርነው በመንገድ ላይ ካየናቸው ምልክቶች ተነስተን ነው” ዳኛው፤ “እስቲ ያያችኋቸውን ምልክቶች ንገሩን”
አንደኛው ሰውየ፡ “እኔ ግመሉ ጅራተ ቆራጣ ነው ያልኩት በመንገድ ላይ ካየሁት የግመሉ ፋንዲያ ተነስቼ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ያየሁት ፋንዲያ በአንድ ቦታ ተከምሯል። ግመሉ ጅራት ቢኖረው ኖሮ በጅራቱ እየመታው ስለሚበታትነው በአንድ ቦታ አይከመርም ነበር፡፡ ስለዚህ ፋንዲያው በአንድ ቦታ የተከመረው ጅራት ስሌለው መሆን አለበት”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “እኔ “ግመሉ አንድ ዐይና ነው” ያልኩበት ምክንያት በግመሉ የተበላውን ዛፍ አይቼ ነው፡፡ ያየሁት ዛፍ በአንድ ጎኑ ብቻ ተበልቷል፡፡ የዛፉ ሌላኛው ክፍል ግን ምንም አልተነካም፡፡ ግመሉ በሁለቱም ዐይኖቹ የሚያይ ቢሆን ኖሮ ዛፉን በሁለቱም በኩል ይበላው ነበር፡፡ አንድ ዐይና በመሆኑ ግን የዛፉን ሌላኛውን ክፍል ሳይነካው ሄዷል”
ሶስተኛው ሰውዬ፡ “እኔም ግመሉ ከባድ እቃ ተጭኖበታል ያልኩት የግመሉን ፋና አይቼ ነው፡፡ የግመሉ ፋና ወደ አሸዋው ውስጥ ሰርጉዶ ገብቷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግመሉ ከባድ እቃ የተጫነበት በመሆኑ ነው፡፡ ግመሉ ቀላል እቃ የተሸከመ ቢሆን ኖሮ የእግሩ ፋና ከአሸዋው ውስጥ ጠለቅ ብሎ አይገባም ነበር”
ዳኛው በሰዎቹ ብልህነትና አስተዋይነት ተገረመ፡፡ ከዚያም “በጣም አስገራሚ ሰዎች ናችሁ፡፡ እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ነው የሰጣችሁን፡፡ የማስተዋል ችሎታችሁ ያስደምማል፡፡ እናንተ ከግመሉ ስርቆት ነጻ ናችሁ” በማለት አሰናበታቸው።


   ለየመንና ሊቢያ እንኳን የተባበሩት መንግስታት (UN) እንዲህ አልተሰበሰበም። የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲህ ለምን ራስ ምታት ሆነባቸው? ብላችሁ ጠይቁ! ጉዳዩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ስለሆነ ነው። የኛ ማንሰራራት፣ የነጭ ታዛዥ አሽከር አንሆንም ማለት፣ ከባሪያ ንግድ ጀምሮ የተዘረጋውን የምዕራባውያን ስውር ቀንበር የሚሰብር ኃይል ነው። ኢትዮጵያ የእውነት፣ የማንነት፣ የነፃነት፣ የእምነትና እኩልነት መፍለቂያ ሆና ለዘመናት ኖራለች፣ ከኛ በላይ ይህን እውነት ጠንቅቀው ያውቁታል። በታሪክ፣ ጂኦግራፊና ፖለቲክስም ቁልፍ ሚና አላት። ባጭሩ የኢትዮጵያ መንቃት የአፍሪካ መንቃት መነሻ ነው።
ይሄ በውሸትና አፍሪካውያንን በመበዝበዝ ላይ የተመሰረተ “ዘመናዊ” የእነአሜሪካ ኃያልነት በእነ ቻይናና ሩሲያ ፉክክር ገጥሞታል። አፍሪካውያን ራሳቸውን ችለው የቆሙ እለት ደግሞ ያበቃለታል። እናም እንደ ቆሌ የሚያንቀዠቅዣቸው ይሄ ፍርሃት ነው። አሁንም ደግሜ የምነግራችሁ ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ እምሽክ ቢል UN ደንታው አይደለም። እንዳንሸወድ። አንድነታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ይጠንክር!!!!


Saturday, 28 August 2021 14:33

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by

   "ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት በቂ ነው!"
                                         ደጀኔ አሰፋ


                    ወዳጅ ሃገራት ዛሬ ነሐሴ 20 ቀን 2013 በፀጥታው ምክር ቤት ያስተጋቡት ድምፅ፡-
••••••
አባት ሃገር ራሽያ ቃል የለንም!!! በቃ ዝም ብለናል!!
እህት ሃገር ቻይና ውለታሽን ለመመለስ ያብቃን!!
ወዳጅ ሃገር ህንድ ያደረግሽውን አንረሳውም!!
ወዳጅ የሰጠን የኢትዮጵያ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!! ኢትዮጵያ ብቸኛ አይደለችም!! ኢትዮጵያ አትረሳውም!!
ኬንያ እንዳለች አይቆጠርም!! አፍሪካዊ ስትሆን ያኔ እንገናኛለን!! ከቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ እናወራለን!!
እንኳንም ጆሞ ኬንያታ ያልኖሩ!!! ለኡሁሩ አዘንኩ!!
ዛሬ .... የአሜሪካ ሸፍጥ ተደፍቋል!!
የእንግሊዝ ሴራ መና ቀርቷል!!
አሜሪካ ብቻዋን ቆማ እራቁቷን ቀረች!!
እንግሊዝ ክፋቷን ይዛ ተቁለጭልጫ ቀረች!!
ጌታቸው ረዳ፣ ባይደን ያድንህ እንደሆን ዛሬ ተናገር!!
ጁንታው ህፃናትን ለጦርነት መማገዱን ግፍና ሰቆቃ መፈፀሙን፣  የተኩስ አቁም ስምምነትን መግፋቱን፣ አማራና አፋር ክልሎችን መውረሩ... በአጠቃላይ በአሜሪካ ቀሚስ ስር ለወራት የተደበቀው የጁንታው ግፍ እና ወንጀል ተጋለጠ!!
 እውነት አሸነፈ!!!
አሜሪካም እንግሊዝም ጁንታውም በፀጥታው ምክር ቤት ተወቀጡ!! ተሸከሸኩ!! ፈጣሪ በወዳጆቻችን በኩል አሳፈራቸው!! ረፈረፋቸው!! ከእውነት ጋር ተጣልተዋልና ያፍራሉ!! ገና ይሸማቀቃሉ!! ኢትዮጵያ እያሸነፈች እየጎመራች ትቀጥላለች!! ተመስገን!!
“በዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን የቆማችሁ ሃገራትን አመሰግናለሁ!! በአንፃሩ ጫና እናድርግ የምትሉና “ነገሽን ልወስንልሽ” የሚሏት ሃገራት ግን ሃገሬ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነፃነት ታሪክ ያላት ናት!! እሴትና ሞራል ያላት ሃገር ነች!! ማንም ጫና ስላደረገብን ወይም ጉዳዩን ሴንሴሽናል በማድረግ አይሆንም!! ለህዝባችን መደረግ የሚገባውን ነገር እናውቃለን!! የውጭ ጫናን የሚቀበል አንዲትም ኢትዮጵያዊት_ነፍስ እንደሌለች ካለፈው ተምራችሁ አሁን ትክክለኛውን ትምህርት ብትወስዱ እመክራችኃለሁ!!” ብሏቸዋል - የኢትዮጵያ ልጅ፣ ታዬ አፅቀስላሴ - ለአሜሪካ ለእንግሊዝና መስሎቻቸው....
አሁን በዓለም አደባባይ .....
ቅቡልነትና አቅም ያለው መንግስት እንዳለን ወዳጆቻችን መስክረዋል!! ችግሩን በራሳችን እንደምንፈታው ተነግሯል!! በሰብአዊ እርዳታ ስም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መዳፈር ክልክል ነው ብለዋል!! ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን ደግመው ደጋግመው አረጋግጠዋል!! ሌሎችም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል!! ዶክተር አብይ አሻንጉሊት መንግስት ስላልሆነላቸው፣ ለጊዜው ምጣችን ቢበዛም ዘለቄታዊ ጥቅማችን፣ ታሪካዊ የነፃነት ክብራችንና ሉዓላዊነታችን ተከብሮ ለዘላለም እንዲኖር ስለሚሆን የወቅቱን ፈተና እንደ ሙሉ ደስታ እንቆጥረዋለን!! አብቹ በርታ!! የምወድህ የሃገሬ ህዝብ በርታልኝ!! የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ማስጠበቁ ለዛሬው ውጤት ማማር ሚናው የትየለሌ ነው!! አንድ ስንሆን ወዳጆቻችን ደስ ይላቸዋል!! ጠላት ይዋረዳል!! ጉልበታችን ያይላል!! አሁንም እንቀጥል!! አንድ እንሁን!! እንበርታ!! እንያያዝ!! መጭው መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ ነው!! በጣም ደስ ብሎኛል!! ደስስስስ ይበላችሁ!! የኢትዮጵያ አምላክ ዛሬም የተመሰገነ ይሁን!! ወዳጆቻችን ይባረኩ!! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!




            የጥላቻ ቃላትና ሀረግ ለዘር ፍጅትና ለዘር ማጥፋት አቀጣጣይ መሳርያ ሆነው ያውቃሉ:: በዚህ ሰበብ በየሀገሩ በሕግ የታገዱና የሚያስጠይቁ ቃላት፣ ሀረግና ምልክቶች አሉ፡፡ የሃገር፣ የዜግነት፣ የሰንደቅ ዓላማን ክብር የሚያዋርዱ፣ በማንነት፣ በቀለም፣ በጾታና በሃይማኖት ላይ ተመስርተው ጥላቻና የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ የሚያደርጉትን በሕግ ያገዱ በርካታ ሀገራት አሉ፡፡ ሩዋንዳ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየምና ካናዳ ጥቂት ምሳሌ ናቸው፡፡
“እቺ ሀገር” የሚለው ሀረግ ኢትዮጵያ ሀገሬ ወይም ሀገራችን የሚለውን ቃል ተክቶ ወደ መዝገበ ቃላታችን ከገባ 30 ዓመት ሆኖታል፡፡ ቃሉ አግላይ፣ የሀገር ክብርን የሚደፍቅና እራስን ከሀገር የሚነጥል ነው። ሀረጉ በተለይ ኢትዮጵያን ሀገሬ ብሎ መጥራትን የሚጸየፉ ነገር ግን ጥቅሟን የሚፈልጉ ሃይሎች የፈጠሩት ከፋፍለህ ግዛው ነው፡፡ ይህ ጸያፍ ሀረግ ተደጋግሞ ስለተነገረ ዛሬም አዕምሯችን ላይ ታትሞ ከላንቃችን ጋር ተጣብቆ አልላቀቅ ያለን በባለስልጣኑ፣ በአርበኛው፣ በሰራዊቱ አባላት፣ በፖለቲከኛውና በአክቲቪስቱ ዘንድ እንደዘበት የሚነገር ቃል ሆኗል፡፡   
ላላፉት 30 ዓመታት የሀገርን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ፣ ከፋፋይ፣ እርስ በርስ የሚያናቁሩን፣ የክፋትና የመሰሪነት ቃላት እንደ አሸን ተራብተው በጥላቻ እንድንተያይና በደም እንድንፈላለግ አድርገውናል፡፡ እነዚህ ቃላት እስር፣ እንግልትና ስደት ካደረሱብን ጉዳት በላይ እንደ ተተኳሸ ጥይት በመሆን አስጠቅተውናል፣ ለጥላቻና ለግጭት ዳርገውናል፣ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ከባድ ዋጋ አስከፍለውናል ፡፡
ኢትዮጵያ ሁላችንንም አቅፋና ደግፋ የምትይዝ ለሁላችንም የምትመች የእኩልነት ሀገር እስክትሆን ድረስ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን በርካታ ተሃድሶዎች ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ አንዱ ተሃድሶ ደግሞ እንዲዚህ ዓይነት ከፋፋይና ለጥፋት በመሳርያነት የሚያገለግሉ ቃላቶችን ከመዝገበ ቃላታችንና ከአንደበታችን የሚያስወገድ የባህል አብዮት ማካሄድ ነው።
እንዲወገዱ የምንሻቸው፣ እነዚህ ቃላት በትውልድ ወስጥ ዳግሞ እንዳያንሰራሩ ከመገናኛ ብዙኅን፣ ከትምህርት ተቋማትና በአስተዳደር ቋንቋነት ጭምር መገልገያ ከመሆን በሕግ እንዲታገዱ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኢትዮጵያዊነት የትኛውንም ጫናና ተጽእኖ ተቋቁሞ የሚዘልቅ ጽንሰ ሃሳብ እንደሆነ ዛሬም በተግባር እየታየ ነው። የበለጠ እናጠብቀውና መደላድሉን እናጠነክረው ዘንድ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያውያንን የከበበውን ፈርጀ ብዙ እሾህና አሜኬላ በየጊዜው ልናጸዳና ልናጠራ ያገባል፡፡

   (አማን መዝሙር)
ዘንድሮ መቼስ ያላየነው የለም። ቅድም በቴሌቭዥን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እጅግ ብዙ ለመዝመት የተሰበሰቡ ወጣቶች በጥላሁን ገሰሰ «እናት ሐገር ኢትዮጵያ» በሚለው ዘፈን እየዘለሉ ሲጨፍሩ አይቼ ገረመኝ። ኸረ የኢትየጵያን ባንዲራ አቅፎ የሚያለቅስ ቄሮ (ያው ወጣት ሁሉ ቄሮ ነው) አየሁና ለመጀመሪያ ጊዜ የገዛ ህዝቤን እንደማላውቀው ተሰማኝ!
መቼስ ይሄ ሁሉ ወጣት ተከፍሎት ነው ወይም አስፈራርተውት ነው የዘመተው ለማለት ይከብዳል። እሺ አስፈራርተውት ይዝመት፣ አስፈራርተውት ግን በጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ልቡ እስኪጠፋ አይጨፍርም
ብቻ በዚህ ሶስት አመት ያላየነው ነገር የለም። ነገሮች እንደ ሰርከስ ትግራይ ሲገለባበጡ አይተናል።
ባለፈው ስታሊን የሚባል የህውሓት Gifted ውሸታም አለ። ውሸት በማን ያምራል ብትሉኝ በስታሊን እላችኋለሁ። በቃ ተፈጥሯዊ ውሸታም ነው። ታለንትድ ነው። የሚዋሸውን ነገር መጀመሪያ ራሱ አምኖት ነው እሚዋሸው። መዝናናት ስፈልግ እሱን ነው እማየው።
ባለፈው የኢትዮጵያ መከላከያ መቀሌ ሊገባ ሰአታት ቀርቶት ሁሉ ስታሊን በቴሌቭዥን መጥቶ «ለወሬ ነጋሪ ሳናስቀር እየደመሰስን ነው» ይል ነበር። እስከዛሬ ስታሊን የደመሰሳቸው ወታደሮች ብዛት እንኳን ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የለም። መቶ አስር ሚሊየን ህዝብ ደምስሶ ጨርሶ ከመጪው ትውልድ ሁሉ እየተበደረ ደምስሷል። ናቲና ሙክታሮቪች’ኮ አንዳንዴ ስልታዊ ማፈግፈግም ያደርጋሉ። ስታሊን አያፈገፍግም። የኢትዮጵያ ወታደር መቀሌ ገብቶ ራሱ ስታሊን ብቻውን ቆቦን ተቆጣጥሮ ቆይቷል። አንዳንዴ እንደ ቻርሊ ቻፕሊን ብቻውን አንድ ሜካናይዝድ ጦር ይከብባል። ስታሊን ያልጣለው አውሮፕላንም የለም። ደስ ሲለው እንደውም ሰው አልባ ድሮን በሚሳኤል ይመታና ፓይለቱን ይማርካል ብቻ ልጁ ያዝናናኛል።
እና ይሄ ስታሊን ባለፈው ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ጋቢሳ ከተባለ ባጠናው ባጠናው ምን እንደሚፈልግ እስከ ዛሬ ካልገባኝ ሰው ጋር ይወያያል።
እንዲህ አለ ስታሊን፤ «እንደው ግን ቄሮ ምነው ዝም አለ? ለምን ይሄን እድል ተጠቅሞ መንግስትን አያንቀጠቅጥም? ምን ሆኖ ነው ጭጭ ያለው?» ሲል ህዝቅኤል እንዲህ አለ ... «እኔም ግራ የገባኝ እሱ ነው»
እኔን ግራ ይግባኝ ሲመስለኝ ቄሮ ትግሉን ጨርሶ «ትግልህን ጨርሰሃል ወደ ቤት ግባ» ተብሎ ወደ ቤቱ ከገባ ቆየ። በወንድማማች መሃከል ያለ conflict of power አይመለከተውም። ይኸው አሁን ሁሉን ትቶ በጥላሁን ገሰሰ ዘፈን እስክስታ እየወረደ ወደ ጎንደር እየተጓዘ ነው። (እዚች ጋ ፈገግ እንላለን )




               እና...
እባክህ መንግስት ሆይ! አንዳንዴ ከአይሁድ መጽሐፍ (ቅዱስ) ፊትህን አዙርና የሀገርህን ስነ-ጽሑፍ አንብብ። ሃዲስ አለማየሁ በፍቅር እስከ መቃብራቸው፣ በፊት አውራሪ መሸሻ የግብር እልፍኝ የተገኘው በዛብህ ቦጋለ፣ በ”ማህሌተ ገንቦው”፣ እመቤቲቱንና ጌቶችን ሲያወድስ፣ ፊታውራሪ መሸሻ ግምጃ ቤታቸውን ጠርተው “ንሳ ንሳ ይሄንን ድማም ተማሪ  ሙሉ ልብስ ሸልመህ አምጣልኝ።” እስከ ማለት ያደረሳቸውን ትዕዛዝ ያሰጣቸውን ውዳሴ ያገኙት መጠጥ ከጠጣ የቅኔ ተማሪ ነበር። (ፍቅር እስከ መቃብር ገጽ 81-82)
የአዳም ረታችን “ግራጫ ቃጭሎች” ያ እምቦሳው መዝገቡ፣ የእእን ቁጣ ግልምጫና አቃጣሪነት፣ የአባቱን የዱቤን እርግጫና ኩርኩም ከቁብ እንዳይቆጥር ያደረገውና ያስረሳው ጉዳይ፣ የማንቆርቆራ ጠጅ መሆኑን አለማንበብህም ጎድቶሃል። (ግራጫ ቃጭሎች ገጽ 41-43)
አለማየሁ ገላጋያችንም “ቅበላ” በተሰኘ መጽሐፉ፤ “ሕይወት አሰልቺና አታካች መሆኑ የሚታወቀው መጠጥ በጠጡ ሰዓት ነው።” ይለናልም። (ገጹ ጠፍቶኛል)
በእውቄያችንም “አዳምኤል” በተሰኘች መድበሉ ማህሌተ ገንቦ የተሰኘች ግጥም አለችው። ጽዋችንን ከፍ አድርገን ቸር የዋሉልንን ስለማወደስ የምታወሳ ግጥም ናት። እንዲህ ትሰኛለች።
ማህሌተ ገንቦ
ባጭር ቀረን ስንል - እድሜ ላበደሩን
ቀርፀው ላሳመሩን
ለኩሰው ላበሩን
ቺርስ!!
ፊታችንን ዐይተው
እንደተቸገርን - ካይናችን ላወቁ
ስለማርያም ብለን
እስክንለምናቸው - ቆመው ላልጠበቁ
ቺርስ!!!
ወድቀው ለማይጥሉ -ነግሰው ለሚያነግሱ
ነውራችንን ዐይተው
ልክ እንደ ድመት ኩስ ፣ ለሚያለባብሱ
ብድር አበድረው ፈጥነው ለሚረሱ
ቺርስ!!!!
ላባ ላረጉልን ፣ የመከራ ሸክሙን
ቀልደው ላሳቁን ፣ ተጫውተው ላከሙን
በቸከ ዘመን ላይ-
ስጋ ለበስ ትንግርት -ሆነው ላስደመሙን
ቺርስ!!!!!
(አዳምኤል ገጽ 21)
መጠጣት የምንፈልግበትን ብዙ ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ የሥነ-ጽሑፍ ፊታውራሪዎቻችንን ካነበብክ ግን በበቂ ይነግሩሃልና አንብብና እኛን ፍታን። እንጠጣበት።


Tuesday, 03 August 2021 17:15

የተጠላች ሰላም!

Written by

 የጅብ ቆዳ ገፍፈን - ከበሮ ብንወጥር፥
“እንብላው” ጩኸቱ - በተመታ ቁጥር::
ኧረ ምን ኾነናል?
በሰላም ዐልጋ ላይ - በጦርነት መብረቅ - ስናልቅ ይታየናል!
ምነው ሰላም ፈራን?
የሚጮኸው ኹሉ - ወደ ባሩድ ሽታ - ዘውትር የሚመራን?

 መክፈቻ፡-
ቻርለስ ዲከንስ (ነፍስ ይማር!) “A Tale of Two Cities” የተባለውን ዝነኛ መጻሕፉን፣ በዚህ ዝነኛ አንቀፅ ይጀምረዋል (ይከፍተዋል)፡፡
“It was the best of times, it was the worst of times, it was the age of wisdom, it was the age of foolishness, it was the epoch of belief, it was the epoch of incredulity, it was the season of Light, it was the season of Darkness, it was the spring of hope, it was the winter of despair, we had everything before us, we had nothing before us . . .”
በምድር ቆይታዬ ከዚህ አንቀፅ በተሻለ የሰው ልጅን ሕይወት የሚወክል የቃል ስብስብ አላየሁም፡፡ የሕይወት ታሪክህ የትም መቼም ቢፈጭ፣ ዱቄቱ ከዚህ አንቀፅ የተለየ አይሆንም፡፡
ሕይወትህ በዚህ የመክፈቻ አንቀፅ ይከፈታል፣ በዚህ የመክፈቻ አንቀፅ ይጠረቀማል፡፡
መጠርቀሚያ፡-
ሌቭ ኒኮላየቪች ቶልስቶይ (ነፍስ ይማር!) “What Men Live By and Other Tales” በሚል ርዕስ ባሳተመው ክፍለ-ዘመን-ጠገብ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ ውስጥ “Three Questions” የተሰኘ ታሪክ ተካትቷል፡፡ የዚህ ታሪክ የመዝጊያ (የመጠርቀሚያ) አንቀፅ፣ የሕይወትህን የመሀል መልክ ያሳይሃል፡፡ የሕይወትህ የመሀል መልክ ይህ ነው፡-
“… There is only one important time and is Now. The present moment is the only time over which we have dominion. The most important person is always the person with whom you are, who is right before you, for who knows if you will have dealings with any other person in the future. The most important pursuit is making that person, the one standing at you side, happy, for that alone is the pursuit of life.”
ሕይወት በዲከንስና በቶልስቶይ ሜዳ ላይ ያለች ኳስ ናት፡፡ (ለአንዳንዱ የጨርቅ፣ ለአንዳንዱ የወርቅ ኳስ!) ሕይወታውያን ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሕግና እረፍት አልባ የጽሞና ጨዋታ፡፡ አንዳንዶች ጽሞናውን ሰብረው ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌ መንግሥቱ ለማ (ነፍስ ይማር!)
“ምንድነው ሰበቡ…
ለምንድነው አልኩኝ፤ ለምን ምክንያት፤
ይህ ዓለም መኖሩ አዱኛ ሕይወት፤
ህጻን መወለዱ አርጅቶ ሊሞት፤
ለምንድነው አልኩኝ
ለምን ምክንያት፡፡”
ደግነቱ!.... ደግነቱ!.... በዚህ ሜዳ ግብ የሚያስቆጥርም ሆነ የሚቆጠርበት የለም፡፡ በቃ!... በቃ!... ተጫውቶ… ተጫውቶ…
ተጫውቶ… ተዝለፍልፎ መውደቅ፡፡
ዛሬ ልደቴ ነው (ነፍስ ይማር!)

Saturday, 17 July 2021 15:46

አስታራቂስ ማነው?

Written by

ጥግ ጥጉን መያዝ ለሕዝባችን ይጠቅማል ብሎ ኹሉም ለሕዝቡ ራሱን ወክሎ ሲቆራቆዝ በሚውልበት ጊዜ፣ ያንንም ይህንንም፣ ግራውንም ቀኙንም፣ ያልያዙ ሰዎች የግድ ያስፈልጉናል። ሕዝብም ኾነ ግለሰቦች ዕድሜ ልክ አይቀያየሙም፤ አንድ ወቅት ዕርቅ ይፈለጋል። አስታራቂ ሽማግሌ እንደ አባይ ድርድር ከውጭ ሀገር ልናፈላልግ ነው?
ሽማግሌነት በዕድሜ መኾኑ እየቀረ የመጣ ይመስለኛል። ባለዕድሜዎቹም በጊዜው ማዕበል ተስበው ጥግ ጥጉን ይዘው እየተቆራቆዙ እያየን ነው። ተስፋ የሌለ እየመሰለ ነው። በዚህ መሃል ምንም ዓይነት መለኪያና ወሰን ሳይኖረው ጽንፉን ያልያዘ የግብር “ሽማግሌ” ያስፈልገናል፤ ኹሉም ቂም ያልያዙበት። ይህንን ሰው ከየት ነው የምናመጣው?
ማነው “አስመሳይ” ሳይባል “አንተም ተው፣ አንተም ተው” ብሎ ሊያደራድር የሚችልና በኹሉም የሚደመጥ? ማነው በሰው ቁስል እንጨት ሲሰድ የማይገኝ? ማነው “መኻል ሰፋሪ” እየተባለ ሲሰደብም ዋጥ አድርጎ መቆም የቻለ? ይህን ሰው መፈለግ ያለብን ጊዜ ላይ አይደለንም? እንዲህ ዓይነት ሰው ብቅ ብሎ “ተዉ! ምን እናድርግ?” ማለት ያለበት ጊዜ እየዘገየ አይደለም? ይህንን ዓይነት ሰው ወደ አደባባዩ አሁን ካላመጣን፣ ያለው አካሄድ መቼ እንዲለወጥ ነው የምንጠብቀው?


Page 1 of 3