Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 September 2011 09:47

ኢሕአዴግንም ተቃዋሚንም ያስማሙ ጉዳዮች - ግድብና የኑሮ ውድነት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሥልጣን መልቀቅና ሥልጣን መረከብን ለመለማመድ ያህል የሰንደቅ ዓላማ ቀን...
ዓውዳመቶቻችን የአፍሪካ ህብረትን መቀመጫ እንዳስቀይሩብን...  
አንዳንድ ጊዜ ሁላችንንም የሚያግባባ (የሚያስማማ) ነገር ሲገኝ ደስ ይላል አይደል... (ብዙ ጊዜ ከምንግባባበት
ይልቅ የማንግባባበት ስለሚበዛ ነው) እናም በ2003 ከአንድ በላይ የተግባባንባቸው ነገሮች ስለተገኙ እራሳችንን ..ኮንግራ!.. ብንል ግምት ውስጥ የሚከተን አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ምን መሰላችሁ? አንደኛው ያለ አግባብ የኢቴቪ የፕሮግራም ማድመቂያ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ነው፡፡

(ኢቴቪ በግድቡ ጉዳይ የድል አጥቢያ አርበኛ የሆነ አልመሰላችሁም?) በዚህ ጉዳይ መቼም እስካሁን ማንም ተቃውሞ አላሰማም (ግብን ጨምሮ)  
የኑሮ ውድነቱም ሌላው የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድ ድም ያስማማ ጉዳይ ሆኖ    አልፏል - በ2003 ዓ.ም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢሕአዴግም እራሱ የዋጋ ንረቱን መቼ ካደ? በእርግጥ በኑሮ ውድነቱ መነሻዎች ላይ ልዩነቶች ተስተውለዋል፡፡ ኢሕአዴግ የኑሮ ውድነቱ የመጣው ኢኮኖሚው ያለ ቅጥ በመመንደጉ ነው ብሏል ልበል? ተቃዋሚዎች ደግሞ ችግሩ ከኢኮኖሚ ፖሊሲው ነው በሚል ተወቃሹ ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ ኢህአዴግ ነው ባይ ናቸው፡፡ እንደው ከጀመርኩት አይቀር ብዬ ገፋሁበት እንጂ የዛሬ ወጌ ዋነኛ አጀንዳ ባለፈው ጳጉሜ 6 ቀን 2003 ዓ.ም ለግድቡ መገንባት አስተዋኦ ያደረጉ ወገኖች መሸለማቸው ነው፡፡ እንግዲህ እንደሰማችሁት ሕዝቡና የነጋዴው ህብረተሰብ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደየአደረጉት አስተዋኦ፤ ..ወደር የለሽ..፤ ..የላቀ.. የመሳሰሉት በየዘርፋቸው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ አሁን ስለ ሽልማቱ ወይም ስለ ሽልማቱ ደረጃ አይደለም የምናነሳው፡፡ ይልቁንም በዚህ የሽልማት ሂደት አንድ ከሽልማቱ የተዘነጋ ወሳኝ ቡድን እንዳለ ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ ምናልባት ከሁሉም በላይ ተሸላሚ መሆን የነበረበት ነገር ግን ሆነ ተብሎ ወይም በሐበሻ የይሉኝታ ባህል የተነሳ ሳይሸለም የቀረው አንድ ወገን አለ፡፡ እስቲ ማን እንደሆነ ገምቱ? (ሽልማት ባይኖረውም) 5 ሚሊዮን አባላት አሉኝ የሚለው (በሳይንስ ባይረጋገጥም) ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ነው እንዴ... ማነው የግድቡን ሐሳብ መጀመሪያ የጠነሰሰውና ነው? ማነው ራሳችን እንሠራዋለን ብሎ እኛንም ጭምር ያነሳሳው? (ምንም እንኳን ከአቅማችን በላይ ቢሆንም)
ቦንድ የሚሏትን ብልሃት አምጥቶ የተሰበሰበችውን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ የቻለው እኮ ..ኢህአዴግ ነፍሴ.. ባመነጨው የምዕተ ዓመቱ ድንቅ ሐሳብ ነው በርግጥ ..የወር ደሞዝ በዓመት.. በተባለችው መዋጮ በርካቶች ተማረው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ግን እኮ በኢሕአዴግ አልነበረም የተማረሩት፡፡ በመዋጮውም አልነበረም፡፡ በፍፁም!! የተማረሩት በድህነታችን ነው፡፡ የተማረርነው በኑሮ ውድነቱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ..ድህነትና የኑሮ ውድነቱም ቢሆኑ ግድቡን ከመገደብ ወደ ኋላ አናፈገፍግም.. በሚል ቆራጥነት እንዴት ደሞዛችንን እንደምንገድብ ደህና አድርጐ አስተማረን፡፡ ያቺ 80 ቢሊዮን. ብር ገና ገና .. ገና .. ገና .. ብትሆንም የኢህአዴግ አነሳሽነትና የእኛ (የህዝቡ) ተነሳሽነት ሳይደነቅ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ሆኖም ለሽልማቱ ጊዜ ግን ኢህአዴግ ለምን እንደተዘለለ አልገባኝም፡፡ እንኳን ሊሸለም ስሙ እንኳ አልተጠራም እኮ ስለዚህ በዚህች አጋጣሚ የታላቁ ግድብ የመመሰጋገን ፕሮግራም ላይ ብዙም ባይሆን ሚጢጢዬ ቅሬታ አለኝና እነሆ ተቀበሉኝ ብያለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ እስካሁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቅሬታ ሰሚ ቦርድ ተቋቁሟል ብዬ አምናለሁ፡፡ እናም ቅሬታዬን ተቀብሎ እንደሚሆን ያድርገው እላለሁ፡፡ (በቅድሚያ 50 በመቶ ክፈሉ የሚባለው ለግብር ብቻ ነው አይደል!) ያለዚያ መቼም ቢሆን መተዛዘባችን xYqRM (እፎይ ቅሬታዬን tnfSkù)    
ቀጣዩ ወጌ ከሰንደቅ ዓላማችን በዓል ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይሄ እንኳን ቅሬታ ሳይሆን ወደፊት ዝም ከተባለ ቅሬታ ሊሆን የሚችል ሐሳብ ቢጤ ነው፡፡ (እኔ የምለው የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበርን በተመለከተ የቅሬታ ሰሚ ቦርድ ተቋቁሟል እንዴ?)   
ሐሳቤ ምን መሰላችሁ? ይሄን በየዓመቱ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለምን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በሃላፊነት አንሰጣቸውም? ከእነ ሙሉ ክብሩና ግዴታW ማለቴ ነው፡፡ ያኔ እነሱም ከመቃወም ብቻ የተሻለ ሃላፊነትና ግዴታ ይሰማቸዋል፡፡ ቀስ እያሉ ሌሎች ሃላፊነቶችንም መስጠት ይቻላል፡፡ የዚህ ነገር ዋና ዓላማው ምን መሰላችሁ?   ኢሕአዴግም ሥልጣን መልቀቅን፣ ተቃዋሚዎችም ሥልጣን መረከብን በትንሽ በትንሹ እንዲለማመዱት ማድረግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ጥያቄ (ሐሳብ) በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ወይም እንደ ልጅነታችን በ..ፀባይ.. የተሰነዘረ መሆኑን ገዢው ፓርቲ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ወዳጆቼ በሰው ሥልጣን ድርቅ ማለት ለማንም አይበጅም፡፡  
አሁን ደግሞ እስቲ ወደ ማህበራዊ ጉዳዮች እንግባ፡፡ ስለ ዓውዳመቶቻችንና የጐንዮሽ ችግሮቻቸው (Side effects) ትንሽ እናውራ፡፡ አንድ ወዳጄ ሰሞኑን በዲቪዲ ሰጥቶኝ ያየሁት የውጭ አገር ኮሜዲ (Stand-up comedy) ትንሽ ደፈር ትንሽ ፈጠጥ ብሎብኛል- ለእኛ አገር ማለቴ ነው፡፡ ባለቤቶቹማ የለመዱት ነው፤ ባህላቸው ሆኗል፡፡ ኮሜዲያኑ በዜግነት አሜሪካዊ ይመስለኛል፡፡ በትውልድ ካናዳዊ ነው፡፡ በእናቱ ግን ህንዳዊ፡፡ በባህል ደግሞ የካናዳና የአሜሪካ ድብልቅ ነው፡፡ ይሄ ኮሜዲያን ረስል ፒተር ይባላል፡፡   
አቤት በዓለም ሕዝብ ሲላጥ! እድምተኞቹም የተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ናቸው፡፡ አረቦች፣ ቻይናዎች፣ ህንዶች፣ አሜሪካኖች፣ ጥቁሮች... ወዘተ በህንዶችና በቻይናውያን የአነጋገር ቅላፄ እንደጉድ ያሾፋል፤ ይቀልዳል፡፡ ታዲያ ፊት ለፊቱ ተቀምጠው እየሰሙት ነው፡፡ ያውም ፍርፍር ብለው እየሳቁለት፡፡ ማን ነበር ..የተዋጣለት ቀልድ የሚባለው የተቀለደበትም ወገን አብሮ ሲስቅ ነው.. ያለው፡፡ የሚቀልድባቸው ሁሉ አብረው በሳቅ ይፈርሳሉ! መጀመርያውኑ እኮ ገንዘባቸውን ከፍለው ወደ አዳራሹ ሲገቡ እንደሚቀለድባቸው እያወቁ ነው፡፡ ህይወትን ቀለል አድርጐ መውሰድ ማለት ይሄ ነው - ነገር አለማካበድ! በኢሕአዴግ ቀልደን ኢሕአዴጐች አብረውን ከሳቁ ቀልዱ የተዋጣለት ነው እንደማለት ነው፡፡ ኢሕአዴጐች ካኮረፉ ግን ቀልዱ ቀሽም ነው ይላሉ - የቀልድ ኤክስፐርቶች፡፡ ለተቃዋሚዎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ በተቃማዊዎቹ ላይ በተፈጠረ ቀልድ ተቃዋሚዎችም ሆዳቸውን ይዘው መሳቅ አለባቸው፡፡ ያለዚያስ? ሌላውን በሳቅ አፍርሶ ባለቤቶቹን ካስኮረፈ ደረጃውን የጠበቀ ቀልድ (ኮሜዲ) አይደለም ባይ ናቸው-የቀልድ ኤክስፐርቶቹ፡፡ (በ2004 ለኮሜዲያኖቻችን ትንሽ homework ሰጠኋቸው አይደል!?) ለነገሩ የፖለቲካ ዝንባሌ ያላቸው ኮሜዲያኖች እጅግ ጥቂት ስለሆኑ ብዙም አያስጨንቀንም፡፡ ወደ ረስል ፒተር ስንመለስ ለዛሬ ቦምቤይን በተመለከተ የቀለደውን እንይለት፡፡ - ከአጀንዳችን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ስላለው፡፡ ወደ እናቱ አገር  ቦምቤይ ሄዶ እንደነበር የሚያወሳው ረሰል፤ ..ልክ ከአውሮፕላን ስትወርዱ ሽታው አይጣል ነው.. ሲል የእናቱን አገር ቆሻሻነት (መጥፎ ሽታ) ይተቻል፡፡ ሁሉም ከአውሮፕላን ሲወርድ ..ካካ እያደረገ.. የሚያልፍ ነው የሚመስለው እስከማለትም ይደርሳል - ኮሚዲያኑ፡፡
የቦምቤይን አፍና አፍንጫ የሚያሲዝ ክፉ ሽታ ዝም ብዬ አላነሳሁትም፡፡ የሰሞኑን የመዲናችንን ሽታ በደንብ አጢናችሁታል? ወይስ አፍንጫችሁ ከመለማመዱ የተነሳ ትዝም አይለው? የእኛ አፍንጫ ትዝ ባይለውም የዓለማቀፉን ማህበረሰብ (International community) አፍንጫ እንደሚቆረቁረው ግን እንዳትረሱ፡፡ እኔ በበኩሌ ዓውዳመቶቻችን እንኳንም በዓመት አንዴ ብቻ የሚመጡ ሆኑ ብያለሁ! አውዳመት እንዲህ ከተማ የሚያበላሽ ከሆነ እኮ ብዙም እንዲመጣ የምንመኘው ላይሆን ነው! በእርግጥ ችግሩ ከአውዳመቶቹ ሳይሆን ከእኛው ይመስለኛል - ከእኛው ስል ከባህላችን፣ ከልማዳችን፣ ከኋላቀርነታችን፣ ከቸልተኝነታችን... ወዘተ... ወዘተ... ወዘተ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ወይ እኛ እንቀየር አሊያም ደግሞ አውዳመቱ ይቀየር! (ማለቴ የአውዳመት አመጋገባችን)
አንዳንድ የሥነ ባህል ተሟጋቾች በአውዳመት መብላት ይቅር ያልኩ መስሏቸው ዕድሜ ይፍታህ የሚያስበይን ወንጀል አድርገው ሊቆጥሩት ይችላሉ፡፡ እኔ ግን ሳስበው ከተማን ጤና በሚያውክ አሰቃቂ መጥፎ ሽታ ከመበከል የከፋ አደጋ ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንዳይሆን ሎቢ የሚያደርጉ ወገኖች ሁነኛ ሰበብ አድርገው ሊጠቅሱት እንደሚችሉ ማሰብ አይከፋም፡፡ (ጋዳፊ ቢሄዱም ሌሎች ጋዳፊዎች አይጠፉም) ይህቺን የአውዳመት ጉዳይና ተያያዥ መጥፎ የከተማ ጠረን ማንሳቴ መጪው የመስቀል በዓል ነው ብዬ ነው፡፡ እንኳን ለብርሃኑ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ!!

 

Read 2661 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 09:50