Saturday, 24 September 2011 09:43

ዘመን ሲልከኝ ባልታዘዝስ?

Written by  lelissagirma@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ከሶስት ሳምንት በፊት በዚሁ ጋዜጣ    ላይ ..ወፍጮው ውስጥ ያለው መንፈስ..     በሚል አርዕስት አንድ መጣጥፍ
አቅርቤ ነበር፡፡ ...መጣጥፉ በሰው ልጅ ውስጥ ያለውን ..መንፈስ.. ምንነትና ባህርይ ለመረዳት ሙከራ ያደረኩበት ነው፡፡ ...ዶ/ር ዳኛቸው (በአዲሱ አመት እትም ላይ) ያቀረቡት ሁፍ ደግሞ፤ የትውልድን ጥያቄ ከዘመን ተልዕኮ ጋር አገናዝቦ የሚያትት እንደነበረ ታስታውሳላችሁ፡፡በዶ/ር ዳኛቸው ሁፍ የሰፈሩት ሃሳቦች፤ በተዘዋዋሪ ከእኔ ጥያቄያዊ መጣጥፍ ጋር የተገናኘ ስለመሰለኝ፤ በነገሩ ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ለመጠየቅ ተነሳሁ (አንዳንድ ጥያቄ ከአሮጌው አመት ብቻ ሳይሆን ከአሮጌው ትውልድም ዘሎ አዲሱ ውስጥ ያስተጋባል)፡፡ ...በትምህርት ክ/ጊዜ ብቻ ሳይሆን ጋዜጣ ላይም በመጠየቅ፤ ከአዋቂ ሰው መልስ ማግኘት ይቻላል፡፡ ...አንዳንዴ ትክክለኛ ጥያቄ ራሱ መልስ ነው፡፡ ...ፍልስፍና ትክክለኛ ጥያቄን መጠየቅ ዋና ተግባሩ ነውና፡፡

ወፍጮውን የሚያሽከረክረውና የሚያንቀሳቅሰው መንፈስ ምንድነው?
ወፍጮውን የሚነዳው መንፈስ፤ ..የዘመን ተልዕኮ.. እንደሆነ ነው በዶክተር ዳኛቸው ሁፍ የተገነዘብኩት፡፡ ወፍጮው (ሰው)፣ የዘመንን ተልዕኮ አስፈፃሚ (አስፈጪ)፣ አልያም ፈፃሚ (ፈ) እንጂ፤ ሌላ ምንም አይደለም፡፡ ..የዘመን ተልእኮ.. የሚባለው ትእዛዝ ወይም መመሪያ ከማን ሊመጣ ይችላል?... ..የዘመን ተልዕኮ..ውን፣ ለልዑኩ የሚሰጠው፣ ፈጣሪ ወይም ታሪክ፣ አሊያም ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰው መራጭ ካልሆነ ምርጫ የለውም፡፡
ሥዩመ እግዚአብሔር የሆነው ንጉስ፤ በወፍጮ ቋንቋ ከተተረጐመ፤ አሌክትሪሲቲን ከማመንጫው ተቀብሎ፣ ሀይል ጨምሮ ወይንም ቀንሶ፣ ወደ ቤት የሚያቀርብ አንድ እቃ ነው፡፡ እንደ ትራንስፎርመር፣ ሰርኪዩት ብሬከር፣ ኮንትሮል ፓናል፣ ፓወር ግሪድ ... ወዘተ፡፡ ኮንትሮል ፓናል እና ወፍጮ ሁለቱም እቃ ናቸው፡፡ አንዱ የመፍጨት ሌላው የመቆጣጠር ተግባር በሰሪያቸው የተሰየመላቸው፡፡ መቆጣጠር ሳይሆን ለህዝቡ የበላይ ተልእኮን ከቀጥተኛ ኮረንቲ ወደ ህዝባዊ ኮረንቲ (ህገ-መንግስት) ቀይሮ ማቅረብም ሊሆን ይችላል፤ የስዩመ እግዜሩ ተልእኮ፡፡ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉስ እና ስዩመ እግዚአብሔር ህዝብ... የተለያየ አይነት እቃ ቢሆኑም፤ እቃ ግን ናቸው፡፡
ግን እውነት የሰው ነገር እንደዛ ነው?... ከሆነ፤ የእኔ መየጠቅ ምን እርባና አለው? ጥያቄውም ከእኔ፣ መልስም ካለ... ከመላሹ የሚመጣ አይደለምና - የጥያቄ ተልእኮና የመልስ ተልእኮ የተሰጠን እቃ ከሆንን፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው ሄግልን ጠቅሰው፤ የዘመን መንፈስ ትውልዱን እንደሚነዳው ነግረውናል፡፡ ዘመን ትውልዱን ይቀርፃል እንጂ ትውልድ ዘመኑን ሊቀር አይችልም፤ እንደማለት ነው፡፡ በአጭሩ ..የሰው ልጅ ምርጫ የለውም.. ነው፤ በጥቅሉ የንሱ ሀሳብ፡፡ ምርጫ ደግሞ ነፃ እስካልሆነ ድረስ ምኑን ምርጫ ሆነ?
ስለዚህ፤ ጥያቄው (በትውልዱ ውስጥ የእኔ ጥያቄ) ..ምርጫ አለን ወይንስ የለንም?.. የሚል ነው፡፡ ...ሞኝ፣ ግትርም አይደለሁም፡፡ ምርጫ በእርግጥም የሌለን ፍጥረቶች ልንሆን እንችላለን፡፡ በብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ስር ህልውናችን የተገደበ እንደሆነ አልጠፋኝም፡፡ በቅድሚያ መታዘዝ ላለብን የህጐች ክምር መታዘዝ አለብን፡፡ ግን በተገደበልንም ውስጥ ሆነን ወደ ውጭ ለመምረጥ እናስባለን፣ እንጠይቃለን... ይህም መምረጥ የመቻል ባህሪያችን ነው፡፡
ህዝብን ማን ይምራ? ለሚለው የዶክተር ጥያቄ፤ ..ነፃነቱን የሚፈልግበት ምርጫው.. የሚል መልስ እኔ እሰጣለሁ፡፡ እኔ በወፍጮ ቋንቋ ራስህን ግለ ብባል፤ የራሱን ኤሌክትሪክ በትንሽ ናፍጣ አመንጭቶ፤ በራሱ እሳት የራሱን ስሜት ወደ እውቀት ለውጦ፣ አዲስ አፈጫጨት እየሞከረ ወፍጮ መሆን ነው ምርጫዬ፡፡ የዘመን መንፈስ ሲነዳውም የሚያውቅ፤ እና በዘመን ወንዝ ውስጥ የራሱን ታንኳ ሰርቶ ለመንሳፈፍ የሚሞክር፤ በትውልድ ውስጥ የምገኝ ነጠላ ዛፍ ነኝ፡፡ በውስን ተፈጥሮዬ ውስጥ ወሰን የለሽ ምርጫ እንዳለኝ የማምን ፍጡር ነኝ፤ እላለሁ፡፡ ...የማመራው በማይቀርልኝ መንገድ ወደ ማይቀርልኝ መድረሻ ከሆነ ደግሞ፤ ወንዙን በጥፍሬ በመቧጠጥ ሚስማር በቆርቆሮ ላይ ሲፋቅ የሚያወጣውን ጩኸት ለመፍጠር የምሞክር አመፀኛ ጠያቂ ነኝ፡፡
አመ በስክነት የሚለወጠው፤ በመልስ ብቻ ነው፡፡ ወይንም በለውጥ፡፡ መልስ፤ በድንቁርና ታሪክ ላይ የለውጥ አብዮት የሚፈጥር የምርጫ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ለዶክተሩ ጥያቄዬን አቀርባለሁ፡፡ ነፃ ምርጫ የሚባል ነገር አለ ወይንስ ህልም ነው?... አሁን ያወራሁት የአመ ፍላጐቴ እራሱ፤ በዘመን ትውልድነቴ የተሰጠኝ ተልዕኮ ነው? |I feel like a pair of rugged claws scutting across the floors of silent seas´ ያለው ማን ነበር? ገጣሚው ቶማስ እስተርንስ አሊየት ነው”” እሱም አመፁ ሲበርድለት ጐባጣ የነበረው እና ለመቺው (ለታሪክ፣ ለሀይማኖት፣ ለእጣፈንታ፣ ለፈጣሪ፣ ለባህል) ያስቸገረውን ጭንቅላቱን ቀና አድርጐ፣ በዘመን ተልዕኮ መዶሻ ተቀጥቅጦ ቦታውን ያዘ፡፡ በስተመጨረሻ፡፡
...ከፍተኛው ተልዕኮ በሰው ውስጥ ሲሰራ የቆየው ገድል የሰው ልጅ ታሪክ ነው? የታሪክ እድሜ ራሱ የሚቀጥለው፤ በሰው ልጅ ንሰ ሀሳብ እና በአብዮት ሰአት አቆጣጠር መሆኑ፤ የትውልድ ተልዕኮ በዘመን ጥያቄ ላይ ያለው ምላሽ አይመስልም?... መስሎኛል፤ ከመሰለኝ ደግሞ ነው፡፡ ሊመስለኝ (ሊገባኝ) የሚችለውን ነው እንዲገባኝ ወይንም እንዲያገባኝ የምሞክረው እንጂ... ሊገባኝ የማይችለውማ ምንስ ጥያቄና መልስ ያስፈልገዋል፡፡
በተፈጥሮው በግ ሆኖ ራሱን እረኛ አድርጐ የቆጠረውን የፈጠራ ታሪክ ታውቁታላችሁ?... እረኛ የመሆን ምርጫ እና የመፈፀም ብቃት ባይኖረው የተመኘውን ባልተመኘ ነበር፡፡...
ሰው፤ ምርጫ የለሽ ..የዘመን ተልእኮ.. ወፍጮ ከሆነ፤ መልካም አስተዳደር ወይንም ዲሞክራሲ ወፍጮውን የበለጠ ምርታማ እንዲሆን የሚቀቡ የግራሶ እና የዘይት አይነቶች ናቸው፡፡ በዘመን ተልእኮ ውስጥ ሳይፋጭ እንዲነጉድ የሚረዱት ህልሞቹ፡፡ ምናልባት፤ የዘመን ተልእኮ በሰው ላይ የሰራው ጥበብ ይሆናል፡፡ ጥበብ ከሆነ፤ ከግሪኮቹ የተፈጠረ ጥበብ ለኛ ምናችን ነው? ...ከዴሞክራሲ ህልም አንድ ተጨባጭ ዳቦ አይሻልም ነበር? ሰው፤ ምርጫ አልባ እቃ ከሆነ፤ ህዝብ ራሱን አስተዳድሮ አያውቅም ማለት ነው፡፡ ራሱን በራሱ፣ ለራሱ እያስተዳደረ እንዲመስለው፤ የተለያዩ ህልሞችን ለማየት ግን ይሞክራል፡፡ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ነው ነጥቡ፤ ህልምን ማየት እና እውን እንዲሆን ለማድረግ መሞከር ራሱ ዋና የምርጫ መገለጫ ነው፡፡
በስዩመ እግዚአብሔር ንጉስ ላይ ብቻ ነው እንዴ ህዝብን ማስተዳደር ትልቅ ሀላፊነት የሚሆነው? ወይንስ ንጉሱን በተሸከመው በግለሰቡ ላይ?... ልማታዊ መንግስት፤ የልማት ዘመናዊ ተልዕኮውን መሸከሙ ሊከብደው ይችላል፡፡ እኔ በልማታዊ ወንዝ ውስጥ ያለ ምርጫዬ እና ያለ ነፃነቴ እየተነዳሁ የምሄድ ዛፍ ምን ተብዬ ልጠራ .....የኔ ስስ ትከሻ ምን ተብሎ ይጠራ ተሸክሜ የምኖር ምድርን ከአትላስ ጋራ.. እንዳለው በእውቀቱ ስዩም፡፡
የዘመን መንፈስ የሚነዳና ምርጫ የሌለን ፍጡሮች ከሆንን፤ የዘመን መንፈስ ተልእኮ ምን እንደሆነ ቢያንስ ማገናዘብ ወይንም መገንዘብ እንችላለን?
የዘመን መንፈስ በስዩመ እግዚአብሔር ወደ ህዝብ ሲተላለፍ እና በስዩመ ህዝብ ወደ ህዝብ ሲተላለፍ ተገላቢጦሽ የሆነ ፍሰት ነው ያለው፡፡ አገልግሎት አቅራቢው የነበረው ባሪያ ተገልጋይ ይሆናል፡፡ ...የዘመን መንፈስ እንደ ማዕበል የሚነሳ እና የሚወድቅ አንዴ ወደ ፊት ሌላ ጊዜ ወደ ኋላ የሚል ነገር ነው ማለት ይሆን?... ንጥረ ነገር ነው ወይንስ ሞገድ ነው?... ግዑዝ ይመስላል፡፡ ምርጫ የሌለው... ህያው ሊባል የማይቻል ነገር፡፡...
ሰው ግን ምርጫ አለው - ..የሚችለውን ነገር የመቀየር፣ የማይችለውን ነገር አለመቀር እና በመቀየር እና ባለመቀየር መሀል ያለውን ልዩነት ማወቅ..... እንደሚለው yA.A መፈክር፡፡ ወይንስ ይህንንም ምርጫ የሚወስንለት የዘመን መንፈስ ነው?
በተፈጥሮ ላይ ምርጫ የለም (ሰው ሊገባው የሚችል ምክንያታዊ ምርጫ)፡፡ መጥፎ እና ጥሩ፣ ቀይ እና ጥቁር፣ ጊዜ እና ቦታ የሚባሉ ማነፃፀሪያዎች የሉም፡፡ ንርም ሆነ ምርጫ በሰው መስተሃልይ እና በውጫዊው ተፈጥሮ መሀል የሚደረጉ መግባባቶች  ናቸው፡፡ ካለ ምርጫ ዕውቀትም የለም፡፡ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለው እውቀት ምርጫ ባይኖር አንድ በሆነ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለውም ስሜት እንደዚሁ፡፡... በእያንዳንዱ ሳንባ ውስጥ ያለው አየር ብቻ ተመሳሳይ ነው፡፡ እሱንም ግን በምርጫ መተንፈስን መቀጠል ወይንም ማቋረጥ ይቻላል፡፡
ህዝብ ሳይሆን ግለሰብ ነው ምርጫ ያለው፡፡ ግለሰብ ምርጫ ከሌለው ህዝብ ምርጫ ሊኖረው አይችልም፡፡ የህዝብ ታሪክ በግለሰብ በተቀሰቀሰ አብዮት ይለወጣል፡፡ እንግዲህ እንደ ሀይማኖቱ ይለያያል፡፡ ..ህዝብ ታሪክን ለወጠ.. ሲል አንዱ፣ ..ታሪክ ህዝብን.. ይላል ሌላው፡፡ ሁለቱም መንገዶች፤ የግለሰቡን ምርጫ ከራሱ ቁጥጥር ውጭ ለማውጣት የተቋቋሙ ሀይማኖቶች ናቸው፤ ለኔ፡፡ ...ተሳስቼ ይሆን? መሳሳቴን እንደ ጥያቄ ይቆጠርልኝ፡፡ መልስ ሳገኝ መሳሳቴን አርማለሁ፡፡ ስታረም መሳሳቴን አምናለሁ፡፡
ምርጫ ካለ ለውጥን ከራሳችን ውስጥ ለማፍለቅ ሀሳብ እንለዋወጣለን፡፡ ጭቆናችንን በነፃነት ለመተካት እንፍጨረጨራለን፡፡ ከላይ የተፃፈልንን እየኖርን ከሆነማ፤ ከስር ሰርዘን ደልዘን ለመፃፍ የምንሞክረው ለምንድነው? Can one change what’s written on high by counter writing it on down low . . . ? ወይንስ፤ ከላይም የተፃፈው ከታችም በምርጫችን የምንፈው ሁለቱም ከላይ ነው?... ወይንም ሁለቱም ከታች (ከሰው)?
ለመሆኑ፤ የአሁኑ የዘመን መንፈስ የሚያስፈም ..ስዩመ ራሱ.. ቢኖር... ያ ራሱን ለራሱ ግብ ብሎ የሰየመ ሰው፤ የራሱን ያስፈፀመ ይመስለዋል እንጂ እያስፈፀመ ያለው የዘመንን መንፈስ ነው ማለት ነው?
..የዘመን ተልእኮ.. እና መሰሎቹ እያገላበጥኩ ስመለከታቸውና ስጠይቅ... አንድ ገታቸው ታየኝ፡፡ መጥፎ እና ጥሩ የሚባል ነገርን የሚያጠፉ ሀሳቦች ናቸው፡፡ መጥፎን ለማጥፋት ጥሩ ሆነህ ትዋጋና... መጥፎን ታስወግዳለህ፡፡ በኋላ፤ ብቻውን ሲቀር፣ መጥፎን ለመሆን ጥሩነቱን ይቀይራል፡፡ ሌላ ጥሩ ነኝ ባይ ጥሩ አላማ አንግቦ፣ ጥሩ አብዮት ቀስቅሶ የቀድሞውን ለመድገም እንደ አዲስ ይመጣል፡፡ ታሪክ ራሱን እንደሚደግም እንኳን አያውቀውም፡፡ (ሰው የራሱን ጥያቄ በተሻለ ሳይሆን በባሰ ጥያቄ ሲደግም፤ ታሪክ ራሱን ደገመ ይባላል)
ምናልባት ዶክተር ዳኛቸው ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የእኔን በተሻለ ጥያቄ በሌላ በጥያቄ አሊያም በመልስ ሳይደፍኑ ትክክልነታቸውን ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡... በወጣትነት ለተጠየቀ ጥያቄ እና ፍለጋ፤ መልስ እና ግኝት ሆኖ የሚመጣው በእድሜ መውደቂያ ላይ ነው ይላሉ፤ የብስለት ተናጋሪዎች፡፡ በእድሜ ጉብጠት ላይ የሚቃና መልስ፤ የእውቀት ሳይሆን የእምነት ነው፤ እላለሁ እኔ፡፡

Read 3460 times