Saturday, 24 September 2011 09:10

በባሎቻቸው ክፉኛ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ተበራክተዋል

Written by  ጽዮን ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

.ዳዬሪየ ዛሬ እናቴ የሞተችበት ቀን ነው፡፡ እናቴን ማን እንደገደላት ልንገርሽ? አባቴ ነው፡፡ ዛሬ እናቴን ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ጉድጓድ ውስጥ ሲከቷት አየሁ፡፡ አሁን ብቻዬን ነኝ፡፡ ትምህርት ቤት ሲከፈት ለጓደኞቼ እናቴ የት ሄደች እንደምላቸው አላውቅም..... እናቷ በአባቷ የተገደሉባት የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ ከእናቷ ቀብር ስትመለስ በዳዬሪዋ (በግል ማስታወሻ መፃፊያዋ) ላይ ያሰፈረችው ነው፡፡

የ42 ዓመቷ ሟች ዮዲት አሰፋ ከቀድሞ ባላቸው የፌደራል ፖሊስ አባል ኮማንደር ግርማ ሞገስ ጋር ጋብቻ የፈፀሙት በ1995 ዓ.ም ነበር፡፡ ትዳራቸው ባለመስመሩ ከስድስት ወር በኋላ ፍቺ ፈመው ለየብቻቸው መኖር ይጀምራሉ፡፡ ከዓመታት በኋላም እንደገና በትዳር ለመኖር በመፈለጋቸው እርቅ አውርደው በአንድ ላይ መኖር ጀመሩ፡፡ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ አብረው መዝለቅ ባለመቻላቸው መልሰው ተፋቱ፡፡
ፍቺው አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ እና ሟች ዮዲት ኑሯቸውን ቀጥለዋል፡፡ አባት ደግሞ ለብቻው መኖር ጀምሯል፡፡ ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም እናት ልጇን ትምህርት ቤት አድርሳ ወደ ሥራ ለመሄድ ታክሲ ጥበቃ ቆማለች፡፡ አካባቢው በሰዎች ተሞልቷል፡፡ ትራፊክ ፖሊስ እና ሥነሥርዓት አስከባሪ ፖሊሶችም በአካባቢው አሉ፡፡ የሚመጣውን ያልገመተችዋ ዮዲት፤ ታክሲ ለማግኘት ከወዲህ ወዲያ ትላለች፤ ይኼኔ አንድ ሰው ተጠጋት፡፡ መሳሪያ ወደ ደረቷ ደግኖ ተኮሰባት፤ አስፓልቱ ላይ ተዘረረች፡፡ ሰዎች ተረባረቡና ፒያሳ ወደሚገኘው ዩኒቨርሳል ክሊኒክ ወሰዷት፡፡ ከዛም ወደ ጥቁር አንበሳ፡፡ ህይወቷን ግን ማትረፍ አልተቻለም፤ ከሦስት ሰዓት ቆይታ በኋላ ወደማትመለስበት ዓለም ሄደች፡፡ ህይወቷ አለፈ፡፡
በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች መሳሪያ የተኮሱትን እጆች ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ፡፡ ተጠርጣሪው የሟች የቀድሞ ባለቤትና የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ አባት ኮማንደር ግርማ ሞገስ ነበሩ፡፡
እናትም አባትም በድንገት ያጣችው ታዳጊ፤ ትምህርት ቤት ሲከፈት ስለ እናትና አባቷ ለጓደኞቿ ምን ብላ XNdMTnግራcW ተጨነቀች፡፡ መተንፈሻ ስታጣ ማስታወሻዋ ላይ መፃፍ ጀመረች፡፡
..ወቅቱ ትምህርት ቤት የተዘጋበት ጊዜ በመሆኑ ትምህርት ቤት ሲከፈት ለጓደኞቿ እንዴት አብዝታ ትጨነቅ ነበር፡፡ ሞታለች እንዳትላቸው ወሬውን ሚስጥር አድርጋ መያዝ ፈልጋለች፡፡ አለች እንዳትላቸው ደግሞ እናቷ ትምህርት ቤቷ እየሄደች ጓደኞቿን ትጋብዝላት ስለነበር አለመኖሯን ያውቁባታል፡፡ ልጅቷ ጭንቀት ውስጥ ወደቀች፡፡ ግራ ሲገባት ቤተክርስቲያን ውሰዱኝ እና እናቴን እንዲመልስልኝ እግዚአብሔርን ልጠይቀው እያለች ቤተክርስቲያን ትሄዳለች፡፡ እንድትረሳልን ብለን ማስታወሻዋን ደበቅንባት፡፡ ትምህርት ቤትም ልንቀይርላት ፈልገን ከቤታቸው ቅርብ የሆነው ካቴድራል ትምህርት ቤት እየሞከርን ነው፡፡ በኋላም እንደፈራችው ትምህርት ቤት ተከፈተ እና ጀመረች፡፡ ከትምህርት ቤት እንደመጣችም፤ ..ተማሪዎቹ እኮ ሰምተው ጠበቁኝ፤ አንዷ ጓደኛዬ አባቷ ነግሯት እሷ ለተማሪዎቹ በሙሉ ነገረቻቸው፤ አስተማሪዎቹም ሰምተዋል.. አለችኝ፡፡ ምን አለ ልጁን እንኳን ቢያይ?.. የሟች አክስት መናገር አልቻሉም፡፡ በዮዲት ሞት ቤተሰቡ በሙሉ መበጥበጡን ነገሩን፡፡
የ70 ዓመቱ የሟች አባት አቶ አሰፋ በሐረር ከተማ ጠበቃ ናቸው፡፡ ባለቤታቸውን ከቀበሩ ገና ሦስት ዓመታቸው ነው፡፡ ከሁለት ወንድ ልጆቻቸው ሌላ የነበረቻቸው አንዲት ሴት ልጅ ህይወት አልፏል፡፡ የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊም ከሟች ወንድም ጋር ኑሮ መጀመሯን ገለፁልን፡፡ ፊታቸው የሐዘን እና የተስፋ መቁረጥ ድባብ አረብቦበታል፡፡
ከዚህ ቀደም ተጠርጣሪው እቤታቸው ድረስ ሄዶ መሳሪያ ይዞ ሲዝት እንደነበር እና በወቅቱ ሁለቱም ባለመኖራቸው ድርጊቱ ሳይሳካ መቅረቱን ገልፀው ሁኔታው ስላሳሰባቸው ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስደውት ነበር፡፡ ታስሮም በ100 ብር ዋስ መለቀቁን ይናገራሉ፡፡
..ልጄ በልጇ አባት፣ በፈታችው ባሏ፤ በሕዝብ ገንዘብ በተገዛ በመንግሥት መሳሪያ ህይወቷ ጠፍቷል፡፡ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ከዋለም በኋላ ከሌሎች እስረኞች በተለየ በእስር ቤት ግቢ ውስጥ እየተዝናና፤ ከቤተሰቦቹ እና ከጓደኞቹ ጋር እንደልብ እየተገናኘ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ትእዛዝ ከሰጠም ከአምስት ቀናት በኋላ ነበር ወደ ቃሊቲ የወረደው፡፡ ይህ የሚያሳየው የሕጉን መላላት እና መድሎ እንዳለው ነው.. በማለት ስለተጠርጣሪው ኮማንደር ግርማ የእስር አያያዝ ያብራራሉ፡፡
ሌላዋ ተጠቂ ወ/ት ቤተል አዲሱ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ ነዋሪ ነች፡፡ የ21 ዓመቷ ወጣት ወላጆች ኑሮ አነስተኛ በመሆኑ እድገቷ ከድህነት ጋር በሚደረግ ትንቅንቅ የተሞላ ነበር፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በገባችበት ወቅት የጐረቤት ሰዎች በሚያደርጉላት ጥቂት እርዳታ ጦም የማደር ያህል እየኖረች በዲላ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል በ2003 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ትምህርቷንም በማጠናቀቋ ወደ ወላጆቿ ቤት ተመልሳ ትሄዳለች፡፡
መስከረም 4 ቀን 2003 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል ገደማ አንድ ሰው ወደ ቤታቸው ይመጣና ድምፁን በወንድሟ ድም ቀይሮ ወደ ውጭ ይጠራታል፡፡ በሩን ከፍታ ስትወጣ ሰልፈሪክ አሲድ ከፊቷ ጀምሮ በደረቷ እና በሰውነቷ ላይ ደፍቶባት በወደቀችበት ትቷት ይሄዳል፡፡ የቤተልን የስቃይ ድም የሰሙ ጐረቤቶች አፋፍሰው አካባቢያቸው ወደሚገኝ ሆስፒታል ቢወስዷትም ሆስፒታሉ ወደ አዲስ አበባ ይልካቸዋል፡፡ ወላጆቿም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ቤተልን ፈጥነው ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡበት አቅም ስላልነበራቸው መዋጮ እስኪያሰባስቡ ሁለት ቀናት ይወስድባቸዋል፡፡ በመጨረሻም መስከረም 6 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል ያስተኟታል፡፡  
..አሁን በዓይኔ መጣ.. በሚል መሪ ሐሳብ ስር የተሰባሰቡ ድርጅቶች እና ግለሰቦች፤ በኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት አማካኝነት በትናንትናው ዕለት በሸራተን ሆቴል የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ግለቦች እና ቤተሰቦች በተገኙበት ውይይት አካሂደው ነበር፡፡
አማርኛ መናገር የሚያዳግታቸው እናቷ፤ ..ልጆቼን ተቸግሬ ነው እያሳደኩ ያለሁት፡፡ ተሳክቶልኝ አንዷን አስተምሬ ለዚህ አበቃሁ ስል እንዲህ ያለ ችግር ገጠመኝ፤ አሁን እኔ እሷን የማሳክምበት አንዳችም ገንዘብ የለኝም፡፡ እባካችሁ ተረባርባችሁ ልጄን አትርፉልኝ.. በማለት ተሰብሳቢውን አስተዛዝነው በኦሮምኛ ቋንቋ ጠየቁ፡፡
በአዳራሹ ከተገኘው ሰው በተደረገ መዋጮም ከ20 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቦ ተለገሳቸው፡፡ ወጣቷ ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅም ተኝታለች ወደተባለበት የካቲት ሆስፒታል አመራን፤ ተጐጂዋን ለማነጋገርም ሆነ ፎቶ ለማንሳት ማስታወሻ መሰል ነገር እንድንጽፍ ተነገረን፤ የተባልነውን አደረግን፡፡ በወቅቱ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተሩ እና አስተዳደሩ ባለመኖራቸው አቶ አየለ ቸርነት የተባሉ የሆስፒታሉ ሠራተኛ ወደ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ስልክ ደውለው እንድንገባ ፍቃድ ጠየቁልን፤ ነገር ግን እንዲህ አይነት አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች በጋዜጠኞች እንዳይጐበኙ ፍትህ ሚኒስቴር ስለከለከለ ሊያስገቡን እንደማይችሉ ገለፁልን፡፡ በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርገው ሰኞ ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁን ነገሩን፡፡
ድርጅቶቹን እና ግለሰቦቹን በሸራተን ሆቴል ያሰባሰበው ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) ወ/ሮ አበራሽ ኃይላይ ላይ በደረሰው አደጋ መነሻነት ነው፡፡ ..አሁን በዓይኔ መጣ.. የሚለውን መፈክርም አንድም በአበራሽ ዐይኖች ላይ ከደረሰው ጉዳት እና ..አሁን ገና በዐይኔ መጣ.. በሚል የመጨረሻ ምሬት ከሚገለበት አባባል እንደተወሰደ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ አበራሽ ኃይላይ እና አቶ ፍሰሃ ታደሰ ለሰባት ዓመታት ያህል በትዳር አብረው ቆይተዋል፡፡ ትዳራቸው መቀጠል ባለመቻሉም ከአራት ወራት በፊት ፍቺ መፈፀማቸው እና መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም አቶ ፍሰሃ ወ/ሮ አበራሽ የምትኖርበት ቤት በመሄድ እጆቿን አስሮ ዐይኗን በስለት ወጋግቶ ካጠፋ በኋላ በአካላቷ ላይ ተጨማሪ ጉዳት አድርሶ፣ ራሷን ስታ በወደቀችበት ትቷት መሄዱ እና እዚህ አገር በህክምና ስትረዳ ቆይታ ከአቅም በላይ በመሆኑ ወደ ባንኮክ መወሰዷ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የተጐጂዋ አጐት አቶ አስመላሽ ሞላ አበራሽ አደጋው ከደረሰባት በኋላ ለፖሊስ እና ለሀኪም በሰጠችው ቃል፤ አቶ ፍሰሃ ማምሻውን ወደ ቤቷ ሄዶ ወደ ውጪ ሊሄድ በመሆኑ ስጦታ ሊሰጣት እንደፈለገ በመግለ፣ በሩን ካስከፈታት በኋላ በሽጉጥ አስፈራርቶ ራሷን ስታ እንድትወድቅ ካደረገ በኋላ፣ በስለት ዐይኗን እንደወጋት፣ ከወጋም በኋላ ከስለቱ ጋር አብሮ እጁን እያስገባ ዐይኗን እንደቆራረጠው፤ ጭንቅላቷ እና እጆቿ በስለት እንደተወጉ እና ወገቧ ላይ በደረሰ ጉዳት መንቀሳቀስ እንደማትችል ነው፡፡ ቤቷ ከደረሱም በኋላ የቤቱ ወለል እና ግርግዳ በደም እንደተጨማለቀ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ክፍል እንደተጐተተች ማየታቸውን ገልፀውልናል፡፡  
እንዲህ ያለውን አሰቃቂ ወንጀል የፈፀመ ግለሰብ ላይ መንግሥት አፋጣኝ የሆነ ሕጋዊ እርምጃም እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
አሁን በባንኮክ ስላለችበት ሁኔታም ሲያስረዱ፤ የአንድ ዐይኗ ሜዳው ሙሉ ለሙሉ ባዶ መሆኑን፤ የዐይኖቿን ብርሃን የመመለስ ተስፋ መሟጠጡን ገልፀው፤ በአንደኛው ዐይኗ ነርቭ ላይ የደረሰው ችግር ወደ ጭንቅላቷ እንዳይዛመት ህክምና እየተደረገላት ከመሆን ውጭ ምንም ተስፋ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪውን በሚመለከት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቦሌ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት ቀርቦ፤ ድርጊቱን የፈፀመው በስካር መንፈስ ተነሳስቶ እንደሆነ፣ ድርጊቱም ቢሆን የብዙሃን መገናኛ ያጋነኑት እንጂ እንደተገለፀው የከፋ አለመሆኑን፤ ይህንንም ወ/ሮ አበራሽ ልትመሰክርለት እንደምትችል በመግለ የተበታተኑትን ንብረቶቹን መሰብሰብ እንዲችል በዋስ እንዲለቀቅ ቢጠይቅም ፖሊስ በዋስ ቢለቀቅ መረጃ ይጠፋብኛል፤ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለቱ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ጉዳዩን ለማየትም ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በትዳር አጋራቸው፣ በቀድሞ ባላቸው፣ በፍቅር ጓደኛቸው ወይም በወንዶች ጉዳት የደረሰባቸው እና ህይወታቸውን አጥተው በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሪፖርት የተደረጉ የጥቃት ዝርዝሮችም በውይይቱ ላይ ቀርበው ነበር፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት እና ተጠርጣሪው አቶ ምንአለ አቻም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ጋብቻ ፈመው የኖሩ ናቸው፡፡ ሦስት ልጆች ወልደዋል፡፡ በሚያዚያ 30 ቀን 2003 ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ተጠርጣሪው ጭንቅላትና መላ ሰውነቷን ደብድቦ፤ እጅና እግሯን ሰባብሮ ቀጥሎ አሲድ ደፍቶባታል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ሰላማዊ ግንኙነት አልነበራቸውም፤ እሷም እንዲለያዩ ጠይቃዋለች፡፡ ተጐጂዋ በዚሁ ሰበብ ሞታለች፡፡ ተጠርጣሪው ጠፍቷል፡፡ ፖሊስ ፍለጋ እያደረገ ቢሆንም እስካሁን አልተገኘም፡፡
ሟች ወ/ሮ ግዜሽወርቅ እና ገዳይ ጌቱ ቶሎሳ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ስድስት ልጆች አሏቸው፡፡ ገዳይ በጥር ወር ..ባኤ.. ገብቶ ሁለተኛ ልጃቸው ከእርሱ እንዳልተወለደ ራዕይ እንደታየው ነግሯታል፡፡ በዚሁ ተጣልተው ቆይተዋል፡፡ ነገሩ እየተካረረ ሲመጣ ሟች እንዲለያዩ ጠይቃው የነበረ ቢሆንም በሰኔ ወር 2002 ዓ.ም በሽጉጥ ገድሏት በራሱ ፈቃድ እጁን ሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ ለፍ/ቤት ቀርቦ ፍ/ቤቱ የገዳዩን መፀፀትና ለጥፋቱ ምክንያት የሆነውን ነገር መነሻ በማድረግ ቅጣቱን በማቅለል የ13 ዓመት እሥራት ፈርዶበታል፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ቅጣቱ ሊከብድበት ይገባል ሲል ለዐ/ሕግ ጥያቄ አቅርቦ ይግባኝ ተጠይቋል፡፡
ስማቸውን መግለ ያልተፈለገ ተጐጂ ከተጠርጣሪው ጋር በጋብቻ ኖረዋል፡፡ ልጆች ወልደዋል፡፡ ተጐጂዋ በ2002 ዓ.ም ተጠርጣሪው የፈላ ውሀ ደፍተውባቸዋል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በሄደበት ወቅት ከዓመት በፊት አፍንጫቸውን ቆርጠዋቸው እንደነበረ ተረድቷል፡፡ ጉዳዩ ለፍ/ቤት ቀርቦ ክስ አልተመሰከረባቸውም ተብሎ በነፃ ተለቀዋል፡፡
ሟች ወ/ሮ ዘነበች ቢረጋ እና ገዳይ አዳነ አስፋው ባልና ሚስት ሆነው ኖረዋል፡፡ ገዳይ b17/5/2003 በገጀራ መትቶ ገድላቸዋል፡፡ ልጃቸውም በገጀራው መትቷታል፡፡ እርሷ ግን ተርፋለች፡፡ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19 ዓመት እሥራት ፈርዶበታል፡፡
ወ/ሮ እመቤት ጌታቸው እና አቶ ከበደ ተሰማ ከሚያዚያ 1999 ጀምሮ እንደባልና ሚስት ሲኖሩ ቆይተዋል፡፡ በመጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም ጭንቅላቷ ላይ በዱላ መትቶ በአደረሰባት ጉዳት ቀኝ ጐኗ አይሰራም፡፡ ጉዳዩ በፍ/ቤት ሲታይ ቆይቶ 4 ዓመት ከ6 ወር እሥራት ተወስኖበታል፡፡ ፍ/ቤቱ ይህንን የወሰነው የቅጣት መመሪያውን መነሻ አድርጐ ነው፡፡
ወ/ሮ እናኑ አዱኛ ጉዳት አድራሽ አቶ ሰላም እሸቱ ያለ ኮንዶም የግብረስጋ ግንኙነት እንዲያደርጉ ያቀረበውን ጥያቄ ሟች ባለመቀበል ምክንያት ግራ ዓይኗን በጩቤ በመውጋት ህይወቷ አልፏል፡፡ ጉዳት አድራሹ ከተሰወረበት ስፍራ በተደረገው ክትትል ተይዞ ለፍርድ ቀርቧል፡፡
ወ/ሮ ሳራ አፈወርቅ እና ትዳር የነበረው ግለሰብ አቶ ዕፁብ ተፈራ የፍቅር ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ..ሚስጥራችንን ሚስቴ እንድታውቅ አድርገሻል.. በማለት መኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ በጥይት ገድሏታል፡፡
ወ/ሮ ውብዳር አስናቀ እና ገዳይ አለማየሁ አርጋ በትዳር የቆዩና ሁለት ልጆች ያፈሩ ሲሆን በመኪና ብረት ጭንቅላቷን በመደብደብ ለህልፈተ ህይወት ከዳረጋት በኋላ ፊቷን ሸፈኖ ሲወጣ፣ የ11 ዓመት ልጃቸው ድርጊቱን በማየት ከተሰወረበት ቦታ ሊያዝ ችሏል፡፡
ወ/ት አሚናት ሰኢድ እና ፍቅረኛዋ ከነበረው አቶ ሙስጠፋ ኑሩ ጋራ አብረው ካመሹ በኋላ በድንገት ተፈጥሯል በተባለ ምክንያት በጩቤ ወግቶ ገድሏታል፡፡
ወ/ት ሰናይት እና ገዳይ አምሀ ሁነኝ አለም አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ቀበሌ 10/11 ነሐሴ 15/2003 ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ሟቿ ሰናይት ከጉዳት አድራሹ ጋር በክፍያ ተስማምተው ለግብረስጋ ግንኙነት አብረው ከሄዱ በኋላ አንገቷን አንቆ ገድሏታል፡፡
የ24 ዓመቷ ወ/ሮ ሳራ አህመድ እና አቶ አብዱል ናስር ኡመር ቀለበት አድርገው (ኒካ አስረው) በትዳር ለሁለት ዓመት ሲኖሩ ቆይተው ተጠርጣሪው ስምንት ጥይቶችን በመተኮስ በስድስቱ ጥይት አካላቷን ደብድቦ በመግደል ተሰውሯል፡፡
የሟቿ ወንድም አቶ ሙክታር በዕለቱ በስብሰባው ላይ ተገኝቶ ሁኔታውን ያስረዳ ሲሆን ተጠርጣሪው በሐረር ፖሊሶች ድክመት ሊያዝ እንዳልቻል በመግለ ጉዳዩን የአዲስ አበባ ፖሊሶች እንዲከታተሉት ጠይቋል፡፡
በትዳር አጋራቸው፣ በቀድሞ ባላቸው፣ በፍቅር ጓደኛቸው እና በቀድሞ የፍቅር ጓደኛቸው በጥይት እየተደበደቡ፣ በአሲድ እየተቃጠሉ፣ በስለት እየተወጉ እና በሌሎች ጐጂ ነገሮች አካላቸው ለከፋ ጉዳት እና ለሞት የተደረጉ ሴቶች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ጉዳት እየከፋ እና እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ተምረው እና ሠርተው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ይረዳሉ የሚባሉ ወጣቶችን ህይወት እየቀጠፈ ልጆችን ያለ አሳዳጊ ቤተሰብን ያለጧሪ እያስቀረ ነው፡፡
በሌሎች አገራት ተመሳሳይ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ግን ድርጊቱን የፈፀመው አካል ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ መግቢያ ቀዳዳ ስለሌለው የመጀመሪያ እርምጃው እራሱን ማጥፋት እንደሆነና ፖሊስም ድርጊቱን የፈፀመውን ግለሰብ የገባበት ገብቶ እንደሚይዘው በምሳሌ አስቀምጠው የተናገሩት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር የቀድሞ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፤ ..እኛ አገር ግን፤ ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦች እንኳን መግቢያ ቀዳዳ ስለማጣት ሊያስቡ እና እንደገና ኑሮን ለመቀጠል ይፈልጋሉ.. ብለዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ስለመባባሳቸው ምክንያት አንድ ስማቸውን መግለ ያልፈለጉ የሕግ ባለሞያ ..እነዚህ ችግሮች ማኅበረሰቡ እንከኖች ናቸው፡፡ ዛሬ የተባባሱ ሳይሆኑ የነበሩ እና አሁንም ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ማኅበራዊ እንከኖችን ከማረሚያ መንገድ አንዱ በሕግ ነው - የጥቃቱ ሰለባዎች መብቶቻቸውን በሕግ ማስፈፀም የሚችሉበት ንቃተ ሕሊና በመፍጠር፡፡ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን መቻል ብቻ ሳይሆን መብታቸውን ሊያስከብሩ የሚችሉበት ተእኖ መፍጠር መቻል አለባቸው.. ይላሉ፡፡
..ማኅበረሰባችን እነዚህን እንከኖች የሚጠየፍበት ሥርዓት አልፈጠርንም..፤ የሚሉት የሕግ ባለሞያው፤ ከሕግ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ከድርጊቱ ፈፃሚ ቤተሰቦች ጨምሮ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን እንዲያወግዝ፣ የፍትሕ አካላት ድርጊቱን በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ሕጉን ያገናዘበ ፍርድ እንዲሰጡ በማድረግ እንዲሁም የመንግሥት፣ የግል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኅብረተሰቡን የማስተማር ሥራ ቢሠሩ ችግሩን ቀስ በቀስ ማስወገድ አሊያም እጅግ በጣም መቀነስ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
የሕግ አማካሪው አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል፤ እንደዚህ ያለ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦች ለሕግ ሲቀርቡ ሕግ አስፈፃሚዎች ሕጉን በሚገባ እንደማይፈጽሙ ይናገራሉ፡፡
ሕጉን በአግባቡ አለመተርጐም፤ የዋስትና አሰጣጥ፣ የቅጣት አወሳሰን፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አለማዋል የመሳሰሉት ጉዳዮችን በሚመለከት የተበዳይ እና የተጠርጣሪን ሕገ መንግስታዊ መብት በሕጉ መሰረት ባለመዳኘት ምክንያት የሚሰጠው ቀላል ቅጣት ወይም ጉዳት አድርሶ ማምለጥ፤ ለሌሎች ወንጀሎች መደፋፈር እንደሚሆኑ ይገልፃሉ፡፡
በተጨማሪም፤ ለማኅበረሰቡ የማሳወቅ እና የማስተማር ሥራ የሚሠሩ ማኅበራት በአዲሱ አዋጅ መሠረት የገንዘብ እጥረት ስላጋጠማቸው ጉዳት ሲደርስ ለመከላከልም ሆነ ጉዳት ሳይደርስ ትምህርት ለመስጠት እንደተሳናቸው ይገልፃሉ፡፡          
በአቶ ደበበ ሀሳብ የማይስማሙት የሕግ ባለሞያዋ ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፤ የጠፋው ፍላጐቱ  እና መነሳሳቱ እንጂ ገንዘብ ከአገር ውስጥ አሰባስበው ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡
አቶ ደበበ በበኩላቸው፤ ለእንኳን የማስተማር ሥራ ሊሠሩ የቢሮ ኪራይ እና የሠራተኛ  ደሞዝ ለመክፈል ያለባቸው ችግር ፊት ለፊት ያገጠጠ ሀቅ ነው.. በማለት የወ/ሮ መዓዛን ሐሳብ አልተቀበሉትም፡፡ የሴቶቹ ጥቃት ያሳሰበው የፀረ ሴቶች ጥቃት ዘመቻ አስተባባሪዎች፤ ፒቲሽን አሰባስበው ለጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ደብዳቤ ልከዋል -  መንግስት ጉዳዩን እንዲያጤነው፡፡

 

Read 5576 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 11:49