Saturday, 17 September 2011 10:23

=ሕይወት እንደ ተረት

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

..ህይወት እንደ እመት ቦቦሊና አሮጊት ናት፡፡     ግን ሁሌም ጨርቅ አስጥሎ ለማሣበድ የሚያስችል አንዳች መላ አታጣም.. ይላል፤     አሌክሲስ ዞርባ፤ የካዛንታኪስ ገፀ ባህርይ፡፡ ከእነዚህ መላዎችዋ አንዱ አዲስ ዓመት ነው፡፡ ህይወት ሰርክ አዲስ ናት፡፡ በመደጋገሟ ኃይሏ አይቀንስም፡፡ ሁሌም ልባችንን እንደ ሰቀለች ታኖረናለች፡፡ ህይወት ሰማያዊ፤ በደም በሥጋ ትተርከናለች፡፡ የሰው ልጅ መሬታዊ፤ በቃል፣  በዜማ፣ በቀለም፣ በኪነ ቅርፅ ኮርጆ ይተርካታል፡፡ አንዳንዴም በትረካው እርሷን ለማስናቅ ይዳዳናል፡፡

ህይወት፤ ሁሌም ቢነበቡ ከማይሰለቹ ..ታላላቅ ተረቶች.. አንዷ ነች፡፡ እንደ ኤዞፕ ወይም እንደ ተራኪዋ - የአላዲን? ልጃገረድ ባለ ጥበበኛ እጅ ስትገባ፤ ተደጋግማ ብትነገርም ሁሌም እንደ አዲስ የምንሰማት ውብ ..ተረት.. ናት፡፡ ህይወትን ..ተረት.. በሚያደርግ ጠቢብ ትርጉም ታገኛለች፡፡ ትከብራለች፡፡ህይወት ..ተረት.. ከመሆንዋ በፊት ትርጉም የለሽ ናት - ዝብርቅርቅ የዕብድ ቃል፡፡ ወደ ትረካ ስትመጣ ትርጉም ትይዛለች፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ከእንስሳት እድር ወጥቶ ማዕረግ የሚያገኘው በትረካ ነው፡፡ በቦታ እና በጊዜ ተበታትኖ የነበረ ህይወት ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ትቀመራለች፡፡ ምርጥ ታሪክ ትሆናለች፡፡
ህንዳዊቷ የልቦለድ ደራሲ አሩንዳቲ ሮይ በአንድ ጽሁፍዋ ..ምርጥ ታሪክ ማለት፤ ትናንት ሰምተናቸው፤ ዛሬም ደግመን ለመስማት የምንፈልጋቸው ናቸው፡፡ ከየትኛውም የታሪኩ አንጓ ብትጀምሩ ይመቻችኋል፡፡ ምርጥ ታሪኮች፤ ያልታሰበ ወይም ያልተገመተ -አስደንጋጭ? አጨራረስ የመከተል ጮሌነት ያላቸው አይደሉም፡፡ እንደምንኖርበት ቤት ወይም እንደ ወዳጅ ጠረን የምታውቃቸው እንጂ አዲስ አይደሉም፡፡
..ታሪኩ እንዴት እንደሚጠናቀቅ እናውቃለን፡፡ ግን እንደማናውቅ ዓይነት ጆሮአችንን ከፍተን፤ ልባችንን ሰጥተን ታሪኩን ለመስማት ዝግጁ ነን፡፡ ነገሩ፤ አንድ ቀን እንደምንሞት ስናውቅ፤  ሞት የሌለብን ሆነን መኖር ነው፡፡ በታላላቅ ታሪኮች ውስጥ ማን እንደሚሞት፣ ማን እንደሚኖር፣ ማን አፍቃሪውን እንደሚያገኝ ማን እንደማያገኝ ታውቃላችሁ፡፡ ግን እንደገና እንዲነገራችሁ፤ እንደገና እንድታውቁት ትፈልጋላችሁ፡፡ ይኸ ነው የምርጥ ታሪኮች ምትሃት፣ አስማት፣ እንቆቀቅልሽ.. ትላለች ሮይ፡፡
ህይወትም እንዲህ ዓይነት ድንቅ ታሪክ ናት፡፡ በአዲስ ዓመት መንፈስ አሙቃ፤ በተደጋጋሚ ባየነው አስማቷ አፍዝዛ፤ አሮጌውን አዲስ አድርጋ አሳይታ ልታሰክረን ትመጣለች፡፡ ሽርጉድ ታሰኘናለች፡፡ በህፃናቱ አንደበት፤ እያዜመች ከፊታችን ቆማለች፡፡ ይኸው አሁን፤ ..አበባዬ ሆይ ለምለም፤ ባልንጀሮቼ ለምለም.. እያለች፤ እንደ ገና ልባችንን ታሞቀው ይዛለች፡፡
..ህይወት እንደ እመት ቦቦሊና አሮጊት ብትሆንም፤ ... ሺህ ጊዜ ከአልጋ ተጋድማ፤ ሺህ ጊዜ በድንጋሌ -ሀሳብ - እይታ?  ከመደብዋ ትነሳለች፡፡ ዳግም ትወለዳለች፡፡ ምትሃት ነች፡፡
..ለምን? እንዴት?.. የሚል ጥያቄ በማንሳት ለዛዋን፣ ጣዕሟን ማበላሸት ትርፍ የለውም፡፡ ይልቅስ በተስፋ ዝናብ ያጨለጨለ ምናብ አድላ፤ በአዲስ ዓመት እንደገና ልትሞሽረን ከመጣችው ምትሃተኛ ህይወት ጋር መተቃቀፍ ነው፡፡ እኔ ስታቀፋት እንዲህ ሆነ፤
..ከየት መጣሁ ሳልል ከአንድ ሥፍራ ዱብ አልኩ፡፡ በመደነቅ ፈንታ የሚያሳስበኝ ክፉ ነፋስ ዱብ አለ፡፡ ህይወት ድግግሞሽ መሆኗን የሚያስታውሱኝ ትናንሽ ቀበሮዎችን ታሰሩ፡፡ የፅጌ መስኩን የሚያማስኑ ቀበሮዎች ታገሱ፡፡ በዘላለም ሜዳ እና ሰማይ፤ በጊዜ ማሣ ዳር ከበቀለች እና ፍፃሜው በማይታወቅ ህዋ ውስጥ ብቻዋን ካለች ዛፍ ላይ ከሰራችው ጎጆ እንቁላልዋን ታቅፋ የተቀመጠች ርግብ ሆኜ ነቃሁ፡፡ እኔው ራሴ፤ ከእንቆቅልሽ እንቁላል ውስጥ ክሌውን ሰብሬ እንደ ጫጩት ብቅ ስል እራሴን አየሁት፡፡
ይኸን ተዓምር ለማወደስ ፈለግኩት፡፡ ከሰው ዕድሜ የላቀ ዕድሜ ያለው ..ቋንቋ.. ለመንኩ፡፡ የተወሰደ ልሳኔ እንዲመለስልኝ ጠየቅኩ፡፡ በኃያሉ አምላክ ዙፋን ፊት ቆሜ ውዳሴውን እንዳወርድ ይፈቀድልኝ ዘንድ ማለድሁ፡፡ የተዘረጋ እጄ ሳይታጠፍ፤ ምስጋና የተራበ ልቤ ዘመረ፡፡ የምስጢር ወይንጠጅ ተጎነጨሁ፡፡ ታላቁን ውቂያኖስ የምትውጥ አንዲት ጠብታ ከፍቅር ላምፋ ላይ እንደ ጤዛ ጠብ ስትል አየሁ፡፡
ድንገት ደግሞ፤ ኃይለኛ ውሽንፍር የቀላቀለ የጥርጣሬ ወጀብ ተነሳ፡፡ ወጀቡም የነፋስ ድንኳኔን ካስማ ሊነቅለው ታገለ፡፡ ያኔ ልቤ በእምነት ጀልባ ተሳፈረች፡፡ ይኸው በፍቅር አምባ፤ የተስፋ ድንኳን ተተክሏል፡፡ ልቤም ወደዚያው እየቀዘፈች ስትሄድ ተመለከትኳት፡፡ አራቱም አቅጣጫዎች ጠቀሱኝ፡፡ አዜብ፣ መስእ፣ ሊባ እና ባህር ጠሩኝ፡፡ የዕፀ በለስ ማዕበል ተነሳ፡፡ ጀልባዋን ሊውጣት አገሳ፡፡ የትዕቢት ባህር ፎገላ፡፡
ያኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈረሱን እየጋለበ መጣ፡፡ በእረፍት ውሃ ዳርቻ ለመቀመጥ የሚታገለውን መሬታዊ ፍጡር ሊታደገው በነጩ ፈረሱ ጋለበ፡፡ የትዕቢት ባህር ፀጥ አለች፡፡ የእፀ በለስ እሣት ተዳፈነች፡፡ የክፋት አፍንጫ ተፎነነች፡፡ ጀንበር ገብታ እስክትወጣ ድረስ ህይወት ሰልፍ ሆኖ ቆየ፡፡
ቀንም ሆነ፤ ማታም ሆነ፤ ሁለተኛ ቀን፡፡ የማለዳ ፀሐይ ስትወጣ፤ የፍቅርን ሰረገላ የሚስቡት ነጫጭ ፈረሶች እየተቅበጠበጡ መጡ፡፡ የሌቱ የሀሳብ ዝርፊያ ተገታ፡፡ ፈረሶቹ በማለዳው ጮራ እያብለጨለጩ ይታዩኛል፡፡ ክፉዎች ሊነኩት በማይችሉት የፍቅር ልጓም፤ እየኮለኮለ የሚጋልበው አምባላይ ፈረስ መጣ፡፡ ..የወይኑን ተክል ከቀበሮዎቹ ጠብቁ፡፡ የወይኑን ማሣ እንዳያማስኑት ትጉ.. የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ነቃ አልኩ፡፡ ግን ስለሆነው ነገር ከማወቄ በፊት ሁሉም ነገር ፀጥ አለ፡፡ ከሩቅ ስፍራ እንደሚመጣ ነፋስ እየተውጀበጀበ ከጆሮ የገባው፤ በልስላሴው እያዘናጋ ኪሶቼን በረበራቸው፤
ካህን የነፍሴ አገልጋይ፤
XNQLF xTt¾M ወይ፤ የሚል ዜማ ነው፡፡
ሃሌ - ሃሌ ሉያ፤  ፀባኦት - ኤልሻዳይ፤ ሃሌሉያ፤ ዛሬ ህይወት ታሪክ መሆን አልፈለገችም፡፡
ከተራራው ጀርባ፤ ከወንዙ ባሻገር
የተጨዋወትነው፤ ብዙ ምስጢር ነበር..
እያለ ያዜመው ማን ነበር? ህይወት የሮማንቲካዊ ቅርጽ የያዘ ተረክ ስትሆን እንዲህ ነው፡፡
የፈረሰው የእውን እና የህልም ዓለም ግድግዳ እንደ ገና ቆመ፡፡ ህይወት እንዲህ ትዘፍናለች፡፡ እንዲህ ትተረካለች፡፡ ህይወት እንዲህ በቀለም ተስላለች፡፡ ነገ በሌላ ካንቫስ ሌላ፣ በሌላ ሰዓሊ እጅ በአዲስ ቀለም እንደ አዲስ ዘመን በልምላሜ አጊጣ ታድሳ ትመጣለች፡፡ ህይወት ትንግርት ናት፡፡ እንኑራት፡፡ አበባዬ ሆይ ለምለም፡፡
ጨፍር ጎበዝ ደንስ ጎበዝ
ህይወት የምትፈቷት እንቆቅልሽ አይደለችም፡፡ በድንቅ ተጥለቅልቃችሁ የምትኖሯት ተዓምር ነች፡፡ በፍርሃት እና በፍቅር የምንዘምራት የሞት እና የትንሣዔ መዝሙር ናት፡፡ አሁን ባግዳድ ልውሰዳችሁ፡፡ ተረት ልንገራችሁ፡፡ የሃማሉን ቁጥብ እና የሦስቱ የባግዳድ ወይዛዝርት ታሪክ የዘመን መለወጫ ስጦታዬ ነው፡፡
ከዘመናት በአንዱ ዘመን፤ ባግዳድ ውስጥ ሚስት ሳያገባ በላጤነት ብቻውን የሚኖር ቁጥብ የሚሉት ሐማል ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን በጎዳናው ዳር ቦዝኖ፤ ቅርጫቱንም ደገፍ ብሎ  እንደ ቆመ አንዲት ወይዘሮ መጣች፡፡ በወርቅ የተጠለፈና የወርቅ ጉንጉን ጥለት ያለው ሙሉ ሐር ቀሚስ እንደለበሰች ከፊቱ ቆመች፡፡ ጫማዋ ወርቅ፤ ፀጉሯም በወርቅ የተጌጠ ነው፡፡ ዓይነ ርግብ ያደረገች ይህች ሴት፤ ብርሃን የሚረጩ ጥቋቁር ዓይኖች ያሏት ናት፡፡ እይታዋ ቅዝዝ ልስልስ ያለው፤ ፍጹም የተዋበችው ያቺ ሴት እንደ ሙዚቃ በአማረ ድምፅ ..ቅርጫትህን ይዘህ ተከተለኝ.. አለችው፡፡
ሐማሉ ቁጥብ ፍፁም ተደንቆ እና የሚሰማውንም ማመን አቅቶት፤ ..ያአላህ! እንዴት ያለች የተባረከችና ዕድላም የሆነች ቀን ነች.. አለ፡፡ ያንን ብሎ ቅርጫቱን አፈፍ አድርጎ ከትከሻው ጣለ፡፡ከአንድ ቤት ደርሳ እስከ ቆመች ድረስ ተከተላት፡፡ በዚያም በሩን አንኳኳች፡፡ የናዛሪው ሽማግሌ ፈጥነው ብቅ አሉ፡፡ የወርቅ ሳንቲም ተቀበሉ፡፡ በእሱም እንደ ወይራ ዘይት ኩልል ያለ የወይንጠጅ አምጥተው ሰጥዋት፡፡ እርሷም ቀስ አድርጋ ከቅርጫቱ ውስጥ አስቀመጠችው፡፡ ..አንሳና ተከተለኝ.. አለችው፤ ሐማሉን ቁጥብ፡፡ ..ሰው ያሰኘውን ሁሉ የሚያገኝበት አላህ የባረከው ቀን ይሄ ነው.. እያለ ቅርጫቱን ተሸከመ፡፡ አሁንም ከአንድ የአትክልት መሸጫ ሱቅ በር ደርሰው እስኪቆሙ ተከተላት፡፡ በዚያም የሻሚ አፕል፣ የኦስማን ኩንች፣ የአማን ኪሽኒት፣ የአባይ ወንዝ ያበቀለው ዱባ፣ የግብፅ ሎሚ፣ የሱልጣኒ ብርቱካን እና ትርንጎ ገዛች፡፡ ከቅርጫቱም አኖረች፡፡ ደግሞ መልካም ማዕዛ ያላቸው የአደስ ፍሬዎች፤ ሽታው የሚያውድ የአልፓይን ሐረግ፣ የደማስቆ ኔኑፋረስ እና ከሞሜላ፣ እንደ ደም ቀይ የሆነ ፅጌሬዳ፣ የቫዮሌት፣ የኢግላንታይን፣ የፈካ የሮማን እና የአደይ አበባዎች በቅርጫቱ ተጨመረ፡፡ ከዚያም ..በል አንሳ.. አለችው፡፡ አንስቶ ተከተላት፡፡TN> እልፍ ብሎ ደግሞ ከሉካንዳ ቤቱ ቆመች፡፡ ..አምስት ኪሎ ሥጋ ቁረጥልኝ.. አለች፡፡ ከፈለች፡፡ በሙዝ ቅጠል ጠቅልሎ ሰጣት፡፡ ከቅርጫቱ ጨመረች፡፡ አሁንም ..በል አንሳ.. አለች፡፡ ሃማሉ ተሸከመ፡፡ ተከተላት፡፡ደግሞ ከአንዱ ግሮሰሪ ቆመች፡፡ ከዚያም ደረቅ ፍራፍሬዎችን ገዛች፡፡ ለውዙን፣ ዘቢቡን ጨመረች፡፡ ከምግብ በኋላ የሚቀርቡ ጣፋጭ ተከታዮችንም አከለች፡፡ ..ሐማል አንሳ ተከተለኝ.. አለች፡፡ ቅርጫቱን አነሳ፡፡ ተሸከመ፡፡ ተከተላት፡፡
ከጣፋጭ መሸጫ ሱቅ ገብታ፤ ዝርግ የሸክላ ሰሃን ገዝታ፤ እንደ ዝባድ ያሉ ለዓይን እና ለአፍንጫ የጣመ ጠረን ያላቸው መዋቢያ ዕቃዎችን በሰሃኑ አስቀምጣ፤ ከቅርጫቱ ጨመረች፡፡ ..ሃማል አንሳ.. አለች ቀጠለች... ቀጠለች...በዚህ ጊዜ፤ በፍፁም ደስታ የተጥለቀለቀው ሐማል፤ ..ይሄን ሁሉ ዕቃ እንደምትገዢ አስቀድመሽ ብትነግሪኝ ፈረሴን ወይም ግመሌን ይዤ እመጣ ነበር.. አላት፡፡ እሷም ፈገግ አለችና ..ወሬውን ተወው፤ በልማ እንሂድ  አይዞህ፤ ኢንሻ አላህ፤ ጠቀም ያለ አስብ ታገኛለህ.. አለችው፤ ማጅራቱን በእጇ መታ እያደረገች፡፡
ደግሞ ከሽቱ መሸጫ ሱቅ ገባች፡፡ የፅጌሬዳ፣ የብርቱካን፣ የአደይ፣ የቫዮሌት፣ አበቦች መዐዛ ያላቸውን ፈሳሾች ገዛች፡፡ አንድ የሽቱ ማርከፍከፊያ ጠርሙስም ገዛች፡፡ እጣኖችን፣ ሰንደሎችን ገዛች፡፡ በእስክንድሪያ የተሰሩ ሻማዎችን ሸመተች፡፡ ከዚያም በቅርጫቱ ጨምራ ..አንሳና ተከተለኝ.. አለች፡፡ ሄዳ ከአንድ ሰፊ ግቢ ቆመች፡፡  በግቢው የሚታየው ቤት እጅግ ያማረና አምዶቹ ሞገስ የሰጡት ቤት ነው፡፡ ባለ ሁለት ተካፋች የሆነው እና ከጥቁር እንጨት የተሰራው የቤቱ በር ላይ ቀይ የወርቅ ቅጠል ተለብጦ ይታያል፡፡ ከበሩ እንደ ደረሰች ዓይነ እርግቧን ወደ ጎን አደረገች፡፡ እናም በቀስታ አንኳኳች፡፡ ሐማሉ ከኋላዋ እንደ ቆመ፤ ስለ እመቤቲቱ ቁንጅና፣ ተወዳጅነት እና የደስደስ በስተቀር ሌላ የሚያስበው አልነበረውም፡፡ በሩ ተከፈተ፡፡
ጉድ ነው፡፡ በሩን የከፈተችው ረዘም መለል ያለች ወጣት ናት፡፡ የቁንጅና አብነት የምትሆን፤ የአዕምሮ ብሩህነትን የታደለች ፍጹም ግርማ ሞገስ ያላት ወጣት ናት፡፡ ግንባሯ እንደ ነጭ አበባ ሆኖ ጉንጮቿ እንደ ቀይ ፅጌሬዳ የቀሉ ናቸው፡፡ ብሩህነትን የተላበሱት ዓይኖቿ እንደ ጊደር ወይም እንደ ሜዳ ፍየል ስክት ያሉ ናቸው፡፡ ቅንድቦቿ የአዲስ ጨረቃ ቅርፅ የያዙ ናቸው፡፡ አፏ የጠቢቡ ሰለሞንን ቀለበት የመሰለ ሲሆን ከንፈሮችዋ ፍም ናቸው፡፡ ጥርሷም በክር ተለክቶ የተደረደረ ሉል ይመስላል፡፡ አቤት አንገ አንገትዋ እንደ ሚዳቋ አንገት መለል ያለ ነው፡፡ ጡቶቿ ሞላ ያለ ሮማን ይመስላሉ፡፡ ስትራመድ፤ ሰውነቷ በለበሰችው ቀሚስ ውስጥ እንደ ፀጉር ጉንጉን ይሽመለመላል፡፡ እምብርቷ፤ አንድ ብልቃጥ የወይራ ዘይት ይይዛል፡፡
በጥቅሉ የምድር ባለቅኒያት ሁሉ በቅኔያቸው ያወደሷት ሴት ትመስላለች፡፡ ቁጥብ፤ በዚህች ሴት እልፍኝ ገብቶ በሚያየው እና በሚሰማው ነገር ሁሉ እየተደመመ ቆየ፡፡ ከወይዛዝርቱ ጋር ተላመደ፡፡ ተፈቀደ፡፡ እናም ግጥም በወይንጠጅ እየተጎነጨ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ..በአላህ ብቻችሁን ናችሁ፡፡ እኔ በዚሁ ብቆይ ምን ይመስላችኋል?.. ብሎ ጠየቀ፡፡ ጥያቄውን ከመቀበላቸው በፊት ከሦስቱ ሴቶች አንዷ ጥያቄ አቀረበች፡፡ ጥያቄውም ..ምንም ነገር ብታይ አንድም ጥያቄ ላታነሳ ማሃላ ታደርጋለህ?.. አለችው፡፡  ሐማሉ ቁጥብ ..እምላለሁ.. አለ፡፡ ከመሃላው በኋላ ..ወዲያ ሂድና እዚያ ከበሩ ላይ የተፃፈውን ነገር አንብብ.. አሉት፡፡ በወርቅ ፊደል ከበሩ የተፃፈው ቃልም እንዲህ የሚል ነው፡፡ ..የማይኮነስረውን ነገር የሚያወራ  ሰው፤ የማያስደስተውን ነገር ይሰማል.. ተረቱ ይቀጥላል፡፡ ህይወት የምንፈታት እንቆቅልሽ ሳትሆን የምንኖራት ትንግርት እንደ ሆነች ስንቀበል የማይኮነስረንን አናወራም የማንወደውንም አንሰማም፡፡ ከፍ ሲል ቀንጨብ ያደረኩት የሪቻርድ በርተን ተረት ይቀጥላል፡፡ ተረቱም የኛ ህይወት ነው፡፡ ህይወት እንደ ቁጥብ እመቤት ነች፡፡ እኛም ሐማሎቿ ነን፡፡ እመቤት ህይወት፤ መጪውን ዘመን እንደ ቁጥብ በሸክሟ፣ በስጦታዋ፣ በፀጋዋ አምበሽብሻ ታሳድረን፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፡፡ ተረቴን መልሱ...

 

Read 6547 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:26