Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:47

ምርኮ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለማን ያካፍል ሚስጥሩን? ደግሞስ ምን ብሎ ነው የሚያካፍለው? ለምንም የማይመች ነው ነገሩ፡፡
ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ ማድረግ የተገደደውን ግን አደረገ፡፡ ለአንድ ሺ አንድ ጊዜኛ የቀኝ እጁን መዳፍ ተመለከተ፡፡ አዲስ ድንጋጤ/ያየውን ነገር ሊለምደው አልቻለም፡፡ ልቡ እንደሚበጠር ጤፍ ሳሳበት፣ ለዝናብ እንደተጋለጠ አሸዋ ተሸረሸረበት፡፡
ደጋግሞ ስለተመለከታቸው ነው መሰል ትኩረት የሰጣቸው የመዳፉ መስመሮች ጐልተው ታዩት፡፡
አንዳንዶቹ ለዘመናት የጅረት መውረጃ ሆነው ያገለገሉ ያህል ጉልህ ናቸው፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ጉንዳን የሄደበትን መንገድ የመፈለግ ያህል አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ዋናው ነገር፣ እነዚህን መስመሮች ከተለያየ አቅጣጫ በመመርመር ስለራሱ አንድ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደሚቻል ተምሮአል፤ ደርሶአልም፡፡

የትኛውን የአካል ክፍሉን ይሆን የሚያጣው? ጆሮውን? አይኑን? እጁን? እግሩን? የትኛውን? “በሃያዎቹ የእድሜህ አጋማሽ ላይ አካለ ስንኩል ትሆናለህ” በመዳፉ ላይ የተሸከመው የመስመር ማህተም ያረፈበት ጸሊም መልእክት/፡፡ አሁን እድሜው ሃያዎቹን አጋምሷል፡፡ 
ደጋግሞ፣ ደጋግሞ ተመለከተ መዳፉን፡፡ አዲስ መልእክት ፍለጋ ግን አይደለም፡፡ ከስጋው የተበጁት የመዳፉ መስመሮች በአፍታ ይለወጣሉ ብሎም አይጠብቅም፡፡ ግን ደጋግሞ፣ መላልሶ አያቸው፡፡
በእጁ ላይ የአካለስንኩልነት መልዕክት ተሸክሞ ከዚህ በላይ መጓዝ አልቻለም፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ችሎአል፡፡ ተሸክሞአል፡፡ ሆኖም ሸክሙ ቀስ በቀስ ጉልበት እያገኘ፣ የሱ ጉልበት ደግሞ እየሳሳ መጣ፡፡
አሁን መፍትሔ መገኘት አለበት፡፡ የሆነ አይነት መፍትሔ፡፡ ከሆነ አቅጣጫ ጠብ ብሎ ሸክሙን የሚያቀል መፍትሔ፡፡
ስለሚጐለው አካሉ በማውጠንጠን የተሞላው አእምሮው አንድ ሃሳብ አቋረጠው፡፡ ይህ ሃሳብ ያለፈበትን ቀጭን መንገድ ተከትሎ አእምሮው ተንፈስ አለ፡፡ አዎ እነዚህን መፃፍ ማንበብ የተማረባቸውን መጻሕፍት ማቃጠል አለበት፡፡ አእምሮው ውስጥ የተደፋው መርዝ የተቀመጠው እነሱ ውስጥ አይደል?
ከቤት ከተቀመጡበት አወጣቸው፡፡ ብዛታቸው ሶስት ነው፡፡ ክብሪት አውጥቶ ሊለኩሳቸው አሰበ፡፡
ግን ቤተሰቦቹ ምን ይሉታል? ህመሙ የባሰበት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ሌላውን አማራጭ ተከተለ፡፡ ሶስቱንም መጻሕፍት በጀርባው ስር ሸጉጦ ወደ ሽንት ቤት ገባ፡፡ መጀመሪያ መጠኗ አነስተኛ የሆነችውን መጻሕፍት በሽንት ቤቱ አፍ ቁልቁል ለቀቃት፡፡ ቀጥሎ አካሉን በተመለከተ መርዶውን በግልጽ ቋንቋ ያረዳውን አሽቀንጥሮ ዶለው፡፡ “ለእናንተ የሚገባችሁ ቦታ ይህ ነው” የሚል ይመስላል፡፡
ሆኖም ከሽንት ቤቱ ወጥቶ ቤት ከመድረሱ በፊት የመዳፉ መስመሮች ላይ አፍጦ ነበር፡፡ የትኛውን አካሉን? መቼ? እንዴት?...መልስ ያልተገኘላቸው አስጨናቂ ጥያቄዎች፡፡
2
“ቹችዬ ሃኪም ቤት መሄድ አለብህ፡፡ የበለጠ እየከሳህ ነው፡፡ ደግሞ ፍዝዝ ትላለህ፡፡ ከዚህ የበለጠ ዝም ብለን ልናይህ አንችልም” አለችው እህቱ፡፡
የሚሰጠው ምላሽ አጣ፡፡ የሚታይበትን ለውጥ ተመልክተው ታናሽ እህቱና እናቱ ምን እንደነካው መጠየቅ ከጀመሩ ወራቶች አለፉ፡፡ ወደ ህክምና ሊወስዱት መለማመጣቸው ሰነባብቷል፡፡ አሁን ግን በእንቢታው ሊገፋበት አልቻለም፡፡ ከየትም አቅጣጫ ቢሆን ጠብ የምትል እርዳታ ከተገኘች የምትናቅበት ጊዜ አይደለም፡፡ ግን ምን ብሎ ለሃኪሙ ያስረዳዋል? መዳፉ ላይ ያረፈውን ማህተም ሃኪሙ ሊለውጥ ይቻለዋል?
እናትየው የሴት ልጃቸውን ጥያቄ ሰምተው ከቤት ወደ ልጆቻቸው ወደ ውጭ ወጡ፡፡
“እውነቷን እኮ ነው ቹችዬ… እኛ እንዲህ ዝም ብለን እያየን አንድ ነገር ብትሆን ምን ይባላል? ኧረ ባክህ እሺ በለን፡፡”
“እሺ” አለ ምናልባትም ከነጋ ከተናገራቸው ጥቂት ቃላት ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ፍዝዝ፣ ድንዝዝ ማለት ነው የሚያበዛው፡፡ ሰዎችንም ቢርቅ መርጧል፡፡
እናትየው ነጠላቸውን ለብሰው፣ ገንዘብ ይዞ ለመምጣት አፍታ አልፈጀባቸውም፡፡
3
“እንዴት ነው የሚያደርግህ?” ጠየቀ፣ ፊት ለፊት ባለ ጠረጴዛ የተቀመጠው ዶክተር፡፡
ምንም የሚናገረው ነገር አልመጣለትም፡፡ አእምሮው ተሰብስቦ ስለጥያቄው አላሰበም፡፡ ጆሮውም በደንብ አላዳመጠም - ቹቹ፡፡
“ፍዝዝ ይላል፡፡ ምግብ በጣም ቀንሷል፡፡ ሌሊት ላየው ሲሄድ ሲገላበጥ ነው የሚያገኘው፡፡ እንቅልፍ የለውም፡፡” አሉ እናትየው፤ ዶክተሩ ፊቱን ወደእሳቸው ሲያዞር፡፡ ለታማሚው ዝምታ የበለጠ ትኩረት የሰጠ የሚመስለው ዶክተር ብእሩን አሹሎ አቀረቀረ፡፡
4
“ይሁና … ይሁና … አካለ ስንኩልነት በኔ አልተጀመረ” አለ ከሚገላበጥበት አልጋ ላይ ሆኖ፡፡
በአፉ የሚገባው ኪኒን ከሚሰጠው እረፍት ይልቅ በአይኑ እየተወረወሩ የሚገቡት የመዳፉ መስመሮች የሚፈጥሩት ሁከት ይሰማዋል፡፡ ድንገት አንድ ነገር እንዳሰበ ሁሉ ከአልጋው ተቻኩሎ ተነሳ፡፡ እንደነገሩ ለባብሶ ወጣ፡፡ ወደ መንገድ፡፡
“ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ” ከጉዞዋ ያስቆማትን እዛ ሰፈር የማትጠፋ እውር የኔ ቢጤ፡፡ “ምን ገዶኝ ጠይቀኝ፤ ደግሞ እኔን ብሎ ተጠያቂ” አለች የያዘችውን ዱላ በሁለት እጆቿ እየተደገፈች፡፡ አረፍ ማለት የፈለገች ትመስላለች፣ በሰበቡ፡፡
“አይነስውርነትን እንዴት ለመድሽው?”
“እግዜር አይስጥ እንጂ አንዴ ከሰጠ የማይለመድ ምን አለ”
“አይ ማለቴ እንዴት ነው መለማመድ የሚቻለው?”
“አይንህ ያያል?” ጥርጣሬ በውስጧ የገባባት መሰለች፡፡ የመጀመሪያ ቀናነቷ ሸሻት፡፡
“አዎ” ቅር እያለው
“መለማመድ ነው የፈለግሽው? ለእውቀት?”
“አዎ” ደገመ ምን ማለት እንዳለበት በቅጡ ሳያስብ፡፡
“በመጀመሪያ ቀጭን ጨርቅ ታዘጋጃለህ፡፡ ከዚያ አይንህ ዙሪያ ትጠመጥመዋለህ”…ብላ የጀመረችውን ሳትጨርስ “አንተ ፌዘኛ አሿፊ” ስትል በያዘችው ዱላ ጐኑ ላይ ለመጠጠችው፡፡ በሃሳብ ናላው ዞሮ ስለነበር ከቆመበት አልተንቀሳቀሰም፡፡ ለዘብ እያደረገች ደጋገመችው፡፡ ግትር ብሎ ከቆመበት ሲቀር ጤንነቱን ስለተጠራጠረች እየተወለካከፈች ሮጠች፡፡
5
“ቹቹዬ ሌላ ዶክተር ጋ እንሂድ” አለችው - እለት ከእለት፣ ከሰአት ሰአት ጤንቱ ላይ ለውጥ ስትናፍቅ የቆየች እህቱ፡ ሌሊት ሌሊት በመድሃኒቱ ጉልበት እንቅልፍ ይወስደው ከመጀመሩ በቀር ፍዝዝ ማለቱ፣ ከሰውነት መውጣቱ አልቀረም፡፡ እንደውም ብሶበታል፡፡ አንዳንዴ በጥልቅ የሚያውጠነጥነው ነገር አንዳለ ይሰማታል፡፡ “በቃ ዶክተሩ ምንም ሊያደርግልኝ እንደማይችል ነገርኩሽ አይደል? አይገባሽም” መለሰ ቆጣ ብሎ፡፡ ለቁጣ የሚሆን ጉልበት እንኳ ሰውነቱ እንዳልቋጠረ ስታውቅ ይበልጥ አዘነችለት፡፡ ፍቅር ይዞት ይሆን እንዴ? ግን ፍቅር ይህን ያህል አሰቃቂ ይሆናል? ለረዥም ሰአት ፍዝዝ የሚለው ለምንድነው? ዶክተሩስ ሊረዳው የማይችለው ጉዳዩ ምን ቢሆን ነው? አውጠነጠነች፡፡ ችግሩን ከአዲስ አቅጣጫ ለማየት አእምሮዋ ተከፈተ፡፡
የትኛው የአካል ክፍሉን ነው የሚያጣው? በምን አይነት አደጋ? በየትኛው ሰአት? ከዛ በኋላስ እድል ፋንታው ምንድን ነው? አእምሮው ለአንዱም ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፡፡ እያንዳንዱ ጥያቄ ግን ጭንቅላቱን ምላሽ ካላገኘሁ በሚል እንደክፉ አውሬ በጥርሱ ወግቶ ይዞታል፡፡
እያንዳንዱ ጥያቄ በአእምሮው ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ጭንቀት…ጭንቀት፡፡ ጥያቄዎቹ ጭንቅላቱን የፈላ ሽሮ ብረድስት እንደሚከፍት ከፍተው መውጣት የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ አንድ ሃሳብ ከተወጠረ አእምሮው ድንገት ፈለቀ፡፡ ለተራበ ሆዱ በስላ የተንጠለጠለች ፍሬ ያየ ሰው ያህል ሃሳቡን ሊገብር እና ተንፈስ ሊል ተቻኮለ፡፡ ከእነሱ ቤት አስራ አምስት ደቂቃ ያህል ያስኬዳል፡፡ ሄደ፡፡ ጣውላ መሰንጠቂያ ድርጅት ነው፡፡ በር ላይ ቆመ፡፡ አመንትቶ ግን አይደለም፡፡
ጆሮ የሚሰነጥቅ ድምጽ ከድርጅቱ ወደ አየሩ ይረጫል፡፡ ጣውላ መሰንጠቂያ ማሽኑ ጣውላ ሲሰነጥቅ አሊያም ሲልግ የሚያሰማው ድምጽ ነው፡፡ ቹቹ ሰተት አለ ወደ ውስጥ፡፡ ለማሽኑ አጐረሰው፡፡ ማሽኑ አሁን የጐረሰው ነገር እንደተለመደው ጣውላዎች አልተናነቀውም፡፡ በቅጽበት ነው የሰለቀጠው፡፡ ለሁለት ለየው፡፡
የሰፈሩ አየር በተደናገጡ የድርጅቱ ሰራተኞች ጩኸት ተጣበበ፡፡ በድንዛዜ የተዋጠው ቹቹ በሰዎች እንደተከበበ ወድቆ ከተኛበት አንድ ነገር ለማረጋገጥ ፈለገ፡፡ እንጥፍጣፊ ጉልበቱን ተጠቅሞ ተመለከተ፡፡ “በሃያዎቹ የእድሜ አጋማሽ ላይ አካለስንኩል ትሆናለህ” የሚል ፀሊም መልእክት የለም - ከጉንዲሽ እጁ ላይ፡፡



Read 7859 times