Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:35

የቤተ እስራኤላውያኑ እናቶች ማህፀን ምነው ድንገት ነጠፈ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በተጋጋለበት በ1984 ዓ.ም ነበር የእስራኤል ጦር ሃይልና የስለላ ድርጅቱ ሞሳድ አስር ሺ የሚሆኑ ቤተእስራኤላውያንን፣ በሱዳን በኩል በአውሮፕላን በማጓጓዝ የዘመናት ተስፋና ጉጉታቸውን እውን ያደረጉላቸው፡፡ ይህንን ወደ ተስፋይቱ አገር የተደረገ ጉዞ (አሊያህ) ቤተእስራኤሎቹም ሆኑ የእስራኤል መንግስት “ዘመቻ ሙሴ” በሚል ስያሜ እስከዛሬ ድረስ ከፍ ባለ አድናቆት ያስታውሱታል፡፡ የእስራኤል የጦር ሀይልና የደህንነት ጐበዛዝት በ“ዘመቻ ሙሴ” አስር ሺ የሚሆኑትን ቤተእስራኤላውያን ወደ ቅድስቲቱ የተስፋዋ ሀገራቸው ማጓጓዝ ቢችሉም ልባቸው ገና ጨርሶ አላረፈም ነበር፡፡ ምነው ቢባል ዘመቻውን እያካሄዱት የነበረው የአረብ ሊግ አባል፣ እስላማዊና እንደ እስራኤል “ጠላት” ሀገር ተደርጋ በምትቆጠረው በሱዳን ውስጥ ስለነበር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ እስራኤል ውስብስቡን “ዘመቻ ሙሴ”ን በተቻላት አቅም ሁሉ ለማፋጠን ብትሞክርም አጥብቃ የፈራችውን ነገር ማስቀረት አልቻለችም፡፡ 

የሱዳን መንግስት ለዘመቻ ሙሴ አይቶ እንዳላየ በመሆን (በእርግጥ አብዛኛውን ነገር አያውቅም ነበር) ሲሰጥ የቆየውን ድጋፍ ማቋረጡን ያስታወቀው ድንገት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ “ዘመቻ ሙሴ” ገና በግማሽ መንገድ ላይ እንዳለ ቀጥ አለ፡፡
የሱዳን መንግስት ድንገተኛ ውሳኔ በተለይ በኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ሠፊ ቀጠና በአሳር በመከራ በማለፍ በርካታ ቀናትን ከፈጀ አስቸጋሪና ፈታኝ የእግር ጉዞ በኋላ፣ ሱዳን ገብተው ለተሠባሠቡት ቤተእስራኤላውያን ዱብእዳ ብቻ ሳይሆን ልባቸውን ሊያፈርሰው የደረሰ አስደንጋጭ ጉዳይም ነበር፡፡
እናም ታዲያ አስራ አምስት ሺ የሚሆኑት ቤተእስራኤላውያን ተሠባስበውበት በነበረው የሱዳን በረሀ ላይ ለመቅረት በመገደዳቸው፣ በታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ ውስጥ እንደተፃፈው፣ የቀደሙት አባቶቻቸው በሲናይ በረሀ ላይ ለአመታት እንደባዘኑት ሁሉ እነሱም ለአመታት መባዘን ግዴታቸው ሆነ፡፡ በዚህ ክፉ እጣ የተነሳም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት እንደጓጉና እንደተመኙት የልባቸው ሳይደርስ መከረኛ ህይወታቸውን ለሱዳን በረሀ ገብረዋል፡፡
በ1991 ዓ.ም ግን ለሠባት አመታት ያህል የተኛና ያንቀላፋ መስሎ የነበረው የእስራኤላውያን ጠባቂ፣ በአዲስ መንፈስ ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ ክንዱን አፈርጥሞ ለኢትዮጵያውያን ቤተእስራኤሎች “እነሆኝ አለሁ!” አላቸው፡፡ እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ “ለከርሞ በእየሩሳሌም እንገናኝ” ሲባባሉና አሊያሃቸውን ለመፈፀም በበረሀ ሲባዝኑ የነበሩ ከዘመቻ ሙሴ የተረፉት ቤተእስራኤላውያን “እነሆ የተስፋውን ቀን ጥበቃ ፍፃሜው አሁን ነው!” ተባሉ፡፡
እንደተለመደው የእስራኤል መንግስት ከጦር ሀይሉ፣ ከስለላና ከደህንነት ተቋማቱ በልዩ ብቃታቸው የመለመላቸውን ጐበዛዝቱን “ዘመቻ ሶሎሞን” የሚል ስም የወጣላትን ኢትዮጵያውያን ቤተእስራኤላውያንን ወደ እስራኤል የማጓጓዝ አሊያህ እንዲያስፈጽሙ ወደ አዲስ አበባና ጐንደር በግልጽ አሠማራ፡፡ እነሱም ቀደም ብለው በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አባልነት ተመዝግበው ለዚሁ ዘመቻ አፈፃፀም ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት የተለያየ ዜግነት ካላቸው ይሁዲዎች ጋር በመተባበር፣ ድፍን አለሙን ሁሉ ጉድ ባስባለ ቅንጅትና ብቃት አስራ አራት ሺ ሶስት መቶ ሀያ አምስት ቤተእስራኤላውያንን ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ቻሉ፡፡
በ“ዘመቻ ሶሎሞን” እንደቀድሞው “ዘመቻ ሙሴ” ያለ የጉዞ መንቀራፈፍ ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ እናም እስራኤል አስራ አራት ሺ ሶስት መቶ ሀያ አምስቱን ቤተእስራኤላውያን ተስፋይቱ አገር አጓጉዛ ያጠናቀቀችው በ1983 ዓ.ም በግንቦት 17 እና 18 ቀናት ውስጥ በነበሩት ሠላሳ ስድስት ሰአታት ብቻ ነበር፡፡
ከ“ዘመቻ ሶሎሞን” አስደናቂ የአፈፃፀም ገድሎች ውስጥ ዋነኛውም ይሄው አስገራሚ የማጓጓዝ ፍጥነትና እንከን አልባ ቅንጅት ነበር፡፡
እነኚያ በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን ተሳፍረውበት የነበረው ሄርኩለስ አውሮፕላን ቴልአቪቭ ከተማ ቤን ጉርየን አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሠና እግራቸው ገና መሬት እንደረገጠ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ በማይቻል የደስታ ስሜት ተውጠውና በግንባራቸው ተደፍተው ቅድስቲቱን የተስፋዋን ሀገራቸውን እየተሳለሙ እንባቸውን አፈሰሱ፡፡
ከአስደናቂው የ“ዘመቻ ሶሎሞን” አሊያህ በኋላ ቀጣዩ ስራ የነበረው ቤተእስራኤላውያን ከእስራኤል ዘመናዊና አውሮፓዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ የማድረግ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከዘመቻው በኋላ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ያለፉትም ይህን አድካሚና እልህ አስጨራሽ ስራ በማከናወን ነው፡፡
በእነዚህ አመታት ውስጥ በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤላውያንን በተመለከተ ይዘገቡ የነበሩት አለም አቀፍ ዜናዎች ሁሉ ዋነኛ ትኩረታቸው ያደረጉት ስለ አስደናቂው የ“ዘመቻ ሶሎሞን” አፈፃፀምና ቤተ እስራኤላውያኑ በእርስ በርስ ጦርነት ከምትታመሠውና በማያቋርጥ የረሀብ አለንጋ ከምትገረፈው ኋላ ቀሯ ኢትዮጵያ ወጥተው ወደ ስልጡኗና ባለፀጋዋ ሀገር መግባት በመቻላቸው ምን ያህል እድለኛ እንደሆኑ ማሳየትና ማዳነቅን ነበር፡፡ ያኔ በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሲሠጡ የነበሩ የእስራኤል ባለስልጣናት፣የሟቹን እስራኤላዊ ዊልያም ሳፋየርን የቆየ ንግግር ሳይጠቅሱ አያልፉም ነበር፡፡
ዊልያም ሳፋየር በ1985 ዓ.ም በዘመቻ ሙሴ አማካኝነት ወደ እስራኤል የገቡትን ቤተእስራኤላውያን ካየ በኋላ፣ እስራኤላውያን እስከ ዛሬም ድረስ ታሪካዊና አይረሴ ነው የሚሉትን ንግግር አደረገ፡፡ “እነሆ አሁን በዚህ ታሪካዊ ዘመቻ አማካኝነት በሺ የሚቆጠሩ ጥቁር ህዝቦች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በባርነት ተግዘውና በሠንሠለት ታስረው ሳይሆን በክብርና በዜግነት ወደ አንድ የሠለጠነ ሀገር ውስጥ መግባት ቻሉ!”
ዊልያም ሳፋየር ረዥም ደቂቃዎች በፈጀው በዚያ ንግግሩ፣ የተስፋዋንና የቃልኪዳኗን መሬት እስራኤልን አምላክ እንደገባልን ቃል ኪዳን መሠረት ልንወርሳትና የዘላአለም ርስታችን ልናደርጋት እነሆ ሀገርና ባህር አቋርጠን መጣን የሚሉትን ቤተእስራኤላውያን በተደጋጋሚ የገለፃቸው፣ “ጥቁር ህዝቦች” እያለ እንጂ “ይሁዲዎች” ወይም “እስራኤላውያን” በሚል አልነበረም፡፡ ያኔ ከእስራኤላውያንም ሆነ ከቤተእስራኤል ተወካዮች የቀረበ ማስተካከያም ሆነ የተቃውሞ ጉምጉምታ ጨርሶ አልነበረም፡፡
ኢራናውያን “በደልን በማሸነፍ ለመበቀል መርሳትን የመሠለን ፍቱን ዘዴ የሚያስንቅ የለም” ይላሉ፡፡ የአረብ ቤዶይኖች በበኩላቸው ደግሞ “ያለ ሀይልና ስልጣን ንዴት ብቻውን አጥፊ ጠላት ነው” የሚሉት አባባል አላቸው፡፡ ቤተእስራኤላውያን የዊልያም ሳፋየርን ንግግር በዝምታ ያለፉት ከሁለቱ አባባሎች አንደኛውን አሊያም ሁለቱን በማሰብ፣ ምናልባትም ደግሞ የንግግሩ ዋነኛ መልዕክት በጊዜው በቅጡ አልገባቸው ኖሮ እንደሁ ያኔም ሆነ ዛሬ በትክክል የሚያውቅ የለም፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ ግን የያኔው የዊልያም ሳፋየር ንግግር በተለያዩ የእስራኤል ባለስልጣናት በተለያየ ጊዜ መጠቀሱ፣ቤተእስራኤላውያኑ በወደፊቱ የእስራኤል ኑሮዋቸው ዘራቸውንና ቀለማቸውን በተመለከተ ምን አይነት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ሁነኛ አመላካች ነበር፡፡
“ዘመቻ ሶሎሞን” በድል ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ባለፉት ሃያ አንድ አመታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተለይም ሃይማኖታቸውን ወደ ኦርቶዶክስ ክርስትና በመለወጣቸው የተነሳ “ፈላሻ ሙራ” እየተባሉ ተለይተው የሚጠሩ ቤተእስራኤላውያን እየተንጠባጠቡም ቢሆን አሊያቸውን በመፈፀም ወደ እስራኤል መግባት ችለዋል፡፡
ባለፈው አመት ሀምሌ ላይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩት “ፈላሻ ሙራ” ቤተእስራኤላውያን አሊያቸውን ፈጽመው ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ሠበብ አስባብ እየፈጠረ ነገር ይጐትታል፣ ይባስ ብሎም ይከለክላል እየተባለ የሚወቀሰው የእስራኤል መንግስት፤ ሁሉም ቤተእስራኤላውያን ተጠቃለው ወደ እስራኤል እንዲገቡ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ አስፈፃሚው አካልም ቀደም ብለው እንደተካሄዱት አሊያዎች ሁሉ ይሄንንም ትዕዛዝ ለማስፈፀምም “ዘመቻ የእርግብ ክንፎች” የተባለ የጉዞ ዘመቻ በመንደፍ፣ የሁለት ዙር የጉዞ ፕሮግራም አዘጋጀ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ሁለት መቶ አርባ፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ሶስት መቶ ስልሳ በድምሩ ስድስት መቶ “ፈላሻ ሙራ” ቤተእስራኤላውያንን ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በማጓጓዝ ለእስራኤል መሬት እንዲበቁ ተደረገ፡፡
ሶስት መቶ ስልሳዎቹን ቤተእስራኤላውያን የጫነው አውሮፕላን ቴልአቪቭ ቤን ጉርየን አውሮፕላን ማረፊያ እንዳረፈ፣ የተለያዩ የእራስኤል ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደ ልዩ ስነስርአት፣ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤላውያን ተጠቃለው ወደ እስራኤል እንደገቡና አሊያህአቸው እንደተፈፀመ በይፋ ተገለፀ፡፡
ቤተእስራኤላውያኑም ከአውሮፕላኑ እንደወረዱ የቀደሙት ወገኖቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣ በከፍተኛ የደስታ ሲቃ ተይዘው መሬቲቱን እየተሳለሙ አነቡ፡፡ አንዳንዶቹም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተንሰቅስቀው አለቀሱ፡፡
እነሱ እንዲህ ሲሆኑ እንዲሰፍሩበት የተወሰነው አቪም የመጠለያ ማዕከል የሚገኝበት የሻአር ሀነጌቭ ክልል ምክር ቤት አባልና የአይሁድ ድርጅት ለእስራኤል ሊቀመንበር በየተራ ንግግር እያደረጉ ነበር፡፡ በተለይ የአይሁድ ድርጅት ለእስራኤል ሊቀመንበር የሆኑት ናታን ሻረንስኪ “ከሀያ አመታት በኋላ በዚች በዛሬዋ እለት ወንድምና እህት ሲገናኙ ማየት በእውነት ተአምር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን አይሁዶች እስራኤልን እንደለቀቁ የሀኑካህ (የሶሎሞን ቤተመቅደስ እንደገና መገንባትን ለመዘከር የሚደረግ) ክብረ በአል አልነበረም፡፡ አሁን ግን የሀኑካህን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም ክብረ በአሎች አብረን እናከብራለን፡፡ ምስጋና ለእስራኤል መንግስት ይሁንና አሁን ሁላችንም እኩል አይሁዳውያን እኩል እስራኤላውያን ሆነናል” በማለት በከፍተኛ ጭብጨባ የታገዘ ንግግራቸዉን አደረጉ፡፡ በዚህ የናታን ሻረንስኪ ስሜታዊ ንግግር መካከል ግን በጭብጨባው ውስጥ የተዋጠ አንድ ከፍተኛ ማጉረምረም ነበር፡፡ ምንጩም በስፍራው ከተገኙት የቤተእስራኤሎች ድርጅቶች መሪዎችና የመብት ተሟጋች ተቋማት አመራሮች ነበር፡፡ የናታን ሻረንስኪ ንግግር ዊልያም ሳፋየር ከዛሬ ሀያ ሠባት አመት በፊት ካደረጉት ንግግር በእጅጉ ይለያል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የቤተ እስራኤላውያኑ ድርጅቶች መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች የሰሙት ንግግር ካንጀታቸው ጠብ ሊልላቸው ጨርሶ አልቻለም፡፡ ለምን ቢባል እግራቸው የእስራኤልን መሬት ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ፣ በዘራቸውና በቀለማቸው የተነሳ በየእለቱ የሚደርስባቸው መድልዎና ከፍተኛ የመብት ረገጣ የናታን ሻረንስኪን “ሁላችንም እኩል እስራኤላውያን ነን” ንግግር አምኖ ለመቀበል ጨርሶ የማይቻል ስላደረገባቸው ነበር፡፡ እስራኤል እንደ ሀገር ቆማ የዛሬውን ማንነቷን ያገኘችው፣ እንደቤተእስራኤሎቹ ሁሉ ከመላው ክፍለ አለማት በተሠባሠቡ አይሁዳውያን ህዝቦች መሆኑን ማስረዳት ያዋጁን በጆሮ እንደመናገር ተደርጐ ሊቆጠርብን ይችላል፡፡ ህንዳውያን “ቁመና፣ አለባበስና የፊት ለፊት ገጽታ አሳሳች ወይም አታላይ ነው” የሚል የዘወትር አባባል አላቸው፡፡ ቤተ እስራኤላውያን የእስራኤል ቁመናና የፊት ለፊት ገጽታ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ አታላይና አሳሳች መሆኑን ለመረዳት የፈጀባቸው ጊዜ በአመታት የሚቆጠር ሳይሆን የአንድ እጅ ጣቶች እንኳን በማይሞሉ ወራቶች ብቻ ነው፡፡
ቤተ እስራኤላውያን የዘመናዊቷና የተስፋዋ ሀገራቸው የእስራኤል ኑሮ እንዳሰቡትና ለዘመናት ተስፋ አድርገው እንደጓጉለት እንዳልሆነ መረዳት የጀመሩትና በዘርና ቀለማቸው የተነሳ “ኩሽም” (ባሪያ) የሚል አዲስ ተቀጽላ ስም ያተረፉት፣ በአዲስ መጤነት የሰፈሩበትን ካምፕና ካምፑም የሚገኝበትን የከተማውን ስም ገና በቅጡ እንኳ ለይተው ሳያውቁት ነበር፡፡
እንዲህም ሁሉ ሆኖ ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ እንደ ቤተ እስራኤሎች ያለ ተጋፊ ያልሆነ፣ የሰጧቸውን በምስጋና የሚቀበሉና ታጋሽ ልበ ሰፊ የህብረተሠብ ክፍል በምድረ እስራኤል በመብራት ፈልጐ ማግኘት ጨርሶ አይቻልም፡፡ በየጊዜው የሚደርስባቸውን ያን ሁሉ የዘረኝነት ግፍና በደል ከቻለ እንዲያወስግድላቸው ካልሆነ ደግሞ እንዲያስታግስላቸው ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ያለመታከት ለእስራኤል መንግስት ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡ ለዚህን ያህል አመት ጥያቄአቸው የቀረበለት የእስራኤል መንግስት ይሠጣቸው የነበረው መልስ ግን ሁለት አይነት ብቻ ነበር፡፡
“ከኢትዮጵያ የችጋርና የሰቆቃ ኑሮ በገላገልናችሁ ደሞ የምን ውለታ ቢስ መሆን ነው? ይልቁንስ የእስራኤል መንግስት ላደረገላችሁ ነገር ሁሉ በጣም አመስግኑት!” የሚልና “መጥፎ አናጢ ሁሌም በመጋዙ ያመካኛል” የሚል፡፡ (መቸም የዚች አነጋገር ትርጉም ለኢትዮጵያዊ ትጠፋዋለች ማለት ዘበት ነው!)
እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መፍትሄ ቢከለክላቸውም ቤተእስራኤላውያን ለእስራኤል መንግስት ያላቸው ከበሬታና አድናቆት ይህን ያህል ቀንሶ አያውቅም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ከአምላክ ቀጥሎ በምድር ላይ ያላቸው መተማመኛ መንግስት ብቻ ነበር፡፡
ያን ሁሉ በደልና ግፍ ሲቀበሉ ቀድመው ለአመጽ ከመጠራራት ይልቅ በየቤታቸው እየተብሰለሰሉ የእስራኤል መንግስት የሚወስደውን እርምጃ በከፍተኛ ትዕግስት የሚጠባበቁትም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ በ1985 ዓ.ም እንዳደረጉት አይነት በእስራኤል እየደረሠባቸዉ ያለውን ከፍተኛ የመብት ረገጣና የዘርና ቀለም መድልዎ ወደ አደባባይ በመውጣት የሚቃወሙት መሸከም ከሚችሉት በላይ ሲሆንባቸው ብቻ ነው፡፡ ያኔ የእስራኤል ራቢኔት ወይም የሀይማኖት አባቶች ጉባኤ ለከፍተኛ ውርደትና መሸማቀቅ የዳረጋቸውን የ “ሂዱሽ ሀይሁድ ሚክቫህ (የመታደግ ጥምቀት) ሀይማኖታዊ ትዕዛዝ አንድ ወር የዘለቀ የስራ ማቆምና የረሀብ አድማ በመምታት ተቃውመው ትዕዛዙን ማሻር ችለዋል፡፡
ከዛን ጊዜ ጀምሮም ቤተ እስራእላውያን ላለፉት ሀያ ሠባት አመታት እጅግ ብዙ የመብት ረገጣና የዘርና ቀለም መድልኦ እየተጋፈጡ ኖረዋል፡፡ ቤተእስራኤላውያን በእስራኤል ጠቅላላ ማህበረሠብ ውስጥ የተመደበላቸው ደረጃና በተግባርም የተዘጋጀላቸው ቦታ ከሁሉም የመጨረሻ የሆነው ብቻ ነው፡፡ ቤተ እስራኤላውያን በዘራቸውና በቀለማቸው የተነሳ የተስፋዋና የቃልኪዳኗ ሀገር እያሉ በሚጠሯት እስራኤል መቀዳጀት የቻሉት “የክብር ስም” “ኩሽም” የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ባሪያ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሳለፉት የብዙ ዘመናት የነዋሪነት ታሪክ የተለያዩ ችግሮችን አሳልፈዋል፡፡ በማናቸውም የኢትዮጵያ የማህበረሠብ ክፍል ዘንድ ግን ኩሽም ወይም ባሪያ ተብለው ተንቀውና ተዋርደው ጨርሶ እንደማያውቁ ራሳቸው እማኝ ናቸው፡፡
ከማንም ምንም ነገር ይደረግልኛል ብለው የማይጠብቁ ወይም የማይተማመኑ፣ ሳይደረግላቸው በቀረ ጊዜ ቀረብኝ ብለው ስለማያዝኑ ወይም ስለማይበሳጩ እነሱ የተባረኩ ናቸው፡፡ ቤተ እስራኤሎች ግን ለዚህ ጨርሶ አልታደሉም፡፡ ችግሮቻው አይነታቸውም ሆነ ፈርጃቸው ብዙ ስለሆነ ከመንግስት የሚጠብቁት የዚያኑ ያህል ብዙ ነው፡፡ በዚህ ሂደት መሀል ታዲያ ሁለት ነገሮችን በሚገባ ለመረዳት ችለዋል፡፡ ከሌሎች የሚለምኑ የማማረጥን ፀጋ እንደማያገኙና “ግመል መካ ደርሶ መምጣት ቢችልም ሀጂ እንደማይባል” እነዚህን እውነታዎች በእርግጥም በደንብ አውቀዋቸዋል፡፡ የእስራኤል መንግስት ከሌሎቹ ዜጐቹ እኩል እንደማይመለከታቸው፣ መርጦና ይሁነኝ ብሎ አበጅቶ ከሠጣቸው የመጨረሻው ደረጃ ወደ ላይ ከፍ እንደማያደርጋቸው አሁን በደንብ ተገንዝበውታል፡፡
ይህ በየእለቱ በግልጽ የሚታይ እውነታ የሚያስደገንጠውና የሚያሳቅቀው ሌሎችን እንጂ የእስራኤል መንግስት ቁብ የሚሠጠው ወይም ነገሬ ብሎ የሚወዘወዝበት ጉዳይ አይደለም፡፡ የስነ ምህዳር ባለሙያዎች “መጥፎ አለባበስ እንጂ መጥፎ የአየር ፀባይ ብሎ ነገር የለም” ይላሉ ይባላል፡፡ የእስራኤል መንግስት የቤተ እስራኤሎችን ችግርና የእለት ተዕለት ፈተና ለማስረዳት የሚሞክረውም ይህንን አባባል በመጥቀስ ነው፡፡ የቤተእስራኤሎች ችግር የእስራኤል የአየር ሁኔታ መጥፎ ሆኖባቸው ሳይሆን እነሱ ለአየር ሁኔታው የሚስማማ ልብስ መልበስ ስላቃታቸው ወይም መጥፎ አለባበስ ስለለበሱ ነው የሚል ነው፡፡
በእስራኤል ምድር ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው ግን የእስራኤል መንግስት ከሚለው በእጅጉ የተለየ ይልቁንም ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ ቤተእስራኤላውያን የመጨረሻውን ዝቅተኛ የህብረተሠብ ደረጃ እንደያዙ በዘርና ቀለማቸው እለት ተእለት የሚደርስባቸውን ከፍተኛ በደል ራሳቸው ብቻ እየተጋፈጡ እንዲኖሩ በግልጽ አፍ አውጥቶ ባይናገረውም በተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን ይሁን ብሎ የወሰነ ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተእስራኤላውያን ላይ እየደረሠ ያለው ግፍና ከፍተኛ በደል ደግሞ አሁን የያዙትን የመጨረሻ ዝቅተኛ ደረጃ እንደያዙ እንዲኖሩ ብቻ ሳይሆን ዘራቸው በተራዘመ ሂደት ተመናምኖ እንዲጠፋም የፈለገ ይመስላል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ አረቦች “ቀኑ በረዘመ ቁጥር ብርዱም እየጠነከረ ይሄዳል” ይላሉ፡፡ ቤተእስራኤላውያን በእስራኤል የሚያሳልፉት አስቸጋሪና ፈታኝ ቀናቶች በረዘሙ ቁጥር የችግርና የፍዳቸው አይነትና መጠንም የዚያኑ ያህል እየጠነከረባቸው ሄዷል፡፡ “ኩሽም” ወይም ባሪያ እየተባሉ መጠራታቸውና በመኖሪያ አካባቢያቸውም ሆነ በስራ ቦታቸው የሚቀበሉት የመብት ረገጣና የዘር መድልዎ ሳያንሳቸው፣ አሁን ደግሞ የዘራቸው መባዛት የተፈለገ አልሆነም፡፡ እናም ተረኛው የጥቃት ኢላማ ሆኖ የተመረጠው የቤተእስራኤል እናቶች ወላድ ማህፀን ነው፡፡
ይህ አስደንጋጭና አስፈሪ የዘረኝነት በደል ቤተእስራኤላውያን ከመጥበሻው ድስት ወደ ጋመው ምድጃ እንዲዘሉ አስገድዷቸዋል፡፡ በመኖሪያ አካባቢያቸው፣ በስራ ቦታቸው፣ በትምህርት ቤት፣ በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በትራንስፖርትና በጤና ተቋማት ወዘተ በየእለቱ የሚጋፈጡትን የመብት ረገጣ፣ የዘርና የቀለም መድልዎ ለመንግስት አቤት የሚሉትን አቤት እያሉ፣ የማይሉትን ደግሞ በየራሳቸው ቤተሠብና ልብ ውስጥ ቀብረው እየተብሰለሰሉ ኑሮአቸውን ይገፉታል፡፡ ላለፉት አስር አመታት በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤሎች፣ ቤትና ግቢያቸው በህፃናት ልጆቻቸው የቡረቃ ጩኸት አልደምቅ ማለቱ፤ የሳራና የርብቃ አምላክ በሽልም ያውጣሽ የምትባል ቤተእስራኤላዊት እናት፤ የአብርሀም አምላክ እንኳን ዘርህን አበዛልህ የሚባል ቤተእስራእላዊ አባት እንደ ብርቅ የመታየቱ ነገር ለማንም የልብን ገልጠው የማይናገሩት “የውሽማ ሞት” አይነት ሆኖባቸው ነበር፡፡ የእስራኤልን መሬት ከረገጠችበት ከዛሬ ስምንት አመት ጀምሮ ከባሏ ጋር የምታደርገውን የሚስትነት ወግ ሳታጓድል ማህፀኗ ዘር ማፍራት አለመቻሉ ሌላ ተጨማሪ የጭንቀት አበሳ እንደሆነባት እንደ እማዋይሽ አይነት በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላዊ እናቶች አሉ፡፡ እነሱ ጭንቀታቸውን የሚከፍሉት ዘወትር በየማለዳው በየምኩራቡ ደጀ ሰላም እየተደፉ ሳራን በእርጅና እድሜዋ እንኳን አስቧት በልጅ ፀጋ የባረካት አምላክ እነርሱንም እንዲያስባቸው በመማለድ ነበር፡፡
ባለፉት አስር አመታት የቤተእስራኤል እናቶች ማህፀን፣ ዘር የማፍራት ፀጋው በሀያ በመቶ መቀነሱ በይፋ ሲነገር፣ ፈረሶቻቸው ከተሠረቁ በኋላ ጋጣቸውን የዘጉት የመሠላቸው ቤተእስራኤላውያኑ ነገሩ “ከአምላካችን ቢሆን ነው” በሚል ፊታቸውን ወደ አምላካቸው ለልመና ከማዞር በቀር ሌላ ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡
ቤተእስራኤላውያኑን ተጥደውበት ከነበረው የጋለ የመጥበሻ ድስት ወደ ጋመው ምድጃ እንዲዘሉ ያደረጋቸው ግን ሲባ ሪውቨን የተባለች የሴቶች መብት ተቆርቋሪ ያዘጋጀችው ጥናትና ዘጋቢ ፊልም “ቫኩም” በተሰኘ ፕሮግራም በእስራኤል የትምህርት ማሠራጫ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ፣ ለህዝብ ከታየና የማህፀናቸውን መንጠፍ ሚስጥር ይፋ ካደረገው በኋላ ነበር፡፡ ወላድ ማህፀናቸው ያነጠፈው ወደ እስራኤል ለመምጣት በመዘጋጀት ላይ እያሉ በአሜሪካ የጥምር ስርጭት ኮሚቴ (American Joint Distribution Committee) በሚመራው ክሊኒክ ውስጥ ምንነቱንና የሚያስከትለውን ውጤት ሳይነግሩዋቸው በማባበልም በማስገደድም የወጓቸው ዲፓ-ፕሮቬራ የተባለ (በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም ሀገር ጥቅም ላይ እንደማይውል ይነገራል) የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው፡፡ በክሊኒኩ ይሠሩ የነበሩ ነርሶችና ሌሎች ባለሙያዎች ይህን መድሃኒት እንዴት እንዲወጉ እንዳደረጓቸው ሲባ ሪውበን ያነጋገረቻቸው እንደ እማዋይሽ አይነት ሰላሳ አምስት የቤተእስራኤል “ወላድ የነበሩ” እናቶች በደንብ አድርገው ተርከውታል፡፡
የአይሁዶች የታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ፤ አምላክ የሰው ልጆችን በራሱ አምሳያ ሙሉ፣ ረቂቅና፣ ህብር አድርጐ እንደፈጠራቸው ግልጽ አድርጐ ያስረዳል፡፡ የሰው ልጅ ፍጥረት እዚህ ጐደለው የማይባል ሙሉ ነው፡፡ የሰው ልጅ የፍጥረት አካላቶቹ አንዳቸው ከአንዳቸው ተነጥለው ለብቻቸው የማይቆሙና ሙሉ የማይሆኑ በመሆናቸው ህብር ናቸው፡፡ ሙሉና ህብር በመሆኑም የሰው ልጅ አምላክ መለኮታዊ ሀይሉን የገለፀበት ረቂቅ ፍጥረት ነው፡፡
አይሁዳውያን በመበተናቸው ዘመን በአለሙ ሁሉ ተሰደው ይኖሩ በነበረ ጊዜ፣ ቅድስቲቱ መሬት እየሩሻሌይም ትዝ ባለቻቸው ጊዜ “እየሩሻሌይም ሆይ! ብከዳሽ ቀኝ አይኔ ትክዳኝ! ብረሳሽ ቀኝ ክንዴ ትርሳኝ!” ይሉ የነበረው ቀኝ አይናችንና ቀኝ ክንዳችን ከድተውን በህይወት እንዳለን ስለማይቆጠር፣ መቼውንም ጊዜ ቢሆን አንረሳሽም አንከዳሽምም ለማለትና እግረመንገዳቸውንም የፍጥረታቸውን ሙሉነትና ህብር ለማመልከት ነበር፡፡አምላክ የሰውን ልጅ ሙሉ ረቂቅና ህብር አድርጐ፣ በራሱ አምሳያ ከፈጠረው በኋላ በዝቶና ተባዝቶ ምድሪቱን እንዲሞላት በማዘዝ የራሱን ዘር በማብዛት የሚገኘውን ድንቅና ረቂቅ ፀጋ እንዲያይና እንዲካፈል አድርጐታል፡፡ ይህ ዘርን የማብዛት ልዩና ድንቅ ፀጋ አምላክ ለሰው ልጆች ሁሉ ያዘዘው ትዕዛዝ ብቻ ሳይሆን የሠጠው ተስፋና ምርቃትም ነበር፡፡ አምላክ የአይሁዳውያን ቀደምት አባት የሆነውን አብርሀምን እርሱን ብቻ እንዲያመልከውና ሂድ ወዳለው ቦታ እንዲሄድ ሲነግረው የሰጠው ተስፋና የገባለት ቃል “ዘሩን እንደ ሰማይ ኮከብና እንደ ባህር አሸዋ እንደሚያበዛው” ነበር፡፡ ሚስቱን ሳራን በመበለትነት እድሜዋ የባረካትና የዘመናት የመካንነት ሀዘኗን የካሳት ማህፀኗን በመክፈትና በመባረክ ነበር፡፡
እናም የአምላክ ብዙ ተባዙና ምድሪቱን ሙሏት የሚለው ትዕዛዙም ሆነ “ዘርህን አበዛዋለሁ፣ ማህፀንሽንም እከፍታለሁ” የሚሉት የተስፋ ቃል ኪዳኖቹ የሰው ልጅን እንደፈጠረበት አፈጣጠር ጥልቅና ረቂቅ ናቸው፡፡
የአይሁዶች የታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ፤ የሰው ልጆችን ፍጥረት በተመለከተ ሌላም ተጨማሪ ማብራሪያ አለው፡፡ ይሄው ቅዱስ መጽሀፍ በአምላክ አምሳያ የተፈጠሩትን የሰው ልጆች በዘራቸው፣ በቀለማቸውና በባለጠግነት መጠናቸው ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድና ሁኔታ ልዩነት መፍጠርና በዚህም ልዩነት የተነሳ በእነርሱ ላይ በደል ማድረስ በአምላክ አምሳያ ላይ ልዩነት መፍጠርና በደል እንደመፈፀም ተደርጐ እንደሚቆጠር ያስረዳል፡፡ በዚህ ልዩነት የተነሳ የሰው ልጆችን ያጠፋ ገዥም ሆነ ምስኪን ነዳይ የአምላክን አምሳያ እንዳጠፋ ስለሚቆጠር፣ የሀጢያቱ ዋጋ የሆነውን ሞት ይቀበላል፡፡
ይህን የቅዱስ መጽሀፍ ገለፃና ማሳሠቢያ በጥሞና እንዲያስተውሉት ለራሳቸው ለእስራኤል አይሁዳውያን መልሶ መናገር፣ አምላክ በመለኮታዊ ስልጣኑ የሰጣቸው ዘርን የማብዛት ልዩና ድንቅ ፀጋቸው ለተነጠቀና የእናቶቻቸው ወላድ ማህፀን “ወገኔና ህዝቤ” በሚሏቸው አይሁዶች እጅ እንዲነጥፍ ለተደረገባቸው ቤተ እስራኤሎች ካሏቸው በጣም ጥቂት ምርጫዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህን በማለት ለማስተላለፍ የሞከሩት “እኛን ብትንቁንና ባትፈሩን እንኳን አምላክን እንኳ ፍሩ” የሚል ሀዘን ያታከተው መልዕክት ነው፡፡
ለሌሎች ግን እንደመናፍቅ ሊያስቆጥራቸው ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእስራኤል መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎችን አሊያህ ለማስፈፀም ይሠሩ የነበሩ የእስራኤል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲህ ያለ አቻየለሽና አስደንጋጭ የዘረኝነት ጥቃት፣ በቤተ እስራኤሎች ላይ በመፈፀም ከጀርባቸው ያሉትን ድልድዮች ያቃጥሏቸዋል ተብሎ በቀላሉ መገመትም የሚቻል ነገር አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የእስራኤል መንግስትም ሆነ የእስራኤል የአይሁድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የታሰበውን እንዳልታሠበ፣ የተገመተውንም ጨርሶ እንዳልተገመተ እንዳደረጉት ያስመሰከሩት የተግባር ምላሽ በመስጠት ነው፡፡ የእስራኤል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ክሊኒኮችን ይመራ የነበረው የአሜሪካ ጥምር የስርጭት ኮሚቴ (American Joint Distribution Committee) የሲባ ሪውቨንን በምስልና በፊልም የተደገፈ የጥናት ውጤት እንዲሁ በደፈናው ሽምጥጥ አድርገው ከመካድ ውጪ በነገሩ እጃቸው እንደሌለበት በተጨባጭ ማስረጃ ማስተባበል አልቻሉም፡፡
ከዚህ ይልቅ በዚህ ድርጊታቸው ለወዳጅም ሆነ ለጠላታቸው በግልጽ ማረጋገጥ የቻሉት ዋንኛ ነገር፣ ለቅዱስ መጽሀፋቸው ትዕዛዛትና መመሪያዎች ቁብ እንደማይሰጡና ከጠቅላላው የእስራኤል ህብረተሠብ በአሳዛኝ ሁኔታ የመጨረሻውን ደረጃ ይዘው እድሜ ዘመናቸውን እንዲዳክሩ ለፈረዱባቸው የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎች የሚራራ አንጀት እንደሌላቸው ብቻ ነው፡፡ በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤሎችን እስከ ቁርጭምጭሚታቸው ድረስ ያሠመጣቸው የዘረኝነት ውሀ በጣም የተበከለና ቆሻሻ ነው፡፡
ቆሻሻ ውሀ ደግሞ ማርካት የሚችለው የእሳትን ጥም ብቻ ነው፡፡ ነገሬ ብለው ከጉዳይ አልጣፉትም እንጂ ይህንንም እውነት የእስራአል መንግስትና ሸሪኮቹ የሆኑት መንግስታዊ ያልሆኑ የአይሁድ ድርጅቶች ያጡታል ብሎ መገመት ጨርሶ አይቻልም፡፡
ጥንታዊዎቹ ሮማውያን፤ ዲያቢሎስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ለመድረስ የቤተ መንግስቱን ደረጃ የሚወጣጣው በንግስቲቱ ደንገጡር ቀሚስ ተከልሎ ነው የሚል አሪፍ አባባል ነበራቸው፡፡
ከምኩራቡ ጽስት ጀርባ ላይ ቆሞ ሲያደባ የነበረው “ዘረኝነት” ወደ እስራኤል መሪ ቤተመንግስት ሠተት ብሎ የገባው ግን ባገልጋዮቹ ቀሚስ ተከልሎ ሳይሆን የራሳቸውን የመሪውን እጅ ዘና ብሎ ጨብጦ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሆነ? ለመሆኑ ቤተ እስራኤሎች ዛሬ በእስራኤል ውስጥ ያሉበት ሁኔታ ትክክለኛው ስዕል ምን ይመስላል? በሌላ ጽሁፍ እንገናኝ፡፡

Read 9278 times