Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:30

የምድብ 3 ቡድኖች ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የያዘ ሲሆን ከተለያዩ አገራት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናሎችን በመቀላቀልእና ለአቋም መፈተሻ የሚሆኑ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማሳወቅ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያደርገውን ዝግጅት ቀጥሏል፡፡በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ2 ሳምንት በፊት በስዊድን የሚጫወተው የሱፍ ሳላህ እና በጀርመን የሚጫወተው ዴቪድ በሻህ አካትቶ ልምምዱን መስራት ከቀጠለ በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ሶስት ተጨዋቾችን ቀላቅሏል፡፡

እነሱም ከአሜሪካ ፊላዴልፊያ ፉአድ ኢብራሂም እና ለሲያትል ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በመጫወት ላይ የሚገኘው አብዱል ዋሊ አማንና ለጀርመን ሃንኦቨር 96 በመጫወት ላይ የሚገኘው ካሊድ መስፍን ናቸው፡፡ 
ብሔራዊ ቡድኑን ለማጠናከር በተለያዩ አገሮች የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎችን የማሰባሰቡ ተግባር ቢበረታታም አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች እንቅስቃሴው ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ አስተዋፅኦ በነበራቸው የአገር ውስጥ ተጨዋቾች የመመረጥ እድል ላይ ተፅእኖ እንዳይፈጥር ስጋት አላቸው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በደቡብ አፍሪካ ክለቦች እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በመጫወት ከፍተኛ ልምድ ያለው ፍቅሩ ተፈራ ከብሄራዊ ቡድኑ ተሰላፊነት እንዳይዘለል እየተጠየቀ ነው፡፡ ፍቅሩ ተፈራ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ፍሪስቴት ስታርስ ለተባለ ክለብ ዝውውር የፈፀመ ሲሆን ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ለብሔራዊ ቡድኑ ተመረጥኩም አልተመረጥኩም በደቡብ አፍሪካ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረጌ አይቀርም ብሏል፡፡ለብሔራዊ ቡድኑ አቋም መፈተሻ ወሳኝ የሆኑት
የወዳጅነት ጨዋታዎች ስለመገኘታቸው ሰሞኑን ይፋ በተደረጉ መረጃዎች ተስፋ ሰጭ ሆነዋል፡፡
የኒጀር ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተሸፍኖለት ታኅሣሥ 21 በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን ታኅሣሥ 29 በኳታር ዶሃ ላይ ከቱኒዚያ ጋር እንዲጫወት ስምምነት አለ፡፡
በሁለቱ ግጥሚያዎች መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም ቶጐ ወይም ጊኒ ወጭያቸው ተሸፍኖ ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ላደረጉት ተጨዋቾች የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት እንደተወሰነ ታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሽልማቱ እንዲሰጥ የወሰነው ተጨዋቾቹ የተገባላቸው የማበረታቻ ሽልማት ዘግይቷል ብለው በመጠየቃቸው ነው፡፡
የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባደረገው ስብሰባ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከቤኒንና ሱዳን ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ የተካተቱ ተጨዋቾች አገልግሎታቸው እየተሰላ የገንዘብ ሽልማት እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡በዚህም መሠረት ሙሉ ጨዋታ ለተጫወቱ 100ሺ ብር የሚሰጥ ሲሆን ለተቀሩት ተሰልፈው በተጫወቱበት መጥን እየተለካ የገንዘብ ሽልማቱ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከተጨዋቾቹ ጋር ባደረገው ውይይት ሽልማቱ የዘገየው የገንዘብ ችግር በመኖሩ መሆኑን አስታውቆ አሁን ግን ከስፖንሰሮች ከተገኘው ገንዘብ ሽልማቱ እንደሚበረከትላቸው ገልፆላቸዋል፡፡ በተያያዘ ዜና በወርሃዊው የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የምድብ 3 ቡድኖች የደረጃ ለውጦች አሳይተዋል፡፡
በዚሁ ወር በሴካፋ ታስከር ቻሌንጅ ካፕ በተስፋ ቡድን የተሳተፈችውና ምንም የወዳጅነት ጨዋታ ያላደረገችው ኢትዮጵያ ባለፈው ወር ከነበረችበት ደረጃ 8 እርከኖችን በመውረድ 110ኛ ሆናለች፡፡ ቡርኪናፋሶ ያለ ምንም እርከን ለውጥ በዓለም 89ኛ ደረጃ ላይ ስትረጋ ቬንዝዋላን በአሜሪካ 3ለ1 ያሸነፈችው ናይጀሪያ ባለፈው ወር ከነበረችበት ደረጃ 5 እርከኖችን በማሻሻል በዓለም 52ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም ዛምቢያ በበኩሏ በ4 እርከኖችን ደረጃዋን በማሻሻል በዓለም 35ኛ ሆናለች፡፡ በአፍሪካ 5ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ዛምቢያ ስትሆን ናይጀሪያ 10ኛ፣ ቡርኪናፋሶ 21ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ 34ኛ ላይ ተመዝግበዋል፡፡
በትራንስፈርማርኬት ድረገጽ በተገኘ መረጃ የምድብ 3 ቡድኖችን ለማነፃፀር እንደተቻለው በቡድኑ ወጣትነት ኢትዮጵያ ፤ በብሔራዊ ቡድኑ አጠቃላይ የዝውውር ገበያ ተመን ናይጀሪያ እንዲሁም በፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት ቡርኪናፋሶ ቀዳሚ ናቸው፡፡ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ አሃዛዊ መረጃ መሰረት የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን የሚያሰባስባቸው ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው በድምሩ በ52 ሚሊዮን ፓውንድ በመተመን ብልፃ አለው፡፡ 2ኛ ደረጃ የተሠጠው 29 ሚሊዮን ፓውንድ የተተመነው የቡርኪናፋሶ ቡድን ሲሆን ዛምቢያ በ9.5 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም ኢትዮጵያ ደግሞ በ625ሺ ፓውንድ የዋጋ ግምታቸው ተከታታይ ደረጃ ወስደዋል፡፡
በዚሁ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአራት ፕሮፌሽናል በተባሉ ተጨዋቾች ስንት እንደሚያወጣ የተሰላ ሲሆን 225ሺ ፓውንድ እንደሚያወጣ የተገለፀው ጌቱ ተሾመ እና 175ሺ ፓውንድ የተገመተው አንዋር ሲራጅ አሁን የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋች ያልሆኑ ናቸው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚገኙትና 125ሺ እና 100ሺ ፓውንድ እንደየቅደም ተከተላቸው ያወጣሉ የተባሉት ፍቅሩ ተፈራ እና ሳላዲን ሰይድ ናቸው፡፡
ከምድብ 3 ብሄራዊ ቡድኖች በተጨዋቾቹ ስብስብ ወጣትነት ግንባርቀደሙ 20.5 አማካይ ዕድሜ ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ቡድን ሲሆን ናይጀሪያ በ23.20 ፣ ቡርኪናፋሶ በ26.50 ዓመት እንዲሁም ዛምቢያ በ26.90 ዓመት የየቡድናቸው አማካይ ዕድሜ ተከታታይ ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ስብስብ ከ34 በላይ ከአገራቸው ውጭ የሚጫወቱ ልጆችን በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ ያስመዘገበው የቡርኪናፋሶ ቡድን ቀዳሚ ሲሆን ዛምቢያ በ20፣ ናይጀሪያ በ13 እንዲሁም ኢትዮጵያ በ4 ፕሮፌሽናሎች በተከታታይ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

Read 5181 times