Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 December 2012 15:52

የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች የወሊድ መከላከያ እንዲወስዱ ተገደዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከስምንት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለውን ዴፖ ፕሮቬራ የተባለ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለመወጋት ካልተስማሙ ወደ እስራኤል ሊገቡ እንደማይችሉ ይነገራቸው እንደነበር “ቫኩም” የተሰኘው የእስራኤል ትምህርታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሰሞኑን ባሰራጨው ዘገባ ጠቁሟል፡፡ ወደ እስራኤል ከመወሰዳቸው በፊት በኢትዮጵያ ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፕ የቤተሰብ ምጣኔ ዎርክሾፕ ይሰጠን ነበር ያሉት ሴቶቹ፤ የወሊድ መከላከያውን እንዲወስዱ ያግባቧቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ 

ክሊኒኩን ያስተድድር የነበረው “Joint Distribution Committee” እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውንጀላውን አስተባብለውታል፡፡ 
“የወሊድ መከላከያውን አንወስድም ብለን ነበር፡፡ የማትወስዱ ከሆነ ወደ እስራኤል አትሄዱም፤ እርዳታና ህክምናም አታገኙም ተባልን፡፡ ይሄኔ ፈራን፤ ምንም ምርጫ አልነበረንም፡፡ ያለእነሱና ያለእነሱ እርዳታ መውጣት አንችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ክትባቱን ለመወጋት ተስማማን፡፡ በእነሱ ፈቃድ ነው መውጣት የቻልነው” ስትል ሁኔታውን ለቴሌቪዥን የገለፀችው ከስምንት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ተሰድዳ እስራኤል የገባችው እማዋይሽ ናት፡፡
እሷን ጨምሮ 35 ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች፣ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሳሉ በክትባት መልክ የሚሰጠውን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒት እንዲወስዱ እንዴት ያግባቧቸውና ያስፈራሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በእስራኤል በሚኖሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች ዘንድ በአስር ዓመት ውስጥ የወሊድ መጠን 20 በመቶ ገደማ እንደወረደ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ባቀረበው ዘገባ መሰረት፤ ሴቶቹ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ይሰጣቸው የነበረው ዴፖ ፕሮቬራ የወሊድ መቆጣጠርያ እስራኤል ከገቡም በኋላ ቀጥሏል፡፡
ብዙ ልጆች መውለድ በኢትዮጵያም ሆነ በእስራኤል የሚመሩትን ህይወት አስቸጋሪ እንደሚያደርግባቸውና የወሊድ መቆጣጠርያውን ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆኑ ወደ እስራኤል እንዳይገቡ እንደሚታገዱ ይነገራቸው እንደነበር ቤተ እስራኤላውያኑ ገልፀዋል፡፡
“Joint” ለቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በሰጠው ምላሽ፤ የቤተሰብ ምጣኔ ዎርክሾፕ ለስደተኞች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች አንዱ እንደሆነ ጠቁሞ፤ ልጆቻቸውን አራርቀው እንዲወልዱ የሚማሩበት ነው ብሏል፡፡
“ነገር ግን የቤተሰባቸውን መጠን እንዲያሳንሱ ምክር አንሰጥም፡፡
ይሄ የግል ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ግን እንዲያ ማድረግ እንደሚቻል እነግራቸዋለን” ያለው ጆይንት፤ ክትባቱን አንወስድም ካልን ከህክምናና ከኢኮኖሚ እርዳታ እንታገዳለን፣ ወደ እስራኤል እንዳንሄድም እንደረጋለን ያሉት ግን አልባሌ ነገር ነው ብሏል፡፡ “የህክምና ቡድኑ በኢኮኖሚያዊ እርዳታ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አይገባም፤ ዴፖ ፕሮቬራን በተመለከተ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ሴቶች ዘንድ እጅግ የተለመደ የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው” ብሏል - ጆይንት፡፡
የእስራኤል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ዴፖ ፕሮቬራ የተባለውን የወሊድ መቆጣጠርያ እንዲጠቀሙ እንዳልመከረ ወይም ለማበረታታት እንዳልሞከረ ገልፆ፤ ይሄ ክትባት ጥቅም ላይ ውሎ ከሆነ ከእኛ ፖሊሲ ውጭ ነው” ብሏል፡፡

Read 5778 times