Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 13:24

ከ1ሚ.ዶላር በላይ የሚያወጣው ኢትዮጵያዊ ድረገፅ-ድሬቲዩብ!

Written by 
Rate this item
(19 votes)

ወጣት ቢኒያም ነገሱ የድሬቲዩብ ድረገጽ መስራችና ባለቤት ነው፡፡ በድሬዳዋ የተወለደው ቢኒያም፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዚያው ከተማ ክርስቶስ በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አሁን እንጦጦ በሚባለው የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተምሯል፡፡ በአለማያ ዩኒቨርስቲ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በዲግሪ የተመረቀው ቢኒያም፤ በድሬዳዋ ከተማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተባባሪነት ለሦስት ዓመት ሰርቷል፡፡ በሶማሊያ አርጌሣ በሚገኘው አድማስ ዩኒቨርስቲም በኮምፒዩተር ሳይንስ ሶፍትዌር ለአራት ዓመት አስተምሯል፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት ድሬቲዮብ የተባለውን የቪዲዮ ድረገጽ የጀመረው ቢኒያም፤ ድረገፁ ከፍተኛ ቁጥር የላቸው ተከታታዮች እንዳሉት ይናገራል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል ያለው ድሬቲዩብ፤ በቀን ከ150ሺ በላይ ጐብኚዎች ያሉት ሲሆን በኢትዮጵያ ትልቁ የቪዲዮ ድረገጽ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቢኒያም በቅርቡ ሌሎች ሁለት እህትማማች ድረገፆችንም ጀምሯል፡፡ “ጐጆ ሲኒማ” እና “ማይዘፈን” ይባላሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ ከድሬቲዩብ መስራችና ባለቤት ቢኒያም ነገሡ ጋር ያደረገው ቃለምልልስ እንዲህ ተቀናብሮ ቀርቧል፡፡
ከኮምፒውተር ሶፍትዌር እና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር ትውውቅህ መቼና እንዴት ተጀመረ?
በድሬዳዋ እያለሁ በሃይስኩል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተማሪ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ያን ጊዜ በከተማዋ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት በዲያልአፕ እጅግ ቀርፋፋ በሆነ መንገድ የሚሠራ ነበር፡፡ እናም በተማርኩት ትምህርት ብዙ ለመስራት አይቻልም ነበር፡፡ አርጌሳ ከገባሁ በኋላ ግን ነገሮች ተለወጡ፡፡ በሶማሊያ የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጣን ነው፡፡ የሚከፈለው ዋጋም አነስተኛ ነው፡፡ በአርጌሳ በሚገኘው የአድማስ ዩኒቨርስቲ መስራት ከጀመርኩ በኋላ እዚያ የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጣንና ነፃነት የሚሰጥ ስለነበር፣ በተለያዩ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ስራዎች ላይ ጥናት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ የኢትዮጵያን ድረገፆች ሳጠና ያስተዋልኩት ነገር በይዘት ደካማ መሆናቸውን ነበር፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች እና ፊልሞች በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ እኛ ደግሞ ከአገር ወጣ ስላልን በእረፍት ጊዜያችን እንደዚህ አይነት መዝናኛዎችን እንፈልግ ነበር፡፡ እንደልባችን የአገራችንን ሙዚቃ፣ ፊልምና ሌሎች መረጃዎች ለማግኘት ባለመቻላችን በውስጤ ቁጭት ተፈጠረ፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስርጭቱን በሳተላይት አልጀመረም፡፡ እናም ውጫሌ ከምትባል ከተማ እኛ ወደአለንበት አርጌሳ የሙዚቃ ቪድዮዎች እና ጥቂት የፊልም ስራዎች የተቀዱባቸው ሲዲዎች ይመጡ ነበር፡፡ በሌላ በኩል እንደአማራጭ ይዘነው የነበረው ደግሞ በዩቲዩብ ድረገፅ ይጫኑ የነበሩ ጥቂት የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን መከታተል ነበር፡፡ ዩቲዩብ ላይ ከነበሩት የድሮ ሙዚቃዎች መካከል የእነ መሃሙድ አህመድና የእነ አለማየሁ እሸቴ፣ ከቅርብ አርቲስቶችም የቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎች ይገኙበታል፡፡ ግን አቅርቦቱ ብዙ አማራጭን በመስጠት የተሟላ አልነበረም፡፡ በዓለም አቀፍ አገልግሎት ሰጪው ዩቲዩብ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች ማግኘትም ቀላል አልነበረም፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች አንድ መፍትሄ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገነዘብኩ፡፡ ዩቲዩብ በሚሰጠው አገልግሎት ማንም ሰው የራሱን ድረገፅ ዲዛይን አድርጎ የሚፈልጋቸውን መረጃዎች ማሰራጨት የሚችልበት መንገድ አለ፡፡ የሙዚቃ ቪድዮች እና ፊልሞችን ለደንበኞች ፍላጎት በሚያመች መንገድ ለማቅረብ በሚያስችለው የዩቲዩብ አሰራር ላይ ትኩረት አደረግሁ፡፡ ኢምቤዲንግ ይባላል፡፡ ከአንድ ዌብሳይት የሚገኝ መረጃን በራስህ ዌብ ሳይት ለተጠቃሚዎች ማድረስ የምትችልበት አሰራር ነው፡፡ በዚህ መንገድ የኢትዮጵያን ቆየት ያሉ ተወዳጅ የሙዚቃ ቪድዮችን እና ፊልሞችን ራሴ በከፈትኩት ድረገፅ መሰብሰብ ጀመርኩ፡፡ ዕቅዴ በድረገፁ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪዲዮዎችና ሌሎች መረጃዎችን አመቺና አማራጭ ያለው አሰራር በመፍጠር መስራት ነበር፡፡
እናም ድሬቲዩብ የሚል ድረገጽ ጀመርክ…?
አዎ፡፡ ስሙን የመረጥኩት በመጀመርያ ትውልዴ ድሬዳዋ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ዓለምአቀፉን የዩቲዩብ አገልግሎት ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ሳስብ ድሬቲውብ ትክክለኛ ስያሜሆነልኝ፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ድሬ ማለት ትርጉም አለው፡፡
ድሬ ማለት ቦታ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ድሬ ትዩብ በማለት የቪድዮ ቦታዎች የሚለውን የድረገፁን ትክክለኛ አገልግሎት ማመልከት ተቻለ፡፡ ይህ ድረገፄ ስራውን እንደጀመረ ዋንኛዎቹ ስራዎች የኢትዮጵያን የተለያዩ የሙዚቃ ቪድዮዎች እና ፊልሞች በማደን በድረገፁ ማህደር ማሰባሰብ ነበር፡፡
ጎን ጎን በድረገፁ ስለሚገኙ አገልግሎቶች በተለያዩ የኢትዮጵያ ድረገፆች የማስተዋወቅ ተግባራትን አከናውን ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበሩ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ድረገፆችም መካከል አንዳንዶቹ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልኛል፡፡ በማስተዋወቁ ላይ ትኩረት ያደረግነው ሰዎች አንድ ጊዜ ድረገፃችንን ከጐበኙ በኋላ ሌላ ግዜ በፍላጐት ተመልሰው የሚጎበኙበትን እድል ለመፍጠር ነበር፡፡ በድረገፁ የምናቀርባቸውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪድዮች ስብስብ መብዛት እና አማራጮችን በማስፋት ብዙ ተጠቃሚዎች እንዲኖሩን በመፈለግ በርካታ ስራዎችን አከናውነናል፡፡
ድሬ ቲዩብ በጀመርን ጊዜ ከዩቲዩብ እና ከተለያዩ ምንጮች የሰበሰብናቸው ከ36 በላይ የሙዚቃ ቪድዮዎች ነበሩ፡፡ እነሱን በሚያመች መንገድ ከፋፍለን በድረገፁ በማስገባት አቀረብን፡፡ በቀን እስከ 130 ድሬ ቲዩብን የሚጎበኙ ደንበኞች በጥቂት ጊዜ ልናፈራ ችለናል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ በዚያው ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስርጭቱን በሳተላይት በመጀመሩ የሙዚቃ ቪድዮዎችን በብዛት ማሰባሰብ የምንችልበት እድል ተፈጠረ፡፡ በቴሌቭዥን ጣቢያው የሚቀርቡ የሙዚቃ ቪድዮዎችንና የተለያዩ ተወዳጅ ፕሮግራሞችን ለምን አናሰባስብም ብለን ተነሳን፡፡
የኢቴቪን ቪድዮዎች ስትቀዳ እንዴት ነበር….ስምምነት ነበረህ?
በገዛ ፈቃዴ የጀመርኩት ስራ ነው፡፡ ከማንም ጋር አልተነጋገርንም፡፡ ከቴሌቭዥን ጣቢያው በተለይ የሙዚቃ ቪድዮዎችን እሰበስብ ነበር፡፡ ጎን ለጎን ትኩረት የሚስቡ ፕሮግራሞችን ተከታትዬ እየቀዳሁ ማከማቸት ነበረብኝ፡፡ ዋና አለማዬ አነስተኛ አቅርቦት የነበረውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪድዮዎችን ለማስፋት እና በድሬ ቲውብ አገልግሎትም ያለውን አማራጭ ለማብዛት ነበር፡፡ በተለያየ ምክንያት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የቀረቡ የሙዚቃ ቪድዮዎችንና ተወዳጅ ፕሮግራሞችን መመልከት ያልቻሉ ሰዎች በድሬቲዩብ ዕድሉን አገኙ፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪዲዮዎች በተፈለገ ጊዜ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠርንም እያሰብኩ ይህን ተግባሬን ቀጠልኩ፡፡ በወቅቱ አስፈላጊውን ፍቃድ ማግኘት የሚለውን ነገር ማሰብ የማይቻል ነበር፡፡ ከግዜ በኋላ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ፈቃድ ማግኘት ያስፈልግ እንደነበር ግን አምንበት ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚገኙ የምስል ክምችቶችን የምታሰባስቡት እንዴት ነበር?
የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ አንድም በየጊዜው ጣቢያውን በመከታተል አስፈላጊ የምንላቸውን እንቀዳለን፡፡ ካልሆነም ደግሞ ቀኑን ሙሉ የጣቢያውን ፕሮግራሞች በመቅዳት መስራት ነበር፡፡ በየማታው የቀኑን ቅጂ መልሶ በመከለስ አስፈላጊ የቪድዮ ምስሎችና ፕሮግራሞችን ቆራርጦ እና አስተካክሎ የማዘጋጀት ስራ እንሰራ ነበር፡፡ ይሄንን ከአምስት ዓመት በፊት እዚያው አርጌሳ እያስተማርኩ በነበርኩበት ወቅት ሰርቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሃላፊዎች ያለፈቃዳቸው ስሰራ የነበረውን ነገር ሲያውቁ በሰጡት ምላሽ ደስተኞች መሆናቸውንም ተረዳሁ፡፡ ቴሌቭዥን በወቅቱ በድረገፅ የሚያስተላልፈው ስርጭት አልነበረውም፡፡ እኔ የከፈትኩት ድሬቲዩብ ያን ክፍተት በመሙላቱ ያለፈቃድ መስራቴን እንድቀጥል ያመቻቸ መሰለኝ፡፡ ከግዜ በኋላ ግን ከጣቢያው ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር ፈቃድ የማገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ጀመርኩ፡፡ ከቴሌቭዥን የምናገኛቸውን የቪድዮ ምስሎች ማከማቸት እና በድረገፃችን ማሰራጨት ከጀመርን ከሁለት ዓመት በኋላ ነው ፈቃድ የማግኘቱን ነገር በትኩረት የሰራሁበት፡፡ በመጨረሻም ከኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት ጋር በትብብር መስራት የምንችልበትን ውል ተፈራረመን ስራችንን ቀጥለናል፡፡
በድረገጽ የመዝናኛ አገልግሎታችሁን ለመጀመር የገጠማችሁ ፈተና ነበረ?
ዋናው ፈተና የነበረው በነፃ በምንሰጠው የድረገፅ አገልግሎታችን ላይ ተጠቃሚ እየበዛ በሄደ ቁጥር ወጭያችን እየበዛ መምጣቱ ነው፡፡ የድረገፁን ማካሄጃ ዋና ኮምፒውተር ወይም ሰርቨር መከራየት ነበረብኝ፡፡
በአሜሪካ ከሚገኝ ኩባንያ ለስርጭታችን መቀላጠፍ እና አለም አቀፍ ሽፋን ማግኘት የሚያስችል ሳተላይት በኪራይ ማግኘት ያስፈልግ ነበር፡፡ እነዚህን ለማሳካት እንደጀማሪነታችን የክፍያው መወደድ አስጨንቆኝ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት የድረገፁን 90 በመቶ በጀት ራሴው ነበርኩ የምሸፍነው፡፡ ድረገፁ ያን ያህል እውቅና ስላልነበረው የማስታወቂያ ገቢዎችም አልነበሩኝም፡፡ በወቅቱ ግን የድሬ ቲዩብ ተጠቃሚዎች ብዛት በየቀኑ ከ130 ተነስቶ 300 ከዚያም 400 እያለ ሄደ፡፡ የድረገፁ ጐብኝዎች ቁጥር እያደገ መሄድ የውጭ ፈተና ቢኖረውም ለወደፊቱ ስኬተማ ያደርገኛል በሚል ተስፋ ስሰራ ቆየሁ፡፡ አንዳንድ የኢትዮጵያ ድረገፆች ያደረጉልኝ ድጋፍም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እነኢትዮጵያን ሪቪው፤ ኢትዮሚዲያ፤ አይጋ ፎረም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ድረገፆች በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩና ከፍተኛ ጎብኝዎች የነበሯቸው ናቸው፡፡ “የኢትዮጵያን ተወዳጅ የሙዚቃ ቪድዮችና ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራም ከፈለጋችሁ ድሬቲዩብን ጎብኙ” የሚሉ ማስታወቂያዎችን በማውጣት አበረታተውኛል፡፡ ሌላው ፈተና በሲዲ የወጡትን የኢትዮጵያ ፊልሞች በድሬ ቲዩብ ለማቅረብ ስንሞክር ያጋጠመን ነው፡፡ በእኛ አገር በሲዲ የወጡ ፊልሞች አብቅቶላቸዋል የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ ይህን መለወጥ እንደሚገባ ሃሳብ አመጣሁ፡፡ ብዙ ፊልም ሰሪዎች እና ባለቤቶች ፊልሞቻቸው ያለአግባብ እየታየ ነው በሚል ቅሬታ ተፈጠረባቸው፡፡ እናም ይከፈለን የሚል ጥያቄ ያቀርቡ ጀመር፡፡ በዚህ የተነሳም አላስፈላጊ አለመግባባቶች ከሚፈጠሩ ብለን ከሁለት ዓመት በፊት ፈልሞችን በድረገፁ የማቅረብ ስራውን አቋረጥነው፡፡ ይህን የወሰንነው ወደክፍያ አገልግሎት ለመግባት በማሰባችን ነው፡፡ እኛ በድሬቲዩብ የምናጋራቸውን የቪድዮ ምስሎች ለተጠቃሚዎች የምናቀርበው በነፃ ነበር፡፡ በዋናነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀርቡ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዳያስፖራው ተደራሽ የማድረግም ፍላጎት ነበረን፡፡
ድሬ ቲዩብ እንደሌሎች ድረገፆች የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዴት አላተኮረም? ድረገፁ ለምን በመዝናኛ ላይ ማተኮሩን መረጠ?
እኛ ስንጀምር በሰፋ እና በተደራጀ መልኩ በመዝናኛ ዘርፍ የሚሰራ ድረገፅ አልነበረም፡፡በወቅቱ የነበሩ ድረገፆች በአብዛኛው በፖለቲካ ጉዳዮች እና በዜና ላይ አተኩረው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም በድሬቲዩብ የቪድዮ ምስሎችን በተለይም በመዝናኛ ላይ የሚያተኩሩትን አሰባስበን በፈርቀዳጅነት ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ፍላጐት ነበረን፡፡ ምንም እንኳን በገበያ ላይ ያለው ሁኔታ ባያደፋፍርም ወደፊት ገቢ ሊያመጣ ይችላል በሚል ገባሁበት፡፡ የሚገርምህ እኛ መዝናኛ ላይ የሚያተኩር ድረገፅን በጀመረን ማግስት ተመሳሳይ ድረገፆች በብዛት ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ እኛ ፈርቀዳጅ ብንሆንም ተከትለውን በተመሳሳይ ዘርፍ መስራት የጀመሩት ድረገፆች ሃሳባችንን ኮረጁ ብለን አልተጨነቅንም፡፡ ኢንተርኔት በባህርይው የቅጂ ተግባራት የሚከናወኑበት መድረክ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የቪድዮ ድረገጽ በመጀመር ዩቲዩብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቸኛው ነው፡፡ የቪድዮ ምስሎችን ይጭናል፤ ሰዎች ይህን ይመለከታሉ፡፡ ይዝናኑበታል አስተያየት ይሰጡበታል፡፡ እኛም ኢትዮጵያዊውን የቪድዮ ምስሎች ማጋርያ ድረገፅ የፈጠርነው ለዚህ ነው፡፡
ገበያው ሰፊ ነው፡፡ የተለየ አቀራረብ እና ፈጠራ መጠቀም ደግሞ ተመራጭ ያደርጋል፡፡
በአገራችን ያለውን የኢንተርኔት አጠቃቀም ደረጃ እና ባህል እንዴት ትገልፀዋለህ?
መሻሻል አለበት፡፡ በቂ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ ጋር መድረስ የሚገባ ከሆነ፤ እድገት መፋጠን አለበት ከተባለ፤ ኢንተርኔት ለማህበራዊ ህይወት ብቻ ሳይሆን በርካታ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስፈልግ አገልግሎት መሆኑ ከታመነበት የአጠቃቀም ባህሉ እንዲያድግ መጣር ያስፈልጋል፡፡
ኢንተርኔት ትልቅ እውቀት የሚያስፈልገው አገልግሎት አይደለም፡፡ ማንበብና መፃፍ ከቻልክ ብቻ ብዙ አገልግሎት እና ጥቅም ሊሰጥህ ይችላል፡፡ በቅርቡ አንድ የሰማሁት ዜና አለ፡፡ በገጠር አካባቢ ብዙ ያልተማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአይፖድ አጠቃቀምን በአምስት ወር ውስጥ ለምደውታል የሚል ነው፡፡ በኢንተርኔት ፈጣንና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ማዳረስም ማግኘትም ትችላለህ፡፡ የሰው ንቃትም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ እንግዲህ በአገራችን እነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎች ግምት ውስጥ ገብተው አገልግሎቱ እንዲያድግ በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት በኩል በቂ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡
ብዙ ሰዎች ኢንተርኔት ለተማረ ሰው ብቻ እንደሚሆን ስለሚያስቡ አይቀርቡትም፡፡ ከመንግስት አንፃር ደግሞ ኢንተርኔት አገልግሎትን በማፋጠንና በማቀላጠፍ በቂ ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በጣም በተንቀራፈፈ እድገት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ብዙ ያሳጣል፡፡ ወቅታዊ እውቀትና መረጃ የማግኘት እድልን ይገድባል፡፡ በኢትዮጵያ የሚሰሩ ድረገፆች ገበያቸውን በዋናነት በዲያስፖራው ላይ ማተኮራቸውም ለዚህ ነው፡፡
በእርግጥ አሁን ሰዎች ብዙ ጊዜያቸውን በኢንተርኔት ማህበረሰብ ድረገፆች ላይ ስለሚያሳልፉ፣ እኛም የገበያ ስትራቴጂያችንን ከዚሁ ጋር አያይዘን እየሰራን ነው፡፡ በፌስቡክ እና በሌሎች የማህበረሰብ ድረገፆች እየተጠቀምን ያሉንን አዳዲስ ነገሮች እያስተዋወቅን ነው፡፡
በሶሻል ሚዲያዎች አጠቃቀም በጎ ነው ብዬ የምጠቅሰው ነገር አለ፡፡ ሰው ፎቶውን በማቅረብ በግሉም ሆነ ሁሉንም በሚያጋራ ጉዳይ ላይ መወያየቱ ብዙ ባያስተምርም መቀጠል አለበት፡፡ በገሃዱ አለም ያለው ማህበራዊ አኗኗር በኢንተርኔት መደረጉ ብዙ የሚወገዝ አይደለም፡፡
በድረገጽ ቢዝነስ ያለው የገበያ ፉክክር ምን ይመስላል?
በድረገፅ ቢዝነስ “ይዘት ንጉስ ነው” የሚባል ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ድረገፆች ተከፍተው ቶሎ የሚያቋርጡት በርካታ ጎብኝ ለማፍራት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ የማይሳካላቸው አመቺ የማዳረስ እንቅስቃሴ ስሌላቸው እና በዚህም ትኩረት አድርገው ስለማይሰሩ ነው፡፡ ምቹ ባለመሆናቸው፣ ወቅታቸውን የጠበቁ መረጃዎች ስለማያቀርቡ ቶሎ የመፍረስ እጣ ያጋጥማቸዋል፡፡ በቂ ጥናት እና እውቀት ካለመኖርም ጋር ይገናኛል፡፡ ማንኛውም ድረገፅን ለመክፈት የአሰራር ደረጃዎች አሉ፡፡ የመጀመርያው ይዘቱ ለየት ያለና ፈጠራ የታከለበት መሆኑ ነው፡፡ ሌላ በድረገፁ ያሉ ይዘቶችን ወቅቱን በጠበቀ መረጃ አስተካክሎ እና አዘጋጅቶ ለማቅረብ መቻል ነው፡፡
ማንኛውም ድረገፅ አዲስ ነገር መያዙ እና ከሌላ ያልተኮረጀ መሆኑን እንደጉጉል ያሉ የማፈላለጊያ ድረገፆች ይከታተሉታል፡፡ የራሱን ትኩስ፤ አዲስ እና በደንብ የተሰራ መረጃ ያቀረበ ትኩረት ያገኛል፡፡ በእንደ ጉጉል አይነት የማፈላለጊያ ድረገፆች ጐብኚዎች እንዲመለከቱት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቆም ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ድረገፁ መፍረስ አይቀርም፡፡
ድረገፆች ከሌላ ያልተቀዳ ትኩስ መረጂዎችን ስለማቅረባቸው ጉጉል ክትትል የሚያደርገው እንዴት ነው?
ለምሳሌ የኩኩ ሰብስቤ አዲስ ዘፈን ወጣ እንበል፡፡
ይህን ሙዚቃ ድሬቲዩብ ለቀቀ፡፡ በዚያው ቅፅበት ጉግል ድረገፁን ይይዘዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ድረገፆች ተመሳሳይ ዘፈን ቢለቁ ጉጉል ቀዳሚ የሚያደርገው የመጀመርያውን አቅራቢ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ እኛ አገር ያሉ ድረገፆች ወቅቱን የጠበቁ የማይሆኑት አንድም በስንፍና የተነሳ ነው፡፡ በኢንተርኔት አገልግሎቶች መቸገራቸውንም ምክንያት የሚያደርጉ ይኖራሉ፡፡ ግን ከቪድዮ ምስል አቅራቢ ይልቅ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለማቅረብ የሚቀለው በፅሁፍ የሚዘጋጅ ድረገጽ ሲሆን ነው፡፡ በእርግጥ በቪድዮ ምስሎች አቅራቢነት ለሚሰራ ድረገፅ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ያስፈልጋል፡፡ እኔ በምሰራበት ዘርፍ የሚሰራ ብዙ ስለሌለ እኔን በፍጥነት አሳድጎኛል፡፡ እናም እኔ ባለሁበት የኢንተርኔት አገልግሎት ብዙም ተፎካካሪ የለኝም፡፡
የምትጠቀመው ሰርቨር በአሜሪካ የሚገኝ ነው
ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ድረገፆች እኮ ከጅምሩ ይሰሩት የነበረው እና አሁን የሚንቀሳቀሱት በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን አማካኝነት ነው፡፡ ሁሉም ሰርቨሮቻቸውን ከውጭ አገራት ተከራይተው ነው የሚሰሩት፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቨር ለመከራየት ውድ ስለሆነ ይከብዳል፡፡ በተጨማሪም የሰርቨር አገልግሎት ለግለሰብ ፈቃድ የሚሰጥበት አይደለም፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት ለድሬቲዩብ እየተጠቀምንበት ያለው ሰርቨር በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ነው የሚገኘው፡፡ ይሄም በመሆኑ በከፍተኛ አቅም ዳታን ለማሰራጨት እና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት አግዞናል፡፡
በድሬ ቲዩብ “አዲስ ነገር ምን ተከሰተ” በሚል ማተኮር እንፈልጋለን፡፡ በሙዚቃ ስፔሻላይዝ የማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ ምን አዲስ ዜና ክስተት አለ እያልን ምን አዲስ ሙዚቃ ወጣ፤ የተለያዩ የሙዚቃ ኮንሰርቶች እና የመዝናኛ ዝግጅቶች ላይ በተለየ እና ቀዳሚ በሚያደርግ አቅም ልንሰራ እንፈልጋለን፡፡ እየሰራንም ቆይተናል፡፡ በፊልምም ተመሳሳይ ነው፡፡
የቪዲዮ ምስሎችን ከኢቴቪ ውጭ ከየት ነው የምታገኙት? ክፍያስ አለው?
አሁን የቪድዮ ምስሎችን ከራሳቸው ከአርቲስቶች እያገኘን ነው፡፡ እንደ ቴሌቭዥን ጣቢያ አዳዲስ ሙዚቃዎች እና ፊልሞች ሲኖሯቸው ቅድሚያ አምጥተው ይሰጡናል፡፡
የሚከፍሉት ወይም የምንከፍላቸው ነገር የለም፡ በነፃ ነው፡፡ የክፍያ ነገር ብዙ ግራ ሲያጋባን ቆይቷል፡፡ የምናስከፍለው ነገር የለም፡፡ አዲስ ሙዚቃ መውጣቱን ሁሉም ማወቅ አለበት፡፡ ያንን እድል በድረገፃችን እናቀርባለን፡፡ ድሬቲዩብን ልክ እንደቴሌቭዥን ጣቢያ ልትቆጥረው ትችላለህ፡፡ ስራው መረጃን ማካፈል፤ ማሳወቅ እና ማዝናናት ነው - በአጠቃላይ ማስተዋወቅ ልትለው ትችላለህ፡፡
ድረገፃችን አንደኛ ጎብኝዎችን ከአሜሪካ እንዲሁም ተከታዩን ብዛት ከኢትዮጵያ እያገኘ ነው፡፡ እናም ድሬቲዩብ ላይ አዳዲስ ስራቸውን የሚያቀርቡ አርቲስቶች እውቅናቸውን የማስፋትና ተፈላጊነታቸውን የማሳደግ ጥቅም ያገኛሉ፡፡
በየሁለት ቀኑ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ይደርሱናል፡፡ ደረጃቸውን ጠብቀው የተሰሩ ፊልሞች በኦሪጅናል ቅጂ ሲመጡልን እኛ በስታንዳርድ እና ሃይዴፍኔሽን ጥራታቸውን ጨምረን እናቀርባለን፡፡
ሌሎች ምንጮቻችን የሰሩትን ፊልም እና ምስል በድረገፃቸው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ባላቸው ላይ እናተኩራለን፡፡ እነፎክስ ኒውስ፤ሲኤንኤን፤ ቢቢሲ እና ሌሎችም ደጋግመው በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ ፊልሞችን ይሰራሉ፡፡ ያንን ተከታትለን ለደንበኞቻችን በትኩሱ እናጋራለን፡፡ እነዚህ ፊልሞች እንዳያመልጡን የሚያደርጉ አለርቶች አሉን፡፡ አንዳንድ ወኪሎቻችን እየላኩልንም እናገኛለን፡፡
በቅርብ ጊዜ ደግሞ የራሳችንን ፊልሞች እየሰራን ነው፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችና በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የፊልም ዳሰሳዎችን በራሳችን የፊልም ቀረፃ እያዘጋጀን በማቅረብ ላይ ነን፡፡ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፤ ባዛሮች፤ ፌስቲቫሎች እና የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ የሚያሳዩ ዝግጅቶች እየተከታተለን የዜና እና የቪድዮ ምስል ሰርተን እየለቀቅን ነው፡፡ እኛ የምናቀርበው መዝናኛ እና በጎ ነገር ያለው መረጃ ነው፡፡ ጎብኝዎቻችንም ጥራቱንና ብቃቱን የጠበቀ አገልግሎት እንድንሰጣቸው ይጠብቃሉ፡፡
የኢንተርኔት ፍጥነትን በተመለከተስ….
በእኛ አገር የኢንተርኔት ፍጥነት ለተጠቃሚውም ሆነ ለእኛ አገልግሎት ሰጪዎች በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለፊልም ማሳያ የሚያግዙ 3ጂ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫዎች ውድ ናቸው፡፡ በጣም ፍጥነት ባለው 3ጂ ኢንተርኔት ስትገለገል ወጪውን አትችለውም፡፡ የእኛ የኢንተርኔት ሲኒማ ዋና የገበያ መዳረሻዎች ከኢትዮጵያ ውጭ በአሜሪካ፤ በአውሮፓ እና በአውስትራሊያ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ በእነዚህ የዓለማችን ክፍሎች የቪድዮ ማሳያ ድረገፆችን ስትገለገል በወር ቢያንስ 5 ዶላር ድረስ እየከፈልክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ባይኖረውም በዓለማችን በጣም ውድ ዋጋ ካላቸው አገራት የሚፈረጅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍጥነት ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎት ከሚሰጡ 5 አገራት አንዷ ናት፡፡ ግን ዋጋው ከፍተኛ መሆኑ ግን እንደተፈለገው ለተጠቃሚዎችም ሆነ ለአገልግሎት ሰጪዎች የሚያግዝ አልሆነም፡፡
በድረገፅ ሳንሱርና ቅጂ እንዴት ነው?
መንግስት በነደፈው ፖሊሲ ይሰራል፡፡ አገራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ይጥላል ያለውን የኢንተርኔት መረጃ መከልከል ይችላል፡፡ እኛ ግን የምንሰራው በመዝናኛ ላይ ነው፡፡
በጎ ነገርን በማቅረብ ህግ አክብረን ነው የምንሰራው፡፡ከኢሬቴድ ጋር የኮንትራት ውል በመፈፀም ፈቃድ አግኝተን በመስራታችን ተጠቅመናል፡፡ በድሬቲዩብ ከሚገኙ የቪድዮ ምስሎች 70 በመቶውን ያገኘነው ከጣቢያው ነው፡፡ በዚህ ስራችን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በዳያስፖራው ከፍተኛውን ተከታታይ እያፈራ እንደቀጠለ አምናለሁ፡፡ በውጭ አገር የሚኖር ሰው ቲቪ ቁጭ ብሎ ማየት ይቸገራል፡፡ እናም በከፍተኛ ሁኔታ የኛን አገልግሎት እየተጠቀመ ነው፡፡ ከቲቪ የምናገኛቸውን በድረገፃችን ያለአንዳች ስጋት በቀጥታ እናቀርባለን፡፡ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ከራሳቸው ከአርቲስቶች ስለሚቀርብልን ፈቃድ እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ ሙሉ የሙዚቃ አልበም በማውጣት አንሰራም፡፡ ከእኛ ድረገፅ ዳውንሎድ ማድረግ አይቻልም፡፡ በእርግጥ ኢንተርኔት ላይ የወጣ ነገር ኮፒ የመደረግ እድሉ ሰፊ መሆኑን ማንም ያውቃል፡፡ ይህን ህገወጥ ተግባር ጥቂቶች ይፈጽሙታል፡፡ ግን በህገወጥ መንገድ ከድረገፃችን ፊልሞች እየተገለበጡ መሆናቸውን በተለያየ መንገድ ተከታትለን ከደረስንበት፣ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀምን ዝርፊያውን ለማስቆም ጥረት እናደርጋለን፡፡
እንደሚያወጣ ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለድረገፅህ የአገልግሎት ደረጃና የተከታታይ ብዛት ንገረኝ….
እኛ የራሳችን መለኪያ ቢኖረንም የሰራነውን ስራ ለመለካትና ለማነፃፀር የድረገፆቹን መረጃዎች እንመለከታለን፡፡ ልክ ነህ እንዳልከው አሁን ድረገፃችን ለሌላ ሰው ይሸጥ ቢባል ዋጋው ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ድረገፁ በጎብኝ ብዛት በዓለም አቀፍ ደረጃ 25ሺኛ ነው፡፡ እኛን የሚፎካከሩት የኢትዮጵያ ተመሳሳይ ድረገፆች 50ሺኛ አካባቢ ይገኛሉ፡፡ በግል ከሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ድረገፆች ድሬ ቲዩብ በአሜሪካ ባለን ጎብኚ አንደኛ ነው፡፡
ማንም የሚቀናቀነን የለም፡፡ በአሜሪካ ካሉ 600 ቢሊዮን ድረገፆች ደግሞ 9ሺኛ ነን፡፡ አሁን በየቀኑ 150ሺ ሰዎች ድረገፁን እየጐበኙ ነው፡፡ ዋና ተፎካካሪዎቻችን ኢትዮጵያሪቪው እና ኢትዮሚዲያ ከስድስት ወራት በፊት በአሜሪካ ባላቸው ተመልካች ይበልጡን ነበር፡፡ አሁን ግን ድሬ ቲዩብ አንደኛ ሆኗል፡፡ ሁለቱ ዌብሳይቶች በኢትዮጵያ ባላቸው ተከታታይ ብዛትም እኛ እንበልጣቸዋለን፡፡
ምናልባት ድሬ ቲዩብ በኢትዮጵያን ሪቪው እና በኢትዮሚዲያ ሊበለጥ የሚችለው በዓለም አቀፍ የተከታታይ ብዛት ነው፡፡
ከድረ ገፁ የማስታወቂያ ገቢ ታገኛላችሁ?
ከአገር ውስጥ ሳይሆን ከውጭ ኩባንያዎች እናገኛለን፡፡ ከጉግል ጋር ባለን የኮንትራት ስምምነት መሰረት ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር እየሰራን ነው፡፡ ጉጉል ለሚያደርገው ጥቆማ ከምናገኘው ገቢ ኮሚሽን ይወስዳል፡፡
ስለ “ጎጆ ሲኒማ” እና ስለ “ማይዘፈን” ድረገፆች ንገረኝ…
ከሁለት አመት በፊት ፊልሞችን የማቅረብ ስራ አቋርጠን ለተጠቃሚዎች በኢንተርኔት የሲኒማ አገልግሎት ልናቀርብ የምንችልበትን ሃሳብ በመጠንሰስ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ “ጎጆ ሲኒማ” የተባለ ድረገፅ ለመክፈት ወሰንን፡፡ “ጎጆ ሲኒማ” ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የኢንተርኔት ሲኒማ ላይ የሚሰራ ድረገፅ ነው፡፡ በሲኒማ ቤት የኢትዮጵያን ፊልሞች ማየት ያልቻሉ ሁሉ በድረገፁ በክፍያ መልክ የፈለጉትን ፊልም መርጠው መከታተል የሚችሉበት እድል ፈጥረናል፡፡ በዚህ ድረገፅ የሚቀርቡ ፊልሞችን ኢንተርኔት ገብቶ ከፍሎ ማየት ብቻ እንጂ፤ መቅዳት ወይም ማውረድ አይቻልም፡፡ በ “ጎጆሲኒማ” ድረገፅ የምናቀርባቸው ፊልሞች ሶስት አይነት የጥራት ደረጃ አላቸው፡፡ እነዚህን የፊልሞች የጥራት ደረጃዎች ተጠቃሚው እንደሚያገኘው የኢንተርኔት ፍጥነት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት የሌላቸው ደንበኞች ስታንዳርድ ቨርዥን የሚለውን ይጠቀማሉ፡፡ ጥሩ ፍጥነት ያለውን ኢንተርኔት የሚገለገሉ ሃይደፍኔሽን ፊልም እንዲሁም በጣም ጥሩ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ለሚችሉት ፉልኤችዲ ቨርዥን እናቀርብላቸዋለን፡፡በ “ጎጆ ሲኒማ” የሚቀርቡ ፊልሞችን ከማሳየት ባሻገር የተመልካች ብዛትን እየለካን መረጃ እንሰጥ ነበር፡፡ በቂ የመረጃ ፍሰት ባለመኖሩ ብዙ አልገፋንበትም፡፡ “ማይዘፈን” ብለን በከፈትነው ድረገፅ ደግሞ የጀመርናቸው ስራዎች አሉ፡፡ ሙዚቃዎችን በማሳተም እየሰራ ከሚገኘው አዲካ ኮምኒኬሽን ጋር እየተመካከርን ነው፡፡ ሙዚቃዎችን መሸጥ ስንጀምር የገበያውን ሁኔታ መለካት የምንችልበት የአሃዝ መረጃ በማዋቀር ማን ብዙ ሸጠና ሌሎችንም እያሰላን ልናቀርብ እንችላለን፡፡
ፊልሞቹን የምታገኙት እንዴት ነው?
በ “ጎጆ ሲኒማ” የምናቀርበውን ፊልም እንገዛለን፡፡አንድ ፊልም ለሁለት ቀናት በኪራይ እናሳያለን፡፡ ማንኛውም ተመልካች ሁለት ቀን ፊልሙን የመመልከት እድል ይኖረዋል፡፡ ፊልሙን መድገም ካማረህ ሶስት ጊዜ እድል አለህ፡፡ ሀለት ቀኑ ሲያበቃ ሶፍትዌሩ ኤክስፓየር ያደርጋል፡፡ ይህንኑ ሶፍትዌርም እኔ ነኝ የሰራሁት፡፡
ምን አቅደሃል ለወደፊቱ
የኢንተርኔት ሚዲያን በፈርቀዳጅነት እየተቆጣጠርን መሄድ እንፈልጋለን ወደፊት በገዛ የቅጂ መብቴ፣ በራሴ የተሰሩትን የቪድዮ ምስሎች የማቅረብ ፍላጎት አለኝ፡፡
የድሬ ቲዩብ ዜና ከፍተኛ ተከታታይ አለው፡፡ ከዚያ ድራማ፣ ቀጥሎም ሙዚቃ በተመልካች ብዛት ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ ድረገፁ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለአንዳች መታወክ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ነው፡፡
የዘንድሮውን አመት ልዩ የሚያደርገው በራሳችን ፕሮዳክሽን ስራዎች ማቅረብ መጀመራችን ነው፡፡ አሁን በቅርቡ ለአርቲስት አብርሃም አስመላሽ ገቢ ለማሰባሰብ የቻልንበትን ፕሮግራም በድረገፁ አቅርበናል፡፡ ወደፊት ተመሳሳይ ስራዎችን ማከናወን እንቀጥላለን፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዙርያ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን አቅርበናል፡፡
ከዳያስፖራ በቀረበልን ጥያቄ መሰረት ከኢትዮጵያ መንግስት አቶ በረከት ስምኦንን እንዲሁም ከተቃዋሚ ፓርቲ በለንደን የሚገኙትን አቶ ልደቱ አያሌውን አቅርበናል፡፡በድረገፅ በፍጥነት የተጠየቀውን ለማቅረብ መስራት እንቀጥላለን፡፡ በቅርብ ጊዜ የተለያዩ የቀጥታ ሽፋን ስርጭቶችንም ለመስራት እያቀድን ነው፡ ከዚያ የኢንተርኔት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እስከመስራት ድረስ እንጓዛለን፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት እነዚህን ሙሉ ለሙሉ እንጀምራለን፡፡ የረጅም ግዜ እቅዳችን ደግሞ የራሳችንን የቴሌቭዥን ጣቢያ መክፈት ነው፡፡

 

br /

Read 16720 times Last modified on Saturday, 08 December 2012 13:33