Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 13:10

በአፍሪካ ሙስና አልቀነሰም ሶማሊያ በሙስና ተዘፍቃለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በዓለማችን ሙሉ በሙሉ ከሙስና የፀዱ (100%) አገራት እስካሁን ባይገኙም በንፅፅር ግን እጅግ ከሙስና የራቁ መገኘታቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም ሦስት አገራት በአንደኛነት ተቀምጠዋል - ዴንማርክ፣ ፊንላንድ እና ኒው ዚላንድ፡፡ የሚገርማችሁ ግን ዘንድሮ አሜሪካ ከሙስና የራቀች በመሆን 19ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ትራንስፓረንሲ ኮራፕሽን ኢንዴክስ ዘንድሮ በ176 አገራት ላይ ባደረገው ጥናት፤ እጅግ የከፋ ሙስና ከተንሰራፋባቸው አገራት መካከል ሶማሊያ፣ ሰሜን ኮሪያና አፍጋኒስታንን የሚስተካከል አልተገኘም፡፡ በናይጀሪያና ካምቦዲያ ደግሞ ከፍተኛ የባለስልጣናት ሙስና ተንሰራፍቷል ተብሏል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በጉቦና በስልጣን መባለግ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፤ ጥቂት አገራት ብቻ ናቸው መሻሻል ያሳዩት፡፡ በአንዳንድ አገራትማ ተውት! ግማሽ በግማሽ የሚሆነው ህዝብ እንደ ውሃ፣ ትምህርትና ጤና ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንኳን ጉቦ ይከፍላል ይላል - አዲሱ ጥናት፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ቁልፉ መሳሪያ ግልፅነትን ማስፈን ነው የሚለው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፤ ብራዚል የየዕለቱን የመንግስት ወጪ በዝርዝር አትማ ማውጣቷን አድንቋል፡፡ በህዝብ በተመረጡ ሹመኞች የሚፈፀሙ ሙስናዎችን ለማስቆም ጠንከር ያሉ ህጐችን ለመደንገግ እየታተረች እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ 
ቻይና በበኩሏ በሙስና የተወነጀሉት ላይ ከበድ ያለ ቅጣት መጣል የጀመረች ሲሆን የፀረ ሙስና ህጐችንም እያወጣች እንደሆነ ታውቋል፡፡ የሞተር ሳይክል ታክሲ አሽከርካሪው ካምቦዲያዊ ቹም ቫን፤ በአገሩ የሚፈፀመው ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት እንዳስመረረው ይናገራል፡፡ “ፖሊስ አንዳንዴ የተሽከርካሪ አደጋ ሲደርስ ድሆችን ጥፋተኛ (ተጠያቂ) ያደርጋል - ጥፋቱ የሌላም ቢሆን” ብሏል - ቹም ቫን፡፡ ናይጀሪያዊዋ ልብስ ሰፊ ኡኩዲ ናዋ፤ ሙስና የለመዱ ባለስልጣናት መብራት ለማብራት እንኳን ችግር እየፈጠሩብን ነው ትላለች፡፡ “ይሄ ደግሞ በቢዝነሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረብኝ ነው፤ ምክንያቱም ወጪዬን ይጨምረዋል” ያለችው ልብስ ሰፊዋ፤ ለጄኔሬተር ያወጣችውን ወጪ ለማካካስ ደንበኞቿ ላይ ዋጋ ስትጨምር እንደሚናደዱባት ትናገራለች፡፡ አፍጋኒስታን በዓለማችን የከፋ ሙስና ከሚታይባቸው አገራት አንዷ መሆኗን ትራንፓረንሲ ኢንተርናሽናል ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የአሪቱ የንግድ ሚ/ር አንዋር-አል ሃቅ አሃዲ ሲናገሩ፤ “የህዝቡንና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እምነት ማግኘት እንድንችል መንግስት ሙስናን የምንዋጋበት አዲስ ዘዴዎችን መፍጠር አለበት” ብለዋል፡፡ በሙስና ላይ የነበሩ ቅሬታዎችና ምሬቶች የአረብ አብዮት (አመፅ) እንዲቀጣጠል አግዘው ይሆናል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ መንግስታትን ከስልጣን ለመገርሰስ ጉልበት ሆነውም ሊሆን ይችላል፡፡ የአመራር ለውጡ ግን ሙስናን እንዳላጠፋ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በሙስና ዙሪያ መረጃ የሚያሰባስበው በመላው ዓለም ከሚገኙ የንግድ ባለሙያዎች፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኤክስፐርቶች ነው፡፡

Read 4788 times