Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 08 December 2012 11:15

“…አልገድልህምን ምን አመጣው?”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይሄን ታሪክ መቼም ሳትሰሙት አልቀራችሁም…ሁለቱ ሰዎች ይጣላሉ ይመስለኛል፡፡ እናማ…አንደኛው እንደመጠንቀቅ ሲል ሌላኛው ምን ይለዋል መሰላችሁ…“አይዞህ፣ አልገድልህም፡፡” ያኛው ደግሞ ‘ቆቅ ቢጤ’ ስለነበር “አልገድልህምን ምን አመጣው?” ብሎ ጠየቀ!
እናላችሁ…ብዙ ነገር “…ምን አመጣው?” እየሆነብን ተቸግረናል፡፡ስብሰባ ተቀምጣችኋል፡፡ እና ስብሰባው ሲካሄድ ይቆይና ወደ መጨረሻ አካባቢ ሰብሳቢ እንዲሀ ይላል፡፡ “ስብሰባውን በሚገባ ስለተከታተላችሁ አመሰግናለሁ፡፡ አንዳንዶቻችሁ ግን በልባችሁ የስበሰባው ዓላማ ያልተዋጠላችሁ እንዳላችሁ የታወቀ ነው፡፡” እናማ…ጥያቄው ማንም ሰው አፍ አውጥቶ “አልተዋጠልኝም…” “አልተሰለቀጠልኝም…” ምናምን ነገር ባላለበት እንዲሁ ‘ነገር ፍለጋ’ ነው እንጂ “…ያልተዋጠላችሁን ምን አመጣው?” 

እግረ መንገዴን…. የስብሰባ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…‘ቦተሊከኛው’ መድረክ ላይ ሆኖ ‘ይደሰኩራል’፡፡ ታዲያላችሁ… አዳራሹ ውስጥ ካሉት መሀል የሆነ ሰውዬ ቅልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶታል፡፡ እና አጠገቡ የተቀመጠውን ሰው ‘ቦተሊከኛው’ ምን ይለዋል መሰላችሁ…“ወንድም፣ ጎንህ ያለውን ሰው ቀስቅሰው፡፡” ሲለው ያኛው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ያስተኛኸው አንተ…ራስህ ቀስቅሰው፡፡” 
እንዲህ “ራስህ ቀስቅሰው…” የሚባሉ ‘ቦተሊከኞች’ ምን ያህል እንደሚኖሩ ሳስበው የፕሬሚር ሊግ ቲፎዞና የእንቅልፍ አስወሳጅ ቦተሊከኞች’ ቁጥር ተመሳሳይ ይመስለኛል፡፡ ሲመስለኝስ! እንደውም ሰመመን መስጫ ኬሚካል እጥረት ሲፈጠር እንቅልፍ አስወሳጅ ‘ቦተሊከኞች’ እንደ ተንቀሳቀሽ ሰመመን ሰጪ የማያገለግሉትሳ!(“ማን ሲል ነው የሰማሽውን ምን አመጣው?”)
እናላችሁ…የሆነች የድሮ ትምህርት ቤት ‘ክላስሜት’ (የትምህርት ቤት ‘ክላስ’ እንደሆነ ልብ ይባልማ…) ነገር አለቻችሁ፣፡ ታዲያማ…ተጠፋፍታችሁ ትቆዩና ከብዙ ዓመት በኋላ ድንገት ከባሏ ጋር ሆና የሆነ ‘አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤት’ ጉዳይ ልታስፈጽሙ ስትንከራተቱ ትገናኛላችሁ፡፡
(በነገራችን ላይ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንድ ሰሞን “አሥራ አምስት ቀን ይወስድ የነበረውን በአምስት ደቂቃ…” “ሀያ ሦስት ቀን ይወስድ የነበረውን በአሥራ ሦስት ደቂቃ…” ምናምን ይባል የነበረው ነገር…በቃ ተረት ሆኖ ሊቀር ነው! ልክ ነዋ… አንዳንድ ቦታ ጉዳይ ማስፈጸም ማለት እኮ በድሮ ጊዜ ለርስት ክርክር ድሮ ስንቅ እየቋጠሩ አገር ለአገር እየዞሩ ስንቃቸው አልቆ፣ ርስታቸው ተነጥቆ እንደሚቀሩት አይነት ሰዎች ሊሆን ምንም አልቀረው!
የምር እኮ…እዚች ከተማ ውስጥ፣ አይደለም አንዲት ብጣሽ ወረቀት ለማስፈጸም ሦስት ሳምንት ሙሉ በየቀኑ ተመላልስን፣ ለአንድ ቀን ጉዞ እንኳን ለትራንስፖርት የምናወጣው ‘እንደከሰረ አርመን’ በባዶ ሜዳ ያስለፈልፈን ጀምሯል አይደል እንዴ! እንደውም፣ አንዳንድ ቦታ…አለ አይደል…መጉላላት ሲብስባችሁ… “የማትፈጽምልኝ ከሆነ ለበላይ አመለክታለሁ…” ምናምን ሲባል “እስቲ ምን እንደምታመጡ አያለሁ…” የሚል መልስ ለመስጠት ‘የልብ ልብ ያገኙ’ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ…በቃ፣ የምር አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡)
እናላችሁ…ለዚቹ ለዓለም ሕዝብ ቁጥር አንድ ሦስት፣ አራት ያበረከተች ክላስሜታቸሁ ጋር ሰላም ከተባባላችሁ በኋላ ከባሏ ጋር “ሀይ ስኩል አብረን ነበርን…” ምናምን ብላ ታስተዋውቃችኋለች፡፡ ባልም ይተዋወቅና አንድ ሁለት ነገር ከተናገረ በኋላ ምን ይላል መሰላችሁ… “ለመሆኑ ባለትዳር ነህ?” ሲል ይጠይቃል፡፡ የተገናኛችሁት ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ምን ሆኑ ምን ሳያውቅ…አለ አይደለ… ለነገር ካለሆነ “ለመሆኑ ባለትዳር ነህ ማለትን ምን አመጣው?”
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡
ማንኛዋም እንትናዬ ከአሁኑ ሰውዬዋ ጋር ከመገናኘቷ በፊት ያላት ህይወት የራሷ ነው፡፡
(እንደ አንዳንድ የአገራችን ጉዳይ ይህም “ለድርድር የሚቀርብ” አይደለም፡፡) እናላችሁ … “የመጀመሪያ ቦይ ፍሬንድሽ ማን ነበር?” ብሎ የሚጠይቅ ‘የዘመናችን ሰው’ አይገርማችሁም! ወይም “እንትንዬውን ማን እንደወሰደው ካልነገርሽኝ ነገር ትደብቂኛለሽ ማለት ነው!” የሚል ‘የዘመናችን ሰው’ አይገርማችሁም! (ጀሬው…አንዴ ካላመለጡ የይገባኛል ጥያቄ የማይቀርብባቸው ነገሮች እንዳሉ ልብ በልማ!) እንዲህ የሚመሳስሉ አንድ፣ ሁለት ወሬዎች ወዳጆቼ ነግረውኝ…አለ አይደል… ‘‘ክራይ ማይ ቢላቭድ ካንትሪ” ብሎ የሚደሰኩር እንቅልፍ የማያስተኛ ተናጋሪ ሊናፍቀኝ ምንም አልቀረው፡፡
እንዴ…አስቸጋሪ እኮ ነው…ድፍን አገር ዝም ብሎ በ‘ሪቨርስ ጊር’ ቁልቁል ይንደረደራል እንዴ!
የምር…አሁን በተገናኙ በአሥራ ስድስተኛው ዓመታቸው “መጀመሪያ የሳመሽ ወንድ ማነው?” ብሎ መጠየቅን ምን አመጣው! (እሱ ራሱ ‘ሲክስቲን ይርስ’ እንትን ሲል ከርሞ…ተዉት ብቻ፡፡) እግረ መንገዴን…አንዱ ‘መሳም’ የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ (‘ድንቄንም’ ጽንሰ ሀሳብ!) ሲጠቅስ ምን አለ መሰላችሁ…“መሳም ማለት ለወጣት ሴት እምነት፣ ላገባች ሴት ተስፋ፣ ለሽማግሌ ወንድ ደግሞ በጎ አድራጎት ማለት ነው፡፡”
ካነሳነው አይቀር ሌላ ነገር ትዝ አለኝ…ልጅቱ ሰውየዋን ልቡን ለመያዝ የማታደርገው ጥረት አልነበራትም፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ‘ኪስ ሚ ዴድሊ ምናምን’ አይነት ፕሮጀክት ትግበራ ላይ እያሉ ምን ትለዋለች… “የእኔ ፍቅር በህይወቴ የመጀመሪያው የሳምከኝ ወንድ አንተ ነህ…” ትለዋለች፡ እሱ ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ…“ታዲያ በኪሲንግ እንዲህ የተዋጣልሽ የሆንሽው… የመሳም ትምህርት በተልዕኮ ወስደሽ ነው እንዴ?” ጎሽ! እንዲህ ማፋጠጥ ነው እንጂ፡፡ (ወዳጄ… ከዕለታት አንድ ቀን “እኔ ብዙ ስፖርት ስለምሠራ በእሱ ምክንያት ጠፍቶ ነው እንጂ…” ምናምን የተባልከውን ትዝ አለህ! እሱ ነገርም ‘ተልዕኮ’ ምናምን ነበረበት እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…“አልገድልህምን ምን አመጣው?” የሚያስብሉ ነገሮች እየበዙብን ተቸግረናል፡፡ ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዳንዱ ደግሞ አለላችሁ… በሆነ አጋጣሚ ለመጀመሪያ ትተዋወቁና ‘ቃላቶቻችሁን እየጠበቃችሁ’ ስታወሩ ትቆያላችሁ፡፡ ከዛላችሁ… መሀል ላይ ሰውዬ ሆዬ ምን ብሎ ይጠይቃል መሰላችሁ…“ለመሆኑ የየት አገር ሰው ነህ፡፡” ምንም ግንኙነት በሌለው ነገር ውስጥ ድንገት ዘሎ “…ለመሆኑ የየት አገር ሰው ነህን ምን አመጣው?”
ስሙኝማ…እንግዲሀ ጨዋታም አይደል…እንዲሀ አይነት ጥያቄዎች በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ከምታስቡት በላይ ይቀርባሉ፡፡ አንዳንዱ የተወለዳችሁበትን ለማወቅ በተዘዋዋሪ ‘ሊፈትናችሁ’ ይሞክራል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ “የእንትን አገር ሰው ትመስላለህ…” ይላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…ለምሳሌ ስለሌላ ሰው ስታወሩ “እንዴት አይነት ቤት ሠራ መሰለህ?” ምናምን ትባባሉና ከመሀላችሁ አንዱ ምን ይላል መሰላችሁ…“የእንትን አገር ሰው እኮ ነው፣” ይላል፡፡ እናማ…በተለይ ስኬት የሚገለጽበት አንዱ መለኪያ…አለ አይደል… “የእንትን አገር ሰው እኮ ነው፣” በሚለው ሀረግ የሚጠቃለልበት ዘመን ላይ መድረሳችን… ለዲስኩር የሚመመቻቸው ይኖሩ እንደሁ እንጂ ቀሺም ነገር ነው፡፡
ዋናው ነገር ምንም ይሁም ምንም ለነገር ካልሆነ በስተቀር… “ለመሆኑ የየት አገር ሰው ነህ?” ማለትን ምን ያመጣዋል?
ሀሳብ አለን… “ለመሆኑ የየት አገር ሰው ነህ?” ብለው መጠየቅ ስለሚወዱ ሰዎችና ይሄ ጥያቄ ለምን እንደበዛ ጥናት ይካሄድልን፡፡ ልክ ነዋ…ማወቅን የመሰለ ነገር የለማ!
እናላችሁ…አንዱን ሲሉት አንዱ እየተደረበ፣ አንዱ ሲሄድ ሌላው እየመጣ…ብዙ ነገሮች ላይ መኪናው የኋላ ማርሽ ብቻ የተገጠመለት እየሆነ፣ “ኧረ እባካችሁ እንዲህ አይሆንም ማለት ‘ቤተ መቅደስ እንደገባች ውሻ’ እያስቆጠረ…መድረሻችን ሳይሆን መሄጃ መንገዳችንም እንኳን ግራ እያጋባን ነው፡፡
“አልገድልህምን ምን አመጣው?” ከሚያሰኝ ዘመን ያውጣንማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 4355 times

Latest from