Saturday, 01 December 2012 13:26

ዋና ርዕሱን በሞት የተነጠቀው “ልማታዊው” መጣጥፍ

Written by  ጌታሁን ሄራሞ ኬሚካል ኢንጂነር
Rate this item
(1 Vote)

(ደራሲው) የአራት ኪሎ መፍረስ የሚያስከትለው ሰብአዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው የሚል አቋም ቢኖረውም በሌላ አንፃር መፍረስ የለበትም አይልም፡፡ ታዲያ ምን ይሁን ለሚሉትም ፀሐፊው አማራጭ አይሰጥም፡፡”
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በህዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም ዕትሙ፣ የዳዊት ንጉሡ ረታን ጽሁፍ “ጉንጭ አልፋው የዓለማየሁ ገላጋይ ክርክር” በሚል ርዕስ ሥር ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ቀጥሎም በህዳር 8ቀን 2005 ዓ.ም ዕትም ላይ ዳዊት በተለይም የ”አጥቢያ” ልብ ወለድ መጽሐፍን ይዘት በተመለከተ የደረሰው ድምዳሜ ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየት መጠነኛ ሀሳብ መስጠቴ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ዳዊት ንጉሡ በህዳር 15ቀን 2005 ዓ.ም. ዕትም ከአቋሙ ዝንፍ እንደማይል የብዙ ራሶች(ርዕሶች) ባለቤት በሆነው ጽሁፉ ምላሹን አስታውቋል፡፡

በእርግጥ አውቆ የተኛን ሰው መቀስቀስ ድካሙ ብዙ እንደሆነ አልጠፋኝም፡፡ ዳዊት ንጉሡ አሁንም ቢሆን በ”አጥቢያ” መጽሐፍ ውስጥ ፈጽሞ ያልተቀመጠን መደምደሚያ ከራሱ አዕምሮ እየቀዳ የክርክር መድረክ መፍጠርን ሥራዬ ብሎ የያዘው ይመስላል፡፡ 
ደራሲው አለማየሁ የአራት ኪሎ ሰፈር መፍረስ የለበትም የሚል ጽንፈኛ አቋም እንደሌለው በመጀመርያው ጽሁፌ ከመጽሐፉ ገጽ 15 ላይ በመጥቀስ መግለጼ ይታወቃል፡፡አሁንም በከፊል ልድገም መሰለኝ!
“…. (ደራሲው) የአራት ኪሎ መፍረስ የሚያስከትለው ሰብአዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው የሚል አቋም ቢኖረውም በሌላ አንፃር መፍረስ የለበትም አይልም፡፡ ታዲያ ምን ይሁን ለሚሉትም ፀሐፊው አማራጭ አይሰጥም፡፡”
ከዚህ በተቃራኒ ዳዊት ንጉሡ ባለፈው ሳምንት ዕትም ያስቀመጣቸውን አባባሎች እንመልከት፦
ዓለማየሁ ገላጋይ በአጥቢያና በሌሎቹም ፅሁፎቹ የተጎሳቆሉ መንደሮች መፍረስ ተገቢነት የለውም የሚል ዓይነት እሳቤ ያለውን አስተሳሰቡን ለመሞገት ሲነሳ….. ከዚህም በተጨማሪ ፀሐፊው፦
…አሮጌ መንደሮችን የማልማት ሥራን የምንቃወምበት መከራከሪያ ጉንጭ አልፋ ከመሆን እንደማይዘል ዛሬም በአቋሜ ፀንቼ በማስረገጥ እናገራለሁ፡፡ በማለት ለመከራከር ይሞክራል፡፡
ይሁን እንጂ አጥቢያ መጽሐፍ ውስጥ ወጥ የሆነ መደምደሚያ አልተቀመጠም፡፡ ይህ ደግሞ የድህረ ዘመናዊነት እሳቤን የተላበሱ ልብ ወለዶች አጻጻፍ ስልት እንደሆነ ባለፈው ፅሁፌ በሰጠሁት ምላሽ በሰፊው የተብራራ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም የድህረ ዘመናዊነት ልብ ወለዶች ውበት ያለው በእንደዚህ ዓይነት ልስላሴአቸው ውስጥ እንደሆነ ይታመናል፤፤ ዳዊት ምናልባት በእንግሊዘኛ ቃላት ቆጠራ ጊዜውን እንዳያጠፋ እንጂ ዶ/ር ጆኣን ቤንፎርድ “Postmodern Aesthetics and Poetics” በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ ይህንኑ ርዕሰ ጉዳይ በሰፊው አንስተዋል፡፡ በጣም የሚገርመው ዳዊት የዓለማየሁ መጽሐፍ ምድብ ጣቢያዋ ከድህረ ዘመናዊነት ተርታ እንደሆነች መረዳቱን እራሱ በጽሁፉ ውስጥ “የአለማየሁን አጥቢያ መጽሐፍ የድህረ ዘመናዊነት እሳቤ አለመረዳቴን መናገራቸውን አልጠላሁትም” በማለት አረጋግጧል፡፡
ይህ እኮ የኔ ጽሑፍ ማዕከላዊ ተልዕኮው ነበር፡፡ እንግዲህ “አጥቢያ” በድህረ ዘመናዊነት እሳቤ ውስጥ የተቀነበበች መጽሐፍ መሆኗን ከተረዳን፣ ሂሱንም መስጠት የሚገባን በዚያው እሳቤ መለኪያ ሊሆን ግድ ይላል፡፤ ስለዚህ ዳዊት የክርክሩን መቋጫ በተመለከተ እራሱ ፍንጩን ካስጨበጠን በኋላ፣ ለምን እንደገና ያረጀ መሣርያውን አንግቦ እንደ አዲስ ለክርክር ራሱን እንዳዘጋጀ ሊገባኝ አልቻለም….ይህ የዳዊት ስልታዊ ማፈግፈግ በአሜሪካኖቹ የነፃ ትግል ወቅት አንዳንድ ተጋጣሚያን ሙሉ በሙሉ የተሸነፉ እስከሚመስሉ ሰመመን ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ አዘናግተው ድንገተኛ ጥቃትን ለመክፈት ከሚያደርጉት ጥረት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡
ሌላው የሚገርመው ዳዊት “አጥቢያ” መጽሐፍ የድህረ ዘመናዊነትን እሳቤ እንደምታራምድ መረዳቱን ካበሰረን በኋላ፣ የእርሱ ጽሁፍ ስለ ኑሮ ስለሚያወራ የሂስ መመዘኛን ማሟላት እንደሌለበት ይነግረናል፡፡ ለመሆኑ ስለ ኑሮ የሚያወሩ ጽሁፎች ከሂስ ነፃ ናቸው ያለው ማነው? ዳዊት እንደዚያ ይበል እንጂ በመጀመሪያ ጽሁፉ የ”አጥቢያ” መጽሐፍ ክርክር “ጉንጭ አልፋ” ነው በማለት ገምግሞ ነበር፡፡ ግምገማን ማከናወን (Evaluation) ደግሞ ባለፈው ከጠቀስኳቸው ስድስት የሂስ አላባዎች ውስጥ ስድስተኛውና የመጨረሻው ነው፡፡ ችግሩ “አጥቢያ”ን በተመለከተ የዳዊት ብያኔ በትክክለኛው አመክንዮ ላይ አለመመስረቱ ነው፡፡ ዳዊት ልክ ባልሆነ አካሄድ የሌሎች ደራሲዎችን ሥራ “ጉንጭ አልፋ” እስከማለት እያሄሰ፣ የራሱ ጽሁፍ ግን ከሂስ ነፃ እንዲሆንለት የሚማፀን ይመስላል፡፡ በእኔ እምነት ዳዊት ወደማያውቀው ሰፈር ገብቶ መውጫ ቀዳዳው የጠፋበት ይመስላል፡፡
ይሁንና የኔም ሆነ የዳዊት ጽሁፍ እየተስተናገደ ያለው በጥበብ አምድ ላይ ነው፡፡ ይህ የ”ጥበብ” ዓምድ ብስለትንና ጥልቀትን የተጎናጻፉ ጽሁፎችን የሚያስሱ የራሱ ታዳሚያን እንዳሉት ግልጽ ነው፡፡ የጥበብ ሰዎች ደግሞ ልክ እንደ ሕፃናት ምግብ ጣጣውን ጨርሶ ሳይታኘክና ሳይብላላ የሚዋጥ (prefabricated) ምግብ ምርጫቸው አይመስለኝም፡፡ ከሁለቱም ሳምንታት ጽሁፎቹ እንደተረዳሁት ዳዊት ንጉሡ ረታ በልብ ወለድ ድርሰቶች ይዘት ውስጥ እንኳን ሳይቀር ጽንፍ የያዙ “Ready-made” ማጠቃለያዎችን ማሰስ የሚቀናው መስሎ ይታየኛል፡፡ ከዚህም የተነሳ ዳዊት በ”አጥቢያ” መጽሐፍ ውስጥ ደራሲው “አራት ኪሎ ሰፈር መፍረስ አለበት!” የሚል “ልማታዊ መፈክር” ባለማሰማቱ አሁንም ቢሆን የተከፋ ይመስላል፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ የዳዊት ጽሁፍ ዕጣ ፋንታው ከልማታዊ ጋዜጠኝነት ጎራ የሚመደብ ነው፡፡ ይህ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ጠረን ያለው ጽሁፍ ደግሞ መስተናገድ ያለበት በአዲስ አድማስ የጥበብ አምድ ላይ ሳይሆን ምናልባት ወደ ፊት ከተፈጠረ “በልማት” አምድ ላይ ነው፡፡
ግን ግን የከተማውን ከዚያም አልፎ የሀገሩን ልማት የማይፈልግ ማነው? ይህ ሀሳብ እኮ ለክርክር መቅረብ የሌለበት ተራ ጉዳይ መሰለኝ! መግባባት ያለብን መሠረታዊ ጉዳይ ያለው የልማትን ሰፊ ትርጉም ከመገንዘቡ ላይ ነው ፡፡ ልማት ስንል አንድን ሰፈር አፍርሶ በምትኩ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን መገንባት ብቻ አይመስለኝም፡፡ አዳዲስ መንገዶችንም ቀይሶ መስራት ብቻም አይደለም፡፡ የተሟላ የልማት እንቅስቃሴ ከቁሳዊ ነገር ባለፈ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና መንፈሳዊውን ብልፅግና የሚያጠቃልል ነው፡፡ ለምሳሌ ዳዊት አዲስ አበባ መንግስት የሌላት እስኪመስል ነዋሪዎቿ በመልካም አስተዳደር እጥረት እየተናጡ እንደሆኑ ፣ ዲሞክራሲና የፕሬስ ነጻነትም ዓይናችን ፊት እየሟሟ በመጥፋት ሂደት ውስጥ እንደሆኑ ጥቆማ ሰጥቶናል፡፡ ከዚህም ባለፈ መሪዎችም ለህዝቡ መልካም አርአያ ከመሆን ይልቅ በሆነው ባልሆነው ዜጎችን እያሰሩ መክሰስን፣ ማሳቀቅንና ማሸማቀቅን እንደመረጡ አስገንዝቦናል፡፡ ይህ የዳዊት ረታ ብሶት የሚያመለክተው መንግስት እያደረገ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ቁስ-ተኮር ብቻ እንደሆነና ዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ገና መቋደስ እንዳልጀመሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ከቅኝ ግዛት ታሪኩ ጀምሮ ነፃነቱን በዳቦ እንደማይለውጥ ያስመሰከረ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ አንዳንድ ደራሲዎች ሚዛናዊ ምናባቸውን ተጠቅመው ጽንፍ ባለመያዛቸው ዳዊት ያን ያህል ባይከፋ መልካም ነበር፡፡
ሌላው ጉዳይ ዳዊት የኔ መጣጥፎች እየተጻፉ ያሉት ከመደበኛው ሙያዬ ጎን ለጎን እንደሆነ ከተናገረው ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከዋና ሙያው ጎን ለጎን ሽርፍራፊ ጊዜዎቹን እየተጠቀመ የሚጽፍ ሰው ደግሞ ለሥነጽሁፍ ሙያ ቅርበት ካለው ሰው መማር ያለበት ብዙ ቁም ነገር እንዳለ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለምሳሌ የህዳር 15ቱ የዳዊት መጣጥፍ ርዕሱ “የክሱ ቻርጅ ተተርጉሞ በአማርኛ ይቅረብልኝ” የሚል ነው፡፡ (“ቻርጅ” አማርኛ ይሁን እንግሊዘኛ አልገባኝም) ይህን ርዕስ እንደተመለከትኩ ፀሐፊው በምንጭ አጠቃቃስ ፤ በትርጉም ስህተትና በሌሎች ቅርፅ ነክ ጉዳዮች ተንተርሶ የሚተቸኝ መስሎኝ ከሂሱ ለመማር ራሴን አዘጋጅቼ ነበር፡፡ የጠበቅሁትና ተስፋ ያደረኩት ቁም ነገር የውኃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ግን ማዘኔ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ዳዊት አብዛኛውን ሰዓቱን በእንግሊዘኛ ቃላት ቆጠራ ያጠፋ ይመስላል፡፡ የጥበብ አምድ ታዳሚ ግን ቃላትን ከመቁጠር ባለፈ ሀሳብንም ለመቁጠር ጊዜውን መስዋዕት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የዳዊት የቃላት ቆጠራ ልክ መሆኑን ለማረጋገጥ የማጣሪያ ቆጠራውን እንድታካሄድ የቤት ሥራውን የሰጠሁት ለሰባት ዓመት ልጄ ነበር፡፡
ጥያቄው ከአቅሟ በታች በመሆኑ ትንሽ ብታንገራግርም፣ የማታ ማታ እኔን አባቷን ላለማስከፋት ብቻ ስትል ቆጥራ ዳዊት ያለው ትክክል መሆኑን በመግለጽ የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች …..በጽሁፌ ውስጥ 130 የእንግሊዝኛ ቃላት ተጠቅሜአለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ያደረኩበት ምክንያቶች አሉኝ፦ የመጀመሪያው በሂስ ዙሪያ በምርምር ላይ የተደገፈ አንድም የአማርኛ መጽሐፍ ባለመኖሩ የባህር ማዶዎቹን መጠቀም ግድ ሆኖብኛል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ለተጠቀምኳቸው የእንግሊዘኛ ሀሳቦች ሁሉ አቅሜ በፈቀደ መጠን የተጨመቀ ትርጉም ለማስቀመጥ ሞክሬአለሁ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ለሁሉም አባባሎች ምንጭ ጠቅሼአለሁ፡፡
ይህን ማድረጌ የጥበብ አምድ ተጋባዦች የበለጠ ምርምር እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ብዬ በማሰብም ጭምር ነው፡፡ በእኔ ዕይታ “የክሱ ቻርጅ ተተርጉሞ በአማርኛ ይቅረብልኝ” የሚለው ርዕስ በራሱ ለዋና ርዕስነት የሚበቃ አይደለም፡፡ ለዚህም ዳዊት እራሱ በመግቢያው ላይ ያለውን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ዳዊት የጽሁፉን መግቢያ የዘጋው እንዲህ በማለት ነበር፦ “የተከሰስኩበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ጠንቅቄ እረዳው ዘንድ የክሱ ቻርጅ ሙሉ በሙሉ በአማርኛ ተተርጉሞ እንዲቀርብልኝ አቤት እላለሁ” ካለ በኋላ “በመቀጠል ወደ ፍሬ ነገሩ ልመለስ” ይለናል፡፡
የት ይደርሳል የተባለው ጥጃ ሉካንዳ ቤት ተገኘ እንዲሉ አንባቢውን እስከ ጽሁፉ መጨረሻ ይዞ ይዘልቃል የተባለው ርዕስ ገና ከጅምሩ የፍሬ ነገሩ አካል እንዳልሆነ ሲነገረን ምን ማለት ይቻላል? ታዲያ የመጣጥፉን ፍሬ ነገር የማይገልጥ ርዕስ በየትኛው መስፈርት ዋና ርዕስ ሊሆን በቃ? ያም ሆነ ይህ በመጣጥፉ ዋና ርዕስ ላይ የ”ግድያ ወንጀል” ቢፈጸምም ውስጡ ሲፈተሽ መጣጥፉ የብዙ ራሶች (ርዕሶች) ባለጠጋና ውል-አልባ ነው፡፡በመጨረሻም ዳዊት ለመጀመሪያ ጽሁፉ በሰጠሁት ምላሽ ውስጥ ስለ ሂስ ሰፊ ትንተናና ማብራሪያ በመስጠቴ ደስተኛ እንዳልሆነ ደጋግሞ አንስቶአል፡፡ ምናልባት በሂደቱ አይጥን በመድፍ እንደመግደል ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅሜ (use of excessive force) እንደሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ግን አሁንም አምዱ የጥበብ እንደመሆኑ መጠን ፅሁፌም እንደዚያው መሆኑን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡
ምናልባትም በህዳር 15ቱ ጽሁፍ ዳዊት “እኔን ምስኪኑን ተከራካሪ እከስሳለሁ በማለታቸው..” የሚል ዓይነት ስሞታ እንዳቀረበ ሁሉ አሁንም ምሳሌዬን በቀጥታ ከአይጥ ጋር አገናኝቶ “እኔን ምስኪኑን ምንትስ ምንትስ…” እንዳይል አደራ እላለሁ!

 

ይህ እኮ የኔ ጽሑፍ ማዕከላዊ ተልዕኮው ነበር፡፡ እንግዲህ “አጥቢያ” በድህረ ዘመናዊነት እሳቤ ውስጥ የተቀነበበች መጽሐፍ መሆኗን ከተረዳን፣ ሂሱንም መስጠት የሚገባን በዚያው እሳቤ መለኪያ ሊሆን ግድ ይላል፡፤ ስለዚህ ዳዊት የክርክሩን መቋጫ በተመለከተ እራሱ ፍንጩን ካስጨበጠን በኋላ፣ ለምን እንደገና ያረጀ መሣርያውን አንግቦ እንደ አዲስ ለክርክር ራሱን እንዳዘጋጀ ሊገባኝ አልቻለም….ይህ የዳዊት ስልታዊ ማፈግፈግ በአሜሪካኖቹ የነፃ ትግል ወቅት አንዳንድ ተጋጣሚያን ሙሉ በሙሉ የተሸነፉ እስከሚመስሉ ሰመመን ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ አዘናግተው ድንገተኛ ጥቃትን ለመክፈት ከሚያደርጉት ጥረት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡

Read 15601 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 13:41