Saturday, 10 September 2011 11:45

ሐረር አሁንም ውሃ እንደተጠማች ነው

Written by  ጽዮን ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ዐፄ  ምኒልክ የመጀመሪያውን የስልክ ጥሪ የደወሉት ወደዚች ከተማ ነው፡፡ የመጀ መሪያው ባንክ የተቋቋመውም በዚች ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያው    የቴምብር ፖስታ የተላከውም ወደዚች ከተማ ነው፡፡የመጀመሪያው ማተሚያ ቤት    የተቋቋመው በዚች ታሪካዋበዚች ታሪካዊ ከተማ ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዙሪያዋ በግንብ የታጠረላት ብቸኛ ከተማም ነበረች፡፡ ከተማዋ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነችባቸውን ክዋኔዎች በሙሉ መዘርዘር የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ ይሁንና በአጠቃላይ ከተማዋ ካላት የዘመን ቅድምና እና ታሪካዊነት የተነሳ በዩኔስኮ ስምንተኛ ቅርስ ሆና ተመዝግባለች፡፡   
ሐረር እና ውኃ

ሐረር በሥልጣኔ የቀዳሚነት ታሪክ ያላት ጥንታዊ ከተማ እንደመሆኗ ከ100 ዓመት በፊት E የቧንቧ ውሃ በማስገባት ከአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ቀጥላ ሁለተኛዋ ከተማ ነች፡፡ ይህች የበርካታ ዘመናዊ ነገሮች ጀማሪ የነበረችው ታሪካዊ ከተማ፤ ከሁሉም ተሽቀዳድማ ለነዋሪዎቿ ያጠጣችውን ንፁሕ ውኃ ከዓመታት በኋላ ነፍጋዋለች፡፡ በጥም የተቃጠሉት ነዋሪዎቿም ሰሚ ፍለጋ  ..ሐረር ትጣራለች.. ማለት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ከተማዋ ግን በቅጡ የሰማቻቸው አትመስልም፡፡
የማያልፍላት ..ቀላድ ዐምባ..
ሥፍራዋ ሰፋፊ የመሬት ይዞታ የነበራቸው ባላባቶች መኖሪያ ስለነበረች ነው ይባላል ..ቀላድ አንባ.. የተባለችው፡፡ ከሐረር ከተማ መንደሮች አንዷ ናት፡፡ ባላባቶቹ ሀብታቸው መሬቱ ብቻ አልነበረም፡፡ ተጠጋግተው የተሠሩት በርካታ ቤቶች የሰፋፊ ግቢዎቹ አካላት ናቸው፡፡ በቀድሞው ዘመን ትርፍ ቤቶች ተወርሰው ለቤት አልባዎች  ሲሰጥ፣ ሰዎች በአንድ ግቢ ተጠቃለው መኖር ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ ከጊዜ ብዛት በዕንጨትም ቢሆን የራሳቸውን ቅጽር እያጠሩ፣ ይዞታቸውን ለማጠናከር (ለመከለል) ሞክረዋል፡፡ ይህ ያልተሳካላቸው ደግሞ በጣም ከመቀራረባቸው የተነሳ ስያሜያቸው ..ክብሪት አምባ.. እስኪባል እርስ በርስ ሲጯጯሁ ይውሉ እንደነበር ይነገራል፡፡ አሁን  የኑሮን ሸክም ለማቃለል ሲዳክሩ ስለሚውሉ ጠቡም ትዝ የሚላቸው አይመስሉም፤ ሰፈሩም ጥ ብሏል፡፡
..ቀላድ ዐምባ.. ትገርመኛለች፡፡ ከዓመት ዓመት እንደሰው ትከሳለች፡፡ ቤቶቹ በነዋሪዎቹ እድሳት ስለማይደረግላቸው እርጅናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጨምራል፡፡ ዱሮ ሰፊ ይመስሉ የነበሩት እየጠበቡ ሄደዋል፤ አንዳንዶቹም ተወላግደዋል፤ ሌሎቹም በተገኘው ነገር የተጠጋገኑ እና የተወታተፉ ናቸው፡፡  
በዚህ መንደር ለዓመታት ምንም ዐይነት ግንባታ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ሰፈሩን ለኑሮ የሚመርጠው ስለሌለ ቤት ተሸጦም ተለውጦም የሚያውቅ አይመስልም፡፡  በቅርቡ የቀበሌው መስተዳድር ጽ/ቤት በመንደሯ መግቢያ ላይ ያስገነባት ባለ አንድ ፎቅ ጽ/ቤት የሰው ዐይን ስለበዛባት፣ ..እየከሳች እና ቁመቷ እየቀነሰ ነው.. እያሉ ይሳለቁበታል፡፡
..ብርቅነሽ፤ ሉሲ፤ አንድ ለእናቱ፤ አስቤሽ አላውቅ.. የማይሏት ነገር የለም፡፡ ባረጁት መንደሮች መካከል የቆመችው ሕንፃም በፈንታዋ ቀብረር ብላ የምታያቸው ትመስላለች፡፡
የመንደሯ ገመና እንዲህ በቀላሉ ተተንትኖ የሚያልቅ እንዳይመስላችሁ፡፡ ለሌሎች አካባቢዎች ውበት የሰጠው ኮብልስቶን እንኳን ቀላድ ዐምባ ሲገባ ተወላግዶ ነው፡፡ ቀላድ አምባ የሚያስቅ፣ የሚያሳዝን፣ የሚያስገርም ገጽታ አላት፡፡ ለወዳደቁ እና ተመልካች ላጡ የሌሎች ከተሞች መንደሮች ምሳሌ ትሆናለች፡፡
ከሣምንት በፊት ወደዚች መንደር ሄጄ ነበር፡፡ መቼም የቀላድአምባ ሰዎች ቤት ባፈራው ነገር መስተንግዶውን ይችሉበታልና ዘመዶቼ ሽር ጉድ ብለው በአቅማቸው ያዘጋጁትን ማዕድ ጋበዙኝ፡፡ ለመመገብ ተሰናድቼ በቀረበልኝ ውሃ ለመታጠብ ጣቴን ዘረጋሁ፤  ውሃው ወደ ጣቴ መንቆርቆር በጀመረበት ፍጥነት መልሼ እጄን ሰበሰብኩ፡፡ ማስታጠቢያውን  ከፊቴ ይዛ የቆመችውን ልጅም፣ ..ምነው በቆሻሻ ውሃ ነው እንዴ የምታስታጥቢኝ.. ስል ቆጣ ብዬ ጠየቅኋት፡፡ ልጅቱ ግራ ተጋብታ አሰሪዎቿን እያየች ተቁለጨለጨች፤ ..ለማስታጠብ ነው ለማቆሸሽ?.. ቆሻሻው ውሃ የፈሰሰበትን እጄን ሸተት እያደረግሁ ጠየቅሁ፡፡ እነርሱ ምንም አልመሰላቸው፤ ..ቆሻሻ እኮ አይደለም፤ የቧንቧ ውሃ ነው፤.. አሉኝ፡፡ ማንኛችን ትክክል እንደሆንን ለማረጋገጥ ውሃውን ከልጅቱ ተቀብዬ እንደገና መልሼ አየሁት፡፡ ውኃው ከመቆሸሹ የተነሣ ይዘቱ ሌላ ስያሜ የሚያሰጠው ነው፡፡ ..አሁን እንደውም ተሽሎት ነው እንጂ ዱሮ ይሄን ጠጥተን ጥርሳችን ላይ የሚጋገረውን በስቴኪኒ ነበር የምናወጣው፡፡ ስጋ በልተን ሳይሆን ውሃ ጠጥተን ስቴኪኒ እንይዝ ነበር፤.. አሉኝ፡፡ ውሃው ከሐረሩ ቀይ አፈር ጋር ተደባልቆ የተበጠበጠ ይመስላል፡፡ ለእነርሱ ግን ቆሻሻ አይደለም፤ ከቧንቧ እንደቀዱት ውሃ ያህል ንፁሕ ነው፡፡  
ሐረር ከተማ የከርሰ ምድር ውሃ ስለሌላት ፊቱንም ቢሆን ውሃ የምታገኘው ከሐረማያ ሐይቅ ነበር፡፡ በ1990 ዓ.ም አካባቢ ውሃውን ከሐይቁ ስቦ ለከተማው ነዋሪ ለማዳረስ የሚያገለግለው ማከፋፈያ መሥመር የጥራት ጉድለት ስላጋጠመው ውሃ የሚለቀቀው በፈረቃ ነበር፡፡
በ1996 ዓ.ም የሐረማያ ሐይቅ ሙሉ በሙሉ በመድረቁ ከተማዋም በውሃ ድርቅ ተመታች፡፡ በወቅቱም ሐረር ይሄ ነው የማይባል የውሃ ችግር ገጠማት፡፡ የክልሉ መንግሥት ..አጣዳፊ የውሃ ፕሮጀክት.. በሚል አምስት፤ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ደግሞ ሁለት በአጠቃላይ ሰባት የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው ጥራቱን የጠበቀ ውሃ መስጠት ተጀመረ፡፡ ውሃው ጥራት ይኑረው እንጂ መጠኑ በጣም አነስተኛ በመሆኑ የከተማዋ የውሃ ችግር ተባባሰ፡፡
..ኧረ የሰው ያለህ፤ ሐረር ትጣራለች´
CG„ እየተባባሰ ሄዶ የከተማዋንና የነዋሪዎቿ የመኖር ህልውና መፈታተን ጀመረ፡፡ የከተማዋ ቧንቧዎች ሙሉ ለሙሉ ደረቁ፡፡ ችግሩ እየከፋ ሲሄድ ..ኧረ የሰው ያለህ፤ ሐረር ትጣራለች.. በሚል የቅስቀሳ ፕሮጀክት የድረሱልን ጥሪ ማሰማት ተጀመረ፡፡  ሐረር ምንም ዐይነት የከርሰ ምድር ውሃ ስለሌላት ከድሬዳዋ ከተማ ውሃ ለመውሰድ የሚያስችል ጥናት ተካሄደ፡፡ የሁኔታውን አሳሳቢነት ዘግይቶም ቢሆን የተገነዘበው የፌደራል መንግሥት፤ በውሃ ሀብት ሚኒስቴር በኩል እጁን አስገባ፡፡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ 227 ሚሊዮን ብር በ40 ዓመት በሚጠናቀቅ ክፍያ ብድር ተወስዶ፣ 67 ሚሊዮን ብር የክልሉ መንግስት፣ 45 ሚሊዮን ብር ከውሃ ልማት ፈንድ ፣ ፕሮጀክቱ ከተጀመረም በኋላ 5.5 ሚልዮን ዩሮ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በብድር፣ በአጠቃላይ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ መሠራት ተጀመረ፡፡
ፕሮጀክቱ የት ደረሰ?
የዚህን ፕሮጀክት የሲቪል ሥራ በ20 ወራት አጠናቆ ለማስረከብ ተፈራርሞ ፕሮጀክቱን  የወሰደው የቻይና ድልድይ እና መንገድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ነው፤ ሥራውም የ71 ኪሎ ሜትር ዋና ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ፣ አራት የውሃ መግፊያ ጣቢያዎች፣ ወደ 20 የሚጠጉ የውሃ ማጣሪያ ቢርካዎችን ለመሥራት ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በ20 ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት፣ ከ80 ወራት በላይ ቢያስቆጥርም እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሥራ አልጀመረም፡፡
የቻይናው ድርጅት የጠየቃቸው የግንባታ ግብአቶች መወደድ፣ መሥመሩ በሚያልፍባቸው አነስተኛ የገጠር ቀበሌዎች የሚከፈሉ የካሳ ክፍያ እና የመሳሰሉት ጥቃቅን ችግሮች ለፕሮጀክቱ መዘግየት  እንደምክንያት ቀርቧል፤ ነገር ግን ለመረጃው ቅርብ የሆነ ወዳጄ ለፕሮጀክቱ መዘግየት አንዱንም ምክንያት በምክንያትነት ለመቀበል እንደሚቸግረው ይገልጻል፡፡ ፕሮጀክቱ በታቀደበት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ያልተጠናቀቀው፤ በኮንትራክተሩ የአቅም ችግር እና የተገዙት ዕቃዎች ጥራት ጉድለት እንደሆነ አጫውቶኛል፡፡
የፕሮጀክቱን ሁለተኛ ምዕራፍ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ ለመሥራት ጨረታ ያሸነፈው ..ቴክኖፋብ.. የተባለ የሕንድ ኩባንያ ነው፡፡ እርሱም በ300 ቀናት ሠርቶ ለማጠናቀቅ ተፈራርሞ የወሰደውን ፕሮጀክት ሳያጠናቅቅ 1700 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡
ይኸው ለፕሮጀክቱ ቅርበት ያለው ወዳጄ እንደነገረኝ፣ በፕሮጀክቱ ዲዛይን መሠረት ውሃውን ከድሬዳዋ ዳገት ገፍተው ወደ ሐረር የሚያመጡ እያንዳንዳቸው አራት ፓምፖች የተጣመሩበት አራት ጣቢያዎች ተሠርተዋል፡፡
በዲዛይኑ እና በዕቅዱ መሠረት በአንዱ ጣቢያ ከሚገኙት አራቱ ፓምፖች ሦስቱ እያንዳንዳቸው በጋራ በሰከንድ 300 ሊትር ውሃ መግፋት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ተጠናቀቀ ተብሎ የሙከራ ሥርጭት በሚጀመርበት ወቅት ግን ከእነዚህ አራት ፖምፖች በአንድ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችለው አንዱ ብቻ ሆነ፡፡ በአንድ ጊዜ በየጣቢያዎቹ ካሉት ሦስት ፖምፖች ሁለቱ ፖምፖች አገልግሎት መስጠት ሲገባቸው ይህ አልተሳካም፡፡ በየስምንት ሰዓት ዕረፍት በአንድ ፓምፕ ብቻ ተራ በተራ ከመሥራት በስተቀር በዲዛይኑ መሠረት አገልግሎቱን ሊሰጡ አልቻሉም፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሚያዚያ  2003 ዓ.ም ጀምሮ የሙከራ ሥርጭት ቢጀምርም፣ የውሃ ፈረቃውን ከ15 ቀን ወደ አንድ ሳምንት ዝቅ ከማድረግ ባለፈ ለከተማው ሕዝብ የመጠጥ ውሃ በአግባቡ ማዳረስ አልተቻለም፡፡
ነዋሪዎቹ በሳምንት አንድ ቀን የሚመጣውን ንህም ሆነ ድፍርስ ውሃ ሳይታክቱ ባገኙት ዕቃ ሞልተው ሳምንት ይጠብቃሉ፡፡ ወዳጄ እንዳጫወተኝ ውሃ ለሐረር ነዋሪዎች የቤንዚን ያህል ሆኗል፡፡ የቤት ሠራተኛ ለመቅጠር ሲደራደሩ እንኳን ..ልብሷን የምታጥበው ቤቷ ነው? ወይስ ቤቴ?.. የሚል መስፈርት አላቸው፡፡  እግር ጥሏችሁ በአንድ መኖሪያ ቤት ብትገቡ በግቢው ውስጥ የተደረደሩት ቢጫ የዘይት ጄሪካኖች በቅርቡ ከአስመጪዎች ላይ የተሰበሰበው የምግብ ዘይት በሙሉ ሐረር ተወስዶ በየመንደሩ የተራገፈ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡
በፕሮጀክቱ ዕቅድ መሠረት የቧንቧ መሥመር ዝርጋታው ከተከናወነ እና አዲሱ ከአሮጌው ጋራ ከተቀናጀ በኋላ፣ ውስጡ መታጠብ ሲገባው ሥራው በሚገባ ባለመከናወኑ ውሃው አንዳንዴ ድፍርስ ሊሆን መቻሉን ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ ለእርሱ ግን የውሃው መደፍረስ ይህን ያህል አላሳሰበውም፡፡ ውሃውን የሚገፉት ፓምፖች ሙሉ ለሙሉ መሥራት ይጀምሩ እንጂ ድፍርሱ በጊዜ ሂደት ይጠራል የሚል እምነት አለው፡፡
መቼ?
የውሃ መግፊያ ፓምፖቹን የዘረጋው ድርጅት እስከ አሁን ስሕተቱን አላመነም፡፡ ..እኔ ጥራት ባለው ዕቃ በትክክል ነው የገጠምሁት፤ ፓምፖቹ መሥራት ያልቻሉት የኤሌትሪክ ኃይል እጥረት በመኖሩ ነው..፤ ይላል፡፡
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ያሠራው እና ግዢው የተፈመው በውሃ ሀብት ሚኒስቴር በኩል በመሆኑ ክርክሩ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ተይዟል፡፡ መፍትሔው ምን እንደሆነ የሚመጣውን ከመጠበቅ በቀር አንድም የከተማው ነዋሪ አያውቅም፡፡ ደግነቱ ሐረሮች አሁን ሁሉንም ለምደውታል፡፡ ለእኛ ቆሽሾ የሚታየን ውሃ ለእነርሱ ንፁሕ ነው፤ ከቧንቧ ውሃ ጋር በሳምንት አንድ ጊዜ መገናኘቱንም ለምደውታል፡፡ 400 ሚሊዮን ብር የወጣበት ፕሮጀክት ፓምፖች ቢሠሩም ባይሠሩም እነሱ በጀመሩት መንገድ ይቀጥላሉ፡፡ የሚመጣውንም ከመጠበቅ ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡  
ድሬንስ ምን አጋጠማት?
በከርሠ ምድር ውሃ ክምችት ከአዲስ አበባ ቀጥላ ሁለተኛ ወደሆነችው ድሬዳዋም ጐራ ብዬ ነበር፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ በዚች ከተማም የውሃ እጥረት ተከሥቷል፡፡ አንድ ቀን ይመጣል፤ አንድ ቀን ደግሞ ይጠፋል፡፡ ምናልባት በየተራ በሥራ ላይ በምትገኘው አንዲት ፓምፕ እየተገፋ ወደ ሐረር የሚሄደው ውሃ ድሬዳዋ ላይ እጥረት ፈጥሮ ሊሆን ይችላል ብዬ ወደ ድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ አመራሁ፡፡ የድሬዳዋ ውሃ እንደማያልቅ እና ከርሠ ምድሯ ሁሉ በውሃ የተሸፈነ እንደሆነ ያገኘሁት መረጃ ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን የውሃው ጨውነት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ከጊዜ ብዛት አብዛኛውን የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች እንደሚዘጋ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ቧንቧዎቹ በየጊዜው ክትትል እየተደረገ ካልታጠቡ የውሃ መቋረጥ ያስከትላሉ፡፡ የከተማው አስተዳደር እና የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በጉዳዩ ላይ የተሟላ ክትትል ባለማድረጉ ድሬዳዋ ውሃ ላይ ቆማ ውሃ የምትጠማ ከተማ መስላለች፡፡ ..የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው.. የሚባለው መልካውን ሞልቶ በገጽ ምድር ለሚፈሰው ብቻ ሳይሆን እንደ ድሬ በከርሠ ምድር ውኃ ላይ ለቆሙት ከተሞችም ነው ቢባል ሐቅ አይሆንምን?

 

Read 2245 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:50