Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 September 2011 11:41

ኑሮና ህይወት በ2003እነሆ አዲሱ ዓመት መጣ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አሮጌውም ወደ ኋላ ቀረ፡፡ አዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ ይዞልን ስለመምጣቱ
አስረግጠን መናገር ባንችልም አሮጌው ዓመት ጭኖብን ያለፈውን የኑሮ ቀንበር ወደ ኋላ መለስ ብለን መታዘብ አይቸግረንም፤ አዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ ሞሻሽሮ ከፊታችን የሳለብን የሚያጓጓ ህይወት ስለመኖሩ አፋችንን ሞልተን ለመናገር ቢገደንም፤ አሮጌው ዓመት በኑሮ ውጥንቅጥ አጨመላልቆ በወጉ ሳናጣጥመው የነጠቀንን፣ ድፍርስ ህይወት፣ እያሰብን አንዳንድ ነገሮችን መዘከር አያቅተንም፡፡ ነገን መተንበይ የሚያስችል የነቢይነት ዓቅም ባይኖረንም ትናንትን ቆም ብሎ ለመገርመም፣ ትዕግስት አያንሰንም፡፡

ህይወት ሁሌም ጣፋጭ ናት፣ ኑሮ ነው ጐምዛዛ፡፡ አዲስ ዓመትም አዲስ የቀን መቁጠሪያ ሰሌዳ ነው፤ የአዲስ ተስፋ ጐህ የሚወለደው ከጐምዛዛ ኑሮ ነፃ ከሆነች፣ ውብ ህይወት ላይ እንጂ፣ ከአዲስ ቀን መቁጠሪያ ሰሌዳ ላይ አይደለም፡፡ ዕድሜም ቢሆን ተቀምሮ፣ ተለክቶ፣ ተመዝኖ ድምሩ የሚገለፀው ህይወትና ኑሮ፣ ከሚያደርጉት የዕለት ተዕለት ግጥሚያ ውጤት በኋላ ነው፡፡ ..ደጉ..፣ ..ወርቃማው.. ..ውቡ.. ዘመን ያ ነበር፡፡ ..ከባዱ..፤ ..መራራው.. እና ..ማስጠሎው.. ጊዜም ያኛው ነበር፤ መባባሉ የሚመጣውም፤ ከየትም ሳይሆን ከዚያው ከህይወትና ከኑሮ ግብግብ ውጤት ላይ ነው፡፡ የኑሮ ፈተና ገዝፎ የህይወትን ውበትና ጣዕም ክፉኛ ከደቆሰው፤ በሰው ልጅ ምናብ ውስጥ የሚሳለው የዘመን ስዕል ጨፍጋጋ መሆኑ አይቀሬ ነው የግብግቡ ውጤት በተቃራኒው አቅጣጫ አመዝኖ ህይወት የኑሮን ፈተና በጣጥሳው ካለፈች ደሞ የዘመን ምስልም በውስጣችን፣ ፈክቶና ደምቆ ይሳላል፡፡
ያገባደድነውን (የሸኘነውን) ዓመት 2003ትን በህይወት መስኮት አሻግረን ካየነው፤ ልክ እንደቀደሙት ዓመታት ውብ ነበር፣ ጣፋጭ ነበር፡፡ ልክ እንደቀደሙት፣ ዓመታት፣ ህይወት በ2003ትም አይጠገቤ ፀጋ ነበር፤ ምክንያቱም ህይወት ሁሌም፣ መቼም በምንም ሁኔታ ውስጥ ጣፋጭና አይጠገቤ ስለሆነ፡፡ ልደትና፣ ሞት፤ ሐዘንና ደስታ፣ ስኬትና ውድቀት፤ ፍቅርና ጥላቻ፤ ጋብቻና ፍቺ ማግኘትና ማጣት፣ መሰደድና (ስደት) እና፣ ከስደት መልስ፣ ጥጋብና ረሃብ፤ መዝናናትና መጨናነቅ ወዘተ ሁሉም እንደሁልጊዜው ሁሉ ባሳለፍነው ዓመት በ2003ትም በህይወታችን ውስጥ መጥተዋል ሄደዋል ተፈራርቀዋል፡፡ 2003ትን፣ በኑሮ መነጽር አሻግረን ካየነው ግን ዓመቱ እጅግ ፈታኝና ተፈታታኝ እንደነበረ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ኑሮ እንደ ህይወት ቋሚ የተፈጥሮ ቀመር የለውም፤ ኑሮ እንደ ህይወት ሁሌም፤ አንድ ዓይነት ጣዕምና ለዛ የለውም፤ ህይወት፣ የተፈጥሮ ፀጋ የመሆኑን ያህል ኑሮ፤ የጊዜ፣ የቦታና፣ የሁኔታ ድምር ግዴታ ነው፤ ሁለቱ ፍፁም ከተራራቀ ምንጭ የሚቀዱ ነገሮች ናቸው ሁልጊዜም፤ ይፋለማሉ፡፡
ህይወትና ኑሮ ባሳለፍነው ዓመት የህልውና መድረክ ላይ ያደጉትን፣ የሞት ሽረት ፍልሚያ በቅርብ ርቀት መለስ ብለን ስናየው፤ በእጅጉ መደነቅ፣ ሊቃጣን ይችላል፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ከኖርንባቸው ጊዜያት ይልቅ በራሳችን ህልውና ላይ ራሳችንን ተመልካች (ታዛቢ) አድርገን፣ በፍልሚያው መድረክ ጠርዝ ላይ ቆመን በትዕይንቶቹ የተመሰጥንባቸው ጊዜያት በልጠውብን ግራ እንደተጋባን የባጀንበት ዓመትም ነው - 2003፡፡
ህይወትም ያለ ፍቅር ወጥም ያለ ጨው፣ ጣዕም አልባ ናቸው፡፡ ኑሮ ማንም ባሻው ሰዓት ከህይወትም ላይ ፍቅርን፣ ከወጥም ላይ ጨውን መንጠቅ ያምረዋል፡፡ በተለይ የኛ የከተሜዎቹ ህይወትና ወጥ፣ መቼና እንዴት ማጣፈጫውን በኑሮ አንደሚነጠቅ መተንበይ አይቻልም፡፡ የኑሮ ድንዛዜ፣ በፍቅር ላይ ዱካክ ይጥላል፡፡ የፍቅር ዱካኩ ደግሞ፣ የህይወትን ጡንቻ ያዝላል፡፡ የከተሜ የፍቅር ቴርሞ ሜትር ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ተከታታይ ማሽቆልቆል ማሳየቱን አንክድም፤ ቢያንስ በዓመት አንድ ቀን፣ ከተፍ የሚለውና ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕውቅናቸው እየሰፋ የመጣው የቫለንታይን ዴይ (የፍቅረኞች ቀን) አቧራ ለብሶ የከረመውን የፍቅር ቴርሞሜትር ለመጠራረግና የፍቅርን ሙቀት ለመለካት ምክንያት ሆኖናል፤ (ዕድሜ lGlÖÆላይz¤>N!)
ባሳለፍነው ዓመት የተከበረውን የፍቅረኞች ቀን በፍቅር ለማክበር ሳይሆን በአግራሞት ለመታዘብ ከታደሉት፣ ..የፎረሹ.. ወገኖች እንደ አንዱ ሆኜ፣ ፈንጠር ብዬ ሳየው፣ በቀይ ቀለም ድባብ ውስጥ፣ የአብዛኛውን ከተሜ አፍቃሪ ፍቅር ባለበት እንዲቆም የሚያስገድድ ቀይ የኑሮ መብራት መብራቱን አስተውያለሁ፡፡ በዚያ ሳምንት የማውቃቸው ብዙ ጥንዶች ቀልባቸውን መሰብሰብ ተስኗቸው ነበር፡፡ የስጦታ ዕቃ ዋጋ ንረት፤ የመገባበዣና የመዝናኛ ቦታ ምርጫ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በቃል ኪዳን ቀለበት የመተጫጨት ዕቅድ፣ ዕቅዱን ለመተግበር የሚጠይቀው የገንዘብ ወጭ ስሌት ከገቢ ልቆ መገኘት ወዘተ... የፍቅረኞችን ናላ ሲያዞሩ ከሰነበቱ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ልብ ያሰበው ብዙ፣ ኑሮ የፈቀደው ግን ጥቂት ወይም ምንም ሆነና፤ የፍቅረኞች ቀን ከዋዜማ እስከ ማግስት፣ የብዙ ጥንዶችን ፍላጐት መሙላት እንደተሳነው፤ በቀይ አልባሳት፣ በቀይ ጌጣጌጥ፣ በቀይ አበባ፣ በቀይ ወይን በቀይ መብራት እንዲሁም በኑሮ ላይ ጥርስ በነከሱ አፍቃሪዎች በልልህ የደፈረሱ ቀያይ ዓይኖች ድባብ ውስጥ እንደነገሩ ተከብሮ አረፈ፡፡ ብዙ ድንዛዜ፤ አያሌ ዱካክ እንዳንዣበበበት፤ እዚህም እዚያም lRomantic mood የተሰየሙ ጥንዶች ..ተጫወት..ንጂ ..ተጫወች..ንጂ እንደተባባሉበት የአምናው ..ቫለንታይን ዴይ.. ተሸኘ፡፡ በርግጥ ከብዙሃኑ አፍቃሪ ከተሜ ጋር ሲነፃፀር ቁጥራቸው ..ኢምንት.. ሊባል የሚችል አፍቃሪዎች ከከበረ ጌጣጌጥ እስከ አዲስ መኪና ሊደርስ (ሊበልጥም) የሚችል ስጦታ፤ ተቀባብለው በላቀ ፈንጠዝያ፣ ዕለቱን አክብረውት ይሆናል፡፡
የብዙሃን ከተሜዎች የፍቅር ቴርሞሜትር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ክንዱን እያበረታ፣ ጡንቻውን እያፈረጠ የመጣው ..ኑሮ..፤ በአብሪው ቀይ መብራት ..ባለህበት ቁም.. መባሉን አምነው ለመቀበል ተገደዋል፡፡ እኔን ጨምሮ በርካታ የፎረሹ ብጤዎቼ ደሞ፤ ቢያንስ በዚያ ሰሞን መፎረሻችንን አወድሰን ..እፎይ.. ብለናል፡፡ የፍቅርን ዳገት መውጣት ላልጀመሩ ለጋ ወጣቶች፤ መጭው (አዲሱ) ዘመን ምን ዓይነት መብራት እንደሚያሳያቸው አናውቅም፡፡ በተስፋና በምኞት ደረጃ ግን መጭው ..ቫለንታይን ዴይ.. ቀኝ ኋላ ዙር የሚል የከፋ የኑሮ መብራት እንደማይበራበት ተስፋ እናደርጋለን፤ እንመኛለን ምክንያቱም ፍቅር የህይወት ቅመም ነው፡፡ ህይወት ደሞ ሁሌም ጣፋጭና የማይጠገብ ፀጋ ነው፡፡ በህይወት ውስጥ ሁሌም ተስፋና ምኞት አለ፡፡ የኑሮ መጐምዘዝ ባለበትም ቢሆን፡፡
ባለፈው ዓመት (2003) ያስተናገድነው የህይወትና የኑሮ ግብግብ እንዲህ በዋዛ የሚታይ እንዳልሆነ የ..ብዙሃኑ.. መደብ አባላት የሚመሰክሩት ገሃድ ዕውነታ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙሃኑ ህዝብ ህልውናውን የተፈታተነው የኑሮ ጡጫ እያንገሸገሸው ውጦታል፡፡  የማይጠገብ የተፈጥሮ ፀጋው፣ ህይወቱ ህመሙ በበረታ የኑሮ ቡጢ ተወግሮበታል፡፡ የህይወቱ መሠረት የሆኑትን የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመልበስ፣ የመጠለያ ማግኘት ፍላጐቶቹን መኖር በሚያስችል ደረጃ እንኳን ማሟላት በተደጋጋሚ ፈተና ገጥሞታል፡፡ በተለይ ከተሜው የንቀት ቅምጥሎችን የግል ብልጽግና ሩጫ አዳማቂ፣ የበይ ተመልካች መሆኑ ሳያንሰው፤ የኑሮ መደብ ለይቶ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን ብዙሃን ነዋሪ አነጣጥሮ ለሚወጋው የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ንረትና የገበያ አለመረጋጋት ሲዳረግ ፈጥኖ የሚታደገው መከታ ማጣቱ ግራ ሲያጋባው ከርሞአል፡፡
ይመጣል ተብሎ ከተነገረለት ዓመታት ያስቆጠረው የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪና ማስተካከያ ዕውን በሆነበት ባለፈው ዓመት አጋማሽ ገደማ በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የፍጆታ ዕቃዎች ዕጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋትና የንግድ ስርዓት ውጥንቅጥ በመፈጠሩ የነዋሪው ህይወት ተፈጥሮአዊ ጣዕሙ ርቆት፣ የኑሮ ስልተ ምት ተወነባብዶባት ነበር፡፡
መንግስት የችግሩ ምንጭ የጥቂት ..ጉልቤ.. ነጋዴዎች አሻጥር መሆኑን ገልፆ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ሲዘጋጅ፣ ..ጉልቤ.. የተባሉት ነጋዴዎች ደንገጥም አለማለታቸው የችግሩን ምንጭ ደረስኩበት የሚለው መንግስት፤ ችግሩ ስር እስኪሰድና ዓይን ያወጣ የንግድ ስርዓት አልበኝነት በተለይ በከተሞች ውስጥ እስኪስፋፋ ድረስ ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠቱ፤ ራሱ ነዋሪውም ጉሮሮውን በሁለት መዳፎቻቸው ስር አስገብተው ሲያሻቸው ..አነቅ.. ሲላቸው ..ለቀቅ.. እያደረጉ የሚያስጨንቁት ነጋዴዎች ..ጃስ.. ባሉትና በአንገብጋቢውም በማያንገበግበውም ሸቀጥ ላይ የገበያ ዋጋ ሽብር በነሱበት ቁጥር አለቅጥ መበርገጉ፤ ሌሎችም ምክንያቶች ተደራርበው የህይወቱ ጣእም በኑሮ ትርምስ ውስጥ እንደበረዶ ቀልጦ እንዲጠፋ አደረጉት፡፡ የከተማ ኑሮ በአስተማማኝ የንግድ ስርዓት፣ በሰለጠነና ሊተነበይ በሚችል የኢኮኖሚ ሳይንስ የማይመራና ማንም ባሻው ሰዓት ወዳሻው አቅጣጫ ሊቀለብሰው የሚችል ኑሮ እስኪመስል ድረስ፣ በነዋሪው ጫንቃ ላይ ደነሰበት፡፡ ገበያ እንደጀምበር፤ ንፋስና ደመና በራሱ ሰዓት ራሱን መራ፤ ...በመንግሥት በኩል የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎች፤ ከመተግበራቸው አስቀድሞ በጉልቤ ነጋዴዎቹ ስለሚታወቁ እያንዳንዱ XRM© በአፍራሽ የአፀፋ እርምጃ እየተሰናከለ፣ ሰዶ የማሳደድ ሩጫው አፋጣኝ ውጤት ማምጣት ተሳነው፡፡ በእነዘይት ስኳርና ሌሎች የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የተከፈተው ገበያውንና አቅርቦቱን የመቆጣጠር ዘመቻ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ፈር መያዙ ውጤታማ ስራ ነው ቢባልም፣ የወቅቱ እርምጃዎች ሁሉ የተጠኑ ነበሩ አያሰኝም፡፡ በስጋና በቢራ ላይ ተጥሎ የነበረውና (ቀድሞውንም በኑሮ ውድነቱ ጫንቃው አብዝቶ ተላላጠበትና ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ለሚገፋው ነዋሪ ቅንጦት በሆኑት ስጋና ቢራ ላይ መዘመቱ ግራ ማጋባቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) ብዙም ሳይቆይ በመንግስት ማፈግፈግ መልሶ የተቀበለው እርምጃ እንደኪሳራ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በነዚህና ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ሳቢያ፣ ገዢ ህጐችና ህግ አስፈፃሚ አካላትን ያሰለፈው መንግስት፤ ወጪና ገቢ ንግዱን የሚያሽከረክሩት ነጋዴዎች ለመሸናነፍ ባደረጉት ትግል ውስጥ በእጅጉ የተቸገረውና የተወዛገበው ህዝብ፤ ከሁለት ወገን የሚሰነዘሩትን ፍላፃዎች በጉሮሮው እየመከተ ማዕበሉን አልፏል፡፡
እንደቀደሙት ጊዜያት ባለፈው ዓመትም ወርሃዊ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን በተከታታይ አስተናግደናል፡፡ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪም በተጓዳኝ ተከናውኗል፡፡ በርግጥ (በዚህ ረገድ የዓመቱ የመጨረሻ ወራት ከደሙ ንፁህ ነን ማለት ይችላሉ) ቀድሞ ባሉት ዓመታት የከተማ ድሃ ወጥቶ መግባትን ሲያስብ፣ የከተማ አውቶቡስን ዋስትናው አድርጐ ይናና ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየናረ ከመጣው የነዳጅ ዋጋ ጋር የከተማ ድሃ የመጨረሻው የጉዞ አማራጩ እግሩ ብቻ ሆኗል! ጠግቦ የማይበላ ሰው በእግሩ ረጅም ጉዞ በተጓዘ ቁጥር ይዝላል፡፡ ረጅም ጉዞ ተጉዞ ያገኛትን ካልሰራ ደግሞ ያከተምለታል፡፡ እንደ መንገዱ ሁሉ የህይወት ጉዞውም በኑሮ ዝለት ይደክማል፡፡ የኑሮ ዝለትም የህይወትን ተፈጥሮአዊ ጣእም ምኞት ተስፋና ደስታ ያጐመዝዝበታል፡፡ ስለሀገራችን የነዳጅ ዋጋ ተከታታይ ጭማሪ መንስኤ ለማወቅ የሚሻ ሁሉ ጥያቄውን ሲያቀርብ መንስኤው የዓለም የነዳጅ ዋጋ ንረት መሆኑ ይነገረዋል፡፡ ዘወትር ምሽት የገበያ ዜና በሚዲያ ሲተነተን ያያል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ማለቱን ይረዳል፡፡ የሀገር ቤት የነዳጅ ዋጋ ግን የመጨመር እንጂ የመቀነስ ነገር አይታይበትም፤ የገበያና የኢኮኖሚ ሳይንስ (ቀመር) ከኒውክሌር ሳይንስ ቀመር በላይ ውስብስብና ከባድ መሆኑን ይገምታል፡፡ ነዳጅ በዓለም ገበያ ሲጨምር እኛ ጋርም ይጨምራል... ሲቀንስም ቢሆን ይጨምራል!... እኔን ባይገባኝንጂ አሰራሩ ልክ ነው በማለት ራሱን በማይችለው ሃሳብ ሲወዛገብ ይውላል... ያድራል!... የነዳጅ ዋጋ ተእኖ በእለት ጉርሱ በዓመት ልብሱም ላይ ተእኖ ስላለው በጉዳዩ ላይ ሁሌም አብዝቶ ይወዛገባል፡፡ አንዳንዴም መኪና ያለው ሁሉ ቤንዚን መግዛት አያቅተውም፤ ቡታጋዝ ያለው ሁሉ ነጭ ጋዝ መግዛት አያቅተውም የሚለውን ከነዳጅ ድጐማ መነሳት ጋር የተያያዘውን የመንግስት አቋም ፍትሃዊ አይደለም በማለት ይኮንናል፤ እንዲህ...እንዲህ... እያለ ሲብሰከሰክ ያመሻል... ይነጋል...
ህይወት ወደ ማህበራዊ ህይወት ያመራል!... ማህበራዊ ህይወት፤ አንዱ የሌላውን ዝምድና አብሮነትና አጋርነት የሚሸምትበት መድረክ ነው፤ ዝምድናና ወዳጅነት ደሞ የሚያስከፍሉት ዋጋ አለ፤ ሀዘንና ደስታን ለመካፈል ብድር በምድር ለመመለስ ሰው ይተጋል!... ለእከሌ... ይህን ብሰጥ ለእከሊት ይህን ባደርግ... እከሌ... ጋር... ይህን ገዝቼ... ብሄድ... ወዘተ... ብዙ ጥያቄ ብዙ የቤት ስራ፤ ብዙ የልብ መሻት ብዙ የህሊና እዳ ተግተልትሎ ይመጣል፡፡ ያሰቡትን መፈፀም መቻል፣ ያሉትን አድርጐ መገኘት የውስጥ እርካታን የውጭ ኩራትን ያላብሳል፡፡ ህይወት ያለማህበራዊ ህይወት ጐደሎ (የማይሞከር) ነው!... የማህበራዊ ህይወት ግዴታዎች ደሞ መስጠትና መቀበልን ምርኩዝ አድርገው ይኖራሉ፤ ማህበራዊ ህይወት ደስ ይላል... ደስ ከማሰኘቱም የተነሳ ማህበራዊ ኑሮን ይፈጥራል... ኑሮ ደሞ ከቀድሞዎቹም አመታት በከፋ ሁኔታ ካቻምናና አምና አለቅጥ ኮምጥጧል፡፡ ሰው ምን ይዤ?... በምን ተጉዤ ምን ለብሼ? ማንን አስከትዬ? ካለው ልቀላቀል? እያለ መጠበብ መጨነቅ፤ መሸሽ መደበቅ፤ መዋሸት መራራቅ ይዟል፡፡ mÀW ምን ይዞ እንደሚጠብቀን ባናውቅም ያለፈው ዓመት ማህበራዊ ህይወታችን በኑሮ ጡጫ ያለርህራሄ ተደቁሷል!...
ህይወት ሁሌም ጣፋጭና የማይጠገብ ፀጋ ነው!... ኑሮ ግን ይጐመዝዛል... የተሰናበትነው አመት (2003) ኑሮ በርካታ የህይወት በረከቶችን ዘና ብለን እንዳናጣጥምበት አላፈናፍን ብሎናል፡፡ የተራዘሙ ወይም የተሰረዙ ሠርጐች፤ ያልተደገሱ ልደቶች፤ ያልደመቁ አውደ አመቶች (በአላት) ወዘተ... ምን ያህል እንደሆኑ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ወልዶ የመሳም ዘርቶ የመቃም ሃሴት በቃኝ አይባልም አንድ ልጅና አንድ ጐል አያስተማምንም ይደገም እንዳልተባለ ያለውን ይባርክልን ይበቃል! ማለት ተዘውትሯል!... የዛሬ ልጅ የትምህርት ውጭ ናላ ያዞራል፡፡ ለባለ አምስት ደረጃ ምሳ ዕቃ የሚመጥኑ የተለያየ ምግብ ማዘጋጀት ይቸግራል!... እንደምንም ሁለቱን አስይዞ ሦስቱን እንደ ‘Spare lunch box’ ማስቀመጥ ነው፡፡ የዛሬን ልጅ ለማዝናናት የሚወጣው ወጪ የድሮን ልጅ ለአቅመ አዳም ለማድረስ በቂ ነበር ይሉናል ወላጆቻችን! (የኛን ልጆች life ሲያዩ በግርምት) እድሜ ለኑሮ! ልጆቻችን ብሮቹን እንደሻሞላ ቀስረው ቶሎ  እየቀያየሩ ፍልሚያ ቢጫወቱበትንኳ አይረኩም! የነሱ ደስታ ያስደስተናል፤ ህይወትን ሙሉ ያደርጋታል፤ ኑሮው ግን ይህንንም ደስታ ነፈገን፡፡ እየፈራን ወልደን እየፈራን አሳድገን እዚህ ደርሰናል፤ የነገን እንጃ!
ህይወት ውብ ናት፤ ነግዶ ማትረፍ ሰርቶ ማግኘትን ታስመጥናለች፡፡ ኑሮ ግን በዚህም በዚያም ወጥሮናል፡፡ የተሰናበትነው ዓመት ያልታሰበ የንግድ ግብር ተመን አሸክሞናል፡፡ ቀድሞም የእኛን የግብር ነገር እንደ አይጥና ድመት አባሮሽ አያጣውም፤ ግብር የመክፈል ተነሳሽነትና በግብር ክፍያ የማመን ዝንባሌ (አመለካከት) ለመፍጠር የተደረገው አመታት የፈጀ ጥረት መልካም ውጤት ማምጣት መጀመሩ ጐሽ ሲያሰኝ፤ ድንገት ግብር ከፋዩን የሚያስበረግግ ዱብዳ የግብር ተመን መምጣቱ ጤናማ አካሄድ አይመስልም... ይሄ ዱብእዳ ዞሮ  ያው የፈረደበት ህዝብ ላይ ማረፉ አይቀሬ ነው!... መንግስት በነጋዴው ላይ ያሰረውን ልጓም በሳበ ቁጥር፣ ነጋዴው በሸማቹ (ተገልጋዩ) አንገት ላይ የደገነውን ሸምቀቆ ማጥበቁ ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው! በአሮጌው አመት ማብቂያ ላይ የወረደው የግብር ዱብእዳ መዘዙ ለአዲሱ ዓመት ሊመዘዝ ይችላል ብለን ብንሰጋም አይፈረድብንም፡፡ በምክንያት የማሳመንና የመተማመን ችግር አለብን!...
ተሰናባቹ ዓመት (2003) ካጐናፀፈን በረከቶች አንዱ ብዙሃኑ የመንግስት ሠራተኛ ለአመታት ሲቁለጨለጭበት የኖረው የደሞዝ ጭማሪና የእርከን ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ነው! ሌላውና ከዘመናት አሮጌ ታሪካችን ያላቀቀን ብስራት ደሞ በታላቁ ወንዛችን በአባይ ላይ የሚነባው ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ግድብ መጀመሩ ነው፡፡ በተለይ የግድቡ መገንባት ብስራት ህዝብና ሀገር፤ እድገትና ተስፋ፤ ምኞትና ጥረት በአንድነት እንዲነሳሱ ትልቅ ጉልበት ፈጥሮአል... ኑሮ ቢጐመዝዝምንኳ ህይወት ሁሉም ውብና የማይጠገብ ፀጋ ነው በህይወት ውስጥ ሁሉም ተስፋና ምኞት አለ፤ በህይወት ውስጥ ሁሉም ጥረት አለ! መጪው ጊዜ በኑሮ ጡጫ ለተደቆሰው፣ የህይወትን ጣእም እፎይ ብሎ ማጣጣም ለተሳነው ለብዙሃኑ ድሃ ህዝብ... በጆሮው ሳይሆን በሆዱ የሚያጣጥመው የኑሮ በረከት የሚያካፋበት ይሆን ዘንድ እንመኛለን!... ያንን ተስፋ ይዘን ያለ የሌለ ሞራልና አቅማችንን አሟጥጠን፣ አሁንም ከኑሮ ጋር እንፋለማለን! አበባየሆይ ብለን አዲሱን ዓመት እንቀበላለን!... ሌላ ምን አማራጭ አለን?!
/ደረጀ አያሌው የቀድሞው የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛ እና የመዪልዬ መዪለይ መጽሐፍ ሐፊ ነው፡፡/

 

Read 5766 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:43