Saturday, 10 September 2011 11:24

የዓለም እውነታ የተገላቢጦሽ እየሆነነው!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

አብዛኞቻችን ከአንደኛ ደረጃእስከ ከፍተኛ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን የተከታተልነው ትምህርታችንን ስንጨርስ የጡረታ ምንዳ በሚያስገኝ በመንግስት መስሪያ ቤትተቀጥረን፣ ወላጆቻችንን የመጦር ሃላፊነትን ከወዲሁ ተሸክመን ነው፡፡ ይህንን ሃላፊነት በሆነ አጋጣሚና ምክንያት ችላ ብንለው ወይንም ብንረሳው ወላጆቻችን በጭራሽ ችላ ሊሉትና ሊረሱት አይችሉም፡፡  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ታሪካዊ ሀላፊነታችንን ለአፍታም ቢሆን ችላ ብለን እንዳንዘነጋው፣ በጥሞና ማስገንዘብና ማስታወሳቸውን አይተውም፡፡ ለምን ብትሉ ከሁሉም ነገር በላይ ቀድሞውኑ እኛን የመውለዳቸውና የማስተማራቸው ዋናው አላማ አድገን፣ ተምረንና ስራ ይዘን እነሱን እንድንረዳና እንድንጦር ስለሆነ ነው፡፡

ይህን ጉዳይ የድሮ ዘመን አስተሳሰብና አሠራር እንጂ በአሁኑ ዘመነኛ ጊዜ የማይሠራ፣ ያረጀ ያፈጀ ጉዳይ ነው ካላችሁ፣ መቶ በመቶ ተሳስታችኋል እንኳ ባይባል፣ ዛሬም ድረስ ከሞላ ጐደል እንዳለና ጨርሶም ሳይጓደል እየተሠራበት እንደሆነ ለማረጋገጥ፣ በከተማችን እየታተሙ በሚወጡ ጋዜጦችና መጽሔቶት ላይ የሚታተሙትን የልደትና የትምህርት ምርቃት የበጐ ምኞት ማስታወቂያዎችን ማየትና ማንበቡ ብቻ ይበቃል፡፡
የልደትም ሆነ የትምህርት ምርቃት የበጐ ምኞት ማስታወቂያ መግለጫዎች፣ የያዙት መልእክት ከሞላ ጐደል አንድ ሰው እየፃፈ የሚያዘጋጃቸው እስከሚመስሉ ድረስ አንድ አይነት ናቸው፡፡ ..ልጃችን እከሌ ወይም እከሊት ለዚህን አመት ልደትህ እንኳን አደረሰህ፤ አድገህና ተምረህ ወላጆችህንና ሀገርህን ለመርዳት ያብቃህ.. የሚለው የልደት በአል የመልካም ምኞት መግለጫ በጋዜጣም ላይ ወጣ በመጽሔት ጾታው ላይ ይለያያል እንጂ ሁሉም አንድ አይነት ነው፡፡ ለትምህርት ምረቃ የሚወጡት የመልካም ምኞት መግለጫዎችም እንዲሁ አንድ አይነትና ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የሁሉም መግለጫዎች ዋነኛ መልእክታቸው፣ የተሸከምነውን አድገን፣ ተምረንና ስራ ይዘን ወላጆቻችንን የመጦር ኃላፊነታችንን እንዳንዘነጋው ማስታወስ ነው፡፡
የሃያ ስምንት አመት ወጣተ ግርማም ይህን ኃላፊነት ተሸክመው ካደጉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገራችን ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ የሁለት እህቶቹና የአራት ወንድሞቹ ታላቅ ነው፡፡ የመጀመሪያም የመጨረሻም ከሆነውና እድሜ ልካቸውን በመዝገብ ቤት ማህደር አከናዋኝነት ከሠሩበት የጐንደር የቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት፣ የሁለት መቶ ሠላሳ አምስት ብር የጡረታ አበላቸውን ይዘው አባቱ ከስራ የተገለሉት ከዛሬ አስር አመት በፊት ነበር፡፡ እናቱ እንደ አብዛኞቻችን እናቶች የቤት እመቤት ናቸው፡፡ ከጓዳቸው ወጥተው ፊታቸውን ለሰውና ለፀሐይዋ ያስመቱት፣ እያደር አልገፋና የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ትግል የሆነባቸውን የኑሮ ቀንበር፣ ለመግፋትና ቢያንስ በቀን አንዴ ባይጣፋጥ እንኳ ከርስ የሚሞላ ምግብ ለቤተሰባቸው ለማቅረብ በሚል ጉልት ከሰል መሸጥ ሲጀምሩ ነው፡፡
ግርማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስኪገባ ድረስ ትምህርቱን የተከታተለው እዚያው ተወልዶ ባደገበት የጐንደር ከተማ ነው፡፡ ከጐንደር አዲስ አበባ መጥቶ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ሲገባ፣ እርሳስና ደብተር ገዝቶ የሚረዳው ይቅርና በስምም ሆነ በአይን የሚያውቀው ሰው እንኳ አልነበረውም፡፡ እናም የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን ለአራት አመታት ተከታትሎ ለመጨረስና በቢኤ ዲግሪ ለመመረቅ ያደረገውን ተጋድሎና የከፈለውን መስዋዕትነት መራራነት ከእሱው በቀር ሌላ ማንም በሚገባ ሊያስረዳ አይችልም፡፡ ወላጆቹ ትምህርቱን ሲጨርስ እንደምንም ብሎ ስራ በመያዝ እነሱን እንዲጦር ዘወትር ከማሳሰብ ውጪ yዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ያለ አንዳች አጋዥ እንዴት ሊጨርስ እንደሚችል ብዙም የሚጨንቃቸው አልነበሩም፡፡
አባቱ የራሳቸውን የልጅነት የቆሎ ተማሪነት ህይወታቸውን ብቻ እያሰቡ፣ ተማሪ ቀለቡንና ማደሪያውን በብላሽ ካገኘ ሌላ ምን ይፈልጋል ባይ ነበሩ፡፡ የእሱን ነገር ሲያስቡት ግራ የሚጋቡትና በጭንቀት የሚንገላቱት እናቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የፈለጉትን ያህል ግራ ቢጋቡና ቢጨነቁ ሊያደርጉለት የሚችሉት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ድህነት እጃቸውን በእጅጉ አሳጥሮታል፡፡
የአራት አመቱ በፈተናና በውጣ ውረድ የተሞላው የዩኒቨርስቲ የትምህርት ጊዜ አልቆ የተመረቀ ቀን፣ ሌሎች ተመራቂ ጓደኞቹ በደስታ ስሜት ተውጠው ዘና ሲሉና ሲቦርቁ ግርማ የደስታ ይሁን የሀዘን ባልለየለት ስሜት ተውጦ ነበር፡፡ የዚያኑ ቀን ማታ ዶርሙ ውስጥ ብቻውን ሲያድር፣ ግራ በተጋባና በሆደ-ባሻነት ስሜት ተንሰቅስቆ አልቅሶ ነበር፡፡
በዩኒቨርሲቲ የአራት አመት ቆይታው ተነግረው የማያልቁ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን ተጋፍጦ አሳልፏቸዋል፡፡ እዚያ ሌሎች ነገሮች እንጂ ቢያንስ የምግብና የመጠለያ ችግር አልነበረበትም፡፡ ተመርቆ ዩኒቨርሲቲውን ለቆ ሲወጣ ግን ከሌሎች ችግሮቹ በተጨማሪ ለምግቡና ለመኝታውም ማሰብና መጨነቅ ይኖርበታል፡፡
ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ደግሞ ስራ ፈልጐ የማግኘት ዋነኛው ጉዳይ ከፊት ለፊቱ ይጠብቀዋል፡፡ በየቦታው እየተዘዋወሩ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ ማንበብና የስራ ማመልከቻውን በየመስሪያ ቤቱ ለማስገባትና እድልን ለመጠባበቅ፣ ለአፍ ቁራሽ ዳቦ ለጐንም ማረፊያ የሚሆን ጥግ የግድ ነው፡፡ ግርማ ይህ ሁሉ ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን የለውም፡፡ ስለዚህ ስራ ፈልጐ ለማግኘት አዲስ አበባ ከሌሎች ከተሞች የተሻለች ብትሆንም አዲስ አበባ ለመቆየት የሚችልበት ምንም አይነት ነገር ስለሌለው፣ ወላጆቹ ወዳሉበት ወደ ጐንደር ከተማ መመለስ አንድና የመጨረሻ ግዴታው ነበር፡፡ ይህም የመጨረሻውና ብቸኛው እድሉ ሆኖ እንኳ እንዴትና በምን ልመለስ የሚሉትን ሁለት ጥያቄዎች መመለስ እጅግ አስጨናቂ ነገር ነበር፡፡ በእርግጥም ጐንደር የሚያደርሰው አውቶብስ ትኬት ቆርጦ መሳፈር የሚያስችል ሽራፊ ሳንቲም ለሌለው እንደ ግርማ ላለው አሳዛኝ ምንዱባን ጉዳዩ የምር አስጨናቂ ነበር፡፡ ያኔ ለመሆኑ እንዴት አድርገህ ጐንደር መምጣት ቻልክ ብለው ሲጠይቁት የሚሰጠው መልስ ..በእግዚአብሔር ተአምር.. የሚል ነበር፡፡
እርሱ ተአምር ባለው ሁኔታ ጐንደር ወደ ወላጆቹ በተመለሰ በማግስቱ፣ ከቢሮ ቢሮ እየተዘዋወረ ስራ ለመቀጠር መሯሯጥ ጀመረ፡፡ ግን እንዲህ በቀላሉ አልሆነለትም፡፡ በሠባተኛው ወር ያመለከተበት ስራ ለውድድር ፈተና ተጠራ፣ ፈተናውን ወስዶ አለፈ፡፡ የመጨረሻውን የቃል ፈተና ግን ማለፍ ሳይችል ቀረ፡፡ በዘጠነኛው ወር ላይ ሌላ የቅጥር ፈተና ተፈተነ፡፡ ይህንንም እንደበፊቱ የቃል ፈተናውን አላለፍክም ተብሎ ስራውን ሳያገኝ ቀረ፡ ልክ በአመቱ እንደገና ተፈተነ፡፡ ይህንን ግን መውደቁን ያወቀው ገና በመጀመሪያው ፈተና ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ሶስት የቅጥር ፈተናዎችን መፈተን ቻለ፡፡ አንዱን ራስህን መግለጽ አትችልም በሚል፤ ሁለተኛውን በቂ የስራ ልምድ የለህም በሚል፤ ሶስተኛውን ደግሞ የቋንቋና ነገሮችን የመረዳት ችሎታህ አመርቂ አይደለም ተብሎ ፈተናውን ማለፍ ሳይችል ቀረ፡፡
በዚህ ሁሉ ጊዜ ለግርማ መቋቋም ያልቻለውና ፈተና የሆነበት ስራ ማግኘት አለመቻሉ ሳይሆን ቤት ሙሉ ልጅ ወልጄና አስተምሬ የሚጦረኝ ልጅ ሳላገኝ፣ በችጋር ልሞት ነው የሚለው የአባቱ የጧትና የማታ እሮሯቸውን ማዳመጥ ነበር፡፡
ስራ የማግኘት ተስፋው ከእለት እለት እየተሟጠጠና ተስፋ እየቆረጠ የመጣው ግርማ፣ ከዚህ አስጨናቂ የህይወት ፈተና ለመላቀቅ የመጨረሻ መፍትሔ ነው ብሎ ያመነበት ነገር ይህችን ሀገር ጥሎ የትም መሰደድን ነበር፡፡ እናም ከአመት በላይ ለሆነ ጊዜ ልጆች በማስጠናት ያገኘው ከነበረው መጠነኛ ገንዘብ መቆጠብ የቻለውን ያህል ይዞ ከቀናቶቹ ሁሉ በአንዱ የተረገመ ቀን፣ በመተማ አቋርጦ፣ ደቡብ ሱዳን ጁባ በስደት ገባ፡፡
ጁባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የአረብ ሬስቶራንት ውስጥ በአስተናጋጅነትና በትርፍ ጊዜውም ማስቲካና ሲጋራ መሸጥና ሌሎች ስራዎችን እየሠራ፣ ሶስት የስደተኝነት አመታትን በጂባ ካሳለፈ በኋላ ዋና አላማውን በተቻለው ዘዴ ሁሉ አውሮፓ መግባትን በማድረግ፣ ሰሜን ሱዳንን ሰንጥቆ ወደ ግብጽ ተሻገረ፡፡ ከግብጽ አልጀሪያ፤ ከአልጀሪያ ሊቢያ፤ ከሊቢያ እንደገና ወደ ሞሪታኒያ በማምራት በህገወጥ ሰው አሻጋሪዎች ጀልባ ተሳፍሮ ወደ ካናሪ ደሴት፣ ከዚያም እንደገና የተለየ ተአምር ብሎ በቆጠረው ሁኔታ ህይወቱ የሻርክ ሲሳይ ከመሆን ተርፎ፣ የተመኛትን አውሮፓን ማየትና ስፔን መግባት ቻለ፡፡
ግርማ ስፔን እንደገባ የተሰማው ስሜት ለዘመናት ተሠምቶት የማያውቅ የእፎይታና ከችግር ሁሉ የመገላገል ስሜት ነበር፡፡ ክፋቱ ይህ የእፎይታ ስሜት የቆየው ከሳምንት ላልበለጠ ጊዜ መሆኑ ነበር፡፡ እንዲያ ቀን ከሌት ሲመኛትና የችግሩ ሁሉ መፍቻ ዋና ቁልፍ አድርጐ የቆጠራት አውሮፓዊቷ ሀገር ስፔይን፣ የተቀበለችው እጆቿን ዘርግታ ሳይሆን ከዚህ በተቃራኒው ነበር፡፡ በቀላሉ አገኘዋለሁ ብሎ ተማምኖት የነበረው ስራ እንኳን በቀላሉ ሊገኝ ከጐንደሩ መባዘንም የበለጠ ሆነበት፡፡
እንኳን በሰለጠነበት የኢኮኖሚስትነት ሙያው ይቅርና የሆቴል ቤት ሠሀንና ብርጭቆ ማጠብና ሽንት ቤት የማጽዳት ስራን እንኳ ማግኘት እንደሰማይ የራቀ ሆነበት፡፡
የቀኝ ጨለማ የወደቀበት ግርማ፤ በስፔን ቆይታው ስራ የማግኘት እድሉ ከፀጉርም እንኳ የሠለለች እንደሆነ የተረዳው ከዚህ በፊት ከስደተኞች በቀር ሌሎቹ ስፔናውያን ጨርሰው የማይደፍሩት ለነበረው መናኛ የጉልበት ስራ እንኳ በመቶና በሺ የሚቆጠሩ ስፔናውያን የዲግሪ መአታቸውን ይዘው ሲሟሟቱ ሲያያቸው ነበር፡፡ ከዚያ ስፔንን ለቆ ወደ ፈረንሳይ ተሻገረ፡፡ ፈረንሳይም ለግርማ ከስፔይን ያልተለየች ነበረች፡፡
ከዚህ ሀገር ይሄኛው ይሻላል እየተባለ ሲወራ ወደሰማበት ያለ ህጋዊ የጉዞና የመኖሪያ ፈቃድ እንደተራ ወሮበላ ከባቡር ባቡር እየተሹለከለከ ጣሊያንና ቤልጅየምን አዳረሰ፡፡ እንኳን ስራ ማግኘት ያለ ፖሊስ ማሳደድ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ወንበር ላይ ለማደር እንኳ አዳጋች ሆነበት፡፡
በመጨረሻ ፖርቹጋል ሊዝበን ከተማ ተሻገረ፡፡ ፖርቹጋል የደረሰው ግርማ፤ ሊዝበን ከተማ በሠላም ብትቀበለውና ከፖሊስ የአይጥና የድመት ድብብቆሽ ትንሽ ፋታ ቢያገኝም ለዚህ ሁሉ መንከራተትና እንግልት የዳረገውን ስራ የማግኘት ፍላጐት ሊያሳካ ግን ጨርሶ አልተቻለውም፡፡ የፖርቹጋል የስራ አጡ ቁጥር ከስፔይን ጋር የሚወዳደር ነበር፡፡ በወር ከሶስት መቶ ዩሮ በላይ ለማይከፈልበት ተራ የጉልበት ስራ እንኳ የአመልካቹ ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር ነበር፡፡
ስራ ፍለጋ ከወዲያ ወዲህ ሲንከራተት ለሚያገኛቸው የሱ ቢጤ ስራ ፈላጊዎች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የተመረቀበትን የቢኤ ዲግሪውን ኮፒ ሲያሳያቸው ክው ብሎ እስኪደነግጥ ድረስ ወገባቸውን ይዘው ይስቁበታል፡፡
አንተ በአንድ ቢኤዲግሪ እንዲህ ከሸለልክ እኛስ ይህን ሁሉ ይዘን ምን እንበል እያሉ የያዙትን ሁለትና ሶስት ማስተርስ ዲግሪ እያሳዩ ያላግጡበታል፡፡
ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ግርማ በየእለቱ ስራ ፍለጋ መንከራተቱን አላቋረጠም፡፡ ለዚያውም ያለምንም ህጋዊ የስራና የመኖሪያ ፈቃድ፡፡
ዛሬ ያለችው አውሮፓ እኛም ሆነ የተቀረው አለም ትናንት እናውቃት ከነበረችው አውሮፓ በእጅጉ የተለየች ሆናለች፡፡ ትልቁም ችግር ይሄው ነው፡፡ የብልጽግናና የመልካም ነገሮች ቤት የነበረችው አውሮፓ፤ ዛሬ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ተወጥራ የተያዘች ሆናለች፡፡ እንደ ግርማ አይነቱ አሳዛኝ ስደተኛ ያላወቀው እውነትም ይህ ነው፡፡ ግርማም ሆነ የሱ ቢጤ ሌላው ያሉበትን ሁኔታ በበለጠ እንዲረዱ የሃያ ዘጠኝ አመቷን ባለ አረንዴ አይን ለግላጋ ፖርቹጋላዊ ወጣት ናታሊሮ ሳንቶስን ቢያገኟት፣ አዱኛ ብላሽ እያለ ያገሬ ሰው እንደሚተርተው የአለምም ሆነ የአውሮፓ ነገር የተገላቢጦሽ እንደሆነ መረዳት በቻሉ ነበር፡፡
እንደ ግርማ ሁሉ ናታሊያ ሳንቶስ፤ የሙሉ ሰአት ስራ ለማግኘት በድፍን ፖርቹጋል ተንከራታለች፡፡ በፓርቶ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ናታሊያ ሳንቶስ በሙያዋ መምህር ስትሆን ላለፉት ስድስት አመታት ስራ በመፈለግ ፍዳዋን አይታለች፡፡ የተሟላ መረጃና የስራ ልምድ ያላት ናታሊያ ባለፉት ስድስት አመታት ለሶስት መቶ ስልሳ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመምህርነት እንዲቀጥሯት ብታመለክትም ስራ ማግኘት የቻለችው ከዘጠኝ ወር ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ የመምህርነት ስራ ማግኘት እንደ ሰማይ የራቀባት ናታሊያ፤ ኑሮዋን ለመደገፍ ሌላ አማራጭ ስላልነበራት በወር አምስት መቶ ዩሮ የሚያስገኝ የአጭር ጊዜ ስራዎችን ለመስራትም ከሌሎች ስራ ፈላጊ ያገሯ ሰዎች ጋር ግብግቧን ገጥማለች፡፡ ይህንንም የምታገኘው እጅግ እድለኛ በሆነችበት ቀን ብቻ ነበር፡፡ ለአውሮፓዊ እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ በሃያ ዘጠኝ አመቷ እንደሷው ስራ አጥ ከሆኑት ወላጆቿ ጋር የምትኖረው ናታሊያ፤ የኑሮውን ቀንበር በመጠኑም እንኳ ለመቋቋም እንዲያስችላቸው በሚል በጓሯቸው የተከሉትን አትክልት በመንከባከብ ታግዛቸዋለች፡፡
ያለስራ ቦዝኖ መቀመጡና ስራ ፍለጋ መንከራተቱ ያስመረራት ናታሊያ፤ ቢጨንቃት ለአንድ አመት ከምግብና ከመጠለያ በቀር ቤሳ ሳንቲም የማይከፈልበትን የበጐ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ወደ ፖላንድ ሄዳ አንድ አመት አሳልፋ ተመልሳለች፡፡
ይህን ያደረገችው በፖላንድ ያገኘችው የስራ ልምድ በሀገሯ ፖርቹጋል ሊያግዘኝ ይችላል በሚል ተስፋ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡
ኢትዮጵያዊው ግርማ ስራ ፍለጋ ከሀገር ሀገር እየዞረ እንደተንከራተተው ሁሉ ናታሊያም ከፖላንድ መልስ ወደ አየር ላንድ በመጓዝ ስራ ለመፈለግ ሞክራ ነበር፡፡ እንደ ክፉ አጋጣሚ ሆነና ገና እግሯ እንደረገጠ የአየርላንድ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ እናም ስራ ማግኘት እንኳንስ ለመጤዋ ፖርቹጋላዊት ለአየርላንድ ዜጐችም ጭንቅ ሆነ፡፡
በዚህ ሁሉ የህይወት ውጣውረድ ክፉኛ የተንገላታችው ናታሊያ፤ ጨርሶ ተስፋ ሳትቆርጥ ዩኒቨርሲቲ ተመልሳ በመግባት የልዩ ፍላጐት ተማሪዎች አስተማሪ ለመሆን ስልጠና ወስዳ ተመረቀች፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ፖርቹጋል በገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ የሀገሪቱ የትምህርት በጀት በከፍተኛ መጠን በመቀነሱ በትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጐት መምህራን ቁጥር ከአምስት ወደ አንድ ዝቅ እንዲል አስገደደ፡፡ ይህ ሁኔታ እንደ ናታሊያ ላሉት ተጨማሪ ቦታ ሊያስገኝ ይቅርና የነበሩትንም በመቀነስ ተጨማሪ መምህራን የስራ አጡን ቁጥር እንዲቀላቀሉ አስገደደ፡፡ ናታሊያንም በዚህ ዘርፍ የሞከረችው ሙከራ ፍሬቢስ ሆኖ ቀረ፡፡
ይህ ሁኔታ እጅግ ያናደዳት ናታሊያ ..ጨርሶ ተስፋ አልቆርጥም ሌላ ዘዴ እሞክራለሁ እንጂ.. ትላለች፡፡ በልቧ የወጠነችው ሌላ ዘዴ ግን የተለየ ነገር ሳይሆን ልክ ኢትዮጵያዊው ግርማ በመጨረሻ እንደ መፍትሔ እንዳስበው ሀገሯን ጥላ መሰደድን ነው፡፡.. አንዱ ሀገር ተሰድጄ የእድሌን እሞክራለሁ እንጂ እዚሁ ቁጭ ብዬ ሀገሬ ፖርቹጋል ገና የምትሰጠኝን አልጠበቅም ብላለች ናታሊያ፡፡ ሌሎችም የሚያስቡት እንዲሁ ነው፡፡
የናታሊያና የመሰሎቿን ስደት አስገራሚና የተለየ የሚያደርገው ነገር ታዲያ ለስደት የመረጡት ሀገር ነው፡፡ እነዚህ አውሮፓዊ ዜጐች ለስደት የመረጡት ሀገር ሌላ የአውሮፓ ወይም የአሜሪካ ሀገራትን ሳይሆን የቀድሞ የቅኝ ግዛታቸው ወደሆኑት የላቲን አሜሪካና አፍሪካ ሀገራትን ነው፡፡
ፖርቹጋላዊታ ስራ አጥ ናታሊያ ሳንቶስ፤ በሀገሯ በፖርቹጋል ለአመታት ባዝና ያጣችውን ስራ ፍለጋ ለመሰደድ እየተዘጋጀች ያለችው ወደ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛምቢክ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ወደ አንጐላና ብራዚል፡፡
ኢትዮጵያዊው ግርማ ለዚህ ሁሉ እንግልትና ስደት የዳረገውን ምክንያት አልተናገረም፡፡ ፖርቹጋላዊቷ ናታሊያ ግን ከሀገሯ ባንኮች የሌለውን እየተበደረ ገንዘቡን እንዳሻው ሲበትነው ከኖረው የሀገሯ መንግስት ራስ አልወርድም ትላለች፡፡ እናም እኔ ምንም ሚና ሳይኖረኝ ባንኮችና መንግስት በፈጠሩት ችግር አለአግባብ ከምቀጣ፣ ቤተሰብ ጓደኛ፣ ሀገር ባህል፤ ምናምን እያልኩ ጣጣ ሳላበዛ ወደ ሞዛምቢክ ተሠድጄ እዚያ የእድሌን እሞክራለሁ ብላ ታጥቃና ቆርጣ ተነስታለች፡፡
ወደ አውሮፓ ለመሰደድ እንደ ግርማ የቆረጡ ስንት ኢትዮጵያውያን እንዳሉ በእርግጠኝነት አላውቅም፡፡ ወደ ቀድሞ የቅኝ ግዛቶቻቸው ሀገር ወደ ሞዛምቢክ ብራዚልና አንጐላ ለመሰደድ የቆረጡ በርካታ ፖርቹጋላውያን እንዳሉ ግን አውቃለሁ፡፡ በፖርቹጋል የሚገኘው የብራዚል የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ የ60.000 ፖርቹጋላዊ ስራ ፈላጊዎችን የቪዛ ማመልከቻ ተቀብሏል፡፡ የአንጐላ ኤምባሲ ደግሞ የ23.787 ፖርቹጋላውያንN የቪዛ ማመልከቻ ተቀብሏል፡፡ አብዛኞቹ አመልካቾች አንድና ከአንድ በላይ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ አንድ ሲቪል መሀንዲስ በፖርቹጋል የወር ደመወዙ 900 ዩሮ ነው፡፡ በአንጐላ ግን አራት እጥፍ ማግኘት ይችላል፡፡ እንግዲህ እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ እያየነው ያለውም በፊት በፊት ጨርሶ ሊሆን የማይመስለንን ነገር ነው፡፡ ለሁሉም ግን መልካም አዲስ አመት ይሁንላችሁ፡፡

 

Read 4071 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:32