Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 September 2011 13:03

አዲሱ የኦባማ ሚስጢራዊ ጦርነት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ኦሳማ ቢላደን በፓኪስታን አቡታባድ በተባለው ቦታ በአሜሪካ ልዩ ኮማንዶዎችከተገደለ በኋላ፣ አሜሪካ በየመንና በሶማሊያ የሚገኙ የአልቃይዳ ቡድኖችላይ በተመሳሳይ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቢላደን ላይ ያገኙትን ስኬት በሌሎች የአልቃይዳ አባላትም ላይ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ ኃይሎች ሚስጢራዊ በሆነ የተራቀቀ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ልውውጥ በመታገዝ፣ የአልቃይዳን አከርካሪ ለመስበር በኤደን ባህረ ሰላጤ ኮሽታው የማይሰማ ጦርነት እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ “Obama’s New Secret War” በሚል ርዕስ The Middle East የተባለው መጽሔት ባቀረበው ዘገባ፣ በኦባማ የበላይነት የሚመራው ጦርነት፣ ምንም ዓይነት የጦርነት ነጋሪት ሳይመታ በልዩ ኮማንዶዎችና ሰው አልባ በሆኑ የጦር አውሮፕላኖች (unmanned ariel vehicle) የሚደረግ ሲሆን፣ ፍንጭ ሳይተው የሚፈልጉትን የአልቃይዳ አባል በማጥመድ ግድያ ይፈጽማሉ፡፡

በአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ጂምሎቢ ..ዋሽንግተን በአልቃይዳ ላይ የምትወስደውን እርምጃ ቀይራለች፡፡ ለአሜሪካ ስጋት ናቸው በማለት የፈረጀቻቸውን የተለያዩ የአልቃይዳ ክንፎች የማደን ተግባሯን እጅግ ጨምራለች.. ብለዋል፡፡
ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ የዚህ ዓይነቱ ጥቃት በሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች የተካሄደ ሲሆን፣ ይኸውም በፓኪስታን፣ አፍጋኒስታን፣ በኢራቅ እና በሊቢያ አየር ላይ በተደጋጋሚ በማንዣበብ የሚፈልጉትን ኢላማ መትተዋል፡፡ ልዩ ኮማንዶዎቹም ሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ በሚወስዱት ምስጢራዊ ጦርነት ጥቃት ለተገደለው የአልቃይዳ አባል ኃላፊነት አይወስዱም፡፡
በየመን ሰንዓ የሚገኙ የደህንነት ባለሥልጣናት ሲናገሩ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ ኮሽታ የማያሰሙ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች በሰንዓ ሰማይ ላይ በማንዣበብ በምስራቅ ሰንዓ የሚገኘውን ሻባዊ የተባለውን የነዳጅ ቦታ የጥቃት ኢላማ በማድረግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ የደህንነት ባለሥልጣናቱ አክለውም ሲጠቅሱ፣ በሰኔ ወር 18 የሚደርሱ ጥቃቶች የተካሄዱ ሲሆን 140 ሰው ተገድሏል ብለዋል፡፡ ከ18 ጥቃቶች ውስጥም ስድስቱ የተካሄደው አልቃይዳ ተስፋፍቶበታል በሚባለው በአረቢያን ባህር በስተደቡብ በሚገኘው በአባያን አውራጃ አካባቢ ሲሆን፣ ይህም በየመንና በሳውዲ አረቢያ ድንበር መካከል የሚገኘው የአረቢያን ፔኔንሱላ የአልቃይዳ ዋነኛው ቡድን (AIQaeda in the Arabian peninsula) ላይ ነው፡፡
ባለፈው ሚያዚያ ወር በኦባማ የሚመራው ልዩ ኮማንዶ ጦር የአልቃይዳ ዋነኛ መሪ በነበረው ኦሳማ ቢንላደን ላይ እርምጃ በመውሰድ ከፓኪስታን የደህንነት ባለሥልጣናት ምንም መረጃ ሳያገኝ ግዳጁን ተወጥቷል፡፡ የፓኪስታን መንግሥትም ሆነ የደህንነት ባለሥልጣናቱ ልዩ ኮማንዶ ኃይሎቹ ቢላደንን ገድለው እስኪወጡ ድረስ ምንም ፍንጭ አለማግኘታቸው ሚስጢራዊ ጦርነቱ እጅግ በተራቀቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መካሄዱ የሚጠቁም ነው፡፡
ይሁን እንጂ ቢላደን በፓኪስታን ከተገደለ በኋላ፣ ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል በማለት ፓኪስታን በአሜሪካ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ያቀረበች ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ፓኪስታናውያንም ቁጣቸውን በአሜሪካ ላይ ገልዋል፡፡ ..ሞት ለአሜሪካን! ቢላደን ሰማዕት ነው! ቢላደን ቢሞትም ሺህ ቢላደኖች አለን!.. የሚሉ መፈክሮችን በአደባባይ ይዘው ወጥተዋል፡፡ ዋሽንግተን አሁንም በእነዚህ አገራት እየወሰደች ያላቸው እርምጃ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንደሚያስነሳበት ብታውቅም የራሷን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ የሚበልጥ ነገር እንደሌለ አምናለች፡፡ በሌላ በኩል ባላት ወታደራዊ የበላይነት ያሻትን እያደረገች እንደሆነም አንዳንድ ዓለም አቀፍ ፖለቲከኞች እየገለ ነው፡፡
በዚህ ሚስጢራዊ ጦርነት ልክ ቢላደን ሲገደል የፓኪስታን የደህንነት ኃይሎች መረጃ እንደሌላቸው ሁሉ በሌሎች አገሮች የሚገኙ የደህንነት ኃይሎች መረጃ ሊያገኙ በማይችሉበት ሁኔታ ነው የሚካሄደው፡፡
አሜሪካ በሽብርተኝነት ላይ አዲስ ሚስጢራዊ ዘመቻ ለመክፈት የተገደደችው፣ የኦባማ አስተዳደር ወደ ኋይት ሀውስ ሲገባ፣ አገሪቱ ከገባችበት ማንኛውም ጦርነት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትወጣለች በሚል ቃል ኪዳን በመሆኑ፣ የአሁኑ ሚስጢራዊ ጦርነት ባህርይ፣ ምንም ዓይነት የኮንግረስ ጫናዎችና ክልከላዎች እንዳይኖር በማድረግ ፕሬዝዳንቱ በነጻነት ውሳኔ የመስጠት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የሚያካሂዱት ነው በማለት ጂን ግላሰር የተባሉ Panti-Klar.com የተባለ ድረገ ተንታኝ ገልፀዋል፡፡
ጂን ግላሰር ሲቀጥሉ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በቀጣዮቹ አመታት በብሔራዊ ፀጥታ ፖሊሲዋ ቅድሚያ የምትሰጠው፣ በውስጣዊ የፖለቲካ ምስቅልቅል የገቡት የአረብ አገራት ለሽብርተኝነት መፈልፈያነት ያላቸው አመቺነት እየጨመረ ስለሚሄድ በአካባቢው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታለች፡፡ ለምሳሌ ሽብርተኞች የመንን ከሁሉም አገሮች በተሻለ ሁኔታ ራሳቸውን ለማደራጀትና በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የምትመች አገር አድርገው ቆጥረዋታል በማለት ጂን ግላሰር ትንታኔያቸውን አቅርበዋል፡፡
በቡሽ አስተዳደር ዘመን በየመን የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ኤድመን ሃል፤ ..በአረቢያን ፔኔንሱላ የሚገኙትን የአልቃይዳ ኃይሎች ለማኮላሸት የአየር ጥቃት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ የበቀል እርምጃ ወደ ራሳችን እያመጣን እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን.. ብለዋል፡፡
እንደ ኦባማ አስተዳደር እምነት በአረቢያን ፔኔንሱላ የሚገኘው ዋነኛው የአልቃይዳ ቡድን ከሌሎች ጂሃዲስቶች በበለጠ በአሜሪካ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ያደርሳል የሚል ነው፡፡ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ ላይ ከተነጣጠሩ ሦስት ጥቃቶች በስተጀርባ በአረቢያን ፔኔንሱላ የሚገኘው አልቃይዳ ያደራጀው ነው፡፡
በህዳር 2009 ሜጀር ኒዳል ማሊክ ሃሰን የተባለ አሜሪካዊ ሙስሊም ወታደራዊ ሳይካትሪስት በቴክሳስ ፎርት ሁድ ውስጥ 13 ወታደሮችን ገድሏል፡፡ እንደገና ከአንድ ወር በኋላ አንድ ናይጄሪያዊ ሙስሊም በዲትሮይት አየር መንገድ ውስጥ የመንገደኞች አውሮፕላን ሊያጋይ ሲል በፀጥታ ኃይሎች ተደርሶበት ተይዟል፡፡ በጥቅምት 2010 በኮምፒውተር ፕሪንተር ቀለም መያዣ ውስጥ ሁለት የሚፈነዱ የታሸጉ ጥቅሎች ባለቤትነታቸው የአሜሪካ በሆኑ UPS እና FDX በተባሉ ዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት አውሮፕላኖች ውስጥ ሲላኩ፣ በብሪታኒያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የደህንነት ኃይሎች ተይዟል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የሽብር ተግባሮች በስተጀርባ ያለው ደግሞ በአረቢያን ፔኔንሱላ የሚገኘው አልቃይዳ እንደሆነ ዋሽንግተን ደርሳበታለች፡፡
በቀጣይ ከሽብርተኝነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የመን ያላት ሚና የላቀ ነው፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በለውጥ ፈላጊዎች ተቃውሞ መረጋጋት የጠፋባት አገር ሆናለች፡፡ የመንን ለ32 ዓመታት በበላይነት ሲመሩ የነበሩት አሊ አብደላህ ሳላ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተነሳባቸው በኋላ ስልጣናቸውን ላለመልቀቅ አስር አይነት ነገር ሲቀባጥሩ በመጨረሻ ጭንቅላታቸውና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመትተዋል፡፡ ከመስከረም 11/2001 የአሜሪካ ጥቃት በኋላ የመን የአልቃይዳ መፈንጫ እንደሆነች የተረዳችው አሜሪካ፣ ለአብደላህ ሳላህ በየዓመቱ 60 ሚሊዮን ዶላር የመደበች ቢሆንም የአብደላህ ሳላህ አስተዳደር አልቃይዳን ከየመን ሊያጠፋ አልቻለም፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላም አሜሪካ በስፈራው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አሰማርታለች፡፡ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖቹ በቀዳሚነት በሚስጢራዊ መንገድ የአልቃይዳን ታጣቂዎች ለመምታት ሲንቀሳቀሱ፣ አገሪቷ በአንድ ሰው አገዛዝ ሥር መሆንዋንም ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በአረቢያን ፔኔንሱላ የሚገኘው የአልቃይዳ ቡድን እና በሶማሊያ የሚገኘው አልሸባብ አል-ኢስላሚያ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መሄዱን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ ቡድን፣ በሚያዚያ ወር ከአሜሪካ ኢንተሌጄንስ ኤጀንሲ (ሲ.አይ.ኤ) ካገኘው መረጃ በመነሳት፣ ከፍተኛ የአልሸባብ አመራርን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ችሏል፡፡
አህመድ አብዱልቃድር ዋርሴም ተብሎ የሚጠራው የአልሸባብ አመራር የተያዘው ከየመን ወደ ሶማሊያ በጀልባ ለመሻገር እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት፣ የተያዘው የአልሸባብ አመራር፣ በዋነኛነት አልሸባብን ከአረቢያን ፔኔንሱላው አልቃይዳ ቡድን ጋር ለተፈጠረው ግንኙነት ትልቁን ሚና እንደተጫወተ አረጋግጠዋል፡፡ በሌላም በኩል ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አልቃይዳ በየመን ከሚገኙ ጂሃዲስት ታጣቂዎች፣ ከአልሸባብ ጋር ያላቸውን ጥምረት በማጠናከር ከሶማሊያ ውጭ በተለይም በአሜሪካ ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ለማካሄድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ነው፡፡
የምዕራባዊያንና የሳውዲ አረቢያ የደህንነት ተቋማት፣ በአልቃይዳና በአልሻባብ መካከል የተፈጠረው ጥምረት ዋና አላማው ቀይ ባህርን እና ሕንድ ውቅያኖስን የሚያገናኘውን ባብ አል ማንዴብ የተባለውን ዋነኛ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ መስመርን ለመቆጣጠር እንደሆነ ቢገለም፣ ብዙዎች የሽብርተኞቹን ውጥን የማይጨበጥ ቅዠት ነው ብለውታል፡፡
በሌላ በኩል የሁለቱ ቡድኖች ጥምረት የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅና የአለም ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች በሆነችው በሳውዲ አረቢያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአረቢያን ፔኔንሱላው አልቃይዳ የተመሰረተው በጥር 2009 ዓ.ም ሲሆን፣ በወቅቱ በሳውዲ አረቢያ የሚገኘው የአልቃይዳ ክንፍ በሳውዲ ንጉሳዊ መንግስት ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በተከፈተበት የፀረ-ሽብርተኝነት ኦፕሬሽን ከተዳከመ በኋላ፣ ከየመኑ ቡድን ጋር ውህደት በመፍጠር የአረቢያን ፔኔንሱላው አልቃይዳ እውን ሊሆን ችሏል፡፡
በየመን አልቃይዳ አሁን ባለው ሁኔታ ከመደራጀቱ በፊትም ቢሆን ኦሳማ ቢላደን ያደርግ ለነበረው ዓለም አቀፍ ጥቃት ዋነኛ ማዕከል በመሆን አገልግላለች፡፡
እ.ኤ.አ ከ1979-89 ዓ.ም አፍጋኒስታን በወረሩት በቀድሞ የሶቭየት ኃይሎችና በአፍጋን ሙጃሃዲኖች መካከል በተካሄደ ውጊያ ሙጅሃዲኖችን ለማገዝ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመናዊያን ወደ አፍጋኒስታን በፈቃደኝነት ሄደው ነበር፡፡ ሶቭየቶች ተሸንፈው አፍጋኒስታን ነፃ ከወጣች በኋላ ወደ አገራቸው ከተመለሱት የመናዊያን የተወሰኑት በመንግስት ጦር ውስጥ ሲቀላቀሉ፣ አብዛኞቹ ግን ጂሃዲስቶች ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ቢላደን ከሙጂሃዲኖች ጋር በመሆን የሶቭየትን ጦር ከተዋጋ በኋላ ወደ የመን ተመልሷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይም ኦሳማ ቢላደን የመናዊያን የሚበዙበትን የጂሃዲስቶች ቡድን በማደራጀት፣ በደቡብ ሰንዓ ወደብ በሚገኙት የአሜሪካ ወታደሮች ላይ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም የመጀመሪያውን ጥቃት አካሄደ፡፡ ከዚያም የጂሃዲስ እንቅስቃሴውን እያስፋፋ በመምጣት እ.ኤ.አ በ1998 ዓ.ም የቀድሞ ጂሃዲስት ወዳጆቹን በማሰባሰብ አልቃይዳን አቋቋመ፡፡
በዚያው ዓመትም በኬኒያና በታንዛኒያ በሚገኙት የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት በማድረስ በርካቶች ለሞት ዳርጓል፡፡ ኦሳማ ቢላደን የሳውዲ ዜግነት ያለው ቢሆንም፣ የዘረ ሃረጉ የመጣው ግን ከየመን ነው፡፡ ቢላደን ቢሞትም በርካታ የመናዊያን የእርሱን ዱካ ተከትለዋል፡፡
በአረቡ ዓለም የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በየመን ውስጥ የበለጠ ሊጠናከሩ ይችላሉ የምትለው አሜሪካ፣ በተለይም የአሊ አብደላህ ሳላህ አስተዳደር መንገዳገድ የመንን የሽብርተኞች ወፈንጫ ሊያደርጋት ይችላል የሚል ግምት አላት፡፡ አሊ አብደላህ ሳላህ በጥይት ከተመቱ በኋላ በሳውዲ ሕክምና ያገኙ ቢሆንም፣ ፊታቸውን ጨምሮ 40 በመቶ የሚሆነው የሰውነታቸው ክፍል መቃጠሉን የሳውዲ አረቢያ ዶክተሮች ገልፀዋል፡፡ ፊታቸውም ጥላሸት ለብሷል፡፡ አብደላህ ሳላህ አልቃይዳን ለመዋጋት በየዓመቱ ከአሜሪካ በሚያገኙት ገንዘብ የምዕራባዊያን ደጋፊ እንደሆኑ ቢገለጽም፣ አንዳንዴም በሚያራምዱት ፀረ-ምዕራባዊ አቋም ምክንያት ባለ መንታ ልብ እንደሆኑ አንዳንድ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች ይገልቸዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ እርሳቸው የሳውዲ ሕክምናቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና ስልጣን ለመያዝ ወደ የመን መመለሳቸውን ለአረቢያን ፔንሱላው አልቃይዳ አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይሆናል በማለት ዩናይትድ ስቴስትና ሳውዲ አረቢያ ተቃውመዋል፡፡
በ2009 በየመንና በሳውዲ አረቢያ ድንበር ላይ የአረቢያን ፔኔንሱላው አልቃይዳ ከተደራጀ ከወራት በኋላ አሜሪካ በጂሃዲስቶች ላይ ሚስጢራዊ ጦርነት የጀመረች ሲሆን፣ ለዚህ ተግባር ያቋቋመችው የመጀመሪያው የፀረ-ሽብርተኝነት ተቋምም |US Joint  Special Operation command´ የተባለውና ከሲ.አይ.ኤ መረጃ እየሰበሰበ በክሩዝ ሚሳየልና ሰው b¸nù የጦር አውሮፕላኖች የሚደረግ ጥቃት ነበር፡፡ በዚህም ኦፕሬሽን ቢላደን ሰለባ ሊሆን ችሏል፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ወራቶች ወዲህ ሲ.አይ.ኤ በሠራዊቱ ውስጥ ያሉትን የራሱን ካድሬዎች (Paramilitar Cadres) በየመን ውስጥ ለተከፈተው የፀረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ መረጃ እንዲያሰባስቡ አንቀሳቅሷል፡፡ ሲ.አይ.ኤ ከዚህ በፊት ፓኪስታን ውስጥ በተከፈተው ዘመቻ 1400 አክራሪ ሙስሊም ታጣቂዎችን ለመደምሰስ ከቻለበት ኦፕሬሽን ጋር በሚመሳሰል በሰው አልባ የጦር ጄቶችና በወታደራዊ ጥቃቶች የሚካሄደው ዘመቻ ውጤታማነቱ ስለታመነበት በድጋሚ ይህንኑ በየመን ግንባርም የማካሄድ ዕቅድ ይዟል፡፡
ሲ.አይ.ኤ በሚስጢራዊነት በሚያካሂደው የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ዋናው የመጫወቻ ህጉ በተለይ ከአሜሪካ የጦር ኃይሎች መለያ ባህርይ አንፃር ሲታይ እጅግ የላቀ ነው፡፡
የአሜሪካ የጦር ጀቶች በየመን የሚያካሂዱት ድብደባ እንዲቆም የተደረገው ከአንድ አመት በፊት ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ የስለላ መረጃውን ተከትሎ በተፈፀመው የአየር ድብደባ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን በመገደላቸው ነው፡፡ በወቅቱ የፕሬዚዳንት አብዱላህ ሳላህ የቅርብ ሠው እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአውራጃ ገዢ ሳይቀሩ በድብደባው ተገድለዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴስት ሽብርተኞችን ለማጥፋት እጅግ የላቀ የስለላና የቴክኖሎጂ ጦርነት ብትከፍትም ሽብርተኞችም በዚያው መጠን እየተራቀቁና እየመጠቁ በመምጣት አዳዲስ የሽብርተኝነት ጥቃት እየከፈቱ እንደሆነ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡
በአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ (FBI) እስካሁን በበረራዎች ላይ ሊደረጉ ስለታቀዱት ጥቃቶች የደረሰው መረጃ አለመኖሩን ቢገልጽም፣ ሽብርተኞች ፊታቸውን ወደ አቪየሽን ኢንዱስትሪ ሊያዞሩ ስለሚችሉ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብሏል፡፡ በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የሚገኙ አየር ማረፊያዎች፣ በአሜሪካ እንደሚገኙት አየር ማረፊያዎች የመንገደኞችን ሙሉ የሰውነት አካል ሊያሳዩ የሚችሉ ስካነር የሌላቸው ናቸው፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚገልት ሽብርተኞች ሊጠቀሙ ያሰቡት በሠውነት ውስጥ የሚቀበረው ፈንጂ፣ ሣይንሳዊ መጠሪያው Pentaery thrital tetranit rate (PETN) የተባለው ሊሆን እንደሚችል ተገልል፡፡ ይህ ፈንጂ በተለይ በሠዎች የሆድ እቃ፣ ጀርባና ጡት ውስጥ በመለስተኛ ቀዶ ሕክምና ሊቀበር የሚችል ነው ተብሏል፡፡
አንድ አጥፍቶ ጠፊ በሠውነቱ ውስጥ ፈንጂ ከተገጠመለት በኋላ ወዲያው ቢንቀሳቀስ በአለማችን ላይ በሚገኙ በርካታ አየር ማረፊያዎች ውስጥ የሚገኙ የመመርመሪያ ስካነሮች በሰውነት ውስጥ የተገጠመን ፈንጂ ለመለየት የሚያዳግታቸው ናቸው፡፡
በሰውነት ውስጥ የተቀበረው ፈንጂ እንዲፈነዳ የሚደረገው በመርፌ በሚሰጥ መድሃኒት አማካኝነት ነው፡፡
አሜሪካ አዲስ በጀመረችው ሚስጢራዊ ጦርነት በርካታ የአልቃይዳ አባላትን ማደን እንደሚቻል ብትገልጽም በሌላ በኩል ደግሞ ንፁሃን ዜጎችን በመፍጀት ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አደገኛ ክስተት እንዳይፈፀምና አጠቃላይ የፖለቲካ ውጥንቅጥ እንዳይፈጠር ተሰግቷል፡፡
አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በየመን ሚስጢራዊ ወታደራዊ ጦርነት በማድረግ ላይ ብትገኝም በየመን የተፈጠረውን ፖለቲካ ቀውሱን ተከትሎ የአረቢያን ፔነኔሱላው አልቃይዳ በአገሪቱ ደቡባዊ ግዛት መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡ በመጋቢት መጨረሻ ጃአር የተባለችውን ከተማ በቁጥጥር ስር አድርጓል፡፡
ከዚያም በግንቦት መጨረሻ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የደቡባዊውን ከተማ የሆነችውን ዚን ጂባርን በቁጥጥራቸው ስር ሊያደርጉ ችለዋል፡፡
በተጨማሪም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚታመኑ የታጠቁ የጎሳ መሪዎች ከዋናው ከተማ ሰነዓ በስተደቡብ 150 ማይልስ ርቀት ላይ የምትገኘውን ታይዝ የተባለች የየመን ሁለተኛ ከተማን በሰኔ መጀመሪያ በከፊል በቁጥጥር ስር አድርገዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች አገላለ፤ አሜሪካ አሁን እየወሰደች ያለው የፀረ ሽብር ዘመቻ ውጤታማ ቢመስልም ሁኔታው ሽብርተኞቹ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ዜጐች ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ የሚያነሳሷቸው ከመሆኑም በላይ ዓለም አቀፍ ቀውስን የሚያባብስ ይሆናል፡፡

Read 10059 times