Print this page
Saturday, 03 September 2011 12:28

.ፍቅር አነሰኝ. . ... ወይስ ..ሥልጣን አነሰኝ.....?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)
  • የአፍሪካ አምባገነኖች ..እትት በረደን. . ... እያሉ ነው

..ስንዴ ዳቦ ጋገርኩ በጨረቃ ፍም
በልቼ ላልበላ አወጡልኝ ስም..
(የጋዳፊ እንጉርጉሮ)
አንጋፋዋ የአገራችን አቀንቃኝ አስቴር አወቀ ደስ ባይላትም በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች በእሷ ዜማዎች እየቆዘሙና እያንጐራጐሩ ነው ተብሏል፡፡ አይገርምም የፍቅር ዜማዎች በአምባገነኖች ሲወደድና ሲደነቅ፡፡ ለነገሩ አምባገነኖቹ ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡም ያለ አስቱ ዘፈኖች አንሰማም ብሎ አሻፈረኝ ብሏል አሉ፡፡ ሆኖም  ጋዜጣው ወደ ማተምያ ቤት እስከገባበት የመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በትክክል ምክንያታቸውን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደነገሩኝ ግን የድምፃዊቷ ዜማ ውስጣዊ ስሜታችንን ይገልልናል ባዮች ናቸው፡፡ እኔማ ነገሩ አልዋጥልህ ብሎኝ ብዙ ሳወጣና ሳወርድ ሰንብቻለሁ፡፡

አምባገነኖች ፍቅር ይገባቸዋል እንዴ? ሥልጣን እንጂ! ለነገሩ በምዕራብ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የህዝብ አመ ከተቀሰቀሰና አምባገነን መሪዎች በስጋት እንቅልፍ ማጣት ከጀመሩ በኋላ በአፍሪካ ብዙ ነገሮች ተመሰቃቅለዋል እየተባለ ነው፡፡ መሪዎቹ የፍቅርና የፖለቲካ ዜማዎችን መለየት ተስኗቸዋል፡፡
የህዝብ አመ ስጋት በቤተመንግስታቸው ላይ ካረበበባቸው አምባገነኖች አብዛኞቹ ..እትትት . . . አልቻልኩም ብርዱን . . ... የሚለውን የአስቱን ዜማ እየኮመኮሙ ነው ተብሏል፡፡ እንደ ሶሪያና የመን ባሉት አገራት የሚገኙ አምባገነን መሪዎች ደግሞ ..ተኝቼ ላልተኛ መባነኑ ባሰኝ.. የሚል ስንኝ የሚገኝበትን የድምፃዊቷን ዘፈን እያዳመጡ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥ ስንኙ ወደ ጆሮአቸው ሲደርስ ..ገዝቼ ላልገዛ መሳቀቁ ባሰኝ.. ወደሚል እንደሚቀየር ታውቋል፡፡ እምጥ ይግቡ ስምጥ ያልታወቁት የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ከሚወዱት ህዝባቸው የመለየታቸው ነገር ያስከተለባቸውን የልብ ስብራት የሚገልጽ የመሰላቸውን የአስቱ ዜማ እተደበቁበት ሆነው እያንጐራጐሩ ነው ተብሏል - ..መለያየት እኔን ጐዳኝ ብቸኝነቱ.. እያሉ ነው ሌት ተቀን፡፡ ጋዳፊ በተለያዩ አገራት ባንኮች ፍሪዝ የተደረገው 150 ቢሊዮን ዶላርና ከቤተመንግስታቸው ስር የደበቁት ለ4ሚ. ህዝብ የሚበቃ እህል ትዝ ሲላቸው ደግሞ ..ስንዴ ዳቦ ጋገርኩ በጨረቃ ፍም/ በልቼ ላልበላው አወጡልኝ ስም.. የሚለውን ስንኝ እየደጋገሙ እንደሚያዜሙ የትሪፖሊ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ሌላው የአምባገነን መሪዎች ተወዳጅ ዜማ ..ፍቅር አነሰኝ.. የሚለው የድምፃዊቷ ዜማ ሲሆን ..ፍቅር አነሰኝ፤ መውደድ አነሰኝ፤ ናፍቆት አነሰኝ፤ ትዝታ አነሰኝ፤.. የሚሉትን ስንኞች ..ሥልጣን አነሰኝ፤ መግዛት አነሰኝ፤ መግደል አነሰኝ፤ ማሰር አነሰኝ.. በሚል እየቀየሩ እንደጉድ እያቀነቀኑት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ በተለይ ህዝባቸው ከሥልጣን እንዲወርዱ እየወተወቱአቸው ያሉ መሪዎች ..ፍቅር አነሰኝ.. የምትለዋ ዜማ ተመችታቸዋለች፡፡  ነገርዬዋ ግን ..ፍቅር አነሰኝ.. ሳይሆን ..ሥልጣን አነሰኝ.. ለማለት ነው (ሥልጣን አልጠገብኩም ለማለት) በቅርቡ አመ እንቀሰቅሳለን የምትሉ ከሆነ እገድላችኋለሁ፤ ማንም አያድናችሁም ሲሉ የአገራቸውን ህዝብ በማን አለብኝነት ያስጠነቀቁት የጋምቢያው መሪ ዓይነት ደግሞ ከድምፃዊቷ ..ሰበቡ.. የተሰኘ ዜማ ውስጥ ..ያንቀጠቅጠኛል ብርቱ ዛር አለብኝ/ የምወደውን ልጅ ሌላ ሲነካብኝ.. የሚሉትን ስንኞች በመውሰድ ..ያንቀጠቅጠኛል ብርቱ ዛር አለብኝ የምገዛውን ህዝብ ሌላ ሲነካብኝ.. በሚል ቀይረው እያዜሙት ነው ተብሏል፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡም በአስቱ ዜማዎች የተማረከ ይመስላል ..የእኔ እህህ ማለት ላንተ ሙዚቃ.. እያለ በአምባገነን መሪዎቹ ላይ እንጉርጉሮውን ተያይዞታል፡፡
..ሰበቡ.. - የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርጫ
በአገራችን በየቀኑ በንዴት የሚያጨሱን አያሌ ጉዳዮች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ግን ማጨስ ብቻ ሳይሆን የሚያቃጥሉም ናቸው - ብግን የሚያደርጉ፡፡   
ባለፈው እሁድ በደቡብ ኮሪያ በተካሄደውና አትሌቶቻችን በተካፈሉበት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር አስደማሚ ድል ካስገኘልን ብቸኛ አትሌት በቀር በየትኛውም ዘርፍ ሳይቀናን ቀርቷል፡፡ አንዲት በዓለም መድረክ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንታይባት ነገር ብትኖረን እሷንም ኬንያዎች ተረከቡን፡፡ አሁን እንግዲህ አትሌቲክስ ድሮ ቀረ ልንል ትንሽ ነው የቀረን፡፡ ድል የሚያመጣ ተተኪ ሯጭ መፍጠር አልቻልንም - ዕድሜ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽናችን! ልብ በሉ! ኢህአዴግ እንኳን የማይደፈረውን ደፍሮ በመተካካት ፖለቲካዊ ዘይቤ አዳዲስ የኢህአዴግ አመራርን (ባለስልጣናትን) በቀድሞዎቹ ምትክ ለማስቀመጥ እየታተረ ባለበት ዘመን፣ ወጣት አትሌቶችን ማፍራት ወይም መተካት አቅቶናል፡፡ ይሄ ታዲያ አያበግንም፡፡ ለሰሞኑ የአትሌቲክስ ውጤት አለመገኘት ከፌዴሬሽኑ አካባቢ የተሰጠው ምላሽ ደግሞ የበለጠ የሚያበግን ነው፡፡ የአትሌቶቹ ችግር ..የአጨራረስ ችግር.. ነው የሚል አዲስ የሚመስል የተለመደ ሰበብ ተሰንዝሯል፡፡ ይሄኔ ነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዘፈን ምርጫው የአስቱ ..ሰበቡ. . ... እንደሆነ የገባኝ፡፡
አዲሱን ሰበብ ገና እንደሰማሁት እርር ብግን ብዬ ነበር፡፡ ወዲያው ግን ፍልስፍና ቢጤ አማረኝ፡፡ ግን እኮ በአገሬ ምድር በሰበብ ሱስ ያልተያዘ ማንም የለም፡፡ አልኩና ተናናሁ፡፡ የመንግስት ባለሥልጣኑ ለፈፀመው ስህተት ወይም ጥፋት ሰበብ አያጣም - ከተጠያቂነት ነፃ የሚወጣበት፡፡ የፓርቲ አመራሮች ኢ-ዲሞክራሲነታቸውን ሲጠየቁ በቂ ሰበብ ይፈጥራሉ - የማያሳምን ቢሆንም፡፡ ከሥልጣን እንወርዳለን ያሉ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮችና ሚጢጢዬ የፖለቲካ ሃላፊዎች ሳይቀሩ ጊዜው ሲደርስ ከሥልጣን መውረድ የማይችሉበትን ለእነሱ አሳማኝ ለእኛ ግን ፈሞ የማያሳምን (ጭራሽ ጥርጣሬያችንን የሚያባብስ) ሰበብ ይዘውልን ከተፍ ይላሉ፡፡ እዚህ ጋ ግን ይሄ ሁፍ በፓርቲያቸው ውሳኔ ግፊት ወይም ጫና ላልተወሰነ ጊዜ በሥልጣን የቀጠሉ መሪዎችን እንደማይመለከት ልጠቁም እወዳለሁ፡፡ ነገሩን የበለጠ ለማጥራት አብነት ብጠቅስ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለምሳሌ የመኢአዱ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ሥልጣን በቃኝ ብለው ሊያስረክቡ በተገኙበት የመጨረሻ መድረክ ላይ ፓርቲው ባቀረበው ተማኖ ላልተወሰነ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡ እንደኔ ቢሆን ግን አሻፈረኝ ብለው ከስልጣን ቢወርዱ ይሻላቸው ነበር፡፡ ለምን ቢባል . . .መልካም ስማቸውን እንደያዙ ከፖለቲካው ዓለም ይሰናበቱ ነበር፡፡ በፓርቲያቸው ግፊት (ጫና) ዳግም አመራር ላይ ከወጡ በኋላ የተፈጠረው ውስብስብ ችግር (ምስቅልቅል) ለማንም ቢሆን የሚመኙት ዓይነት አይደለም፡፡ በመኢአድ ውስጥ እንደሰፈር ጐረምሶች ጐራ ተለይቶ መደባደብ የተጀመረው ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን በቃኝ ብለው ከተመለሱ በኋላ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ እንደው ለነገሩ የአፍሪካ የፖለቲካ ስልጣን ሱስ የሚያሲዝ ሃሺሽ ነገር ይኖረው ይሆናል እንጂ አንዳንድ መቋቋም የማይችሉት ቀውስ ሲያጋጥም እኮ ..በቃኝ አልቻልኩም.. ብሎ በገዛ ፈቃድ ሥልጣን መልቀቅ ይቻልም ነበር፡፡ ቀውስ ባያጋጥምም ሥልጣን ደከመኝ ወይም ሰለቸኝ በሚል ሰበብ ትንሽ እረፍት መውሰድ ለጤናስ ቢሆን ይመረጥ አልነበር፡፡ በዚህ በዚህስ ጠ/ሚኒስትሩ በስንት ጣዕማቸው! ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን እንደታከታቸውና እንደሚለቁ በይፋ የተናገሩ ፖለቲከኛና የአገር መሪ ነበሩ (በነበር ቀረ እንጂ!) ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ግን ጉድ ¿‰cW የተናገሩትን እንዳይፈሙ መሰናክል ሆኖ ተጋረጠባቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ..ሥልጣን በቃኝ.. የሚለውን ነገር ደፍረው በመናገራቸው ብቻ አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ ይሄን ጊዜ እናንተ ሰሞኑን የአንድ ዓመት ገደማ የጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትን የጃፓኑን መሪ እያሰባችሁ ይሆናል፡፡ ጃፓን በ5 ዓመት ውስጥ 6 ጠ/ሚኒስትሮችን ማፈራረቋን በማሰብም ከአገራችሁ ጋር ለማነፃፀር ዳድቷችሁ ይሆናል፡፡ እውነት እንዲህ ያለ ድርጊት ሞክራችሁ ከሆነ ትልቅ ስህተት እየፈፀማችሁ መሆኑን እወቁት፡፡ እንደኔ እንደኔ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ቀዳሚ ከሆኑት የዓለማችን አገራት አንዷ የሆነችው ጃፓን ጠ/ሚኒስትሮችን እንደ ሸሚዝ መቀያየሯ የዲሞክራሲያዊነትና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማሳያ ሳይሆን የፖለቲካ አለመረጋጋት መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡ ይታያችሁ በ5 ዓመት 6ጠ/ሚኒስትሮችን እኛ አገር በ20 ዓመት አንድም ጠቅላይ ሚ/ር አልተለወጠም፡፡ የማናችን ነው ጤናማ ፖለቲካ? የእኛ ነዋበዚህ ጉዳይ ግን ከዚህ የበለጠ አልከራከርም፤ ባይሆን ራሱ ኢህአዴግ ያስረዳችሁ ወይም ይከራከር፡፡
አያችሁልኝ የፖለቲካና የሥልጣን ነገር በወሬ እንኳን እንዴት እንደሚያስት! አንዴ ከገቡበት እኮ መውጣት መከራ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ጉዳይ ጀምሬላችሁ ነበር፡፡ ፖለቲካና   ሥልጣን አንሸራተው ወሰዱኝ እንጂ! ወደ ቀደመው ርዕስ ጉዳያችን ስንመለስ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰዎች የአትሌቶቻችን ችግር የአጨራረስ ችግር ነው የሚል ሰበብ ማምጣታቸው ጠቅሼ ነበር፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ የውስጥ ምንጮች እንደጠቆሙኝ ግን ይህቺ አባባል ወይም ሰበብ ከራሱ ከኢህአዴግ የተኮረጀች ናት፡፡ አንድ ጊዜ ፓርቲው ድክመቱ እየተነቀሰ ሲተችበት ..የፖሊሲ ችግር የለብንም ችግራችን የአፈፃፀም ነው..  የሚል ሰበብ ይዞ እንደመጣ አትዘነጉትም፡፡ ፌዴሬሽኑ የሰሞኑ ያልታሰበ የአትሌቲክስ ሽንፈት ሲገጥመው የአፈፃፀም ችግር የምትለዋን የአጨራረስ ችግር በሚል ቀይሮ ከች አለልን (ታዲያ ይሞታል እንዴ!) ለነገሩ እጥር ምጥን ያለች አሪፍ ሰበብ ናት! ለዘለቄታው የማታዋጣ ብትመስልም፡፡ እኔን ደስ ያለኝ ደግሞ ..የአጨራረስ ችግር.. የሚለው አባባል ለመላው አገራችን የሚሰራ (የሚሆን) ሁሉን አቀፍ ሁነኛ ..ሰበብ.. የመሆን አቅምና ብቃት ያለው መሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለስልጣናት የአስቱን ..ሰበቡ . . ... ብጋብዝስ? . . . እንደ አዲስ ዓመት ስጦታ ቢቆጠርልኝ ደግሞ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንልኝ ነበር፡፡ የነገ ሰው ይበለን!!

 

Read 4321 times Last modified on Saturday, 03 September 2011 12:32