Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 08 August 2011 14:06

የ..ሐምሌ ስንኞች..

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው እሁድ በቢሾፍቱ ሲኒማ አዳራሽ ኪነጥበባዊ ዝግጅቱን ያቀረበው ..ሆራ ቡላ.. ታዋቂዋን አርቲስትና የማስታወቂያ ባለሙያ ሙሉ ዓለም ታደሰና በ..ሰው ለሰው.. ተከታታይ የቴሌቭዢን ድራማ ልጇ ብሩክን ሆኖ የሚሠራውና የድራማው አዘጋጅ አርቲስት ሰለሞን አለሙ ፈለቀን የክብር እንግዶች በማድረግ የጋበዘ ሲሆን አርቲስቶቹ ልምድና እውቀታቸውን ለደብረ ዘይት ወጣቶች አጋርተዋል፡፡

በአዝማሪ ጋሻሁን ማሲንቆ የተጀመረው የሥነ ጽሑፍ ውሎ፤ ሙሉ ዓለምን ..የኢትዮጵያ ንግስት.. በማለት አድንቋታል፤ ኪነ ጥበባዊ አበርክቶዋን በማጉላት፡፡ አስተዋዋቂዎችም ትውፊተ ክረምትን በምሳሌ አስደግፎ በማስተንተን የእለቱ ዝግጅት ..የሐምሌ ስንኞች.. እንደሚባል አበሰሩ፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ጴጥሮስ በታቦር ተራራ ለክርስቶስ ..እነሆ ለኛ በዚህ መሆን መልካም ነው፤ ሦስት ዳስ እንሥራ. . ... ያለውን ወሰዱ፡፡ አንድ ዳስ ለግጥም፣ አንድ ዳስ ለጥበብ ዝክር፣ ሌላ ዳስ ለነሙሉ ዓለም ቆይታ አደረጉ፡፡
በግጥም ዳስ ውስጥ ከቀረቡት የእለቱ ግጥሞች አንዱ ..ለምን ይሆን?.. የተሰኘው የቤዛ ከበደ ግጥም ነበር፡፡
..ለምን ይሆን?..         
አምላክ በጥበቡ
ሁሉን ሲያሰማምር
ምድርን ሲዘረጋ
ሰማይን ሲወጥር
ፍጥረታትን ሁሉ
በትዕዛዙ ሲያኖር
አዳምን ሲሠራው
አፈርን አቡክቶ
እስትንፋሱን ሲፈጥር
በእጁ መዳፍ ነበር
ከዛም
የአዳም ብቸኝነት
ፈጣሪን አሳስቦት
ከጎኑ አጥንት ወስዶ
ሔዋንን ሰራለት
ፈጣሪ አምላኩ
ይሄን ሁሉ ነገር
ለአዳም ሲያደርግለት
ታዲያ ለምን ይሆን?
የግራ ጎን አጥንቱን
ሽንፈት አረገበት፡፡
አብዛኞቹ ወጣቶች የሆኑት የሆራ ቡላ አባላት በሥነ ፍጥረት ብቻ ሳይወሰኑ የዘመኑን ኑሮ የተመለከተ ምፀታዊ G_MM አቅርበዋል፡፡
የመ ሕግ ለኑሮ
የ..መ.. ሕግ ለኑሮ
የሚላስ የሚቀመስ ላማረው ጉሮሮ
የመጀመርያ ..መ.. ከቁርስ መታቀብ
በጨው እየበሉ ቅባት ነገር ማሰብ
በምሳ መወሰን
በቅርብ እንደበሉ ራስን ማሳመን
የመጨረሻው ..መ.. እንቅልፍ መጠቀም
ከቅዠት ሌማት ላይ የሌለን መቃረም፡፡ (በፀጋ አዳነ የቀረበ)
ሌሎችም በርካታ ግጥሞች ለታዳሚው እና ለክብር እንግዶች የቀረቡ ሲሆን የግጥሙ አቅራቢዎች ከአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ እስከ ስልሳ ዓመት አረጋዊት የተሰባጠሩ ነበሩ፡፡
የእሁዱ ..የሆራቡላ.. ሥነ ጽሑፍ አንደኛው ምናልባትም የብዙዎችን ትኩረት የሳበውና የዝግጅቱ ማጠቃለያ የሆነው ከክብር እንግዶች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ቃለ ምልልስ አድራጊው ከመደበኛ ቃለ ምልልስ ያልተናነሰ ቃለ ምልልስ ከአርቲስት ሙሉአለም ታደሰ እና ከአርቲስት ሰለሞን ዓለሙ ፈለቀ ጋር አድርጓል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ከጥያቄና መልሶቹ ጥቂት ቆንጥሮ ማየት ይቻላል፡፡
የክብር እንግዳው ሰለሞን ዓለሙ ፈለቀ ..የምትወጂውን ግጥም አንዴ ብታቀርቢልን .....   አላት ሙሉ ዓለምን፡፡ ለቃለ ምልልሱ ወደ መድረክ የጠራቸው የሆራቡላው አቶ ጌታቸው ለማም ..ሙሉ ዓለም አርአያ የሆነችሽ ሴት ማነች?.. አላት፡፡
እሷም በ..ሰው ለሰው.. የቴሌቪዢን ድራማ ልጇ ብሩክ የሆነውን ሰለሞንን በማየት ..የልጄን ጥያቄ መጀመሪያ ልመልስ.. በማለት ሕዝቡን ዘና አድርጋዋለች፡፡
..በጣም ደስ ከሚለኝና ሁሌ ይዤ ከምዞረው የነቢይ መኮንን ስውር ስፌት የግጥም መጽሐፍ የውሻው አቤቱታ የሚለውን ላንብላችሁ. . ... በማለት ካነበበች በኋላ ሌላውን ጥያቄ ወደመመለሱ ሄዳለች፡፡
..አርአያ የሆነችኝን ሴት መጥቀስ ካስፈለገ አለምፀሐይ ወዳጆን እጠቅሳለሁ፡፡ ዓይናለም ተስፋዬም አርአያዬ ናት፡፡ ሁለቱም አሁን ሀገር ውስጥ የሉም፡፡..
..ረቡዕ ቀዶ ሕክምና አድርገሽ እሁድ ትያትር ላይ ተውነሻል መባሉን አንብቤአለሁ፡፡ አልተጋነነም?..
..አልተጋነነም፡፡ በ1983 መገባደጃ የመጀመሪያዬ የሆነውን ትያትር ..የሌሊት ርግቦች.. እየተወንኩ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ታከምኩ፡፡ ከሐኪም ቤት ጠፍቼ ትያትሩ ላይ በመስራት ተመልሻለሁ፤ ወደ ሀኪም ቤት፡፡ ይህንኑ የተረዱት ሃኪሞች የሙያ ሥነምግባሩን ብንረዳልሽም ይኼንን አንፈቅድልሽም.. ብለውኛል፡፡..
..መኪና ገዛሽ?..
..በፊት ጊዜ በማስታወቂያ የሚያውቁኝ አንዲት ሴት ገና መኪና ሳይኖረኝ ታክሲ ውስጥ አይተውኝ ምን ልትፈልጊ ነው ቃርመሽ ትያትር ልትሰሪ እንጂ መኪና አጥተሽ ነው? ሲሉኝ እግዚአብሔር ካለ ለወደፊት መኪና ይኖረኛል አልኳቸው፡፡ ቆይቶ ቆይቶ ሆንዳ መኪና ገዛሁ፡፡ ከዚያ ወዲህ ደግሞ አሁን ዲኤክስ መኪና አለችኝ፡፡ ብቻ የሀብታም መኪና ስታይ ትደነግጣለች እንጂ፡፡..  
..ሳትወጂያት የሰራሻት ገፀባህርይ ትኖር ይሆን?.. ተብላም ተጠይቃለች፤ ታዋቂዋ አርቲስት  
..በነገራችን ላይ መፃሕፍት በጣም አነባለሁ፡፡ ገፀባህርይዋን ጠልቼ ሳይሆን ያለ መልኬ በሜካፕ ፊቴን አጠይሜ የሠራሁበትን የ..ከአድማስ ባሻገር.. ዋን ሉሊትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሦስት ሳምንት ብቻ እንደሰራሁ ወደ አሜሪካ ሄጃለሁ፡፡ ፈታኝ ገፀባህርይ የ..ውበትን ፍለጋ..ዋ አርሴማ ነች፤ የፊልሙን ሳይሆን በትያትሩ፡፡..
..ራስሽም ለአዘጋጆች ፈታኝ ነሽ ስለመባሉስ?..
..የቤት ሥራውን ሳይሰራ ከመጣ ለአዘጋጅ ፈታኝ ነኝ፡፡ ጐበዝ ተማሪ መምህሩን እንደሚሞግተው፡፡ ሆኖም ግን የተሰጠኝ ብቻ ሳይሆን ያልተሰጠኝን የሌሎች ገፀባህርያት ጽሑፈ ተውኔትም አነባለሁ፡፡ የትወና ሐራራን ለመወጣት ትያትር ይሻላል፡፡ ፊልም ላይ ..ከት.. ስለሚሉ ይከትክታቸውና ብዙ አይመችም፡፡..
ሙሉዓለም ዝነኝነትን አስመልክቶ ለቀረበላትም ጥያቄ ምላሽ ሰጥታለች፡፡
..ዝነኝነት አጥር ነው፤ ነፃነት ያሳጣል፡፡ መንገድ ላይ እየበላሁ መሄድ እፈልጋለሁ፤ አልችልም፡፡ መንገድ ላይ እየዘፈንኩ መሄድም እወድ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ያሳጣሃል፡፡..
..ከእድሜዬ ብሰጠው ብለሽ ያለምሽው ይኖራል?..
..ወጋየሁ ንጋቱ ነው፡፡ ስላልደረስኩበትና አብሬው ስላልሰራሁ ይቆጨኛል፡፡..
ሌላው የጥበብ እንግዳ ሰለሞን አለሙ ፈለቀ ስለትዳር ተጠየቀ፡፡
..አንድ የሦስት ዓመት ሌላ የሦስት ቀን ልጅ አለኝ፡፡ ከባለቤቴ ጋር አብረን አንኖርም፡፡ አሁን የቤት እቃዎች እያሟላሁ ነው፤ እቃ በማጋዛቱና በመግዛቱ የ..ሰው ለሰው.. እናቴ ሙሉአለም እያገዘችኝ ነው፡፡..
..የጥበብ ጅማሮህ ምን ይመስላል?..
..ምስራቅ አጠቃላይ ተማሪ ሆኜ የሚኒ ሚዲያ አባል ባልሆንም የወላጆች ቀን አንድ ስራ አቀረብኩ፡፡ አሁን ላይ ጥሩ ቴክኒክ እንዳልነበረው ብረዳም ለወላጆች በሁለት ሁለት ብር ታየ፡፡ ከዚያ የቀጠለ ነው የአሁን እኔነቴ፡፡ በፐርቼዚንግ የኮሌጅ ዲፕሎማ አለኝ፡፡ በተመረቅኩበት ሙያ ግን የሰራሁት ለሁለት ወር ብቻ ነው፡፡
..ሰለሞን ፈጠራን በደቦ ያዋጣል?..
..ውጤቱ ያማረ ነው፡፡ ከዚያ ቀድሞ በሚመጣው በሀሳብ ግን ያጋጭሃል፡፡ ሙሉዓለም ልምምድ ላይ ታደክምህና ቀረፃ ሲጀመር እንደነ ኃይሌ 10ሺህ ሜትር ሩጫ ጥላህ ትሄዳለች፡፡..
..አንተንስ ዝና እየመጣ ነውና እንዴት አደረገህ?..
..አዶኒስ ጓደኛዬ ነው፡፡ በብዕር ስም ስለሚጠቀም መንገድ ላይ ብርቱካን እየበላ ቢሄድ በአካል ስለማያውቁት የሚያስቆመው የለም፡፡..
የሆራቡላ አባላት ሙሉዓለምንና ሰለሞንን የሚጠይቁት ጥያቄ ካለ እንዲጠይቁ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
..አርሴማ በመድረክ አይበቃም ነበር?.. አንደኛው ለሙሉዓለም የተሰነዘረ ጥያቄ ነው፡፡
..ይበቃ ነበር፡፡.. መለሰች - አርቲስቷ፡፡  
..የንጉሥ አርማህ ዋ ዘቢባ ከባድ ባህርይ ነች ትያለሽ ብዬ ገምቼ ነበር?..
..የሐረር ልጅ ስለሆንኩ የዘቢባ ባህርይ አልከበደኝም.. በማለት በዘቢባ የተኮላተፈ አማርኛ መልሳለች፡፡
ሰለሞን ለኪነጥበብ አዘጋጆቹ ..ክብር ይገባል.. በማለት ያደነቀ ሲሆን ..ከዚህ በኋላ.. ከእንግድነት ይልቅ በተሳታፊነት ብገኝ ደስ ይለኛል፡፡.. ብሏል፡፡
ለሁለቱም የክብር እንግዶች የ..ሆራቡላ.. ትሩፋት የሆኑ ሁለት ሁለት የግጥም መፃሕፍት ተበርክቶላቸዋል፡፡  
በመጨረሻ በዕለቱ የታደሙ የኪነጥበብ አባላት ሙሉአለም ወጣቶችን ምን እንደምትመክር ጠይቀዋት ነበር፡፡   ..እዚህ ያለው ወጣት ቢመክረኝ እመርጣለሁ፡፡ ቢሆንም ታግላችሁ ለመውጣት ሞክሩ፤ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ሥራዎቻችሁ የጋን ውስጥ መብራት መሆን የለባቸውም፡፡.. ብላለች፡፡

 

Read 7419 times Last modified on Monday, 08 August 2011 14:11