Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 24 November 2012 12:01

ጨጓራ እና ‘ሙሉ በግ…’

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እኔ የምለው…አንዳንዴ ግርም ይለኛል… ብዙ ነገሮችን ስታዩ ምንድነው መተሳሰባችንን እንዲህ ሙልጭ አድርጎ የወሰደብን አያስብላችሁም? እንዴ…ሥራ ፈላጊ ቢኖርም እኮ ጭማሪ ማግኘት ያለበት ጭማሪውን ለምን አያገኝም፡፡ ገና ለገና ‘ትርፍ ከፍ ለማድረግ’ እየተባለ የሠራ ሰው ለሥራው የሚመጥን ክፍያ ሳይሰጠው ሲቀር በጣም ቀሺም ነው፡፡
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሆነ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ እናላችሁ… “ስትረክቸር የሚሉት ነገር ተሠርቶ እየተበተነ ስለነበር ህዝቤ ሁሉ ቋምጦ እየጠበቀ ነው፡፡ “መቼም ዘንድሮ ኑሮ እንዲህ በተወደደበት በሽ ነው የሚያደርጉን…” እየተባለ…እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ሳቅ ሳቅ የሚላቸውም አይጠፉም፡፡
እንደውም አንዳንዶቹ “ይሄ ፍራንክ ሲመጣ ሎጅ የሚባለውን መዝናኛ ዘንድሮ ሄጄ ዓለም ዘጠኝ ካላልኩበትማ…” እያሉ ዕቅድ ሳያወጡ አይቀርም፡፡

ታዲያላቸሁ… ‘ስትረክቸር’ የተባለው ሲመጣ የአንዳንዶቹ ጭማሪዋ ይሄ ‘ቺክንፊድ’ እንደሚሏት ጂንስ እንኳን የማትገዛ! እንደውም አንዳንዶቹ ባለህበት እርገጥ ሲባሉ ሌሎቹ ጭራሽ በኋላ ማርሽ…ተንደርድረው ያርፉላችኋል፡፡ ሠራተኞቹ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…“ይሄ ምን ስትረክቸር ነው፣ ስትሬቸር ነው እንጂ…” ምን ያድርጉ… ቀና ብለው የነበሩትን አጋደማቸዋ!
“ሁለት ሦስት ግሬድ ከፍ እላለሁ…” ያለ ሁሉ አጨብጭቦ ሲቀር የምር ያሳዝናል፡፡ “እኛ ግሬድ ስንጠብቅ ብሬዳችንን ሊያሳጡን ምንም አልቀራቸው…፡” አሉ እንዳማራቸው የቀሩ ምስኪኖች፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ እያጓጉ የማስቀረት ነገር እዚሀ አገር እየተለመደ ነው፡፡
(አሁንማ እዚህ አገር ‘እየተለመዱ ያልሆኑትን’ ነገሮች መቁጠሩ ሳይቀል አይቀርም፡፡) እንደ አገር የተነገረለት “ልብ አንጠልጣይ…” ፊልም የምርም ልባችሁን በብሽቀት አንጠልጥሎት ያርፋል፡፡ ሰውየው የደሞዝ ማነሱ አበሳጭቶት አለቃው ዘንድ ይሄዳል፡ “ጌታዬ በማገኘው ደሞዝ እኔና ሚስቴን ለማኖር አቅቶኛል…” ይለዋል፡ አለቅየው ምን አለ መሰላችሁ…“እና አሁን አፋታኝ እያልከኝ ነው!”
ከዚህ አይነት አለቃ ይሰውራችሁማ!
ስሙኝማ…ዘንድሮ እየተማረ ቤቱ የሚውል ስለበዛ ነው መሰለኝ አንዳንድ መሥሪያ ቤት መብት እንኳን መጠየቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ “ጌታዬ፣ አይደለም ደሞዝ ሊጨመርልኝ እርከን እንኳን ካገኘሁ መጋቢት አቦ ሰባተኛ ዓመቴ ነው…” ምናምን ቢባል የሚሰጠው መልስ “አትለኝም! እስከዛሬ ምንም አልተሰጠህም!” ሳይሆን ምን ይላል መሰላችሁ… “ከፈለግህ መሄድ ትችላለህ፣ ሥራ ፈላጊ እንደሆነ ሞልቷል…፡፡”
የፍራንክን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ነገር ስሙኝማ…ሰውየው ከሚስቱ ጋር ሆቴል ተከራይቶ አንድ ቀን ያድራል፡፡ እናላችሁ ጠዋት ሂሳብ ሲከፍል መቶ ሀምሳ ብር ክፈል ይባላል፡፡
“ምን! ለዚህ ክፍል መቶ ሀምሳ ብር!”
“የሆቴሉ ደረጃ ነው፡ ደግሞም ምግብን ያካትታል፡፡”
“እኛ መቼ ምግብ በላን!”
“የእናንተ ጥፋት ነው፡ ልትበሉ ትችሉ ነበር፡፡”
“እንዲህ ነው! እሺ እንዲህ ከሆነ ሚስቴን በመሳምህ መቶ ሀምሳ ብር አለብህ፡፡”
“እኔ ሚስትዎን መቼ ሳምኩኝ!”
“የአንተ ጥፋት ነው፣ ልትስማት ትችል ነበር፡፡”
እንዲህም አለ ለካ! የምር… ‘እያስመጨመጩ’ ገንዘብ መሰበሰብ አንዱ ቢጀምር እዚህ አገር በሰርጉ ማግስት “አንቺ ከቤት ወጣ በዪና እየተሳምሽ ፍራንክ መሰብሰብ ጀምሪ እንጂ!” የሚል ‘ሀዝባንድ’ መአት እንደሚሆን እጠረጥራለሁ፡፡ የኮሌጅ ተማሪዎች እንትናዬዎቻቸውን “ሹገር ዳዲ ጠብ አድርጊና መጨበሻ ይዘሽ ነይ እንጂ…” የሚባልባት አገር ነች እኮ!
እኔ የምለው…አንዳንዴ ግርም ይለኛል… ብዙ ነገሮችን ስታዩ ምንድነው መተሳሰባችንን እንዲህ ሙልጭ አድርጎ የወሰደብን አያስብላችሁም? እንዴ…ሥራ ፈላጊ ቢኖርም እኮ ጭማሪ ማግኘት ያለበት ጭማሪውን ለምን አያገኝም፡፡ ገና ለገና ‘ትርፍ ከፍ ለማድረግ’ እየተባለ የሠራ ሰው ለሥራው የሚመጥን ክፍያ ሳይሰጠው ሲቀር በጣም ቀሺም ነው፡፡ “እከሌ ምን አለ?” “እነ እከሌ ምን ተባባሉ?” “እከሌና እከሊት ምን እያወሩ ነው?” ምናምን ከመባባል ይልቅ “እከሌ ለመሆኑ በሥራው ምን ያህል ይተጋል?” “እከሊት ምን አዲስ ነገር እየሠራች ነው?” ምናምን የምንልበት ጊዜ አይናፍቃችሁም! እናላችሁ…ሰው የሚሠራውን ከማየት ይልቅ የሚያወራውን መስማት የምንፈልግ ቁጥራችን በጣም፣ እጅግ በጣም እየበዛ ነው፡፡ ተረጋግቶ የሆድ፣ የሆዳችንን ለማውራት ወይ ‘የተከለለ ጫካ’ ምናምን ነገር ይዘጋጅልን እንጂ በየመንገዱና በየሬስቱራንቱማ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ አሀ…የእንትናን እንትናዬ “እኔ እሱ ሊያውቅ የማይችልበት፣ ሰው የማያየን ቦታ አውቃለሁ…” ለመባባል እኮ እየከበደን ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ለካፌዎችና ለሬስቱራንቶች ሀሳብ አለን… “የልብ የልባችሁን የምታወሩባቸው፣ ድምጽ የማያስወጡና የማያስገቡ ቪ.አይ.ፒ. ቦታዎች አሉን…የሚል ነገር ይጀምሩልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን ጠላህ አትሉኝም…የሰው ‘ተንቀሳቃሽ ስልክ እንጨት’! ምን አለፋችሁ…የዴቴክቲቭ (ቂ…ቂ…ቂ…) መነጽር ከማድረጋቸው ሌላ ገመድ ያልተዘረጋበት የስልክ እንጨት በሏቸው፡፡
እንዴ…አላስወራ የሚል በዛብና! ሰፊ በሆነው ሜዳ፣ መተላለፊያ እንደ ልብ ባለበት “ሰዉ ተጨናንቆ ማለፊያ ማግደሚያ አጣን እኮ…” ጭር ያለ ቦታ ላይ ቆም ብላችሁ ወሬ ስትጀምሩ ከየት መጣ ሳትሉት ‘ጥላ ነገር ይጋርዳችኋል፡፡ እናንተም “በራድዮን ሳይነገር የፀሀይ ግርዶሽ መጣ እንዴ…” ብላችሁ ቀና ስትሉ ምን ብታዩ ጥሩ ነው… የሆነ አጅሬ አጠገባችሁ ተገትሯል፡፡ የምር ግርም ይላል… አንዳንዱ እኮ ገና ከወዳጃችሁ “ሰላም ነው?” (መቼም “እንደምን አደርክ?” “በጎ አደርሽ ወይ? ልጆቹ እንዴት ናቸው” መባባል ቀርቷል…) ተባብላችሁ ሳታበቁ ከማዶ መንገድ ተሻግሮ፣ በመኪና ውስጥ ተሽሎክለኮ ተንደርድሮ አጠገባችሁ ይደርስና ቀጥ ይላል፡፡ የምር ግን…ጨዋታም አይደል…በአራተኛ ማርሽ ተንድርድሮ ሳያበርድ፣ የጎማ መፋጨት ሳያሰማ ቀጥ ሲል አይገርማችሁም! ገና ለገና ‘ፉዞ የሚሆን ሞተር’ የለንም ተብሎ የዚሀ አይነት “የቅሽምናዎች ሁሉ እናት…” ደስ አይልም፡፡ሀሳብ አለን…ሰው የሆድ የሆዱንም ሲያወራ አጠገብ መጥተው እንደ ጅብራ የሚገተሩ ሰዎች የአፈር ግብር ይክፈሉልንማ! ቂ…ቂ…ቂ… መቼም ዘንድሮ ከፍራንክ ጋር የታያያዘ ነገር ሆኗል የሁለት ጆሮዎቻችንን የመስማት ኃይል በአሥር እጥፍ የሚጨምርላቸው! እናላችሁ…ለማህበረሰብ አጥኚዎች እንኳን የምናስቸግር ሰዎች እየሆንን ነው፡፡
“ጉድ!” የምንልበት ነገር እየበዛ፣ “ይሄ ምን ያስገርማል!” የምንልበት ነገር እየቀነሰ ሲመጣ “ኧረ ሀዲዱን ከስራችን ማን ወሰደው?” የሚያሰኝ ነው፡፡ አሀ…ባቡሩ ሀዲድ በሌለበት እየተንደረደረ ነዋ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ፈገግ የምታሰኝ ነገር ስሙልኝማ! እዚህ ከተማችን የሚገኝ ሥጋ መሸጫ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… አንድ ኪሎ የበግ ሥጋ ሰባ ብር ምናምን ይላል፡፡
ታዲያላችሁ…የ‘ሙሉ በግ’ ዋጋም አለላችሁ፡፡ አሪፉ ነገር ምን መሰላችሁ… ‘ሙሉ በግ’ ስትገዙ ምን ይመረቅላችኋል…“ጨጓራ”! አሁን ለኩምክና የእኛን አገር የመሰለ ይገኛል! መጀመሪያ ነገር በጉ ያለ ጨጓራ ‘ሙሉ’ የሚሆነው እንዴት ነው! ገና ለገና “አበሻ ዱለት ይወዳል…” (‘ሌሎች ነገሮችን’ እንደሚወድ ማለት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ተብሎ ምን የሚሉት ‘ማርኬቲንግ’ ነው! እናላችሁ… ይቺ ከተማ አሁን፣ አሁን በብዙ ነገሯ አልገባን እያለችን ቆሽት የሚያበግነው ነገሯ በዝቷል፡፡ ትርጉም ሊሰጥባቸው የሚያስቸግሩ ነገሮች እየበዙ ሲሄዱ ነገርዬው ደብለቅለቅ ይላል፡፡ ከሙሉ አካል ላይ ባዕድ አካል ይመስል ጨጓራው እየተነጠለ በመደበኛነት ሳይሆን በ‘ምርቃትነት’ ሲቀርብ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ብዙ ነገሮቻችን “የጨጓራ ምርቃት” እየሆኑ የአንዳንድ ነገሮችን እንቆቅልሽ መፍታቱ ‘የአይንስታይንን ጭንቅላት’ ሊጠይቅ ምንም አልቀረው፡፡ ጨጓራው ሳይነጠል ‘ሙሉውን በግ’ የምናገኝበትን ጊዜ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 18255 times

Latest from