Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 11:19

እወርካ ሥር የገደለ፣ ዘወትር እወርካ ሥራ ያደፍጣል!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ የላቲን አሜሪካ ተረት እንዲህ ይላል፡-
የአንድ ሀገር ህልውና ሊደፈር ነው ተባለና መሪው ዋና ዋና ሰዎችንና ህዝቡን ሰብስቦ፤ “ጀግናው የሀገሬ ህዝብ ሆይ! አገራችን አደጋ ላይ ናት፡፡ የጎረቤት አገሮች ወራሪዎች ሊደፍሩን አሰፍስፈዋል፡፡ ምርጫችን ከሁለት አንድ ነው “እንዋጋ?” ወይስ አንዋጋ?” አንዱ እጁን አወጣና፤
“ምንም ምክክር አያስፈልግም፡፡ እንዋጋ!!” አለ፡፡

ሌላው ቀጠለ፡- 
“ጦርነት ሰልችቶናል፡፡ ከዚህ ቀደም በተካሄደው ጦርነታችን ብዙ ሰው አልቆብናል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሞብናል፡፡ ኢኮኖሚያችን ደቅቋል፡፡ ስለዚህ ሌላ ጦርነት ይጎዳናል እንጂ ምንም አይፈይደንም!”
“ጦርነቱን እኛ ነን የፈለግነው ወይስ እነሱ?” አሉ አንድ አዛውንት ተነስተው፡፡ ህዝቡ አጉረመረመ፡፡ ደሞ ጦርነት ከፍላጎት ሆነ እንዴ? እንደማለት ነው፡፡
ቀጠለ ሀሳብ፡፡
“ከዚህ ቀደም ሊወርሩን ያሰቡት እነዚህ ጠላቶቻችን፤ ሁሌም እኛን ከማወክ እንደማይቆጠቡ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ በማያዳግም እርምጃ ልንቀጣቸው ይገባል፡፡ ሲሆን ከነጭራሹ አሸንፈናቸው፤ አገራችን ነው የሚሉትንም ቦታ አክለን መውሰድ ነው የሚገባው!” ህዝቡ አጉረመረመ፡፡ “የሰውንም አንነካ የራሳችንንም አናስነካ፣ እንደማለት፡፡” በዚህ መካከል አንድ ረጋ ያሉ አዛውንት ተነሱና፤ “ጎበዝ የሁላችሁም ሀሳብ ተስማምቶኛል፡፡ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡ ብንሸነፍስ?” ይሄኔ አንድ ጎረምሣ ተነስቶ፤ ድምፁን ጎላ አድርጎ በድንፋታ መልክ፤
“መሸነፍ?!” መሸነፍማ ለደቂቃም መታሰብ የለበትም፡፡ እኛ በነሱ ልንሸነፍ? ሞተናላ!”
ሁሉም በተራ በተራ እየተነሱ፤
“ሞተናላ!”
“ሞተናላ!”
አሉ፡፡
እኒያ አዛውንት ግን አሁንም ተነሱና፤ “ጎበዝ! እንዲያው ላንድ አፍታም ቢሆን ጠላቶቻችንን እናስባቸውና ብናሸንፍ ምን እንደምናረጋቸው ያሰብነውን ያህል፤ ብሔራዊ ስሜታችንም፣ ስሜታዊነታችንንም፤ ባለራዕይነታችንንም፤ ጀግንነታችንንም … ለጊዜው ጋብ አድርገን፤ እስቲ ድሉ በዚያኛው ወገን ቢዞር ምን እንደምናደርግ ለትንሽ ጊዜ ብናስብ ምን ይጎዳናል?” ብለን እንጠያየቅ፡፡ ስለጀግንነታችን ለብዙ ዓመታት ተናግረናል፡፡ እስቲ ዛሬ እንኳን ስለሽንፈታችን በጀግንነት እንወያይ!! መሸነፍ ትልቁ ባለውለታችን ነው የምንለው፤ ከዚህ ቀም የተሸነፍንበትን ምክንያት ማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ አደባባይ አውጥተን ለማውራት ስንደፍር ነው! የድፍረት ሁሉ ድፍረት ይሄ ነው ጐበዝ! ሽንፈትን መቀበል!” ብለው ተቀመጡ፡፡
ከዚያ በኋላ ታፍኖ የቆየ ይመስል ህዝቡ ሁሉ በይፋ ከዚህ ቀደም የተሸነፉበትን ሁኔታ በድፍረት አብራራ!!
***
ሽንፈትን መቀበል ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ሲያሸንፍ ጉራ አይነዛም፡፡ የዓለም ታላቅ ኃይለም ያሸንፍ አገራዊ ኃይል፤ በምን ሁኔታ አሸነፈን እንጂ፤ አልሸነፍም ማለትን መመርመር አለብን፡፡ የማረከውን ሰው በሰብዓዊ መንገድ ለመያዝ የሚችል ተዋጊ ጀግንነትን ከጭካኔ በመለስ ማየት አይሳነውም፡፡ ምህረት ለማድረግም ፍርሃትና ሥጋት አይኖርበትም፡፡ “የተጠማ ከፈሳሽ፣ የተበደለ ከነጋሽ” የሚለው ምሣሌያዊ አነጋገር በቀላሉ ይገባዋል፡፡ ምርጫ፣ በተለይም በአገራችን፣ በሚካሄድበት ጊዜ የሚያጋጥመን የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽ፤ 1ኛ/ የተሸናፊው ሽንፈትን አለመቀበል እና 2ኛ/ የአሸናፊው ዘራፍ ባይነት ነው፡፡ ይህ ማለት ከምርጫው በኋላ አሸናፊና ተሸናፊ አይጥና ድመት ናቸው ማለት ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ዐይን መተያየት ቀርቶ እንደ ዜጋ መተሳሰብም ይቀራል፡፡ “የማትወልደውን ሶሻሊዝም ሲያማምጡዋት፤ ከነ ካፒታሊዝሟም አስወረዳት!” እንደተባለው ነው፡፡ አዲስ ሥርዓት መፍጠር ቀርቶ አሮጌውንም ማጣት አለ፡፡ ቁልቁል ማደግ የሚባለው ዓይነት!
የፓለቲካ ፀሐፍት እንዲህ ይላሉ :-
“ዲሞክራሲ በምርጫ ሳጥን ብቻ ሳይሆን፤ በኑሮአችን ድርና ማግ ውስጥ ሁሉ የሚኖር መሆን አለበት፡፡
ሁሉን ጐራሽ የሆነ አሠራር (One size-fits - all logic) ከተከተልን ፖለቲካውም ሆነ ባህሉ ልሙጥ ይሆናል፡፡ ይህም ህዝብን ሽባ ያደርገዋል፡፡” ከዚህ ይሰውረን፡፡ ሥልጣንን ማጋራት፣ ሥራን ማከፋፈል ይቻለን ዘንድ ትምህርታችንን ይግለጽልን!
የችግር ጊዜ ሁኔታዎች ይለዋወጣሉ፡፡ የላዩ ታች የታቹ ላይ ቦታ ሊቀይር ይችላል፡፡ በደስታው በተድላው ጊዜ የሚደረገው ሁሉ ይቀራል፡፡ “የአብራ - ቅዳው ጊዜ ከዓለሚቱ ጋራ ስላለፈ የጠጅ ባለወግ ይቅርና የጠላ እንግዳ ስንኳ አይታይም ነበር” እንዳሉት ነው አንድ ደራሲ፡፡ ድህነት ጥላውን ሲጥል ማጀት ጓዳው መራቆቱ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብም ይራቆታል፡፡ ዕምነት ይመነምናል፡፡ ጀግንነት ይኮሰምናል፡፡ ቆራጥነት ይከሳል፡፡ የሌለው ላለው ያድራል፡፡ ተገዢ ገዢውን ከልኩ በላይ እጅ ይነሳል፡፡ አድር ባይነት የዕለት የሠርክ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ወደ ግዞት ሂዱ የተባሉ አንድ የዱሮ ሰው ምህረት ጠይቁ ተብለው በጐን (በሾርኔ) ቢነገራቸው አሻፈረኝ አሉ፤ አሉ፡፡ ህዝቡ ይሄኔ፤
“በየነ በየነ፣ ሊጋባ በየነ
እንደኮራ ሄደ፣ እንደተጀነነ
ጠጅ ጠጣ ቢሉት፣ ውሃ እየለመነ” ሲል ገጠመላቸው ይባላል፡፡
ይህን ዓይነት ወኔ ዛሬ ጨርሶ ጠፍቷል፡፡ ድህነት ውጦታል፡፡
ሐምሌት እንደሚለን፤
“በንጉሥ ፍርፋሪ የፋፋን ትል፣ አሣ አገኘችና ቅርጥፍ
አሣ አጥማጅ እሱዋን ቅርጥፍ!
ትል መልሳ እሱን ቅርጥፍ!
ሆድን ሞልቶ እንደስልቻ
በልቶ ለመበላት ብቻ!!”
(ፀ.ገ/መ)
ሁሌ በተለመደው የፖለቲካ መንገድ መሄድ ለህዝብ ዕድል አይሰጥም፡፡ ሌላው ይቅርና ለፖለቲከኛው ለራሱም ዕድል አይሰጥም፡፡ እስከንቅዘት (degeneration) ብቻ ነው ጉዞው፡፡ ወደ አዲስ አይን መክፈት አያመራም፡፡ የትኛውም ዘመን በየትኛውም ፓርቲ አንድና አንድ መንገድ ብቻ ልከተል ባለ ሰዓት የሚከሰት ችግር ነው፡፡ የታየ፣ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው!! “እወርካ ሥር የገደለ፣ ዘወትር እወርካ ሥር ያደፍጣል” የሚባለው እንዲህ ሲሆን ነው!

 

“ጦርነት ሰልችቶናል፡፡ ከዚህ ቀደም በተካሄደው ጦርነታችን ብዙ ሰው አልቆብናል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሞብናል፡፡ ኢኮኖሚያችን ደቅቋል፡፡ ስለዚህ ሌላ ጦርነት ይጎዳናል እንጂ ምንም አይፈይደንም!”

Read 5903 times Last modified on Saturday, 24 November 2012 11:33