Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 17 November 2012 12:55

በ36ኛው የሴካፋ ሻምፒዮና ከፍተኛ ፉክክር ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኡጋንዳ አዘጋጅነት ከሳምንት በኋላ እንደሚጀመር በሚጠበቀው የ2012 ሴካፋ ታስከር ቻሌንጅን ካፕ ለሻምፒዮናነት ከባድ ፉክክር እንደሚኖር ተጠበቀ፡፡ በታሪክ ለ36ኛ ጊዜ ለሚደረገው ሻምፒዮናው የምድብ ድልድል ባለፈው ሰኞ ሲወጣ የሞት ምድብ በተባለው ምድብ 1 የ12 ጊዜ ሻምፒዮኗ ኡጋንዳ፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችው ኢትዮጵያ ፤ ኬንያ እና አዲሷ አገር ደቡብ ሱዳን ተገናኝተዋል፡፡ በምድብ 2 ሱዳን፤ ታንዛኒያ፤ ብሩንዲ እና ሶማሊያ ሲደለደሉ በምድብ 3 ደግሞ ሩዋንዳ፤ ዛንዚባር፤ ኤርትራ እና ብቸኛዋ ተጋባዥ አገር ማላዊ ተመድበዋል፡፡ ከሶስቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የጨረሱት 6 አገሮች እና ከየምድቦቹ ጥሩ ሶስተኛ ደረጃ ያገኙት ሁለት አገራት ወደሩብ ፍፃሜ የሚያልፉ ይሆናል፡፡

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ክፍል እንደገለፀው በሴካፋው ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የምትሳተፈው በተስፋ ቡድን ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ የሚካፈለውን ዋናውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡ በተስፋው ቡድን 21 ተጫዋቾች ከ11 ክለቦችና ከውጭ ሀገር ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከተጨዋቾቹ መካከል ቢኒያም ሀብታሙ ከሀዋሳ ከነማ ፣ሳምሶን አሰፋ ከሐረር ቢራ ደረጀ አለሙ ከሰበታ ከነማ በግብ ጠባቂነት ፤ ጋቶች ፓኖሞ እና፣መሱድ መሐመድ ከኢትዮጰያ ቡና ፣ያሬድ ዝናቡና መስፍን ኪዳኔ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጥላሁን ወልዴ ከመከላከያ ፣ አብዱከሪም ሀሰን ከመብራት ኀይል፣ ኤልያስ ማሞ ከኢት.ንግድ ባንክ እና፣ሙላለም መስፍን ከአርባ ምንጭ ከነማ በአማካይ መስመር ፤ ዳዊት ፍቃዱ ከደደቢት፣ዮናታን ከበደ ከመብራት ኋይል፣ አመለ ሚልኪያስ ከአርባምንጭ፣ ፍቅሩ ተፈራ ከደቡብ አፍሪካ ሱፐር ስፖርት ዩናትድና አብርሃም ካሳዬ አሜሪካን ከአላባማ ከሎሌጅ በአጥቂ መስመር ለመሰለፍ ተጠርተዋል፡፡ ዩሱፍ ሳላህ ከስዊድን የሚመጣ ሲሆን ውጭ ሀገር የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውን ተጫዋቾችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስመጣትና ያላቸው ብቃት ተፈትፎ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚሰለፉበት ሁኔታ ለማመቻቸት የግንኙነት ስራውን ተጠናክሮ መቀጠሉን ፌደሬሽኑ ገልጿል፡፡በሴካፋው ውድድር ከሚሰለፉ ተጫዋቾች መካከል ደቡብ አፍሪካ ለምታዘጋጀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሰለፉ ተተኪ ተጫዋቾች ሊገኙባቸው እንደሚችሉ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የተስፋ ቡድኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በዋና አሰልጣኝነት፣አቶ ዳንኤል ገ/ማርያም በረዳትነት እንደሚያሰለጥኑት ታውቋል፡፡በ36ኛው የሴካፋ ታስከር ቻሌንጅ ካፕ የሞት ምድቡ ፉክክር ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በሚያደርጉት ጨዋታ ሲጀመር ኡጋንዳ እና ኬንያ በሁለተኛው ጨዋታ ይገናኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር እንዲሁም በመጨረሻ ጨዋታ ከኬንያ ጋር ትገናኛለች፡፡ በኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት 4ኛ ዓመታቸውን የያዙት ስኮትላንዳዊው ቦቢ ዊልያምሰን ለሱፕር ስፖርት በሰጡት ቃለምልልስ ምድቡን አስቸጋሪ ያሉት ሲሆን ከኬንያ ጋር ያለውን ተቀናቃኝነት የማያሰጋ ብለውታል፡፡ ኬንያ እና ኡጋንዳ በሴካፋ እና በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች የረጅም ግዜ ትንቅንቅ ያላቸው ሲሆን ኡጋንዳ 20 ጊዜ ኬንያ 17 ጊዜ ሲያሸንፉ በ19 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
የዘንድሮው የሴካፋ ሻምፒዮና ተሳታፊዎች ደካማ ቡድኖች እንደሚያቀርቡ በመገለፁ እንዳይቀዛቀዝ ቢሰጋም ውድድሩ በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ተሳታፊ ለሆኑ የዞኑ ብሄራዊ ቡድኖች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው እየተገለፀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ ፌደሬሽኖች በውድደሩ ከዋናው ይልቅ በወጣት ቡድኖቻቸው ለመሳተፍ መፈለጋቸው ማስታወቃቸውም ፉክከሩን ይቀንሰዋል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን የ2012 የሴካፋ ታስከር ቻሌንጅ ካፕ መሰናዶ በተመለከተ ከምክር ቤቱ ጋር ተወዛግባ የነበረችው ኬንያ ምርጥ ቡድኗን በማሰለፍ ለዋንጫው ድል ትኩረት ማድረጓ ሲዘገብ፤ በሰርዴቪች ሚሉቲን የምትሰለጥነው ሩዋንዳ እንዲሁም የሴካፋ ምክር ቤት መቀመጫ የሆነችው ታንዛኒያ ለተሳትፏቸው ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸው ተገልጿል፡፡ ሩዋንዳውያን ዘንድሮ ዋንጫውን ለማግኘት መጓጓታቸውን የሃገሪቱ ጋዜጦች ሰሞኑን ሲዘግቡ ሰንብተዋል፡፡ ተርቦቹ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀውን የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን የሚያሰለጥነው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ነው፡፡ ሚቾ ስለ ሴካፋ ውድድር በሰጠው አስተያየት ሻምፒዮናውን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚገለፅ ጠቅሶ የሩዋንዳ ቡድን ወደ ትልልቅ ውድደሮች ወይም ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት በመጀመርያ ይህን የሴካፋ ውድድር ማለፍ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ከሴካፋ በኋላ ለ2014 የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ውድድር የ11 ቀናት ዝግጅት ለማድረግ ወደ ቱኒዚያ ይጓዛል ተብሏል፡፡ በተጋባዥነት በውድደሩ ለመሳተፍ ከጠየቁ አገራት መካከል ማላዊ ሲሳካላት ለአፍሪካ ዋንጫ ሳታልፍ የቀረችው ካሜሮን እና የደቡብ አፍሪካዋ ዚምባቡዌ ለመካፈል ጥያቄ አቅርበው አልሆነላቸውም፡፡ በሴካፋው ውድድር ካሜሮን የመግባት እድል ቢኖራተም ሀ23 ቡድኗን ለመላክ በመፈለጓ የተሳትፎ እድሉ ሳይሰጣት መቅረቱን የሴካፋ ምክርቤት አስታውቋል፡፡ ከሴካፋ ምክር ቤት አባል አገራት ጅቡቲ ብቻ የማትካፈል ሲሆን ለውድድሩ ከፍተኛ ጉጉት ያሳየችው ሶማሊያ ካምፓላ ገብታ ከሳምንት በፊት ዝግጅቷን እንደጀመረች ታውቋል፡፡




Read 4650 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 13:55

Latest from