Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 12:55

ለዋልያዎቹ ዝግጅት ብሄራዊ ርብርብ ያስፈልጋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሳላዲን እየተወራለት ነው
በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉ መካከል 14 ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካ፤ በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ሰሞኑን ባደረጓቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በይፋ ዝግጅታቸውን ጀመሩ፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የበቃችው ኢትዮጵያ እና ማላዊ ፊፋ ለወዳጅነት ጨዋታዎች ባወጣው ፕሮግራም የሉበትም፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ጋና ከኬፕቨርዴ በሊዝበን ፤ ረቡእ እለት ደግሞ በአሜሪካዋ ሚያሚ ናይጄርያ ከቬንዝዋላ ጋር እንዲሁም በጆሃንስበርግ አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ ከሻምፒዮኗ ዛምቢያ፤ አይቬሪኮስት ወደ አውሮፓ ተጉዛ ከኦስትሪያ ጋር ተጫውተዋል፡፡

በተመሳሳይ ቀን የሰሜን አፍሪካዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎች ሞሮኮ ሌላዋን የአፍሪካ ዋንጫ አላፊ አገር ቶጎን በሜዳዋ ስታስተናግድ፤ ቱኒዚያ ከስዊዘርላንድ ጋር እንዲሁም አልጄርያ ከቦስኒያ ሄርዞጎቪና ተገናኝተዋል፡፡ ኒጀር ለአፍሪካ ዋንጫ ሳታልፍ የቀረችውን ሴኔጋል ስታስተናግድ፤ ዲሪኮንጎ ከምድብ ሦስቷ ቡርኪናፋሶ እንዲሁም አንጎላ እና የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ያላገኘችው ኮንጎ ሞሮኮ ላይ ተጋጥመዋል፡፡
የምድብ 3 ቡድኖች ሁኔታ
ለ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ከተዘጋጁት ምድቦች በተለይ ምድብ 3 አሁንም በማነጋገር ላይ ነው፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብሔራዊ ቡድኑ ቢያንስ 3 የወዳጅነት ጨዋታዎች እንዲያደርግና የመጨረሻ ዝግጅቱን በደቡብ አፍሪካ እንዲያከናውን በጥረት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎቹ ምናልባትም ከጋና፤ ከኮትዲቯርና ከአልጄርያ ጋር እንደሚሆኑ ተጠብቋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ስኬታማ ለማድረግ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተካ አስፋው ሰብሳቢነት የሚንቀሳቀስ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ፤ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችን ያስተባበረው ኮሚቴው እስከ 50 ሚሊዮን ብር ገቢ በማሰባሰብ በአፍሪካ ዋንጫው ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ እየተገለፀ ነው፡፡ በ4 የአፍሪካ ዋንጫዎች ለጋና ብሄራዊ ቡድን የተሰለፈው የቀድሞ ተጨዋች ሳሚ ኩፎር ምድብ 3 ቀላል አለመሆኑን በመመስከር በተለይ ለዋንጫ ግምት የተሰጣት ናይጄርያ ከባድ ፉክክር ከዛምቢያ፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከኢትዮጵያ ይጠብቃታል ሲል ለሱፕር ስፖርት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ዛምቢያ የሻምፒዮናነት ክብሯን ለማስጠበቅ እንደምትችል የተናገረው ደግሞ የሱፕር ስፖርት ተንታኝ የሆነው የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ጋሪ ቤይሊ ነው፡፡
ከምድብ 3 በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ግንባር ቀደሟ ዛምቢያ ስትሆን ከአፍሪካ 5ኛ ከዓለም 41ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ናይጄርያ ከአፍሪካ 10ኛ ከዓለም 57ኛ ፤ ቡርኪና ፋሶ ከአፍሪካ 23ኛ ከዓለም 89ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 28ኛ ከዓለም 102ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን የሚያሚ ጨዋታ የቼልሲዎቹ ቪክቶር ሞሰስ እና ጆን ኦቢ ሚኬል ባይኖሩም የኒውካስትሉ አጥቂ ሾላ አሞቢ ለ10 ዓመታት ለብሄራዊ ቡድን ሳይጫወት ቆይቶ በ31 አመቱ ለብሄራዊ ቡድኑ ግልጋሎት የሚሰጥበትን እድል አግኝቷል፡፡ በሌቫንቴ ስፔን ላሊጋ ውስጥ የሚጫወተው ኦቦፋሜ ማርቲንስም ቡድኑን ተቀላቅሏል፡፡
ሳላዲን እየተወራለት ነው
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ባደረገቻቸው 6 ጨዋታዎች 5 ጎል ያገባው ሳላዲን ሰይድ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ይታያሉ ተብለው ከሚጠበቁ አዳዲስ ኮከቦች መካከል ተጠቃሽ እየሆነ ነው፡፡ ሳላዲን ሁለት ጎሎችን በሱዳን ላይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ፤ 3 ጎሎችን ሁለት በመካከለኛው አፍሪካ እንዲሁም አንድ በደቡብ አፍሪካ ላይ ለ20ኛው የብራዚል ዓለም ዋንጫ ማጣርያ በተደረጉ ግጥሚያዎች ላይ አስቆጥሯል፡፡ ከ1 ዓመት በፊት ደግሞ ለ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ላይ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ከናይጄርያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ሳላዲን 2 ጎሎች እንዳገባም ይታወሳል፡፡ ከ2007 እኤአ ወዲህ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመሃል አጥቂ ተሳለፊ የሆነው የ24 ዓመቱ ሳላሃዲን ለዋልያዎቹ በአጠቃላይ 12 ግጥሚያዎች አድረጎ 9 ጎሎች አግብቷል፡፡ በግብፁ ክለብ ዋዲ ዳጋላ ኤፍሲ 1 ዓመት ከ3ወር በላይ የቆየው ሳላዲን በትራንስፈርማርኬትዶት ዩኬ በቀረበው መረጃ መሰረት በገበያው የዝውውር ሂሳብ ግምቱ 100 ሺ ዩሮ ነው፡፡ ሳላዲን በአፍሪካ ዋንጫው የሚያሳየው ብቃት በእርግጠኛነት ወደተሻለ የፕሮፌሽናል ደረጃ እንደሚያደርሰው የተለያዩ መረጃዎች እየገለፁ ናቸው፡፡
የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ በምድብ 3 የመክፈቻ ግጥሚያ ከኢትዮጵያ ጋር ሲገናኙ ዋና ስጋታቸው ሳላሃዲን ሰይድ የሚያሳየው ብቃት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በግብፅ ለሚገኝ ክለብ የሚጫወተውን ሳላዲን ሰይድ እንዲጠነቀቁ ለተጨዋቾቻቸው ያሳሰቡት የዛምቢያው አሰልጣኝ አጨዋወቱን እንዳስተዋሉ ተናግረው ከአፍሪካ አዲስ ከወጡ ምርጥ ተጨዋቾች አንዱ መሆኑን ለኤምቲኤን ፉትቦል በሰጡት አስተያየት መስክረዋል፡፡
ቀድሞ የግብፁ ክለብ ዋዲ ደጋላ አሰልጣኝ የነበሩት ቤልጅማዊው ዋልተር ሜውስም ሳላዲን ሰይድ ለናይጄርያ እና ለዛምቢያ ቡድኖች ፈታኝ እንደሚሆን ለኤምቲኤን ፉትቦል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎች ውጤታማነት የሳላዲን ብቃት ይወስናል ያሉት እኝህ አሰልጣኝ ተጨዋቹ በአፍሪካ ዋንጫው ያልተጠበቀ ኮከብ ይሆናል ብለዋል፡፡ ተጨዋቹ ከዓመት በፊት በግብጹ ክለበ ዋዲ ደጋላ ለሙከራ በተሰለፈበት የመጀመርያ ጨዋታ ብቃቱን ተመልክተው የ3 ዓመት ኮንትራት ለክለቡ እንዲፈርም መወሰናቸውን የገለፁት ቤልጅማዊው ሳላዲን ሰይድ ችሎታ ያለው፤ በቴክኒክ ብቃቱ ጠንካራ፤ ጥሩ ፍጥነት እና ቦታ አያያዝ የሚችል ምርጥ አጥቂ በማለት አድንቀውታል፡፡
የምዕራብ አፍሪካ የበላይነትና የጋና ቦነስ
በ29 አፍሪካዋንጫ ላይ ከሚሳተፉ 16 አገራት ስምንቱ ብሄራዊ ቡድኖች ምእራብ አፍሪካን የወከሉበት ሁኔታ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያጋጠመ ሲሆን በዋንጫው የፉክክር ሚዛን ብልሣ እንዲኖራቸውም ምክንያት ሆኗል፡፡ በ2008 እና በ2012 በተደረጉ የአፍሪካ ዋንጫዎች 7 ብሄራዊ ቡድኖች ምእራቡን የአፍሪካ ክፍል ወክለው መሳተፋቸው የዞኑ እግር ኳስ ከፍተኛ ለውጥ በማሳየት ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡ በ2010 የደቡብ አፍሪካው 19ኛው ዓለም ዋንጫም አፍሪካን ከወከሉት ስድስት ብሄራዊ ቡድኖቹ ሶስቱ ከምእራብ የተወከሉት ጋና፤ ኮትዲቯርና እና ናይጄርያ ነበሩ፡፡ የምእራብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ ሰሜን አፍሪካውያን ይዘውት የነበረውን የበላይነት እየሸረሸሩ ናቸው፡፡ ከ1994 ውዲህ በተደረጉት 12 የአፍሪካ ዋንጫዎች ምእራብ አፍሪካን የወከሉ 7 ብሄራዊ ቡድኖች ለዋንጫ ፍልሚያ በቅተዋል፡፡በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሻምፒዮናነት ፉክክር በአፍሪካ የስፖርት ተንታኞች ቅድሚያ ግምት ያገኙት 6 አገራት ጋና፤ኮትዲቯር፤ አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ፤ ሻምፐዮናነቷን ለማስጠበቅ የምትሰለፈው ዛምቢያ አልጄርያ እና ናይጄርያ ሆነዋል፡፡
ያልተጠበቀ ድል ያስመዘግባሉ የተባሉት ብሄራዊ ቡድኖች ደግሞ ቱኒዚያ፤ሞሮኮ፤ አንጎላ እና ዲ ሪፕብሊክ ኮንጎ ናቸው፡፡ የሻምፒዮናነት እድል የላቸውም የተባሉት 6 አገራት ኢትዮጵያ፤ ኬፕቨርዴ፤ ኒጀር፤ቶጎ፤ ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ናቸው፡፡ለአፍሪካ ዋንጫው ድል አድራጊነት ከፍተኛ ግምት ካገኙት የምእራብ አፍሪካ ቡድኖች አንዷ ጋና ስትሆን ለዝግጅት እና እስከ ዋንጫው ለሚደረግ ግስጋሴ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን 8 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደያዘ ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የመጨረሻ ዝግጅት እቅድ የነበረው የጋና ብሄራዊ ቡድን ሃሳቡን በመቀየር በውድደሩ የዋዜማ ሰሞን በአቡዳቢ የ11 ቀን ዝግጅት እቅድ በማውጣት እና 1.06 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመያዝ መስራት ጀምሯል፡፡
ለጋና ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ለአፍሪካ ዋንጫው ከዝግጅት እስከ ዋናው ውድድር ለተጨዋቾች በቀን 100 ዶላር ለአሰልጣኞች እና ለባለሙያዎች በቀን 150 ዶላር አበል ለመክፈል ፌደሬሽኑ መዘጋጀቱን ሲያስታውቅ የየጨዋታው አሸናፊነት ቦነስን በ50 በመቶ በማሳደግ ጥቋቁር ክዋክብቶቹን በማነሳሳት ላይ ነው፡፡ እያንዳንዱ የጋና ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች በአፍሪካ ዋንጫው ብሄራዊ ቡድኑ ለሩብ ፍፃሜ ከደረሰ 17500 ዶላር፤ ግማሽ ፍፃሜ ከገባ 20ሺ ዶላር፤ ለደረጃ ጨዋታ ከተደረሰ 22ሺ ዶላር እንዲሁም ለዋንጫ ጨዋታ ከተበቃ 25ሺ ዶላር በነፍስ ወከፍ ቦነስ እንደሚሰጥ ቃል ተገብቷል፡፡
የአውሮፓ ምርጦች
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎቹ አገራት ሰሞኑን ባደረጓቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በአውሮፓ ሊጎች የሚገኙ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን እንደፈለጉት አለማካተታቸው በአንዳንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ ይሁንና እነዚህ ተጨዋቾች በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሚጀመርበት ወቅት የአውሮፓ ሊጎች ፋታ ስለሚያገኙ ሙሉ ለሙሉ ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው ግልጋሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ አንደኛ ዲቪዚዮንና በሻምፒዮንሺፕ ደረጃ በሚገኙ ክለቦች የሚጫወቱ ከ21 በላይ አፍሪካውያን ለየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ለመሰለፍ ደቡብ አፍሪካ ይሰነብታሉ፡፡ አርሰናል የጋናዎቹን ኢማኑዌል ፍሪምፖንግ፡ ጄሴ ቡዋቴንግ፣ የአይቬሪኮስቱን ዠርቪንሆ የሞሮኮውን ቻማክ በአፍሪካ ዋንጫው ያጣል፡፡
ቼልሲ የናይጄርያዎቹን ኦቢ ሚኬል እና ቪክቶር ሞሰስ እንዲሁም የቡርኪናፋሶውን በርትራንድ ትራዎሬን ይለቃል፡፡ ፉልሃም የማሊውን ማሀመዱ ዲያራ፤ ማንችስተር ሲቲ የአይቬሪኮስቶቹን የቱሬ ወንድማማቾች ፤ ዌስት ብሮም የናይጄርያውን ፒተር ኦዲምንጉዌ ለአፍሪካ ዋንጫው በመስጠት ይጠቀሳሉ፡፡ በሜትዝ፤ በሞናኮ፤በአርሰናል፤ በማንሲቲ፤ በሪያልማድሪድ እና በቶትንሃም ሆትስፕርስ ክለቦች የተጨዋተው የቶጎው ኢማኑዌል አደባዬርም አለ፡፡
በፈረንሳይ ለማርሴይ ፤ ሎረንቴ እና ለሌንስ እንዲሁም በሰሜን ለባርሴሎና እና ለሲቪያ አሁን በቻይና ለሚገኘው ዳሊያን አርቢን ክለብ ፈርሞ የሚጫወተው የማሊው ሰይዱ ኪዬታ፤ በጋና ቡደን አሳሞሃ ጊያን እና ሱሊ ሙንታሪ፤ ጆን ኦቢ ሚኬል ኢኬቹኩ ኡቼ እና ያኩቡ አያጌቢኒ በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን፤ በእንግሊዝ እና በስፔን ክለቦች ይጫወት የነበረውና አሁን በቱርክ የሚገኘው የአንጎላው ማኑቾም ለአፍሪካ ዋንጫው ከሚጠበቁ ክዋክብት ይጠቀሳሉ፡፡
ዲዲዬር ድሮግባ በ34 ዓመቱ፤ የ29 ዓመቱ ያያ ቱሬ፤ ኢማኑዌል ኤቡዌ እና ዲዲዬር ዛኮራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አንጋፋ ተጨዋቾች ተብለው ሲጠቀሱ አገራቸውን ለድል ለማብቃት የመጨረሻ እድል ይዘው ለአፍሪካ ዋንጫው ድምቀት ይፈጥራሉ የተባሉ ናቸው፡፡

 

Read 6302 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 13:04