Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 11:15

ያልጠለቀችው የቀብሪ ደሃር ፀሐይ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከሠላሣ ስድስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ምድር የሃዘን፣ የሥቃይና የመከራ ምድር ሆኖ ነበር፡፡ ገና በክረምቱ መግቢያ ወቅት የዚያድባሬ መንግስት ወታደሮች በዶሎ፣ በቡሬና በጐዴ ከተሞች ላይ ወረራ አካሄዱ፡፡ ህፃናት፣ ሴቶችንና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ሣይቀር እየገደሉ ከተሞቹን ተቆጣጠሯቸው፡፡በምሥራቃዊው የአገሪቱ ክልል አካባቢ ውጥረቱ አየለ፡፡ በሠላም ወጥቶ መግባት የማይታሰብ ሆነ፡፡ በብረት ለበስ መሣሪያዎች፣ በመድፍና በቢኤም 23 ሮኬቶች ተደራጅቶ ለወረራ የመጣውን የሶማሊያ ጦር ለመቋቋም የሚያስችል መሣሪያ ቀርቶ ሮጦ ለማምለጥ አቅም እንኳን ያልነበራቸው ደካማ የጅጅጋና ዙሪያዋ አካባቢ ነዋሪዎች ሐምሌ 12 ቀን 1969 ዓ.ም ማለዳ ላይ መከራ ዘነበባቸው፡፡

የሶማሊያ ጦር እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን ዘመናዊ መሣሪያ በመጠቀም አካባቢውን ዶግ አመድ አደረገው፡፡ የቀብሪ ደሃር፣ ጅጅጋ፣ ደገሃቡር፣ ጐዴና ዋርዴር ከተሞች በጠላት ቢኤም 23 ሮኬቶችና መድፎች ጋዩ፡፡ ከሞት መንጋጋ ለማምለጥ የሚራወጡት የአካባቢው ነዋሪዎች ሽሽታቸውን ቀጠሉ፡፡ ልጆቻቸውን ጉያቸው የታቀፉ እናቶች፣ ሕፃን ልጁን እሽኮኮ ብሎ የሚሸሽ አባት፣ ደካማ እግራቸውን እየጐተቱ የሚሮጡ ሽማግሌና አሮጊት፤ አካባቢው ለስደት በሚራወጡ ነዋሪዎች የሰቆቃ ጩኸት ተሞላ፡፡
ከመጣበት የሞት ሠራዊት መሸሹን እንጂ ወደየት እንደሚሸሽ የማያውቀው ስደተኛ ነፍሱን ለማዳን እየወደቀ እየተነሣ ይሮጣል፡፡ አራስ ልጇን አቅፋ፣ የሁለት ዓመት ህፃን ልጇን ደግሞ በጀርባዋ አዝላ የምትሮጠው የቀብሪደሃር ነዋሪዋ ወ/ሮ በቀለች በየነ፤ ከስደተኞቹ መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ሁለት ህፃናትን ታቅፋ መሮጧን የተመለከቱ ጐረቤቶቿ፤ በእጇ የታቀፈችውን አራስ ልጅ ተቀበሏት፡፡ ሩጫው ቀጠለ፡፡ የከባድ መሣሪያ ድምፅ ጆሮአቸው ላይ እየጮኸ ከሚሮጡት ሰዎች መካከል አንዲት እናት በመድፍ ፍንጣሪ ተመትታ ወደቀች፡፡ በጀርባዋ ካዘለችው ህፃን ልጄ ጋር በመድፍ ፍንጣሪው የተመታችው እናት ወ/ሮ በቀለች ነበረች፡፡ ከወደቀችበት ተንገዳግዳ ተነስታ ወደፊት ሮጠች፡፡ በጀርባዋ ያዘለችው ህፃን ግራ እጁ በመድፍ ፍንጣሪ በመመታቱ ደሙ እንደውሃ ይፈሣል፡፡
እጁ የተንጠለጠለችው በቀጭን የክንድ ሥጋው ብቻ ነበር፡፡ እናት ጀርባዋ በደም ተነክሯል፡፡ የመድፍ ፍንጣሪ የእሷንም የግራ ጡት ቆርጦታል፡፡ ደሟ እንደ ጉድ ይፈሳል፡፡ ተቆርጦ የተንጠለጠለውን ጡቷን ከደረቷ ጋር በለበሰችው ጨርቅ አሥራ ሽሽቷን ቀጠለች፡፡ በጀርባዋ ላይ ያዘለችው ህፃን ከድካሙና ከረሃቡ በላይ ከተቆረጠው እጁ የሚፈሰው ደሙ አድክሞታል፡፡ ትንፋሹ እምብዛም አይሰማም፡፡
የሽሽት ጓደኞቿ በሁኔታዋ እጅግ አዘኑ፡፡ በጀርባዋ ያዘለችው ህይወት የሌለው ህፃን መሆኑን በማሰብ “ሬሣ ይዘሽ ሽሽት አትሂጂ፤ በቃ አንዱ ጋ ጣይውና ሂጂ፤ ተሸክመሽው መሄድ አትችይም” አሏት፡፡ ከደረቷ ላይ ተቆርጦ ከተንጠለጠለው ጡቷ ደሟ እንደውሃ ፈሶ ያደከማት እናት፤ በጀርባዋ ያዘለችው ህፃን ህይወት እንደሌለው መስማቷ እጅግ አስደነገጣት፡፡ ከሞት መንጋጋ ልታድነው ይዛው የተሰደደችው ልጇን ሞት አሣዶ እንደያዘባት ስታውቅ እጅግ አዘነች፡፡ አማራጭ አልነበራትምና የተንጠለጠለ እጅ የያዘውን ሕፃን ልጇን በአንድ ዛፍ ጥላ ሥር ጥላው ሄደች፡፡ እናት ከሽሽት ጓደኞቿ ጋር እግሯ ወደመራት ስደቷን ቀጠለች፡፡ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ አካባቢውን በማሰስ ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች በደም ተከብሎ ከዛፍ ሥር የወደቀውን የሁለት አመት ህፃን አገኙት፡፡ ህፃኑ ይንቀሣቀሣል፡፡ ነፍስ እንዳለው ሲያረጋግጡም ከወደቀበት አንስተው ህክምና ሊያገኝ ወደሚችልበት ሥፍራ ወሰዱት፡፡ ያልተቆረጠች ነፍስ ሆነችና ግራ እጁ በክንዱ ላይ ተቆርጦ ህይወቱ ተረፈ፡፡
የዚህ ታሪክ ባለቤት ዛሬ የሰላሣ ስምንት ዓመት ጐልማሣ ሆኗል፡፡ ከትናንት በስቲያ የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ሰለባ ኢትዮጵያውያን ማህበር አዘጋጅቶት በነበረው ሲምፖዚየም ላይ ያገኘሁት ይህ ሰው መሀመድ አህመድ ይባላል፡፡ መሀመድ ይህንን ዘግናኝ የጦርነት ታሪኩን ሲያጫውተኝ እምባና ሣግ እየተናነቀው ነበር፡፡ በሞቃዲሾ ሆስፒታል ገብቶ ግራ እጁን ተቆርጦ ህይወቱ ከተረፈ በኋላ የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ለኢትዮጵያውያን ምርኮኞች ወደተዘጋጀው የእሥር ቦታ ወሰዱት፡፡ የዚህችን ዓለም የመከራ ፅዋ ገና በሁለት ዓመት ዕድሜው መቅመስ የጀመረው ህፃን፤ እጅግ ዘግናኝ በሆነው የሶማሊያ እስር ቤት ለአሥራ አንድ አመታት ታስሯል፡፡ በ1981 ዓ.ም የኢትዮጵያና የሶማሊያ መንግስታት በደረሱበት የሠላም ስምምነት መሠረት፤ እስረኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲደረግ ለአገሩ አፈር በቃ፡፡ አባት፣እናት፣ እህት፣ ወንድም ያልነበረው መሀመድ፤ ወደ አገሩ ቢመጣም መግቢያ አልነበረውምና መንግስት ወላጆቻቸውን በጦርነቱ ላጡ ልጆች ወዳዘጋጀው የማሣደጊያ ካምፕ አስገባው፡፡ ግራ እጁን ስለ አጣባት ሁኔታና ስለቀድሞ ታሪኩ እንደእሱ ሶማሊያ ውስጥ በስደት ላይ ከነበረው አጐቱ ይሰማ የነበረው መሀመድ፤ ቤተሰቦቹ በህይወቱ ይኖራሉ ብሎ ለደቂቃም አስቦ አያውቅም፡፡ በዛ የጦርነት እሣት መሃል ሬሣ ታቅፈሽ አትሂጂ ተብላ ዛፍ ጥላ ሥር ጥላው የሄደችው እናቱ፤ የፈንጂ ፍንጣሪው ያደረሰበት አደጋ በህይወት ለመቆየት የሚያስችላት አለመሆኑ ተነግሮታልና ተስፋ ቆርጧል፡፡ ሕይወቱን የታደጉለት የሶማሊያ ወታደሮችም በምን ሁኔታ ላይ ሆኖ እንዳገኙት የወሬ ወሬ ሰምቷል፡፡ ኑሮ በካምፕ ውስጥ ቀጥሏል፡፡ ከካምፕ ህይወት ውጪ ብዙም የህይወት ልምድ የሌላቸው ወጣቶች የእርስ በእርስ ፍቅራቸው ደስ ይላል፡፡
አንድ ቀን መሀመድ ከካምፕ ጓደኞቹ ጋር ከግቢው ለመውጣት በራፍ ላይ ደርሷል፡፡ አንዲት ሴት የልብስ ቦርሳዋን እንዳንጠለጠለች ወደ ካምፑ ታመራለች፡፡ ፊቷ በእንባ ታጥቧል፤ ሁኔታዋ በጣም አሣዘነው፡፡ ምን ሆና ነው ሲልም ቆም ብሎ በሃዘን ተመለከታት፡፡ እያነባች ወደ ካምፑ ገባች፡፡ የሴትየዋ እምባ ውስጡን ያሣዘነው መሀመድ፤ ከጓደኞቹ ጋር ከግቢው ወጥቶ ሄደ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ ከኋላው ስሙ ሲጠራ ሰማ፡፡ ዳይሬክተሩ ቢሮ በአስቸኳይ እንደሚፈለግ
ምን አጠፋሁ ብሎ ራሱን እየጠየቀ ወደተጠራበት ቢሮ ሄደ፡፡ በቢሮው ውስጥ ያቺ በመግቢያው በር ላይ በእምባ እየታጠበች ያያት ሴት ቁጭ ብላለች፡፡ ዳይሬክተሩ “ይህቺ ሴት ማነች” ብሎ ሲጠይቀው አላውቃትም ነበር መልሱ፡፡ “እናትህን ብታያት ታውቃታለህ?” ዳይሬክተሩ ደግሞ ጠየቀው፤ በፍፁም ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡ ከዚህ በላይ ታግሳ መቆየት ያልቻለችው እናት፤ እየጮኸች ልጇ ላይ ተጠመጠመች፡፡ መሀመድ ታሪኩን ያጫወተኝ ወጥቼ ካልፈሰስኩ እያለ ከሚተናነቀው እምባው ጋር እየታገለ ነው፡፡ ገና ከህፃንነት እድሜው ጀምሮ ከዚህች ምድር ሥቃይና መከራ ጋር እየታገለ አድጓል፡፡ የልጅነት ህይወት፣ የእናት የአባት ፍቅር፣ የአገርና የወገን ስሜት የሚባሉትን ነገሮችም እምብዛም አያውቃቸውም፡፡ ግን ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ በህይወት ቆይቶ ዛሬን ለማየት ታድሏል፡፡ የሶማሊያ ፈንጂ ግራ እጁን እንጂ ህይወቱንና ተስፋውን ሊነጥቁት አልቻሉምና ዛሬ የሰላሣ ስምንት አመት ጐልማሣ ሆኖ፣ ትዳር ይዞ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ በትምህርቱ ባለመግፋቱ ላይ አካል ጉዳተኝነቱ ተጨምሮበት ህይወቱን ከባድ አድርጐበታል፡፡ ዛሬ ኑሮውን እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አድርጐ በአንድ የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት መስጫ ውስጥ ተቀጥሮ በሚያገኘው ጥቂት ደመወዝ ቤተሰቡን ያስተዳድራል፡፡ እዛው መፀዳጃ ቤቱ አካባቢ 100 ብር እየከፈለ በሚኖርበት ቤት ውስጥ ህፃን ልጁን ያሣድጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ጦርነት ሰለባ ኢትዮጵያውያን ማህበር በግዮን ሆቴል ያለፈው ሐሙስ ሳምንት አዘጋጅቶት በነበረው ሲምፖዚየም ላይ ከነበሩት የጦርነቱ ሰለባዎች አብዛኛዎቹ በዕድሜ የገፉና የደከሙ ናቸው፡፡ ከህይወታቸው (ከዕድሜያቸው) ላይ በግፍ የተቀሙት አስራ አንድ ዓመታት እጅግ ለከፋ ጉስቁልናና የአእምሮ ጉዳት ዳርጐአቸዋል፡፡ በሐዋይ፣ በመንዴራና በቡርወይኔ እስር ቤቶች ውስጥ ያሣለፏቸው አስራ አንድ የሥቃይ፣ የመከራና የግፍ ዘመናትን ሲናገሩ አንጀት ይበላሉ፡፡ ከነቀዘ ማሽላ የተቀቀለ ንፍሮ፣ የበቆሎ ሙቅና ቀጭን ገንፎ ለአስራ አንድ ዓመታት ሲመገቡ ኖረዋል፡፡ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ እየተዘጋጀ የሚቀርብላቸው ምግብ ጤንነታቸውን በእጅጉ አቃውሶት ህይወታቸውን እዛው እስር ቤት ውስጥ ያጡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም እንደነበሩ እማኞቹ ይናገራሉ፡፡ ዓለም ዘንግቷቸው፣ የት እንዳሉ ተረስተው ከቆዩ ከዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ፣ እውነታውን መቀበልና ማመን ተስኖአቸው ነበር፡፡ የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ስደተኞቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ብዙ ተስፋ ሰጥተዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ግን ተስፋው የሚጨበጥ አልሆነም፡፡ የደርግ መንግስት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅትም ለእነዚህ ከስደት ተመላሽ ወገኖች ብዙ ተስፋዎች ቢሰጣቸውም አንዱም ተሣክቶ ለማየት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ እጅግ በሚዘገንን ህይወት ውስጥ እንዳሉና ዛሬም ኑሮአቸው ከስደት ዘመኑ ያልተሻለ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡ “ለዓመታት በስደት አገር በግፍ ድርጊት መቆየታችን ሣያንስ ዛሬም በገዛ አገራችን በረሃብና በችግር ማለቃችን ነው፡፡ ችግራችንን መንግስትና ወገኖቻችን ሊያውቁልንና ከጐናችን ሊቆሙ ይገባል” ይላሉ፡፡ በእነዚህ የጦርነት ሰለባዎች ስም ከተቋቋመ አምስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ማህበርም አሁን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆነ በሲምፖዚየሙ ላይ ተገልጿል፡፡ ከማህበሩ ጋር አብሮ ለመሥራትና ለወገኖቻቸው አለኝታነታቸውን ለማሳየት በርካታ ድርጅቶችና የኪነጥበብ ማህበራት ፈቃደኝነታቸውን በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ ተናግረዋል፡፡
የእነዚህ የጦርነት ሰለባ ኢትዮጵያውያን እምባ ታብሶ የምናይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

 

br /

Read 4452 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:27