Saturday, 14 July 2012 06:52

የባህል ለውጥ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

የባህልን ትርጉም ፍለጋ ስማስን እንደ መነሻ  … ባህል ለውጥ ነው፤ ብያለሁ … እንደ መከተያ፡- ባህልን እንዲለዋወጥ የሚያደርገው ደግሞ … ማስመሰል ነው ብልስ? (ምን ይለኛል!)

የምንቀዳው ከአባቶቻችን ከሆነ፣ የአባቶቻችን ባህል ብዙ ቅርፁን

ሳይቀይር አብሮን መኖሩ አይቀርም፡፡

… “የአባቶቻችን ቤት ባዶ ይሁን ኦና /በኛ ቁመት በኛ መጠን አልተቀለሰምና” ካልን ደግሞ፤ ከሌላው ለመኮረጅ መሄዳችን አይቀርም፡፡

የወፎቹ ወንዴ ዝርያ የሚዘምረው ባለ አንድ አይነት ቅላፄ ዜማ (dialect) አለው፡፡ ለምሳሌ ስምንት ወንዴ ወፎችና ሌሎች ጐረቤት የሚገኙ የዚህኑ ቁጥር የሚያክሉ ወፎች በአንድ ላይ እየተቀባበሉ የሚዘፍኑት ዘፈን አለ፡፡

ከተፈጥሮ ስጦታው በመነሳት ተፈጥሮን የማንሳት እና የመጣል አቅም ፈጥሯል፡፡ ይህ አቅሙ ታሪኩ ነው፤ የባህል ታሪክ፤ ትውፊት፡፡ የዚህ አቅሙ ታሪክ ነው… የሀሳብ ታሪክ፡፡ የዚህ አቅሙ ታሪክ ነው በአጭሩ… የስልጣኔ ታሪክ፡፡

የሰውን ልጅ እንደ ግለሰብ ማንነቱ ብቻ ማሰብ እሩቅ አላራምድብሎኛል፡፡

ስለዚህ፤ የሰውን ልጅ በጥቅሉ የሚገልፀውን ቋንቋ መረዳት አስፈለገኝ፡፡ ሁሉም የትርጉም ቀስቶች የመሩኝ ወደ አንድ ማጠቃለያ ሆኖ አገኘሁት፡፡

ይህ፤ ሁሉም ትንንሽ የትርጉም ጅረቶች ወደ ወንዝ … ወንዙ ወደ ባህር … ባህሩ ደግሞ ውቂያኖስ ሆኖ የሰው ልጅ ማንነት የሚጠቃለልበት የመጨረሻው ስፍራ … እንደ ቀላል በሶስት ፊደል ስንጠራው የኖርነው መሆኑ ይደንቃል፡፡ ስለዚህ ቃል ማወቅ ማለት … ስለ ሰው ልጅ በአጠቃላይ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ ሁሌ ግራ የሚያጋባን የማንነታችን ጥያቄ ትርጉም የመልስ ደብዳቤ ደረሰው እንደ ማለት ይሆንልናል፡፡ ይህ ባለ ሦስት ፊደል ቃል “ባህል” ይባላል፡፡

የባህል ባህሪ ምንድነው?

ባህል የሚለው ቃል በውስጡ ምን ምን እንደሚያካትት እንጂ … እንደራሱ (የቃል ፍቺ) ቅልብጭ ያለ ማንነት ሰጭ ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ ባህል ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ እንጂ አመክንዮአዊ የትርጉም እልባት ያልተሰጠው ባህል፤ በውስጡ ምን ምን ያካተተ እንደሆነ በብዛት ተዘርዝሯል፡፡

ባህል በውስጡ ቋንቋን፣ አለባበስን፣ አኗኗር ዘይቤን፣ ፋሽንን፣ በአጠቃላይ የጥበብ ዘርፎችን፣ አስተሳሰብን፣ የስነ ምግባር ደንቦችን፣ እምነትን፣ ተስፋን ጭምር ያቀፈ ነው፡፡ …

ዝርዝሩ ግን ጥቅል ትርጉም አይሰጠንም፡ ባህል ማለት፤ ሁሉም ነገር ማለት ነው ብንል እንኳን መልስ አይሆነንም፡፡

በተዘረዘሩት የባህል ዘርፎች ላይ ግን የምናስተውለው ነገር አለ፡፡ ይኼውም ነገር … እነዚህ በባህል ውስጣዊ ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሱት መገለጫዎች በሙሉ … ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለወጡ ገፅታዎች መሆናቸውን ነው፡፡

ስለዚህ፤ እቅጩን ካስፈለገ፤ እኔ ለባህል ምንነት የምሰጠው ትርጉም፡- “በየጊዜው የሚለወጥ የሰው ልጅ ማንነት” የሚል ነው፡፡ የሚለወጥ ነገር በሙሉ ተስፋና ታሪክ አለው፡ ታሪክ ያለፈው ከለውጥ በፊት የነበረው ባህል ከሆነ፤ ተስፋ ደግሞ ባህል ወደፊት መሆን የሚፈልገው … የባህል ራዕይ ነው፡፡

የሰው ልጆችን ባህል ከዛሬ ወደ ነገ ወይንም ባህልን ከተስፋና ራዕይ ጋር ወደፊት ወስዶ በማጨባበጥ ባህልን ወደ ትውፊት (Tradition) የሚለውጠው ነገር “ሀሳብ” ነው ይላሉ፡፡ … መላምታዊያን!

የሰው ልጅ የባህል ዝግመት አሊያም ፍጥነት ለውጥ፣ በሐሳቦች አማካኝነት የተከሰተ ነው ማለታቸው ነው፡፡ … ነገር ግን፤ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ሀሳብ ራሱ ከሰው ልጅ የሚመነጨው በቋንቋው፣ በጥበቦቹ፣ በእምነቶቹ አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ታሪክ በሀሳብ አማካኝነት የሚለዋወጠው ባህሎች ገድል ነው ልንል እንችላለን፡፡ ነገር ግን፤ የሰው ልጅ ሀሳብ ራሱ በባህል ውስጥ የሚጠቃለል ከሆነስ? … ያኔ የሰው ልጅ ታሪክ ራሱ የባህሉ ታሪክ ሊሆን አይደልን?

የባህልን ትርጉም ፍለጋ ስማስን እንደ መነሻ  … ባህል ለውጥ ነው፤ ብያለሁ … እንደ መከተያ፡- ባህልን እንዲለዋወጥ የሚያደርገው ደግሞ … ማስመሰል ነው ብልስ? (ምን ይለኛል!)

… የባህል ውርርስ ሽግግር ትውውቅ … ተደጋግሞ ሲባል ብዙ ጊዜ ሰምተናል፡፡ በህይወት እስካለን ድረስም መስማታችንን እንደምንቀጥል አልጠራጠርም፡፡

የባህል ውርርስ ማለት … መቅዳት እና ማስቀዳት ማለት ነው፤ በአጭሩ፡፡ … ለምሳሌ እኔ የአንድ የፈረንጅ ቋንቋን ስማር፣ የቋንቋ እውቀቱን ብቻ ሳይሆን ባህሉንም አብሬ እየቀዳሁ  ነው፡፡ … እውቀት እና ከእውቀት የሚመነጩ ሀሳቦችም የተቀዱ ናቸው፡፡ … ከግሪክ ሮማ - ከሮማ አውሮፓ - ከአውሮፓ - አፍሪካ - ሰሜን አሜሪካ፡፡

“ያልተቀየጠ ባህል ነው ያለን” የሚል ህዝብ (የእኛን የመሰለ) እንኳን ስንት እርስ በራሱ እንኳን የተቀዳዳው ነገር አለ፡፡ ከግብፅ፣ ከአረብ፣ ከታንዛኒያ ከኬንያ…፡ ባህል ማለት ማስመሰል ነው፡፡ ከአንዱ መውሰድ ለሌላው መስጠት … የተሰጠውም ለሌላ ማቀበል ይኖርበታል፡፡ የሰው ልጆች ዋና ባህሪ ባህል ከሆነ፣ ባህል ደግሞ ማስመሰል /መምሰል imitation ነው፡፡ ሜም (meme) ይሉታል በፈረንሳይኛ፡፡ መቅዳት ማለት ነው፡፡ እውቀት ራሱ ከሆነ ቦታ የተቀዳ ነው፡፡ ከተፈጥሮም ይሁን የተቀዳው አልያም ከተመክሮ … ግን የተቀዳ ነው፡፡ … እውቀት ብቻ ሳይሆን እምነትም (እንደ ሀሳብነቱ) ከሆነ ቦታ የተወረሰ ነው፡፡ እምነቱ ወደ እለታዊ የአኗኗር ዘዴ እና ስርዓት ገብቶ ሲቀላቀል ሀይማኖት ይባላል፡ ምንም አይነት እውቀት ከውጫዊ ተፈጥሮ በሰውኛ አእምሮ የተቀዳ መሆኑ ብቻ meme ያደርገዋል፡፡

እስቲ በኒውዚላንድ ስለሚገኝ ሳድልባክ (Saddle back) የተባለ ወፍ እንደ ሀሳባችን መመዘኛ ምሳሌ አድርገን እንመልከት፡-

የወፎቹ ወንዴ ዝርያ የሚዘምረው ባለ አንድ አይነት ቅላፄ ዜማ (dialect) አለው፡ ለምሳሌ ስምንት ወንዴ ወፎችና ሌሎች ጐረቤት የሚገኙ የዚህኑ ቁጥር የሚያክሉ ወፎች በአንድ ላይ እየተቀባበሉ የሚዘፍኑት ዘፈን አለ፡፡ እንደተሟላ ኦርኬስትራ እየተቀባበሉ ሲዘምሩ፤ አንዳንዴ፤ ከአንድ ቅላፄ በላይ የሆኑ ዜማዎች ያወጣሉ፡፡ አባት ወንድ ወፍ እና ልጅ ወፍ የሚዘምሩት ዘፈን እንዲህም ሆኖ የተለያየ ነው፡፡ ልጅየው ወፍ የለመደውን ዘፈን ከአባቱ በዘረመሉ የወረሰው ሳይሆን ከሌሎች ወፎች በመቅዳት መሆኑን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረገው ሳይንቲስት (P.F.Jenkins) ይገልፃል፡፡

[N.B ማስመሰልን እንደ መጥፎ ነገር እንመለከተው ነበር፤ እኔና እኔ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ የዘመናችንን ባህል የተመለከትን እንደሆነ ከሚገባው በላይ በማስመሰል የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በወጣቶቹ ላይ ደግሞ ይህ ባህርይ የበለጠ ይጐላል፡፡ ሁሉም መሆን የሚፈልጉት አንድ Idol አላቸው፡፡ የክፍለ ሀገሩ ልጅ የአዲስ አበባውን መምሰል ሲፈልግ … የጨርቆሱ የቦሌውን መሆን ሊፈልግ ይችላል፡፡ የቦሌው ልጅ ደግሞ የሀርለሙን ልጅ መሆን ሊመኝ … ወዘተ፡፡ የሀርለሙ ደግሞ አፍሪካዊ መሆን ይሆናል ህልሙ፡፡ መምሰል የምንፈልገው ብቻ ሳይሆን፤ ልንመስለው የምንፈልገው … ሊመስለን መፈለጉን መዘንጋት የለብንም፡፡ (ምእራባዊ ከአፍሪካዊ ጋር የሚያደርገው ጋብቻ ትርጉሙ ይሄ ይሆን?) የእንቅስቃሴ ህግ ደንብ (Dynamism) ነው]

ባህልን በሳይንሳዊ እይታ ለመረዳት ካስፈለገ የዝግመተ ለውጥ (evolution) ፅንሰ ሀሳብን እንደ መነፅር አድርጐ መገልገል ይጠቅመናል፡፡ በዝግመተ ለውጥ ሂደት የሰው የተፈጥሮ ብልጫ (Biological advantage) አንጐሉ ነው፡፡ ተፈጥሮ አንጐልን ይሰጠዋል፡ በተፈጥሮ ብልጫ ስጦታው ተጠቅሞ የሚፈጥረው ነገር ግን… የራሱ ግኝት ወይንም ፈጠራ ነው፡፡ በአጭሩ (በጥቅሉ) ባህል ብለን የጠራነው ነገር ነው ይህ ፈጠራው፡ … ከአካል የዝግመተ ለውጥ ውጭ ፍጡሩ (ሰው)… እርስ በራሱ እየተማማረ፣ እውቀት እየተወራረሰ … ራሱን በራሱ … ከተፈጥሮው የዝግመተ ሂደት ፍጥነት በላይ የሚያሳድግበት መንገዱ ነው፡፡ በሰውነት አካሉ መለወጥ ያልቻለበት ዘገምተኛ ውስንነት በባህሉ ወሰን አልባ የለውጥ ፍጥነት ተቀድሟል፡፡

ከተፈጥሮ ስጦታው በመነሳት ተፈጥሮን የማንሳት እና የመጣል አቅም ፈጥሯል፡፡ ይህ አቅሙ ታሪኩ ነው፤ የባህል ታሪክ፤ ትውፊት፡ የዚህ አቅሙ ታሪክ ነው… የሀሳብ ታሪክ፡፡ የዚህ አቅሙ ታሪክ ነው በአጭሩ… የስልጣኔ ታሪክ፡፡

በባዮሎጂያዊ መንገድ ያገኘውን የዘረ መል ተፈጥሮ እንኳን በባህሉ የመለወጥ አቅም ላይ ዘንድሮ ደርሷል፡፡ (ጀኔቲክ ኢንጂነሪንግን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን) ይህ ባህል ሳይንስ ተብሎ የሚጠራው ነው፤ ትርጉሙም “To know” ማለት ነው፤ በላቲን ቋንቋ፡፡ … የማወቅ ባህል ብለን ልናሳጥረው እንችላለን፡፡ የማወቅ ባህልም የሚካተተው በዛው በባህል ምህዳር ውስጥ ነው፡፡ ባህል ሁሉንም ነገር ያጠቃልላል፡፡

The old gene selected evolution, by making brains, provides the soup in which the first memes arose. Once self copying memes had arisen, their own, much faster, kind of evolution took off. Imitation, in the broad sense, is how memes can replicate.

እንግዲህ ባህልም በመወራረስ የሚገኝ ሆኖም፤ አንዳንዱ ባህል ለአጭር ጊዜ እንደ ፋሽን ብቅ ብሎ እልም የሚል ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ እንደ ሀይማኖት ለብዙ ዘመናት የሚቆይ ይሆናል፡፡ … ይህም ባህሪው ከተፈጥሮው ወይንም በተፈጥሮ ትዕዛዝ ከሚታዘዘው የአካል ባህሪው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ለምሳሌ ተፈጥሮ በምርጫ ሂደቱ (Natural Selection) …. ጥሩውን ዘረ-መል ወስዶ መጥፎውን እንዳይበዛ ቀጭቶ እንደሚያስቀረው ሁሉ፤ ባህልም በራሱ ረገድ የሚነግሰውን ወይንም የሚወርሰውን እና እንደ እባጭ አብጦ ከፈነዳ በኋላ የሚሟሽሸውን ይመርጣል፡፡

የአይሁዶች ሀይማኖታዊ ህጐች ለብዙ ሺ አመታት መቆየት ሲችሉ … የሴቶች ታኮ ጫማ የማድረግ ባህል ደግሞ መቆየት አቅቶታል፤ እንደማለት፡፡

መቅዳት፣ መኮረጅ፣ መማር፣ ማስመሰል … ሁሉ ባህልን መውረሻ መንገዶች ናቸው፡፡ የምንቀዳው ከአባቶቻችን ከሆነ፣ የአባቶቻችን ባህል ብዙ ቅርፁን ሳይቀይር አብሮን መኖሩ አይቀርም፡፡ … “የአባቶቻችን ቤት ባዶ ይሁን ኦና /በኛ ቁመት በኛ መጠን አልተቀለሰምና” ካልን ደግሞ፤ ከሌላው ለመኮረጅ መሄዳችን አይቀርም፡፡ በሁለቱም አካሄድ ግን ባህል ይኖራል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ጉዳይ… ባህል ሁልጊዜም እንደሚኖር እና መኖሩንም የምናረጋግጠው በመለወጡ መሆኑን ነው፡፡ … ምኒሊክን ለመሆን የፈለገ የዛሬ ትውልድ … ምኒሊክን የሚሆነው በራሱ ዘመን እንደመሆኑ በባህል ረገድ የአድዋ ጦርነት ዘመን የነበረውን ትውልድ በጭራሽ ሊመስል አይችልም፡፡

ወደ ምዕራብ ተሻግሮ ሊዮርናንዶ ዳቬንቺን መሆን የፈለገውም የዘንድሮ ልጅ ዳቬንቺን ሊመስል የሚችለው አስቀድሞ ከቆየበት የባህል ወንዝ አፈሳሰስ አቅጣጫ ተወራርዶ ከተቀናነሰ በኋላ ብቻ ይሆናል፡፡

If a black and white person mate, their children do not come out either black or white: they are intermediate.

ከተፈጥሮና ከተሞክሮ የቱ ይበልጣል?

ለዚህ ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚቀርበው ልበ ሙሉ መልስ “Nature always wins” የሚል ሲሆን፤ ተሞክሮ ማለት በአጭሩ ያው ባህል ማለት ነው፡፡ ባህል ምን ያክል ከባድ እንደሆነ በተወሰኑ ምሳሌዎች ብንመለከትስ?

ምሳሌ 1፡- ባህልን የመገንዘብ ወይንም በባህል የመቀበል ወይ የማቀበል አቅምን ከአእምሮ ነው ያገኘነው፤ ብያለው፡፡ It’s our Biological Advantage ይኼን አእምሮ ወይንም የማወቂያ መሳሪያችንን እንኳን ጠንካራ ባህል እንዳንጠቀምበት ሊያደርገን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ (ሀይማኖታዊ አልያም ሳይንሳዊ) ሀሳብን አስመስለን መኖር ጀምረን ባህል ካደረግነው በኋላ … ይህ ባህላችን ወይንም ሀይማኖታችን የሚለንን ነገር ነው የምንሰማው? ወይንስ አእምሮአችን የሚለንን?

ተፈጥሮአችን (አእምሮአችን) በደንብ እንዲሰራ በቀን ውስጥ ሦስት ጊዜ መመገብ አለብን፤ይህ የተፈጥሮው ህግ ነው፡፡ ነገር ግን በሀይማኖቱ ምክንያት ሰው ሶስት ቀን ያለ ምግብ ይቆያል፡፡ ተመክሮ (ባህል) በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሀያልነት ለማሳየት አንድ የመጨረሻ ምሳሌ ልጥቀስና ላጠናቅቅ፡፡

… ወሲብን ላለማከናወን እስከመጨረሻው መታቀብ (Celibacy) በተፈጥሮአችን የተሰጠን ነገር አይደለም፡፡ ዘረ-መላችን ራሱን በተቻለው መጠን እንዲያራባ ተደርጐ የተበጀ ነው፡፡ በዘረ-መላዊ እይታ፤ የህይወት ዋነኛው አላማ ዘርን መተካት፣ ብሎም ተተኪው ዘር … መተካካቱን እንዲቀጥል ማስቻል ነው፡፡

ባህታዊ (ወሲብ በቃኝ) እንዲል የሚያደርገው ሀሳቡ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀሳብ ወደ አኗኗር ሲቀየር ባህል ሆኗል፡፡ የግለሰብ ባህል የማህበረሰቡን ከኋላው መርቶ ሊያስከትል ይችላል፡፡

በዚህ አመት የተነዛ ወሬ እንደነበረም (ትዝ ይላችኋል) መስማማታችሁንም ሰምተናል፡፡ ግብረ ሰዶማዊያን ስብሰባ አካሄዱ … ወዘተ የሚል ወሬ፡፡ … ይህም ባህል በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሀያልነት የሚያሳይ የወሬ አይነት ነው፡፡ … ዘረ-መል የተፈጥሮአችን ንድፍ የሰፈረበት የቁም ፊደል ነው፡፡ በዘረ መላዊ እይታ ደግሞ ግብረ ሰዶም የመጥፎ ዘረ-መል ባለቤትነትን አመልካች ነው፡፡

ምክንያቱም፤ ግብረ ሰዶምን እንደ ግንኙነት መንገድ የመረጠ ባዮሎጂያዊ ፍጡር፣ ሰው የሆነ ዘር ስለማይበዛ ነው፡፡ ተፈጥሮን የሚፃረር ተመክሮ … የባህል እርገት ነው ተብሎ የሚተረጐመው ወይንስ ዝቅጠት የሚለው ላይ ነው ትልቁ ጥያቄ?

ባህል ሌላው ቀርቶ የስነ ምግባር እምነትን በማህበረሰቡ ላይ የመበየን ሀይል አለው፡፡ ጥሩ እና መጥፎ፣ ወይንም ትክክል እና ስህተት የሚሉ አስተሳሰቦች በባህል አማካኝነት ተደንግገው የሚፀድቁ ናቸው፡፡

የባህል እርገት ወይ ዝቅጠት የሚለውን ለመበየን ራሱ የምንችለው በባህል አማካኝነት ነው፡፡ ባህል ተፈጥሮን በመሰለ ቁጥር ግን መልካም ጐዳና እንደያዘ ልቁጠረውና … የዛሬውን ፅሁፍ ላብቃ፡፡

 

 

Read 5798 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:13