Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 July 2012 13:55

“እየነገርናቸው ሲያዩት እንደዋዛ ከተለበለበው የተላጠው በዛ!” - የወሎ ሰው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ የሀይማኖት ሰው አንዲት ወዳጅ ነበረቻቸው፡፡ የብዙ ልጆች እናት ናት!

ለመስበክም፣ ለጨዋታም ወደዚች ሴት ዘንድ ብቅ ሲሉ ክፉኛ ልባቸው ይነካል፡፡ እናም ለአንዳንድ የቅርብ ሰዎቻቸው ሲገልፁዋት፤ “ባተ-ተረከዟ ይቆጡኛል ያለ የተቀጣ፣ ዳሌ ሽንጧ ግራ ቀኝ ሲል ሰልፍ የሚያስከብር፣ ዐይኗ አንዴ እሚያባባ አንዴ ወኔ እሚቀሰቅስ፤ ስትስቅ፣ እንኳን ስቃልኝ ምነው በሳቀችብኝና ጥርሷን ባየሁት የምታሰኝ፣ ስብከት ስታዳምጥ ውበቷ የበለጠ የሚደምቅ፣ ወደዚህ ምድር እንድትመጣና እኔ እንዳያት የፈቀደውን አምላክ የበለጠ እንድወደው ያደረገች፤ የቁንጅና ተምሳሌት ነች!” ይላሉ፡፡

እንዲያ እሚወዷት ሴት ክፉኛ ታመመችና ከአልጋ ዋለች፡፡ ነጋ ጠባ ህመሙ እየባሰባት ለህይወቷ እያሰጋት መጣ፡፡ ስለዚህም እኒያን ወዳጇን የሃይማኖት ሰው አስጠራቻቸው፡፡

“ደህናም አላደርሽ ወዳጄ?” ሲሉ ጠየቋት፤ ከሰላምታ ይልቅ ፍርሃትና ሥጋት በበዛው ቃና፡፡

“ዛሬስ ብሶብኛል ኧረ!” አለች እያቃሰተች፡፡

“ለምን አስጠራሺኝ?”

“የመጨረሻ ኑዛዜዬን፣ የመጨረሻ ቃሌን ለእርስዎ ልንገርዎ ብዬ ነው፡፡”

“እሺ ልስማዋ!” ብለው የቤቱ ሰው እንዳይመጣ የመኝታ ቤቱን በር ቆለፉና፤

“በጄ ንገሪኝ!” አሉ

“እንደሚያውቁት 6 ልጆች ናቸው ያሉኝ፡፡”

“በጄ?”

“ትልቁን፣ የመጀመሪያ ልጄን ከህግ ባሌ ነው የወለድኩት!”

“በጄ?”

“ሁለተኛውን ልጄን ከሁለተኛው ባሌ ነው የወለድኩት”

“በጄ?!”

“ሦስተኛውን ልጄን ከወታደሩ ወዳጄ ነው የወለድኩት”

“በጄ?! ያንን አስረዳለሁ!”

“አራተኛውን ልጄን ከአዳማው ወዳጄ ነው ያፈራሁት”

“በጄ ልጄ?! ያንን አሳውቃለሁ”

“አምስተኛውን ልጄን ከከብት አርቢው ውሽማዬ ነው የወለድኩት!”

“እሺ! በጄ አሳውቃለሁዋ!”

“የመጨረሻውንና ስድስተኛውን ትንሹን ልጄን የወለድኩት፤ ትዝ ይልዎት እንደሆነ ከ3 ዓመት በፊት እኛ ቤት ድግስ ተደግሶ፣ እርሶ አምሽተው የመጡ ዕለት፤ እኔጋ ነበር ያደሩት፡፡ ያኔ ነው የፀነስኩት!”

ይሄኔ አናዛዡ ሰውዬ፤

“እንግዲህ አንቺ ያለብሽ ዝም ብለሽ መሞት ነው!” አሉ፡፡

***

አንቺ ያለብሽ ዝም ብለሽ መሞት ነው ከሚል ሁሉ ይሰውረን፡፡ ነውር ፈፅመን ብፁዕ ለመምሰል ከመጣር ያድነን፡፡ ከመንገድ ሁሉ ምክንያታዊ የሆነውን መምረጥ ለመጪው ዘመን ህልውናችን ፍቱን መድሃኒት ነው! ከአጉል-ተስፋም ሆነ ከሟርት ምክንያታዊነት ይክሳል፡፡ ዝቅተኝነትን እንዳንቀበልና ወይም ራሳችንን በራሳችን የምንጐዳ እንዳንሆን ወደዚህ የሚጋብዙንን ሁኔታዎች ሁሉ መከላከል አለብን፡፡ “ባርነት ስህተት ካልሆነ ምንም ነገር ስህተት አይሆንም!” ይለናል አብርሃም ሊንከን፡፡ ክብሩን የማያስገስስ ህዝብ ይኖረን ዘንድ እንፀልይ፡፡ እንጣጣር፡፡ ዕቡይነትንና ራስ-ወዳድነትን እናስወግድ! አስመሳዩን ባለሙያ ከእውነተኛው ባለሙያ ለመለየት ዐይናችንን ይግለፅልን! የበይ-ተመልካች፣ የኢፍትሐዊነት-ተመልካች፣ የብኩንነት-ተመልካች አንሁን! ልዩነትን ለመቻልና Vive la difference ለማለት አቅሙን አያሳጣን! በየትም በኩል የሚከሰቱ ድብቅ ምኞቶችን መዝኖ አንጥሮ የሚያይ አዕምሮ ለማዳበር በእውቀት እራሳችንን እንገንባ! ሒቸንስ የተባለው ፀሃፊ፣ እውቅና በሳል የፕሬስ ሰው ያለውን በግጥም ስናስበው፤

“ፀጥታን አትምረጥ፤ ይናገር ልሳንህ

አትጨነቅ ለዚያ፣ አርምሞ ምን ገዶህ

ረዥም ዝምታ የሚያጐናፅፍህ

ያይቀሬው ቀን ፋታ፣ መቃብር አለልህ!

ፀጥታን አትምረጥ፣ ይናገር ልሳንህ!” ይለናል፡፡

ሃያላን መንግሥታት በሃይል በመጠቀም ሀገራትን በቅኝ በሚይዙበት ዘመን አንድ መርህ ነበራቸው - ከፋፍለህ - ግዛ (Divide and Rule) የሚል፡፡ ሲሰነባብቱ መርሁን “አገር ልናቀና ነው የመጣነው” ወደሚል ይለውጡታል ይባላል፡፡ (Civilization mission እንዲሉ) ፀሀፌ-ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤ “ከእየሩሳሌም ድረስ ያመጣነውን ደወል የኩሊ መውጫና መግቢያ አድርጋችሁ ስታበቁ፤ ‘አገር ልናቀና ነው የመጣነው’ ትሉናላችሁ!” እንዳሉት አይነት ነው፡፡ ቅኝ ገዢዎች ውለው ሲያድሩና ተገዢው የአቅኚዎች አገዛዝ በቃኝ ማለት ሲጀምር፤ ገዢዎቹ ባመቻቸው መንገድ ሁለ በመከፋፈል ሊያስተዳድሩ ይጥራሉ፡፡ እነሱን መስለው እነሱን ሆነው የሚያስተዳድሩ አገረ-ገዢዎችንም ይፈጥራሉ፡፡ ይሾማሉ፡፡ ከዚያ ወኪላቸውን በእግራቸው መትከልና አገሩን ጥለው መውጣት ይሆናል የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው፡፡ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን ሰር ፔንደረል ሙን የተባለ አገረ-ገዢ በመጨረሻ ከህንድ ከወጡት እንግሊዛውያን አገረ-ገዢዎች አንዱ ነበር፡፡ የህንድ ቆይታውን በገለፀበት የትውስታ መፅሃፉ ርእስ ሁሉንም ነገር ጨርሶታል፡፡ ርእሱን “Divide and Quit!” ብሎታል፡፡ “ከፋፍለህ ውጣ ወይም ከፋፍለህ ጥርግ-በል” እንደማለት ነው፡፡ በየሀገሮቹ የምናየው ሁሉ የማን ሥሪት ነው፣ ምን አይነትስ ስርዓት ነው፤ የሚለውን የሚያስገነዝብ ታሪክ ነው፡፡

ሁኔታዎችን ቆም ብሎ አለመመልከት ለማንም አይጠቅምም፡፡ ዛሬም ሀገርን ማስጠበቅ፣ የህዝብን ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ የሚሄድ ነገር ካለ፤ ቢያንስ ለምን ሆነ ብሎ ማሰብ ያባት ነው፡፡ ሰዎችን ወገኖቼ ናቸው ብሎ ማሰብ፣ ሚዛናዊ መሆን፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ብስለትን ማሳደግ፣ በማንኛውም ወገን ቢሆን፣ ከህዝብ የሚደበቅ ነገር እንደማይበጅ ማወቅ፤ ሲሆን ግንዛቤውን በሃቀኛ መንገድ ማዳበር፤ በሰከነ መንገድ ሁኔታዎችን አጢኖ መጓዝ፣ “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲይሆን” ደንባራዋን በቅሎ መግራትና ቃጭሉን መቀነስ፤ ፈረንጆች How the steel was tempered የሚሉትን ዘዬ ማሰላሰል፣ “አትሙት ላለው መላ አለው” የሚለውን ብቻ ሳይሆን “ሳይቃጠል በቅጠልን” መመርመር፤ …አስፈላጊ ነው፡፡ የቁም ነገራችን ቁምነገር “ፀረ-ቁም-ስቅል ኮሚቴ” ሲያቋቁሙ መሳቅ ሳይሆን፤ ቁም-ስቅልን መቀነስ ነው!! ሀገር የምትጠናው፣ ህዝብ ተስፋ አለኝ የሚለው፣ የተሻለ ህይወት ሲታይ ነው፡፡ አለበለዚያ እንደውሎው ገጣሚ፤

“እየነገርናቸው፣ ሲያዩት እንደዋዛ

ከተለበለበው፣ የተላጠው በዛ” የሚለው ይበዛል፡፡ ያ ደግሞ ደግ አይደለም!

 

 

Read 4019 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 13:58