Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 May 2012 12:19

“የቆቅ ለማዳ የለውም፤ እባብንም ቆዳው ለሰለሰ ብለህ ቀበቶ አርገህ አትታጠቀውም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ የጀርመኖች ተረት እንዲህ ይላል፡፡

አንድ እረኛ በጐችን ለግጦሽ አሰማርቶ በጫካ ውስጥ ሲዘዋወር አንድ የአንበሳ ግልገል ያገኛል፡፡ ከዚያም

እንዲህ ሲል ያስባል (በግርድፉ ግጥሙ እንዲህ ይተረጐማል)

“ይህ ያንበሳ ግልገል፣ ምን አንበሳ ቢሆን

ከበግ ጋር ካደገ፣ ይተዋል ፀባዩን

በጥርሱ መናከስ

በክርኑ መደቆስ

ያየውን ማሳደድ

ዱር ገደል መሰደድ

ጉልበት ለማሳየት

ጧት ማታ ማጋሳት

የጫካው ንጉሥ ነኝ፣ ለማለት ማጓራት

የደኑን አራዊት፣ ስገዱልኝ ማለት

ይህ ሁሉ ይቀራል፣ በግ ሲሆን አንበሳው

ገና ህፃን ሳለ፣ ከበግ ጋር ሳኖረው”

አለና ያ እረኛ፣ ግልገሉን አቀፈው

እየደባበሰ፣ ለማዳ አደረገው፡፡

እረኛው አንበሳውን ከበጐቹ ጋ እያገደ በመከራ ሣር መጋጥ አስተማረው፡፡ አንዳንዴ ሲያሳክከው በጐቹ

በቀንዳቸው ያኩለታል፡፡ ይተሳሰባሉ፡፡ ይተዛዘናሉ፡፡

ቀስ በቀስ አንበሳው እየጐረመሰ፣ ጡንቻው እየፈረጠመ፤ በጐቹን ከተኩላ እየተከላከለ፣ እንደታላቅ ወንድማቸው

እየኮሩበት መኖር ቀጠለ፡፡

አንድ ቀን እንደተለመደው በጐቹን እረኛው ወደ ግጦሽ ሜዳ አሰማርቶአቸው ሲግጡ ውለው ውሃ

ወደሚጠጡበት ሐይቅ ወሰዳቸው፡፡

አንበሳውም ውሃ ሊጠጣ ጐንበስ ሲል የራሱን ምስል ውሃ ውስጥ አየ፡፡ በከፍተኛ ድንጋጤ ከግራና ከቀኙ

ያሉትን በጐች እየበረጋገደ እየጣለ እግሬ - አውጪኝ ብሎ ሮጠ፡፡

በጐቹ፤

“ኧረ ና የእኛ ወገን ነህ፡፡ ውሃ ውስጥ ያየኸው የራስህን ምስል እንጂ ሌላ አንበሳ አይደለም” አሉት፡፡

አንበሳው ግን፤ አስገራሚ መልስ ነው የሰጣቸው፡፡

“እኔ የዱር አራዊት ንጉሥ እንጂ የቤት እንስሳ አይደለሁም፡፡ ምስሌ ግርማ ሞገሴን አስታውሶኛል፡፡ እናንተ

የተፈጠራችሁት በግ ሆናችሁ ኖራችሁ በመጨረሻ ጌታችሁ እንዲበላችሁ ነው፡፡ እረኛው የሚጠብቃችሁ

ለመበላት እስክትደርሱ እንጂ ደግ ሆኖ እንዳይመስላችሁ! እኔ የዱር አራዊት ንጉሥ ነኝና ወደዚያው ሄጃለሁ፡፡

አብረን ስለኖርን እኩል ነን ማለት አይደለም!!” ብሏቸው ወደ ደኑ ገባ፡፡

***

በገዛ ምሥላችን ከመኩራራት ይሰውረን፡፡ ሁሌ “ንጉሥ ነኝ”፣ “ንጉሥ እንድሆን ነው የተፈጠርኩት” ከሚል

ያድነን፡፡ የማይለምደውን በግድ እናልምድ ብለን፣ የማይለወጠውን ይለወጣል ብለን ከመዳከር ያትርፈን፡፡

ከአስብቶ አራጅ እንድን ዘንድ እንፀልይ እንደምንል ሁሉ፤ “ፍየል ፈጁን አውሬ፣ ፍየል አርደህ ያዘው”

የሚለውንም ተረት ልብ እንል ዘንድ ልቡና ይስጠን!

“እኔስ ባገሬ

እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ”

ዘፈን እንጂ በተግባር ከባድ መሆኑን ማንም ጅል አይስተውም፡፡

“እኔ ለራሴ ኩራት ይዞኛል”

ራስ አበበ ልከውብኛል

የሚለውም የሠርግ ዘፈን፤ የመሣፍንቱንና የመኳንንቱን ክብርና ጀግንነት ያወድስ እንደሁ እንጂ የዛሬን ሙሽራ

ላያኮራ ይችላል፡፡

“የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው

በእንግሊዝ አናግሪያቸው” የሚለውም ዘፈን ቢሆን፤ የተማረችውን ሙሽራ ያሞግስ እንደሁ እንጂ፤ ለትምህርት

ያልታደለችውን ገጠሬ ሙሽሪት አይዞሽ አይልም፡፡ ምናልባት የእንግሊዝኛን ክብር ይጠብቅ ይሆናል በአስኳላኛ

አነጋገር፡፡ (በዊንጌት ተማሪ ቤት፣ በበዕደ ማሪያም ተማሪ ቤት፣ በሳንፎርድ ተማሪ ቤት አድርጐ በሊድስ

ዩኒቨርሲቲ በኩል ላሰበ ሰው “እንግሊዝ እረኛችን ነው” ቢል አይፈረድበትም፡፡)

“እገሌ አንደበተ - ርቱዕ ነው” “እገሌ ነገር አዋቂ ነው” “እገሌ ንግግሩ መሬት ጠብ አትልም” የሚለው አባባል ቦታ እሚኖረው የመናገር ነፃነት ባለበት አገር መሆኑ አይካድም፡፡ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት ህገ-መንግስታዊ መብቶች ልንጠቀምባቸውና ልንታገልላቸው የሚገቡ መብቶች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ “እንዳይሄድ መንገድ ዝጋበት” የሚልም ሆነ “እንዳይሄድ እግሩን ቁረጠው” የሚል፤ ክፋታቸው ይለያይ እንጂ ሁለቱም ፀረ - ዲሞክራሲ ናቸው፡፡ ሀሳዊ መሲህ እንዳለ ሁሉ ሀሳዊ ዲሞክራትም አለና ከሁለቱም መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ልቡ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሆነን “ሃዋርያም” ሆነ “ምዕመን” ዲሞክራት እንዲሆን አለምደዋለሁ ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ለማንኛውም “የቆቅ ለማዳ የለውም፤ እባብንም ቆዳው ለሰለሰ ብለህ ቀበቶ አርገህ አትታጠቀውም” የሚለውን አገርኛ ተረት ማስተዋል ከብዙ አባዜ ያድናል!

 

 

Read 5373 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:22