Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 11 February 2012 10:05

ከሁሉም ምን ይብሳል - የጉልቻ ውሰት፤ የቢላ ደነዝ፤ ከሸንጐ ሲመለሰ ድምፁን የማያሰማ ባል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከቻይና ተረቶች ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

በጥንት ዘመን አንድ እንጨት ነበረ ይባላል፡፡ ወደ ጫካና ወደ ተራራ በየቀኑ እየሄደ እንጨት ያመጣ ነበረ፡፡ ይሄ እንጨት - ቆራጭ የመጨረሻ ስስታም ነበር ይባላል፡፡ ከብር የተሰራ ዕቃውንና ገንዘቡን ሁሉ ሸሽጐ ከማስቀመጡ የተነሳ “ወደ ወርቅ እስኪለወጥ ድረስ አልነካውም” ብሎ ቆልፎ ያቆየዋል ይባላል፡፡ በዓለም ላይ ካለ ከማናቸውም ነገር አስበልጦ ወርቅ ይወድዳል፡፡  አንድ ቀን እንደልማዱ ጫካ ሄዶ ሳለ አንድ ነብር ድንገት ይመጣበታል፡፡ ለማምለጥ ብዙ ቢሮጥም ሊያመልጥ አልቻለም፡፡ ነብሩ የሰውዬውን ልብስ በጥርሱ ነክሶ አንጠልጥሎ ይዞት ይሄዳል፡፡

የእንጨት - ቆራጩ ልጅ አባቱ የደረሰበትን አደጋ በመመልከት ጦር ይዞ እየሮጠ ሊያድነው ይመጣል፡፡ ነብሩ ሰው አንጠልጥሎ ስለሆነ የሚሮጠው፤ ልጁ ቀድሞ ደረሰበት፡፡ ነብሩ ሰውዬውን የያዘው የልብሱን ጫፍ ነክሶ በመሆኑ አባት አልተጐዳም ነበር፡፡

ልጁ ነብሩን ሊወጋ ገና ሲቃጣ፤ አባትዬው ያያል፡፡ ከዚያም ጮክ ብሎ፤

“ልጄ፤ አደራህን ቆዳውን እንዳታበላሸው! ቆዳው እንዳይበላሸ! ቆዳውን ሳትበሳ ለመግደል ከቻልክ ብቻ ግደለው! በዛሬ ጊዜ የነብር ቆዳ ስንትና ስንት ያወጣል መሰለህ!”

ልጁም፤

“አባዬ! አንተ ዳን እንጂ ለቆዳው አትጨነቅ!” አለው፡፡

አባትየውም፤

“የለም ልጄ! በነብር ቆዳ ቀልድ የለም፡፡ ዋጋው የትየለሌ ነው፡፡ ቆዳውን ሳታበላሽ ነው መግደል ያለብህ!”

አባት ይሄንን መመሪያ እየሰጠ ሳለ ነብር ሆዬ አንጠልጥሎት ወደ ጫካው እመር ብሎ ይገባል፡፡ ነብሩ፤ ልጁ በጭራሽ ሊደርስበት ወደማይችልበት ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ ገባ፡፡ አባትዬውንም ብጭቅጭቅ አድርጐ ጨረሰው!

***

ከህልውናችን በላይ የነብሩ ቆዳ ከሚበልጥበት ዘመን ያድነን! ብሩ ወርቅ እስከሚሆን ኑሮ ከሚያማቅቀን ክፉ የስስት ቀን ያውጣን! ህይወታችን የሚያተርፍልንን ወጣት በብር እመን ከምንልበት ህይወት ይሰውረን! የነብሩን ቆዳ ስንንከባከብ የሰው ቆዳ እንዳይበሳሳ መጠንቀቅ አለብን… መክሊት ስናባርር የህዝባችንን ምሬት እንዳናባብስ፣ የአንዱን ጉሮሮ ስንዘጋ የሌላውን ባዶ እንዳናደርግ ፍፁም ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ “ከቶውንም ከሚጮህ ሆድ የበለጠ ድምፅ የለም!” ይላሉ ገጣሚያን፡፡

“ተራራም ካነባ ሰምበር ይሰራል” ይላሉ፤ የድሬዳዋ ዙሪያ ገበሬዎች፡፡ ጉዳዩ ማንባቱን የሚያይለት አለ ወይ? ሰምበሩን የሚንከባከብለትስ ታዳጊ አለው ወይ? ነው፡፡ “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ልብ ካላልን ምሬት ምንድን ነው? የሚለው ሀሳብ በቀላሉ አይዋጥልንም፡፡ “የበላችው ያቅራታል፤ በላይ በላዩ ያጐርሷታል” የሚለውን አለመዘንጋት ዋና ነገር ነው፡፡

ልጅነታችን ከአዋቂነታችን ጋር ከተጋጨብን መምራት አዳጋች ይሆናል፡፡ በተማሪ እንቅስቃሴ ዘመን የነበረን አቋም ከዛሬው በሳል የመሪነታችን ዘመን ጋር የግድ ካልተኳኳነ ብለን የምናጣምመው ታሪክም ሆነ የምንፈጥረው ወልጋዳ መላ መኖር የለበትም፡፡ የጋና ህዝብ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን እሳቤ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ባለው አቻ እሳቤ ማስተካከል ስንፈልግ “ጫማው ሲጠብ እግሩን መቁረጥ” በሚለው አካሄድ መራመድ የለብንም፡፡

“ጠላት ከእኛ መሬት ትርፍ አገኛለሁ ሲል

እኛስ ከእኛ መሬት እንደምን እናጉድል”

የሚለውን የአበው ግጥም አንርሳ፡፡

ዛሬም ደግመን የምንጠቅሰው አንድ አባባል አለ:-

“ወንዙን አቋርጠህ ሳትጨርስ እናትየዋን አዞ፤ አትሳደብ” የሚለው የሃይቲዎች አነጋገር፡፡ እናትህ ወንዙን ሙሉ በሙሉ እስከምታቋርጥ እንደምታስተውልም እይ ነው የአነጋገሩ አንዱ ገፅታ፡፡ ለሁሉም ግፍ ተበቃይ አለውም ነው፡፡ በሌላ አቅም አቅም-ግንባታ፣ በሌላ ህብረት የአፍሪካ ህብረት፣ በሌላ አህጉራዊነት ፓን-አፍሪካኒዝም፤ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ መሆኑ እየታወቀ፤ የግለሰቦችን ቅን ተዋፅኦ ሳይቀር የምንደፈጥጥበት ሁኔታ መፈጠሩ አግባብ አይሆንም፡፡ “የቄሣርን ለቄሣር… የጃንሆይን ለጃንሆይ… የንኩሩማን ለንኩሩማ… የኔሬሬን ለኔሬሬ… የካውንዳን ለካውንዳ… የማንዴላን ለማንዴላ… የዴዝሞንድ ቱቱን ለዴዝሞንድ ቱቱ…” እያልን መጓዝ ማንን ገደለ?

“ከጓጓ ዘመድ፤ ቁርጡን ያሳወቀ ዘመድ” የሚለው ተረት ቡጡ ድንቅና ድምቅ ነው፡፡ ይሄን ድምፃችንን ለማሰማት በቂ ድምፅ አጣን - ምን ይደረግ? የምንል ከሆነም እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ነው! “እኔ ካመንኩበት እናንተ ምን አገባችሁ”ም እኮ ደህና ቋንቋ ነው፡፡ ችግሩ እሚመጣው “እናንተን ወክዬ አቋም ያዝኩ አርፋችሁ ተቀመጡ!” ሲባል ነው፡፡

ባለፈው ዘመን፤ “ቀይ ሽብር”ና “ነጭ ሽብር” የሚለው “ፍልሚያ” በነበረበት ሰሞን፤ አንድ የመንግሥት ተቃዋሚ ለእሥር ምርመራ ቀርቦ፤

“ለምንድን ነው የእናንተ ፓርቲ ሰው የሚገድለው?” ተብሎ ተጠየቀ አሉ፡፡ ተቃዋሚው ሲመልስ፤

“እሥር ቤት ስለሌለው ነው!” ነበር ያለው፡፡

ዛሬ ደግሞ መቼም እድሜ ዘልዛላ ነውና “እሥር ቤት የሌለው መንግሥት!” ስለሚባል ፌዝ ሁሉ የምንወያይበተ ሸንጐ ዘንድ አድርሶናል፡፡

የኢኮኖሚ ሁኔታው ሲባባስ፤ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሹሮ አበድሪኝ!” የሚለው ተረት የዕለት የሰርክ ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ ህይወት ሲዳከም “መርፌ ሲለግም ቅቤ አይወጋም” የሚለው አነጋገር ይደምቃል፡፡ ኑሮ ሲከፋ ባል ከሚስቱ የሚሸሽገው የአደባባይ ውሎ እየበረከተ ይመጣል፡፡ ይሄኔ ነው፤

“ከሁሉም ምን ይብሳል - የጉልቻ ውሰት፣ የቢላ ደነዝ፣ ከሸንጐ ሲመለስ ድምፁን የማያሰማ ባል” የሚለው የጉራጊኛ ተረት ትርጉሙ የሚገባን!?

 

 

Read 4849 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:08

Latest from