Saturday, 28 July 2012 11:20

ወርቁን ፍለጋ…

Written by  ዋሲሁን በላይ (አዋበ)
Rate this item
(1 Vote)

ፀሐይ በለስላሳ ነፋስ ታጅባ ወደ ሠፈሯ እየወረደች ነው፡፡

ፀጥታው ደስታን ይወልዳል…የሬስቶራንቱ፡፡

እዚህ፤

ድርብ…አይኗ ልብን ሠርስሮ ያደማል፣ ስባ በምታጉተለትለው የሲጃራ ጭስ ህልሟን የምትፈልግ ነው የሚመስለው፡፡ ክፉ ህልም፡፡

አጠገቧ የተቀመጠው ግራ ገብቶታል፡፡

እዛ፤

አዝመራ…የብርጭቆውን ወገብ በእልህ ጨብጣ ተስፉ ላይ አፍጣለች፤ ተስፉ ንዴቱ እየበረደ ቢሆንም በቁጣው ውስጥ ፀሐይ ጠልቃለች፡፡ አዝመራ ውሉ እንደተተበተበ ቱባ ክር ብትክትክ ብላለች፡፡ የእርጥብ እንጨት ጭስ ይመስላል፡፡ ሳታስበው እንባዋ ፈሠሠ…ወረደ…አልከለከለችውም…የጨበጠችው ጐርደን ጅን ውስጥ ገባ፤ ብርጭቆው አፍ ላይ የተወሸቀውን የተከረከመ ግማሽ ሎሚ አንስታ አፍዋ ውስጥ ወተፈችው፣…ከተስፉ ክፋት የበለጠ አይመርም፣ ከተስፉ መሠሪነት የላቀ አይኮመጥጥም…ፊቱ ላይ ብትተፋበት በወደደች…ግን…የሱን ያህል ባለጌ አይደለችም፡፡ ያለቀሰችውም እሷ ፈልጋው ሳይሆን ልቧ ተንሸራቶባት ነው…ማዕዘኑ ከቦታው እንዲሸሽ ግምብ ተንዶ፡፡

እዚህ፤

ድርብ ወርቅ…ሞገስ ላይ የንቀት አይኗ ጉልበቱን ሰብሯል፣ አጠገቧ የተቀመጠውን ፓኮ በግራ እጇ አንስታ የመጨረሻውን ኩል ሲጃራ ለኮሰች…ንቀቷ ጨምሯል…

“ስማ…አንተ እኮ ፒያሳ ልብስ ለብሰው፣ በቆራጣ ፎጣ ተወልውለው መስተዋት ውስጥ ከሚሰቀሉት አሻንጉሊቶች በምንም አትሻልም…እንዲያውም እነሱ አይበልጡህም ብለህ ነው…ከፋም ለማ ያገለግላሉ…”

ይሔ ቅልጥማም ቀውላላ…አንገቱን አቀረቀረ…ጉልበቱ ምላሱ ላይ ነው…ድርብ ሁልጊዜም ትላለች…

“አንተ ማለት እኮ ቁመናህን አሳምረህ…እንደ መልከቀና ሴተኛ አዳሪ ራስህን ለታይታ ገበያ የምታቀርብ…ጥርብ መሀይም ነህ…! በመፈጠርህና አንተን በማፍቀሬ እፀፀታለሁ…”

በግራ እጁ አገጩን ደግፎ በግማሽ እይታ…ሸረፍ አድርጐ ተመለከታት

“እየውልሽ ድርብ…” ምንም ፍሬ ያለው ነገር ስለማያወራ አላስጨረሰችውም

“ምናልባት ለፍቅር ስል ማጐንበሴን እንደተሸነፈ ሰው…ቆጥረኸው ከሆነ…ትልቅ ስህተት ነው…! የሆነ ነገር ሲፈለግ…የሆነ ነገር እየጣሉ ነው…”

አፍጣበት ስለሆነ ያወራችው…አጐንብሳ ነበር…የለበሰቻት ስስ ካናቴራ እነዛን ሳስተው

ልብ የሚያሳሱትን ጡቶቿን አሳየው…ልቡ ተርገፈገፈ…ስንት ሌሊት…ተደስቶባቸዋል…

ስንቴ ስሟቸዋል…ስንቴስ መጧቸዋል…ስንቴ!…በሙሉ አይኑ ጊዜ ሠጥቶ ናፍቆቱን ሊወጣ አልቻለም…ቀና አለች፡፡

“አየሽ ድርብ - የሰው ልጅ የተሰማውን ሲናገር…ሌላኛውን ሰው ሊሰማው ይችላል ብሎ መጠንቀቅ ይጠበቅበታል…”

እንደ አዲስ ጀበና ገነፈለች…

“ላንተ ነው የምጠነቀቀው…? ላንተ…” ቁጣዋ ሰይፉ የተሳለ ነበር “ውይ…እንዴት እንደጠላሁህ ባወቅህ…?!... ላንተ…” በንዴት የተለበጠ ፈገግታ ወረወረች…

“ሴት ልጅ ፍቅር ጠየቀችኝ ብለህ ቀፎ ልብህን ተራራ ላሳከልከው ላንተ ለባዶው…” የኮሶ መድኃኒት የተጋተች መሰለች፡፡

እዛ፤

አዝመራ እንባዋን በደረቅ ጅን አጣጥማዋለች፣ ተስፉ የመጣላትን ኦፕሬቲቭ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለቴ ፉት አለው ፊት ለፊቱ የተቀመጠችው እምትወደው፣ ቆዳዋን ገፋ ብታለብሰው…የማትሰስተው አዝመራ…የክረምት አግቢን ክንፍ ያህል ስስ መስላ ታየችው…በሞቀ ትንፋሽ ብትንትኗ የሚወጣ… ግን…ጉልበቷ ምን ያህል እንደሆነ ያውቃል…ውሽልሽል የሸንበቆ ማገር እንዳልሆነች…ገብቶታል…፡፡ ያጣችውን ለማግኘት ቀሚሷን አትገልብም፡፡ ዝምታዋ ቋንቋ እንዳለው ያውቃል…ቁጣዋ እሳት ነው - ከነደደ የማይበርድ! - ያለምንም ምክንያት ምንም አታደርግም፡፡ እሱ ግን እሷን አቅፎ ሌላ ይቀጥራል፡፡

ልጅነቷን ገብራለታለች…ጊዜዋን እንጂ ወኔዋን አልሠጠችውም፡፡ ተስፋዋን እንጂ…ሴትነቷን አላንበረከከውም፡፡ እንደመውደቅና እንደመሸነፍ እምትጠላው ነገር እንደሌለ ጠንቅቆ ያውቃል…ታዲያ እንዴት ብሎ ነው…”በቃ…አልወድሽም” የሚላት፡፡ እሺስ ብላ ትቀበለዋለች…?

እዚህ፤

ድርብ እሳቱ ላይ ገንፍላም…እሳቱ አልጠፋም፤ ሞገስ በሩጫ የዳበረው ፉርሽካ ሰውነቱን እንደታቀፈ ተቀምጧል…እንደ እውቀት ማነስ ያለ ክፉ በሽታ ተጠናውቶታል…

“ትንሽ ሰው መሆንህን ታውቃለህ…? ከታዋቂ ሰዎች ጋር ስለዋልክ…የታወቅህ መሠለህ…? እባብ የሄደበት እንጨት እባብ አይሆንም! አየህ ከትልቅ ሰው ጋር ስለተዋለ ትልቅ አይኮንም!...የኔ ቅል እራስ…

ራስን ለትልቅ ነገር ማድረስ ነው ትልቅነት…ቁመናን አስውቦ …ገላን በፋሽን ሸፍኖ ሲቀብጡ መዋል አዋቂ አያደርግም…!”

“እየሰደብሽኝ ነው?”

“አንተ አልክ…” በዝምታ ውስጥ ቁጣዋ በደመና እንደተሸፈነ ጥቁር ሰማይ ሲሠነጠቅ ይታያል፡፡

“እና…የሚያለመልም ምርቃት ነው የምታዥጐደጉጅልኝ…?” ለመጠየቅ ያህል ጠየቀ

“ዝም ብለህ ስማኝና…ለመወሰን ምርጫውን ትመርጣለህ…ቸኩሎ ማማት…ይቅርታው ይርቃል…!” መሸማቀቁ ፊቱ ላይ ያስታውቃል…አንገቱን ሰብሮም አጐንብሷል፡፡

“ስድብን በጥሞና የሚሠማ ምን አይነት አንጀተ ደንዳና ቢሆን ነው…?”

ሲጃራ ለመለኮስ ፓኮውን…ቦርሳዋን…ፈለገች…አጣች…ይብስ ተበሳጨች፡፡

“ስማ ስድብ መሆኑ የሚታወቀው…የተናገርኩትን ቃል…ሰሙን ካየኸው ነው…ወርቁ ግን ህይወት ነው…፤ ፍቅርን ነው የሚሰብከው…በርሃ ላይ ለምለም ቅጠል መፈለግ ሆነብኝ እንጂ…!” ብስጭትጭት አለች…

“አንዲት የተገፋች “አይ ሚን”…ፍቅርን ስትል የተናቀች…ሳትሰስት…የፍቅር እጇን ዘርግታ…እጇን የተረገጠች…ምስኪን አፍቃሪ…ስትለምን… እምቢ ተብላ… እግዜር ይስጥልኝ ስትባል ምን ይሰማሃል…?!”

“ምናልባት የእኔ ልብ ያንቺን ንፁህ ፍቅር መሸከም የማይችል ከሆነስ…?”

“ፍቅርን መሸከም የማይችል ልብ…አለም ላይ አልተፈጠረም…መያዝ ካልቻልንበት ትንሿም ነገር ትከብደናለች፡፡ መለመን (ጠበቅ አደረገችው) የለመደ ሰው እሚሆነውን ያጣል…!” እንዳቀረቀረ…ቀረ….

“እኔን የተረዳሽኝ አልመሰለኝም…”

የድምጿ ልስላሴ…ፍቅር በነበሩበት ወቅት ትህትና እንደነበራት ይጠቁማል…ግን ቁጣዋ አሁን…ያለው…እንደ ባህር ዛፍ ስር…ጠልቋል…”መጀመሪያ አንተ አልተረዳኸኝም!” “ሴት ልጅ ጠይቃኝ…እንዴት ነው እሺ የምላት” የሚለውን ልፍስፍስ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ቀሽም ትምክህት ከዚህ ቀፎ ህሊናህ አውጥተህ ጣለው፡፡”

በተናገረችው ቁጥር ቃላቶቿ ቁስል ላይ እንደተነሰነሰ ጨው ቆጠቆጠው…ባዶነቱን ለመሸፈን የሚጣጣረው ነገር ሁሉ የህጻን ልጅ ዳዴ ሆነበት…ቆመ ሲባል መውደቅ፡፡

ማንም ስንፍናውን ነግሮት አያውቅም…ሮጦ እንደሚቀድማቸው ደካሞች…ሌሎችን በምላሱ ጉልበት መጉዳት ይፈልጋል…! ግን አልሆነለትም፡፡

“አሁን የምትይው ሁሉ ከጫማ ላይ ካልሲ እንደማድረግ ነው”

“ለምን ከኮፍያ በላይ አንገት አይሆንም!” ከገባህ ያ ማለት አንተ ማለት ነህ..ኮፍያ ላይ የበቀለ አንገት…” ዝምታን መረጠ፡፡ ከዚህ የተሻለ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡

ቤቱ ቀስ በቀስ በጥንዶች እየተሞላ እያንዳንዱ ጠረጴዛ ላይ ሻማ ተለኮሰ፡፡ የሆነ ያልታወቀ ውብ ሰፈር መሠለ፡፡

እዛ፤

አዝመራ ተስፉ ላይ የጥላቻ ድንኳኗን ደኩናለች፡፡ የካስማዎቹ ጥልቀት ልክ የለውም፡፡ ክፉ ለመሆን ብላ አይደለም… እንዲህም ተበድላ እንዲህም ተከድታ “በቀል” ይሉት የጅል ሀሳብ ልቧን አልማረከውም…፤

***

አዝመራ ጅኑ ሳይሆን የተስፉ ክፉ ተግባር አናቷ ላይ ወጥቶ አስክሯታል…

“ስወድህ እንደነበር…ታውቅ ነበር…?” ተለሳልሳ ነበር የጠየቀችው…

“አውቃለሁ”…በመጠየፍ አየችው… “አታውቅም…አንተ ማለት የእንግዴ ልጅ ማለት ነህ ውርዴ!” ባረቀችበት …ቀና ብሎ ግራ ቀኝ ተመለከተ…ሀፍረት ልቡን ሰነጠቀው…ቢያጋጫት በወደደ…ግን…ዝምታን መረጠ፡፡ ተስፉ መቼም ቢሆን በአዝመራ የሚጨክን ልብ የለውም…ፍቅር “ሀ” ብላ ያስኮመኮመችው እሷ ናት…በምንም ሁኔታ ሊከፍለው የማይቻለው ውለታ አለበት፡፡ ምናልባት…እሷን ከካሳት በዝምታ ነው እንጂ በምንም ሊሆን አይችልም፡፡ አብረው ቢሆኑም እንኳ አይኗ እያየ የሌላ ሴት ከንፈር በከንፈሩ ሲያሟሽላት አይታለች፣ አልካዳትም፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ምንትስ እንደረገጠ ጫማ … ከልቧ ደጅ አስቀምጣዋለች … እሱን እሹሩሩ የምትልበት የፍቅር አንቀልባዋ ተቀዷል … እንኳን የሱን ፍቅር የራሷን እምነት እንኳ ትይዝበት ስፍራ የላትም፤ ደብል ጂን አዘዘች፡፡ “አይበቃም?” አላት፤ በመከዳት የሞጨሞጩትን … ሲወጣና ሲገባ የሚመጨምጫቸውን ዛጐል የመሠሉ አይኖቿን እያያቸው …

“ምናባህ አገባህ…” በፍቅር አይን አየችው … ከንፈሩ እንደኩበት እስኪፈረከስ ግጥም አርጋ ብትስመው በወደደች … ግን የሌላ ሴት ጣዕም እንደምትቀበል ገባት፤ ከቀጠሮአቸው ሰዓት ቀድማ መጥታ ቀድማ መጠጡ ላይ ተጥዳ ነበር ያገኛት … የመጨረሻ ለመነጋገር ነበር …

እዚህ፤

ሞገስ የድርብን የስቃይ ጣር አልቻለም፤ ብዙ ሌሊቶች ህልሙ እጇ ላይ ጥሎታል … ይሁን ብላ ያለፈቻቸውን እውነቶች አንሶላ ውስጥ በትኖታል፤ እሷን እየተኛ ሌላ ሴት ነበር የሚያስበው… ድርብን የጠራ እየመሠለው … ሥንትና ስንት ቀን የስንት ሴቶችን ስም አንቆለጳጵሷል … ለፍቅር ብላ …ችላው ነበር… ዛሬ ግን አልቻለችም፡፡

የገዛ አፉ ነበር ጉድ የሰራው … አውርቶ ውሎ አውርቶ ቢያድር አይሰለቻትም ነበር … ዛሬ ግን ለምን ምላሱ እንደሚቀድም ገብቷታል፡፡ ጭንቅላቱ ባዶ ስለሆነ … በጥርሱ በጠረባ ይጥላል … ጠረጴዛው ላይ የወረወራቸውን እጆቹን አፈፍ አድርጋ … “ስለማይሆንልኝ ነው እንጂ … አንተን ቀንበር አንገትህ ላይ አስሬ እንደ በሬ ባርስብህ … ለምንም የማትጠቀም አሻንጉሊት …!”

“ተይ …ድርብ…ተይ…?” ልመና አይመስልም አለማመኑ …

“አንተ የትኛው ቤተክርስቲያን ነበርክ … ቀን በቀን ጠዋትና ማታ ሳልሳለምህ የማይመሸው የማይነጋው …እ…?” እጁን ወረወረችበት … የሀፍረት ካባውን ደረበችው፡፡

“አንተ የኔን የፍቅር ጥያቄ ብትቀበል ማነው በአደባባይ ይሰቀል የሚልህ… ማነው? እስቲ  ንገረኝ… …” ቃሉን መጨረስ አቃታት …

“ራሴን ከመስጠት በላይ ምን ልሁንልህ…?”

“እኔ ምን ሁኚልኝ ወጣኝ …”

“እንጃ” እንባ ተናነቃት … ማመኗ አስጠቃት … እጆቿን ስታወራጭ ብርጭቆው መሬት ወርዶ የራሱን ብሶት አሠማ … ምንም አልመሠላትም … ይኼ የወንድ ጉቶ ለዛውም ምሳር ያጣ …እንደ ብርጭቆው ድቅቅ ቢልባት በምን  አንጀቷ …

“ውይ ሞገስ …ውይ … አሁን አንተም እንደ ሌሎች ወንዶች ዘጠኝ ወር ሙሉ ሴት ማህፀን ውስጥ ተቀምጠህ ነበር? ው.ይ.ውይ.ውይ…!” ማዘን ከምትችለው በላይ አዘነች፡፡

“ይሄን ያህል ስሜት አልባ ጨካኝ አድርገሽ ባትመለከችኝ መልካም ነው” ሙሉ ሰውነቷን ጠረጴዛውን አስታካ ወደ እሱ ተጠጋች … አይኗን አይኑ ውስጥ ሰርስራ ከተተች … አሁን ልቡ ውስጥ ናት … ከጉራ የዘለለ ..  ከአውቃለሁ ባይነት ሌላ ምንም የለም … መልክና ቁመና … ተንቀሳቃሽ አሻንጉሊት …

“ድብን አድርጌ ስላፈቀርኩህ አላፍርም … አየህ ይሄን መብቴን ማንም አይነፍገኝም … ብጐዳ ለትንሽ ጊዜ ነው … የጣቱን ጥፍር እያሳየችው … “ልፍስፍስ! እንደ አንተ አይነት ትንሽና ኩሩ የሚመስሉ ባዶ ወንዶች … ሰጋቱራ ናቸው … ገለባ…! ፍቅርን እምቢ ስለተባለች ድርብ ተሠብራ የምትወድቅ መስሎህ ከሆነ ሞኝህን ፈልግ …” ትንፋሽ አጠራት … አፏ ደረቀ… ምላሷ ውስጥ ተጣበቀባት… እምትጠጣው አጣች፤ ሁሉም ነገር አልቆባታል…፡፡

እዛ፤

አዝመራና ተስፉ በእየልቦቻቸዉ እውነትን ፍለጋ ስደት ጀምረዋል፡፡ ሴት ልጅ ለጠየቃት የምትፈቅድ … ላሽኮረመማት የምትገለፍጥ የሚመስለው ቀሽም ወንድ ሁሉ … ዛሬ ጉዱ ፈልቷል … ልቡ እንደ ክራር ክር ተወጥሯል፤ ሴት ልፍስፍስ የምትመስለው ልፍስፍስ ወንድ ሁሉ ዛሬ መልስ እንደ ውሃ ጥም አቃጥሎታል፡፡

በመኖር መስመር ላይ … በመስጠት ህግ መቀበል አለ፡፡ ባለመፈለግ ሒደት ደግም … ሊሰበሩ የሚችሉ ልቦችን አግባብቶና ተግባብቶ አለመፈለግን ማስረዳት … ለሌላው ሰባራ ልብ ይሄኛው ወጌሻ መሆን ይችላል … እንጂ … “ወንድ እኮ ነኝ” በሚባል የነተበ አቡጀዲ ተሸፋፍኖ ከመቅረብ … ምንም ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ህይወትም እንዲህ አይደለችም!!

በነፃ የተገኘ ነገር ሁሉ ርካሽ አይደለም… ፍቅር ደግም የትም ቦታ ውድና ክቡር እንጂ ዋጋው ወርዶ አያውቅም… ለዚህ ነው… እዛና እዚህ ያሉት ወንዶች የስም አንቀልባ ላይ በቦዶነት ታዝለው በምንምነት የሚኖሩት፡፡ አዝመራን የውስጧ ቀን መሽቷል… ምንም ብርሃን አይታያትም ብሎ ነበር የሚያስበው… እሷ ግን በመፈለግ ውስጥ አለማግኘት እንዳለ ታውቃለች… ተስፊን እንዴት ብላ ነው  የምትረሳው… ያ ሁሉ ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ በቶሎ አይረሳም፡፡

እዚህ፤

ነገሩ ሊደመደም ይመስላል … ለሞገስ… /ራቁቱን ሆኖ ለፈራው/ በሞቀበት አንቋላጭ እንደሆነ አጠጥታዋለች … ይብላኝ እንጂ በምላሱ ተታላ ለምትሸነፍለት ሴት … እሷማ…

የብርጭቆውን ከንፈር በጣቱ እየዳበሠ አይን አይኗን ከተመለከተ በኋላ

“ያንቺ የመውደድ መብት እንደሚጠበቀው ሁሉ እኔም … ተቀበይ…”

“ገደል ግባ!”

“አመሠግናለሁ”

“ድጋሚ ገደል ግባ!!”

“በድጋሚ አመሠግናለሁ” ነውሩ ነበር ትህትና እንዲናገር ያደረገው፡፡

“አንድ ነገር ልንገርህ …” ደርቆ እንደሚራገፍ ነጠላ ተርገፈገፈች …

“አንድ ነገር ልንገርህ?”

“ትችያለሽ…” ምናልባት ሰው ከሆነ ትህትና እያሳየ ነው … ምንም ስትለው ነውሩን ታቅፎ ከሷ መለየትን መርጧል፡፡

“እንደውም የወንድ አልጫ … ቀፎ ራስም ሆነህ አፈቅርሀለሁ… ግን ፍቅሬን ውሰድ ብዬ አልለማመጥህም … ህፃን ልጅን ሙዳ ሥጋ ዋጥ ማለት አንቆ መግደል ነው… ስለዚህ… የኔን ፍቅር መቀበል አትችልም” ሲያንሰኝ ነው ብሎ ምንም አላላትም … ሞገስ ራሱን ያውቀዋል፡፡ ጥርሷን ለከፈተችለት ሁሉ ቀሚሷ ውስጥ መግባት ይፈልጋል፡፡

“ስለ ሁሉም አመሠግናለሁ…” አቀረቀረ…

ከማዶ፤

ሙሉ ውሃ ሰማያዊ ሱፍ ያደረጉ … ቁመናቸው እሚያስገርም … ሽበታቸው ውበቱ የጐላ… የደስ ደስ ያላቸው ሽማግሌ… በቀይ ከረባት ተሽቆጥቁጠው … ወለሉ መሀል ላይ ቆሙ … ለስላሳ ጉሮሮአቸውን … አለሠለሡ … ሁሉም ጥንዶች ተመለከቷቸው… አስተናጆቹ በግርምት ተውጠው ፈዘው ደርቀዋል…

በልበ ሙሉነት የቆሙት አዛውንት… ድጋሚ ሁሉንም በአይናቸው ጐማ ተሽከርክረው ቃኙ… ሁለመናቸው ይጣፍጣል፡፡ እሚወደድ ተዋናይ ይመስላሉ… ለስለስ አርገው አወሩ… ድምፃቸው እንደ ዋሽንት ይጣፍጣል… ሁሉም አይኖች እኚህ አዛውንት ላይ ተጠምደዋል … በአነጋገራቸው ያልተመሠጠ የለም፡፡ የሁሉም ጆሮዎች እጅ ወደ ላይ ብለዋል፤ ግራ እጃቸውን ወገባቸው ላይ አስደግፈው እንደሰባኪ ቀኝ እጃቸውን እያወናጨፉ … እንደ ተዋናይ በተመጠነ አረማመዳቸው ተቃኝተው…

ይሔ ቀይ ኮርማ … ክፉ አመል ትራሱ…

በረት ሙሉ ከብቶች … እንደዚህ ማመሱ…

ምናለ ቢያርዱልን … አሞሌ እያላሱ!!

ፀጥ አሉ … ሁሉም ማንሾካሾክ ጀመረ … ድርብና አዝመራ እሚያዋሩት ሰው ስለሌላቸው … እዛ እና እዚህ ሆነው ሽማግሌውን በተመስጦ ያያሉ… ሽማግሌው ሁሉንም ቃኙ… አልጠገቡም… መልሠው በስስት ተመለከቷቸው… ጫጩቶቿን ከጭልፊት እንደምትከላከል ዶሮ በእቅፋቸው ሽሽግ ቢያደርጓቸው በወደዱ … አሁንም በስስት ተመለከቷቸው፡፡ የጥም ስንኞቹን መመንዘር የልቦች ድርሻ ሆነ… ሁሉም እንዳሻው ወርቁን ፍለጋ ልቡ ውስጥ ሮጠ… ከፍቅረኛው ጋር አንሾካሾከ… ከፍቅረኛዋ ጋር አንሾካሾከች…

“ሆሆሆ… ተናግሮ አናጋሪ ሽማግሌ”

“እ.እ. ተልኮ እኮ ነው…”

“ሰው እማይገባው ይመስላቸዋል … አሁን የእኛን ስሜት ለማወቅ እኮ ነው” የሁሉም ሰዎች ልቦች እነዚህንና የመሳሰሉትን አጉተመተመ…

ሽማግሌውም … እንደ ተዋናይ እየተንጐራደዱ ወደ መሀል ቀረቡ፣ እንደ ሰባኪም ቀዝቀዝ ብለው ይሄን ግጥም አንቆረቆሩት … ከንግግራቸው ጋር አብሮ ዋሽንት የሚመስል የድምጽ ቃና ይወጣል … ይሰማል፡፡ አይኖች ፈጠው… ልቦች ተከፍተው… ማስተዋል የራቃቸው ሁሉ … ተሰብስበው… እኚህን ሽማግሌ… በልቦቻቸው ያያሉ… ለምንድን ነው ሀይ ባይ የሌላቸውን… ለዛውም ሬስቶራንት ውስጥ … ለዛውም የከፋቸው … ደስታ የራቃቸው…  አፍቃሪ ሴቶች ባሉበት!

ጥሬን የለገመ … ይህ ትንሽ ስልቻ… ግን አንድ ማሳ ‘ሚፈጅ

ተቀምጦ ነቀዘ… ለዘር እንኳ እንዳይበጅ…!

ዘመን ያነገሰው … በዘሩ አቅልሞ … ቀምቶ ሲበላ

የአፉን ያስዘርፋል… ምድረ አሰጅ /የእንግዴ ልጅ/ሁላ፡፡

ዝም ብለው! ቀጥ አሉ! … አስተያየታቸው የግሳጼ ነው፡፡ ሁሉም ወንድ፣ ሴት ጉያ ውስጥ ማሙቷል… ወኔው ክዶታል…. አሉ በልባቸው!! በአይናቸው እየተፋጁ፣ በአንደበታቸው እየተጋረፉ …እቺን አሉ…

እኔማ ምን ልሆን … ይብላኝ እንጂ ላንተ

“በቃን” ይሉት ወኔ ልብህ ውስጥ የሞተ!!

ሁሉንም ከገረመሙ በኋላ በስጨት ብለው ወጡ፡፡ …

ያልተቋጩ የፍቅር ጥያቄዎችም ከዚህ በኋላ አፋቸው ተሳሰረ… አይኖች ብቻ ሰርስረው ይመለከታሉ… እዛና እዚህ መልስ ሳይሰጣጡ… እኚህ ሽማግሌ መሀል ገቡ፡፡

 

 

 

Read 4187 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:30