Saturday, 26 May 2012 12:27

ወይ ቢሻን!

Written by  ዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(0 votes)

የዘንድሮው ፀሐይ ደግሞ ለጉድ ነው፡፡ ቀበለ ጉዳይ ኖሮኝ ሄጄ ፀሐዩ አናት አናቴን ሲለኝ ውሎ አሁን ከቤቴ ገብቼ አረፍ ማለቴ ነው፡፡ ለማን ነው አቤት የሚባለው ጐበዝ!... ስንት ዓመት ስሰራበት የነበረውን ሱቅ ድንገት ደርሶ ልቀቅ እባላለሁ? ቀበሌ ስደርስ እንደኔው አቤት ባዩ ብዙ ነው፡፡ መፍትሄ የምናገኝ መስሎን ፀሐይ ስንንቃቃ ዋልን፡፡ዳሩ የሚያዳምጥ ሲገኝማይደል? መዋከብ ብቻ አንዴ ወዲህ - አንዴ ወዲያ… እንዲህ ተሁኖ ወር ሲደርስ ደሞዙን የማይቀበል የለም፡፡ የኋላ ኋላ “ዛሬ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ነንና ነገ ተመለሱ” ተባልን፡፡እንዲሁ ባሳብ ስባዝን ችግሬን የማዋየው ሁነኛ ሰው ስፈልግ - ሳወጣ ሳወርድ ቆየሁና አንድ ጐበዝ ሰው አስታወስኩ፡፡ እንዴት ዘነጋሁት? ያውም ከዚሁ ከኔው ቤት ሳይርቅ በዚያ ላይ ደግሞ ጋዜጠኛ ነው ወይ ግሩም በእጅ የያዙት ወርቅ… አይደል የሚባለው ከሱ መቼም መላ አየጠፋም፡፡ ኋላ ከስራ ሲመጣ ጠብቄ ችግሬን አማክረዋለሁ አልኩና የድካሜን ጣመን ልወጣ ወደ አልጋዬ አመራሁ፡፡

እውነትም ደክሞኝ ኖሯል፡፡ አመሻሸ ላይ ነቃሁ እስከ አሁን ሳይመጣ አይቀርም አልኩና ጐረቤቴን ፍለጋ ወደቤቱ አዘገምኩ፡፡ እንደልማዱ ከበረንዳው ላይ ተቀምጧል፡፡ ሁሌም የሚነበብ ነገር ይዞ እዚያ ላይ አንገቱን ደፍቶ ሲያነብ ነበር የማውቀው፡፡ ዛሬ ግን በእጁ ቢየዘውም አያነበውም፡፡ አጠገቡ እስክደርስ አላየኝም፡፡ በሃሳብ ጭልጥ ብሎ ነጉዷል፡፡

“ደህና አመሸህ ማንደፍሮ” ስለው ነው እንደመባነን ብሎ ከሄደበት የተመለሰው

“ደህና አመሹ ጋሼ!” አለኝ ከተቀመጠበት እየተነሳ

“ኧረ ቁጭበል… አይገባም” አልኩት ካጠገቡ ካለው ወንበር ላይ እየተቀመጥኩ፡፡

“ምነው ዛሬ በሃሳብ ሸመጠጥክሳ?” አልኩት አከታትዬ

በዝምታ ሲያየኝ ቆየና “አዩ ጋሼ ይኸን የጋዜጠኝነት ሥራ ከያዝኩ ከአራት አምስት አመት ሆነኝ - ነገር ግን… ባልሳሳት ከዚህ ሁሉ ዓመታት ግማሽ የሚሆነውን በስብሰባና በግምገማ ብቻ ያባከንኩት ይመስለኛል፡፡ ያውም ጠብ ላይል” ሲበሳጩና ሲናደዱ የሚውሉበት ግምገማ፡፡

“ለምን ትበሳጫለህ ልጄ”

“ሰው ነዋ ጋሼ… ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በየደቂቃው ወደ እስስትነት ሲቀየር ለምን አያበሳጭም ጋሼ… የዛሬው ደግሞ…

“ዛሬ ደግሞ ምን አጋጠመህ?”

“አዩ ጋሼ… ዛሬ ጠዋት የየክፍሉ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ሠራተኞች እንደተለመደው ለግምገማ አለቃችን ቢሮ ውስጥ ተቀምጠናል፡፡ በጠረንጴዛው መሃል ላይ በብርጭቆ የተመላ ብዙዎች እንዳሉት ቢሻን ማይ ውሃ ተቀምጧል፡፡

ምን ምን?

“ቆይ አስጨርሱኝ… ከአለቃችን ጐን የተቀመጠው የመምሪያ ኃላፊ ብርጭቆውን አንስቶ ከቀመሰ በኋላ “ውሃ ነው” አለንና ብርጭቆውን አስቀመጠው፡፡ አንደኛው የክፍል ኃላፊ ደግሞ በተራው ብርጭቆውን አንስቶ ቀመሰውና “ቢሻን ነው!” አለ

“እሺ!”

አለቃችን ደግሞ በተራው ተነሳና

“በጄ እሱ ደግሞ ምን አለ?”

እሱም ቀመሰውና “ማይ ነው” አለ

“ጉድ እኮ ነው እሺ”

ሌላውም ተሰብሳቢ በየተራው እየተነሳ አንዱ ማይ፣ አንደሃው ቢሻን ሌላው ውኃ ነው እያለ ተቀመጠ፡፡

“አንተስ ምንአልህ?”

“ልነግሩህ አይደለ?... የኔምተራ ደረሰና አንስቼ ቀመስኩት ከዚያም በእናንተ ሃሳብ አልስማማም፡፡ የሻችሁን በሉት… ነገር ግን የቀመስኩት ይኮመጥጣል፡፡ አልኳቸውና ብርጭቆሙን አስቀመጥኩት፡፡ ከዚያማ ሁሉም እኔ ላይ መጮህ ጀመሩ “ከመቼ ወዲህ ነው ማይ የሚኮመጥጠው… ከመቼ ወደሆነው ቢሻን የሚኮመጥጠው… ከመቼ ወዲህ ነው ውኃ የሚኮመጥጠው… ይህ የምሁር ትምክተኛነት ነው” አሉኝ… አሉኝ፡፡

አለቃችን እስቲ ሁላችሁም ሃሳባችሁን አብላሉትና ከዕረፍት መልስ አንድ ወጤት ላይ ለመድረስ እንሞክር አለንና ለሻይ እረፍት ወጣን፡፡ ስንወጣ አንድ አለሁ አለሁ የሚል ወጠጤ ጋዜጠኛ ተከተለኝና “ማንደፍሮ ምን ማለትህ ነው?” አለኝ

“ምኑ?”

“የአሁኑ አባባልህ ነዋ “ማይነው” ሲል አለቃችንን አዳምጠኸው የለ?

“እና?”

“ሞኝ ነህ ልበል? አለቃህ ማይ ነው ካለ አንተም በቃ ማይ ነው ማለት አለብህ፡፡ ስለ ጣእሙ ምን አገባህ በቃ ማይ ነው ማለት የቅትሃል፡፡

“አባባልህ አልገባኝም፡፡”

“ነገሩኮ ቀላል ነው ማንደፍሮ… ገባህም አልገባህም አለቃህ የሚውን በል በቃ… መኖር ማደግ ከፈለግህ ብልጠ ሁን” አለኝና ሄደ፡፡ …አዩ ጋሼ ስልጣንና ሹመት ፍለጋ አድር ባይ መሆናቸው ሳያንስ፣ ይህን አድርባይነታቸውን እንደ ብልጠት ቆጥረው ሲመፃደቁባት ሳይ ያናድደኛል… ያበሳጨኛል፡፡

“እሺ ከዚያስ እንዴት ሆናችሁ?” አልኩት መጨሻውን ለማወቅ ጓጉቼ የሱን መበሳጨት ወደጐን እየተውኩ፡፡

ተመልሰን ስንገባ ያለቃዬ ፀሐፊ “ከስብሰባው በኋላ ሊያነጋግራችሁ ይችላል እስከዚያው እባካችሁ አረፍ በሉ” ብሎ በእንግሊዘኛ ስትናገር ሰማኋትና እንግዶቹን ለማየት ዘወር አልኩ፡፡ የውጭ ሀገር ዜጐች ናቸው፡፡ አልፌያቸው ገባሁ፡፡

ያው እንደመጀመሪያው በሦስት ተከፍለው የከራከራሉ፡፡

“ማይ ነው

ውሃ ነው

ቢሻን ነው” እየባባሉ፡፡

“ይኸ ነገር መቋጫ ላይኖረው ነው?” አልኩኝ በልቤ ወዲያው አለቃችን አንድ ሃሳብ አቀረበ፡፡ እኛ መስማማት ካልቻልን እሱን ለማነጋገር የመጡት የውጭ ሀገር ዜጐች (አሜሪካዊያን ናቸው) እንዲያስማሙን

“ሁሉም በአንድ ድምፅ ተቀበለው!” “ማሽላ እያረረ ይስቃል” እንዲሉ መሳቅ ጀመርኩ፡፡

“እንዴት ማለት?”

“አዩ ጋሼ… በደንብ ጠንቅቄ አውቃቸዋለሁ፡፡ አንዳንዴ አለቃችን “በቃ!... ወስኛለሁ ወስኛለሁ…” ብሎ ባለው ሥልጣን ተጠቅሞ ጉዳዩን ካልዘጋው በቀር አንዳቸው ላንዳቸው በጭራሽ እጅ አይሰጡም፡፡ ስህተትን አምኖ በመቀበል፣ በመታረም ማሸነፍ አይሆንላቸውም “ማን ከማን ያንሳልና!” የሁሉመ መፈክር ነው፡፡ በአጋጣሚ ልክ እንደ አሁኑ አጋጣሚ ተፈጥሮ ሳይሸናነፍ አስታራቂ ከተገኘ ደስታቸው ነው፡፡ አሁንም በአንድ ድመፅ የተስማሙት ለዚህ ነው፡፡

“እና ፈረንጆቹ መጡ?”

“አዎና… አለቃችን አስጠርቷቸው ገቡ፡፡ ገብተው እንደቆሙ የልዩነታችን መነሻ ተነገራቸውና ቀምሰው ምን እንደሆነ እንዲነግሩን ጠየቃቸው፡፡”

“እሺ”

“ፈረንጆቹ አላቅማሙም፡፡ ሁለቱም ተራ በተራ ቀመሱና በአንድ ድምፅ ከፈገግታ ጋር ወተር!” አሉ

“እሺ”

“ሁሉመ ሰው አጨበጨበ!... አጨበጨበ!... አጨበጨበ!... ህም በድምፅ ብልጫ ይወሰን ተባለ፡፡

ቆጠራ አላሰፈለገውም፡፡ ከኔ የተቃውሞ ድምፅ በቀር በሙሉ ድምፅ “ወተር!” ተባለና አጀንዳው ተጠናቀቀ፡፡ እውነት በድምፅ ብልጫ ሀሰት ተበላች፡፡ ይኸው ነው አለና በረጅሙ ተነፈሰ፡፡

“ቆይማ… አንተ ግን ለምንድን ነው ይኮመጥጣል ያልከው?”

“አዩ ጋሼ በብርጭቆው ውስጥ ያለው… የርስዎና የኔ ቢጠዎች ያውም የብዙዎች በየዶሴው ያነባነው እምባ ተጠራቅሞ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጠረንጴዛው ላይ የተቀመጠው የተከማቸ ዶሴ እንጂ በብርጭቆ የተመላ ውሃ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኛ የብዙዎቻችን እምባ… በየዶሴው የተከማቸ እምባ… ላንዳንደቹ ማይ… ላንዳንደቹ ውሃ ላንዳንዶቹም ቢሻን ነው ወተር!” አለኝና ተነስቶ ቆመ፡፡

ደህና እደር ሳልለው ወደ ቤቴ ማዝገም ጀመርኩ፡፡ ወይ ቢሻን ቤቴ ከገባሁ በኋላ ነው የሄድኩበትን ጉዳይ መዘንጋቴ የታወሰኝ፡፡

እኔስ የትኛውን ፈረንጅ ይዤ ቀበለ ልሂድ… ከኛ ታች ቀበሌ ያለውን ባለጋራዡን አንቶንዮን ለምኜ ይዤው ብሄድስ?... ሰላቶም ቢሆን ያው ፈረንጅ ነው፡፡ ቀበሌዎችስ ደጅ የሚጠናውን የኛን እምባ ምን ይሉት ይሆን? ቢሻን… ማይ ወይስ በጥልያንኛ አናፊያሬ?... ቂ…ቂ….ቂ…ቂ ወይ ቢሻን!

 

 

 

 

 

Read 3082 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:32