Wednesday, 04 April 2012 09:42

ፊዮሪ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(2 votes)

ፊዮሪ ፊዮሪ መውደቂያሽ ከየት ይሆን…አንቺ ቅዝቃዜሽ ከጥቅምት ንፋስ የበረታ…አንቺ ሙቀትሽ የፀሐይ አንኳር የሆነ…አንቺ ፊዮሪ መውደቂያሽ ከየት ይሆን? ይኼው ዛሬም ከጨለማው ውስጥ ሆኜ የትካዜዬን ፉጨት አፏጫለሁ፡፡ የቤትሽ መአዘን ሀሳቦቼን አዝሎ በክፍሉ ወስጥ ብዝሀ አድርጐኛል፡፡ ትዝ ይልሽ ነበር…. ስከተልሽ?  ብከተልሽስ አንቺ ምን ገዶሽ…ነገር ግን መከተሌን አታውቂም ነበር፡፡ ፒያሳ ሰሜን ሆቴል አካባቢ ቅጂው ከየት እንደሆነ ለመንደሩ ግር ባለው አረማመድሽ ወደ ፊት ስትሄጂ፣ የሰፈሩ ብላቴና ከምኞቱ ጠቀስ ላይ ሲያወጣሽ አንቺም ስሜታቸው እየገባሽ ስትራመጂ … በዛ አረማመድሽ ትዝ ይልሽ ነበር … ፒያሳ ሰሜን ሆቴል አካባቢ ስትራመጂ? አንቺ ሳታይኝ እኔ ስከተልሽ፣ በአካል ሳይሆን ባይኔ ልጠብቅሽ ልከላከልሽ፣ ልንከባከብሽ፣ ላሳምርሽ ስሞክር … ባይናቼ ብቻ ጥረቴን ሳስተጋባ ሳታይኝ፡፡ ቀጥለሽ የሰሜን ሆቴል በር ላይ ሄደሽ ስትቆሚ … አይ ፊዮሪ! ያቋቋምሽ ቅኔስ ቢሆን ማን ዘርፎት ያውቃል? ያ ሁሉ ሲሆን አይሽ ነበር …

ዛሬም ቢሆን ከጨለማው ውስጥ ተቀምጬ ሲጋራዬን እየማግሁ ይታየኝ የለ ቆመሽ  ቆመሽ ስታበቂ … ፈገግ ብለሽ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ስትዞሪ አላየሺኝም ነበር፡፡ እኔ ግን አይንሽን ተከትዬ ተመልክቻለሁ፡፡ አንዱ ያንን ቀይ መኪናውን ከፍቶ ወጥቶ በዛ በ”ምንም” ከንፈሩ ጉንጭሽን ሲስመው … ስትሰሚው አላየሺኝም እንጂ እኔስ ሳይሽ ነበር፡፡ ከዛም ይዞሽ ወደ ሆቴሉ ዘለቀ…አይ ፊዮሪ?!

ይታወስሽ ይሆን…..

የዛን ቀን ማታ የከንፈርሽ ፈርጥ ሊፒስቲክሽ ከቦታው ተገሎ…ያይንሽ ሽፋሽፍት ጨለማ ሆኖ … ነጩን የብሌንሽን መደብ ለአለም ወንድ መጣሪያ ያደረገልሽ ኩልሽ ስፍራውን ስቶ…አረማመድሽ አንቺን ጥሎሽ አለም መስሎ … አዋዋልሽን ሲናገርብሽ … ሲመሽ መጥተሽ፣ ከጨለማው ቤትሽ ውስጥ ገብተሽ፣ መብራቱን ስታበሪው … ከሶፋው ላይ ጠባቂሽን እኔን ስታይኝ…እያጨስኩ…እየቀናሁ ስመለከትሽ … ዘወትር እንዳስለመድሺኝ፣ ለሶስት ደቂቃዎች፣ ቃላት ባልተዘሩበት የድምጽ ምድረ በዳ፣ በዝምታሽ ስትቃኚኝ … ከዛም በእርጋታ እና በስካር መንፈስ ሆነሽ፣ ከፊት ለፊቴ ተቀምጠሽ ታወሪኛለሽ … የዛን እለትስ ምን እንዳልሺኝ ታስታውሻለሽ?...እኔ ትዝ ይለኛል፤ ልንገርሽ…

“…ሰውየው ባለትዳር ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ እኔ ጋር ከመምጣቱ በፊት ከሚስቱ ጋር ተኝቶ ነበር፡፡ ሲላፋኝ ሚስቱ በፍቅሯ ያተመቺው ጠረኗን ከላዩ ላይ አሽትቼዋለሁ…የእኔን ጠረን ደግሞ ሚስቱ አልጋ ውስጥ ሲገባ ታሸተውና ታውቀዋለች…”

አይ ፊዮሪ! ደሞ’ኮ ታዝኚልኛለሽ፡፡ ታወሪ ታወሪና እንባሽ ይመጣል፡፡ ያለ ከልካይ የሚዘንቡት የእንባሽ ዘለዎች የሚናገሩት ቢያጡ…አይ ፊዮሪ!

ካለቀሽ በኋላ አታወሪም…እንደኔ ትሆኛለሽ…ዝም ትያለሽ፡፡ ከተቀመጥሽበት ተነስተሽ እኔን ከተቀመጥኩበት ታነሺኛለች፡፡ ይሄ ሁኔታሽ ሁልጊዜ ያስደስተኛል፡፡ ከአልጋ ስንገባ በረዶ የነበረው ሰውነትሽ ወዲያው ይግላል፡፡ ሁለመናሽ ይሞቃል፡፡ ሳቅ በሳቅ ትሆኛለሽ…ጸጉርሽ ይለሰልሳል…ፊትሽ ያብረቀርቃል … እላዬ ላይ ወጥተሽ ስትላፊኝ አይኖቼን እጨፍናለሁ፡፡

“ወንድ አይደለህም…አይኖችህን ግለጥ…ወንድ አይደለህም?” እያልሽ በጥፊ ትመቺኛለሽ፡፡ አይ ፊዮሪ…ዛሬ ልንገርሽ እንጂ…አይኖቼን ያልገለጥኩት የሰሜን ሆቴሉን ጐረምሳሺን ዳግም ላለማየት ስላልፈለግሁ እኮ ነው….ለኔ ሳይሆን ለራስሽ ሲል የሚዘለውን የጡትሽን ዘንግ ላለማየት እኮ ነው…ፊዮሪ! አሁን ልንገርሽ…የኔ ያልሆነውን ላለማየት ስለፈለኩ ነው አይኖቼን ያልገለጥኩት፡፡

ዛሬም ቢሆን አይኖቼ አልተገለጡም…እጨለማ ውስጥ አይንን ቢገልጡት ምን ይፈይዳል፡፡ ከፊት ለፊት ብርሃን ከሌለ አይን ምን ጥቅም አለው…? እናማ ፊዮሪ በጨለማ ውስጥ የትካዜዬን ፉጨት እያፏጨሁ…ሀጥያቶችሽን እያሰብኩ እወድሻለሁ፡፡ ትዝ የሚሉኝን ሳልመርጥ አስብሻለሁ፡፡ ቀናኢ የተባሉ ተግባሮችሽ የትኞቹ እንደሆኑ ለማሰብ የትም የስሜት መቃ ላይ አልወጣም…

ካስታወሽ ልንገርሽ…

መጀመሪያ ላይ ስንተዋወቅ ቃል የገባሁልሽ ነገር ነበር…ቃል መግባት የጀመርኩትም የጨረስኩትም የዛን እለት ነበር፡፡ ምን ያህል መብረር እንደምትፈልጊ የነገርሺኝ እለት…ምድር እንድትሞትብሽ የፈቀድሽላት ሴት መሆንሽን ያመንኩ እለት…የምትኖሪው ለምክንያት ተፈልገሽ ሳይሆን ምክንያትን ልታጠፊ መሆኑን የነገርሽኝ ቀን! በዛ ቀን ቃል ስገባልሽ ትዝ አለሽ … ከጆሮሽ ተጠግቼ ያንሾካሾኩልሽ ምስጢር! አሁንም ቢሆን ያዥው አትናገሪው … እነዛን የሚስጥር ቃላቶች!

በማንም የሰው ዘር ሊገመት የማይችል ዱብዕዳ አሳየሺኝ…ጠዋት ሳይሽ አንድ ሆነሽ ማታ ስትገቢ ብዙ ሆነሽ ትገቢያለሽ…ብዙ የማላውቅሽ አንቺን ይዞሽ! ደሞ አይንሽ አይንሽ! አይንሽ! አይንሽ! አይንሽ! …………..አይ ፊዮሪ!

እኔ ያው እንደተፈጠርኩ እንዳለሁ ነኝ…ልክ ፈጥረሽ እንደለቀቅሽኝ! ማንነቴ ውስጥ ምንም አይነት ንፋስ ሳላስገባ፣ ከያኔው ከድንግሉ ዝምታዬ ጋር … ከዛው ከጨማው ክፍልሽ ውስጥ በዛው የትካዜ ፉጨት ታጥሬ፡፡

ፊዮሪ በቀላሉ የማይፈርስ አቅም እንዳለሽ እያመንኩ ነበር … ለእስካሁኗ ደቂቃ ባለሁበት ህይወቴ ስበር የመጣሁት፡፡ ዛሬ ግን አቅምሽን በሀሳብ ብቻ ልመለከተው በመጣጣር ላይ ነኝ፡፡ የማገኝሽ ይመስለኛል…አይ ፊዮሪ! ለማንም በማንም ላይ ምንም ብትሰሪ መቼም የጥፋተኝነት ስሜት እንደማይሰማሽ ነግረሺኝ ነበር፡፡ በወንድ ስጋ ላይ መራወጥ ብቸኛው የህይወትሽ ፍልስፍና እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህን ሁሉ አርገሽ ለመንገድ እንኳን የሚሆን ስባሪ ሳንቲም እንደማትቀበያቸው ይገባኛል፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ወደ ውስጥሽ የዘለቀ ወንድ፣ እራሱን ከምድር እስከመሰረዝ እንደሚያፈቅርሽ ሰምቻለሁ ፊዮሪ! ገድል መስራት ይመቸኛል … ካንቺ ጋራ ይህችን የህይወት ገድል ሳደርግ፣ የሚጣፍጥ በሽታ ከውስጥ ይንጠኛል፡፡

ዛሬ ጥለሺኝ ስትሄጂ የተሰማኝ ግማሽ ጀግንነት …ግማሽ እውነት…ግማሽ እምነት …  እስከመቼ እንደሚቆይ አላውቀውም፡፡ ለዛም ይመስለኛል፤ ጨለማን ዋጠኝ ብዬ የምማፀነው፣ ተመልሰሽ ስትመጪ እንዳያዩሽ አይኖቼን ካንቺ ለመሰወር እንዲመቸኝ…አይ ፊዮሪ!

ይኸውልሽ ዛሬም አንቺ አቅቶሽ የራቅሺውን…እኔም የምመኘውን የህይወት እርቀት በፉጨት እጠራዋለሁ፡፡ የመጨረሻ ቀናችንን ሁሌ እንደትላንት እያሰብኩት ዛሬ ላይ እጠብቅሻለሁ፡፡

የመጨረሻው ቀናችን…

የመጨረሻ ቀናችንማ … እነዛን ሃጢያቶችሽን ካይንሽ ላይ ያፀዳሁበት ቀናቶች መሰሉኝ…ወደ ጽድቅ አለም ሊከቱሽ የሚታገሉሽን አይኖቼን መፍራት የጀመርሽበት ቀን መሰለኝ…የተበሳጨሽበት ቀን መሰለኝ…አይ ፊዮሪ! ስትበሳጪ አታስደነግጭም…አዎ የመጨረሻው ቀናችንን እንደ ትላንት እየቆጠርኩት ዛሬ ላይ ቆሜ እጠብቅሻለሁ፡፡

እስከዛ አስብሻለሁ፤ ልክ እስካሁን ሳደርገው እንደነበረው፡፡ በጆሮሽ የነገርኩሽን ግን እንዳትረሺ …ትንቢቴን አታውሪው…ፊዮሪ! ሲጋራዬን በጨለማ እየመጠጥኩ አስብሻለሁ፡፡ እስካገኝሽ አላለቅስም… አልስቅም… ስለሌላ አላስብም…አይኔን አልገልጥም…በግማሹ ጀግንነቴ አልናኝም…ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ …በትካዜ ከጨለማሁ ሰምጬ አፏጫለሁ………፡፡

 

 

Read 4381 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:47