Saturday, 17 March 2012 09:51

ታች - መሐል

Written by  ሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ መስሪያ ቤት ከተቀጠርኩ ትንሽ ጊዜ አለፈኝ፡፡ “ጊዜ ንጽጽር ነው” የሚለው የሰአቱ አቆጣጠር ትዝ ሲለኝ ቀና ብዬ ተመለከትኩት፡፡ ሰአት አልፎኛል፡፡ ሰላሳ አመት እንደማለት ነው፡፡ አንድ ሰአት እና አንድ አመት ብዙ ለውጥ የላቸውም፡፡ ህይወት እና ስራ አንድ ናቸው፡፡ ሀገር እና መስሪያ ቤትም እንደዛው፡፡ በመስሪያ ቤቱ በእየማለዳው እነቃለሁ፡፡ ብዙ ቢሮዎች አሉት መስሪያ ቤቱ፡፡ መስሪያ ቤቱ ይንቀሳቀሳል፤ ስራው ግን አይንቀሳቀስም፡፡ ስራው ቢንቀሳቀስ ለውጥ ይመጣ ነበር፡፡ ቢሮዎቹ በሙሉ በር አላቸው፡፡ የበሩን ቁልፍ የያዘው ሰው፤ የቢሮው ሃላፊ ነው፡፡ በሮቹ ብዙ አይነት ናቸው፡፡ ወደ ውስጥ የሚያሳዩ ግን የማያስገቡ በሮች አሉ፡፡ ወደ ውስጥ የሚያስደምጡ እንጂ የማያሳዩም… የማያስገቡም በሮች አሉ፡፡ አንዳንዱ በር፤ እንደ ስዕል የተሳለ እንጂ አገልግሎት የማይሰጥ፣ ለማንኳኳት ብቻ የተፈጠረ የሚመስል ነው፡፡ “የእውነት ቢሮ” እንደዛ አይነቱ ነው፡፡ የቢሮውን ተጠሪ አቶ እውነትንም አይቻቸው አላውቅም፡፡

ታይተው የማይታወቁት ሰውዬ በር ላይ ቆሞ ሲያንኳኳ የሚውል አንድ ሽማግሌ አለ፡፡ ያንኳኳል እንጂ ለመክፈት ምንም ሙከራ ሲያደርግ፣ በቁልፉ ቀዳዳ አጮልቆ ሲመለከት አላጋጠመኝም፡፡ አልፌው ወደ ራሴ ቢሮ እገባለሁ፡፡ “የፀሐፊ ቢሮ” ይላል፡፡ እኔና ሌሎች አራት ባልደረቦቼ አብረን የምንሰራበት ነው፡፡ ስራችን እስካሁን መጠበቅ ነው፡፡ የምንጠብቀው ጥበቃን ነው፡፡ እርስ በራሳችንም በአይነ ቁራኛ እንጠባበቃለን፡፡ ስራ የምትሰራ በማስመሰል የሚጠበቀውን መጠበቅ እና መጠባበቅ ጥሩ እንደሆነ አምኜበታለሁ፡፡

የአቶ እውነትን ቢሮ የሚያንኳኳው ሰውዬ፤ የዛሬ አንድ አመት ገደማ በሩን የሚያንኳኳበት ድምጽ በጣም ጨምሮ ስራ አላሰራ ቢለን፣ ከየቢሮአችን አንገታችንን ተራ በተራ ብቅ እያደረግን ብንመለከተው፣ የሚንኳኳው በር ድንገት ከውስጥ ቁልፉ ሲንቀጫቀጭ ተሰማ፡፡ ሊከፈት መሆኑን ሲያውቅ፣ ሲያንኳኳ የነበረው ሰውዬ እንዴት በሩጫ እንደተሰወረ አትጠይቁኝ፡፡ በሩም፤ ተንቀጫቀጨ እንጂ አልተከፈተም፡፡ በማንኳኳት የሸመገለውም ሰውዬ ከሮጠበት አልተመለሰም፡፡ ጠራጊዎቹ ጠዋት  መጥተው አፀዳድተው ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዴ ይቀራሉ፡፡ ይኼኔ፤ የህሊና ቁሻሻው ተከማችቶ አላስቀምጥ ይላል፡፡

እስካሁን የተዋወቅኩት ሰራተኛ የለም፡፡ ከሁሉም ጋር በአንገት ሰላምታ እንለዋወጣለን፡፡ ደሞዝ ከፋዩን አቶ “ድህነትን” ብቻ ስሙን አውቀዋለሁ፡፡ ደሞዜ በምስጋና መልክ ነው የሚከፈለኝ፡፡ “በድህነት ያስተማረ ያሳደገህን መስሪያ ቤት የምትከፍልበት ወቅቱ እነሆ ይላል” ከአቶ ድህነት ጠረጴዛ በላይ ያለው መፈክር፡፡ በተቀበልኩት ምስጋና የወሩን ቀለቤን ለመሸመት ገበያ እወርዳለሁ፡፡ ከድህነት እጅ የሚገኝ ምስጋና በጣም ተፈላጊ ነው፡፡

በአለፈው የሆነ ነገር ፃፍልኝ ብው አቶ ታሪክ የሚባሉ የመስሪያ ቤታችን ባልደረባ ደብዳቤ ይዘው መጡ፡፡ ደብዳቤው መሀተም ብቻ ያለበት ነበር፡፡ የደብዳቤውን መልዕክት በወረቀቱ ላይ ማስፈር የኔ ስራ ነው፡፡ አቶ ታሪክ፤ ህልም የመሰሉ ጭርጭስ ያሉ ሰውዬ ናቸው፡፡ ለኔ እና ለጽሑፍ ክፍሉ ይዘው የመጡት ስራ የመስሪያ ቤቱን ታሪክ ለሦስት ሺ ምናምነኛ አመት ክብረ በአሉ ጽፈን እንድናዘጋጅ ነው፡፡

አቶ ታሪክ በጣም የተከበሩ ሰው ናቸው፡፡ የሰጡንም ስራ የተከበረ መሆኑን መግለጫ አላስፈለጋቸውም፡፡ አቶ ታሪክ ሲራመዱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተ ተራ ሰው፣ በጣም ግራ ተጋብቶ ይስቃል፡፡ እኔም ስቄ ነበር፡፡ የሚራመዱት ወደ ኋላ ነው፡፡ ጫማቸውም ወደ ኋላ የዞረ ነው፡፡ በዛ ላይ ጥምም..ም…ም..ም ያሉ ናቸው፡፡ ብዙ ቦታ ተሰብሮ እንደገና እንዳደገ ዛፍ፡፡ ዛፍ ሳይሆን ስራ ስር የሆነ ጉቶ፡፡ እንግዲህ ለኛ ለፀሐፊዎቹ የተሰጠን ስራ ያንን ሁሉ ጠማማ ስር ማቃናት ነው፡፡ አሊያም በደንብ አድርጐ መቆላለፍ፡፡

ስንጠብቀው የነበረው ስራ መጣ፤ ግን መጠበቃችንን አላቋረጥንም፡፡ ትንሽ ገፋንበት፡፡ ስራው ጭፍርር ያለ ነው፡፡ ከየትኛው ጀምረን እንደምናበጥረው  አጠያያቂ ሆነብን፡፡

ስራ አስኪያጁ በስልክ ደውለው ስራውን ከመጀመራችን በፊት የተከበሩ አቶ ባህል ጋር ምክክር እንደሚያስፈልግ ነገሩን፡፡

የአቶ ባህልን ቢሮ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ወደ ላይ እና ወደ ታች እየወረድን ብንፈልገው ልናገኘው ሳንችል ቀረን፡፡ የመስሪያ ቤቱ ባላገር ወደሚገኝበት ወጥተን በሮቹን ማሰስ ጀመርን፡፡ ባላገሩ ላይም “ጀለሴን” ልናገኘው አልቻልንም፡፡ ከብዙ ፍለጋ በኋላ የተከበሩትን አቶ ባህል፣ በዘመናዊ ሙዚቃ እና መጠጥ እየተዝናኑ አገኘናቸው፡፡ ሰክረዋል…ልንገባባ አልቻልንም (ጭፈራቸው ያስፈራል)፡፡ በዛ ላይ ለመሰደድ እያሰብኩ ነው አሉን፡፡ ትተናቸው ተመለስን፡፡ ወደ ከተማ የመስሪያ ቤቱ ህንፃ ክንፍ፡፡

“ፀሐፊዎች ናችሁ አይደል?” አለች አንዲት ጉስቁል ያለች የጽዳት ሰራተኛ፡፡

“አዎ” አልናት፡፡ አቋራጭ ልታሳየን እየመራች ወደ አንድ በር ወሰደችን፡፡ “የውሸት መግቢያ” ይላል፡፡ ከፍታ አስገባችን፡፡ ከጀርባችን በሩን ዘጋች፡፡ በሩ ላይ የተፃፈውን ጽሑፍ አንገታችንን አዙረን አነበብን፡፡ “የአቶ እውነት ቢሮ” ይላል፡፡ ሲንኳኳ እንጂ ሲከፈት አይተነው የማናውቀው በር በእውነት አድራሻ ወደ ውሸት የሚወስድ ነበር፡፡ በውሸት አድራሻ ደግሞ ወደ እውነት፡፡ እውነትም ውሸትም የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁለቱም መተላለፊያ ኮሪደር ናቸው፡፡ እኛም ዞር ብለን ጽሑፉን ባናይ ውሸት ውስጥ የገባን በመሰለን ነበር፡፡ በእውነት በር የገባውም ዞር ብሎ ካላየ ውሸት እውነት መስሎት ይቀራል፡፡ ወደ ቢሮአችን ተመለስን፡፡ አቶ ታሪክ ፊታቸውን ወደ ጀርባ፣ ጀርባቸውን ወደ ፊት አድርገው ተቀምጠዋል፡፡ እኛ ከድሮው ወደ ዛሬ እንድንመለስ እየጠበቁ፡፡ ከአቶ ባህል ጋር ያደረግነውን ግራ የተጋባ ውይይት ጠቅሰንላቸው፡፡

“ማነው ባህል፣ ባህል ከመሞቱ በፊት የወለደው ልጅ አለው ነው የምትሉኝ” አሉን

“አቶ ባህልን ሰክረው አገኘናቸው ነው ያልኖት አባባ” አልኩ፡፡ እየሰሙኝ እንደሆነ ግን ምንም ማረጋገጫ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የጥንቱን ገድል የሚሰማ ከመሬት ስር የተተከለ ጆሮ ነው ያላቸው፡፡ ጆሮአቸውን ከድሮው ነቅሎ ወደ ዘንድሮ ማምጣት… ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡

አቶ ባህል፤ አቶ ታሪክ ሞተዋል ይላሉ፡፡ አቶ ታሪክ ደግሞ አቶ ባህልን ቀብሬ ብቻ ሳይሆን ገድዬ የተመለስኩት እኔ ነኝ ይላሉ፡፡ አቶ ታሪክን የመግደል አቅም ያለው ግን ፀሐፊው ብቻ ነው፡፡

አቶ ታሪክ ያሳለፉት ገድል ካልተተረከላቸው ወይንም ካልተተረተላቸው ይሞታሉ፡፡ ግራ አጋብተውኛል፡፡ በዚህ ላይ የራሴ ህይወት ደግሞ ጐርምሶ ሊውጠኝ መጥቶብኛል፡፡ ሚስት ይፈልጋል፡፡ ተው! ብለውም አልሰማ ብሎኛል፡፡ የራሴን ታሪክ ሳልፅፍ እንዴት ነው የታሪክን ታሪክ የምጽፈው?... ታሪክ ሳልሰራ… ታሪክ አልጽፍም ብዬ ወሰንኩ፡፡

ወደ ሴቶች ቢሮ ማመልከቻዬን ይዤ ሄድኩ፡፡ ማህተም አስመትቼ፡፡ የሴቶች ቢሮ ብዙ የንኡስ ክፍሎች አሉት፡፡ ወንዶች ባል መሆን ሲፈልጉ፣ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ክፍል አለ፡፡ በአላቂ እና በቋሚ ሴትነት የሚቀርቡ ሴቶች ግምጃ ቤት ይገኛሉ፡፡ ወንዶች ባል መሆን ሲፈልጉ ብቻ ሳይሆን ወንዶች ሚስት መሆን ሲፈልጉም ወደዚሁ ቢሮ ነው የሚመጡት፡፡ “በአንደኛ ደረጃ የምትፈለገው የሴት አይነት መግለጫ” የሚለው ክፍት ቦታ ላይ “ጭንቅላት ያላት” የሚል ሞላሁበት፡፡ ክፍሉ ሙሉ ስለሆነ ማመልከቻዬን አስገብቼ ወጣሁ፡፡ ጐደልኩ፡፡ ወደ ቢሮዬ ተመልሼ ቁጭ እንዳልኩ አንድ ጥያቄ ትን አለኝ፡፡ ጀርባዬን ደብድቤ ከመሞት ተረፍኩኝ፡፡ “ጭንቅላት ማንስ እንዳለው እንዴት አውቃለሁ?” ጭንቅላት እንደ ጥርስ መብቀል እና አለመብቀሉ አይታይህም፡፡ ወይንም መበስበሱና መሸረፉ፡፡

ጨጓራ እንዳለው ሲበላ ይታወቃል፡፡ ጭንቅላት እንዳለው እንዴት ማወቅ ይቻላል? አቶ ባህልም ሆነ አቶ ታሪክ ጭንቅላት እንዳላቸው ማወቅ አልችልም፡፡ በመሰረቱ ለጐረመሰው ህይወቴ ሚስት እንጂ ጭንቅላት ምን ያደርግለታል?.. “በፍቅር ለመጠቃት ተጋላጭ የሆነች” ማለት ነበረብኝ፡፡

ተመልሼ ወደ ሴቶች ቢሮ ሮጥኩ፡፡ “ጭንቅላት ያላት” የሚለውን ሰርዤ ደልዤ “ብር ያላት” ብዬ ሞላሁበት፡፡ ወደምፈልጋት አይነት ሚስት ለመድረስ… የማልፈልገውን አማራጭ መውሰድ ነበረብኝ፡፡ “ወደ ገነት ለመድረስ አጭሩ አቋራጭ ገሀነም ነው” ይላል፤ የትዳር ግምጃ ቤቱ ላይ በታላቅ ቃለ አጋኖ የተፃፈው መፈክር፡፡

ደስ ብሎኝ ወደ ቢሮዬ ተመለስኩ፡፡ አንድ ነገር በስኬት ያከናወነ ትከሻዬ ተጣጥፎ ከተሰበሰበበት እንደ ጃንጥላ ተከፍቶ በእኔ ላይ ፎከረ፣ አንዣበበ፡፡ ትከሻዬ እኔንም ያስፈራራኛል፤ እንደዚህ ሲደነፋብኝ፡፡ ትከሻዬ የእኔ ከሆነ ሌሎቹ ላይ አይደነፋም?!... አይደነፋልኝም “በመሰረቱ ትከሻችሁ የእናንተ አይደለም” ብሏል አህያ ነጂው፡፡ “የማሸክማችሁም የማሳርፋችሁም እኔ ነጂው ነኝ”…እኔ የምሸከመው በልቤ ነው፤ ትከሻው እኔ ላይ ቢጫንም ንብረትነቱ የመንግስት ነው፡፡ መንግስት የአቶ ታሪክን ግለህይወት እንድጽፍ አዞኛል፡፡ የተጫንኩትን ሃላፊነት ማዳረስ እና ማራገፍ አለብኝ፡፡ ትከሻዬን ትቼ ስራዬ ላይ ተመሰጥኩኝ፡፡ አቶ ታሪክን ከየት ጀምሬ እንደምጽፋቸው ግን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከላይ? ከታች? ወይንስ ከመሐል? አቶ ታሪክን ፎቶ ግራፍ ማስነሳት ቢቻል እኮ እኔም ለመፃፍ በመሞከር ባልተጐሳቆልኩ ነበር፡፡

“እኔ አባትህ ሀይማኖተኛ ነኝ”  አቶ ታሪክ ያሉኝ ድንገት ትዝ አለኝ፡፡ ሀይማኖተኛ ከሆኑ ሀይማኖታዊ ታሪክ ነው ያላቸው ማለት ነው፡፡ ሳይንሳዊ አይደለም፡፡ ይኼንንም መገንዘብ እኮ የአባት ነው፡፡ አቶ ሳይንስ የመስሪያ ቤቱ የመጨረሻ ፎቅ ላይ ናቸው፡፡ ማን እዛ ወስዶ እንደሰቀላቸው አላውቅም፡፡ በብርሀን ፍጥነት ነው የፎቁ ርቀት የሚለካው፡፡ አሳንሳርም ሆነ መንኮራኩር የለም፡፡ አቶ ሳይንስም ወደ ምድር አይወርዱም፤ እኛም አንወጣም፡፡ … የተከበሩ ጋሼ ሀይማኖት ቢሮ ግን ምድር ቤት ነው፡፡

ስለ ሰማይ ቤት ገድል የሚሰብኩት ከምድር ቤት ነው፡፡ ከላይ የተፃፈውን ማንበብ የሚቻለው ከታች ብቻ ነው? ከምድር ቤት …

ምድር ቤት ስወርድ ሰማይ ቤት መግባት የሚፈልጉ ሰዎች … ያፈሩትን ንብረት ተሸክመው ተሰልፈዋል፡፡ ቲኬት ኦፊሱ እቃቸውን እየመዘነ ቀረጥ ይቀበላል፡፡ የበረራ ቅልጥፍና እና አስተማማኝነቱን በሰባኪዎቹ አማካኝነት እያስነገረ ነበር፡፡ … የሆነ ነገሩ ቅር አሰኘኝ፡፡ “ምድር ቤት” ይላል የስፍራው መግለጫ፡፡ የመስሪያ ቤቱ የሀይማኖት ሰራተኞች በሙሉ የሚገኙበት ነው፡፡

ግን ተጠራጠርኩ፡፡ ወሬ ሰምቻለሁዋ፡፡ በአንደኛ ፎቅ እና በምድር ቤት መሀል ባለው ጠባብ ክፍተት ላይ፣ በተመሳሳይ ቢሮ ከፍተው የሚሰሩ ጠንቋዮች አሉ፡፡ ከህጋዊ ሀይማኖተኞች ትኬት ለመቁረጥ ሄዶ ወደ “አዎንታዊ” ሳይሆን “አሉታዊ” ሰማይ ቤት አድራሻው ጠፍቶበት ተጭበርብሮ የሚቀር፡፡ … እርግጥ እስካሁን በትክክለኛው ትኬትም ይሁን ተመሳስሎ በተሰራው የተጓዘ ሰው መጓዙን እንጂ መድረሱን አሳውቆን አያውቅም፡፡ መሳሳትም ሆነ ትክክልነት የሚለው ክርክር ምድር ቤት ነው ያለው፡፡ የአቶ ታሪክ ታሪክ የአየር መንገዱ ታሪክ ነው ማለት ነው? ግን የትኛው አየር መንገድ …?

ሁሉም  ነገር ስለተምታታብኝ ለተወሰኑ አስርት አመታት በካፍቴሪያው ውስጥ በስራ የደከመውን አእምሮዬን ሳሳርፍ ቆየሁ፡፡ በዳማ ጠጠር ቼዝ መጫወት እንደሚቻል ያስተማረኝ አንድ ሰው (የግራ አገባብ አባቴ):- “የሰው ልጅ ዋናው ስራ እረፍት ማድረግን መቻል ነው” ይለኝ ነበር በካፊቴሪያው ቆይታዬ፡፡ በሱስ እረፍት አጥቶ ተሰቃይቶ ሲሞት ካየሁ በኋላ እረፍት በቅቶኝ ወደ ስራ ተመለስኩ፡፡ ከአስር ደቂቃ እረፍት በኋላ መስሪያ ቤቱ ድንገት ተለዋውጦ ጠበቀኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡

… ወደ ራሴ የስራ ገበታ ሮጥኩ፡፡ ሁሉም ነገር በብሩህ ነገር የተወለወለ ይመስላል፡፡ ጠረጴዛዬ የብር መስታወት መስሏል፡፡ የስራ ባልደረቦቼም መጠባበቅ ትተው እየሰሩ ነው፡፡ ተዘግተው እድሜ ልክ ውስጣቸውን አይተን የማናውቃቸው በሮች ወለል ብለው ተከፍተዋል፡፡ ወለልም አላቸው፡፡ በፎቆቹ መሀል  መገናኘት እንዳይኖር ደረጃ ከዚህ ቀደም አልነበረም፡፡ ከላይ ወደ ታች ለመውረድ በሰው ጀርባ እየታዘሉ ነበር፡፡ ወደ ታች ወርደው መልሰው ወደ ቀድሞው ምቾት መውጣት ያልቻሉት ደግሞ በገመድ ይንጠለጠላሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ድንገተኛ ለውጥ ምንድነው ምክንያቱ? ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ምክንያቱን ግን ሳይነግሩኝ አስቀድሜ አውቄዋለሁ፡፡ አቶ ታሪክ ሲሞቱ ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ “አቶ ታሪክ ወይዘሪት ተስፋን አጭተው አገቡ” አሉኝ፡፡ “ከእንግዲህ ስለ ድሮው ሳይሆን ስለ ወደፊቱ ብቻ እንድንፅፍ ፈቃዳቸው ሆኗል”

ደስታ ድንገት እንደ ሳቅ አመለጠኝ፡፡ ሆዴ ለስራ በመጓጓት ጮኸ፡፡ መልዕክት ከትዳር ቢሮ ተልኮልኝ እንደሆነ ለማወቅ ውስጤን ከፍቼ አየሁ፡፡ መልዕክት አልደረሰኝም፡፡ ውስጤ መልዕክት ለመቀበል ፈቃደኛ እስካልሆነ ቢላክም አይደርሰኝም፡፡ ብዙም ግን ደስታዬን አላደፈረሰውም፡፡ “የዳኛቸው ወርቁ ምንድነው?” ብዬ ራሴን ጠየኩ፡፡ ወርቁ ድንገት ተገለፀልኝ፡፡

“ህብረ ቃሉ ዳኛቸው ነው፡፡ ሰሙ፤ ዳኝነት ወርቁ፤ አደፍርስ ነው” ቢሆንም ደስታዬን አላደፈረሰውም፡፡ ውሎ አድሮ አቶ ታሪክ ሚስታቸውን አስረጅተው እንደሚገድሏት አውቃለሁ፡፡ ወደ ኋላ የሚያድግ ወደ ፊት ከሚሮጠው ጋር ሊስማማ እንደማይችል ለውስጤ ግልፅ ነው፡፡ ቢሆንም ደስታዬን አላደፈረሰውም፡፡

 

 

 

 

 

Read 3143 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:54
More in this category: « ፊዮሪ ንስሃው »