Saturday, 10 March 2012 10:25

ንስሃው

Written by  ህላዊ ተስፋዬ
Rate this item
(0 votes)

አባ ማቴዎስ ዛሬ ስሜታቸው ድብልቅልቅ ብሎ ነው ከአልጋቸው የተነሱት፡፡ ሰሞኑን በጣም ደስ ብሏቸው ነበር የከረሙት፡፡ ሳራ (ያሳደጓት ልጃቸው) ከሁለት ቀን በኋላ ልታገባ ነው፡፡ በዛ ላይ እህቷ ርብቃ የዛኑ ቀን ቅዳሜ የኮሌጅ ትምህርቷን ትመረቃለች፡፡ ከምትማርበት ከተማ ወደነሱ የገጠር ከተማ ዛሬ እንደምትገባ ደውላ ነግራቸዋለች፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን የ3 ወር ነፍሰጡር እንደሆነች በስልክ ለአባ ማቴዎስ አብስራቸዋለች፡፡ እሳቸው ግን በደስታ ይሁን በምን ባይታወቅም ስሜታቸው እርብሽብሽ ብሎባቸዋል፡፡ እናም ውጪ ሃገር ላለችው ለሦስተኛዋ ልጃቸው ለሮዛ ደውለው ጤንነቷን ካረጋገጡ በኋላ ቀለል አላቸውና ወደ ቤተክርስትያናቸው ተጓዙ፡፡

አባ ማቴዎስ ረጅም ቁመና ያላቸው፤ ቀጠን ያሉ፤ ቀይ፤ መልከመልካም አዛውንት ናቸው፡፡ ነጩ ጢማቸው ቀጥ ብሎ ወርዶ ሲታይ አገጫቸው ላይ የተተከለ ቄጠማ ይመስላል፡፡ ጥቁሩ ቀሚሳቸው ከትልቁ ያንገት መስቀላቸው ጋር ግርማ ሞገስ አጐናፅፎዋቸዋል፡፡ በባህሪያቸውም የተመሰገኑ ናቸው - አባ ማቴዎስ፡፡

ከሚያገለግሉባት ቤተክርስቲያን ከደረሱ በኋላ መጀመሪያ ፀሎት አደረሱና ሰውም ስላልነበር ቁጭ ብለው፣ ስለቅዳሜው ሰርግና ምርቃት እያሰቡ ፊታቸው በደስታ መፍካት ጀመረ፡፡ ሃሳባቸው በትዝታ ወደ ኋላ ተመለሰ፡፡ እዚህ ቤተክርስቲያን ስራ ከጀመሩ 32 አመት ያህል ሆኖአቸዋል፡፡ እስከመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ አመታት ድረስ ህይወት ለሳቸው አሰልቺ ድግግሞሽ ነበር፡፡ ጧት ይመጣሉ፤ ይፀልያሉ፤ ቅዳሴ ካለ ይቀድሳሉ፤ አንዳንዴም ንስሃ ይቀበላሉ፡፡ እንደውም ንስሃ ሲቀበሉ ደስ ይላቸው ነበር፡፡ ልክ ሃኪም የህመምተኛውን ቁስል ወይም ስብራት ሰፍቶ፣ ሸፍኖ፣ አሽጐና አክሞ እንደሚልከው ሁሉ እሳቸውም በእግዚአብሔር ቃል ማደንዘዣ ወግተው ውስጡን አጥርተው ፈውሰው ይልኩታል፡፡

በዘጠነኛው አመት ላይ ነበር የህይወታቸውን አሰልቺ ድግግሞሽ የሚቀይር ክስተት የተፈጠረው፡፡ እንደተለመደው አንድ እሁድ ጠዋት ምእመናኑን እያስተማሩ አይናቸው አንዲት ጐስቋላ ሴት ላይ አረፈ፡፡ ሴትየዋ ፊቷ ላይ ጭንቀት ይነበብባት ነበር፡፡ አይኖቿ እንባ አዝለዋል፡፡ ከንፈሯ ይንቀጠቀጣል፡፡ አባ አፋቸው ቃላቱን ያውጣ እንጂ ሃሳባቸው በሙሉ እሷ ላይ ነበር፡፡ ግራ እንደተጋቡ እያስተማሩ ሳለ ተነስታ ተፈተለከችና  ከቤተክርስትያኑ ወጣች፡፡ እሳቸውም ስለሷ እያሰቡ ትምህርታቸውን ጨርሰው ሰዎቹን ካሰናበቱ በኋላ፣ ወደ ውስጥ ሲገቡ ያቺ ሴትዮ ተቀምጣበት የነበረው ወንበር ስር አንድ ሻንጣ ተቀምጦ ይመለከታሉ፡፡ ቀረብ ብለው ሲያዩት አንዲት አራስ ህፃን ተቀምጣለች - ሻንጣው ውስጥ፡፡ በሚንቀጠቀጥ እጃቸው የሻንጣውን ዚፕ ወደ ታች ሲከፍቱት አይኖቻቸው ፍጥጥ ብለው ቀሩ፡፡ ሴትየዋ ጥላ የሄደችው አንድ ሳይሆን ሦስት ቀያይ የሚያምሩ መንታ ህፃናትን ነበር፡፡ ሦስቱም እንቅልፍ ወስዷቸዋል፡፡ ዚፑን ቀስ ብለው ወደ ላይ መለሱትና ታቅፈው ቤታቸው ይዘዋቸው ሄዱ፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነበር የአባ ማቲዎስ ህይወት የተቀየረው፡፡ ኦና ጐጆአቸው ህይወት ዘራባት፡፡ ቀዝቃዛ ህይወታቸው ሙቀት ሞላው፡፡ እነዚህን ሦስት መንታ ህፃናት ሳራ፣ ርብቃና ሮዛ ብለው ስም አወጡላቸው፡፡ ሴቶቹም እያደጉ ሲመጡ የመልካቸውና የባህሪያቸው መመሳሰል እየቀረ መጣ፡፡ ሳራ ብዙ ጊዜ ቤት የምትውል፣ ቤቷን የሙጥኝ ያለች ልጅ ሆነችና እዛው ከእሣቸው ጋር እዛች ትንሽ የገጠር ከተማ ቀረች፡፡ ብቃ ደሞ ትምህርቷን ጐበዝ ስለነበረች ከተማ ሄዳ ኮሌጅ መማር መረጠች፡፡ ሮዛ ውጪ ለመሄድ በጣም ትጓጓ ነበር፡፡ እንዳሰባቸውም አልቀረ፣ በወንድ ጓደኛዋ አማካኝነት በጋብቻ ወደ ውጪ ሀገር ሄደች፡፡

ይህንንም ያንንም አንድ ጥግ ላይ ቁጭ ብለው እያሰቡ፣ ወደ ንስሃ መቀበያው ሳጥን አንድ ሰው ሲገባ አዩና ተነስተው ወደዚያ ሄዱ፡፡ ያቺ ሳጥን ንስሃ የሚቀበሉባት ስትሆን ሰውየውን የማያሳይ፣ ድምጽ ብቻ መተላለፊያ ያላት ሳጥን ናት፡፡ እንደገቡ “እንዴት አደሩ አባቴ” አላቸው ጐርናና ድምጽ፡፡

“እንዴት አደርክ ልጄ” ብለው ሠላምታውን መለሱለት፡፡ “አባቴ ሃጢያቴን ለመናዘዝ ነው የመጣሁት፤ ስራዬ ከብዙ ሴቶች ጋራ ስለሚያገናኘኝ ለኔ ትልቅ ፈተና ነበር፤ ብዙውን ጊዜም ራሴን ጠብቄ ነበር፤ አሁን ግን ተሳሳትኩ፤ ከሚስቴ ውጪ ሌላ ሴት ጋር ሄድኩ” አላቸው፡፡

አባ ማቴዎስ ግርም የሚላቸው፣ ከሚቀበሉት ንስሃ የአብዛኛው ሠው ሃጢያት ዝሙት መሆኑ ነው፡፡ የሲኦል መግቢያ ቁልፍ የሠው ልጅ ብልቱ ላይ ሳይሆን አይቀርም ብለው ያስባሉ፡፡ ፀሃፊውን ባያስታውሱትም አንድ መጽሃፍ ላይ ያነበቡት ትዝ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን እንዲህ አለው “ጥሩም መጥፎም ዜና አለኝ” አዳምም፤ “ምንድን ናቸው?” አለው፡፡ “ጥሩው ዜና ጭንቅላት (ህሊና) እና ብልት ፈጥሬልሃለሁ፡፡” መጥፎው ዜና ደሞ ሁለቱንም በአንዴ መጠቀም አትችልም፤ አንዱ ሲሰራ አንዱ ስራውን ያቆማል፡፡ እንግዲህ ባንዱ ማንነቱ ሲመሽ ይተኛል፤ በሌላ ማንነቱ ሲነጋ ይፀጽተዋል፤ ወደ እሳቸውም ይመጣል፡፡ “ይገርማል!” አሉ አባ-ለራሳቸው፡፡

ሠውየው ንስሃውን ጨርሶ ሲወጣ፣ ሁለተኛው ሠውዬ ወደ ሳጥኗ ገባ፡፡ ትንሽ ፀጥ ብሎ ከቆየ በኋላ ሠላምታ እንኳን ሳይሠጣቸው በጭንቀት በተወጠረ ስሜት “አባቴ እኔ በጣም ሃጢያተኛ ነኝ፤ እግዜር እንዴት ብሎ ይቅር እንደሚለኝ አላውቅም” አለ፤ አባም “አይዞህ ልጄ በልብህ ከተፀፀትክና ከልብህ ካመንከው የማይሆን ነገር የለም” አሉት፡፡

“ከምኑ ጀምሬ እንደምነግርዎ አላውቅም፤ እናትና አባቴ እዚህ ቢኖሩም እኔ ከተማ እማር ነበር፤ እዛ እየኖርኩኝ ከአንዲት ወጣት ልጅ ጋር ተዋወቅሁ፤ ተቀራረብን፡፡ በጣም እንዋደድ ነበር፤ ከሷም ሌላ ሴት አላውቅም ነበር፤ በኋላ አንድ ሁለት አመት አብረን እንደቆየን ለእኔ ሳታሳውቀኝ ሌላ ሠው አግብታ ወደ ውጪ ሃገር ሄደች፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ህይወቴ ተመሰቃቀለ፤ ተሠቃየሁኝ፤ በሙሉ እምነቴ ተደግፌያት ሳለ ስትሄድ ወደቅሁኝ፤ ራሴን ለማጥፋት ሁለት ጊዜ ሞክሬ ተረፍኩኝ፡፡”

“አቤት እንዴት ያለችው ጨካኝ ናት!” አሉ - ለራሳቸው፡፡ የማደጐ ልጆቻቸውን መልካምነትና ርህራሄ አሠቡናም ደስ አላቸው፡፡ ወዲያው ደሞ ፈገግታቸው ጠፍቶ ፀፀት ተሠማቸው፡፡ “አቤት እኛ!” አሉ፤ “አንዱ ለመደሠት አንዱ መውደቅ አለበት፤ በአንዱ ብልግና የኛ ጨዋነት ይገናል፤ እኛ እኮ እንገርማለን፤ ስናማርር ቆይተን ወድቆ በረንዳ የሚለምነውን ስናይ ተመስገን እንደዚህም መሆን አለ እንላለን፡፡

እኛ የምንጽናናው በሌላው ማጣት ነው፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ያ ሠውዬ ፀሎቱ ያልተሠማለት “ተመስገን በተለይም እንኳን እንደዚህ ቀራጭ አላደረግኸኝ” ስላለ አደል፡፡” ራሳቸውን ታዝበው ይቅር ይበለኝ አሉ፡፡

ልጁ መናዘዙን ቀጥሎዋል፤ “ከዛ ጊዜ ጀምሮ ሴቶቹ ላይ በቀል አደረብኝ፤ ጠላኋቸው እዚህ እዛ ማለት ጀመርኩኝ፤ ከጊዜ በኋላ ከአንዷ ጋር ተቀራረብን፤ የተወሠነ ጊዜ እንደቆየን እንድንጋባ ጠየቀችኝ፤ እኔም ልቤን ባልሠጣትምና ባላምናትም ቆንጆና ጥሩ ባህሪ ስለነበራት እሺ ብያት ቀን ቆርጠን ስንጠብቅ፣ በመሃል ውጪ ሃገር ያለችው የድሮዋ ፍቅረኛዬ አፈላልጋ በጓደኛዬ አማካኝነት በስልክ አገኘችኝና ከሠውየው ጋር ግንኙነት የጀመረችው ውጪ እንዲወስዳት ብላ እንደነበርና እዛም ሄዳ የህሊና እረፍት አጥታ ሆስፒታል መግባቷን ከኔ በላይ እንደተሠቃየች፤ አሁን ሠውዬውን ፈትታው ብቻዋን እንደምትኖር፣ ከኔም ጋር አብራ መኖር እንደምትፈልግ አልቅሣ ነገረችኝ፡፡

እኔም ድሮም በጣም እወዳት ስለነበር መጨከን አልቻልኩም፡፡ ከዚህ በፊትም ለበደልኳቸው ሠዎች በጣም ተጸጸትኩኝ፡፡ መረጋጋት አልቻልኩምና ወደ እርስዎ ጋ መጣሁ፡፡ አሁን ፕሮሠሡን ጨርሼ ነገ ጠዋት ወደሷ ልሄድ ነው፤ ግን ከሁሉ የተሠማኝ እዚህ ከተማ ያለችው ምስኪን ጓደኛዬን ዝም ብዬ ጥያት ልሄድ ስለሆነ ነው፤ እሷ ቅዳሜ ልታገባኝ እየተሠናዳች ነው፡፡ በዛ ላይ ከተማ ያለችው የኮሌጅ ፍቅረኛዬ  ደውላልኝ የ3 ወር እርጉዝ መሆኗን አረዳችኝ፡፡ አባ እውነቴን ነው፤ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ ሦስቱም እህትማማቾች መሆናቸውን አላወቅሁም ነበር፡፡ የሚገርመው ደሞ …”

አባ ማቴዎስ ከዛ በኋላ ያለውን ነገር አልሠሙትም፡፡ ከመቀመጫቸው ተንሸራተው መሬት ወድቀው ነበር …

 

 

Read 3040 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 10:29